ዘላለማዊው መልእክት

ዘላለማዊው መልእክት

ሰዎች ከመለኮታዊ መመሪያና ከነቢያት ተልእኮ በራቁ ቁጥር ዕድለቢስነትና ጨለማ በሰው ልጆች ሕይወት ላይ ያጠላሉ። አላህም መልክተኞቹን አከታትሎ ይልካል፦

{ከመልክተኞቹ በኋላ ለሰዎች በአላህ ላይ አስረጅ እንዳይኖር፣አብሳሪዎችና አስጠንቃቂዎች የኾኑን መልክተኞች (ላክን)፤አላህም አሸናፊ ጥበበኛ ነው።}[አል ኒሳእ፡165]

አላህ መልክተኛ ሳይልክላቸው ማንንም አይቀጣም፦

{መልክተኛንም እስከምንልክ ድረስ የምንቀጣ አይደለንም።}[አል እሰራእ፡165]

ዒሳ  ከተላኩና አላህ (ሱ.ወ.) ወደራሱ ካነሳቸው በኋላ የሰው ልጆች በማይምነት፣በጥመት፣በግፍና በጨለማ ተዋጡ። መለኮታዊ ሃይማኖቶችም የጠራውን የተውሒድ እምነት በጣዖታዊነትና በሽርክ በለወጡ አጥፊዎች አማካይነት ለመዛበት ለመጣመምና ለክለሳ አደጋዎች ተጋለጡ። ለአላህ ኃያልነትና ለተውሒዱ ተጻራሪ የሆኑ እምነቶችን በማራመድና ተገቢ ያልሆኑ ባሕርያትን ለርሱ በመስጠት ረገድ በአምልኮም ሆነ በአነዋነዋር በመጽሐፉ ባለቤቶችና በጣዖታውያን ሙሽሪኮች መካከል ልዩነት አልነበረም። በዚህ ግዙፍ የሽርክ፣የኤቲዝም፣የአላህን ቃልና መለኮታዊ መጽሐፎችን የማዛባትና የመለዋወጥ ማዕበል ውስጥ፣የመጽሐፉ ባለቤቶች የአላህን ኪዳንና የአላህን ቃል በግድ የለሽነት ከጀርባቸው ኋላ በመጣላቸው፣እውነቱን ደብቀው ሐሰትን በግልጽ በመንዛታቸው፣የአላህን እገዳዎች በመጣስ የአላህን መብቶችና የፍጡራንን መብቶች በመጣሳቸው፣ግላዊ ጥቅሞቻቸውን ከእውነት ያበለጡ መሪዎቻቸውና ካህኖቻቸው እንዳደረጉት ሁሉ የሚያውቁትን እውነት ለገንዘብና ለሹመት በመለወጣቸው . . አውዳሚ ጦርነቶች ተስፋፉ፤አምባገነንነት ሰፈነ። የሰው ልጆች በክህደትና በአለዐዋቂነት ምክንያት ልቦናን ባጠቆረ ድቅድቅ ጨለማ ውስጥ ለመኖር ተገደዱ። መልካም ስነምግባር ጨቀየ፤ሰብአዊ ክብርም ተዋረደ፤በምድሪቱ ላይ ጥፋት ተዛመተ። በዘመኑ መንገዱን ለሰው ልጆች ሊያበራና ወደ ቀጥተኛው ጎዳና ይመራቸው ዘንድ የነቢይነትን ችቦ ያነገበ፣የቅን መመሪያን ብርሃን የያዘ ታላቅ የለውጥ አራማጅ መሪን በመላክ አላህ (ሱ.ወ.) ካልታደገው በስተቀር ሰብአዊነት በጣእረ ሞት ውስጥ መሆኑን፣ለውድመትና ለጥፋት መቃረቡን ዘመኑን ያስተዋለ ሰው በቀላሉ ይረዳል።

የሰው ልጆች በዚህ ጽልመታዊ ሁኔታ ውስጥ እያሉ ነበር አላህ ነቢዩን  የላካቸው። መልክተኛው ይሆኑ ዘንድም ሙሐመድን  መረጣቸው፦

{የአላህ መልክተኛና የነቢዮች መደምደሚያ ነው፤}[አል አሕዛብ፡40]

ከነቢዩም ጋር መላውን የሰው ዘር ከጥመትና ካለመታደል የሚታደገውን መሪ ብርሃንም ላከ። በዚህም ይህን ሃይማኖት ምሉእ አድርጎ ለሰው ልጆች የለገሰውን ታላቅ ጸጋውን አዳረሰ። ነቢዩም  ይህን ዘላለማዊ እውነታ ለዓለማት ሁሉ ተደራሽ ለማድረግ በጽናት ታገሉ፦

{(ሙሐመድ ሆይ!) ለዓለማትም እዝነት አድርገን እንጅ አልላክንህም።}[አል አንቢያ፡107]

ዓለማት ሁሉ የመታደልን መንገድ ይከተሉ ዘንድ በእዝነትና በርኅራሄ ተላኩ።

ለሰው ልጆች የዘላለማዊ ተድላና የደስተኝነት መንገድን ለማሳየት ላደረጉት ታላቅ ተጋድሎ ከማንም ሰው ዋጋም ሆነ ወሮታ ፈላጊ አልነበሩም። አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{በላቸው፦ በርሱ ላይ ምንም ዋጋ አልጠይቃችሁም፤እኔም ከተግደርዳሪዎቹ አይደለሁም።}[ሷድ፡86]

ይልቅዬ ፈጣሪ አምላካቸው ንጉሥ መልክተኛ ከመሆንና አገልጋይ መልክተኛ ከመሆን አማርጧቸው የአላህ አገልጋይ ባሪያውና መልክተኛው መሆንን መርጠዋል። በመሆኑም ነቢዩ  እንደማንኛውም ሰው ሰብአዊ ሕይወትን ነበር የኖሩት፤ባልደረቦቻቸው እንደሚራቡ የሚራቡ፣እነሱ እንደሚቆስሉ የሚቆስሉም ነበሩ፤አብሯቸው ይሠሩም ነበር፤የአላህ ባሪያና አገልጋዩ በመሆናቸውም ይኮሩ ነበር፤ጌታቸው አላህም (ሱ.ወ.) ሲያከብራቸውና እርሱ ዘንድ የመጨረሻው ክቡር ደረጃ በሆነው ማዕረግ {ባሪያችን} በማለት ነው የጠራቸው። አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{ምስጋና ለአላህ ለዚያ መጽሐፉን፣በውስጡ መጣመምን (መማታትን ያላደረገበት) ሲኾን በባሪያው ላይ ላወረደው ይገባ።}[አል ከህፍ፡1]

ከዚህም አልፈው ነቢዩ  ማንም ሰው ከሚገባቸው ያለፈና የተጋነነ ክብር እንዳይሰጣቸው ያስጠነቅቁ ነበር። ይህን በማስመልከትም እንዲህ ብለዋል፦ {ክርስቲያኖች የመርየምን ልጅ (ዒሳን) ከልክ አሳልፈው እንዳሞገሱት ዓይነት አታሞግሱኝ። እኔ የአላህ ባሪያ እንጅ ሌላ አይደለሁምና፤የአላህ ባሪያና መልክተኛው በሉኝም።} [በቡኻሪ የተዘገበ] ነቢዩን  ያያቸውና ያወቃቸው ሰው ሁሉ እውነተኛነታቸውንና ፍጹምነታቸውን ወዲያውኑ ይረዳል፤በክቡር ስነምግባራቸውና በመጠቀ ባህርያቸውም ይመሰጣል። ይህም ከወዳጆቻቸው በፊት ጠላቶቻቸው፣ከሙስሊሞችም በፊት ከሓዲዎች ራሳቸው አውቀው ምስክርነታቸውን የሰጡበት ጉዳይ ነው! ጌታቸው አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ሲል የመሰከረላቸው መሆኑ ብቻ በቂያቸው ነው፦

{አንተም በታላቅ ጠባይ ላይ ነህ።}[አልቀለም፡4]

አላህ (ሱ.ወ.) የነቢያትና የመልክተኞች መደምደሚያና ማጠቃለያ አድርጎ የመረጣቸው መሆኑ ብቻ ከምንም ምስክርነት በላይ ነው። ተልእኮአቸው ተሟልቶ ሲጠናቀቅም፣አላህ (ሱ.ወ.) መልክታቸውን ለሰው ልጆች የተላለፈ የመደምደሚያው ዘላለማዊ መልክት አድርጎ እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ በማቆየት እሳቸውን ወደራሱ ወስዷቸዋል።