የነቢይነት ድምዳሜ፦

የነቢይነት ድምዳሜ፦

አላህ (ሱ.ወ.) በጥበቡ ለመላው የሰው ልጅ አጠቃላይ፣ለሁሉም ዘመንና ስፍራ ምቹ የሆነ ዩኒቨርሳል መልክቱን አስይዞ ሙሐመድን  ልኳል። አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{አንተንም ለሰዎች ሁሉ በመላ፣አብሳሪና አስጠንቃቂ አድርገን ቢኾን እንጂ አልላክንህም፤ግን አብዛኞቹ ሰዎች አያውቁም።}[ሰበእ፡28]

ይህን ዓለም አቀፍ ዘላለማዊ መልክቱንም ከመለወጥና ከመበረዝ ጠብቆት ከመዛባትና ከመቀያየር እንከን የተጠራ ሆኖ እስከመጨረሻው ድረስ ከሰው ልጆች ጋር የሚኖር ሕያው መልክት አድርጎታል። ለዚህም ነው የመጨረሻውና የማጠቃላያው መለኮታዊ መልክት እንዲሆን የተደረገውና ሙሐመድም  ከኋላቸው ምንም ነቢይ የማይመጣ የነቢያት መደምደሚያ የሆኑት። በዚህም አላህ (ሱ.ወ.) መለኮታዊ መልክቶቹን ምሉእ አድርጎ ሕግጋቶቹን በማጠቃለል ግንባታውን አጠናቋል።

በዚህ ምክንያትም ሙሐመድ  ይዘው የመጡትን መጽሐፍ የቀደሙት መለኮታዊ መጻሕፍት ተቆጣጣሪ ገዥ፣ሸሪዓቸውንም የቀደሙትን ሸሪዓዎች (ሕግጋት) ሁሉ የሚሽር አድርጎ ጠብቆ የማኖር ኃላፊነቱን አላህ (ሱ.ወ.) ራሱ በመውሰዱ ታላቁ ቁርኣን በድምጽና በጽሑፍ ባልተቋረጠ ተከታታይ የዘገባ ሰንሰለት ከትውልድ ወደ ትውልድ በመተላለፍ ላይ ይገኛል። የሃይማኖቱ ሕግጋት ተግባራዊ አፈጻጸምም ከዕባዳዎቹና ከዝርዝር ድንጋጌዎቹ ጋር ምሉእ በሆነ የተአማኒነት ደረጃ ባልተቋረጠ የዘገባ ሰንሰለት ለኛ ደርሷል።

የነቢዩን  የሕይወት ታሪክና ነቢያዊ ፈለጋቸው (ሱንና) የተጠናቀሩባቸውን መድበሎች ያነበበ ሰው፣ባልደረቦቻቸው (ሶሓባ) የነቢዩን  አጠቃላይ ሁኔታዎች፣የተናገሩትንና የሠሩትን ሁሉ በተሟላ መልኩ ጠብቀው ለሰው ልጆች አቆይተዋል። አላህን እንዴት ያመልኩ እንደነበረ ዕባዳቸውን፣ዝክራቸውንና ዱዓቸውን፣እስትግፋራቸውን፣ጅሃዳቸውን፣ደግነታቸውንና ፣ለባልደረቦቻቸውና ወደርሳቸው ለሚመጡትም ያደርጉ የነበረውን አያያዝ ወደር በሌለው ታማኝነትና ጥንቃቄ ለትውልዶች ጠብቀው አስተላልፈዋል። ደስታና ሐዘናቸውን፣ጉዞና ዕረፍታቸውን፣እንዴት ይበሉና እንዴት ይጠጡ አንደነበረ፣እንዴት ይተኙና ከእንቅልፍ እንዴት ይነሱ እንደነበረ ጭምር ዘግበዋል።

ይህን ሁሉ አስተውለን ስንመለከት ይህ ሃይማኖት ከመበረዝና ከመዛባት አደጋ በአላህ (ሱ.ወ.) ጥበቃ የሚደረግለት ሃይማኖት መሆኑን እንገነዘባለን።

በዚህን ጊዜም ሙሐመድ  የነቢያትና የመለክተኞች መደምደሚያ መሆናቸውን እንረዳለን። አላህ (ሱ.ወ.) ይህ መልክተኛ የነቢያት መደምደሚያ መሆኑን ሲነግረን እንዲህ ብሏልና፦

{ሙሐመድ፣ከወንዶቻችሁ የአንድም ሰው አባት አይደለም፤ግን የአላህ መልክተኛና የነቢዮች መደምደሚያ ነው፤አላህም በነገሩ ሁሉ ዐዋቂ ነው።}[አል አሕዛብ፡40]

ለዓለማት ሁሉ እዝነት፦

አላህ (ሱ.ወ.) ነቢዩ ሙሐመድን  ወደ መላው የሰው ዘር የላካቸው፣ለዓለማት ሁሉ ለወንዱም ለሴቱም፣ለትንሹም ለትልቁም እዝነት ርህራሄና ጸጋ አድርጓቸው ነው። ይህም ብቻ ሳይሆን በርሳቸው ላላመኑትም ጭምር ረሕመት አድጓቸው ነው አላህ የላካቸው። እዝነትና ጸጋው ነቢዩ  በሕይወት ዘመናቸው በወሰዷቸው አቋሞች ውስጥ የተንጸባረቀ ሲሆን፣በተለይም በርህራሄና በእዝነት ሕዝባቸውን ወደ አላህ ተውሒድ በጠሩ ጊዜ ሰዎቹ አስተባበሏቸው፤ ከትውልድ አገራቸው ከመካ እንዲሰደዱ አድርጓቸዋል፤የመግደል ሙከራም ፈጽመውባቸዋል፤አላህ (ሱ.ወ.) ግን በቂያቸው ነበርና የቁረይሾችን ሴራ አክሽፎ ውድቅ አድረገ። አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{እነዚያም የካዱት ሊያስሩህ፣ወይም ሊገድሉህ፣ወይም (ከመካ) ሊያስወጡህ ባንተ ላይ በመከሩብህ ጊዜ፣(አስታውስ)፤ይመክራሉም፣አላህም ተንኮላቸውን ይመልስባቸዋል፤አላህም ከመካሪዎቹ ሁሉ በላይ ነው።}[አል አንፋል፡30]

የተፈጸመባቸው ያ ሁሉ ግፍ ግን ለነርሱ ማዘንንና ወደ አላህ መንገድ እንዲመጡ ያላቸውን ጉጉትን ብቻ ነበር ለነቢዩ  የጨመረው። ይህን አስመልክቶ አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{ከጎሳችሁ የኾነ፣ችግራችሁ በርሱ ላይ ጥኑ የኾነ፣በናንተ (እምነት) ላይ የሚጓጓ፣ለምእመናን ርኅሩህ አዛኝ የኾነ መልክተኛ፣በእርግጥ መጣላችሁ።}[አል ተውባህ፡128]

በተጨማሪም ድል አድርጓቸው በአሸናፊነት መካ በገቡት ቀንም ያለ ምንም በቀል {ነጻ ናችሁ ሂዱ} ብለው ነበር ምሕረት ያደረጉላቸው። ከሐዲዎቹን በሁለት ተራራዎች መሀል አጣብቆ ለማጥፋት አላህ (ሱ.ወ.) መልኣክ በላከላቸው ጊዜ፣{አላህ (ሱ.ወ.) ከአብራኮቻቸው አንድ አላህን ብቻ የሚግገዙ ሰዎችን ያወጣ ይሆናልና የለም እታገሳለሁ} ነበር ያሉት። አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{(ሙሐመድ ሆይ!) ለዓለማትም እዝነት አድርገን እንጅ አልላክንህም።}[አል አንቢያ፡107]

ነቢዩ  በእርግጥ ለዓለማት ሁሉ፣ለሰዎች ሁሉ፣የቆዳ ቀለም፣ቋንቋ፣አመለካከት፣እምነትና ቦታ ሳይለይ ለመላው የሰው ዘር የተላኩ እዝነትና ዘላለማዊ የአላህ ጸጋ ናቸው።

የነቢዩ  እዝነትና ጸጋ በሰው ልጆች ላይ ብቻ የተወሰነ ሳይሆን ለእንስሳትና ለግዑዝ አካላትም ጭምር የተዘረጋ ነው። የአንድ የመዲና ነዋሪ ባልደረባቸውን ግመል ባለቤቱ በረሃብ ስላሰቃየው የአላህ መልክተኛ  በግመሉ ሁኔታ አዝነውና ራርተው ባለቤቱ ለግመሉ ደግ እንዲሆን እንዳያስርበውና ከአቅሙ በላይ እንዳይጭንበት አዘዋል። ነቢዩ  አንድ ሰው ጫጩቶቿን የወሰደባትን እርግብ አይተው ልባቸው በማዘኑ ጫጩቶቹን እንዲመልስላት አዘዋል። {ባረዳችሁ ጊዜ አስተራረዱን አሳምሩ} [በሙስሊም የተዘገበ] ያሉትም ነቢዩ  ናቸው። እዝነትና ርህራሄያቸው ወደ ግዑዝ አካላትም ተዳርሷል፤በዚህ ረገድ ነቢዩ  ስለተለዩት ዋይታ ላሰማው የተምር ግንድ ሆዳቸው ራርተው ከመናገሪያ ምንበራቸው (መድረክ) ወርደው ግንዱ እስኪረጋጋ ድረስ አቅፈውታል።

ርህራሄና እዝነታቸው በግላዊ አቋምና በሁነቶች ላይ ብቻ የተወሰነ የግል ዝንባሌ ሳይሆን ለሰዎች የደነገጉት መለኮታዊ ትእዛዝ፣ሕግ፣መመሪያና ቋሚ ስነምግባርም ነው። ለሰዎች ርህሩህ አዛኝና ገር መሆንን ሲያበረታቱና አስቸጋሪና አስጨናቂ መሆንን ሲያስጠነቅቁም ነቢዩ  እንዲህ ብለዋል፦ {አላህ ሆይ! ከሕዝቦቼ ጉዳዮች መካከል በአንዱ ነገር ኃላፊነት ተሰጥቶ ለነሱ አስቸጋሪና አስጨናቂ የሆነን ሰው አንተ አስቸጋሪና አስጨናቂ ሁንበት፤ከሕዝቦቼ ጉዳዮች መካከል በአንዱ ነገር ኃላፊነት ተሰጥቶ ለነሱ ገርና ርህሩህ የሆነውን ሰው ደግሞ አንተ ገርና ርህሩህ ሁንለት።} [በሙስሊም የተዘገበ] እናም እዝነትና ርህራሄ ከነቢዩ  ታላላቅ ባህርያት መከከል አንዱ ሲሆን፣የእዝነትና የሰላም ሃይማኖት በሆነው እስላም ውስጥም አንዱ መሰረታዊ መርሕ ነው። (19)

በነቢዩ  መላክ መላው የሰው ዘር መታደሉ ፦

የሙሐመድ  ዘመነ ተልእኮ መጥቶ በሙሐመድ ነቢይነት በረከት አላህ (ሱ.ወ.) ሰዎችን ወደ ቀጥተኛው የተውሒድ መንገድ መራቸው። መመሪያው በያዛቸው ማብራሪያዎችና መግለጫዎች ጥልቀትና ምጥቀት ከቃላት ገለጻና ከዐዋቂዎች ዕውቀት በላይ ነው። ጠቃሚ ዕውቀትን፣በጎ ሥራን፣ታላላቅ ስነምግባራትንና ቀጥተኛ ፈለግን ለሰው ልጆች ያበሰረ ሲሆን፤ እውቀትና ተግባርን ያካተተ የሁሉም ሕዝቦች ጥበብ አንድ ላይ ተደምሮ ቢመጣ ከዚህ ዘላለማዊ መለኮታዊ መመሪያ በብዙ እጅ አንሶ ይታያል። ለዚህም ምስጋና ሁሉ ለጌታችን ለአላህ ይሁን። (20)

ዐቂዳን (እምነትን ) በተመለከተ ከሙሐመድ  መላክ በፊት ባእድ አምልኮና በአላህ ማጋራት ቀደም ሲል ለክለሳና ለመዛባት አደጋ የተጋለጡ መለኮታዊ መጻሕፍት ባለቤቶች በሆኑት ዘንድ እንኳ ሳይቀር ምድርን አጥለቅልቀው ነበር። ይህን አስከፊ ሁኔታ ለመለወጥ የአላህ መልክተኛ  የጠራ ተውሒድንና አንድ አላህን ብቻ ከርሱ ጋር ማንንም ምንንም ሳያጋሩ እርሱን ብቻ የመግገዛት እምነትን ይዘው መጡ። ሰዎችንም ከፍጡራን አምልኮ ወደ አንዱ ፈጣሪ ጌታ አምልኮ አሸጋገሩ። በተውሒድ ልቦናን ከሽርክ ርክሰትና ከባዕድ አምልኮ ቆሻሻ አጸዱ። አላህ (ሱ.ወ.) የላካቸው ከርሳቸው የቀደሙ ነቢያትና መልክተኞች ይዘው የመጡትን ትምሕርት በማስያዝ ነበር። አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{ከአንተ በፊትም፣እነሆ ከኔ ሌላ አምላክ የለምና ተገዙኝ በማለት ወደርሱ የምናወርድለት ቢኾን እንጂ ከመልክተኛ አንድንም አልላክንም።}[አል አንቢያእ፡25]

አላህ (ሱ.ወ.) በተጨማሪ እንዲህ ብሏል፦

{አምላካችሁም አንድ አምላክ ብቻ ነው፤ከርሱ በቀር ሌላ አምላክ የለም፤(እርሱ) እጅግ በጣም ርኅሩህ አዛኝ ነው።}[አል በቀራህ፡163]

በማሕበራዊው ሕይወት በኩልም ነቢዩ  የተላኩት ግፍና ጭቆና በተንሰራፋበት፣የሰው ልጆች በጌታና በሎሌ መደብ ተከፋፍለው በአስከፊ የመደብ ጭቆና በሚሰቃይበት ወቅት ነበር። ነቢዩ  ሰዎችን ሁሉ ዐረብና ዐረብ ያልሆነ፣ነጭና ጥቁር ሳይባል እኩልነትን የሚያሰፍን፣አላህን በመፍራትና በሚፈጽሙት መልካም ተግባር ብቻ ካልሆነ ማንም ሰው ከሌላው ሰው ፈጽሞ የማይበልጥ መሆኑን የሚያበስር ሰብአዊ እኩልነትን ይዘው ነው የመጡት። ይህን በማስመልከት አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{በላጫችሁ፣በጣም አላህን ፈሪያችሁ ነው፤}[አል ሑጁራት፡13]

አላህ (ሱ.ወ.) ለፍትሕ አስተካካይነት፣ለበጎ ሥራና ለማሕበራዊ ተራድኦ ጥሪ ሲያደርግ፣ከግፍ ከመጥፎ ድርጊትና ከማንኛውም በደል ከልክሏል። አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{አላህ በማስተካከል፣በማሳመርም፣ለዝምድና ባለቤት በመስጠትም ያዛል፤ከአስከፊም፣(ከማመንዘር)፣ከሚጠላም ነገር ሁሉ፣ከመበደልም ይከለክላል፤ትገነዘቡ ዘንድ፣ይገሥጻችኋል።}[አል ነሕል፡90]

ይህ ብቻ ሳይሆን የሌሎችን ሕሊናዊ መብቶች እንዲከበሩ አድርጎ ሰዎች አንዱ በሌላው ላይ እንዳይሳለቅ ከልክሏል። አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{ወንዶች ከወንዶች አይቀልዱ፤ከነርሱ የበለጡ ሊኾኑ ይከጀላልና፤ሴቶችም ከሴቶች (አይሳለቁ)፤ከነሱ የበለጡ ሊኾኑ ይከጀላልና፤ነፍሶቻችሁንም አታነውሩ (ከፊላችሁ ከፊሉን አይዝለፍ)፤በመጥፎ ስሞችም አትጠራሩ፤ከእምነት በኋላ የማመጥ ስም ከፋ፤ያልተጸጸተም ሰው፣እነዚያ እነሱ በዳዮቹ ናቸው።}[አል ሑጁራት፡11]

በስነምግባር መስክም የሰው ልጆች ግብረገብነትና መልካም ባሕርያት ክፉኛ ባዘቀዘቁበት ወቅት ነበር ነቢዩ  የተላኩት። የመጡትም ሰዎችን ወደ መልካም ስነምግባርና ምስጉን ባሕርያት እንዲመለሱና በበጎ በይነሰባዊ ግንኙነቶች እንዲታደሉ ለማድረግ ነው። የአላህ መልክተኛ  እንዲህ ብለዋል፦ {የተላክሁት መልካም ስነምግባራትን ምሉእ ለማድረግ ነው።} [በበይሀቂ የተዘገበ] አላህ (ሱ.ወ.) ስለ ነቢዩ  ታላቅ ስነምግባር ሲገልጽ እንዲህ ብሏል፦

{አንተም በታላቅ ጠባይ ላይ ነህ።}[አልቀለም፡4]

ነቢዩ  የምጡቅ ስነምግባርና የመልካም ባሕርያት ሁሉ፣የቁጥብነት፣የተግባቦት፣የአብሮነትና የመልካም አነጋገር ቁንጮ ምሳሌ ብቻ ሳይሆኑ የመልካም ነገሮች ሁሉ መልካም አርአያ ነበሩ። አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{ለናንተ፣አላህንና የመጨረሻውን ቀን የሚከጅል ለኾነ ሰው፣አላህንም በብዙ ለሚያወሳ፣በአላህ መልክተኛ መልካም መከተል [አርአያ] አላቸው።}[አል አሕዛብ፡21]

የሴት ልጅን በተመለከተ በቅድመ እስላም አስከፊ ግፍና ጭቆና ይደርስባት የነበረ ሲሆን፣ነቢዩ  የተላኩት ሴቶች በሕብረተሰቡ ውስጥ ምንም መብት ያልነበራቸውና የተዋረዱ፣ሌላው ቀርቶ ሰው ነች ወይስ አይደለችም? በሚለው ላይ እንኳ ወንዶች በሚወዛገቡበት፣በሕይወት የመኖር መብት አላት ወይስ እንደተወለደች ተግደላ ትቀበር ?! ብለው በሚከራከሩበት ዘመን ነበር። የማህበረሰቡ ሁኔታም አላህ (ሱ.ወ.) ቁርኣን ውስጥ ቀጥሎ የገለጸውን ይመስል ነበር፦

{አንዳቸውም በሴት ልጅ በተበሰረ ጊዜ፣እርሱ የተቆጨ ኾኖ፣ፊቱ ጠቁሮ ይውላል። በርሱ ከተበሰረበት ነገር መጥፎነት፣በውርደት ላይ ኾኖ፣ይያዘውን? ወይስ በዐፈር ውስጥ ይደብቀውን? (በማለት እያምታታ) ከሰዎች ይደበቃል፤ንቁ፣የሚፈርዱት (ፍርድ) ምንኛ ከፋ!}[አልነሕል፡58-59]

ሴት ልጅ ተራ መጫወቻና፣የሚገበያዩባት አሻንጉሊትና ተዋራጅ አልባሌ ዕቃ ተደርጋ ትቆጠር ነበር።

አላህ (ሱ.ወ.) ነቢዩን  ሲልካቸው ለሴት ልጅ ክብሯን አስመለሰላት። አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{ለናንተም ከነፍሶቻችሁ (ከጎሶቻችሁ) ሚስቶችን ወደነርሱ ትረኩ ዘንድ መፍጠሩ፣በመካከላችሁም ፍቅርንና እዝነትን ማድረጉ፣ከአስደናቂ ምልክቶቹ ነው፤}[አል ሩም፡21]

ይልቅዬም በእናትነቷ አንድትከበርም ትእዛዝ አስተላለፈ። አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{ጌታህም (እንዲህ አዘዘ)፤- እርሱን እንጂ ሌላን አትገዙ፤በወላጆቻችሁም መልካምን ሥሩ፤}[አል እስራእ፡23]

ነቢዩም  ለሴት እንደ እናት ከወንድ ቅድሚያ ሰጥተዋታል። አንድ ሰው ወደ ነብዩ r መጥቶ ፦ {የአላህ መልክተኛ ሆይ! ለኔ መልካም አያያዝና ለደግነቴ ከሁሉም ይበልጥ ባለመብት የሆነው ማነው? ሲላቸው ፦ እናትህ ናት አሉት፤ከዚያስ? አላቸው፤እናትህ ናት፣አሉት፤ከዚያስ? አላቸው፤እናትህ ናት አሉት፤ከዚያስ? አላቸው፤አባትህ ነው አሉት።}[በቡኻሪና ሙስሊም የተዘገበ] ትንሽ ልጃገረድ ሆናም አክብሮት እንዲቸራት ሲያዙ ነቢዩ  ፦ {ሦስት የሚያስጠጋቸው፣የሚራራላቸውና የሚያሳድጋቸው ሴቶች ልጆች ያሉት ሰው ገነት ለርሱ ተገቢው ሆናለች} ሲሉ የአላህ መልክተኛ ሆይ! ሁለት ብቻ ቢሆኑም? ተብለው ሲጠየቁ {አዎ፣ሁለት ብቻ ቢሆኑም} ብለዋል። [በአሕመድ የተዘገበ] በተጨማሪም እንደ ሚስትም ክብር እንዲሰጣት አዘው ይህን ማድረግ ከበላጭነት መለኪያ ጋር አያይዘዋል፦ {በላጫችሁ ለቤተሰቡ ከሌላው ይበልጥ ጥሩ የሆነ ሰው ነው፤እኔ ከሁላችሁም ይበልጥ ለቤተሰቤ ጥሩ ነኝ።} ብለዋል። [በትርምዚ የተዘገበ]