የዘላለማዊው መልክት መጠሪያ ስም ምንድን ነው?

የዘላለማዊው መልክት መጠሪያ ስም ምንድን ነው?

እያንዳንዱ ሃይማኖት መጠሪያ ስሙን ያገኘው ከሃይማኖቱ መስራች ግለሰብ ስም፣ወይም ሃይማኖቱ ከተገኘበት የተለየ ሕዝብ ወይም ጎሳ ስም ነው። ዞሮስቲሪያኒዝም ከመስራቹ ከዞሮስት፣ቡድሂዝም ከመስራቹ ከቡድሃ፣ይሁዳዊነት እምነቱ ከተገኘበት ነገድ ከይሁዳ፣ክርስትናም ከመስራቹ ከኢየሱስ ክርስቶስ የተገኙ መጠሪያ ስሞች ናቸው። እስላም ግን ከዚህ ሁሉ የተለየ ነው።

እስላም ከግለሰብ ወይም ከአንድ የተለየ ሕዝብ ወይም ነገድ ጋር የተሳሰረ አይደለም። ለአላህ (ሱ.ወ.) እርሱን ብቻ ለመግገዛትና ለርሱ ብቻ ለመታዘዝ ራሱን ለርሱ የሰጠ ሰው ሁሉ ለርሱ የሰለመ ሰው ነው። የነቢያትና የመልክተኞች መደምደሚያ የሆኑትን ሙሐመድን  የተከተለ፣ይዘው ለመጡት እውነተኛው ሃይማኖት የተገዛ፣ነቢዩን አምኖ በመቀበል ፈለጋቸውን ተከትሎ የተጓዘ ሰው ሁሉ፣በየትኛውም ዘመንና ስፍራ ቢሆን፣የየትኛውም የቆዳ ቀለም ወይም ጎሳና ብሔር አባል ቢሆን እውነተኛው ሙስሊም እርሱ ነው።

ዘላለማዊው መልክት ለመላው ዩኒቨርስ ጭምር ነው፦

እስላም መላው ዩኒቨርስ የሚጓዝበትና የሚመራበት ነው። አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{በሰማያትና በምድር ያሉ ሁሉ፤በውድም በግድም ለርሱ የታዘዙ [የሰለሙ፣ሙስሊም የሆኑ]፣ወደርሱም የሚመለሱ ሲኾኑ (ከሓዲዎች) ከአላህ ሃይማኖት ሌላን ይፈልጋሉን?}[ኣሊ ዒምራን፡83]

በዩኒቨርስ ውስጥ ያለው ማንኛውም ነገር ለተወሰነና ቋሚ ለሆነ ሕግ ተገዥ መሆኑ የሚታወቅ ነው። ፀሐይ፣ጨረቃ፣ከዋክብትና መሬት ቅንጣት ያህል እንኳ ሊጥሱት በማይችሉና አላህ (ሱ.ወ.) በተፈጥሮ ውስጥ ባኖራቸው ቋሚ ሕግጋት ይመራሉ። የሰው ልጅም ጭምር አስተውለን ብንመለከት ሙሉ በሙሉ ለአላህ የተፈጥሮ ሕግጋት ተገዥ መሆኑን እንረዳለን። ሕይወቱን ከሚመራው መለኮታዊ ውሳኔ ውጭ መተንፈስ፣የውሃ የምግብ የብርሃንም ሆነ የሙቀት ፍላጎት ሊሰማው አይችልም፤የሰራ አካላቱ ለዚህ የአላህ (ሱ.ወ.) ውሳኔ ተመሪ ሲሆን እያንዳንዱ አባለ ገላ ተግባሩን ሚፈጽመው በዚህ አላህ (ሱ.ወ.) ባኖረለት የተፈጥሮ ሕግ መሰረት ብቻ ነው።

ይህ አጠቃላይ መለኮታዊ የተፈጥሮ ሕግም በፍጥረተ ዓለሙ ውስጥ ከግዙፉ የጠፈር ኮከብ እስከ ቅንጣቷ የምድር አቶም ድረስ ምንምና ማንም በውድም ይሁን በግድ የሚገዛለትና የሚመራበት መለኮታዊ ሥርዓት ነው። በሰማያትና በምድር፣በመካከላቸውም ያለው ሁሉ ለዚህ መለኮታዊ ቅንብር ተገዥና ተመሪ (የሰለመ) እስከሆነ ድረስም እስላም (ለአላህ ተመሪ መሆን) የመላው ዩነቨርስ ሃይማኖት መሆኑ ግልጽ ይሆናል፤እስላም ማለት የአላህን ትእዛዛት በመፈጸምና ከከለከለው በመታቀብ ወዶ ለርሱ መግገዛትና ማደር ነውና። ፀሐይ፣ጨረቃና መሬት፣አየርና ውሃም፣ብርሃን ጨለማና ሙቀትም፣ዛፉና ድንጋዩም፣አራዊትና እንስሳቱም . . ሁሉም ለርሱ ተገዥዎችና ተመሪዎች ናቸው። አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{ለናንተም በሰማያት ያለውንና በምድርም ያለውን ሁሉ በመላ ከርሱ ሲኾን የገራላችሁ ነው፤}[አል ጃሢያህ፡13]

ሌላው ቀርቶ ጌታውን የማያውቅ፣መኖሩንና ፈጣሪ አምላክ መሆኑን የሚያስተባብል ኢአማኝ፣ወይም ከርሱ ሌላ ባእድ አምልኮ የሚያካሄድና የሚያጋራ ሙሽሪክ ሰው እንኳ ከተፈጠረበት ፍጥረቱ አኳያ መለኮታዊ የተፈጥሮ ሕጉ የሚገዛው በመሆኑ ተገዥና ተመሪ ነው።

የሰውን ልጅ ሁለት ነገሮች ይጋፈጡታል፦

የመጀመሪያው፦ ለርሱ መመራትንና መታዘዝን፣እርሱን መግዛትን፣እርሱን መውደድና ወደርሱ መቃረብን፣እርሱ የሚወደውን ሐቅን፣በጎ ምግባርንና እውነት መናገርን መውደድን፣እርሱ የሚጠላቸውን ውሸት፣ሸርና ተንኮል፣ግፍና በደልን መጥላትን፣እነዚህን ተከትለው የሚመጡ ገንዘብ፣ቤተሰብና ልጅ መውደድን፣የመብላት የመጠጣትና የወሲብ ፍላጎቶችን የመሳሰሉና አላህ (ሱ.ወ.) በሰዎች ውስጥ ያኖራቸው ተፈጥሮአዊ ጉዳዮችን ሁሉ የሚመለከት ነው።

ሁለተኛው፦ የሰው ልጅ መሻትና ምርጫው ነው። አላህ (ሱ.ወ.) መልክተኞችን ወደ ሰው ልጆች ልኳል፤እውነትን ከሐሰት፣ቅን መመራትን ከጥመት፣በጎውን ከክፉው ይለይበት ዘንድ መላኮታዊ መጻሕፍትን አስተላልፎአል። ምርጫውን በግልጽ ግንዛቤ ላይ ይመሰርት ዘንድም አእምሮንና የማስተዋል ብቃትን ቸሮታል። ሰለዚህም ከሻ በጎውን መንገድ መርጦ ይከተልና ወደ እውነትና ወደ ቀጥተኛው መንገድ ይመራዋል፤ካስፈለገውም በምርጫው እኩይ መንገድ ይከተልና ወደ ክፋትና ውድመት መንገድ ይወስደዋል። አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{ ፦ እውነቱም ከጌታችሁ ነው፤የሻም ሰው ይመን፤የሻም ሰው ይካድ፣በላቸው፤እኛ ለበደለኞች አጥርዋ በነሱ የከበበ የኾነችውን እሳት አዘጋጅተናል፤(ከጥም) እርዳታንም ቢፈልጉ፣እንደ ዘይት ዝቃጭ ባለ፣ፊቶችን በሚጠብስ ውሃ፣ይረዳሉ፤መጠጡ ከፋ! መደገፊያይቱም ምንኛ አስከፋች!}[አል ከህፍ፡29]

ከመጀመሪያው ነጥብ አንጻር የሰውን ልጅ ከተመለከትነው ከጥንተ መሰረቱ ለአላህ ተመሪ ለመሆን የተፈጠረ፣ለዚሁ የተገራና እንደተቀሩት ፍጥረታት ሁሉ ከዚህ ውጭ መሆን የማይችል መሆኑን እንገነዘባለን።

ከሁለተኛው ነጥብ አኳያ ካስተዋልነው ደግሞ የመምረጥ አቅም የተቸረው፣የፈለገውን የሚመርጥ ከሻው ተመሪ ሙስሊም መሆን ከፈለገም አስተባባይ ከሓዲ መሆን የሚችል ሆኖ እናገኘዋለን። አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{እኛ፣ወይ አመስጋኝ ወይም ከሓዲ ሲኾን መንገዱን መራነው፤(ገለጽንለት)።}[አል ደህር፡3]

በዚህ ምክንያትም ሰዎችን ሁለት ዓይነት ሆነው እናገኛቸዋለን። እነሱም፦

ፈጣሪውን የሚያውቅ፣ጌታው ገዥውና አምላኩ መሆኑን አምኖ እርሱን ብቻ የሚያመልክ፣ወዶና ፈቅዶ በሚመርጠው ሕይወቱ የርሱን ሕግና ሥርዓት የሚከተል፣በተፈጥሮው ለጌታው ወደደም ጠላ ተመሪ እንደሆነ ሁሉ በፍላጎቱና በምርጫውም ለርሱ ውሳኔ ተገዥ የሆነ ሰው ነው። ሙስሊምነቱን (ለአላህ ተገዥነቱን) ምሉእ ያደረገ ምሉእ ሙስሊምም እንዲህ ዓይነቱ ሰው ሲሆን፤ነቢያትና መልክተኞችን ወደርሱ የላካቸውን፣የዕውቀትና የመማር ችሎታን የቸረውን ፈጣሪ ጌታውን ያወቀ በመሆኑ ዕውቀቱ ትክክለኛ ዕውቀት ሆኗል። አእምሮውን አሰርቶ ግንዛቤንና ማስተዋልን ያጎናጸፈውን አንድ አላህ ብቻ እንጂ ሌላን ላለመግገዛት የወሰነ በመሆኑም አእምሮውና አስተሳሰቡ ትክክለኛ ሆኗል። የመናገርንና የአንድበትን ጸጋ የሰጠውን የአንድ አላህን ጌትነት ብቻ የሚቀበል በመሆኑ አንደበቱም ሐቅን ብቻ የሚናገር ትክክለኛ አንደበት ሆኗል። አሁን በገዛ ምርጫውና በፍላጎቱ በሚሆኑት ነገሮች በአላህ ሕግና መመሪያ ተመሪ በመሆኑ በሕይወቱ ውስጥ የቀረው ነገር እውነት ብቻ ሆኗል። ፍጥረታት ሁሉ የሚግገዙትንና ለወሳኔዎቹ ተገዥ የሆኑትን ጥበበኛውንና ዐዋቂውን አንድ አላህን ብቻ የሚያመልክ በመሆኑም በርሱና በዩኒቨርሱ ውስጥ ባሉት የተቀሩ ፍጥረታት - አላህ (ሱ.ወ.) ለርሱ የተገሩ አድርጓቸዋልና - መካከል የትውውቅና የመናበብ ትስስርም ተመስርቷል። አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{እርሱ መልካም ሠሪ ኾኖ ፊቱን ወደ አላህ የሚሰጥም ሰው፣ጠንካራን ገመድ በእርግጥ ጨበጠ፤የነገሩም ሁሉ ፍጻሜ ወደ አላህ ነው።}[ሉቅማን፡22]

ዘላለማዊው መልክት የሁሉም ነቢያትና መልክተኞች ሃይማኖት ነው፦

እስላም አላህ ለመላው የሰው ልጅ ያስተላለፍው ዩኒቨርሳል ሃይማኖት ነው። አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{አምላካችሁም አንድ አምላክ ብቻ ነው፤ለርሱም ብቻ ታዘዙ፤ለአላህ ተዋራጆችንም አብስራቸው።} [አል ሐጅ፡34]

እስላም የሁሉም ነቢያትና መልክተኞችም ሃይማኖት ነው። አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{በአላህና ወደኛ በተወረደው (ቁርኣን)፣ወደ ኢብራሂምም፣ወደ እስማዒልና ወደ ኢስሐቅም፣ወደ ያዕቁብና ወደ ነገዶቹም በተወረደው፣በዚያም ሙሳና ዒሳ በተሰጡት፣በዚያም ነቢያት ሁሉ ከጌታቸው በተሰጡት፣ከነርሱ በአንድም መካከል የማንለይ ስንኾን አመንን፤እኛም ለርሱ (ለአላህ) ታዛዦች ነን በሉ።}[አል በቀራህ፡136]

ሁሉም የአላህ መልክተኞች አምነውበታል፤ለአላህ (ሱ.ወ.) መስለማቸውንም አውጀው ወደርሱ እንዲመጡም ለሌሎች ጥሪ አድርገዋል። አላህ (ሱ.ወ.) ነቢዩ ኑሕን  አስመልክቶ እንዲህ ብሏል፦

{የኑሕንም ወሬ በነሱ ላይ አንብብላቸው፤ለሕዝቦቹ ባለ ጊዜ (አስታውስ)፤፦ ሕዝቦቼ ሆይ! በናንተ ውስጥ ብዙን ጊዜ መቆየቴ በአላህም ታምራት ማስታወሴ በናንተ ላይ የከበደ ቢኾን፤በአላህ ላይ ተጠግቻለሁ፣ነገራችሁንም ከምታጋሩዋቸው (ጣዖታት) ጋር ኾናችሁ ቁረጡ፤ከዚያም ነገራችሁ በናንተ ላይ ድብቅ አይኹን (ግለጹት)፤ከዚያም (የሻችሁትን) ወደኔ አድርሱ፤ጊዜም አትስጡኝ (ከምንም አልቆጥራችሁም)።}[ዩኑስ፡71-72]

ነቢዩ ኢብራሂምን  አስመልክቶም አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{ጌታው ለርሱ ታዘዝ [ስለም] ባለው ጊዜ (መረጠው)፤ለዓለማት ጌታ ታዘዝኩ [ሰለምኩ] አለ።}[አልበቀራህ፡131]

ኢብራሂምም  ልጆቻቸውንና ዝርዮቻቸውን ከርሳቸው በኋላም እስላምን እንዲከተሉ አዘዋል። አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{በርሷም (በሕግጋቱ) ኢብራሂም ልጆቹን አዘዘ፤ያዕቆብም፣(እንደዚሁ አዘዘ)፤ልጆቼ ሆይ! አላህ ለናንተ ሃይማኖትን መረጠ፤ስለዚህ እናንተ ሙስሊሞች ኾናችሁ እንጂ አትሙቱ (አላቸው)። ያዕቆብን ሞት በመጣበት ጊዜ፣ለልጆቹ ከኔ በኋላ ማንን ትግገዛላችሁ? ባለ ጊዜ፣ቀራቢዎች ነበራችሁን? (እነርሱም) አምላክህንና የአባቶችህን፣የኢብራሂምን፣የእስማዒልንና የእስሐቅንም አምላክ፣አንድ የኾነውን አምላክ፣ እኛ ለርሱ ፍጹም ታዛዦች [ሙስሊሞች] ኾነን እናመልካለን አሉ።}[አልበቀራህ፡132-133]

ስለ ነቢዩ ሙሳም  አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{ሙሳም አለ፦ ሕዝቦቼ ሆይ! በአላህ አምናችሁ እንደኾነ፣በርሱ ላይ ተጠጉ፤ታዛዦች [ሙስሊሞች] እንደ ኾናችሁ (አላህ ላይ ትመካላችሁ)።}[ዩኑስ፡84]

የአልመሲሕ ዒሳን  ዜና አስመልክቶም አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{ወደ ሐዋርያትም በኔና በመልክተኛዬ እመኑ፣በማለት ባዘዝኩ ጊዜ፣(አስታውስ)፤አመንን፤እኛም ሙስሊሞች መኾናችንን፣መስክር አሉ።}[አልማእዳህ፡111]

እስላም ነቢዩና መልክተኛው ሙሐመድ  ይዘው የመጡትና ለመላው የሰው ዘር የተላለፈ፣አላህ (ሱ.ወ.) ለባሮቹ ምሉእ አድርጎት ከሃይማኖት በኩል የወደደላቸው የመጨረሻውና የመደምደሚያው መለኮታዊ መልክት (መገለጥ) ነው። አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{ዛሬ ሃይማኖታችሁን ለናንተ ሞላሁላችሁ። ጸጋዬንም በናንተ ላይ ፈጸምኩ። ለናንተም እስላምን ከሃይማኖት በኩል ወደድኩ፤}[አል ማእዳህ፡3]

በዚህ ክቡር ቁርኣናዊ አንቀጽ ውስጥ አላህ (ሱ.ወ.) ለመላው የሰው ልጅ ከሃይማኖት በኩል እስላምን የወደደላቸውና ፈጽሞ የማይጠላው መሆኑን ተናግሯል። እውነተኛው ሃይማኖት እርሱ ብቻ መሆኑንና ከርሱ በስተቀር ከማንም ሰው ሌላ ሃይማኖት ተቀባይነት እንደሌለውም አውጇል። አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{አላህ ዘንድ (የተወደደ) ሃማኖት እስላም ብቻ ነው፤}[ኣሊ ዒምራን፡19]

በተጨማሪም አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{ከእስላም ሌላ ሃይማኖትን የሚፈልግ ሰው፣ፈጽሞ ከርሱ ተቀባይ የለውም፤እርሱም በመጨረሻይቱ ዓለም ከከሳሪዎቹ ነው።}[ኣሊ ዒምራን፡85]

አላህ (ሱ.ወ.) በመጀመሪያው አንቀጽ ውስጥ እርሱ ዘንድ ተቀባይነት ያለው ሃይማኖት እስላም ብቻ መሆኑን ሲያረጋግጥ፣በሁለተኛው አንቀጽ ውስጥ ደግሞ ከእስላም ውጭ ከማንም ሌላ ሃይማኖትን እንደማይቀበልና ከሞት በኋላ መድህን የሚያገኙት የመታደል ባለቤቶች ሙስሊሞች ብቻ መሆናቸውን፣ሙስሊሞች ሳይሆኑ የሚሞቱ ሁሉ በወዲያኛው ሕይወት በእሳተ ገሀነም የሚቀጡ ከሳሪዎች መሆናቸውንም አስታውቋል። ነቢያት ሁሉ ለአላህ የሰለሙና የተገዙ ሙስሊሞች መሆናቸውና ለአላህ ሰልመው ለርሱ ከማይገዙት ነጻ መሆናቸውን ያወጁትም ለዚህ ነው። መዳንንና መታደልን የፈለገና እውነተኛው የሙሳና የዒሳ  ተከታይ ይሆን ዘንድ የወደደ ይሁዲና ክርስቲያን ሁሉ፣ሙሳ ዒሳ፣ሙሐመድና  ሁሉም የአላህ መልክተኞች ሙስሊሞችና ለእስላም ጥሪ ያደረጉ በመሆናቸው፣የመጨረሻውን የእስላም መልክተኛ ሙሐመድን  መከተል ይኖርበታል። እስላም የሁሉም ነቢያትና መልክተኞች ሃይማኖት በመሆኑ ከመደምደሚያቸው ከሙሐመድ  መላክ በኋላ ለኖረ ማንኛውም ሰው እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ሙሐመድን አምኖ በመቀበል ካልተከተላቸውና በቁርኣን ካልተመራ በስተቀር ለአላህ ተገዥ ሙስሊም ነኝ ብሎ ራሱን ሊጠራ አይችልም። ይህን በማስመልከት የአላህ መልክተኛ  እንዲህ ብለዋል፦ {ነፍሴ በእጁ በሆነችው [አላህ] እምላለሁ፣ከዚህ ሕዝብ (ኡምማ) ውስጥ ስለኔ የሰማና በተላኩበት ነገር ሳያምን የሞተ ማንኛውም ይሁዲ ይሁን ክርስቲያን (ዕጣ ፈንታው) ከእሳት ሰዎች አንዱ መሆን ብቻ ነው።} [በሙስሊም የተዘገበ] (30)

የዘላለማዊው መልክት ምሉእነት፦

አላህ (ሱ.ወ.) በመልክተኛ በሙሐመድ  አማካይነት ለመላው የሰው ልጆች ያስተላለፈው ይህ እስላም በአንድ አላህ ብቻ የማመን የተውሒድ ሃይማኖት ነው። አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{ብታጋራ ሥራህ በእርግጥ ይታበሳል፤በእርግጥም ከከሓዲዎቹ ትኾናለህ ማለት ወደ አንተም ወደነዚያም ካንተ በፊት ወደነበሩት በእርግጥ ተወርዷል። እርሱ ብቻ (ሁል ጊዜ) ሕያው ነው፤ከርሱ ሌላ አምላክ የለም፤ሃይማኖትንም ለርሱ ያጠራችሁ ስትኾኑ፣ምስጋና ለዓለማት ጌታ ለአላህ ይኹን፣የምትሉ ኾናችሁ ተገዙት። እኔ ከጌታዬ አስረጂዎች በመጡልኝ ጊዜ፣እነዚያን ከአላህ ሌላ የምትግገዙዋቸውን እንዳልገዛ ተከልክያለሁ፤ለዓለማት ጌታም እንድግገዛ [እንድሰልም] ታዝዣለሁ በላቸው።}[አልሙእሚን፡65-66]

እስላም አለአላህ (ሱ.ወ.) ብቻ ሃይማኖትን ፍጹም አድርጎ ማጥራት ነው። አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{የተለያዩ (ከብር ከወርቅ ከእንጨት የተሠሩ) አምላኮች ይሻላሉን ወይስ አሸናፊው አንዱ አላህ? ከርሱ ሌላ እናንተና አባቶቻችሁ (አማልክት ብላችሁ) የጠራችኋቸውን ስሞች እንጅ አትግገዙም፤አላህ በርሷ ምንም አስረጅ አላወረደም፤ፍርዱ የአላህ እንጅ የሌላ አይደለም፤እርሱን እንጅ ሌላን እንዳትግገዙ አዟል፤ይህ ትክክለኛው ሃይማኖት ነው፤ግን አብዛኞቹ ሰዎች አያውቁም።}[ዩሱፍ ፡39-40]

እስላም በእውነታውና በጠራ ይዘቱ ቢቀርብለት የሰው ልጅ ተፈጥሮ የሚታዘዝለትና የሚቀበለው የአስተዋይ ሚዘናዊ አእምሮ ሃይማኖት ነው። አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{ይህ ትክክለኛው ሃይማኖት ነው፤ግን አብዛኞቹ ሰዎች አያውቁም።}[ዩሱፍ፡-40]

የማስረጃ የአስረጅና የማሳመኛ ነጥብ የአቀራረብ ስልት ያለው ሃይማኖትም ነው። አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{እውነተኞች እንደ ኾናችሁ፣አስረጃችሁን አምጡ በላቸው።}[አልነምል፡64]

የእፎይታ፣የመታደል፣የደስተኝነትና የመረጋጋት ሃይማኖትም ነው፦

{ከወንድ ወይም ከሴት፣እርሱ አማኝ ኾኖ በጎን የሠራ፣መልካም ኑሮን በእርግጥ እናኖረዋለን፤ይሠሩትም ከነበሩት ነገር በመልካሙ ምንዳቸውን እንመነዳቸዋለን።}[አል ነሕል፡97]

ሙሐመድ  ከአላህ (ሱ.ወ.) ተልከው ይዘውት በመጡት ሃይማኖት መልካም የሆኑ ነገሮች ሁሉ የተፈቀዱበት፣ጎጂ የሆኑ እኩይ ነገሮች ሁሉ የተከለከሉበት፣በበጎና ሰናይ ተግባራት ሁሉ የሚያዝ፣ከእኩይና ክፉ ሥራዎች ሁሉ የሚከለክል ሃይማኖት ነው። ገርና ቀላል የሆነ፣አስቸጋሪ ነገር የሌለበት፣መሸከምና መወጣት የማይችሉትን ኃላፊነት በሰዎች ጫንቃ ላይ የማይጥል ምቹ ሃይማኖት ነው። አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{ለነዚያ፣ያንን እነሱ ዘንድ በተውራትና በኢንጂል ተጽፎ የሚያገኙትን፣የማይጽፍና የማያነብ ነቢይ የኾነውን መልክተኛ የሚከተሉ ለኾኑት፣(በእርግጥ እጽፋታለሁ)፤በበጎ ሥራ ያዛቸዋል፤ከክፉም ነገር ይከለክላቸዋል፤መልካም ነገሮችንም ለነርሱ ይፈቅድላቸዋል፤መጥፎ ነገሮችንም በነሱ ላይ እርም ያደርግባቸዋል። ከነሱም ላይ ሸክማቸውንና እነዚያንም በነሱ ላይ የነበሩትን እንዛዝላዎች (ከባድ ሕግጋቶች) ያነሳላቸዋል፤እነዚያም በርሱ ያመኑ፣ያከበሩትም፣የረዱትም፣ያንንም ከርሱ ጋር የተወረደውን ብርሃን የተከተሉ፣እነዚያ እነሱ የሚድኑ ናቸው።}[አል አዕራፍ፡157]

እስላም ለሁሉም ዘመንና በየትኛውም ስፍራ እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ገርና ምቹ የሆነ የተሟላ ሃይማኖት ሲሆን፣የሰው ልጆች ለዚህች ዓለም ሕይወታቸውና ለመጪው ዘላለማዊ ሕይወታቸው የሚያስፈልጓቸውን መንፈሳዊና ቁሳዊ ነገሮች ሁሉ ያካተተ እምነት ነው።

የመታደል፣የደስተኝነትና የሕሊና ዕረፍት መንገድ ነው። የዕውቀትና የስልጣኔ፣የፍትሕና የደግነት፣የክብርና የነጻነት፣የሁሉም በጎና ሰናይ ነገሮች ጎደና ነው። ምንኛ ምሉእ ምንኛ ድንቅ ሃይማኖት!! በጎ ሠሪ ሆኖ ራሱን ለአላህ (ሱ.ወ.) ተገዥ አድርጎ ፈልጎና ወስኖ ከሰለመ ሰው ይበልጥ ያማረ ማን አለና? አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{እርሱም መልካም ሠሪ ኾኖ ፊቱን ለአላህ ከሰጠና የኢብራሂምንም መንገድ ቀጥተኛ ሲኾን፣ከተከተለ ሰው፣ይበልጥ ሃይማኖቱ ያማረ ማነው? አላህም ኢብራሂምን ፍጹም ወዳጅ አድርጎ ያዘው።}[አልኒሳእ፡125]

ይህ ካንተ ከራስህ ይበልጥ ለአንተ አሳቢና ርህሩህ ከሆነው ከፈጣሪ አምልክህ የተላለፈልህ ጥሪ ነው። ከጨለማ ወደ ብርሃን ትወጣ ዘንድ የቀረበልህ ጥሪ ነው። አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{የመጽሐፉ ባለቤቶች ሆይ! በኛና በናንተ መካከል ትክክል ወደኾነች ቃል ኑ፤(እርሷም) አላህን እንጅ ሌላን ላንገዛ፣በርሱም ምንንም ላናጋራ፣ከፊላችንም ከፊሉን ከአላህ ሌላ አማልክት አድርጎ ላይይዝ ነው፤በላቸው። እምቢ ቢሉም፦ እኛ ሙስሊሞች መኾናችንን መስክሩ በሏቸው።}[ኣሊ ዒምራን፡64]

ራሱን ለአላህ (ሱ.ወ.) ተገዥ አድርጎ ለርሱ ከተመራ ሰው በተቃራኒ ደግሞ፣ለዚህ ሃይማኖት ትክክለኛነትና እውነተኛነት አረጋጋጭና አስረጅ የሆኑ ታምራትና ምልክቶች እየጎረፉለት አላህ ያነጸበትን ንጹሕ ተፈጥሮ በክህደትና በማስተባበል መጋረጃ ሸፍኖ፣ተውሒድን በመጻረር በአላህ ማጋራትን (ሽርክን)፣ከእውነት ብርሃን፣ከእርግጠኝነትና ከቅን መመሪያ ይልቅ ተረትና ቅዠትን ለራሱ የመረጠ ሌላ ሰው እናገኛለን።

ለአንድ አላህ ብቻ አገልጋይ ከመሆን ይልቅ ቀሳውስትና ካህናትን ለመሳሰሉ መሰሉ ለሆኑ ሰብአዊ ፍጡራንና ለመልክተኞችም ጭምር ራሱን ተገዥ ባሪያ ያደረገ ሰው፣ንጹሕ ተፈጥሮውን በክሏል። ሰብአዊ አእምሮውን አውልቆ አስቀምጧል። የጠራ ተፈጥሮውን ወደ ጎን ብሎ ለስሜታዊ ዝንባሌዎችና ለተለያዩ ውዥንብሮች ተገዥ ሆኗል፤የሚወለድ ሕጻን ሁሉ የሚወለደው በተፈጥሮው እስላምን ይዞ ነውና። አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{የአላህን ፍጥረት ያችን አላህ ሰዎችን በርስዋ ላይ የፈጠረባትን (ሃይማኖት ያዙዋት)፤የአላህን ፍጥረት መለወጥ የለም፤ይህ ቀጥተኛ ሃይማኖት ነው፤ግን አብዛኛዎቹ ሰዎች አያውቁም።}[አል ሩም፡30]

አሁን አንባቢ ራሱ በአላህ ያስተባበለ ሰው የተዘፈቀበትን የከፋ ጥመትና ግልጥ ማፈንገጥ መገመት ይችላል። አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{እርሱ ያ በምድር ውስጥ ምትኮች ያደረጋችሁ ነው፤የካደም ሰው ክሕደቱ በርሱው ላይ ብቻ ነው፤ከሓዲዎችንም ክሕደታቸው ከጌታቸው ዘንድ መጠላትን እንጂ ሌላ አይጨምርላቸውም፤ከሓዲዎችንም ክሕደታቸው ኪሳራን እንጂ አይጨምርላቸውም፤}[ፋጢር፡39]

የዚህ የመልክተ እስላም መሰረቶች ምንጮችና ልዩ ባሕርያት ምንድን ናቸው?