የእሰላም ምንጮች

የእሰላም ምንጮች

የእስላም ሃይማኖት ሕግጋቱን፣ዐቂዳውንና ዝርዝር ሕጎቹን የሚያመነጨው ከመለኮታዊ ወሕይ (መገለጥ) - ከቁርኣንና ከነቢዩ ሱንና - ሲሆን ሁለቱ የእስላም አበይተ መሰረታዊ የሕግ ምንጮች ናቸው። ከዚህ በመቀጠል ከሁለቱ ምንጮች ጋር አጠር ባለ ሁኔታ እንተዋወቃለን፦

ሀ - ታላቁ ቁርኣን፦

አላህ (ሱ.ወ.) ቁርኣንን ለጥንቁቆች መመሪያ፣ለሙስሊሞች መተዳደሪያ፣እርሱ መመራት ለሻላቸው ሰዎች ልቦና ፈውስ፣መድህን ለወደደላቸው ሰዎች ችቦና ብርሃን ይሆን ዘንድ ወደ መልክተኛው ወደ ሙሐመድ  አስተላልፎታል። ቁርኣን ነቢያትና መልክተኞች ከአላህ (ሱ.ወ.) ተልከው ይዘው የመጡትን መሰረታዊ መርሆዎች ያካተተ መጽሐፍ ነው። ሙሐመድ  ብቸኛው የአላህ መልክተኛ እንዳልሆኑ ሁሉ ቁርኣንም ብቸኛው የአላህ መጽሐፍ አይደለም። አላህ (ሱ.ወ.) ወደ ኢብራሂም ጽሑፎችን አውርዷል፤ሙሳንም በተውራት፣ዳውድን በዘቡር (መዝሙር) አክብሯቸዋል። አልመሲሕ ዒሳም ኢንጂልን ይዘው መጥተዋል። እነዚህ መጽሐፎች ሁሉም አላህ (ሱ.ወ.) ወደ ነቢያቱና መልክተኞቹ ያስተላለፋቸው ወሕይ (መለኮታዊ መገለጥ) ናቸው። ይህ ቁርኣን ከአላህ (ሱ.ወ.) የተላለፈ ወሕይ መሆኑን ከሚመሰክሩ ነገሮች ውስጥ አንዱ፣በሁሉም የአላህ መልክተኞችና ነቢያት ያለ ምንም ልዩነት ማመንን የሃይማኖቱ አንድ አቢይ ማእዘን አድርጎ ያረጋገጠ መሆኑ ነው። አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{እነዚያ በአላህና በመልክተኞቹ የሚክዱ፣በአላህና በመልክተኞቹም መካከል መለያየትን የሚፈልጉ፣በከፊሉም እናምናለን፣በከፊሉም እንክዳለን የሚሉ፣በዚህም መካከል መንገድን ሊይዙ የሚፈልጉ፤እነዚያ በውነት ከሓዲዎቹ እነርሱ ናቸው። ለከሓዲዎችም አዋራጅን ቅጣት አዘጋጅተናል። እነዚያም በአላህና በመልክተኞቹ ያመኑ፣ከነሱም ያልለዩ፣እነዚያ ምንዳዎቻቸውን በእርግጥ ይሰጣቸዋል። አላህም መሓሪ አዛኝ ነው።}[አልኒሳእ፡150-152]

ዳሩ ግና እነዚህ የቀድሞ መጽሐፍት ብዙው ክፍላቸው ጠፍቷል፤አብዛኞቻቸው ከስመዋል፤ለመዛባት፣ለመጣመም፣ለብረዛና ለክለሳ ተጋልጠዋል። (42)

ታላቁ ቁርኣን ግን አላህ (ሱ.ወ.) ከብረዛና ከክለሳ የመጠበቅ ኃላፊነቱን ለራሱ ወስዷል። አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{እኛ ቁርኣንን እኛው አወረድነው፤እኛም ለርሱ ጠባቂዎቹ ነን።}[አል ሕጅር፡9]

በቀደሙት መለኮታዊ መጽሐፎች ላይ ተቆጣጣሪ፣ዋቢና ሻሪ አድርጎታልም። ይህንኑ በማስመልከት አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{ወደ አንተም መጽሐፉን ከበፊቱ ያለውን መጽሐፍ አረጋጋጭና በርሱ ላይ ተጠባባቂ [ተቆጣጣሪ] ሲኾን በውነት አወረድን፤}[አልማእዳህ፡48]

ለሁሉም ነገር አብራሪና መሪ አድርጎት ያስተላለፈው መሆኑንም ገልጾአል፦

{መጽሐፉንም፣ለሁሉ ነገር አብራሪ፣መሪም እዝነትም፣ለሙስሊሞችም አብሳሪ ኾኖ ባንተ ላይ አወረድነው።}[አል ነሕል፡89]

ቁርኣን መመሪያ እዝነትና በረከት መሆኑን ሲገልጽም አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{ስለዚህ ከጌታችሁ ግልጽ ማስረጃ መምሪያም፣እዝነትም በእርግጥ መጣላችሁ፤}[አልአንዓም፡157]

ወደ ቀጥተኛው መንገድ የሚወስድ መጽሐፍም ነው። አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{ይህ ቁርኣን ወደዚያች፣እርሷ ቀጥተኛ ወደ ኾነችው መንገድ ይመራል፤እነዚያንም በጎ የሚሠሩትን ምእመናን ለነሱ ታላቅ ምንዳ ያላቸው መኾኑን ያበስራል።}[አልእስራእ፡9]

የሰው ልጆችን በሁሉም የሕይወት ፈርጆችና የኑሮ ጉዳዮቻቸው ወደ ተመራጩ ቀጥተኛ ጎዳና ይመራቸዋል። (43)

ታላቁ ሕያው መጽሐፍ ቁርኣን ለሰው ልጆች አስፈላጊ የሆኑ ነገሮችን ሁሉ በምልዓት ያካተተ፣መሰረታዊ መርሆዎችን፣የእምነትና የዐቂዳ፣የሕግጋትና የበይነሰባዊ ግንኙነት፣የስነምግባርና የግብረገብነት . . መሰረቶችን አቅፎ ይዟል። አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{በመጽሐፉ ውስጥ ምንም ነገር [ሳንገልጽ] አልተውንም።}[አል አንዓም፡38] (44)

ለ - ነቢያዊው ሱንና (ፈለግ)፦

አላህ (ሱ.ወ.) ቅዱስ ቁርኣንን ወደ መልክተኛው  ሲያስተላልፍ ነቢያዊውን ሱንናም አስተላልፎላቸዋል። አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{እርሱ (ንግግሩ) የሚወረድ ራእይ እንጅ ሌላ አይደለም።}[አልነጅም፡4]

ሱንና እንደ ቁርኣን ሲሆን ይህንኑ በማስመልከት ነቢዩ  እንዲህ ብለዋል፦ {ንቁ ዕወቁ! መጽሐፉና መሰሉ (ሱንና) አብረው ተሰጥቶኛል። መጽሐፉና መሰሉ (ሱንና) አብረው ተሰጥቶኛል።}[በአሕመድ የተዘገበ] ነቢዩ  ለሰዎች የሚያደርሱት እንዲያደርሱ ከአላህ የታዘዙትን ብቻ ነው። አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{ወደኔ የሚወረደውን እንጅ ሌላ አልከተልም፤እኔም ግልጽ አስፈራሪ [አስጠንቃቂ] እንጅ ሌላ አይደለሁም በላቸው።}[አልአሕቃፍ፡9]

በመሆኑም ነቢያዊው ሱንና ሁለተኛው የእስላም የሕግ ምንጭ ነው። ሱንና እሰከ ነቢዩ  ድረስ በሚዘልቅ ትክክለኛና አስተማማኝ የዘገባ ሰንሰለት የተዘገበ የነቢዩ ንግግር፣ተግባር፣ገለጻ ወይ ማረጋገጫ ሲሆን የቅዱስ ቁርኣን ተግባራዊ ማብራሪያ ነው። አላህ (ሱ.ወ.) በቁርኣን ውስጥ የተካተቱ ጠቅለል ያሉ ወይም ማብራሪያና ገለጻ የሚሹ ጉዳዮችን እንዲያብራሩና እንዲተነትኑ ለነቢዩ  ፈቅዶላቸዋል። አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{ወደ አንተም ለሰዎች ወደነሱ የተወረደውን (ፍች) ልትገልጽላቸውና ያስተነትኑም ዘንድ ቁርኣንን አወረድን።}[አልነሕል፡44]

እናም ሱንና ቅዱስ ቁርኣንን ያብራራል፤አንቀጾቹን ይተነትናል፤ጠቅለል ያሉ ድንጋጌዎቹን ይዘረዝራል። ነቢዩ  ወደርሳቸው የወረደውን ቁርኣን አንቀጾች አንዴ በአንደበታቸው ሌላ ጊዜ ደግሞ በተግባራቸው አንዳንዴም በሁለቱም ጭምር ያብራሩ ነበር። ሱንና አንዳንድ ሕጎችንና ድንጋጌዎችን በማብራራት ረገድ ራሱን ችሎ የሚመጣበት ሁኔታም ሊኖር ይችላል። (46)

ነቢዩ  ከአላህ የታዘዙትን በትጋት ይፈጽሙና ለሰዎች ያብራሩ ስለነበር፣እርሳቸው የሰሩትን አይተው እንዲሰሩ ያዙ ስለነበር የጠራው ነቢያዊ ሱንና የእስላም ሕግጋት እምነት፣አምልኮተ አላህ፣በይነሰባዊ ግንኙነቶችና የስነምግባር ደንቦች ተግባራዊ ማብራሪያና መገለጫ ነው። እምነታቸው ምሉእ ይሆን ዘንድ ምእመናን በተግባራቸውና በአንደበታቸውም የነቢዩን  አርአያ እንዲከተሉ አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ሲል አዟል፦

{ለናንተ፣አላህንና የመጨረሻውን ቀን የሚከጅል ለኾነ ሰው፣አላህንም በብዙ ለሚያወሳ፣በአላህ መልክተኛ መልካም መከተል [አርአያ] አላቸው።}[አል አሕዛብ፡21] (47)

ክቡራን የነቢዩ ባልደረቦች (ሶሓባ) የነቢዩን  ንግግሮችና ሥራዎቻቸውን ለቀጣዩ ትውልድ ያስተላለፉ ሲሆን ቀጣዩ ትውልድም ሱንናቸውን በመድብሎች ሰብስቦ በማጠናቀር አቆይቶልናል። የሱንና ዘጋቢዎችና አጠናቃሪዎች በዘገባ ሰንሰለት አበጣጠርና በሀዲስ አሰባሰብ ላይ ጥብቅ መስፈርቶችን ይከተሉ ስለነበር፣የዘገባ ሰንሰለቱ እስከ ነቢዩ  ድረስ የሚዘልቅ ይሆን ዘንድ ሐዲሱን የሰማው ሰው ከሰማበት ሰው ጋር በአካል የተገናኘ ዘመነኛው መሆንን፣በዘገባ ሰንሰለቱ ውስጥ የሚገኙ ዘጋቢዎች ሁሉ በሃይማኖታቸው በመልካም ስነምግባራቸው የታመኑ፣እምነት የሚጣልባቸው ፍትሐዊነትን የተላበሱ ታማኞች መሆንን ለሐዲሱ ትክክለኛነት በመመዘኛነት ያስቀምጡ ነበር።

ቁርኣንና ሱንና ማመሳከሪያ ዋቢና ያዘዙትን መፈጸም ከከለከሉትም መከልከል የሚገባ ሁለቱ መሰረታዊ የእስላም የሕግ ምንጮች መሆናቸውን አምኖ መቀበል ግዴታ ነው። በሁለቱ ምንጮች ውስጥ የሰፈረው ሁሉ እውነት መሆኑን፣የአላህ (ሱ.ወ.)ስሞች፣ባሕርያትና ተግባራት አስመልክቶ በውስጣቸው በቀረበው ሁሉ ማመንና፣አላህ (ሱ.ወ.) ለምእመናን ወዳጆቹ ያዘጋጀላቸው ታላቅ ምንዳና ለአስተባባይ ከሃዲዎች ያሰናዳው መራር ቅጣትም ፍጹም እውነት መሆኑን ማመን ግዴታ ነው። አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{በጌታህም እምላለሁ (አላህ በራሱ መማሉ ነው) በመካከላቸው በተከራከሩበት ፍርድ እስከሚያስፈርዱህ፣ከዚያም ከፈረድከው ነገር በነፍሶቻቸው ውስጥ ጭንቀትን እስከማያገኙና ፍጹም መታዘዝን እስከሚታዘዙ ድረስ አያምኑም (ምእመን አይኾኑም)።}[አልኒሳእ፡65]

በተጨማሪም አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{መልክተኛውም የሰጣችሁን (ማንኛውንም) ነገር ያዙት። ከርሱም የከለከላችሁን ነገር ተከልከሉ።}[አል ሐሽር፡7]

ይህን መንገድ የተከተለ ሰው ምንኛ ታደለ!! የመታደል መንገድም ይህ ነውና!!