እስላማዊው ሸሪዓና ሰው ሠራሽ ሕግጋት . . ልዩነቶችና ተቃርኖዎች

እስላማዊው ሸሪዓና ሰው ሠራሽ ሕግጋት . . ልዩነቶችና ተቃርኖዎች

በእስላማዊው ሸሪዓና በሰው ሠራሽ ሕጎች መካከል ከተለያዩ ሁኔታዎች አንጻር ከፍተኛ ልዩነቶች ይገኛሉ፤ከነዚህም መካከል የሚከተሉትን እናገኛለን፦

ግርማ ሞገስ ቅድስና እና በሰው ዘንድ ያለው ከበሬታ፦

በሃይማኖታዊ ባሕርይው፣በሃይማኖታዊ ይዘቱና ከአላህ (ሱ.ወ.) የተላለፈ መለኮታዊ ከመሆኑ አንጻር፣የእስላም ሸሪዓ ልዩ በሆነ ግርማ ሞገስ፣በቅድስና እና በሰው ልቦና ውስጥ ባለው ከበሬታ ከሰው ሠራሽ ሕጎች ይለያል።

ሸሪዓው ከሰው ልጅ ተፈጥሮ ጋር የተጣጣመ፣ለሁሉም ዘመንና ስፍራ ምቹ መሆኑ ፦

ሕጉን የደነገገው የሆነውንና ወደፊት የሚሆነውን ሁሉ የሚያውቀው፣ስለፈጠራቸው ፍጥረታት ባሕርያት፣ተፈጥሮና ፍላጎቶቻቸው፣እነሱን የሚመለከተውን ማንኛውንም ነገር ከማንም በላይ የሚያውቅ፣ከአድልኦና ከማናንኛውም ዓይነት ዝንባሌ የጠራው የፍጥረታት ፈጣሪ አምላክ አላህ (ሱ.ወ.) ያስረተላለፈው መለኮታዊ ሕግ በመሆኑ፣ እስላማዊው ሸሪዓ በየትኛውም ስፍራና በየትኛውም ዘመን ለሚኖሩ ሁሉም ሕዝቦች ልዩ ሁኔታዎች፣የተለያዩ ስነምረህዳሮች፣ቋንቋዎች፣ብሔሮች፣ባህሎች . . ምቹ የሆነ የሕግ ሥርዓት ነው። አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{ወደ እውነት ተዘንባይ ኾነህ ፊትህን ለሃይማኖት ቀጥ አድርግ፤የአላህን ፍጥረት ያችን አላህ ሰዎችን በርስዋ ላይ የፈጠረባትን (ሃይማኖት ያዙዋት)፤የአላህን ፍጥረት መለወጥ የለም፤ይህ ቀጥተኛ ሃይማኖት ነው፤ግን አብዛኛዎቹ ሰዎች አያውቁም።}[አል ሩም፡30]

ሰው ሠራሽ ዓለማዊ ሕጎች ግን በሰዎች የተደነገጉ ናቸው። ሰዎች ደግሞ ትናንትና ዛሬ ያሻቸውን ያህል በዕውቀት ቢራቀቁም፣ነገ የሚከሰተውን አያውቁም። ከፊሉን የሰው ልጅ ሕርያት ቢያውቁ ሁሉን ማወቅ አይችሉም። ከዚህ ስንነሳም የሚያወጧቸው ሕጎች ከሁሉም የሰው ልጅ ተፈጥሮዎችም ሆነ ከሁሉም የአካባቢ ሁኔታዎች ጋር የሚጣጣሙአይሆኑም። ለአንዱ ሕዝብ የሚስማሙ ቢሆን ለሌላው ሕዝብ የሚበጁ አይሆኑም።

እስላማዊው ሸሪዓ ከእውነታ ከሐቅና ከፍትሕ ጋር የተጣጣመ መሆኑ፦

እስላማዊው ሸሪዓ ከእውነታ ከሐቅና ከፍትሕ ጋር ሙሉ በሙሉ የተጣጣመ የሕግ ሥርዓት ነው። ይኸውም ከአላህ (ሱ.ወ.) የተላለፈ በመሆኑ በሕግ አወጣጡ ውስጥ የመሳሳት፣የግድፈትና እርስበርስ የመጻረር ችግር ፈጽሞ የሌለበት በመሆኑ፣ከበደል፣ከግፍ፣ከጭቆና፣ለስሜትና ለዝንባሌዎች ተገዥ ከመሆን ፈጽሞ የጠራ በመሆኑ ነው። አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{የጌታህም ቃላት እውነተኛና ትክክለኛ ስትኾን፣ተፈጸመች፤ለቃላቱ ለዋጭ የለም፤እርሱም ሰሚው፣ዐዋቂው ነው።}[አልአንዓም፡115]

ከፍላጎቶች የጠራውና የተብቃቃው አላህ (ሱ.ወ.) ብቻ ነው፤የነገሮችን ሁሉ ውስጣዊና ውጫዊ ሁኔታዎች ግልጹንና ስውሩንም በፍጹምነት የሚያውቅ እርሱ ብቻ ነው። ዕውቀቱ ሁሉንም ያካበበ ፍጹማዊ ዕውቀት ያለው አምላክ በመሆኑም ለፍጡራኑ የሚበጃቸውን እንጂ አያዛቸውም፤ከሚጎዳቸው ነገር እንጂ አይከለክላቸውም። ሰው ሠራሽ ሕጎች ግን ለስሕተትና ለግድፈት፣ለመዘንጋትና ለዝንባሌዎች አዝማሚያ የተጋለጡ ናቸው። በመሆኑም ከስህተት፣ከጉድለት፣ከመለውጥና ከመቀያየር ነጻ ሊሆኑ አይችሉም። አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{ከአላህ ሌላ ዘንድ በነበረ ኖሮ፣በርሱ ውስጥ ብዙን መለያት ባገኙ ነበር።}[አልኒሳእ፡82]

እስላማዊው ሸሪዓ ለሰብዓዊ ጎን ትኩረት የሚሰጥ መሆኑ፦

እስላማዊው ሸሪዓ የሰው ልጆች እሳቤ ውጤት የሆነ ተራ ሕግ አይደለም። ኃያሉ ፈጣሪ አላህ (ሱ.ወ.) ለፈጠራቸው ሰዎች ምቹና ተስማሚ አድርጎ የደነገገው ከሰብአዊ ፍጡራን ተፈጥሮ ጋር የተጣጣመ መለኮታዊ ሕግ እንጂ። አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{የፈጠረ አምላክ እርሱ ዕውቀተ ረቂቁ፣ውስጥ አዋቂው ሲኾን (ምስጢርን ሁሉ) አያውቅምን።}[አል ሙልክ፡14]

ገርና ቀለል የሚሆንላቸውንም ከማንም በላይ የሚያውቀው እርሱ ብቻ ነው፦

{አላህ ከናንተ ሊያቃልልላችሁ ይሻል። ሰውም ደካማ ኾኖ ተፈጠረ።}[አልኒሳእ፡28]

ሰው ሠራሽ ሕጎች ግን የሕግ አውጭዎቹን ፍላጎት መሰረት በማድረግ እንደ ዝንባሌዎቻቸውና እንደ አካባቢያቸው ትኩረት የሚቀረጹ ናቸው።

እስላማዊው ሸሪዓ ከመንፈሳዊ ጎን ጋር የተሳሰረ መሆኑ፦

እስላማዊው ሸሪዓ ውስጣዊና አፍአዊ፣ቁሳዊና ሕሊናዊ፣ግልጽና ስውሩንም የሚዳስስ ሁሉን አቀፍ ሕግ ነው። አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{አላህም በነፍሶቻችሁ ውስጥ ያለውን የሚያውቅ መኾኑን ዕወቁ፤ተጠንቀቁትም፤አላህም መሓሪ ታጋሽ መኾኑን ዕወቁ።}[አበቀራህ፡235]

ሰው ሠራሽ ሕጎች ግን በተጻራሪው በግልጹ ቁሳዊ ጉዳዮች ላይ ብቻ የሚያተኩሩ ሲሆን፣ለመንፈሳዊው ጎን ወይም ለመጭው የወዲያኛው ሕይወት ጉዳዮች ምንም ቁብ አይሰጡም። የሰው ሠራሽ ሕጎች መቀጫዎችም በዚህች ዓለም ብቻ የተወሰነኑ ናቸው።