እስላምና ዕውቀት

እስላምና ዕውቀት

የደስተኝነት መንገድ በምንም ዓይነት በማይምነትና ኋላ ቀርነት ሸለቆ ውስጥ ሊያልፍ ስለማይችል፣የግድ የዕውቀትና የሥልጣኔን ጎዳና አቋርጦ ሚያልፍ መሆኑ ጥርጥር ለውም። እንደ እስላም ሃይማኖት የዕውቀትና የዐዋቂዎችን ደረጃ ከፍ ያደረገ፣ለዐዋቂዎችና ለምሁራን ክቡር አያያዝ የደነገገ፣የትምህርትና የዕውቀት ግብይትን ያበረታታ፤ አእምሮን ለመጠቀም፣ለማስተዋልና ለማስተንተን ጥሪ ያደረገ አንድም ሌላ ሃይማኖትም ሆነ ርእዮተ ዓለም የለም። ነቢዩ ሙሐመድ  ያስተማሩትና ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ በዓለም ማእዘናት የተሰራጨን ታላቅ ሥልጣኔ እንዳስገኘው የእስላም ሃይማኖት፣ለዕውቀት ታላቅ ትኩረት የሰጠ ሌላ እምነትም ሆነ አመለካከት ከቶም አልተገኘም። ስለዚህም ለእውቀትና ለመንፈሱ እንግዳ በሆነ አካባቢ ውስጥ የነቢዩ  መላክ፣እውነተኛው የዕውቀት አብዮት ተደርጎ የሚቆጠር ነው። እስላም የመጣው የዕውቀትን ጮራ ለማፈንጠቅና ምድረ ዓለሙን በመለኮታዊ መመሪያ ብርሃኑ ለማዳረስ ነው። አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{የማይምነትን ፍርድ ይፈልጋሉን? ለሚያረጋግጡም ሕዝቦች ከአላህ ይበልጥ ፍርዱ ያማረ ማን ነው?}[አል ማእዳህ፡50]

በዚህ ሃይማኖት ውስጥ ለማይምነት፣ለባዶ ግምትም ሆነ ለጥርጣሬ ቦታ የለም። ወደማያነበውና ወደማይጽፈው ነቢይ  በመጀመሪያ ከአላህ (ሱ.ወ.) የተላለፈው ቁርኣናዊ አንቀጽ የሚከተለው ነበር፦

{አንብብ፣በዚያ (ሁሉን) በፈጠረው ጌታህ ስም። ሰውን ከረጋ ደም በፈጠረው (ጌታህ ስም)። አንብብ፤ጌታህ በጣም ቸር ሲኾን፤ያ በብርዕ ያስተማረ፤ሰውን ያላወቀውን ሁሉ ያሳወቀ ሲኾን።}[አል ዐለቅ፡1-5]

ይህ የመጀመሪያው ርእሰ ጉዳይ ይህን ሃይማኖት ለመረዳት የመክፈቻ ቁልፍ ነው፤የዚችን ዱንያ ሕይወት ብቻ ሳይሆን የሰው ልጆች ሁሉ መመለሻ የሆነውን የወዲያኛውን የኣኽራ ሕይወት ለማወቅም የመክፈቻ ቁልፍ መሆኑ ግልጽ ነው።

ቁርኣን ለዓለም ጉዳዮች ትኩረት የሰጠው የሰጠው ገና መተላለፍ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ መሆኑን ማስተዋል ይቻላል። እንዲያውም ቅዱስ ቁርኣን በአንቀጾቹ ውስጥ እንደ ተረከው ሁሉ ገና የሰው ልጅ ፍጥረት ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ነው ማለት ይቻላል። አላህ (ሱ.ወ.) ኣደምን ፈጥሮ በምድር ላይ ተጠሪ ምትክ አድርጎታል፤መላእክት ይሰሰግዱለት ዘንድም አዟል፤አክብሮታል፤ደረጃውን ከፍ አድርጎ አልቆታልም። የዚህ ከበሬታና ልቅና ምክንያት ምን እንደሆነ ለኛና ለማእክቱም ግልጽ አድርጎ መንስኤው {ዕውቀት} መሆኑን አሳውቋል። ይህንኑ በማረጋገጥ አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{(ሙሐመድ ሆይ!) ጌታህ ለመላእክት ፦ እኔ በምድር ላይ ምትክን አድራጊ ነኝ፤ባለ ጊዜ፣(የኾነውን አስታውስ፤እነርሱም) እኛ ከማመስገን ጋር የምናጠራህ፣ላንተም የምንቀድስ ስንኾን በርሷ ውስጥ የሚያጠፋንና ደሞችንም የሚያፈስን ታደርጋለህን? አሉ፤(አላህ) እኔ የማታውቁትን ነገር ዐውቃለሁ አላቸው። አደምንም ስሞችን ሁሏንም አስተማረው፤ከዚያም በመላእክት ላይ (ተጠሪዎቹን) አቀረባቸው፤እውነተኞችም እንደ ኾናችሁ የነዚህን (ተጠሪዎች) ስሞች ንገሩኝ፣አላቸው። ጥራት ይገባህ፤ከአስተማርከን ነገር በስተቀር ለኛ ዕውቀት የለንም፤አንተ ዐዋቂው ጥበበኛው አንተ ብቻ ነህና (አሉ)። ፦ አደም ሆይ! ስሞቻቸውን ንገራቸው አለው፤ስሞቻቸውን በነገራቸውም ጊዜ፣እኔ የሰማያትንና የምድርን ሩቅ ምስጢር ዐውቃለሁ፤የምትገልጹትንና ያንንም ትደብቁት የነበራችሁትን ዐውቃለሁ አላልኳችሁምን? አላቸው።}[አል በቀራህ፡30-33]

ዕውቀት እስላም ውስጥ ያለውን አስፈላጊነትና የላቀ ደረጃ የተሰጠው መሆኑን ከሚያመለክቱ ነገሮች አንዱ፣ስለ ዕውቀት የተነገረው በፍጥረት ጅማሮ ላይ ብቻ አለመሆኑ ነው። አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{አንብብ}

ይህ አካሄድ በዘላለማዊው ሕያው መጽሐፍ ውስጥ፣በቀጥታም ሆነ ቀጥተኛ ባልሆነ ተዘዋዋሪ መንገድ ስለ ዕውቀት ሳያነሳ የሚያልፍ አንድም ሱራ (ምዕራፍ) የለም ማለት በሚያስችል ሁኔታ የጸና አካሄድ ነው። አላህ (ሱ.ወ.) ከሁሉም በላይ ታላቅ በሆነው የተውሒድ ትእይንት ላይ እንኳ ለዕውቀት ጥሪ አድርጎ ለግብይቱ ትእዛዝ አስተላልፏል። ይህን በተመለከተም አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{እነሆ ከአላህ ሌላ አምላክ አለመኖሩንም እወቅ፤ስለ ስሕተትህም፣ለምእመናንም ምሕረትን ለምን፤አላህም መዘዋወሪያችሁን፣መርጊያችሁንም ያውቃል።}[ሙሐመድ፡19]

የዕውቀትና የዐዋቂዎችን ብልጫና ደረጃ ማመልከት ብቻ ሳይሆን ዐዋቂዎችና ማይማን እኩል አለመሆናቸውንም አረጋግጧል፦

{እነዚያ የሚያውቁና እነዚያ የማያውቁ፣ይተካከላሉን? በላቸው የሚገነዘቡት ባለ አእምሮዎቹ ብቻ ናቸው።}[አል ዙመር፡9]

ዕውቀት የተሰጡ ሰዎች በወዲያኛው የኣኽራ ሕይወት ከሚያገኙት ታላቅ ምንዳ ባሻገር፣በዚህ ዓለም ላይም የላቀ ደረጃና ማእረግ ተሰጥቷቸዋል። አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{አላህ ከናንተ እነዚያን ያመኑትንና እነዚያንም ዕውቀትን የተሰጡትን በደረጃዎች ከፍ ያደርጋል፤አላህም በምትሠሩት ሁሉ ውስጠ ዐዋቂ ነው።}[አል ሙጃደለህ፡11]

ከዚህም ሌላ ቅዱስ ቁርኣን ውስጥ ከዕውቀት በስተቀር ጭማሬ እንዲጠየቅበት የተበረታታ ሌላ ምንም ነገር አልተጠቀሰም። አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{ጌታዬ ሆይ! ዕውቀትንም ጨምርልኝ በል።}[ጣሃ፡11]

ከዚህ ስንነሳም ነቢዩ  የሚከተለውን ማለታቸው የተጋነነ አልነበረም፦ {ዕውቀት ለመገብየት ሲል መንገድ የገባውን ሰው አላህ ወደ ጀነት የሚወስደውን መንገድ ገር ያደርግለታል። መላእክትም ለተማሪው ውዴታ ክንፎቻቸውን ይዘረጋሉ፤ለዕውቀት ፈላጊ ሰው ውሃ ውስጥ የሚገኙ ዓሳዎች እንኳ ሳይቀሩ በሰማይና በምድር ያሉት ሁሉ ምሕረት ይለምኑለታል። ዕውቀት ፈላጊው ተማሪ በአምልኮተ አላህ (ዕባዳ) ላይ በተሰማራው ሰው ላይ ያለው ብልጫ፣ጨረቃ በሌሎች ከዋክብት ላይ ያለው ብልጫ ዓይነት ነው። ዑለማእ (ሊቃውንት) የነቢያት ወራሾች ናቸው፤ነቢያት ዲናርም ሆነ ድርሀም አላወረሱም፣ያወረሱት ዕውቀትን (ዕልም) ብቻ ነው፤እሱን የያዘ ሰው የበዛ የድርሻ ዕድል ወስዷል።} [በሙስሊም የተዘገበ] ለዚህም ነው ከነቢዩ  መላክ በኋላ መስጊዶች የዕውቀት ምንጭና የሊቃውንት አምባ የሆኑት።

{ዕውቀት} (ዕልም) የሚለው ቃልና የተለያዩ እርባታዎቹ በአላህ (ሱ.ወ.) መጽሐፍ ውስጥ የተደጋገመበትን ጊዜ ስንቆጥር እጅግ አስገራሚና አስደናቂ የሆነ ውጤት እናገኛለን። ቃሉ 779 ጊዜ የተደጋገመ ሲሆን፣ይህም በአማካይ በያንዳንዱ የቁርኣን ሱራ ውስጥ ሰባት ጊዜ ያህል ማለት ነው! ይህ {ዐለመ} ከሚለው ባለ ሦስት ሆሄ ስርወ ቃሉ ብቻ ሲሆን፣የዕውቀትን ፍችና ትርጉም የያዙ ሌሎች በርካታ ቃላት ይገኛሉ። ለአብነት ያህል፦ እርግጠኝነት (የቂን)፣መመራት (አልሁዳ)፣አእምሮ (አልዐቅል)፣እሳቤ (ፍክር)፣አስተውሎ (አንነዘር)፣ጥበብ (አልሕክማ)፣ግንዛቤ (ፍቅህ)፣ብርሃን (ቡርሃን)፣ማስረጃ (ደሊል)፣አስረጅ (አልሑጅጃ)፣አንቀጽ (ኣየህ)፣ማረጋገጫ (አልበይነህ) እና ሌሎች በዕውቀት ትርጉም ስር የሚካተቱ ቃላት ይገኛሉ። የነቢዩን ሱንና በተመለከተ ከድግግሞሹ ብዛት ቁጥሩን ማወቅ አስቸጋሪ ይሆናል።

ቁርኣን የፊዚክስ፣የኬሚስትሪ፣የስነሕይወት ወይም የማቴማቲክስ መጽሐፍ ሳይሆን የሕይወት መመሪያ (የህዳያ) መጽሐፍ ነው። ይህም ሆኖ ግን በውስጡ ከተካተተው መካከል ዘመናዊ ሳይንስ ያረጋገጠውን የጸና እውነታ የሚጻረር አንድም ነገር ፈጽሞ የለበትም።

ይህ ሁሉ ኋላ ላይ በእስላማዊው መንግስት ላይ፣ በሁሉም የሳይንስና የዕውቀት ዘርፎች ሰፊ እንቅስቃሴ ያመጣ ጥልቅ አሻራ ነበረው። ያስገኘው ታላቅ ንቅናቄ በታሪክ ውስጥ አቻ ያልተገኘለት፣በሙስሊም ሊቃውንት አማካይነት ታላቅ ሳይንሳዊ ዕድገትና ስልጣኔን ያስመዘገበ፣ለመላው የሰው ዘር ባለውለታነቱን እንደያዘ የዘለቀ ድንቅ ሳይንሳዊ ቅርስ ለዓለም ያበረከተ ታላቅ ንቅናቄ ነበር። ማክስ ማይርሆፍ እንደሚለው ፦ (በአውሮፓ የታየው የኬሚስትሪ ዕድገት በቀጥታ የጃቢር ብን ሐያን ትሩፋት ነው ማለት ይቻላል። ለዚህ ትልቁ ማስረጃ እርሱ ያስገኛቸው ቴክኒካዊ የስያሜ ቃላት በተለያዩ የአውሮፓ ቋንቋዎች ውስጥ ዛሬም ድረስ በማገልገል ላይ የሚገኙ መሆናቸው ነው።)

አልዶ ሚይሊ በበኩሉ እንዲህ ይላል ፦ {ወደ ማቴማቲክስና ወደ ስነፈለክ ስንሸጋገር ደግሞ ከመጀመሪያው አንስቶ የመጨረሻውን ከፍተኛ ደረጃ የተቆናጠጡ ሊቃውንትን እናገኛለን። ከነዚህ ዕውቅ ሳይንቲስቶች መካከል አቡ ዐብደላህ ሙሐመድ ብን ሙሳ አልኸዋሪዝሚ1 በታላላቅ የማቴማቲክስ ሊቃውንቶች ሰንሰለት ውስጥ የመነሻው አንጸባራቂ ዘለበት ነው . . መጽሐፎቹ በአውሮፓ ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ እስከ አስራ ስድስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ድረስ ለማስተማሪያነት ሲያገለግሉ ቆይተዋል።}

ዘግሬድ ሆንካህ {አትተስሪፍ ልመን ዐጀዘ ዐን አትተእሊፍ}2 የተሰኘውን የዘህራዊ መጽሐፍ ቀዶ ጥገናን የሚመለከተውን ክፍል አስመልክታ እንዲህ ብላለች፦ {የዚህ መጽሐፍ ሦስተኛው ክፍል፣የአውሮፓን የቀዶ ጥገና ዕውቀት መሰረቶችን የጣለ፣ይህን የሕክምና ሳይንስ ቅርንጫፍ ወደ ላቀ ደረጃ ከፍ ያደረገ፣በዚህም ቀዶ ጥገናን በአናቶሚ ሳይንስ ላይ የተመረኮዘ ራሱን የቻለ መስክ እንዲሆን ያደረገ በመሆኑ፣አውሮፓ ውስጥ ወሳኝ ሚና ተጫውቷል።} ይህ የዘህራዊ መጽሐፍ ለአምስት ምእተ ዓመታት በአውሮፓ ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ በማስተማሪያነት ያገለገለ ከመሆኑም ባሻገር ለአውሮፓውያን የቀዶ ጥገና ሐኪሞች ዋቢና ማጣቀሻ ሆኖ የቆየ በመሆኑ በአውሮፓ ሕዳሴ ውስጥ ትልቅ ተጽእኖ ነበረው።

ሙስሊም ሊቃውንት ዛሬም ድረስ ለሰው ልጆች አበርክቶአቸውን ቀጥለዋል። አሕመድ ዙወይል3 {የሳይንስ ዘመን} በተባለ መጽሐፍ ውስጥ፦ {ሥራዬ ከቦታ አንጻር ቅንጣቶች በሚዋሐዱበትና በሚለያዩበት በአቶሞች እምብርት ላይ፣ከጊዜ አኳያ ደግሞ አንዲቱ ሰከንድ ግዙፍ ዘመን ወደምትሆንበት በሰከንድ ላይ ያረፈ ነው።} ብለዋል።

እናም ሙሐመድ  ይዘውት የመጡት ይህ ዕውቀት፣ቅን መመሪያና ብርሃን፣የሰው ልጆችን ከተበከለ አረንቋ አውጥቶ ለዘመናት በዕውቀት፣ በስልጣኔና በዕድገት ጎዳና ከፍ ያደረጋቸው መሆኑ በጣም ግልጽ ነው።

እስላም የሳይንሳዊ ሜቶዶሎጂን መንገድ ይዞ የመጣ ሲሆን፣ለምሳሌ ያህል እስላም ከጭፍን ተከታይነት ያስጠነቅቃል። አላህ (ሱ.ወ.) ጣዖታውያንን አስመልክቶ እንዲህ ይላል፦

{አይደለም፣አባቶቻችንን በርሱ ላይ ያገኘንበትን ነገር እንከተላለን ይላሉ፣አባቶቻቸው ምንም የማያውቁና (ወደ እውነት) የማይመሩም ቢኾኑ (ይከተሉዋቸዋለን?)}[አል በቀራህ፡170]

ከሳይንሳዊ ስልት ውጭ በሆነ መንገድ ግምትና ጥርጣሬ መከተልን አስመልክቶ አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{ጥርጣሬን እንጅ ሌላን አይከተሉም። እነርሱም የሚዋሹ እንጂ ሌላ አይደሉም።}[አል አንዓም፡116]

ዕውቀትን፣ሎጂክን፣አእምሮንና ምርምርን የሚጻረረውን ግላዊ ዝንባሌን አስመልክቶም አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{ብዙዎቹም ያለ ዕውቀት በዝንባሌዎቻቸው ያሳስታሉ፤}[አል አንዓም፡119]

ከፍትሕ የሚያርቀውን ጥላቻ አስመልክቶም አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{ሕዝቦችንም መጥላት፣ባለማስተካከል ላይ አይገፋፋችሁ፤አስተካክሉ፤እርሱ (ማስተካከል) ለአላህ ፍራቻ በጣም የቀረበ ነው። አላህንም ፍሩ። አላህ በምትሠሩት ሁሉ ውስጠ ዐዋቂ ነው።}[አል ማእዳህ፡8]

ሳይንሳዊ ነባራዊነትንና ተጨባጭነትን አስመልክቶም አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{ከነዚያ ይሁዳውያን ከኾኑት ሰዎች፣ንግግሮችን ከስፍራዎቹ የሚያጣምሙ አልሉ፤ሰማንም አመጥንም፣ . . ይላሉ}[አል ኒሳእ፡46]

ወሰን አላፊነትንና ክፍፍሎሽን አስመልክቶም አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{(የወቀሳ) መንገዱ፣በነዚያ ሰዎችን በሚበድሉት፣በምድርም ውስጥ ያለ ሕግ ወሰን በሚያልፉት ላይ ብቻ ነው፤}[አል ሹራ፡42]

ሳይንሳዊ ተአማኒነትንና በሰዎች መካከል ፍትሕ ማስፈንን አስመልክቶም አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{በሰዎችም መካከል በፈረዳችሁ ጊዜ፣በትክክል እንድትፈርዱ፣(ያዛችኋል)፤}[አል ኒሳእ፡58]

ፍትሕ አክባሪነትን፣ማስተካከልንና በማንኛውም ሁኔታ ውስጥ እውነትን ብቻ መመስከርን አስመልክቶም አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{እላንተ ያመናችሁ ሆይ! በትክክል (ፍትሕ) ቀዋሚዎች፣በነፍሶቻችሁ፣ . . ላይ ቢኾን እንኳ ለአላህ መስካሪዎች ኹኑ።}[አል ኒሳእ፡135]

ማስረጃን ማረጋገጫንና አስረጅን ማቅረብና መመርመር አስፈላጊ መሆኑን አስመልክቶም አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{እውነተኞች እንደ ኾናች፣አስረጃችሁን አምጡ በላቸው።}[አል ነምል፡64]

ከነዚህም ሌላ ለዕውቀትና ለስልጣኔው መንገድ ሳይንሳዊ ስልትን የሚያኖሩ ሌሎች ብዙ ነገሮች ይገኛሉ።