ቀጠሮ ከሽብርተኝነት ጋር . .

ቀጠሮ ከሽብርተኝነት ጋር . .

ቀጠሮ ከሽብርተኝነት ጋር . . (1)

ጆርጅ ከሕንድ ተመልሷል። ጉዞው በጣም አመርቂ ቢሆንም የተሟሟቀ፣በመረጃዎች፣በውይይቶችና
በጥያቄዎች
የተሞላ ነበር። ለሥራ ጉዳይ ሲላክ ይህ የመጀመሪያ ጉዞው አልነበረም። ሆኖም ግን ትልቅ ስኬት ያስመዘገበበት የመጀመሪያው ጉዞ ነው። ውሎችን በዚህ ብቃትና በዚህ ፍጥነት ማጠናቀቅ የቻለበት የመጀመሪያው የሥራ ጉብኝት ነበር . . ሕንድ በእርግጥ የድንቃድንቆች አገር ናት። የጉዞውን ዝርዝር ሁኔታዎች አይሮፕላኑ ውስጥ ሆኖ አስታወሳቸው። ከሃይማኖቶቿና አእምሮ ከማይቀበላቸው አፈተረታዊ እምነቶቿ ብዙውን ቢጠላም፣ሕንድና ሰዎቿን የመውደድ ስሜት አድሮበታል። ይህ ውዴታ ከጥያቄዎቹ ጥቂቱን ሕንድ ስለመለሰችለት ይሆን? ሕንዳዊ የዘር ግንድ ላላት ካትሪና ካለው ፍቅር የመነጨ ይሆን? ካትሪናን በተመለከተ ገና ያልጠገገ ቁስል ልቡ ውስጥ በመኖሩ ለዚህ ይሆናል የሚለውን ግምት ወዲያውኑ ተወው።
አይሮፕላኑ ለንደን ደረሰ። ሻንጣዎቹን ይዞ ወደ መውጫው ሳሎን ሲያመራ፣ካትሪና ከሁለቱ ልጆቻቸው ጋር እሱን ለመቀበል እየተጠባበቀች ነበር። ከፍተኛ ደስታ ተሰምቶት ወደ ቤት እስኪደርሱ ድረስ ከቤተሰቡ ጋር ሲስቅና ሲጫወት መንገዱን ዘለቀ . .

- አልነገርከንም እኮ . . የኔ ፍቅር ሕንድ እንዴት ነች ?

- እጅግ በጣም ድንቅ ናት፣አገሩም ሰውም ድንቅ ናቸው።

- ውብ መስላ ታይታህ ይሆናል።

- በእውነትም ውብ አገርና ውብ ሕዝብ ነው። በሕይወቴ ካደረኳቸው ጉዞዎች ሁሉ ግሩም ድንቅ የሆነ ጉዞ ነበር።

- በጣም ጥሩ፣እሽ ከዚህ ጉዞ የወደደከው ምኑን ነው ?

- ጉዞው በሁሉም ጎኑ በጣም ጥሩ ነበር። የሚገርመው ግን ከዚህ ጉዞ ውስጥ በተለይ የወደድኩት ነገር ምን እንደሆነ ለይቼ አላውቅም . . ምናልባት ሰዎቹ ጥሩዎችና የሚመቹ በመሆናቸው ምክንያት፣ወይም በኔና ባንቺ ፍቅር ምክንያት . . ምናልባት ደግሞ የኩባንያውን የውል ስምምነቶች በፍጥነትና በብቃት በማጠናቀቄ . . እኔ እንጃ . . ዋናው ነገር በጣም ነው የተደሰትኩበት።

ወደ ልጁ ወደ ማይክል ዞር አለና . .

- ታውቃለህ ? ሕንዳዊውን ማይክል ታስታውሰኛልህ፣ካንተ ጋር በስሙና በተክለ ሰውነቱ የሆነ ተመሳሳይነት አለው . . ፈገግ ብሎ ቀጠለ ፦ አንተ ውዴ ግን ከርሱ ይበልጥ ውብና በብዙ ከርሱ የተሻልክ ነህ . . ሳሊ አንቺ ደግሞ ቁንጅናሽ የኦርሜላን ቁንጅና እንዳስታውስ ያደርገኛል።

ወደ ቤት ሲደርሱ ጊዜው ሄዶ ነበር። አባታቸው የጉዞውን ዝርዝር ነገ ሊያወራላቸው ቃል ከገባላቸው በኋላ ሁለቱ ሕጻናት ለመተኛት ወደ ክፍላቸው ሄዱ። . . ጆርጅም ወደ መኝታ ክፍል ሲሄድ ካትሪና ተውባና አምራ እየጠበቀችው ነበር . .

- ሳሊን ትመስላለች ያልካት ኦርሜላ፣አሳሳቿ ቆንጆ ከረዳ ነች ?

- አዎ . . ልክ ነሽ።

- እንዴት አወቅሃት? ! የቶምና የካኽን ምክር ሰምተሃል ማለት ነው ?

- መጀመሪያ ልትነግሪኝ የሚገባው አንቺ ነሽ . . ከዚህ ቶም ከሚባለው ጋር መቼ ነው የተገናኛችሁት? !

- አልተገናኘሁትም . . ከሁለት ቀን በፊት በቤተክርስቲያን ስነ ሥርዓት ላይ ነው ያገኘሁት። ከኔ ጥያቄ ለምን ትሸሻለህ፣ ኦርሜላ ማን ናት ?

- ኦርሜላ ሆቴል ውስጥ በአጋጣሚ ያገኘኋት ልጅ ነች። በጣም ቆንጆ ነች። የስሟ ትርጉም ውብ ማራኪ ማለት ነው አለችኝ . . ግና ከቶም ጋር እስከ ስንት ሰዓት እንዳመሸሽ ንገሪኝ ።

- እስከ ሌሊቱ መጨረሻ አካባቢ ነው ያመሸነው። ይሁንና ኦርሜላን ያገኘሃት በአጋጣሚና በእግረ መንገድ ነው ብዬ እንዳምንልህ ትፈልጋለህ ? በአጋጣሚ ተገናኝታችሁ ስሟን ከነትርጉሙ አልረሳህም ማለት ነው ?

- አዎ በአጋጣሚ ነው፣ይሁንና አንቺስ የቤተክርስቲያኑ ስነ ሥርዓት እስከ ጧቱ አንድ ሰዓት የዘለቀ ነበር ብዬ እንዳምንሽ ትጠብቂያለሽ ?

- እስከ ንጋት ማምሸታችንን ማን ነገረህ? ! ስለምትጠረጥረኝ ትከታተለኝ ነበር ? ከዚህ ይልቅ ከቆነጃጅት ጋር ያለህን ግንኙነት መከታተል የነበረብኝ እኔ አይደለሁም ? !

- መልካም ፈቃድሽ ሆኖ አሁን መተኛት እፈልጋለሁ . .

ጆርጅ ጀርባውን ለካትሪና ሰጥቶ ተኛ። የተለዋወጧቸው ቃላትና ውይይታቸው ለፍንዳታ ምንም ያህል ያልቀራቸው ስለነበር በእንቅልፍ ለመሸሸግ የመረጠ ይመስላል . . ካትሪናም ይህንኑ በማድረግ ጀርባዋን ሰጥታው ተኛች . . ያንቀላፋ የመሰለው ጆርጅ ከራሱ ጋር መነጋገር ጀመረ . . በአነጋገሬ ጠንከር ብዬባቸው ይሆን?
እውነት
በቤተክርስቲያን
ስነ
ሥርዓት
ላይ
ነው የነበረችው? ክብሯን ነክቼ ይሆን? አስከተለና፦
ምናልባት አድርጌ ይሆናል፣ግን የሚገባት መቀጣጫ ነው፣በኔ ውስጥ እንደዘራችው አእምሮዋ ውስጥ ጥርጣሬ ዘርቼ ተበቅያታለሁ፣ብሎ በማሰላሰል ላይ እያለ እንቅልፍ ይዞት ጨለጠ።
ጧት ከእንቅልፉ ሲነቃ ካትሪና የሚወደውን ዓይነት ቁርስ አዘጋጅታለት ነበር . . የሌሊቱን ቁጣ የተዘናጋ በመምሰል ፈገግ አለላት . .

- የኔ ፍቅር በል ና።

- ፍቅሬ አመሰግናለሁ። የኔ ፍቅር ስጦታውን አልሰጠሁሽም፣ . . ለአፍታ ጠብቂኝ የጠየቅሽውን መስቀል ልስጥሽ . .

- ውዴ በጣም አመሰግናለሁ . . ታድዬ በጣም ያምራል ! ትረሰዋለህ ብዬ ነበር!

- የፍቅሬን ጥያቄ እንዴት አድርጌ እረሳለሁ፣ ከሕንድ ማምጣት የፈለኩት ዋነኛው ነገርም እሱ ነበር።

- ይህን መስቀል ይዘህ ስትመጣ የመንፈስ ቅዱስ ጥበቃ ካንተ ጋር ነበር። በነገራችን ላይ የጥያቄዎችህ መልስ ጉዳይ እንዴት ሆነ?

- ከተለያዩ ሃይማኖቶች፣እምነቶችና፣አመለካከቶችና ፈለጎች ጋር የተዋወቅኩበት ግሩም ድንቅ ጉዞ ነበር።

- የቅዱስ ጄምስን ቤተክርስቲያን ጎብኝተሃል? ኪነ ሕንጻው በጣም ማራኪ ነው!

- አዎ ጎብኝቻለሁ . . በእርግጥ በጣም ድንቅ ነው። በነገርሽ ላይ ክርስቲያኖች ሕንድ ውስጥ በቁጥር ብዙ ይመስሉኝ ነበር። ቁጥራቸው በጣም ውስን መሆኑን ሳውቅ በጣም ገረመኝ።

- አዎ . . ልክ ነህ። አሳዛኝ እውነት ነው፣ሰዎች ወደ አሸባሪዎቹ ለመለወጥ እንጂ የሕንዱ ሃይማኖታቸውን በቀላሉ አይቀይሩም። ቤተክርስቲያን ይህን ሁኔታ ለመለወጥ እስትራቴጂዋን ለመቀየር እያሰበች ነው።

- አሸባሪዎቹ ! ! ሙስሊሞችን ማለትሽ ነው?

- አዎ፣ጨካኝ አረመኔዎቹን ማለቴ ነው።

- ከኩባንያችን የውል ስምምነቶች ፊርማ መካከል አንዱ ከሙስሊሞች ጋር ከመሆኑ፣ከመልካም አያያዛቸው፣ ከተጋግባቢነታቸው፣ከሐቀኝነታቸውና የመርህ ተገዥ ከመሆናቸው ጋር፣ ስሙ ከሪሙሏህ የሚባል አንደኛቸውን ልቤ ፈጽሞ ሊቀበለው አልቻለም፣ለምን እንደሆነ ግን አላውቅም !

- በጎ ነገር አፍቃሪ የሆነው ንጹህ ልብህ ግድያና ውድመት አፍቃሪ የሆነ ልብን መውደድ አይችልም።

- ሊሆን ይችላል። ግን ሕንድ ውስጥ ካጋጠሙኝ ሰዎች ሁሉ ሙስሊሞቹ፣ገሮች ከሁሉም ይበልጥ የሚመቹና ለመርሆዎቻቸው ተገዥዎች ናቸው።

- እንዴት! ከክርስቲያኖች ጋር አልተገናኘህም?

- ተገናኝቻለሁ። ሃይማኖተኛውን ማይክልን አግኝቼዋለሁ። ስነ ምግባሩ መጥፎ ቢሆንም ልቤ ለምን እንደ ወደደው ግን አላውቅም!

- እኩይ ስነ ምግባር ያለው ሃይማኖተኛ ? !

- አዎ . . በጣም በጣም ሃይማኖተኛ ብቻ ሳይሆን አክራሪም ነው። በዚህ ላይ ግን ስነ ምግባሩ የተዛነፈ ነው። ካኽ የውል ስምምነቶቹን እንደሚፈለገው ለማጭበርበር የሕንድ ቆነጃጅት ኮረዶችን ለኔ እንዲያዘጋጅ ጠይቆት እሺ ብሎ ትእዛዙን ፈጽሟል።

- ወየው ጉድ !! ሃይማኖተኛ ሆኖ ኮረዶችን ለዝሙት የሚያቀርብ !

- አዎ . . በጣም የሚገርመው ደግሞ እምቢ በማለቴ በጣም መደነቁ ነው።

- የሌሎችን መብት እየሰረቀ ለዝሙት ጥሪ ያደርጋል! የኔ ፍቅር እንዲህ ያለው ክርስትናን አይወክልም። ክርስትናንና ክርስቲያኖችን ለያይተን ማየት ይኖርብናል።

- ልክ ነሽ . . ያለ ምንም ጥርጥር ይህ በሁለት ጎኑ ትክክል ነው። በአንድ ጎኑ - እንዳልሽው ሁሉ - አመለካከቶችንና ሃይማኖቶችን ከአራማጆቻቸው ለያይተን መመልከት ይኖርብናል፤ተከታዮቹ ለፈጸሙት ስህተት ሃይማኖቱን ተጠያቂ ማድረግ የለብንም። በሌላ በኩል ግን የሰዎች ድርጊት የሚመነጨው ከአመለካከታቸውና ከሃይማኖታቸው አይደለም ወይ ? የሆነ ነገር ከመጠን አልፎ ጎልቶ ሲታይባቸው ከስር መሰረቱ በሃይማኖታቸውና በአመለካከታቸው ውስጥ ችግር መኖሩን አያመለክትም ወይ ? !

- ነው፣ግን የወዳጅህ የማይክል ሁኔታ የተለየ ነው።

- ምናልባት ይሆናል . . የሁሉም እምነት ተከታዮችም ይህንኑ ይላሉ።

- የሐኪሙ ጥያቄዎች ምላሽ ጉዳይስ እንዴት ሆነ?

- መልሶቹ ለኔ ግልጽ የሆኑልኝ ይመስለኛል።

- ታዲያ . . ከችግሩ ተገላግለናላ ?

- የተገላገልነው የሐኪሙን ጥያቄዎች ምላሽ በሚመለከተው ብቻ ነው። መልሱን የምናገኘው መለኮታዊ ሃይማኖቶችን ካስተላለፈው እግዚአብሔር ብቻ ነው። ለታላላቆቹ ጥያቄዎች ምላሽ ለማግኘት መንገዱን የያዝን ይመስለኛል፣ ከዚያም ለደስተኝነት እንበቃለን ማለት ነው።

- የኔ ፍቅር ቀጥል ትደርስበታለህ . . የሐኪሙን ጥያቄዎች ምላሽ ትክክለኛነት እንዴት አወቅህ . . ማለቴ መልሱ መምጣት ያለባት ከመለኮታዊ ሃይማኖት መሆኑን እንዴት እርግጠኛ ሆንክ?

- መልሱ ብዙ ማሰብ የሚያስፈልገው አልነበረም፤መለኮታዊ ያልሆኑ አያሌ የሕንድ ሃይማኖቶችን ያወቅኋቸው ሲሆን ለመላው የሰው ዘር የሚበጁ መሆን ቀርቶ ለራሳቸው ተከታዮች እንኳ የሚበጁ ከመሆን በጣም የራቁ ናቸው። ከሰው ልጅ ተፈጥሮ፣ከፍትሕና ከጥበብ ጋር ተጻራሪ በሆነ መንገድ የሚጓዙ ሃይማኖቶች ሆነው ነው ያገኘኋቸው። እኛ በምዕራቡ ዓለማችን ለነዚህ ሃይማኖቶች ያለን ግንዛቤ በጣም ውስንና ከእውነታው ጋር የማይጣጣም መሆኑንም ለማስተዋል ችያለሁ። ለማንኛውም ይኸ የኔ አስተያየት ነው፣የቶም አስተያየት ምን እንደሆነ ስንገናኝ ነው የማውቀው።

- ቀጠሯችሁ መቼ ነው?

- ከአራት ቀናት በኋላ ነው። . . የሥራ ሰዓት ረፈደብኝ፣የኔ ፍቅር አንቺንም አስረፈድኩብሽ።

- ዛሬ እንደማልመጣ ነግሬ አስፈቅጄያለሁ፣አንተም ዛሬ ወደ ሥራ የማትሄድ መስሎኝ ነበር።

- የለም . . ለጥቂት ሰዓታትም ቢሆን ሄጄ የማስረክበው ሥራ አለኝ . . የኔ ፍቅር ፍቀጂልኝና ልሂድ ስመለስ እንገናኛለን።

ቀጠሮ ከሽብርተኝነት ጋር . . (2)

ጆርጁ ወደ ሥራ ሄደ . . መጀመሪያ ቀጥታ ያመራው ገና ሲያየው ተነስቶ ሞቅ ያለ አቀባበል ወደ አደረገለት ወደ አለቃው ካኽ ቢሮ ነበር . .

- በዚህ ጉዞ ያስመዘገብካቸው ስኬቶች እንዴት ሊሆኑ ቻሉ? ! በጣም የምትገርም ሰው ነህ !

- በእርግጥ ስምምነቶቹ እኛ በምንፈልገው መንገድ ነው የተፈጸሙት። ግን እንዴት አወቅክ? !

- ማይክል የምሥጋና ደብዳቤ ልኮልን ስምምነቱ መፈጸሙን ነግሮናል . . ማይክል ሃይማኖተኛም ቢሆን ጥሩ የሥራ ሰው፣የሰውን ፍላጎትና ስሜቱን የሚረዳና ምላሽ የሚሰጥ ሰው ነው . . (ፈገግ ብሎ) ሙጢዑረሕማን ግን ለምንም የማይመች ደረቅ እንጨት ነው፣ከርሱ ጋር ያለውንስ እንዴት አደረግህ?

- ተስማምተን ሁሉንም ውሎች ተፈራርመናል፤ይኸው ሕንድ በሚገኘው የእንግሊዝ ኤምባሲ ማህተም ተረጋግጦ ለንደን የሚገኘው የሕንድ ኤምባሲ ማረጋገጫ ብቻ ይቀረዋል።

- ዓይኔን አላምንም? ከርሱ ጋር እንዴት መስማማት ቻልክ? !

- ከርሱ ጋር የተደረገው ስመምነት ምናልባት በዓለም ላይ በታም ፈጣኑ ስምምነት ሳይሆን አይቀርም። ቅንጅት የሚጎድለው ቢሆንም ግትር ያልሆነ ንቁና ሁሉንም ተጠቃሚ በሚያደርግ መንገድ የሚያስብ ገር ሰው ነው። የውል ስምምነቱን ወንድሙ ከሪሙሏህ እንዲፈጽመው ነበር ያስተላለፈለት። ወንድምየው ብዙ ደስ የማያሰኝ ቢሆንም ሰብሰብ ያለ የተግባር ሰው ነው።

- ስምምነቶቹ ከፊትለፊቴ የተቀመጡ ቢሆንም የምትናገረውን ማመን ተስኖኛል። ለኔ መጢዑረሕማንም ሆነ ከሪሙሏህ አይመቹኝም። ሕይወትን እንዴት እንደሚመለከቷት አላቅም፣ልክ ውጊያ ሜዳ ያሉ ነው የሚመስለው። ምናልባትም ሙስሊሞች ስለሆኑ በእምነታቸው ባሕሪ ምክንያት ሊሆን ይችላል . . ለመሆኑ የኔን ቆነጃጅት ጉዳይ እንዴት አደረግህ? አንተ ጆርጅ ከኔ ሴቶች ጋር መተኛት ትንሽ እንኳ አላፈርክም ማለት ነው?

- ካንተ ሴቶች ጋርም ሆነ ከሌሎች ጋር አልተኛሁም።

- ታዲያ . . ማይክል ወራዳ ነበር በተለምዶ ለኔ እንደሚያደርግልኝ ላንተ አላደረገም፣ በደንብ አላስተናገደህም በለኛ?

- በተቃራኒው ለኔ በጣም ጥሩ ነበር፣ቆነጃጅቱን እምቢ ብዬ የመለስኳቸው እኔ ነኝ።

- አእምሮ ያለው ሰው እንዲህ ያለውን የማይገኝ አጋጣሚ ያበለሻል ብዬ አላምንም። የኩባንያው የቦርድ ስብሰባ ባይኖር ኖሮ ከቆነጃጅቱ ጋር ለመዝናናት እኔ ራሴ ብጓዝ ደስ ይለኝ ነበር፣ እንዴት ያሉ ማራኪዎች መሰሉህ። አንተ ሕይወትን መቼ እንደምትኖራትና ድንቅ አጋጣሚዎችን መቼ እንደምትጠቀም አላውቅም። ሁሉንም ውሎች ተፈራርመህ ጨርስህ ባትመጣ ኖሮ ጭራሽም መጓዝህን እጠራጠር ነበር ! ያለ ሕንዳውያት ቆነጃጅት ኮረዶች ወደ ሕንድ መሄድ ምን ትርጉም አለው? እውነቱን ለመናገር ማይክል ከሚያቀርባቸው እንቡጦች የሚበልጥ ምን ውበት አለና ነው የተውካቸው? !

- አዎ አለ፣ሆቴሉ ውስጥ ራሷን ያቀረበችልኝ ኦርሜላ በብዙ እጅ የበለጠ ውብ ቆንጆ ነች፤ግና እምቢ ብዬ ነው የተውኳት።

- እኔ እንጃ፣ለመሆኑ ሕይወትንና ዓለማዊ ደስታን እንዴት ነው የምትመለከተው? !

- ዕድሜያችንና ጊዜያችንን ከራሳችን ሸሽተን በሥጋዊ ፍላጎታችንና በጊዜያዊ ደስታ ውስጥ የምንደበቅ ከሆነ፣የሕይወት ትርጉም ምንድነው? የመኖር ዓለማ ምንድነው? የተፈጠርነውስ ለምን ዓለማ ነው?

- አሃ፣ለሐኪምህ ልታቀርበው የሚገባ ድንቅ ሌክቸር ነው። አሁን ይህን እንተወውና ከነዚህ ስምምነቶች በኋላ ቀጣዩን ሥራ የሚመለከቱ ሂደቶችን መጀመር ይጠበቅብናል። ኩባንያው ለስኬታማ ክንውንህ ያለውን አክብሮትና አድናቆትቱን ከምስጋና ጋር ያቀርባል።

- ሂደቶቹን እጀምራለሁ፣በመጪዎቹ ጥቂት ቀናት ውስጥ አጠናቅቃቸዋለሁ። እኔም ኩባንያውን ማመስገን እፈልጋለሁ፣ ጉዞዬ በጣም አስደሳች ነበር።

- ለአንተ አስደሳችነቱ ምኑ ላይ እንደሆነ ባይገባኝም፣ከፈለግህ ካሁኑ የበለጠ አስደሳች ጉዞ እየጠበቀህ መሆኑን ስነገርህ በጣም ደስ እያለኝ ነው።

- ሌላ ጉዞ ? !

- አዎ፣ወደ ቅድስት አገር የሚደረግ ጉዞ።

- የትኛዋ ቅድስት አገር?

- እኔ ቅድስናዋን ባልቀበልም የሦስቱ መለኮታዊ ሃይማኖቶች ተከታዮች ግን ‹‹ቁድስ›› ወይም ‹‹ኢየሩሳሌም›› ወይም ‹‹ቴልአቪቭ›› ቅዱስ አገር መሆኗን ያምናሉ። ቤተሰቦቼ ሁሉ እዚያ ይኖረራሉ፣ወደዚያ እንድመጣ ሁሌ ይወተውቱኛል። እኔ ግን ከሚገባው በላይ ሃይማኖት አጥባቂዎች እነደሆኑ ነው የሚሰማኝ ! እናቴ ይሁዳዊት ናት፣ለኔ ግን ሁሉም ሃይማኖቶች አሳማኝ አይደሉም። የኦርሻሌም ሴኩሪቴ ኩባንያ የላክንላቸውን የቴክኒካል ውል ሀሳብ ተቀብለዋል፣ከፈለግህ አንተ ትሄዳለህ አለዚያ እኔ እሄዳለሁ። ውሎችን ለማሳካት ከኔ የተሻልክ ስለሆነ አንተ ብትሄድ እመርጣለሁ . . የሁለት ሳምንት ጊዜ አለህና አስብበት።

- ጥሩ፣አስቤበት እነግረሃለሁ።

ቀጠሮ ከሽብርተኝነት ጋር . . (3)

ጆርጅ ከሥራ በኋላ በቀጥታ ወደ ቤቱ ተመለሰ . . መንገዱ ከወትሮ በተለየ ሁኔታ የትራፊክ መጨናነቅ ነበረበት። በተለምዶ ከአርባ አምስት ደቂቃ በላይ ያልነበረው ከሥራ ቦታ እስከ መኖሪያ ቤቱ ያለው መንገድ ዛሬ ሁለት ሰዓት ተኩል ወስዶበታል። . . ወደ ቤት የደረሰው ድካም እየተጫጫነው ነበር። ካትሪና ተጣድፋ ተቀበለችው . .

- እግዚአብሔር የተመሰገነ ይሁን፣እንኳን ደህና መጣህ የኔ ፍቅር፣በጣም ተጨንቄ ነበር።

- ዛሬ ምን እንደተፈጠረ እንጃ በትራፊክ መጨናነቅ ምክንያት መንገዱ ሁለት ሰዓት ተኩል ነው የወሰደብኝ !

- ዛሬ የምድር ውስጥ ባቡር መንገድ ሙሉ በሙሉ ተቋርጧል።

- ለምን?

- በሜትሮ በደረሰው የሽብር ጥቃት፣ጌታ ይመስገን እንኳ በማእከላዊው ቦታ አልሆነ እንጂ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በሞቱ ነበር።

- የተጎዳ ሰው አለ?

- ከሁለት ቀናት በፊት የተጋቡ ባልና ሚስት የተገደሉ ሲሆን ሁለት ወንዶች፣አንዲት ሴትና አንድ ሕጻን በፍንዳታው ተጎድተዋል። እነዚህ አሸባሪ ሙስሊሞች ምን ዓይነት ጨካኝ ልብ ይሆን ያላቸው !

ዜናውን በቲቪ ለመከታተል ጆርጅ ሪሞቱን ወሰደ . .

- ሙስሊሞች መሆናቸውን እንዴት አወቅሽ? እሱን ተይና ዜናውን በቲቪ እንከታተል።

- ይህን ጥቃት ለመፈጸም ከነርሱ በስተቀር በጭካኔ የተሞላ ልብ ያለው ሌላ ሰው አይኖርም።

ጆርጅ የሚዲያ ሽፋኑን በቲቪ ተከታተለ፣ፍንዳታው የደረሰው ከአራት ሰዓት በፊት ሲሆን ሁሉም ተንታኞች ጥቃቱን የፈጸሙት ሙስሊም አሸባሪዎች ናቸው በሚለው ላይ ሙለ በሙሉ ተስማምተዋል። ይሁን እንጂ እስካሁን ድረስ በይፋ የተሰጠ የውንጀላ መግለጫ ለም። የእንግሊዝ የፖሊስና የጸጥታ ኀይሎች በከፍተኛ የተጠንቀቅ ሁኔታ ላይ ናቸው። ሁሉም ሰው ወደ ቤት መመለስ ይፈልጋል፣መንገዶች ግን ሙሉ ለሙሉ ዝግ ናቸው።

- ሀሳብሽ ልክ ሳይሆን አይቀርም፣እስካሁን ድረስ በይፋ የተሰጠ መግለጫ ባይኖርም፣ጥቃቱን ያደረሱት አሸባሪ ሙስሊሞች ናቸው።

- እመነኝ ርህራሄ ያልተፈጠረባቸው ልበ ደረቆች ከነዚህ አሸባሪዎች በስተቀር ማንም የለም፣ይህን ማድረግ ሃይማኖታዊ አምልኮ አድርገው ይቆጥሩታል።

- ለሃይማኖታዊ አምልኮና ለጽድቅ ብለው ሰዎችን ይገድላሉ? !

- አዎ . . ‹‹ጅሃድ›› ብለው የሚጠሩት ነገር አላቸው፣በርሱ አማካይነት ሰዎችን መግደልና ማሰቃየትን የአምልኮ ሥራ አድርገው ይቆጥራሉ። በዚህ የሽብር ሃይማኖትና በክርስትና ገርነትና ፍቀር መካከል ያለውን ልዩነት ተመልከት። ኢየሱስ ለሰው ልጆች ብሎ ራሱን ሰዋ፣ተከታዮቹም እንደዚሁ። የሙሐመድ ተከታዮች ግን ከመግደል በስተቀር ሌላ አያውቁም።።

- የነኚህ ሙስሊሞች ነገር የሚገርም ነው። ምናልባት ከሪሙሏህ ፈጽሞ የማይመቸኝ በዚህ ምክንያት ሳይሆን አይቀርም።

- ሰይገድሉህ ወይም ሳያፈነዱህ ከነሱ ዘንድ በሰላም በመውጣትህ እዝግዚአብሔር የተመሰገነ ይሁን።

- ወየው ጉድ፣ይታይሽ ሙጢዑረሕማን ፈንጂ ጠምዶብኝ ሲያፈነዳኝ . . እውነቱን ለመናገር ግን ገርና ምቹ ሰው ነበር፣ በተጨማሪም የሕንድ ዑድ ሽቶ በስጦታ አበርክቶልኛል።

- ችግር የሌለው መሆኑን ሳታረጋግጥ አትጠቀመው፣የተመረዘ ሊሆን ይችላል።

- እኔ የዑድ ሽቶ አልወድም፣ለአስተናጋጁ ለአደም ነው ያመጣሁት። ዝንእንዳመጣለት ጠይቆኝ ነበር፣ወዳጄ አደምን የሚጎዳ ነገር እንደሌለበት ግን ማረጋገጥ አለብኝ።

- ለወዳጅህ ከማበርከትህ በፊት ነጻ መሆኑን አረጋግጥ፣እነዚህ አሸባሪዎች ፈጽሞ የሚታመኑ አይደሉም።

- አስታወስሽኝ . . ከተመለስኩ ወዲህ አደምን አላኘሁትም፣ ከሕንድ ስመለስ እጎበኘሃለሁ ብየው ነበር።

- ለመሆኑ እርሱ ፕሮቴስታንት ነው ወይስ ካቶሊክ?

- ባይገርምሽ አላውቅም ! አልጠየኩትም፣እሱም አልነገረኝም። ነገ ላገኘው እሞክራለሁ፣ምናልባት እጠይቀው ይሆናል . . ዛሬ እናመሻለን ወይስ በቀጥታ ወደ መኝታ ነው?

- ከተወዳጅ ፍቅሬ ጋር ማመሸቱን እመርጣለሁ።

በነጋታው ጆርጅ ወደ ሥራ ላለመሄድና ሥራውን እቤት ሆኖ በስልክና በኢንተርኔት አማካይነት ለመከታተል ወሰነ። የውስጥ ለውስጥ ባቡር መንገዱ በከፊል ብቻ እንጂ ሥራ ስላልጀመረ የትራፊክ መጨናነቁ አሁንም አልቀነሰም። ለአደም ደጋግሞ ቢደውልም ስልኩ ዝግ ነው። የፍንዳታውና የአሸባሪዎቹ ነገር ከምን እንደደረሰ ለማወቅ ቲቪ ከፈተ . . መንግስት የተቀረውን የምደር ውስጥ ባቡር መንገድ ከፍቷል፣በለንደን የሚኖሩ የሕንድ የፓኪሰታንና የዐረብ ዝርያ ያላቸው በርካታ ሙስሊሞችም እንግሊዛውያን ሙስሊሞችንም ጨምሮ በቁጥጥር ሥር ውለዋል። ከሽብር ጥቃቱ በስተጀርባ ሙስሊሞች መኖራቸውን የሚገልጹ ትንተናዎች አሁንም እየጎረፉ ነው። ከጥቃቱ ሰለባዎች አንዱ ሕንዳዊ ሙስሊም ሲሆን በባቡር ጣቢያው የመገኘቱ ሁኔታ ጥርጣሬ አሳድሯል። በዚያው ቦታ ላይ የአንድ ሌላ ፓኪስታናዊ መታወቂያ ካርድ የተገኘ ሲሆን ግለሰቡን ለማግኘት ፍለጋው ቀጥሏል . . በተጨማሪም ዜጎችና ነዋሪዎች ሕዝብ በሚሰባሰብባቸው ቦታዎች ላይ ሻንጣ መሰል ነገር ትቶ የሚሄድ ሰው ካጋጠማቸው በተለይም ሙስሊም ከሆነ አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲያደርጉና ለሚመለከተው ክፍል ወዲያውኑ እንዲያስታውቁ መንግስት በጥብቅ አሳስቧል . .
ጆርጅ ዜናውን ተከታትሎ እንዳበቃ ለባብሶ አደምን ለማግኘት ወደ ካፌው አመራ . . ግን አላገኘውም። ሌላውን አስተናገጅ ሲጠይቅ ለአምስት ቀናት ፈቃድ መውሰዱን ነገረው።

- ከመቼ ጀምሮ ነው ፈቃድ የወሰደው? ለምን እንደወሰደ ታውቃለህ?

- ለዩኒቨርሲቲው የሚያቀርበውን የመመረቂያ ጽሑፍ ለማዘጋጀት ጊዜ ለማግኘት ብሎ ነው፤ከሦስት ቀናት በፊት ነው የወሰደው።

ጆርጅ ወደ አደም ቤት ሄዶ ሲያንኳንኳ የከፈተለት ሰው አልነበረም፣መጥቶ እንዳላገኘው የሚገልጽ ማስታወሻ በሩ ላይ ትቶለት ወደ ቤቱ ተመለሰ . . ሲመጣ ካትሪናን ዜና እየተከታተለች አገኛት . .

- የሜትሮውን ፍንዳታ የተመለከተ አዲስ ነገር አለ?

- ምንም አዲስ ነገር የለም። የአሸባሪው ፓኪስታናዊ ፍለጋ አሁንም እንደቀጠለ ነው። ዋነኛው ሰጋት ግን ለንደን ሌላ አዲስ ፍንዳታ እየጠበቃት እንዳይሆን ነው።

- ዛሬ ባገኙትና ሰው ከስጋት ቢገላገል እንዴት ጥሩ ነበር። እነዚህን አሸባሪዎች ምን ዓይነት ጨካኝ ልብ ፈጥሮባቸው ይሆን?!

- ዛሬ ወደ ሥራ ሄደሃል?

- አልሄድኩም፣ሜትሮው ጧት በከፊል ዝግ ነበር። ወደ ወዳጄ አደም ዘንድ ነበር የሄድኩት፣ግና ለመመረቂያ ጽሑፉ ዝግጅት ዕረፍት ስለወሰደ አላገኘሁትም።

- ነገስ ወደ ሥራ ትሄዳለህ?

- አዎ . . አንዳንድ ሥራዎች ስላሉኝ አለጥርጥር እሄዳለሁ፣ ከዚያ ለሐኪም ቶም ቀጠሮ እወጣለሁ።

- አሁንማ ለሐኪሙ ጥያቄዎች ግልጽ ምላሾች ይዘህለት የለም?

- አዎ፣እንደ እድል ሆኖ በመጀመሪያውና በአሁኑም ዙር ወደ ምላሾቹ የተመራሁ ሆኖ ይሰማኛል።

- አንተ ሁሌም ስኬታማ ነህ፣መንፈስ ቅዱስ ካንተ ጋር ነው፣ያግዘሃል።

- አሁንም አዳዲስ ጥያቄዎች እንዳሉት ነው የማውቀው።

- ታውቀዋለህ? !

- አዎ፣አማራጭ እየጠበበኝ የመጣ መሰለኝ። በአጋጣሚ ይሁን ወይም በቶም የተቀነባበረ አሊያም አንቺ እንደምትይው በመንፈስ ቅዱስ ረድኤት ይሁን ግን አላውቅም።

- እንዴት ማለት?

- መጀመሪያ ላይ ምርጫው መልሶቹን ከየት ነው የምናመጣቸው የሚል ነበር። መምጣት የሚችሉት ከፈጣሪ በኩል ብቻ ስለመሆናቸው ለኔ እጅግ በጣም ግልጽ ነበር። የኤቲዝም አመለካከት ወዴትም የማያደርስ የሽሽት አመለካከት መሆኑን አውቅ ነበር። ሥርዓትን ከሥርዓተ አልበኝነት መፍጠር እንዴት ይቻላል? ከፈጠረን በስተቀር ሌላው ለምን እንደተፈጠርን እንዴት ማወቅ ይቻለዋል? ኤቲዝም ምሁራን ነን ብለው ራሳቸውን የሚገምቱ አንዳንድ ሰዎች የሚከተሉት ቢሆንም እንኳ ሰብአዊ አእምሮን፣ ተፈጥሮንና ሃይማኖትን የሚጻረር አዝማሚያ ነው። ከዚያ የሚቀጥለው ጥያቄ ደግሞ ፈጣሪው ማነው? የሚለው ነበር። ሃይማኖቶችና ሰዎች ስለ ፈጣሪ ያላቸውን አመለካከት ለመረዳት፣ ምድራዊ ሰው ሰራሽ ሃይማኖቶችና መለኮታዊ ሃይማኖቶች ብለን በሁለት ጎራዎች ከፈልን። ምድራዊ ሰው ሰራሽ ሃይማኖቶች፣ለሰው ልጅ ጥያቄዎች ምላሽ ማቅረብ ቀርቶ ከሰው ተፈጥሮና ከተከታዮቻቸው ተፈጥሮ ጋር መጣጣም የማይችሉ መሆናቸው በተለይም ከሕንድ ጉዞዬ በኋላ ለኔ በጣም ግልጽ ነበር፡፡ ብቃት ማጣታቸው ብቻ ሳይሆን ለመኗኗር የማይመቹ አጓጉል እምነቶች ናቸው። በመሆኑም አሁን ጥያቄው መሆን ያለበት ከሳይንሳዊና ሰብአዊ እውነታዎች ጋር የሚጣጣም ሎጂካዊ ምላሽ የሚሰጠው ከመለኮታዊ ሃይማኖቶች ውስጥ የትኛው ሃይማኖት ነው? የሚለው ነው።

- ክርስትና የሰው ልጅ መድህን ነው ብየህ የለም?

- ይሁድናስ? እስላምስ?

- የኔ ፍቅር አንድ ቀን በምድር ውስጥ ባቡር መንገድ ላይ የፈንጂ ቀበቶ የታጠቀ ሙስሊም ሆነህ አየሃለሁ ማለት ነው?

- ምናልባት ! ማን ያውቃል፣ወይም ሀብት ከማግበስበስና ከወሲብ በስተቀር ምንም ሀሳብ እንደሌለው ካኽ ያለ ይሁዲ እሆን ይሃናል።

ቀጠሮ ከሽብርተኝነት ጋር . . (4)

በሥራ ላይ እያለ ጆርጅ ካንድ ጊዜ በላይ ለአደም ቢደውልም ሞባይሉ ዝግ ነበር። ሀሳብ ገባው፣ወደ ሐኪም ቀጠሮው ከመሄዱ በፊት ሊያገኘው ይፈልግ ነበር . . ‹‹ከሕንድ ተመልሻለሁ፣ስጦታ ያመጣሁልህ ስለሆነ ባገኝህ ፍላጎቴ ነው። ከቻልክ ደውልልኝ›› የሚል አጭር የጽሑፍ መልእክት ቢልክለትም ምላሽ አላገኘም . .
የሐኪም ቀጠሮው ስለደረሰ ጆርጅ ወደ ክሊኒኩ አመራ። እንግዳ መቀበያ ውስጥ ተቀምጦ የነበረው በራድ ጆርጅን ሲያይ በሰላምታ ተቀበለው . .

- ሕንድንና ቆነጃጅቷን እንዴ አገኘሃቸው?

- ወብና አስገራሚ አገር ነች . . ቀጠሮዬ ደርሷል ወደ ቶም ልሂድ።

- የቸኮልክ ትመስላለህ፣ወይስ ከኔ ጋር መነጋገር አልወደድክም . . ግዴለም !

- ልግባ ትፈቅድልኛለህ?

- ግባ . . ግባ፣የሆነ ሆኖ ግን አንድ ቀን ወደኔ መመለስህ አይቀርም።

ጆርጅ ሲገባ ቶም ሞቅ ባለ ሁኔታ ተቀበለው። የዛሬው ከተለመደው በጣም የበዛ አቀባበል ነበር። እርሱን በማየቱ ቶም በጣም ደስተኛ መሆኑ በግልጽ ይታይ ነበር። እንዲህም አለው፦

- በመገናኘታችን ምን ያህል እንደተደሰትኩ ልነግርህ አልችልም። አመለካከትህን፣አስተያየትህንና ምላሾችን ለመሰማት በጣም ነው የጓጓሁት።

- የኔን ምላሽና አስተያየት በናፍቆት እየተጠባበቅክ ነው ማለት ነው? !

- ምናልበት አነጋገሬ ያስገርምህ ይሆናል . . ግን እውነት ነው . . አዎ እየጠበቅሁ ነው። ያንተ ፍልስፍና ከኔ ሳይንሳዊና ፍልስፍናዊ አካሄድ ጋር የተጣጣመና በሃይማኖት ላይ የማደርገውን ምርምር ከመጀመሬ ጋር የተገጣጠመ ይመስለኛል። ለዚህ ነው አንዳንድ ሃይማኖታዊ ስነ ልቦናዊ ጥናቶችን ለማካሄድ ቀጣይ በሆነ ሁኔታ ወደ ቤተክርስቲያን የምሄደው . . ፈገግ አለና ቀጠለ ፦ ለማንኛውም ይህን እንተወውና ከሕንድ ጉብኝት በኋላ እኔ እንደጠበቅሁት ሁሉንም ሃይማኖቶች ችላ አላልክም ወይ?

- ያለ ጥርጥር አዎ . .

- አላልኩህም እንደ ጠበቅኩት ሆነ፣ ግሩም ድንቅ።

- መልካም ፈቃድህ ሆኖ ተወኝና ልጨርስልህ፣አዎ ሁሉንም ምድራዊ ሃይማኖቶች ችላ ብያለሁ።

- ምን ማለትህ ነው?

- ለትላልቆቹ ጥያቄዎች ምላሽ ማፈላለግ ያለብን በመለኮታዊ ሃይማኖቶች ውስጥ በቀረበው መሰረት ከፈጣሪ አምላክ በኩል ብቻ ነው ማለቴ ነው።

- በምን መብት ነው መለኮታዊ ሃይማኖቶችን ከምድራዊ ሃይማኖቶች የምታስቀድመው?

- መለኮታዊ ሃይማኖቶችን እኔ ከራሴ ተነስቼ አላስቀደምኩም፣ የምድራዊ ሃይማኖቶች ተከታዮች ራሳቸው ሃይማኖቶቻቸው የራሳቸው እጅ ሥራ መሆናቸውንና በየጊዜው እያሻሻሏቸው መሆናቸውን ያውቃሉ።

- እያሻሻሏቸው? !

- አዎ በየጊዜው ያሻሽሏቸዋል ! ምድራዊና ሰው ሰራሽ መሆናቸውንም አምነው ይቀበላሉ። ደሞም ለታላላቆቹ ጥያቄዎቻችን እንደኛ ያሉ ሰብአዊ ፍጡራን እንዴት አድርገው መልስ ያመጣሉ ! ምናልባትም እኛ ከነሱ የተሻለ ግንዛቤና ዕውቀት ሳይኖረን አይቀርም። በተጨማሪም የሆነ እንስሳ ሊፈጥራቸው ቀርቶ ራሳቸውን በራሳቸው መፍጠር እንኳ የማይቻል እንደ መሆኑ፣ የሰው ልጆች የፈጠራቸው ፈጣሪ አምላክ ሳይኖር ለምን እንደተፈጠሩ እንዴት ማወቅ ይችላሉ? ! እነዚህ ምድራዊ ሃይማኖቶች በዓለም ላይ ለሚታየው የኤቲዝም እንቅስቃሴ መፈጠር ዋነኛ መንስኤዎች መሆናቸው አይታህም?

- ልክ መለኮታዊ ሃይማኖቶች ምንም ጥርጥር የሌለባቸው እውነታ እንደሆኑ አድርገህ ነው የምትናገረው !

- እኔ እንጃ . . ጥያቄህ ከመለኮታዊና ምድራዊው አንዱን መምረጥ የሚመለከት ነበር። በዚህ ረገድ ፈጽሞ ጥርጥር የለም።

- ሁለቱን አማራጮች ያስቀመጥከው አንተ እንጅ እኔ አይደለሁም።

- አምነህ ተቀብለህ ጥያቄውንም ያሻሻልከው አንተ ነህ። ባልወደውም በትክክለኛ ሳይንሳዊ መንገድ እየተጓዝን ነው። ስለዚህም በማንኛውም አፍታ መለኮታዊ ሃይማኖቶችንም ችላ ልትላቸውና አብረን ልንተዋቸው እንችላለን፣ያኔም ወደ ወደ ኤቲዝም እንመለሳለን።

- ያ ይሆናል የሚል እምነት የለኝም። ኤቲዝም ወደ ደስተኝነት የማያደርስ የጨለማ መንገድ ነው፤ለዚህ ነው ብዙዎቹ ኤቲስቶች ራሳቸውን የሚያጠፉት።

- አሃሃ፣አንተም በቅርቡ ራስህን ትገድላለህ እያልከኝ ነው? ታዲያ የሃይማኖት አማኞችስ ለምን ራሳቸውን ያጠፋሉ?

- የኤቲዝም መንገድ ጨለማ መሆኑን ታውቀዋለህ ብዬ ነው የምገምተው፣ለዚህም ነው በሃይማኖቶች ላይ የምታደርገውን ጥናት የጀመርከው። ሃይማኖት ያላቸው ሰዎች ለምን ራሳቸውን ይገድላሉ ለሚለው መልሱን እኔ የግድ ማወቅ ያለብኝ አይመስለኝም።

- ሊሆን ይችላል፣ዋናው ነገር እኛ አሁን መለኮታዊ ሃይማኖቶችን እናጥናና ሁሉም ወደምንፈልገው ምላሽ የማያደርሱን ከሆኑ ሌላ መፍትሔ እንፈልጋለን። ከኤቲስትነቴም ጋር ስለ ኤቲዝም የምትናገረውን ብዙውን እጋረሃለሁ። ይሁን እንጂ ምናልባት የግድ መኖር ያለበት አማራጭ በመሆኑ አማራጮቼን ሁሉ ሙሉ በሙሉ እርግፍ አድርጌ መተው አልፈልግም።

- ሦስት ሃይማኖቶች ብቻ ናቸው የቀሩት።

- አሸባሪውን እስላምም እናጠነዋለን ማለት ነው?

- እኔ እንጃ፣ግና አማራጮችን ውድቅ ማድረግ አልወድም ብለህ የለ? !

- አዎ . . እውነትህን ነው። ግና እንደ እብን ላዴን በቶራ ቦራ ተራሮች ውስጥ ስትደበቅ ታየኝ።

- ሽብርተኝነትን አምርሬ ከመጥላቴና አእምሮ አልባነት ፣ሃይማኖት የለሽነትና ጭካኔ ስለመሆኑ እርግጠኛ ከመሆኔ ጋር ሚዘናዊ የሆነ ሳይንሳዊ አካሄድ በጥናቱ ውስጥ እንድናካትተው ያስገድደናል።

- ጊዜ ለመቆጠብ ያህል አሁን ከፊትህ የሚጋፈጥህ ፈታኝ ጉዳይ ከሦስቱ ሃይማኖቶች አንደኛውን የመምረጡ ነገር ነው። እኔ የማቀርበው ሀሳብ በሁሉም ዘንድ ስምምነት በተደረገበት ሃይማኖት ጥናቱን እንድትጀምር ነው።

- ሦስቱም ሃይማኖቶች ስምምነት የተደረገባቸው ናቸው።

- ማለት የፈለኩት አይሁዳዊነትን ነው። ሙሴ አይሁዶች፣ክርስቲያኖችና ሙስሊሞችም ያምኑበታል።

- ገባኝ፣የዚህ ተቃራኒና ግልባጭ ከሆነ ሌላ አቅጣጫ መመልከትም የሚቻል ይመስለኛል።

- እሽ ፈላስፋው፣ እንዴት ማለት ነው?

- ሙስሊሞች በሙሴ በኢየሱስና በሙሐመድ ያምናሉ። ክርስቲያኖች ግን በሙሴና በኢየሱስ ብቻ ነው የሚያምኑት። አይሁዶችን ከወሰድን ደግሞ በሙሴ ብቻ ነው የሚያምኑት።

- ከተቃራኒ አቅጣጫ ትክክለኛ የሆነ አመለካከት ነው፤ይሁን እንጂ የመለኮታዊ ሃይማኖቶች አንጋፋ ከመሆኑ አንጻር በአይሁዳዊነት እንጀምር በሚለው ሀሳቤ አሁንም እንደጸናሁ ነኝ።

- ሙሉ በሙሉ በሀሳብህ እስማማለሁ።

- በአንድ ጊዜ ስለ ታሪክ፣ስለ ፍልስፍና፣ ስለ ርእዮት፣ ስለ ሃይማኖትና ስለ ተጨባጩ ሁኔታ የምታጠና ስለሆንክ፣ ለያንዳንዱን ሃይማኖት በቂ ጊዜ ሰጥተህ እንደምታጠና ተስፋ አደርጋለሁ። አይሁዳዊነትን አውቀህ ስትጨርስ ክርስትናን ከማወቅህ በፊት ውድቅ አታደርገው ወይም አትቀበለው። ጊዜ ወስደህ ክርስትናን ካወቅህ በኋላም እስላምን ከማወቅህ በፊት ውድቅ አታደርገው ወይም አትቀበለው . . ፈገግ ብሎ ቀጠለና ፦ ወደ ቶራ ቦራ ተራሮች ለመሄድ ገፍተህ ከቀጠል ማለቴ ነው !

- መልካም ግን እነዚህን ሃይማኖቶች ለማወቅ ተመራጩ ዘዴ ምን ይመስለሃል?

- ማንበብ፣ ማነጻጸር፣ ማጥናትና መመራመር የማያልቅ ሀብት ነው። እያንዳንዱን እምነት ከሃይማኖቶቹ ሊቃውንት ማወቅ ከቻልክ ተመራጭና ጠቃሚ መሆኑ ጥርጥር የለውም . . ወደ ሕንድ እንደ ሄድክ ሁሉ አይሁዳዊነትን በቅርበት ለማወቅ ወደ ቴልአቪቭም ብትጓዝ ጥሩ ነበር።

- በሚገርም አጋጣሚ በቅርቡ ወደ ቴልአቪቭ የሚደረግ አጭር የሥራ ጉብኝት ቀርቦልኛል። ይሁን እንጂ እስካሁን ለመሄድ ፈቃደኝነቴን አልገለጽኩም።

- ሰሞኑን ከሕንድ የተመለስክ በመሆንህ የግል ሁኔታህን ባላውቀውም ወደ ቴልአቪቭ የመሄድ ዕድሉ ካለ ወደዚያ መጓዝህ በጣም ጠቃሚ ይሆናል . . ክርስትናን በምታጠናበት ጊዜ ደግሞ ወደ ሮማ ተጓዝ። እስላምን ለማጥናት ወደ መካ ሂድ፣ግና አሸባሪዎቹ ወደ መካ እንድትገባ አይፈቅዱልህም !

- አነጋገርህ የቴልአቪቩን ጉዞ እንድቀበለው ስሜቴን አነሳስቷል፤ነገሩን አስብበትና ውሳኔዬን እነግረሃለሁ።

- ዕድለኛ ነህ፣አይሁዳዊያት ሴቶች ማራኪዎች፣ አጫዋቾች፣ የተለያየ የዘር ግንድ ያላቸውና ቁንጅናን በየዓይነቱ የተጎናጸፉ ናቸው። ከሕንዳዊያት ቆነጃጅት በኋላ እነሆማ በአይሁዳዊያቱ ልትዝናና ነው፤ታድለሃል !

ጆርጅ በሐኪሙ አነጋገር ተከፋና ሊያፋጥጠው ፈለገ . .

- አንተም የተለያየ የትውልድ ሐረግ ባላቸው ሴት ታካሚዎችህ ትደሰትባቸው የለ? ! የተለያየ ዝርያ ባላቸው አማኝ ሴቶች ላይ የምታካሄደውን ጥናትህን ለማሟላት በቤተክርስቲያን ድግሶች ላይ ትዝናና የለም ወይ? !

- ማለት የፈለከውን በሚገባ ተረድቻለሁ። ካትሪና ግሩም ድንቅ ናት፣ድንቅነቷ ግን ግራ ቀኝ ሳትል በፍጹምነት ሃይማኖቷን ብቻ ማገልገሏ ነው።

- ምናልባትም በሕንዳዊያት መደሰት ስለምትወድ ይሆናል፣አስቸጋሪውን ጥናትህን ሌሊቱን ሙሉ እስከ ንጋት ድረስ የማታቋርጠው።

- አሁንም ማለት የፈለከው በደንብ ገብቶኛል። እስከ ንጋት የቆየነው ቤተክርስቲያኑ አጠገብ ባለው ሕንጻ ላይ በተነሳው የቃጠሎ አደጋ ምክንያት ነው . . (ወደ ጆርጅ ፊቱን አዞረና በምር አነጋገር ቀጠለ)) ፦ በሴቶች የመጫወት ረዥም ታሪክ ቢኖረኝም ካትሪና ግን ሙሉ በሙሉ ከሁሉም የተለየች ናት። ካቶሊክ ሃይማኖቷንና እሱን ከመስበክ ውጭ በሌላ ነገር ፈጽሞ የማታስብ ሴት ናት።

- ሁል ጊዜ ስትገናኙና ስታመሹ ስለ ሃይማኖት፣ስለ ክርስትናና ስለ እምነት ብቻ ነው የምትወያዩት ብዬ እንዳምንልህ ነው የምትፈልገው? !

- በእርግጥ አይደለም፣ቤተክርስቲያኑ የተለያዩ የምሽት ድግሶችን የሚያዘጋጀው ሰዎችን ወደ ቤተክርስቲያን ለመሳብና ሃይማኖት ለማስተማር ነው

- በነዚህ የጭፈራ ድግሶች ውስጥ ነዋ ብዙዎቹ የፍቅር ትረካዎች የሚጀምሩት? !

- ይህ እውነት ነው። ካትሪና ግን ከቁንጅናዋ ጋርም የተለየች ሴት ናት። ዓላማዋ ቁልጭ ያለ ነው፣ከዚያ ውጭ ስለምንም ነገር አታስብም። ብቸኛ ግቧ ካቶሊካዊነትን ማገልገል፣ሰዎች በኢየሱስ ያላቸውን እምነት እንዲጨምሩ ማድረግ ነው፤ድንቅነቷም በዚህ ነው።

- አሃ፣ለዚህ ነዋ እስክትሰክሩ አብራችሁ የምትጠጡት፣ እምነታችሁ ጨምሮ ለሰው ልጆች ስትሉ ልትሰው? !

- አካሄድህ ፈጽሞ የማይዋጥልኝ ቢሆንም፣ካትሪና የዋለችልኝን ውለታ በከፊል መመለስ የሚገባኝ ይመስለኛል፤ከአስራ አምስት ዓመታት ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ ልቤ ውስጥ እምነትን ቀስቅሳለች . . ልክ ነው በቤተክርስቲያኑ ድግስ ላይ መጠጥ ጠጥቻለሁ፣እኔ እንኳ ኤቲስት ነኝ፣ሃይማኖት አጥባቂዋ ካትሪና በመጠጣቷ ግን ተገርሜያለሁ።

- እምነት ሞልቶ ሲፈስ፣ለሰው ልጆች መድህን ራስን አሳልፎ መስጠት ከጫፉ ሲደርስ፣ጨዋታው ደርቶ፣ሞቅታውና ስካሩ ከመጨረሻው ደረጃ በደረሰ ጊዜ ምን ይሆን የተከሰተው ! !

- እውነቱን ለመናገር ካትሪና ብዙ ላለመጠጣት ብትጥርም፣ ከተከሰተው የእሳት አደጋ ችግር ከተገላገልን በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ከተለመደው በላይ በመጠጣቷ ተዳክማ ነበር።

- ያኔ አንድ ላይ በመንፈስ መጠቃችሁ፣ተዋሀዳችሁ ማለት ነዋ !

- እንዴ አንተ ጆርጅ ! ምንም አስነዋሪ ነገር በመካከላችን አልተከሰተም። ግን መጠጡን ትንሽ ከልክ አሳልፋ ስለነበር አዞራትና ወደ መኪና ተሸክሜ ወስጄ ራሷን እስክታውቅ ድረስ ጠበቅኋት። በዚህ ምክንያት ነው እስከ ንጋት የዘገየነው። ከነቃች በኋላ በሁኔታው ሀፍረት ተሰምቷት አጥብቃ አመሰገነችኝ። ለምስጋናዋ ምላሽ ሳምኳት፣ግን በአድራጎቴ መከፋቷ በግልጽ ይታይ ስለነበር መሳሳቴን ወዲያውኑ ተገነዘብኩ።።

- በጣም ጥሩ . . ድንቅ የፍቅር ትረካ ነው፣ላጨበጭብላችሁ ይገባል !

- ወዳጇና ጎረቤቷ ሳሊ ሙሉውን ጊዜ ከኛ ጋር ስለነበረች የነገርኩህን ሁሉ ከርሷ ማረጋገጥ ትችላለህ። የዚያ ሌሊት ፎቶግራፎች በሙሉ እዚያ ላይ ስለሚገኝ ከኔ የፌስቡክ ገጽም ማረጋገጥ ትችላለህ። ይህን ሁሉ እንድነግርህ ያስገደደኝ ሰው የለም፣አቀራረብህ አፋጣጭ ቢሆንም፣እኔ ላንተ ግልጽ መሆን ስለፈለኩ ብቻ ነው የነገርኩህ። ከሌላው ሰው በተለየ መንገድ አንተን ለምን እንደማይህ አላውቅም፣ምናልባት እኔም ያንተው ዓይነት ጉዳይ ስላለኝ ወይ በሌላ ምክንያት ሊሆን ይችላል።

- የኔው ዓይነት ጉዳይ? !

- በምነግርህ ነገር ትገረም ይሆናል፣የቆየ ውስጣዊ ሀሳብና ጭንቀት አለብኝ። ምክንያቱን ሳላውቅ ካንድ ዓመት ወዲህ በጣም ተባብሶብኛል። በጣም የሚደንቀው አንተ ጥያቄዎችን ይዘህ ወደኔ ከመጣህና ሃይማኖትን ማጥናት ከጀመርኩ በኋላ ግን ለምን እንደሆነ እንጃ ጭንቀቱ መቀነሰ ጀምሯል። በጥያቄዎቹና በመልሶቹ ምክንያት ይሆን? ወይስ ወደ ቤተክርስቲያን በመሄዴ ወይም በሁለቱም ምክንያት ይሆን? በነገራችንን ላይ ያንተው የጭንቀትና የመደበት ችግር አሁን እንዴት ነው? እየሰፈረብህ የሚያስቸግርህ የጥያቆዎችህ ማዕበልስ አሁን እንዴት ነው?

- አሁን አሁን በጣም እየቀነሰ መጥቷል። ምናልባት ወደ ደስተኝነት መንገድ ለመድረስ በሚያስችሉ መልሶች ፍለጋ በመጠመዴና በሕንድ ጉዞዬ ምክንያት ሊሆን ይችላል ጭንቀቱን እንድረሳ ያደረገኝ።

- ‹‹የደስተኝነት መንገድ›› የሚለው ውብ አገላለጽ ነው።

- ልክ ነው፣አንድ ጊዜ መንገድ ላይ ያገኘሁት ሽማግሌ የነገረኝና በአንድ ካፌ ያገኘሁት አስተናጋጅ እውስጤ ያስጸረሰው አባባል ነው።

- ሁሉም ሰው በደስተኝነት ጎዳና መጓዝ ይፈልጋል። እንዲያውም ሁሉም በዚያ ጎዳና ላይ እንዳለ አድርጎ ራሱን ይቆጥራል። እውነታው ግን እውነታነቱን እንደጠበቀ ይቆያል።

- ምን ማለትህ ነው?

- የያንዳንዱ ሃይማኖት፣ቡድን፣ጎራ ወይም ፈለግ ተከታዮች በደስተኝነት ጉዳና ላይ ነን ብለው ይገምታሉ፤በደስተኝነት መንገድ ላይ ያሉት እነሱ ብቻ መሆናቸውን ያምናሉ !! (ፈገግ ብሎ ቀጠለ) ፦ ይህ መቼም አስቂኝ አጋጣሚ ነው !!

- ይሁንና እኔና አንተ ግን ያለ ጥርጥር በደስተኝነት መንገድ ላይ አይደለንም፣ብንሆን ኖሮ አሁን ባለንበት ጭንቀትና ሀሳብ ውስጥ ባልኖርን ነበር !

- ለማንኛውም አብረን ያደረግነውን በከፊል ጠቅለል እናደርገው . . ደስተኝነት የሚገኘው ለታላላቆቹ ጥያቄዎች በሚሰጡ ምላሾች ውስጥ ነው፣የኤቲዝምን አመለካከት ውድቅ በሚያደርግ ሁኔታ መልሶቹ መገኘት ያለባቸው ከሰው ልጅ ሳይሆን ከፈጣሪው በኩል ነው በሚለው ላይ ተስማምተናል። ከዚያም ይህ ፈጣሪ አምላክ ያስተላለፈው ምድራዊ ሃይማኖት ሳይሆን መለኮታዊ ሃይማኖት ነው በሚለው ላይም ተግባብተን፣አሁን ይህ መለኮታዊ ሃይማኖት የትኛው እንደሆነ በመወሰን ሂደት ላይ እንገኛለን።

- የዚህ ሃይማኖት ተከታዮች ናቸው በደስተኝነት መንገድ ይጓዛሉ ተብለው የሚታሰቡት። ካትሪና ከመጀመሪያው ወዳለችኝ አቅጣጫ ወደሚያደርሰኝ እየተጓዝኩ ነው የሚል እምነት አለኝ። ይሁን እንጂ ተጣድፌ እርከኖችን ማምከን አልፈልግም። አሁን አሁን የነዚህ ጥያቄዎች ጫናና ውስብስብነት እየቀነሰልኝ መጥቷል፤ታላላቆቹን ጉዳዮች በጥልቀትና ሳላካብድ ቀለል ባለ መንገድ እያስኬድኩ መሆኔ ይሰማኛል።

- በጌታ መንገድ ሁሉንም ነገር የሰዋችው ካትሪና ትክክለኛ መሆን የሚገባት ነው፤ይሁን እንጂ በጀመርነው መንገዳችን እንዝለቅ፤ከቴልአቪቭ የምትመለስበትን ጊዜ እጠብቃለሁ፣ ስትመለስ ውይይታችንን እንቀጥላለን።

- ተስማምተናል፣ዛሬ አራዝምብሃለሁ ይቅርታ አድርግልኝ . . መልካም ፈቃድህ ከሆነ ወደ ቴልአቪቭ ከተጓዝኩ ቀጠሯችን ከሁለት ሳምንት በኋላ ነው፣ካልተጓዝኩ ግን መጪው ሳምንት ይሆናል።

- ስለ አይሁዳዊነት ለማንበብ በቂ ጊዜ እንድናገኝ ቀጠሯችን ከሁለት ሳምንት በኋላ ነው። መረጃህን ለማበልጸግ ወደ ቅድስት አገር መጓዙን ችላ አትበል።

- ‹‹ቅድስት አገር›› የሚለው ውብ አገላለጽነው !

- አዎ፣ለሁሉም መለኮታዊ ሃይማኖቶች ቅድስት አገር ነች። በዚህ ምክንያት ነው በውስጧና በአካባቢዋ ሁሌ ጦርነቶችን የምናስተውለው።

- ለመጓዝ ጥረት አድርጋለሁ፣እስኪ እንዴት እንደማደርግም አስብበታለሁ።

ጆርጅ ከቶም ዘንድ ሲወጣ በራድ መሰሪ ፈገግታን በተላበሰ ፊት ከውጭ እየጠበቀው ነበር . .

- ካትሪና እንዴት ነች? ትተሃት ወደ ቶራ ቦራ ልትሄድ ነው?

- ቶራ ቦራ? ! !

- ሰው ሁሉ በአጭር ቃላት የሚጫወትብህ ተራ ሞኝ አትሁን !

- ምን ማለት ነው?

- ምንም አይደለም፣ካትሪና ማራኪ ቆንጆ ናት፣ቶምም መልከ መልካም ሎጋ ነው። መሳፈር ትችላለህ ግን ብልህ አስተዋይ እንጅ ሞኝ ተላላ አትሁን።

ጆርጅ መልስ አልሰጠም፣ወዲያውኑ ነው በንዴት ጥሎት የሄደው። በቶምና በበራድ አነጋገር መካከል ያስተዋለው ይህ መመሳሰል አእምሮው ውስጥ እየተመላለሰ ነው . . ለመሆኑ በራድ ከቶም ጋር የተነጋገርኩትን ሰምቶ ይሆን? ወይስ ልብ ለልብ መናበብ የሚሉት ነው?!

ቀጠሮ ከሽብርተኝነት ጋር . . (5)

ጆርጅ ለአደም መደውሉን ቢቀጥልም ምላሽ አላገኘም። ምን ነክቶት ይሆን ብሎ በጣም አሰበ፣ሰጋለት። ካንድ ጊዜ በላይ ወደ ቤቱ ሄዶ አላገኘውም . . ካትሪናም የጆርጅ መጨነቅ ተሰምቷታል . .

- በጣም የተጨነቅህ ትመስላለህ . . ምንድነው ነገሩ?

- አስተናጋጁን ወዳጄን አደምን ማግኘት አልቻልኩም። ብዙ ጊዜ ደወልኩ፣ወደ ቤቱም ካንድ ጊዜ በላይ ተመላልሻለሁ!

- በሽብር ጥቃቱ ምክንያት ጉዳት እንዳያገኝህ ስጋት ነበረኝ። ተጨንቀህ ሳይህ አሳሰበኝ። አደምን በጣም ትወደዋለህ ማለት ነው?!

- ቀለል ያለ የማይከብድ የማያካብድ ሰው በመሆኑ ብዙ ጠቅሞኛል፣የሚናገረው ሁሉ በጣም ያረካኛል።

- የሥራ ባልደረቦቹ ምን ይላሉ?

- የዩኒቨርሲቲ ወረቀቱን ጽፎ ለማጠናቀቅ ፈቃድ ላይ ነው ይላሉ፣ቀደም ሲል እንደነገርኩሽ ሃይማኖቶችን የሚያጠና ተማሪ ነው።

- ፈቃዱ መቼ ነው የሚያበቃው?

- ከነገ ወዲያ ያበቃል። በአንዳንድ ጉዳዮች ላይ ላማክረው ስለፈለግሁ ላገኘው ቸኩያለሁ . . በነገራችን ላይ ወደ ቁድስ ወይም ቴልአቪቭ ወደሚባለው አገር ለሥራ እንድጓዝ ጥያቄ የቀረበልኝ በመሆኑ ላማክርሽ ፈልጌ ነበር።

- ወደ ቅድስት አገር? !

- አዎ፣ኩባንያችን ካንድ የአይሁድ የደህንነት ኩባንያ ጋር የሥራ ውል ለመፈራረም ይፈልጋል።

- ገና አሁን ነው ከጉዞ የተመለስከው፣ሳታርፍ ሌላ ጉዞ አድካሚ እንዳይሆንብህ ስጋት አለኝ።

- አድካሚ አይሆንም፣ይሁን እንጂ ካንቺ ከማይክልና ከሳሊ ጋር ተጨማሪ ጊዜ ማሳለፍ ነበር ፍላጎቴ። ጉዞው ብዙም አልሳበኝም ነበር፣ዛሬ ከቶም ጋር ስገናኝ ግን እንዳልቀር በጣም አበረታቶ ገፋፋኝ።

- ለምን?

- የአይሁድን ሃይማኖት በቅርበት ለማወቅ መልካም አጋጣሚ ይሆናል ነው የሚለው።

- በዚህ ልታምነው ይገባል። ይህ ብቻ ሳይሆን የሁሉም መለኮታዊ ሃይማኖቶች ቅድስት አገር በመሆኗ ሦስቱንም መለኮታዊ ሃይማኖቶች ለማወቅ መልካም አጋጣሚ ነው።

- አንቺስ ምን ትያለሽ?

- ቶም ያነሳው ነጥብ ትዝ አላለኝም ነበር፣ይጠቅመኛል ብለህ የምታምን ከሆነ ተጓዝ፣ከጠቀመህ ደስተኛ ነኝ፤እኔና ልጆቼ በሰላም ተመልስህ የምትመጣበትን በጉጉት እንጠባበቃለን።

- ቶም ያነሳው ነጥብ አሳማኝ ቢሆንም ብዙ ጉጉት አላሳደረብኝም ነበር፣ለማንኛውም ጉዞው በታጣም አጠር ያለ እንዲሆን ለማድረግ እሞክራለሁ።

- አንተ ዕድለኛ ነህ ወደ ድንቃድንቆቹ አገር ተጉዘህ አሁን ደግሞ ወደ ጦርነት ፍጥቻዎችና የፍልሚያዎች አገር ትጓዛለህ!

- ዕድለኝነቴማ በድንቋ ባለቤቴ ባንቺ ነው።

- እኔም አንድ ገጸ በረከት ላቀርብልህ እፈልጋለሁ።

- ምን ይሆን?

- ከጉዞህ ተመልሰህ ትንሽ ካረፍክ በኋላ ፈቃድ ትወስድና ሁላችንም አንድ ላይ ወደ ሮም እንጓዛለን። በዚህም የድንቃድንቆችን አገር፣የጦርነት ፍጥጫዎችን አገርና የአብያተ ክርስቲያናትን አገር ያዳረስክ ትሆናለህ። ካቶሊክን ወደ አገሩ ሄደህ በቅርበት በማየት የደስተኝነት መንገድ የምትለውን ነገር ትተዋወቃለህ።

- እዚያ ሆኜ ቶም እንደሚፈልገው ክርስትናን ይበልጥ ማወቅ እችላለሁ። . . ለመጓዝ የተስማማሁ መሆኔን ነገ ለካኽ ሳልነግር አልቀርም፣ይህ አስጨናቂ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሳይነሳ ባልሄድ ግን ደስ ይለኛል . . ለደህንነታችሁ እርግጠኛ ሳልሆንና ወንጀለኞቹ አሸሪዎች ለፍርድ ሳይቀርቡ አልጓዝም።

- የፍንዳታው ዋነኛ ተጠያቂ ነው ተብሎ የሚገመተው ፓኪስታናዊ አሁንም ገና አልተያዘም፣ወዳጆቹና በዙሪያው የሚገኙ ሙስሊሞች ግን ቁጥጥር ሥር ውለዋል።

- የት አባቱ ያመልጣል፣ዛሬ ወይም ነገ ጋማውን ይይዛሉ። ሽብርተኝነትንና ግድያን በሁሉም ገጽታዎቹ እንዴት እንደምተጠላው ልነግርህ አልችልም !

ጆርጅ ወደ ሥራ ቦታው እንደ ደረሰ ጉዞውን መቀበሉን ለማሳወቅ ወደ ካኽ ቢሮ አመራ። ጉዞው አጠር ያለና ከአራት ቀናት ያልበለጠ እንዲሆንም ጠየቀው።

- አራት ቀን በጣም በቂ ነው።

- ተልእኮዬ በግልጽ ተዘርዝሮና ተለይቶ ተቀምጧል?

- አዎ . . የኦርሻሌም ሴኩሪቲ ኩባንያ የኤሌክትሮኒክስ ደህንነት ጥበቃ ውሎችን ከኛ ጋር ይፈራረማል፣ከሞላ ጎደል በሁሉም ዝርዝር ጉዳዮች ላይ ከስምምነት ደርሰናል።

- መሄድ ሳያስፈልግ ለምን ውሎቹን ብቻ አንልክላቸውም?

- የኩባንያው የቴኒክ መምሪያ ኃላፊ መመለስ የሚገባቸው ብዙ ጥያቄዎች አሏት፣በጣም ብዙ ዝርዝር ማብራሪያዎች ትጠብቃለች። እሷን በአካል ተገኝቶ ማሳመን ግዴታ ነው። የስምምነቱ ዋነኛ ተቀናቃኝ እሷ ናት። የመጨረሻው ውሳኔ የርሷ ነው፣በጉዳዩ ላይ የመወሰን መብት ያላት የመጨረሻው ሰው ናት።

- እንዲህ ከሆነ በዝርዝር ቴክኒካዊ ጉዳዮች ላይ በቂና የተሟላ ግንዛቤና መረጃ ሊኖረኝ ይገባል። የተለዋወጣችሁትን ዝርዝር የተቃውሞ ነጥቦቿን የግድ ማንበብ ይኖርብኛል።

- ልክ ነህ፣ይህ በጣም አስፈላጊ ነው . . ወደዱም ጠሉ በመጨረሻ ውሉን መፈረማቸው ግን አይቀሬ ነው።

- በጣም እርግጠኛ የሆንክ ትመስላለህ !

- በብዙ ምክንያት፣አንደኛ፦ እስራኤላውያን የአሸባሪው ሐማስ ፎቢያ አለባቸው፣ሌላው ቀርቶ ለቴክኖሎጂ አቅሙ እንኳ ስጋት አላቸው፤በመሆኑም የደህንነት ጥበቃ ውሎችን ከኛ ጋርም ሆነ ከሌሎች ጋር ለመፈራረም አያመነቱም።

- እውነት አላቸው፣አሸባሪዎች ርህራሄ የላቸውም፣እኛ ራሳችን ሰሞኑን እዚህ ለንደን ውስጥ ያለንበትን ሁኔታ አታይም? !

- ግና አይሁዶች ከሐማስም ሆነ ከሌላው ሁሉ የከፋ አሸባሪዎች ናቸው !

- እንጃ ሊሆን ይችላል፣የማውቀው ነገር ቢኖር አሸባሪዎች ለንደን ውስጥ ያለ አንዳች ርህራሄ፣ሃይማኖትም ሆነ ሕሊና በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን የመግደል ፍላጎት የነበራቸው መሆኑን ነው !

- አሁን ስለ ሽብርተኝነት ተወኝና . . ሁለተኛው ምክንያት ፦ የቴክኒክ መምሪያ ኃላፊዋ ሌቪ አይሁዳዊት፣አለቃዋም አይሁዳዊ መሆናቸው ነው።

- አልገባኝም፣የርሷና የአለቃዋ ይሁዳዊ መሆን ውሉን እንዲፈርሙ እንዴት ያደርጋቸዋል?

- ሁለቱም ይሁዲዎች እንደ መሆናቸው እኔ ከማንም በላይ አውቃቸዋለሁ። አለቃዋ ቤንያሚን ለራሱ የግል ጥቅም ብሎ ውሉን ከኛ ጋር መፈራረም ይፈልጋል። የቴክኒክ ኃላፊዋ ደግሞ ከርሱ ፍላጎት ውጭ መሆን አትችልም፣ አለዚያ የርሷን ጥያቄዎች ውድቅ ያድርግባታል፣ከሃይማኖት ተነስታ ነው ቃሉን የምትፈጽመው።

- አንተስ አይሁዳዊ አይደለህምን?

- እናቴ አይሁዳዊት ናት፣ስለዚህ እኔም አይሁዳዊ ነኝ ማለት ነው።። ይህ ሦስተኛው ምክንያት ነው። ለዚህ ነው ከኔ ጋር ስምምነቱን ለመፈራረም የተስማሙት . . አለዚያማ እኔ ሀብትና መዝናኛን የሚያስገኝልኝ ካልሆነ በስተቀር ስለ ሃይማኖት ምንም ደንታ የሌለኝ ሰኩላሪስት ዓለማዊ ሰው ነኝ . . ኣ፣በነገራችን ላይ ሌቪ ገና የ25 ዓመት ጉብል ናት፣የዓለም ውብ ቆንጆ ነች። ከርሷ ጋር ለመዝናናት ከፈለግህ ለቤንያሚን ንገረውና ወዲያውኑ ትቀርብልሃለች። ቤንያሚንን በተመለከተ ውሉ እንዲፈጸም ካደረገ ለግሉ አንድ መቶ ሺ ዶላር ለመስጠት ነው ቃል የገባሁለት።

- አንድ መቶ ሺ ዶላር አልበዛም? !

- በጣም ብዙ ነው፣ግና በመደበኛው የስምምነቱ አጠቃላይ ዋጋ ላይ አንድ መቶ ሃምሳ ሺ ዶላር ጨምሬ ስለተስማማ ነው በመቶ ሺው የተስማማሁለት።

- ምን ዓይነት ወራዳነት ነው ጃል !! ይህ በኩባንያውና በአገርም ላይ የሚፈጸም ክህደት ነው፣ቢዝነስ አይደለም !

- ገንዘብ እኛ ዘንድ ሌላ ነገር ነው፣እኛ አይሁዶች አውነተኞቹ ነጋዴዎች ነን። በዚህ ምክንያት ነው በመላው ዓለም ንግድና ቢዝነስ በኛ ቁጥጥር ሥር የሆነው፣በፍቅረ ነዋይም ሆነ በንግድ ሥራ ማንም ከኛ አይወዳደርም።

- አነጋገርህ የአይሁድ ሃይማኖትንና የአይሁዳዊ ሰው ሰብእናን ከሩቁ እንድፈራ አድርጎኛል።

- አሃሃ፣‹‹አንድን አይሁዳዊ ሰላም ብለህ ከጨበጥክ ከሰላምታው በኋላ ጣቶችህን ቁጠራቸው፣ሙሉ ሆነው ካገኘሃቸው በትክክል መቁጠር ስለመቻልህ እርግጠኛ ሁን›› ተብሎ አይደል የሚተረተው . . ዋናው ነገር ለቤንያሚን መቶ ሺውን ስጠውና ነገሮች እንዴት ቀላል እንደሚሆኑ ታያለህ።

- ስለ ስምምነቱና ስለ ባሕርያቱ የውል ስምምነቱን ረቂቅና ተያያዥ ጽሑፎቹን ካነበብኳቸው በኋላ ተነጋግረን እናጠቃልላለን።

- መልካም . . ለቀጣዩ ሳምንት የአይሮፕላን ቦታ አስይዛለሁ፣በዚህ ሳምንት ስምምነቶቻችንና ስብሰባዎቻችንን እንጨርሳለን።

ጆርጅ የውል ስምምነቱን ረቂቅና ተያያዥ ጽሑፎችን ከዝርዝር ቴክኒካዊ ጉዳዮች ጋር በማንበብ ላይ ተጠምዶ እስከ ሥራ ሰዓቱ ማብቂያ ድረስ ከቆየ በኋላ ንባቡን ባይጨርሰውም ዘግይቶ ወጣ። በዚህ ጊዜ ውስጥ ሞባይሉ ዝግ ወደ ነበረው አደም ደጋግሞ ደውሎ ነበር . . ወደ ቤት ተመለሰና የዕለቱን ዜና መከታተል ጀመረ፤ከጉዞው በፊት ፓኪስታናዊው ቁትጥጥር ሥር ቢውል ምኞቱ ነበር።
የፍንዳታውን ፈጻሚ በተመለከት አዳዲስ ግምቶች መሰጠታቸውን፣ተጨማሪ ሰዎች መያዛቸውንና የተያዙት ከእስላማዊ ሽብርተኝነት ጋር ግንኙነት የሌላቸው የተገንጣዩ ሲታ ቡድን አባላት መሆናቸውን በዜናው አዳመጠ . . ምን አዲስ ነገር እንዳለ እየጠየቀች ካትሪና ከጎኑ ተቀመጠች . .

- አስደናቂው የሽብር ጥቃቱ ዜና፣ ፈጻሚዎቹን በተመለከተ አዲስ መረጃ መሰጠቱ ነው !

- ለማስመሰል የሚደረግ ባዶ አነጋገር ነው፣ከአሸባሪዎቹ ሙስሊሞች በስተቀር ይህንን ማንም ሊፈጽም አይችልም።

- ተገንጣዩ የሲታ ንቅናቄ ነው አዲሱ ተከሳሽ።

- ምናልባት አሸባሪዎቹ ጥንቃቄአቸውን ቀንሰው ዘና በማለት እንዲዘናጉ በማድረክ ፓኪስታናዊውን ቁጥጥር ሥር ለማዋል ሲባል የተሰጠ የማሳሳቻ መግለጫ ሊሆን ይችላል።

- በፖለቲካ ዓለም ሁሉም ነገር ሊሆን ይችላል !

ቀጠሮ ከሽብርተኝነት ጋር . . (6)

በቀጣዩ ቀን ጆርጅ በጉዞው ጉዳይና የውል ስምምነቶቹን በማዘጋጀት ላይ ተጠምዶ ቢውልም ለአደም መደውሉን አላቋረጠም፤ይሁን እንጂ የአደም ስልክ አሁንም እንደ ተዘጋ ነው..
ኢሜል
ላከለት፣በፌስቡክ ገጹም መልክት አስቀመጠለት። ከሥራ ባልደረባው አስተናገጅ ማወቅ እንደተቻለው ፈቃዱ ዛሬ ስለሚያበቃ ወደ ሥራ ይመጣል ተብሎ ይታሰባል። ከጉዞው በፊት መገናኘት ጽኑ ፍላጎቱ ነው፣ለጆርጅ ይህ ብዙ ማለት ነው . .
ከሥራ ሰዓት በኋላ . . ጆርጅ በካፌው በኩል አልፎ አደም መምጣት አለመምጣቱን ጠየቀ . . አላገኘውም
!

- ዛሬም አልመጣም።

- የወሰደው ፈቃድ ገና አላበቃም?

- አብቅቷል ግን አልመጣም፣ አልደወለምም፣ ይሄ ልማዱ አልነበረም !

- መቼ ይመጣል ብለህ ትገምታለህ?

- አላውቅም፣ዛሬ ሥራ መጀመር ነበረበት፣የሌለ ሰው ችግሩን እራሱ ነው የሚያውቀው።

- አመሰግናለሁ፣ከመጣ ጆርጅ ብዙ ጊዜ ተመላልሶ ፈልጎህ ነበር ብለህ ንገርልኝ።

- እሽ ጥሩ እነግረዋለሁ።

ጆርጅ ወደ መኖሪያ ቤቱ የተመለሰው የአደም ጉዳይ በእጅጉ እያስጨነቀው ነበር፣በድንገት መሰወሩ ስጋት አሳድሮበታል፣እሱን ለማግኘት ያልተጠቀመው የመገናኛ ዘዴ የለም፤ስልክ፣ኢሜል፣ ፌስቡክ፣ ወደ ቤቱና ወደ ካፌው በተደጋጋሚ መሄድ . . ፈጽሞ ሊያገኘው አልቻለም!

- እንደምን ዋልክ የኔ ፍቅር፣ወዳጅህን አደም አገኘህ?

- አላገኘሁትም። የወሰደው ፈቃድ ያበቃ ቢሆንም ዛሬም ሥራ አልገባም !

- በሽብር ጥቃቱ ምክንያት ጉዳት ደርሶበት እንደማይሆን ተስፋ አደርጋለሁ።

- እኔም ተስፋዬ ነው፣አዲስ ነገር አለ? ሽብርተኛው ተያዘ?

- የሚያሳዝን ነው አልተያዘም . . ቁጥጥር ሥር ውለው የነበሩ አብዛኞቹ ሙስሊሞች ዛሬ መለቀቃቸው ከአፍታ በፊት በዜና ታውጇል!

- ወንጀለኞቹ ተለቀቁ !

- በምርመራ የተረጋገጠው ፍንዳታውን ያደረሱት የተገንጣዩ የሲታ ንቅናቄ አባላት መሆናቸው ነው።

- አሃሃ፣ፊቱ ምንም ምቾት ያልሰጠኝ ሰውየ ከሪሙሏህ ያለኝን ነገር አስታወስሽኝ ፦ ‹‹ሽብርተኛ ከናንተ የፖለቲካ ዓላማ ጋር የማይስማማ ነው፣ከናንተ ጋር ከተስማማ አሸባሪውም ጀግና ነው›› ነበር ያለኝ፣እውነቱን ይመስለኛል . . !

- እኔ ማመን አልችልም፣የፍንዳታ ጥቃቱን ያደረሰው ፓኪስታናዊው ነው ብዬ አምናለሁ። መጀመመሪያ ላይ ማንነቱን በደህንነት ካሜራዎች አማካይነት መታወቁን ነግረውን አልነበረም?

- ከሪሙሏህ ምናልባት እውነቱን ሳይሆን አይቀርም የተናገረው። የሲታ ንቅናቄ ተጠርጣሪዎቹን ቁጥጥር ሥር አውለዋል?

- አዎ፣ጥቃቱ ፖለቲካዊ የወንጀል ድርጊት እንጂ ሽብርተኝነት አይደለም እያሉ ነው።

- ወንጀለኞቹ ተለወጡና ወንጀሉ ከሽብርተኝነት ወደ ፖለቲካ ወንጀልነት ተለወጠ ማለት ነው? !!

- ፈጻሚው ሙስሊም ከሆነ ሽብርተኝነት ይሆናል።

- አሃሃ፣ይህማ በትክክል የከሪሙሏህ አባባል ነው። ዋናው ነገር እውነተኞቹ ወንጀለኞች በቁጥጥር ሥር በመዋላቸው ለንደን አስተማማኝ ሰላም ማግኘቷ ነው።

የጆርጅ ስልክ ሲጮህ ፈጥኖ አነሳው፣ደዋዩ አደም እንዲሆን ምኞቱ ነበር፣በእርግጥም አደም ነበር . . በደስታ ሲቃ አነጋገረው . .

- አንተ አደም በመጨረሻ ተገኘህ፣መጥፋትህ በጣም ነበር ያሳሰብከኝ።

- አዎ፣አጭር ጉዳይ ነበረኝ ካፍታ በፊት ነው ያጠናቀኩት።

- ጥናትህን አበቃህ?

- ጥናትና ምርምሬ ይበልጥ ጥልቀት እዲኖራቸው ነው የተደረገው፣ይህን እንተውና አንተ እንዴት ነህ?

- ጥሩ ሁኔታ ላይ ነኝ፤ላገኝህ እፈልጋለሁ፣አሁን ልምጣ?

- በሥራው ምክንያት ትንሽ ስለ ደካከመኝ ነገ ከሥራ ሰዓት በኋላ ብትመጣ ምን ይመስለሃል?

- ጥሩ ከአስራ አንድ ሰዓት በፊት አንተ ዘንድ እሆናለሁ። በደስተኝነት ሬስቶራንት ለእራት ግብዣ ጠርቼሃለሁ።

- ተስማማን፣ነገ እጠብቀሃለሁ።

ጆርጅ ስልኩን ዘጋ፣ፊቱ በደስታ ፈክቷል . .

- አስተናጋጁን አግኝተህ በማናገርህ በጣም የተደሰትክ ትመስላለህ!

- አዎ፣በአነጋገሩ እውነተኝነት፣አላማካበድና ጥልቅነት ለምን እንደሚሰማኝ አላውቅም !

- ይሁዲ ነው ወይስ ክርስቲያን ነው? ካቶሊክ ይሆን ወይስ ፕሮቴስታንት ?

- እኔ አልጠየኩትም . . ሳገኘው በዚህ ጥያቄ ነው የምጀምርለት . .

በተስማሙበት የቀጠሮ ሰዓት ካፌው ፊት ለፊት መኪናው ውስጥ ጠበቀው፣ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ አደም መጣና ወደ መኪናው ገባ።

- አንተ ሰውየ የት ገብተህ ነው፣በጣም ነው ያሰብኩት?

-

ይህ ያንተ ሰናይነት ነው፣በጣም ይቅርታ እጠይቃለሁ፣ ከአቅም በላይ በሆነ ሁኔታ ለመልክቶችህ ምላሽ መስጠት አልቻልኩም . . የደስተኝነት መንገድ ፍለጋው ዬት እንደደረሰ አብስረኝ፣የጥያቄዎችህ መልሶችስ እንዴት ሆኑ? የሕንድ ጉዞህስ? . .

- የሕንድ ጉዞዬ በጣም የተሳካና በመረጃ የበለጸገ ነበር። በጣም ተደስቼበታለሁ . . ወደ ሬስቶራንቱ ስንደርስ ጫወታንን እንቀጥላለን . .

- ግዴለም . . የተቃረብን መሰለኝ . .

ሬስቶራንቱ ውስጥ ጆርጅና አደም ለሁለት ሰዎች የተዘጋጀ ጠረጴዛ ይዘው ተቀመጡ። አስተናጋጁ የምግብ ሜኑ ይዞላቸው መጣ . . አደም ጆርጅን እያናገረ ሜኑውን ማገላበጥ ያዘ . .

- ይህ ውብ ሬስቶራንት ነው . .

- ተመራጭ ሬስቶራንትህ ይመስላል . .

- ስሙ ያስደስተኛል። ደስተኝነትን እወዳለሁ። የሁሉም የምድራችን አስተዋዮች የጋራ ግብ ሆኖ ይታየኛል። በነገራችን ላይ የሬስቶራንቱ ባለቤት የሌላ አገር ዜጋ ይመስላል፣ከየትኛው አገር ይሆን?

- እንግሊዝ አገር የማሌዝያ ሬስቶራንቶች ጥቂት ናቸው፣ይህ የማሌዝያ ሬስቶራንት ነው፤ማሌዝያን ጎብኝተህ ታውቃለህ?

- አልሄድኩም . .

- ማሌዝያ መጎብኘት ከምፈልጋቸው አገሮች አንዷ ናት፣እስካሁን አላየኋትም። ተፈጥሯ ልክ እንደ ሕዝቧ ተፈጥሮ ማራኪ ነው ይባላል። ሕዝቡ በጣም ቀለል ያለ በጣም ገር የሆነ የሚመች ሕዝብ ነው።

- ማቅለልና አለማካበድ አንዳንድ ጊዜ ጥልቅነትን የሚያመለክት ሲሆን አንዳንዴ ደግሞ ጅላጅልነትና ጀንፈልነትን ያመለክታል።

- እዚህ ግን ጥልቅነትን ነው የሚያሳየው። ማሌዝያ ወደፊት የተራመደች በተለይም በቴክኖሎጂ መስክ ፈጣን ዕድገት በማስመዝገብ ላይ የምትገኝ አገር ነች።

- ጥልቀት ያለው ቀላልነት ያስደስተኛል። (ፈገግ ብሎ ቀጠለና) ፦ ወይም በሌላ አባባል ቀለል ያለ ጥልቅነት . . እሽ የሕንድ ጉዞ ጫወታህን ቀጠል . .

- መጀመሪያ ምግቡን እንዘዝ . .

ጆርጅ አስተናጋጁን ጠራና ሁለቱም ትእዛዛቸውን ነገሩት . . አስተናጋጁ ትእዛዛቸውን ተቀብሎ ሄደ . .

- የሕንድ ጉዞው ጥያቄዎቼን በጉልህ መልሷል፤ወደ ደስተኝነት መንገድ እየተጓዝኩ ነኝ የሚል እምነት አለኝ።

- በጣም ጥሩ !

- ጉዞው ከነገርኩህ የቶምና የካትሪና ጉዳይ በስተቀር ምንም ዓይነት እንከን አልነበረበትም። ለለገስገኝ ምክር ከፍተኛ አክብሮት አለኝ። በጣም አስቸጋሪ በሆነ የስነ ልቦና ሁኔታ ውስጥ ነበርኩ። የነገርከኝ ነገር ትክክለኛ እንደነበር አሁን ለመረዳት ችያለሁ ማለት እችላለሁ።

- የትኛው ነገር?

- ጥርጣሬህ ትክክለኛ ላይሆን ይችላል ብለኸኝ ነበር። ቶም ጉዳዩን በዝርዝር ነግሮኛል፣አሁን ለምን አምኜ እንደተቀበልኩትና ለምን ከቀድሞ የተለወጠ መስሎ እንደታየኝ ግን አላውቅም።

- ዕድሉን ከሰጠናቸው ሰዎች ሁሉ ሊለወጡና ሊሻሻሉ ይችላሉ . . (ፈገግ ብሎ ቀጠለና) ፦ መለኮታዊ ሃይማኖቶችን ከሰው ሰራሽ ምድራዊ ሃይማኖቶች ጋር የማነጻጸሩ ነገርስ እንዴት ሆነ?

- ያለ ምንም ጥርጥር መለኮታዊ ሃይማኖቶች ተቀዳሚና ተመራጭ ናቸው።

- በልበ ሙሉነት እርግጠኛ የሆንክ ትመስላለህ !

- አዎ፣በሰው ሰራሽ ምድራዊ ሃይማኖቶች ውስጥ ይሆናል ተብሎ በማይገመት ሁኔታ መደናበር መኖሩን ነው ያስተዋልኩት። (ሳቀና ቀጠለ) ፦ እስኪ ይታይህ በአይጦች የሚያመልኩ፣በጥንዝዛ የሚያመልኩ፣በቅርጻቅርጽና በድንጋይ የሚያመልኩ . . ሰዎች በዚህ ዓለም ላይ መኖራቸው በጣም አስገራሚ ነው። በእርግጠኝነት ለጥያቄዎቼ ምላሽ የሚሰጠኝ አምላክ አይጥ፣ጥንዚዛ፣ጣዖት ወይም ሌላ እንስሳ ሊሆን አይችልም።

- ስለዚህም መለኮታዊ ሃይማኖት ብቻ ስለመሆኑ እርግጠኛ ሆነሃል ማለት ነው?

- በትክክል ከመለኮታዊ ሃይማኖቶች ከአይሁዳዊነት፣ ከክርስትናና ከእስላም መካከል በአንዱ ውስጥ ብቻ ነው ማግኘት የሚቻለው . .

- የሚቀጥለው እርምጃህ ምድነው የሚሆነው?

- ከመለኮታዊ ሃይማኖቶች ጋር አንድ በአንድ መተዋወቅ ይሆናል። በአይሁዳዊነት እጀምራለሁ . . በነገራችን ላይ ወዳጄ ሃይማኖትህ ምንድነው?

- ምን ይሆናል ብለህ ነው የምትገምተው? ስሜ አደም ነው፣የሰው ልጆች ሁሉ አባት። የአባቴ ስም ደግሞ የነብያትና የሁሉም መለኮታዊ ሃይማኖቶች አባት ስም የሆነው ኢብራሂም ነው።

- እንዴት ማለት?

- አደም የመላው ሰው ዘር አባት ስም ነው። ኢብራሂም ደግሞ የነብያት አባት ስም ነው፣ሙሴ ኢየሱስና ሙሐመድም የኢብራሂም ልጆች ናቸው።

- አንተ ከነብያቱ መካከል ማንን ነው የምትከተለው?

- ሦስቱንም ሃይማኖቶች ለማወቅ አብረን ብንጓዝ ምን ይመስለሃል፣ምናልባት ሃማኖቴን እለውጥ ይሆናል!

- እንደ ባለቤቴ ካቶሊካዊ ትመስላለህ . . ኦ፣ምግቡ ደርሷል . . በዚህ ነገር ተጽእኖ ያሳደርክብኝ ይመስለኛል። የፍልስፍና ባሕሪ አንዳንዴ ነገሮችን ማቅለል ሳይሆን ማወሳሰብ ቢሆንም . . ይህን የማቅለል ፍልስፍናህን አዘውትሬ ስደጋግመው ነው ራሴን ያገኘሁት። እንግሊዛዊ ጠባያችን ሆኖ አንዳንዴ ነገሮችን ከማቅለል ይልቅ ማካበድና ማወሳሰብ ይቀናናል።

- ማቅለል፣ገርነት፣ፈገግታና ደስተኝነት ሁሌም የተያያዙ ቃላት ናቸው።

- በዚህ ልክ ደግሞ ማወሳሰብ፣ እርስ በርስ መቃረን፣ አስቸጋሪነት፣ደካማነትና መናጢነት እርስ በርሳቸው የተያያዙ ቃላት ናቸው . . አልነገርኩህም ሐኪም ቶም ወደ ቴልአቪቭ እንድሄድና አይሁዳዊነትን በቅርበት እንዳውቅ ሀሳብ አቅርቦልኛል። በዚህ ላይ ምን ትላለህ?

- በጣም ጥሩ ነው፣ወደ ቅድስት አገር ትጓዛለህ ማለት ነው !

- ካቶሊካዊ ነህ ብየህ የለም?

- ጉዞው አይሁዳዊነትን ብቻ ሳይሆን ሦስቱንም ሃይማኖቶች ለማወቅም ጠቃሚና አጋዥ ሊሆን ይችላል።

- ወደ ቴልአቪቭ እንደምሄድ ስነግራት ካትሪናም ልክ እንደዚሁ ነበር ያለችኝ።

- ይህን ለማለት የግድ ካቶሊካዊ መሆን የለብኝም። ይህ ሁሉም መለኮታዊ ሃይማኖቶች የሚስማሙበት ጉዳይ ነው . . አገሩ በርካታ የጦርነት ውሎዎችን ያስተናገደ ምድር ነው። ጉዞህ አይሁዳዊነትንና ሌሎቹንም በይበልጥ ለማወቅ በጣም ጠቀሜታ ይኖረዋል የሚል እምነት አለኝ። ያ ማለት ግን ስለ ሃይማኖቶቹ ማንበብን ይተካል ማለት አይደለም።

- ምን ማለት ነው?

- ለጉዞው ስንት ቀን ቀረህ?

- አራት ቀናት።

- እንድታነብ ነው ሃሳብ የማቀርበው፣እኔም ካንተ ጋር ስለ ትልቁ ሃይማኖት ስለ አይሁዳዊነት በብዛት አነባለሁ።

- አይሁዳዊነት ትልቅ ሃይማኖት ነው ! አንተ አይሁዳዊ ነህ እንዴ?

የሦስቱም መለኮታዊ ሃይማኖት ተከታዮች በሙሴ ያምናሉ፣ይህ ግን አይሁዳዊ ለመሆናቸው ማስረጃ አይሆንም። ያላንዳች ቅድመ ውሳኔ ለምን አናጠናቸውም፣ ምናልባት አይሁዳዊ ወይም ክርስቲያን አሊያም ሙስሊም ልሆን እችላለሁና ለኔ ሃይማኖት ምንነት አትቸገር !

- እስላምን ስታነሳ ትዝ አለኝ፣ይህ ከሕንድ እንዳመጣልህ የጠየከው የዑድ ሽቶ ነው።

- ዋጋው ስንት ነው?

- ኣይ፣በነጻ ነው፣ካንድ ሙስሊም በስጦታ የተበረከተልኝ ነው። ካትሪና እንዳስጠነቀቀችኝ ፈንጂ ተጠምዶበት ወይም ተመርዞ ከሆነ ግን እኔ ተጠያቂነት የለብኝም።

- ታዲያ ሽቶውን በምጠቀምበት ጊዜ እኔም አሸባሪ ልሆን ነው ማለት ነዋ?

- ሰሞኑን እዚህ ለንደን ውስጥ በሽብር ጥቃት ምክንያት አስፈሪ ቀናትን አሳልፈን በኋላ ግን ፍንዳታው የሽብርተኝነት ሳይሆን የወንጀል ፍንዳታ ነው ተባልን።

- ለምንድነው የሽብርተኝነት ሳይሆን የወንጀል ፍንዳታ የሆነው?

- አላውቅም ግን በጣም አስቂኝ ነገር ነው። ነገሩ ሕንድ ውስጥ አንዱ ሙስሊም ‹‹ሽብርተኛ ከናንተ ጋር የማይስማማና የማትፈልጉት ሰው ሁሉ ነው›› ያለኝ እውነት ሳይሆን አይቀርም አሰኝቶኛል።

- ሽብርተኝነት ሽብርተኝነት ነው፣ሃይማኖት የለውም፣አገር የለውም። የትኛውም ሃይማኖትም ሆነ አገር በሽብርተኝነት ሊፈረጅ አይችልም። በዕለታዊ ድርጊቶቻችን ውስጥ ለሚስቶቻችንና ወይም ለልጆቻችን በምናደርገው አያያዝ አንዳንዴ ሽብርተኞች መሆናችንን አላስተዋልክም? አገሮችም እንደዚሁ ሽብርተኝነትን የሚዋጉት ራሳቸው የአሸባሪነትን ስልት በመጠቀም ነው። የኃይል እርምጃ፣ሁከትና የጭካኔ ግድያ በማንም ይሁን በማን ቢፈጸም፣፣ከሰብአዊ አእምሮና ከሃይማኖት ሀሁ ጋር የሚጋጭ እኩይ ተግባር ነው !

- በሰሞኑ ፍንዳታ አንዳንድ ሙስሊሞች ሙስሊም በመሆናቸው ብቻ ያለ ኃጢአታቸው ስለ መታሰራቸው ጉዳይ የምትናገር ነው የሚመስለው።

- በትክክል፣ከፍንዳታው ሙሉ በሙሉ ነጻ መሆናቸው ቢረጋገጥም እስካሁንም ድረስ ብዙዎቹ እስር ቤት እየማቀቁ ነው። ታዲያ ይህ ሽብርተኝነት አይደለም ትላለህ? !

- ነው፣ግን ብዙ ጊዜ ሙስሊሞች አሸባሪዎች ናቸው ብዬ ለምን እንደማስብ አላውቅም።

- ይህ አዝማሚያ በጣም የተለመደ ነው፣እኔም አንተም የሽብር ሚዲያና የሽብር ፖለቲካ ኢምፓይሮች ሰለባዎች ነን።

- እንዴት ማለት? ምን ማለት ነው የፈለከው? !

- እነዚህ ኤምፓይሮች እያወቅንም ሆነ ልብ ሳንለው ለሌሎች ያለንን አመለካከትና አቋማችንን በፈለጉት መንገድ ይቀርጹታል። ወራሪዎች ተወራሪ ሕዝቦችን የሚመለከቱት መገደል የሚገባቸው አረመኔዎች አድርገው አይደለም ወይ? ! ሕዝቦች ሌላውን ሕዝብ የሚያዩት ገዳይ ወንጀለኞች አድርገው አይደለም ወይ?! ሃይማኖቶች ሌሎች ሃይማኖቶችን ገዳዮችና አሸባሪ ወንበዴዎች አድርገው አይደለም የሚመለከቱት? !

- ልክ ነህ፣ግን በጣም ስሜታዊ የሆንክ ትመስላለህ . . (ከዚያም ፈገግ ብሎ ቀጠለና) ፦ አንተ ሙስሊም ነህ እንዴ?

- እናማ አንተን ከነሬስቶራንቱ እንዳላፈነዳህ ጠንቀቅ በል!

- ውድ ወዳጄ ቀልዴን ነው።

- እኔም፣ብንሄድና እቤት ብታደርሰኝስ?

- በል እንሂድ።