ነቢዩ ሙሳ

ነቢዩ ሙሳ

እስራኤላውያን ከኢብራሂም u ሲወርድ ሲዋረድ በውርስ የደረሳቸውንና ከዝርያቸው መካከል በሚወለድ ልጅ እጅ የግብጽ ንጉሥ ጥፋት እንደሚከሰት በሚገልታ ትንቢት ላይ ይነጋገሩ ነበር። ይህ የብስራት ትንቢትም በእስራኤላውያን ዘንድ በስፋት የተሰራጨ ስለ ነበር በሹማምንቱ በኩል ነገሩ ወደ ፈርዖን ጆሮ ደረሰ። በዚህን ጊዜ ፈርዖን ትንቢቱን ለማክሸፍ ለእስራኤላውያን የሚወለድ ወንድ ልጅ ሁሉ እንዲገደል ትእዛዝ አስተላለፈ። እስራኤላውያንም ግብጽ ውስጥ የግፍና የሰቆቃ ሕይወት ይገፉ ነበር፦

{ፈርዖን በምድር ላይ ተንበጣረረ፤ነዋሪዎችዋንም የተከፋፈሉ ጓዶች አደረጋቸው፤ከነሱ ጭፍሮችን ያዳክማል፤ወንዶች ልጆቻቸውን በብዛት ያርዳል፤ሴቶቻቸውንም ይተዋል፤እርሱ ከሚያበላሹ ሰዎች ነበርና። }[አልቀሶስ፡4]

አላህ (ሱ.ወ.) ለግፉአኑ የእስራኤል ልጆች ጸጋውን መዘርጋት ፈለገ፦

{በነዚያም በምድር ውስጥ በተጨቆኑት ላይ ልንለግስ፤መሪዎችም ልናደርጋቸው፣ወራሾችም ልናደርጋቸው፣እንሻለን። ለነርሱም በምድር ላይ ልናስመች፣ፈርዖንንና ሃማንንም፣ሰራዊቶቻቸውንም፣ከነሱ ይፈሩት የነበሩትን ነገር ልናሳያቸው፣(እንሻለን)።}[አልቀሶስ፡5-6]

እየዞሩ እርጉዝ ሴቶችን ሁሉ የሚከታተሉና መች እንደሚወልዱ የሚያጣሩ ሠራተኞችንና አዋላጆችን እስከማሰማራት ድረስ ፈርዖን ከሙሳ ለመዳን የተሟላ ጥብቅ ጥንቃቄ ቢያደርግም፣ተቆጣጣሪዎቹም ወንድ ሕጻናትን እንደተወለዱ ወዲያውኑ ሲያርዱ ቢቆዩም፣አላህ (ሱ.ወ.) ግን ለፈርዖን ለሹሙና ለሰራዊቶቻቸው የፈሩትን ማሳየት ፈቃዱ ሆነ።

የሙሳ እናት በወለደች ጊዜም፦

{ወደ ሙሳም እናት፦ አጥቢው፤በርሱም ላይ በፈራሽ ጊዜ በባሕሩ ውስጥ ጣይው፤አትፍሪም፤አትዘኝም፤እኛ ወዳንቺ መላሾቹና ከመልክተኞቹም አድራጊዎቹ ነንና ማለትን አመለከትን።}[አልቀሶስ፡7]

እንዳይገድሉት ስለፈራች ሕፃኑን ሳጥን ውስጥ አድርጋው ወደ ወንዝ ጣለችው፦

{የፈርዖን ቤተሰቦችም (መጨረሻው) ለነርሱ ጠላት ፣ሐዘንም፣ይኾን ዘንድ አነሱት፤ፈርዖንና ሃማንም፣ሰራዊቶቻቸውም ኀጢአተኞች ነበሩ።}[አልቀሶስ፡8]

የፈርዖን ሚስት ልብም በሕጻኑ ሙሳ ፍቅር ተጠመደ፦

{የፈርዖንም ሚስት ለኔ የዓይኔ መርጊያ ነው፤ለአንተም፤አትግደሉት፤ሊጠቅመን ወይም ልጅ አድርገን ልንይዘው ይከጀላልና አለች፤እነርሱም (ፍጻሜውን) የማያውቁ ኾነው (አነሱት)።}[አልቀሶስ፡9]

የሙሳ እናት ግን፦

{የሙሳም እናት ልብ፣ባዶ ኾነ፤ከምእመናን ትኾን ዘንድ በልቧ ላይ ባላጠነከርን ኖሮ ልትገልጸው ቀርባ ነበር። ለእኅቱም ተከታተይው አለቻት፤እርሱንም እነሱ የማያውቁ ሲኾኑ በሩቅ ኾና አየችው።}[አልቀሶስ፡10-11] {(ወደናቱ ከመመለሱ) በፊትም አጥቢዎችን (መጥባትን) በርሱ ላይ እርም አደረግን፤(እኅቱ) ለናንተ የሚያሳድጉላችሁን፣እነርሱም ለርሱ ቅን አገልጋዮች የኾኑን ቤተሰቦች ላመልክታችሁን? አለችም። ወደናቱም፣ዓይንዋ እንድትረጋ፣እንዳታዝንም፣የአላህም የተስፋ ቃል እርግጥ መኾኑን እንድታውቅ፣መለስነው፤ግን አብዛኞቻቸው አያውቁም።}[አልቀሶስ፡12-13]

ሙሳም u በግፈኛው ንጉሥ በፈርዖን ቤት አደገ፦

{ብርታቱንም በደረሰና በተስተካከለ ጊዜ፣ጥበብንና ዕውቀትን ሰጠነው፤እንዲሁም መልካም ሠሪዎችን እንመነዳለን። ከተማይቱንም፣ሰዎችዋ በዝንጋቴ ጊዜ ላይ ኾነው ሳሉ ገባ፤በርሷም ውስጥ የሚጋደሉን ሁለት ሰዎች አገኘ፤ይህ ከወገኑ ነው፤ይህም ከጠላቱ ነው፤ያም ከወገኑ የኾነው ሰው፣በዚያ ከጠላቱ በኾነው ሰው ላይ እርዳታን ጠየቀው፤ሙሳም በጡጫ መታው፤ገደለውም፤ይህ ከሰይጣን ሥራ ነው፤እርሱ ግልጽ ጠላት ነውና፣አለ። ጌታዬ ሆይ! እኔ ነፍሴን በደልኩ፤ለኔም ማር አለ፤ለርሱም ምሕረት አደረገለት፤እርሱ መሓሪ፣አዛኝ ነውና። ጌታዬ ሆይ! በኔ ላይ በመለገስህ ይኹንብኝ (ከስሕተቴ እጸጸታለሁ)፤ለአመጠኞችም ፈጽሞ ረዳት አልኾንም፣አለ።}[አልቀሶስ፡14-17]

የራሱና የእስራኤላዊው ጠላት የሆነውን ግለሰብ ከገደለ በኋላ ግን፦

{በከተማይቱም ውስጥ ፈሪ፣የሚጠባበቅ ኾኖ አደረ፤በድንገትም ያ ትላንት እርዳታን የጠየቀው ሰው በጩኸት እርዳታን ይጠይቀዋል፤ሙሳ ለርሱ፦ አንተ በእርግጥ ግልጽ ጠማማ ነህ አለው። (ሙሳ) ያንን እርሱ ለሁለቱም ጠላት የኾነውን ሰው፣በኀይል ሊይዘው በፈለገም ጊዜ፣ሙሳ ሆይ! በትላንትናው ቀን ነፍስን እንደ ገደልክ፣ልትገድለኝ ትፈልጋለህን? በምድር ላይ ጨካኝ መኾንን እንጅ ሌላ አትፈልግም፤ከመልካም ሠሪዎችም መኾንን አትፈልግም፤አለው። ከከተማይቱም ዳርቻ አንድ ሰው እየሮጠ መጣ፤ሙሳ ሆይ! ሹማምንቶቹ ሊገድሉህ ባንተ ይመካከራሉና ውጣ፤እኔ ላንተ ከመካሪዎች ነኝና አለው። የፈራና የሚጠባበቅ ኾኖም ከርሷ ወጣ፤ጌታዬ ሆይ! ከበደለኞቹ ሕዝቦች አድነኝ አለ።}[አልቀሶስ፡18-21]

ግብጽን ለቆ ወደ መድየን አቅጣጫ አመራ፦

{ወደ መድየን አግጣጫ ፊቱን ባዞረ ጊዜም፣ጌታዬ ቀጥተኛውን መንገድ ሊመራኝ እከጅላለሁ አለ። ወደ መድየንም ውሃ በመጣ ጊዜ፣በርሱ ላይ ከሰዎች ጭፍሮችን (መንጋዎቻቸውን) የሚያጠጡ ኾነው አገኘ፤ከነሱ በታችም (ከውሃው መንጎቻቸውን) የሚከለክሉን ሁለት ሴቶች አገኘ፤ነገራችሁ ምንድን ነው? አላቸው፤እረኞቹ ሁሉ (መንጎቻቸውን) እስከሚመልሱ አናጠጣም፤አባታችንም ትልቅ ሽማግሌ ነው አሉት። ለሁለቱም አጠጣላቸው፤ከዚያም ወደ ጥላው ዘወር አለ፤ጌታዬ ሆይ! እኔ ከመልካም ነገር ወደኔ ለምታደርገው ፈላጊ ነኝ፣አለ።}[አልቀሶስ፡22-24]

ሁለቱ ሴቶች ሙሳ የሰራውን በጎ ሥራ ለአባታቸው ለነቢዩ ሹዐይብ u ተናገሩ። ሹዐይብም ሙሳን u ትጠራው ዘንድ አንደኛቱን ልጃቸውን ላኩ፦

{ከሁለቱ አንደኛይቱም ከሕፍረት ጋር የምትኼድ ኾና መጣችው፤አባቴ ለኛ ያጠጣህልንን ዋጋ ሊሰጥህ ይጠረሃል፣አለችው፤}[አልቀሶስ፡25]

ሙሳም [የአላህ ሰላም በሁለቱም ላይ ይሁን] ወደ ሹዐይብ መጡ።

{ወደርሱ በመጣና ወሬውን በርሱ ላይ በተረከለትም ጊዜ፣አትፍራ፤ከበደለኞቹ ሕዝቦች ድነሃል አለው።}[አልቀሶስ፡25]

ልጅቱ የሙሳን u ታማኝነት ባስተዋለች ጊዜ፦

{ከሁለቱ አንደኛይቱም አባቴ ሆይ! ቅጠረው፤ከቀጠርከው ሰው ሁሉ በላጩ፣ብርቱው፣ታማኙ፣ ነውና አለችው።}[አልቀሶስ፡26]

ሹዐይብም ለሙሳ [የአላህ ሰላም በሁለቱም ላይ ይሁን]

{ስምንትን ዓመታት ልታገለግለኝ፣እኔ ከነዚህ ሁለት ሴቶች ልጆቼ አንዲቱን ላጋባህ እሻለሁ፤ዐሥርን ብትሞላም ከአንተ ነው፤ባንተ ላይ ማስቸገርንም አልሻም፤አላህ የሻ እንደኾነ ከመልካሞቹ ሰዎች ኾኜ ታገኘኛለህ አለው። (ሙሳም) ይህ፣(ውለታ) በኔና ባንተ መካከል (ረጊ) ነው፤ከሁለቱ ጊዜያቶች ማንኛውንም ብፈጽም፣በኔ ላይ ወሰን ማለፍ የለም፤አላህም በምንለው ላይ ምስክር ነው አለ።}[አልቀሶስ፡27-28]

የተስማሙበትን የሥራ ጊዜ ካጠናቀቁ በኋላ ሙሳ u ቤተሰባቸውን ይዘው ተጓዙ፦

{ሙሳም ጊዜውን በጨረሰና ከቤተሰቦቹ ጋር በኼደ ጊዜ፣ከጡር ተራራ ጎን እሳትን አየ፤ለቤተሰቡ (እዚህ) ቆዩ፤እኔ እሳትን አየሁ፤ከርሷ ወሬን ወይም ትሞቁ ዘንድ ከእሳት ትንታግን አመጣላችኋለሁ አለ።}[አልቀሶስ፡29]

በዚህን ጊዜ አላህ (ሱ.ወ.) ወሕይ ላከባቸው፦

{በመጣትም ጊዜ፣ከሸለቆው ቀኝ ዳርቻ፣ከዛፊቱ በኩል በተባረከችው ስፍራ ውስጥ ሙሳ ሆይ! እኔ የዓለማት ጌታ አላህ ነኝ በማለት ተጣራ። በትርህንም ጣል (ተባለ)፤እንደ ትንሽ እባብ ስትስለከለክ ባያትም ጊዜ፣ወደ ኋላ ዞሮ ሸሸ፤አልተመለሰምም፤ሙሳ ሆይ! ተመለስ፤አትፍራም፤አንተ ከጥብቆቹ ነህና (ተባለም)። እጅህን በአንገትጌህ ውስጥ አግባ፤ያለ ነውር ነጭ ኾና ትወጣለችና፤ክንፍህንም ከፍርሃት (ለመዳን) ወዳንተ አጣብቅ፤እነዚህም ከጌታህ የኾኑ ወደ ፈርዖንና ወደ መኳንንቶቹ የሚደርሱ ሁለት አስረጅዎች ናቸው፤እነርሱ አመጠኞች ሕዝቦች ነበሩና።}[አልቀሶስ፡30-32]

ነቢዩ ሙሳ u ግን ቀደም ሲል በገደሉት ጠላታቸውና ባልተባ ምላሳቸው ምክንያት ፈርዖንን ፈሩ፦

{ {(ሙሳ) አለ፦ ጌታዬ ሆይ! እኔ ከነሱ ነፍስን ገድያለሁ፣ስለዚህ እንዳይገድሉኝ እፈራለሁ፤ወንድሜም ሃሩን እርሱ ምላሱ ከኔ የተባ ነው፤እውነተኛነቴንም የሚያረጋግጥልኝ ረዳት ኾኖ ከኔ ጋር ላከው፤እኔ ሊያስተባብሉኝ እፈራለሁና።}[አልቀሶስ፡33-34]

ወንድማቸው ሃሩንን ረዳታቸው ያደርግ ዘንድም አላህን (ሱ.ወ.) ለመኑ፦

{ከቤተሰቦቼም ለኔ ረዳትን አድርግልኝ፤ሃሩንን ወንድሜን። ኀይሌን በርሱ አበርታልኝ። በነገሬም አጋራው። በብዙ እናጠራህ ዘንድ። በብዙም እንድናወሳህ። አንተ በኛ ነገር ዐዋቂ ነህና። (አላህም) አለ፦ ሙሳ ሆይ! ልመናህን በእርግጥ ተሰጠህ።}[ጣሃ፡29-36]

ሙሳና ሃሩን ወደ ፈርዖን ሄደው አንድ አላህን ብቻ መግገዛትን፣በርሱ አለማጋራትን፣እስራኤላውያንን በፈለጉበት ቦታ አንድ አላህን ብቻ መግገዛት ይችሉ ዘንድ ከጭቆና አገዛዙ ነጻ መልቀቅን በተመለከተ የተላኩበትን የአላህን (ሱ.ወ.) መልእክት አደረሱት። ፈርዖንም በትእቢት ተወጥሮ በመኩራራት ሙሳን በንቀት ዓይን ተመለከተ። እንዲህም አለ፦

{(ፈርዖንም) አለ ፦ ልጅ ኾነህ በኛ ውስጥ አላሳደግንህምን? በኛ ውስጥም ከዕድሜህ ብዙ ዓመታትን አልተቀመጥክምን? ያችንም የሠራሃትን ሥራህን አልሠራህምን? አንተም ከውለታ ቢሶቹ ነህ (አለ)።}[አል ሹዐራ፡18-19]

ሙሳም u መልስ ሰጡት፦

{(ሙሳም) አለ፦ ያን ጊዜ እኔም ከተሳሳቱት ኾኜ ሠራኋት።}[አል ሹዐራ፡20]

ያን የፈጸምኩት የአላህ መልክት ሳይመጣልኝና ወሕይ ሳይገለጥልኝ በፊት ነው፣አሉት።

{በፈራኋችሁም ጊዜ ከናንተ ሸሸሁ፤ጌታየም ለኔ ጥበብን ሰጠኝ፤ከመልክተኞቹም አደረገኝ።}[አል ሹዐራ፡21]

በማሳደግና በመንከባከብ ስላደረገላቸው ውለታ ፈርዖን ሲመጻደቅ ሙሳ u መልስ ሰጡት።

{ይህችም፣የእስራኤልን ልጆች ባሪያ በማድረግህ በኔ ላይ የምትመጻደቅባት ጸጋ ናት።}[አል ሹዐራ፡22]

መላውን የእስራኤል ሕዝብ በባርነት ይዘህ ጉልበታቸውን በመበዝበዝና በመጨቆን ለዘመናት የሰቆቃ ሕይወት እንዲመሩ እያደረግህ፣ለኔ ለአንዱ እስራኤላዊ ብቻ በዋልከው ውለታ አትመጻደቅ፣አሉት። በመቀጠልም ሙሳ ላከኝ የሚሉት ጌታ አምላክ የቱ እንደሆነ ፈርዖን ጠየቃቸው።

{ፈርዖን አለ፦ (ላከኝ የምትለው) የዓለማትም ጌታ ምንድነው?}[አል ሹዐራ፡23]

አሳማኝ መልስም ተሰጠው፦

{(ሙሳ) ፦ የሰማያትና የምድር፣በመካከላቸውም ያለው ሁሉ ጌታ ነው፤የምታረጋግጡ ብትኾኑ (ነገሩ ይህ ነው)፤አለው።}[አል ሹዐራ፡24]

ፈርዖንም መሳለቅ ጀመረ።

{(ፈርዖንም) በዙሪያው ላሉት ሰዎች፦ አትሰሙምን? አለ።}[አል ሹዐራ፡25]

ሙሳም u ለማንም ቁብ ሳይሰጡ ጥሪያቸውን ቀጠሉ።

{(ሙሳ)፦ ጌታችሁና የመጀመሪያዎቹ አባቶቻችሁም ጌታ ነው አለው።}[አል ሹዐራ፡26]

ፈርዖን በትእቢቱ ገፋበት፦

{(ፈርዖን) ፦ ያ ወደናንት የላከው መልክተኛችሁ፣በእርግጥ ዕብድ ነው፤አለ።}[አል ሹዐራ፡27]

{(ሙሳ)፦ የምሥራቅና የምዕራብ፣በመካከላቸውም ያለው ነገር ሁሉ ጌታ ነው፣ታውቁ እንደ ኾናችሁ፣(እመኑበት) አለው።}[አል ሹዐራ፡28]

ከማስረጃ ከአመዛዛኝ አእምሮም ሆነ ከአመክዮ የተራቆተው አምባገነኑ ትእቢተኛ ገዥ ፈርዖን ማስፈራራት ጀመረ።

{(ፈርዖን)፦ ከኔ ሌላ አምላክን ብትይዝ በውነቱ ከእስረኞቹ አደርግሃለሁ አለ።}[አል ሹዐራ፡29]

በፈርዖን ሹፈትና በስላቁ ጥሪውን ያላቆሙት ሙሳ u፣በፈርዖን ማስፈራሪያም አልተበገሩም። መልስ ሰጡት፦

{(ሙሳ)፦ በግልጽ አስረጅ ብመጣህም እንኳ? አለው። እንግዲያውስ ከውነተኞች እንደ ኾንክ (አስረጁን) አምጣው አለ። በትሩንም ጣለ፤እርሷም ወዲያውኑ ግልጽ እባብ ኾነች። እጁንም አወጣ፤ወዲያውም እርሷ ለተመልካቾች (የምታበራ) ነጭ ኾነች።} [አል ሹዐራ፡30-33]

ሕዝቡ በሙሳ u እንዳያምን ፈርዖን ስጋት ላይ ወደቀ።

{(ፈርዖን) በዙሪያው ላሉት መማክርት፣ይህ በእርግጥ ዐዋቂ ድግምተኛ ነው፤አለ። ከምድራችሁ በድግምቱ ሊያወጣችሁ ይፈልጋልና ምንን ታዛላችሁ? (አላቸው)። አሉት፦ እርሱን ወንድሙንም አቆይና በየከተሞቹ፣ሰብሳቢዎችን ላክ። በጣም ዐዋቂ ድግምተኞችን ሁሉ ያመጡልሃልና።}[አል ሹዐራ፡34-37]

ፈርዖን ሁሉንም አሳማኝ ማስረጃዎች ካየ በኋላም ማስተባበሉንና ክህደቱን በእብሪት ቀጠለ።

{ታምራቶቻችንንም ሁሏንም (ለፈርዖን) በእርግጥ አሳየነው፤አስተባበለም፤እምቢም አለ። ከምድራችን በድግምትህ ልታወጣን መጣህብን? ሙሳ ሆይ! አለ። መሰሉንም ድግምት እናመጣብሃለን፤በኛና ባንተም መካከል እኛም አንተም የማንጥሰው የኾነ ቀጠሮን፣በመካከለኛ ስፍራ አድርግልን፣አለ። ቀጠሯችሁ በማጌጫው ቀን ሰዎቹም በረፋድ በሚሰበሰቡበት ነው አለ። ፈርዖንም ዞረ፤ተንኮሉንም ሰበሰበ፤ከዚያም መጣ።}[ጣሃ፡56-60]

ሙሳ u በሕዝቡ ላይ የአላህ (ሱ.ወ.) ቅጣት እንዳይወርድ ፈሩላቸው።

{ሙሳ ለነሱ አላቸው ፦ ወዮላችሁ በአላህ ላይ ውሸትን አትቅጠፉ፤በቅጣት ያጠፋችኋልና፤የቀጠፈም ሰው በእርግጥ አፈረ።}[ጣሃ፡61]

የፈርዖን ድግምተኞች በሀሳብ ተለያዩ፤አንዳንዶቻቸው ይህ የድግምተኛ ጠንቋይ ንግግር አይደለም አሉ።

{(ድግምተኞቹ) በመካከላቸውም ነገራቸውን ተጨቃጨቁ፤ውይይትንም ደበቁ።}[ጣሃ፡62]

ይሁን እንጂ አብዛኞቻቸው ከአቋማቸው ተመለሱና፦

{እነዚህ በእርግጥ ደጋሚዎች ናቸው፤ከምድራችሁ በድግምታቸው ሊያወጧችሁ፣በላጭቱንም መንገዳችሁን ሊያስወግዱባችሁ ይሻሉ አሉ። ተንኮላችሁንም አጠንክሩ፤ከዚያም ተሰልፋችሁ ኑ፤ዛሬ ያሸነፈም ሰው ምኞቱን አገኘ (ተባባሉ)።›[ጣሃ፡63-64] {ሙሳ ሆይ! ወይ ትጥላለህ፣ወይም በመጀመሪያ የምንጥል እንኾናለን፣(ምረጥ) አሉ። አይደለም ጣሉ፣አላቸው፤ወዲያውም ገመዶቻቸውና ዘንጎቻቸው ከድግምታቸው የተነሳ እነርሱ የሚሮጡ (እባቦች) ኾነው ወደርሱ ተመለሱ።}[ጣሃ፡65-66]

ሙሳም u ሕዝቡ በድግምተኛ ጠንቋዮች እንዳይፈታትን ሰጉ።

{ሙሳም በነፍሱ ውስጥ ፍርሃትን አሳደረ።}[ጣሃ፡67]

ከአላህ (ሱ.ወ.) ዘንድም ትእዛዝ መጣላቸው፦

{፦ አትፍራ አንተ የበላዩ አንተ ነህና አልነው። በቀኝ እጅህ ያለችውንም በትር በጣል፤ያንን የሠሩትን ትውጣለችና፤ያ የሠሩት ሁሉ የድግምተኛ ተንኮል ነውና፤ድግምተኛ በመጣበት ስፍራ ሁሉ አይቀናውም (አልን)።}[ጣሃ፡68-69] {ወደ ሙሳም፦ በትርህን ጣል ስንል ላክን፤(ጣላትም) ወዲያውኑም የሚቀጣጥፉትን (ማታለያ) ትውጣለች። እውነቱም ተገለጸ፤ይሠሩት የነበሩትም (ድግምት) ተበላሸ።}[አልአዕራፍ፡117-118]

ያልተጠበቀ ታምር ተከሰተ፦

{እዚያ ዘንድ ተሸነፉም፤ወራዶችም ኾነው ተመለሱ። ድግምተኞቹም ሰጋጆች ኾነው ወደቁ። አሉ፦ በዓለማት ጌታ አመንን፤በሙሳና በሃሩን ጌታ።}[አልአዕራፍ፡119-122] {ድግምተኞቹም ሰጋጆች ኾነው ወደቁ፤በሃሩንና በሙሳ ጌታ አመንን፣አሉ።}[ጣሃ፡70]

የፈርዖን ምላሽም የጅላጅል ማስፈራሪያ ብቻ ነበር።

{(ፈርዖንም) ለናንተ ሳልፈቅድላችሁ በፊት ለርሱ አመናችሁን? እርሱ በእርግጥ ያ ድግምትን ያስተማራችሁ ትልቃችሁ ነው፤እጆቻችሁንና እግሮቻችሁን በማናጋት (ግራና ቀኝን በማፈራረቅ) እቆርጣችኋለሁ፤በዘምባባም ግንዶች ላይ እሰቅላችኋለሁ፤}[ጣሃ፡71]

የድግምተኞቹ ምላሽ ለፈርዖን ዱብ እዳ ከመሆኑም በላይ እምነት በምእመናን ላይ የሚያሳድረውን ከባድ ተጽእኖም የሚያብራራ ነበር።

{(እነርሱም) አሉ፦ ጉዳት የለብንም፤እኛ ወደ ጌታችን ተመላሾች ነን። እኛ የምእመናን መጀመሪያ በመኾናችን፣ጌታችን ኀጢአቶቻችንን ለኛ ሊምር እንከጅላለን።}[አልሹዐራ፡50-51]

ፈርዖን ምእመናኑን ማሰቃየት ሲቀጥል አላህ (ሱ.ወ.) እርሱንና ከርሱ ጋር ያሉትን ከሓዲዎች ቀጣቸው።

{የፈርዖንንም ቤተሰቦች፣እንዲገሠጹ በድርቅ ዓመታትና ከፍሬዎችም በመቀነስ በእርግጥ ያዝናቸው። ደጊቱም ነገር (ምቾት) በመጣችላቸው ጊዜ፣ይህች ለኛ (ተገቢ) ናት፣ይላሉ፤ክፋትም ብታገኛቸው በሙሳና አብረውት ባሉት ገደቢስነት ያመካኛሉ፤ንቁ! ገደቢስነታቸው አላህ ዘንድ ብቻ ነው፤ግን አብዛኛዎቻቸው አያውቁም።}[አል አዕራፍ፡130-131]

አላመኑም፤ከክሕደታቸውም ተጸጽተው አልተመለሱም።

{(ለሙሳም)፦ በማንኛይቱም ታምር በርሷ ልትደግምብን ብትመጣብን፣እኛ ለአንተ የምናምንልህ አይደለንም አሉ፤ወዲያውም የውሃን ማጥለቅለቅ፣አንበጣንም፣ነቀዝንም፣እንቁራሪቶችንም፣ደምንም፣የተለያዩ ታምራት ሲኾኑ፣በነሱ ላይ ላክን፤ኮሩም፤ተንኮለኞችም ሕዝቦች ነበሩ።}[አል አዕራፍ፡132-133]

ቅጣቱ ሲጸናባቸው፦

{በነርሱም ላይ ቅጣቱ በወደቀባቸው ጊዜ፦ ሙሳ ሆይ! ጌታህን ላንተ ቃል ኪዳን በገባልህ ነገር ለኛ ለምንልን፤ከኛ ቅጣቱን ብታነሳልን ለአንተ በእርግጥ እናምንልሃለን፤የእስራኤልንም ልጆች ከአንተ ጋር በእርግጥ እንለቃለን፤አሉ። እነርሱም ደራሾቹ እኾኑበት ጊዜ ድረስ ቅጣትን ከነሱ ላይ ባነሳን ጊዜ፣ወዲያውኑ እነርሱ ቃላቸውን ያፈርሳሉ።}[አል አዕራፍ፡134-135]

የገቡትን ቃል ሲያፈርሱና ያሉትን ሳይፈጽሙ ሲቀሩም አላህ (ሱ.ወ.) ተበቀላቸው።

{እነርሱ በታምራታችን ስለ አስተባበሉም፣ከርሷ ዘንጊዎች ስለኾኑም፤ከነሱ ተበቀልን፤በባሕርም ውስጥ አሰጠምናቸው።}[አል አዕራፍ፡136]

የግብጽ ሰዎች ንጉሣቸውን ፈርዖንን በመከተልና የአላህን (ሱ.ወ.) ነቢይና መልክተኛውን ሙሳን u በመጻረር፣በክሕደታቸው በትዕቢታቸውና በእምቢታቸው በገፉ ጊዜ አላህ (ሱ.ወ.) የግብጽን ሕዝብ ኃያልና አስገዳጅ የሆኑ አስገራሚና አስደማሚ ታምራቶቹን አሳያቸው። ይህ ሁሉ ሆኖ ግን ሰዎቹ ከትዕቢታቸው የሚገቱና ከጥመታቸው የሚመለሱ አልሆኑም። ከፈርዖን ሕዝብ በጣም ጥቂቶች ብቻ እንጅ አላመኑም። ሁሉም ድግምተኞችና ሁሉም የእስራኤል ሕዝብ ያመኑ ሲሆን፣የፈርዖንን ግፍና ጭካኔ በመፍራት እምነታቸውን ይደብቁ ነበር። አላህን እንዲገዙባቸውና በሚታዘዙ ጊዜ ለጉዞ ዝግጁ ሆነው አንዱ የሌላውን ቤት ለይቶ አውቀው ይጠብቁ ዘንድ፣የተከታዮቻቸው ቤቶች ከፈርዖን ተከታዮች ቤቶች የተለዩ እንዲሆኑ አላህ (ሱ.ወ.) ለሙሳና ለሃሩን [የአላህ ሰላም በሁለቱም ላይ ይሁን] አሳወቀ።

{ወደ ሙሳና ወደ ወንድሙ፦ ለሕዝቦቻችሁ በምስር ቤቶችን ሥሩ፤ቤቶቻችሁንም መስገጃ አድርጉ፤ሶላትንም በደንቡ ስገዱ፤(ለሙሳ) ምእመናኖቹንም አብስር ስንል ላክን።}[ዩኑስ፡87]

ከዚያም አላህ (ሱ.ወ.) ለባሪያው ለሙሳ u ወሕይ አስተላለፈ፦

{ወደ ሙሳም ፦ ባሮቼን ይዘህ ሌሊት ኺድ፣እናንተ የሚከተሏችሁ ናችሁና ስንል ላክን።}[አል ሹዐራ፡52]

የፈርዖን መልስ ግን የሚከተለው ነበር፦

{፦ ፈርዖንም በየከተሞቹ ሰብሳቢዎችን (እንዲህ ሲል) ላከ፤ ፦ እነዚህ ጥቂቶች ጭፍሮች ናቸው። እነርሱም ለኛ አስቆጪዎች ናቸው። እኛም ብዙዎች ጥንቁቆች ነን፤(አለ)።}[አል ሹዐራ፡53-56]

የአላህ (ሱ.ወ.) ፈቃድ ግን ሌላ ሆነ፦

{አወጣናቸውም፤ከአትክልቶችና ከምንጮች፤ከድልቦችም፣ከመልካም መቀመጫዎችም። እንደዚሁ፣ለእስራኤል ልጆች አወረስናትም።}[አል ሹራ፡51]

ፈርዖንና ሰራዊቱ የእስራኤል ልጆችን ይዘው ለመመለስ ተከተሏቸው።

{ፀሐይዋ ስትወጣም፣ተከተሉዋቸው።}[አል ሹዐራ፡60]

ሲደርሱባቸውም፦

{ሁለቱ ጭፍሮችም በተያዩ ጊዜ፣የሙሳ ጓዶች እኛ (የፈርዖን ሰዎች) የሚደርሱብን ነን፣አሉ።}[አል ሹዐራ፡61]

የአላህ መልክተኛ የሙሳ u ምላሽ ግን በአላህ ላይ ሙሉ በሙሉ በመተማመን፣እርሱን በማወቅና በርሱ ብቻ በመመካት የተሞላ ነበር።

{(ሙሳ)፦ ተውዉ!ጌታዬ ከኔ ጋር ነው፤በእርግጥ ይመራኛል፣አለ።}[አል ሹዐራ፡62]

የአላህ መመሪያና እዝነቱ ለሙሳና ለተከታዮቻቸው ከተፍ አለ፦

{ወደ ሙሳም ባሕሩን በበትርህ ምታው ስንል ላክንበት፣(መታውና) ተከፈለም፤ክፍሉም ሁሉ እንደ ታላቅ ጋራ ኾነ። እዚያም ዘንድ ሌሎችን አቀረብን። ሙሳንና ከርሱ ጋር ያሉትንም ሰዎች፣ሁሉንም አዳን። ከዚያም ሌሎቹን አሰጠምን። በዚህ ውስጥ ታላቅ ታምር አለበት፤አብዛኞቻቸውም አማኞች አልነበሩም። ጌታህም፣እርሱ አሸናፊው፣አዛኙ ነው።}[አል ሹዐራ፡63-68]

በዚህ አስፈሪ ወቅትም አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ አለ፦

{የእስራኤልንም ልጆች፣ባሕሩን አሳለፍናቸው፤ፈርዖንና ሰራዊቱም ወሰን ለማለፍና ለመበደል ተከተሏቸው፤}[ዩኑስ፡90]

እዚህ ላይም ፈርዖን ሞትና መስጠም አይቀሬ መሆኑን አረጋገጠ፦

{መስጠምም ባገኘው ጊዜ ፦ አመንኩ፤እነሆ ከዚያ የእስራኤል ልጆች በርሱ ከአመኑበት በስተቀር ሌላ አምላክ የለም፣እኔም ከታዛዦቹ ነኝ አለ።}[ዩኑስ፡90]

ፈርዖን መማጸን ቢጀምርም ሞት ተረጋግጦበታልና አሁን ጊዜው በጣም ዘግይቷል፦

{፦ ከአሁን በፊት በእርግጥ ያመጥክ፣ከአጥፊዎችም የነበርክ ስትኾን፣አሁን? (ተባለ)።}[ዩኑስ፡91]

ጠላታቸውን በማስጠም አላህ (ሱ.ወ.) በእስራኤል ልጆች ላይ ጸጋውን አሟላ። ባሕሩን አቋርጠው ከተሸገሩ በኋላ ግን፦

{የእስራኤልንም ልጆች ባሕሩን አሻገርናቸው፤ለነርሱ በኾኑ ጣዖታት (መግገዛት) ላይ በሚዘወትሩ ሕዝቦች ላይ አለፉም፤ሙሳ ሆይ! ለነርሱ (ለሰዎቹ) አማልክት እንዳሏቸው ሁሉ ለኛም አምላክን አድርግልን፣አሉት፤}[አል አዕራፍ፡138]

አላህ ከፈርዖንና ከሰራዊቱ ካዳናቸውና በተውሒድ ካከበራቸው በኋላ ግን የጅል ማይማዊ ጥያቄ አቀረቡ፦

{እናንተ የምትሳሳቱ ሕዝቦች ናችሁ፣አላቸው። እነዚህ፣እነርሱ በውስጡ ያሉበት ነገር ጠፊ ነው፣ይሠሩት የነበሩትም ብልሹ ነው (አላቸው)።}[አል አዕራፍ፡139]

ከዚያም ሙሳ u ለጌታቸው ቀጠሮ ሄዱ።

{ሙሳንም ሠላሳ ሌሊት (ሊጾምና ልናነጋግረው) ቀጠርነው፤በዐሥርም (ሌሊት) ሞላናት፤የጌታውም ቀጠሮ አርባ ሌሊት ሲኾን ተፈጸመ፤ሙሳም ለወንድሙ ሃሩን፦ በሕዝቦቼ ላይ ተተካኝ፤አሳምርም፣የአጥፊዎችንም መንገድ አትከተል አለው።}[አል አዕራፍ፡142]

አላህ (ሱ.ወ.) ሙሳን u አነጋገረ፤በንግግሩና በመልክቱም ልዩ አደረጋቸው።

{(አላህም) አለው፦ ሙሳ ሆይ! እኔ በመልክቶቼና በማናገሬ በሰዎች ላይ (በዘመንህ ካሉት) መረጥኩህ፤የሰጠሁህንም ያዝ፤ከአመስጋኞቹም ኹን።}[አል አዕራፍ፡144]

በግሣጼና ሕግጋቱን በያዘው ተውራትም አላህ (ሱ.ወ.) ጸጋውን ለነቢዩ ሙሳ u ዘረጋ።

{ለርሱም በሰሌዳዎቹ ላይ ከነገሩ ሁሉ ግሣጼንና ለነገሩም ሁሉ መማብራራትን ጻፍንለት፤(አልንም)፦ በብርታትም ያዛት፣ሕዝቦችህንም በመልካሟ እንዲይዙ እዘዛቸው፤የአመጠኞቹን አገር በእርግጥ አሳያችኋለሁ።}[አል አዕራፍ፡145]

ሙሳ u ቀጠሮውን ካጠናቀቁና ጌታቸው ተውራትን ሰጥቷቸው ወደ ሕዝባቸው ተመልሰው በመጡ ጊዜ፦

{የሙሳም ሕዝቦች፣ከርሱ (መኼድ) በኋላ፣ከጌጦቻቸው ወይፈንን፣አካልን፣ለርሱ ማግሳት ያለውን፣(አምላክ አድርገው) ያዙ፤እርሱ የማያናግራቸው፣መንገድንም የማይመራቸው መኾኑን አይመለከቱምን? (አምላክ አድርገው) ያዙት፤በዳዮችም ኾኑ። በተጸጸቱና እነሱም በእርግጥ የተሳሳቱ መኾናቸውን ባዩ ጊዜ፦ ጌታችን ባያዝንልንና ባይምረን በእርግጥ ከከሳሪዎቹ እንኾናለን አሉ።}[አል አዕራፍ፡148-149]

ክስተቱ ለሙሳ u በጣም አስበርጋጊ ነበር።

{ሙሳም እየተቆጣና እያዘነ ወደ ሕዝቦቹ በተመለሰ ጊዜ ፦ ከኔ በኋላ የተተካችሁኝ ነገር ከፋ! የጌታችሁን ትእዛዝ ተቻኮላችሁን? አላቸው፤ሰሌዳዎቹንም ጣላቸው፤የወንድሙንም ራስ (ጸጉር) ወደርሱ የሚጎትተው ሲኾን ያዘ፤(ወንድሙም)፦ የናቴ ልጅ ሆይ! ሕዝቦቹ ናቁኝ፤ሊገድሉኝም ተቃረቡ፤ስለዚህ በኔ ጠላቶችን አታስደስትብኝ፤ከአመጠኞች ሕዝቦችም ጋር አታድርገኝ አለው። (ሙሳም)፦ ጌታዬ ሆይ! ለእኔም ለወንድሜም ማር፤በእዝነትህም ውስጥ አግባን፤አንተም ከአዛኞች ሁሉ ይበልጥ አዛኝ ነህ፣አለ።}[አል አዕራፍ፡150-151]

በመቀጠልም ጥጃውን ቀርጾ የሠራውን ሳምራዊ ሙሳ ጠየቁት፦

{(ሙሳ)፦ ሳምራዊው ሆይ! ነገርህም ምንድነው? አለ።}[ጣሃ፡95]

ሳምራዊውም መለሰላቸው፦

{ያላዩትን ነገር (የጂብሪል ባዝራ ፈረስ የረገጠችው መለምለሙን) አየሁ፤ከመልክተኛው (ከፈረሱ ኮቴ) ዱካም ጭብጥ ዐፈርን ዘገንኩ፤(በቅርጹ ላይ) ጣልኳትም፤እንደዚሁም ነፍሴ ሸለመችልኝ፣አለ።}[ጣሃ፡96]

የሙሳ u ምላሽ ግን በማጋራትና በጣዖት አምልኮ ላይ ቁርጥ ያለ ብርቱ ምላሽ ነበር፦

{አለው፦ኺድ ላንተም በሕይወትህ (ለአየኸው ሰው ሁሉ) መነካካት የለም ማለት አለህ፤ለአንተም ፈጽሞ የማትጥሰው (አላህ የማይጥሰው የማይቀር) ቀጠሮ አለህ፤ወደዚያም በርሱ ላይ ተገዢው ኾነህ ወደ ቆየህበት አምላክህ ተመልከት፤በእርግጥ እናቃጥለዋለን፤ከዚያም በባሕሩ ውስጥ መበተንን እንበትነዋለን። ጌታችሁ ያ ከርሱ በቀር ሌላ አምላክ የሌለ የኾነው አላህ ብቻ ነው፤ዕውቀቱ ነገርን ሁሉ አዳረሰ።}[ጣሃ፡97-98]

ከዚያም ሰሌዳዎቹን ከተቀበሉ በኋላ ሙሳ u ወደ ቅድስት አገር አቀኑ።

{ከሙሳም፣ቁጣው በበረደ ጊዜ፣ሰሌዳዎቹን፣በግልባጫቸው ውስጥ ለነዚያ እነርሱ ጌታቸውን የሚፈሩ ለኾኑት መምሪያና እዝነት ያለባቸው ሲኾኑ ያዘ።}[አል አዕራፍ፡154]

ከእስራኤል ልጆች መካከል ከፊሉ በተውራት ውስጥ የተካተቱትን ሕግጋት ለመቀበል ፍላጎት ስላልነበራቸው፣አላህ (ሱ.ወ.) ላይ ተራራ ነቅሎ በላያቸው ላይ እንደ ጥላ አንዣበበባቸው።

{የጡርን ተራራ ነቅለን ከበላያቸው እንደ ጥላ ኾኖ በአነሳነውና እርሱም በነሱ ላይ ወዳቂ መኾኑን ባረጋገጡ ጊዜ (አስታውስ)፤የሰጠናችሁን በብርታት ያዙ፤ትጠነቀቁም ዘንድ በውስጡ ያለውን ተገንዘቡ (አልን)።}[አል አዕራፍ፡171]

መጽሐፉ በመመሪያና በእዝነት የተሞላ ቢሆንም ተራራው እንዳይወድቅባቸው በመፍራት ብቻ ተቀበሉት። የእስራኤል ልጆች ጥመትና ዝንፈት ለነቢዩ ሙሳ u አስቸጋሪ እንደሆነ ቀጠለ። አንዴ ነፍስ ገደሉ። ሟቹ ሀብታም የሆነ እስራኤላዊ ሰው ሲሆን የወንድሙ ልጅ ነበር ማታ አርዶ የገደለው! ገዳዩ ባለመታወቁ ሁሉም እርስ በርስ መወነጃጀል ያዙ። ጉዳዩን ለነቢዩ ሙሳ አቀረቡና {እውነት የአላህ ነቢይ ከሆንክ ገዳዩ ማን እንደሆነ ጌታህን ጠይቀህ ንገረን!} በማለት ስነምግባር በጎደለው ሁኔታ የትእቢት ጥያቄ አቀረቡ። አላህ (ሱ.ወ.) የእስራኤል ልጆችን አንድ ላም አርደው አንዱን ብልት በመውሰድ የሟቹን በድን እንዲመቱ ንገራቸው፣እኔ በፈቃዴ ሕያው አደርገውና ማን እንደ ገደለው ይናገራል፣ሲል ሙሳን አዘዛቸው። ይህን በማስመልከት አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{ነፍስንም በገደላችሁና በርሷም (ገዳይ) በተከራከራችሁ ጊዜ (አስታውስ)፤አላህም ትደብቁት የነበራችሁትን ሁሉ ገላጭ ነው። (በድኑን) በከፊሏም ምቱት አልን (መቱትምና ተነሳ፤ገዳዩንም ተናገረና ሞተ)፤እንደዚሁ አላህ ሙታንን ያስነሳል፤ታውቁም ዘንድ ታምራቶችን ያሳያችኋል።}[አል በቀራህ፡72-73]

ሙሳም ላም እረዱ አሏቸው። ማንኛይቱንም ላም አምጥተው ማረድ በቂያቸው ነበር። በትእቢታቸው ምክንያት ነገሩን አወሳሰቡ። አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{፦ አላህ ላምን እንድታርዱ ያዛችኋል ባለ ጊዜ (አስታውሱ)፤መሳለቂያ አድርገህ ትይዘናለህን? አሉት፤- ከተሳላቂዎች ከመኾን በአላህ እጠበቃለሁ፣ አላቸው።}[አል በቀራህ፡67]

ሰዎቹም እንዲህ ሲሉ መለሱ፦

{ለኛ ጌታህን ጠይቅልን፤እርሷ ምን እንደ ኾነች (ዕድሜዋን) ያብራራልን አሉ፤}[አል በቀራህ፡68]

በራሳቸው ላይ አጠበቁና አላህም (ሱ.ወ.) አጠበቀባቸው፦

{እርሱ እርሷ ያላረጀች፣ጥጃም ያልኾነች . . ናት ይላችኋል . . አላቸው።}[አል በቀራህ፡68]

ያላረጀችና ትንሽ ጥጃም ያልሆነች መሆኗ ተነገራቸው።

{እርሱ እርሷ ያላረጀች፣ጥጃም ያልኾነች፣በዚህ መካከል ልከኛ የኾነች ጊደር ናት ይላችኋል፤የታዘዛችሁትንም ሥሩ፣አላቸው።}[አል በቀራህ፡68]

በራሳቸው ላይ በማጥበቅ ነገሩን አወሳሰቡት፦

{ለኛ ጌታህን ጠይቅልን፤መልኳ ምን እንደ ኾነ ለኛ ይግለጽልን አሉ፤}[አል በቀራህ፡69]

አላህ (ሱ.ወ.) ግን የቆዳ ቀለም አልጠየቃቸውም፣የተለየ የላም መለያም መስፈርት አላደረገባቸውም ነበር፦

{እርሱ እርሷ መልኳ ደማቅ ተመልካቾችን የምታስደስት ዳለቻ ላም ናት፣ይላችኋል አላቸው።}[አል በቀራህ፡69]

ዝግ ስብሰባ ካደረጉ በኋላ ተመልሰው ወደ ሙሳ u መጡ፦

{ለኛ ጌታህን ጠይቅልን፤እርሷ ምን እንደ ኾነች ግለጽልን፤ከብቶች በኛ ላይ ተመሳሰሉብን፤እኛም አላህ የሻ እንደ ኾነ በእርግጥ ተመሪዎች ነን አሉ።}[አል በቀራህ፡70]

ሙሳም መልስ ሰጧቸው፦

{እርሱ እርሷ ያልተገራች፣ምድርን (በማረስ) የማታስነሳ፣እርሻንም የማታጠጣ፣(ከነውር) የተጠበቀች፣ልዩ ምልክት የሌለባት ናት፣ይላችኋል፣አላቸው፤አሁን በትክክል መጣህ አሉ፤ሊሠሩ ያልተቃረቡም ሲኾኑ አረዱዋት (የጠናቸው ኾነው እየከበዳቸው አረዷት)።}[አል በቀራህ፡71]

የእስራኤልን ከተሞችና መንደሮች አንድ በአንድ ካዳረሱ በኋላ በብዙ ችግርና ስቃይ የተባለችውን ላም አግኝተው ማድረጉ እየከበዳቸው አረዷት። በገዳዩ ማንነት ላይ የተወዛገቡበትን ሟች ሬሳ በታረደችው ላም አንዱ ብልት ሲመቱም በአላህ ፈቃድ ሕያው ሆኖ ተነሳ። ሙሳ u ማን ገደለህ? ብለው ሲጠይቁትም ይህኛው ነው ብሎ አሳያቸው።

{(በድኑን) በከፊሏም ምቱት አልን (መቱትምና ተነሳ፤ገዳዩንም ተናገረና ሞተ)፤እንደዚሁ አላህ ሙታንን ያስነሳል፤ታውቁም ዘንድ ታምራቶችን ያሳያችኋል።}[አል በቀራህ፡73]

ወደ ቅድስት አገር በሚደርሱበት ጊዜም ኃያላን የሆኑ ሕዝቦች አጋጠሟቸው፦

{ሙሳም ለሕዝቦቹ ባለ ጊዜ (አስታውስ)፣፦ ሕዝቦቼ ሆይ! የአላህን ጸጋ በውስጣችሁ ነቢያትን ባደረገና ነገሥታትን ባደረጋችሁ፣ከዓለማትም ለአንድም ያልሰጠውን ችሮታ በሰጣችሁ ጊዜ (በናንተ ላይ ያደረገውን ጸጋ) ፦ ሕዝቦቼ ሆይ! ያችን አላህ ለእናንተ ያደረጋትን የተቀደሰችውን መሬት ግቡ፤ወደ ኋላችሁም አትመለሱ፤ከሳሪዎች ኾናችሁ ትመለሳላችሁና። ሙሳ ሆይ! በርሷ ውስጥ ኀያላን ሕዝቦች አልሉ፤ከርስዋም እስከሚወጡ ድረስ፣እኛ ፈጽሞ አንገባትም፣ከርስዋም ቢወጡ እኛ ገቢዎች ነን አሉ። ›[አል ማእዳህ፡20-22] {ሙሳ ሆይ! በውስጧ እስካሉ ድረስ እኛ ፈጽሞ ምንጊዜም አንገባትም፤ስለዚህ ኺድ፤አንተና ጌታህ ተጋደሉም፤እኛ እዚህ ተቀማጮች ነን አሉ።}[አል ማእዳህ፡24]

አላህም በስንፍናቸውና በድክመታቸው ወቅሷቸው፣ ጅሃድን በመተዋቸውና ነብያቸውን በመጻረራቸው ምክንያት ለረዥም ዘመን በምድረበዳ ባዝነው እንዲቀሩ በማድረግ ቀጣቸው። ሙሳም እንዲህ አሉ፦

{፦ ጌታየ ሆይ! እኔ ራሴንና ወንድሜን በቀር (ላስገድድ) አልችልም፣በእናና በአመጠኞቹም ሕዝቦች መካከል ለይ፣ አለ።}[አል ማእዳህ፡25]

አላህም (ሱ.ወ.) ጸሎታቸውን ተቀበለ፦

{፦ እርሷም (የተቀደሰችው መሬት) በእነሱ ላይ አርባ ዓመት እርም ናት፤በምድረበዳ ይንከራተታሉ። በአመጠኞችም ሕዝቦች ላይ አትዘን፣አለው።}[አል ማእዳህ፡26]

መድረሻቸው የት እንደሆነ ሳያውቁ ያለ ምንም ዓላማና ግብ ቀን ከሌሊት፣ጧትና ማታም ዝም ብለው ይጓዙም ነበር። (15)