ስርቆቱ . .

ስርቆቱ . .

ስርቆቱ . . (1)

- ካኽ ለጉዞ ዝግጁ ነኝ . . እንድትረዳልኝ የምፈልገው ነገር ቢኖር ጉዳዩ የመርሕ እንጂ የጥቅም አለመሆኑን ብቻ ነው።

- መልካም . . የምትገባው ግዴታ ግን ይኖራል!

- ግዴታ?! የምን ግዴታ?

- ለሥራ አመራር ቦርዱ ደብዳቤ ጽፈህ የሥራ መልቀቂያ ጥያቄህን መሰረዝህንና የቀረበልህን ጉዞ መቀበልህን ታሳውቃቸዋለህ።

- ለምን?

- ያስነሳኸው አውሎ ነፋስ የፈጠረው ችግር እንዲያበቃ።

- ጥሩ፣ ችግር የለውም። ጉዞው መቼ ነው?

- በአጭር ጊዜ ውስጥ ቦታ ሊያዝልህ ይችላል፤ግን ወዴት ለመሄድ ነው የመረጥከው?

- ወደ ግብጽ ለመሄድ ተስማምቻለሁ።

- እህህ . . አሁንም በደስተኝነት መንገድ ፍለጋው ላይ የጸናህ ትመስላለህ! ከአፍታ በኋላ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊው ትኬቶቹን ይዞልህ ይመጣል፤የመታደል ጉዞ ይሁንልህ።

- አመሰግናለሁ።

ጆርጅ ወደራሱ ቢሮ ሄዶ አስር ደቂቃ ባልሞላ ጊዜ ውስጥ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊው ከተፍ አለ . .

- ለግብጽ ጉዞህ ለተነገወዲያ ኦኬ አስደርጌልሃለሁ። ይመቸሃል?

- ጥድፊያው ለምንድነው?

- እኔ እንጃ፣ይህ የካኽ ፍላጎት ነው። ለማንኛውም መጓዝህ ከኛ ጋር መስራትን ትቀጥላለህ ማለት በመሆኑ አስደስቶኛል።

- አይቀጥልም ያለው ማነው?

- ካኽ ከሥራ ሊያስወጣህ እንደሚፈልግ በሠራተኛው መካከል በስፋት ሲወራ ነበር።

- ቀደም ሲል ፈርቼ ነበር። አሁን ግን አንዱ ሌላውን የሚያባርር ከሆነ እርሱን የማባርረው እኔ ነኝ የሚል እምነት ለምን እንዳሳደርኩ አላውቅም። ለበጎ ስሜትህ አመሰግናለሁ።

- ካኽ ወረቀቶቹን በኢሜይል እንዲልክልህ አስታውሰው ብሎኛል።

- እኔን በጥርጣሬ ዓይን ማየት ጀምሯል፤ከአፍታ በኋላ የፈለገውን ኢሜይል እልካለሁ።

- ሰነዶቹና መረጃዎቹ ተሟልተውና ተቀናጅተው ዛሬ ይደርሱሃል። ጉዳዩን በድንገት ስለ ሰማን ገና አልተዘጋጀንበትም ነበር።

- እጠብቃለሁ . . አመሰግናለሁ።

- ጆርጅ እንደ ወዳጅ የምመክርህ ነገር ቢኖር ካኽን አንድትጠንቀቀው ነው፤ፍቀድልኝ ልሂድ።

- አመሰግናለሁ፣መልካም ስነምግባርና በመርህ መጽናት፤ ማሴርንና ማጭበርበርን ድል እንደሚያደርጉ እርግጠኛ ሁን።

ስለ ጉዞው ለኣደም ለመንገር ጆርጅ የስልክ መነጋገሪያውን አነሳ . .

- ሃሎ . . አንተ ግብጻዊው፣ወደ አገራችሁ ልጓዝ ትኬቴን ኦኬ አስደርጌአለሁ።

- እንኳን ደስ ያለህ . . በእውነት ትልቅ የምስራች ነው። ወንድማቸው አቀባበል እንዲያደርግልህ እንዲደውሉለት ለሸይኽ ባስምም እነግራለሁ፤እንደኔ ወንድም አይደለም እንግሊዝኛን አቀላጥፎ ይናገራል። ጉዞው መቼ ነው?

- ተነገ ወዲያ ነው፤ጉዳዩ ከጠበቅሁት በላይ አጣዳፊ ሳይሆን አልቀረም።

- ሆስፒታል ውስጥ ብቻዬን ስለ ሆንኩ ዛሬ ወደኔ መምጣት ትችላለህ?

- የሚመችህ ከሆነ ከአፍታ በኋላ እመጣለሁ፤አሁኑኑ እንቀሳቀሳለሁ።

- በጣም ይመቸኛል . . እጠብቀሃለሁ።

ጆርጅ ወደ ሆስፒታሉ ደረሰ። ኣደምን አልጋው ላይ ሆኖ ሲያነብ አገኘው . .

- ሰላም፣በንባብ የተጠመድክ ትመስላለህ፣ምንድነው የምታነበው?

- የአላህን መጽሐፍ ቁርኣንን ነው የማነበው።

- ከዚህ በፊት አላነበብከውም ነበር?

- በጣም ብዙ ጊዜ አንብቤዋለሁ፤በየቀኑ ማንበብ እወድለሁ።

- በየቀኑ?! አይሰለቻችሁም?!

- አዎ በየቀኑ የተቻለንን ያህል እናነበዋለን፤በዚህም ለዛውን እናጣጥማለን። የዒሳ [የአላህ ሰላም በርሳቸው ላይ ይወረድ] ታምር በአላህ ፈቃድ ድዳ ሆኖ የተፈጠረውን ሰውና ለምጻምን ማዳን እንደ ሆነ ሁሉ፣የሙሐመድ ታምር ደግሞ ይህ ዘላለማዊ ሕያው መጽሐፍ ቁርኣን ነው።

- ዘላለማዊ ሕያው ስትል ምን ማለትህ ነው?

- ከመዛባትና ከመለዋወጥ የመጠበቁን ኃላፊነት አላህ ራሱ የወሰደው መሆኑን መግለጼ ነው። የሚከተለውን አንቀጽ በቁርኣኑ ትርጉም ውስጥ አላነበብክም ፦{እኛ ቁርኣንን እኛው አወረድነው፤እኛም ለርሱ ጠባቂዎቹ ነን።} [አልሒጅር፡9] . . ስለ እውነት . . ይህን ስታነብ ታምራታዊነቱ አይሰማህም?

- እውነቱን ለመናገር . . ትርጉሙን እያነበብኩ ሳለሁ ትርጉሙን ሳይሆን በኦሪጂናል ቋንቋው ምነው ባነበብኩት ብዬ ተመኘሁ። ትርጉሙን እያነበብኩም በአያሌ ጉዳዮች ላይ እኔን በተለይ የሚያናግረኝ ሆኖ ነው የሚሰማኝ።

- አንተን በይበልጥ የሚያናግሩ ርእሰ ጉዳዮችን አውቃቸዋለሁ።

- እንዴት አወቅህ?

- የአላህ አንድነት (ተውሒድ)፣ስሞቹና ባህርያቱ፣ኃያልነቱ፣ርህሩህነቱና ወዳድነቱ . . ማንኛውንም ሰው በከፍተኛ ደረጃ ጠልቀው የሚሰሙት ናቸው። ይህን ለመንገር ትንቢት ማወቅ አያስፈልገኝም።

- ኦህ፣እውነትህን ነው። በተጨማሪም እስላም ዓለማዊና መንፈሳዊ ሕይወትን ማጣጣሙና ልዩ የሆነ መንፈሳዊነቱ በጣም ከሚማርኩኝ ነገሮች መካከል ናቸው።

- እስላም የሰውን ልጅ ሕይወት በሁሉም ጎኖቹ የተሟላ እንዲሆን ያደርጋል። ዓለማዊ ኑሮን ፈተው ምናኔ፣ምንኩስናም ሆነ ባህታዊነት፣ከፈጣሪ አምላክ መራቅም የለበትም። የልቦና ፍጹምነት እስካለ ድረስ እስላም ሕይወትን በሙሉ አምልኮተ አላህ (ዕባዳ) አድርጎ ይመለከታል።

- ለማንኛውም ተነገወዲያ ወደ ካይሮ መጓዜ ነውና ምን ትመክረኛለህ?

- እህህ፣የዐባይን ውሃ እንድትጠጣ።

- የዐባይን ውሃ መጠጣትም እስላም ውስጥ አምልኮተ እግዚአብሔር ነው ትላላችሁ እንዴ?

- እህህ፣አይደለም እየቀለድኩብህ ነው። በኛ በግብጻውያን ዘንድ ከዐባይ ውሃ የጠጣ ሰው ወደዚያ መመለሱ አይቀሬ ነው ተብሎ ይተረታል፣በአገሩ ውበትና ለሕዝቡ ደግነት ሲባል ማለታቸው ነው።

- ከአገር ሁሉ ላንተ እጅግ ተወዳጇ ግብጽ ናት!

- ያለ ምንም ጥርጥር ግብጽን እጅግ በጣም አብዝቼ እወዳታለሁ፤ወደዚያ የምመለስበትን ቀንም እናፍቃለሁ። ከሁሉም በላይ የምወደው አገር ግን መካና መዲናን ነው።

- ይገርማል! ለምንድነው?

- የተወዳጁና ተፈቃሪው ነብይ የሙሐመድ [የአላህ እዝነትና ሰላም በርሳቸው ላይ ይወረድ] አገር በመሆናቸው።

- እኛ ኢየሱስን አዳኛችን አድርገን እንደምንቆጥረው ነብያችሁ ሙሐመድን አዳኛችሁ አድርጋችሁ ትወስዳላችሁ?

- የአዳኝነት እሳቤ ከእስላማዊ እምነት ጋር ፈጼሞ ሊጣጣም የማይችል እሳቤ ነው። ዒሳ [የአላህ ሰላም በርሳቸው ላይ ይወረድ] ከአላህ የተላኩ መልክተኛ ነብይ ናቸው። ሙሐመድም [የአላህ እዝነትና ሰላም በርሳቸው ላይ ይወረድ] እንዲሁ ከአላህ የተላኩ መልክተኛ ነብይ ናቸው። በመሆኑም በማመኑ ረገድ አንዱን የአላህ ነብይ ከሌላው የአላህ ነብይ አንለይም። እኛ በሁሉም የአላህ ነብያትና መልክተኞች እናምናለን። በኛ ዘንድ ማንኛውንም የአላህ ነብይ የዘለፈ ወይም ክብሩን የነካ ሰው ከሃይማኖት ጎራ ያፈነገጠ ከሃዲ ነው።

- የአይሁድ ነብይ የሆነውን ሙሳ ወይም የክርስቲያኖች ነብይ የሆነውን ኢየሱስን ቢወርፍና ቢያንቋሽሽ እንኳ?

- አዎ፣ቁርኣን ውስጥ የሚከተለውን የአላህ ቃል አላነበብክም ፦{ . . በአንድም መካከል የማንለይ ስንኾን . . }[ [አልበቀራ፡136]

- አንብቤአለሁ . . ቁርአን ውስጥ ልቤን በአድናቆት ከሞሉት አንዱ ይህ ነው። እናንተ ሙሴን፣ኢየሱስን፣ማርየምን፣ከተካታዮቻቸው በበለጠ ታከብራላችሁ። ሁለት ነገሮችን አስታወስከኝ ፦ አንደኛ ግብጻዊው ሰውየ ለካትሪና የሰጠውና{ለኢየሱስ ያለኝ ታላቅ ፍቅር ወደ እስላም መራኝ} የሚለውን በቬንዙዌላዊው ጸሐፊ የተጻፈውን መጽሐፍ፣ሁለተኛ በብሉይ ኪዳን ውስጥ የተጠቀሱ ነብያትን።

- ሁሉም ነብዮች የአላህን አንድነት በማረጋገጥ ለርሱ ብቻ አምልኮ እንዲደረግ ለማስተማር ነው የተላኩት። ይሁን እንጂ በሃይማኖቶች ላይ የደረሰው የመዛባትና የመበረዝ ሁኔታ ባእድ አምልኮ (ሽርክ) እንዲገባባቸው አደረገ።

- ይቅርታ አድርግልኝ እና የራሳችንን ሃይማኖት አንተ አታስተምረንም። ከአይሁዶች ይበልጥ ስለ አይሁዳዊነት፣ከክርስቲያኖችም ይልቅ ስለ ክርስትና የምታውቅ አትሆንም።

- ልክ ነህ። ምናልባት አይሁዶች ከኔ ይበልጥ ያሁኑን ሃይማኖታቸውን፣ክርስቲያኖችም እንዲሁ አሁን ያለውን ሃይማኖታቸውን ከኔ ይበልጥ ያውቁ ይሆናል። ይሁን እንጂ ከአላህ ጋር ሌሎች ባዕድ አማልክት መኖራቸው ግን አእምሮም ሆነ እውነተኛ ሃይማኖት ሊቀበለው የማይችል ነገር ነው።

- እንዴት?

- አእምሮን በተመለከተ አላህ ስለ ምክንያታዊ አስረጅ የሚከተለውን ብሏል ፦{በሁለቱ (በሰማያትና በምደር) ውስጥ ከአላህ ሌላ አማልክት በነበሩ ኖሮ በተበላሹ ነበር፤የዐርሹ ጌታ አላህም ከሚሉት ሁሉ ጠራ።} [አል አንቢያ፡22] ዩኒቨርስ ሁለትና ከዚያ በላይ አቀናባሪዎች ወይም ጌቶች ቢኖሩት ኖሮ ስለሚጋጩና እርስ በርስ ስለሚናቆሩ ሥርዓቱ ሙሉ በሙሉ በተናጋና ውጥንቅጡ በወጣ ነበር። አንዱ አንድ ነገር ሲፈልግ ሌላው ሲቃወም የሁለቱም እቅድ እውን መሆን አይችልም። በሁሉም ነገሮች ላይ መስማማታቸውም የማይታሰብ ነው። ስለዚህም ያለ ምንም ተቀናቃኝና ተቃውሞ የፈለገውን የሚያደርግና እቅዱን የሚያስፈጽም አንድ ብቸኛ ኃያል አድራጊ አምላክ የግድ መኖር አለበት። እሱም አሸናፊው ጌታ አላህ ብቻ ነው። ለዚህ ነው አላህ እንዲህ ያለው ፦{አላህ ምንም ልጅን አልያዘም (አልወለደም)፤ከርሱም ጋር አንድም አምላክ የለም፤ያን ጊዜ (ሌላ አምላክ በነበረ) አምላክ ሁሉ በፈጠረው ነገር በተለየ ነበር፤ከፊላቸው በከፊሉ ላይ በላቀ ነበር፤አላህ ከሚመጥኑት ሁሉ ጠራ።} [አልሙእሚኑን፡91]

- ክርስትናን የሚቃረንና ሙሉ በሙሉ ከሥር የሚንድው ቢሆንም ድንቅ ፍልስፍናዊ ሎጂክ ነው!

- ፍልስፍናዊ ሳይሆን መለኮታዊ ነው። ነብዩ ዒሳ [የአላህ ሰላም በርሳቸው ላይ ይወረድ] የጠራ ተውሒድ ይዘው የመጡ በመሆናቸው፣ጣዖታዊነትን እና ባዕድ አምልኮን እንጂ ክርስትናንም አይንድም። ነብዩ ዩሱፍ [የአላህ ሰላም በርሳቸው ላይ ይወረድ] ሁለቱን የእስር ቤት ጓደኞቻቸውን የጠየቁትን ጥያቄ እንድጠይቅህ ፍቀድልኝ ፦{(የእስር ቤት ጓደኞቼ ሆይ!) የተለያዩ (ከብር ከወርቅ ከእንጨት የተሰሩ) አምላኮች ይሻላሉን ወይስ አሸናፊው አንዱ አላህ? ከርሱ ሌላ እናንተና አባቶቻችሁ (አማልክት ብላችሁ) የጠራችኋቸውን ስሞች እንጅ አትግገዙም፤አላህ በርሷ ምንም አስረጅ አላወረደም፣ፍርዱ የአላህ እንጅ የሌላ አይደለም፤እርሱን እንጅ ሌላን እንዳትግገዙ አዟል፤ይህ ትክክለኛው ሃይማኖት ነው፤ግን አብዛኞቹ ሰዎች አያውቁም።} [[ዩሱፍ፡39-40] ከተለያዩ ባዕድ አማልክትና ከብቸኛው እውነተኛ አምላክ ከአላህ የትኛውን ትመርጣለህ?!

 

- አላህ በዚህ ምንም አስረጅ አላወረደም የምትለው ግን እንዴት ነው?! አዲስ ኪዳን የኢየሱስን አምላክነት በሚናገሩ ጥቅሶች የተሞላ ነው!

- ካቀረብኩልህ ጥያቄ የሸሸህ ከመሆኑም ጋር ውይይታችንን እንቀጥላለን። አዲስ ኪዳን በስህተት የተሞላ መሆኑን ከኔ ይበልጥ አንተ ታውቃለህ። አንዳንድ የአዲስ ኪዳን ቅጂዎችም የአላህን አንድነት የሚናገሩ መሆናቸውን ከኔ በላይ አንተ ታውቃለህ። ሌላው ቀርቶ ከተራ ምክንያት ብንነሳ እንኳ፣እርስ በርስ ሊቃረኑና ሊጋጩ የሚችሉ ከመሆናቸው አንጻር ዩኒቨርስና ስርዓቱ የሚፋለስና የሚበላሽ በመሆኑ ሁለት አማልክት መኖራቸውን አእምሮ በጀ ብሎ እንዴት መቀበል እንደሚችል አላውቅም። አላህ ይህን በማስመልከት እንዲህ ብሏል ፦{በሁለቱ (በሰማያትና በምድር) ውስጥ ከአላህ ሌላ አማልክት በነበሩ ኖሮ በተበላሹ ነበር፤} [አል አንቢያ፡22]{አላህ ምንም ልጅን አልያዘም (አልወለደም)፤ከርሱም ጋር አንድም አምላክ የለም፤ያን ጊዜ (ሌላ አምላክ በነበረ) አምላክ ሁሉ በፈጠረው ነገር በተለየ ነበር፤ከፊላቸው በከፊሉ ላይ በላቀ ነበር፤} [አል ሙእሚኑን፡91]

- ይህ በጣም ትልቅ ጉዳይ ነው። በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያኖች የሚገኙ ሥዕሎችን፣ቅርጻቅርጽና ምስሎችን አምርሬ እጠላለሁ። አንድ ዓይነት ባዕድ አምልኮና የጣዖታዊነት መገለጫ መሆናቸው ይሰማኛል። የመጣሁት ግን ይህን ለመነጋገር አይደለም!

- እስላም ውስጥ እንደ የአላህ አንድነት (ተውሒድ) ውበት፣አርኪነት፣አስደሳችነትና የሕሊና ሰላም አጎናጻፊነት ያለ የሚወደድ ነገር የለም።

- አስደሳችነቱ! አርኪነቱ! የሕሊና ሰላም አጎናጻፊነቱ!

- አዎ፣በአላህ ማጋራትና ባዕድ አምልኮ ልብን ጨምድዶ በመያዝ የሕሊና ሰላም ማጣትን ያስከትላል። የሚከተሉትን አንቀጾች አላነበብክም ፦{እነዚያ ያመኑና እምነታቸውን በበደል ያልቀላቀሉ፣እነዚያ ለነርሱ ጸጥታ አላቸው፤እነሱም የተመሩ ናቸው፤} [አል አንዓም፡82]{(እነሱም) እነዚያ ያመኑ፣ልቦቻቸውም አላህን በማውሳት የሚረኩ ናቸው፤ንቁ አላህን በማውሳት ልቦች ይረካሉ።} [አል ረዕድ፡28]{ከግሣጼም የዞረ ሰው ለርሱ ጠባብ ኑሮ አልለው፤በትንሣኤም ቀን ዕውር ኾኖ እንቀሰቅሰዋለን።}[ጣሃ፡124] . . ለዚህ አለመምጣትህን አውቃለሁ! ለማንኛውም አራዝሜብህ ይሆናልና ይቅርታ እጠይቃለሁ፤የጠየቅኸው ግን አንተ ነህ።

- ይህን ርእስ ከመዝጋታችን በፊት ቁርኣንን ሳነብ ብዙ ጊዜ አእምሮዬ ውስጥ ሲመላለስ የነበረውን ጥያቄ ልጠይቅህ እፈልጋለሁ። በመጨረሻው የቁርኣን አንቀጽ አንዳንድ ሰዎች በትንሣኤ ቀን ዓይነ ስውራን ሆነው እንደሚቀሰቀሱ ተወስቷል፤ይህ ጭካኔ አይመስልም?!

- አላህ ጥራትና ልቅና የተገባው ይሁንና ቁርኣን አላህን በኃያልነት እና በልዕልና በሚገልጹ፣ቸር፣ርህሩህ፣መሓሪ ይቅር ባይ፣ለጋስና አመስጋኝ . . መሆኑን፣ውብና የመጠቁ መልካም ስሞችና ባህርያት ያሉት መሆኑን በሚገልጹ አንቀጾች የተሞላ ነው። የውበትና የወዳድነት ባህርያት እንዳሉት ሁሉ የኃያልነትና የልዕልና ባህርያትም አሉት። አላህ እንዲህ ብሏል ፦{የግርማና የመከበር ባለቤት የኾነው ጌታህ ስም ተባረከ።} [አል ረሕማን፡78]

- ምናልባት ይህ ወደ አእምሮዬ የመጣው ብሉይ ኪዳን ውስጥ የሰፈሩትንና ለግድያ፣ለዘረፋና ለጭካኔ ሥራ የሚያዙ ጥቅሶችን ሁሌ ስለማስታውስ ሊሆን ይችላል።

- አዎ ይህ አንዱ ምክንያት ነው፤እኔ የምጨምረው ሌላ ምክንያት አለ። ያም ክርስቲያኖች በኢየሱስ መገደል የመዳናቸውን ሀሳብ የለመዱት በመሆኑ በትንሣኤ ቀን የሚቀጣውና ገሀነም የሚገባው የምህረት ምስክር ወረቀቱን ከቤተክርስቲያን የመግዛት አቅም የሌለው ደሃ ብቻ ነው ብለው ማሰባቸው ነው።

- ማጥቃት ጀመርክ። ካቶሊኮች እና ኦርቶዶክሶች ዘንድ እንዳለው እኛ ፕሮቴስታንቶች ዘንድ ለሽያጭ የሚቀርቡ የምህረት ማስገኛ ሰነዶች የሉንም። በእርግጥ በኢየሱስ መሰቀል የኛ መዳን እምነት ግን ሁላችንም ዘንድ አለ።

- አንተ እንዳልከው የመዳን እሳቤ ድምዳሜ በሁሉም ጎኖቹ፣ዒሳ [የአላህ ሰላም በርሳቸው ላይ ይወረድ] ሞተው ቤዛ የሆኑለት በመሆኑ ሁሉም ሰው ከኃጢአት ነጻ ሆነዋል የሚል ነው። ይህ ደግሞ የፍርድ ቀንን ፋይዳ ቢስ ከማድረጉ በተጨማሪ በጎ ነገርና ትእዛዛትን መፈጸምም ሆነ አለመፈጸምን ትርጉም የለሽ ያደርጋል። ኢየሱስ አንዴ ከኃጢአት ነጻ ስላደረገ ጽድቅ ሥራ ለምኔ ያሰኛል። እናም ይህ ሁሉ የእግዚአብሔርን ትእዛዛት ለመጣስና ለመርህ ሳይሆን ለጥቅም መስራትን የሚያበረታታ አይመስልህም?

- ሊሆን ይችላል። መርህ ስትል ካኽንና የመስሪያ ቤትህን ጉዳይ አስታወስከኝ፤ተነገ ወዲያ ወደ አገራችሁ ወደ ካይሮ መብረሬ ነውና ምን ዓይነት ዝግጅት እንዳደርግ ሀሳብ ታቀርባለህ?

- ከደወልክልኝ በኋላ ደውየ ስነግራቸው ከአንድ ሰዓት ያህል በኋላ እደርሳለሁ ስላሉኝ ሸይኽ ባስም አሁን መምጫቸው ነው ብዬ እገምታለሁ። ወንድማቸው እዚያ ካንተ ጋር ይሆናል። ከመጓዝህ በፊት ሁሉንም ነገር እንዲያመቻችልህ የምትፈልገውን ሁሉ ካንተ መስማት ይፈልጋሉ፤በምትፈልገው ነገር ሁሉ ለመተባበር ሁላችንም ዝግጁዎች ነን።

- እህህ፣ ለምን?!

- አልገባኝም!

- ለምንድነው የምትተባበሩኝ?! እኔን በማገልገላችሁ ምን ትጠቀማላችሁ?! ለጥያቄው ይቅርታ አድርግልኝ፣ግን ሁሌ ወደ አእምሮዬ ስለሚመጣ ነው።

- አንተ ወዳጄ በመሆንህ በተቻለኝ መንገድ አገለግለሃለሁ። ሸይኽ ባስም ደግሞ ወዳጄ በመሆናቸው ለኔ ሲሉ ይተባበሩሃል። ለጊዜው ማቆየት የምፈልገው ሌላ ምክንያትም ይኖራል።

- ይቅርታ አድርግልኝና ሌላውን ምክንያት ልትነግረኝ አትችልም?

- ግልጽ ልሁንልህና . . እኔና እሳቸውም ምናልባት ትሰልም ይሆናል የሚል ተስፋ ቋጥረናል። በኛ ሃይማኖት አንድን ሰው በአላህ በማመንና እስላምን በመቀበል እንዲታደል ማድረግ ከምርጥ የአምልኮተ አላህ ተግባራት እንደ አንዱ ይቆጠራል።

- ኣደም ይቅር በለኝና እኔ እንድሰልም ከፍተኛ ጉጉት ቢኖርህም ፈጽሞ የምሰልም አይመስለኝም። በመሆኑም እስላምን በማስተዋወቅም ሆነ እኔን በማገልገል በከንቱ አትድከሙ እላችኋለሁ።

- ለኛ አትፍራ፣አንተ ባትሰልም እንኳ በማሰባችንና ጥረት በማድረጋችን ብቻ እኛ ወሮታውን ከአላህ ዘንድ እናገኛለን። የማቀርብልህ አገልግሎት ካለ ለወዳጅነትህ ስል ነውና በዚህም ከአላህ ምንዳ አገኛለሁ። ሰዎችን ማገልገልና መጥቀምም እንዲሁ ከታላላቅ የአምኮልተ አላህ ተግባራት አንዱ ነው። ከዚህ ሁሉ ጋር ግን አላህ መልካሙን ነገር የሻለትን ሰው ልቡን ለእስላም ክፍት ያደርግለታል የሚል እምነት አለኝ። አንተ አስተዋይ አእምሮና ቀና መንፈስ ያለህ ሰው በመሆንህ እስላምን እንደምትቀበልም ጠንካራ አምነት አለኝ።

- ማን ያቃል ሊሆን ይችላል፤ግን አይመስለኝም። በዚህ እንደማትከፋ ግን ተስፋዬ ነው፤ለመሆኑ ዘይቤህ ከበፊቱ ለምን ተለወጠ?

- ምን ማለትህ ነው?

- ስለ ሃማኖትህም ሆነ ስለ ቁርኣን ምንም ነገር አታነሳልኝም ነበር፤አሁን ግን ሙሉውን ጊዜ ስለዚሁ ብቻ ትናገራለህ። በኔ ስትሳለቅና ስትሸነግለኝ ነበር?

- ሁሉንም ሃይማኖቶች እንደምትተውና ወደ እስላም እንደምትደርስ እርግጠኛ ነበርኩ። ወደ እስላም በሚያደርስህ መንገድ ላይ ስትጓዝ ስለነበረ ለምን ላቋርጥህ? በአንዴ እንጂ ሀሳቤን አልለወጥኩም!

- መቼ ነበር?

- ታመህ ሳለህ ኦፕራሲዮኑ ሳይደረግልህ በፊት።

- ለምን?!

- ግልጽ ለመሆን ወደጄ ጀነት ውስጥ የኔ ባልደረባ እንዲሆን ስለምፈልግ እንዳትሞት ሰግቼ ነው . . ሸይኽ ባስም ይኸው መጡ፣ሸይኽ እንኳን ደህና መጡ።

- አሰላሙ ዐለይኩም ወረሕመቱሏህ ወበረካቱህ።

- ወዐለይኩሙ ሰላም ወረሕመቱሏህ ወበረካቱህ።

ጆርጅ በመገረም መንፈስ፦

- እንኳን ደህና መጡ፣የተለዋወጣችሁት አባባል ምንድነው?

- የኛ የሙስሊሞቹ ሰላምታ ነው። አንዱ ለሌላው የሚያደርግ ጸሎት ነው፣ከቁሳዊና መንፈሳዊ እንከኖች ሁሉ እንዲጠብቀው አላህን መለመን ነው። ቁሳዊ ሰላም የአካል የክብርና የንብረት ደህንነት ሲሆን፣መንፈሳዊው ደህንነት ደግሞ ሃይማኖትን ከእንከንና ከጉድለት ማዳን ነው። ከዚያም የአላህን እዝነትና በረከቱን መለመን ነው። ሃይማኖታችን የሠላምና የመተዛዘን ሃይማኖት ነው።

- በድጋሜ ወደ ሃይማኖት ውይይቱ ልትመልሱኝ ነው! እኔ ነገ መንገደኛ ነኝና ምን ዓይነት ፕሮግራም እንዲኖረኝ ነው ሀሳብ የምታቀርቡት?

- የፈለከውን ነገር። ወንድሜ እዚያ ስለሆነ የምትፈልገውን ሁሉ ያመቻችልሃል።

- እዚያ ሄጄ ስለማከናውናቸው ሥራዎች እስካሁን ያወቅሁት ነገር የለም። በኢሜይል ተልኮልኝ ሊሆን ይችላል ብዬ እገምታለሁ። ከመደበኛ ተልእኮዬ ውጭ የራሴ የግል ጉብኝት እንዲኖረኝ ስለምፈልግ የሚጎበኙ ቦታዎችንና ሌሎች ጉዳዮችንም እንድትነግሩኝ እፈልጋለሁ።

- ምን መጎብኘት ነው ምትፈልገው?

- ፒራሚዶችን፣የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያንና አንዳንዳንድ መሪዎቿን፣በተጨማሪም ሙስሊም የሃይማኖት ምሁራንንም ማግኘት እፈልጋለሁ።

- የጠቅስካቸው ነገሮች ሁሉ በጣም ቀላል ናቸው፤በደንብ ስለነገርኩት ወንድሜ ሁሉንም ያመቻችልሃል። በተጨማሪ ግን ውሳኔው ያንተ ሆኖ አንዳንድ ተራ ዜጎችንም አግኝተህ ቀርበህ ብታናግራቸው መልካም ነው የሚል ሀሳብ አለኝ።

- በጣም ጥሩና አስፈላጊ ጉዳይ ነው . . የምታቀርቡልኝ ይህ የማስጎብኝት አገልግሎት ወጭ ምን ያህል ይሆናል?

- እኛ የቱሪስት አስጎብኚ ኩባንያ አይደለንም። እዚያ የሚጠየቀውን የቱሪስት አገልግሎት ክፍያ አንተ ራስህ ትከፍላለህ። ወንድሜን በተመለከተ ግን የእንግዳ መስተንግዶ አገልግሎት ነው፤እንግዳን ተቀብሎ ማስተናገድ እያንዳንዱ ሙስሊም እንዲፈጽም የሚፈለግ የአላህ አምልኮ አካል ነው።

- ሁሉም ሙስሊሞች ይህንን ያደርጋሉ?

- እህህ፣በእርግጥ ሁሉም አይደሉም።

ኣደም ቀና ብሎ እየቀለደበት . .

- ከሌቦችና ከኪስ አውላቂዎች ራስህን ጠብቅ። መቼም ፍጹም የሆነ ተምሳሌታዊ ማህበረሰብ በፈላስፎቹ አእምሮና በተምኔታዊ ዓለማቸው እንጂ በዚህ ዓለም ላይ የለምና ከአባይ ጠንቋች፣ከአምታታዎችና ከሌሎቹም ተጠንቀቅ።

- እስላም ለመልካም ስነምግባር ጥሪ አያደርግም እንዴ?!

- ነብዩ [የአላህ እዝነትና ሰላም በርሳቸው ላይ ይወረድ] {የተላክሁት መልካም ስነምግባራትን ምሉእ ለማድረግ ነው} እንዳሉት ሁሉ መልካም ጸባይና ምሉእ ስነምግባር ማስፈን የተልእኮአቸው መሰረት ነው። ሙስሊሞች ለእስላም ይበልጥ ተገዥ በሆኑ ቁጥር ለመልካም ስነምግባራትም ይበልጥ ተገዥ ይሆናሉ። ጥሩ ስነምግባርና መልካም ጸባያት ከርሳቸው መላክ በፊትም ነበሩ፣እሳቸው የመጡት ግን የመጠቁና የተሟሉ ሊያደርጓቸው ነው። እያዘን አገራችን በኢኮኖሚም ሆነ በተቋማት ደካማና ኋላ ቀር ስለሆነች ጥንቃቄ አድርግ ማለት ፈልገን ነው።

ባስም ቢዝነስ ካርድ አውጥቶ እጁን ዘረጋ . .

- እንካ ይህ የወንድሜን የተሟላ መረጃ የያዘ ካርዱ ነው። የመድረሻ ሰዓትህን ጠቅሰህ ኢሜይል ብትልክለት ወይም ብትደውልለት አይሮፕላን ማረፊያ ይጠብቀሃል . . ወንድሜ እንግሊዝኛ ስለሚናገር ምንም የሚያሰጋህ ነገር አይኖርም።

- እኔም ከአፍታ በፊት ለወንድሜ ደውዬ እኛ ቤት እንዲያስተናግድህ ነግሬዋለሁ፣ግና እንግሊዝኛ ስለማይናገር ለአስጎብኚነት አይጠቅምህም።

- ሁለታችሁንም አመሰግናለሁ፤ዛሬ ማከናወን የሚገቡኝ አንዳንድ ሥራዎች ስላሉኝ እንዳይረፍድብኝ አሁን ለመሄድ እገደዳለሁ። የጉዞ ዝግጅቱን ለማጠናቀቅ ነገ ሙሉውን ቀን ሥራ ቦታ አሳልፋለሁ። በሉ ግብጽ ስደርስ እደውላለሁ፤በጣም አመሰግናለሁ፣ደህና ሁኑ።

- ግብጽም እየጠበቀችህ ናት፣ደህና ሁን።

- እግዚአብሔር ከናንተ ጋር ይሁን።

ስርቆቱ . . (2)

ለግብጽ ተልእኮው ዝርዝር የሥራ መመሪያ ተልኮለት እንደሆነ ለማየት ጆርጅ ኢሜይሉን ከፈተ። ሁለት መልክቶችን አገኘ። አንደኛው ከጃኖልካ ሲሆን ሁለተኛው የሥራ ዝርዝሩን የሚመለከት ነበር። መጀመሪ የጃኖልካን ደብዳቤ ከፈተ . .

{ውድ ወዳጄ ጆርጅ

በሊብያ ቆይታ ከጠበቅሁት በላይ እየረካሁ ነኝ . . እርግጥ ነው በዚህ ሰሞን ሊብያ ውስጥ የጸጥታ ችግር አለ፣የአየሩ ሁኔታም እንዲሁ አስቸጋሪ ነው። ይሁን እንጂ በደረቁ በረሃ ውስጥ የለመለመ እርጥብ መንፈሳዊ ጉብኝት ላይ እንደሆንኩ ነው የሚሰማኝ።

ስለራሴ በየጊዜው የደረስኩበትን አሳውቀሃለሁ፤ የመታደልን መንገድ እስክናገኘው ድረስ አንተም የደረስክበትን አሳውቀኝ።

ማስታወሻ ፦ ወደ ግብጽ እንደምትጓዝ ብትነግረኝ ኖሮ ወደ ሊብያ ከመምጣት ወደ ግብጽ እጓዝ ነበር።

ጃኖልካ}

{ውድ ወዳጄ ጃኖልካ

ወደ ግብጽ እንደምጓዝ ባለመንገሬ ይቅርታ እጠይቃለሁ፤አልጠበኩም ነበር፣የተረጋገጠውም ገና ዛሬ ነው። ስሄድ ሁሉንም ነገር አሳውቀሃለሁ።

ማስታወሻ፦ የለመለመ እርጥብ መንፈሳዊ ጉብኝት ስትል ምን ማለትህ እንደሆነ አልገባኝም። አውነቱን ለመናገር እኔ ግን በአሰልቺ የመንፈስ ድርቀት እንደተመታሁ ነው የሚሰማኝ።

ጆርጅ}

በመቀጠል የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊውን ደብዳቤ ከፈተ።ግብጽ ሲሄድ ማከናወን የሚገባውን ሥራዎች ዝርዝር በአትኩሮት አነበበ። የተሰጠው በጣም አስቸጋሪ ተልእኮ ሲሆን በካይሮ ውስጥ ለመካከለኛው ምስራቅ የቴክኒክና የንግድ ወኪል ማእከል የሚሆን ቢሮ መክፈት ነው። ካኽ ቶሎ ወደ ለንደን እንዲመለስ ስለማይፈልግ ተልእኮውን ሆን ብሎ አስቸጋሪ እንዲሆን ማድረግ ብቻ ሳይሆን የማይቻል አድርጎታል። በመሆኑም ቀሪውን ቀንና ነገን ጨምሮ ካኽን ለማሳፈር የተሰጠውን የሥራ ተልእኮ በሚገባ ለመወጣት በጉዞው ዝግጅት ራሱን ለመጥመድ ወሰነ።
ጆርጅ ግብጽ ውስጥ ከሚገኙ የቴክኒክ ሰራተኞች አስቀጣሪ ኩባንያዎች ጋር መላላክ ጀመረ። ከሁለት ቀናት በኋላ እንደሚመጣም፣አሳወቃቸው። የሚቀጠሩ ሥራ ፈላጊዎች በተቻለ መጠን ለኢንተርቪው ዝግጁ ሆነው እንዲጠብቁት እንደሚፈልግም ገለጸላቸው። ቀሪዎቹን ቀናት ከባስም ወንድም ከጀማል ጋር በመመካከር ቦታ ለመፈለግ በማሰብ ለአንድ ሌሊት ብቻ የሚርፍበትን ትልቅ ሆቴል በኢንተርኔት እንዲያዝለት አደረገ። ጉዞውን ለማሳካት የሚያግዙና የኮንትራት ውሎችን በተገቢው መንገድ ለማዘጋጀት የሚረዱ መረጃዎችን ከኢንትርኔት ላይ መፈለግ ጀመረ።
በሥራውና በተልእኮው ዝርዝር ጉዳዮች ተጠምዶ እያለ ካትሪና መጣች። ከኻክ ጋር ከፍተኛ ፍጥጫ ውስጥ መሆኑንና በቀላሉ እንደማይለቀው ስለሚያውቅ ለሚጠብቀው ኃላፊነት በሚገባ መዘጋጀት የግድ ነው . .

- በጣም አስቸጋሪ ቀን ነበር፣ምን አዲስ ነገር አለ? የምስራች በለን።

- ተነገወዲያ ወደ ግብጽ እጓዛለሁ።

- ተነገወዲያ፣የምን ጥድፊያ ነው?!

- ረዥምና በጣም አስቸጋሪ ተልእኮ ይዤ ነው የምሄደው፤ምናልባት ግብጽን በመምረጤ ተሳስቼ ይሆናል፣ወይም ካኽ በዚህ ሊበቀለኝና ስሜን ሥራ አመራር ቦርዱ ዘንድ ለማጠልሸት ፈልጎ ይሆናል።

- እርሱ ፈለገም አልፈለገ ተልእኮህን በሚገባ እንደምታሳካው እርግጠኛ ነኝ፣ጌታ ካንተ ጋር ነው።

- ካትሪና እወድሻለሁ፤ይህ ጉዞ ከኛው አህጉር ወጭ በሆነ የማላውቀው አገር ውስጥ ለቋንቋው፣ለሃይማኖቱ፣ለወጉ፣ ለልማዱና ለሥርዓቱም እንግዳ ሆኜ ከአንድ ወር በላይ እንዳይወስድብኝ እሰጋለሁ።

- ሊሆን ይችላል፤ይሁን እንጂ በዚህ ጉዞህ ተደሳች እንደምትሆን ከውስጤ ይሰማኛል።

- የኔም ምኞት ይህ ነው፤ኣደም አገሩ ውብና አስደሳች መሆኑን እያረጋገጠልኝ ነው፤ኣደም አገሩን በጣም የሚወድ ይመስላል።

- ሁሉም ሰው አገሩን ይወዳል!

- ልክ ነሽ፣ይበልጥ የሚገርመው ግን ከግብጽ ይበልጥ መካን የሚወድ መሆኑ ነው። ምክንያቱ ደግሞ የነርሱ ነብይ ከአገሮች ሁሉ መካን የሚወድ በመሆኑ ነው! እንዲህ ያለው ምን ዓይነት ፍቅርና ምን ዓይነት ታዛዥነት ነው?! መነኮሳት ለኢየሱስ ያላቸውን ፍቅር አያስታውስሽም?

- ፈጽሞ፤ከዚያ የሚለይ ቢሆንም እንኳ ለኢየሱስ ያለንን ፍቅር ነው የሚያስታውሰኝ።

- በምንድነው የሚለየው?

- እኛ ኢየሱስን የምንመለከተው በአምላክነት ደረጃ ነው። እነሱ ግን መልክተኛ ነብይ ብቻ አድርገው ነው የሚያዩት። እኛ ለኢየሱስ ያለን ፍቅር እኛን ለማዳን ብሎ ራሱን ሰዋ በሚለው እምነት ዙሪያ የሚያጠነጥን ሲሆን፣የነርሱ ግን ከእግዚአብሔር ዘንድ ተልኮ መልካሙን ሁሉ ያስተማራቸው በመሆኑ ዙሪያ የሚሽከረከር ነው።

- የቱን መልካም ነገር ነው?

- እስላምን ነው፣ሁሉም መልካም ነገር የተካተተበት ነው ብለው ያምናሉ።

- ሁሉም መልካም ነገር!

እንደዚያ ነው የሚያምኑት። ለሁሉም የሕይወት ፈርጆች እስላማዊ ትንተና ያቀርባሉ። ከእግዚአብሔር ዘንድ እንደተላለፉ ይናገራሉ።

- {ብለው ያምናሉ . . ይናገራሉ} ስትል ማንን ማለትህ ነው?

- ሙስሊሞችን ማለቴ ነው።

- ቁርኣንን በሚመለከት በላክሽው የመጨረሻ ኢሜይል{ከእግዚአብሔር ዘንድ የተላለፈ ይመስላል} ብለሻል። አባባልሽ በሁሉም መመዘኛ ለኔ ያልጠበኩት ዱብ እዳ ነበር።

- ያልተጠበቀው ዱብ እዳ ግን ቁርኣን በትክክል ከእግዚአብሔር የተላለፈ ስለመሆኑ እንዳጠና ያቀረብከው ጥያቄ ነው። ይህ ዐረቦች የሚያነቡት መጽሐፍ ያለ ምንም መዛባትና መለዋወጥ በሙሐመድ አማካይነት የደረሳቸው ስለመሆኑ ምንም ጥርጠር የለም። ጥያቄው ግን ሙሐመድ እውነተኛ ነው ወይስ አይደለም? የሚለው ነው።

- ከደብዳቤሽ እንደምረዳው እውነተኛ ነው የሚል እምነት እንዳለሽ ነው፣ለዚህ ነው{ከእግዚአብሔር ዘንድ የተላለፈ ይመስላል} ያልሽው።

- የለም እንደሱ ማለቴ ሳይሆን እንደ ብሉይና አዲስ ኪዳን እርስ በርሳቸው የሚጋጩና የሚጣረሱ የተለያዩ ቅጂዎች የሉትም ማለት ነው የፈለኩት።

- ውይይቱ አስደሳች ቢሆንም ከመጓዜ በፊት ማጠናቀቅ የሚኖርብኝ ብዙ የዝግጅት ሥራዎች ስላሉኝ ለማቋረጥ እገደዳለሁ። ለመሆኑ ልጆቹ የት ናቸው?

- በትምህርት ቤታቸው የሽርሽር ጉዞ ፕሮግራም ላይ ለመሳተፍ ሄደዋል፤ትናንት ነግረውህ አልነበረም፣ረሳህ?! ለማንኛውም ከጥቂት ጊዜ በኋላ ይመጣሉ፤በጣም ቢዘገይም ምሳውም ዝግጁ ይሆናል።

- ኦ ረስቼው፣በጣም ርቦኛል የኔ ፍቅር፣በጣም አመሰግናለሁ፤ምሳው እስኪቀርብ ድረስ ፍቀጅልኝና ሥራዬን ላጠናቅቅ።

ስርቆቱ . . (3)

ጆርጅ ካትሪናን እና ልጆቹን ተሰናብቶ ወደ አይሮፕላን ማረፊያ አመራ . . አመሻሹ ላይ በአስራ ሁለት ሰዓት ካይሮ ደረሰ። አስፈላጊውን ሂደት ጨርሶ ሻንጣውን ተረከበ። ወደ እንግዳ መቀበያ ሳሎኑ ሲደርስ{ጆርጅ ኒሶን} የሚል ስሙ፣ ጻሐፊው እንግሊዝኛን በደንብ የማውቅ መሆኑን በሚያሳብቁ ትላልቅ ፊደላት የተጻፈበት ሰሌዳ የያዘ አንድ ሰው አገኘ። ወደርሱ አመራና ምልክት በማሳየት ፈገግ አለ። ሰውየውም ጆርጅን እንኳን ደህና መጣህ ብሎ ተቀበለው . .

- እንኳን ወደ ግብጽ በደህና መጣህ። እኔ የባስም ወንድም ጀማል ነኝ። ይህ የኣደም ወንድም ሙሐመድ ነው፤እንግሊዝኛ በደንብ ስለማይናገር ይቅርታ፣ግን አንተን ለመቀበል ጓግቶ ነው የተገኘው።

- ሁለታችሁንም አመሰግናለሁ . . ክፍል ስለያዝኩ ወደ አይሮፕላን ማረፊያው ሆቴል እንሂድ።

- እንዳልከው ግን ካይሮ ከፍተኛ የትራፊክ መጨናነቅ ያለባት በመሆኑ ሆቴሉ ከከተማው የራቀ ከመሆኑም በላይ በጣም ውድ ነው።

- ለአንድ ቀን ብቻ እንዲያዝልኝ ስላደረግሁ ነገ ብንለውጠው ችግር የለውም። ለመሀል ከተማ ቅርበት ወዳለውና ከተማው ውስጥ ካሉት ትላልቅ ኩባንያዎች ያልራቀ ንጹህ ሆቴል እፈልጋለሁ።

- ብዙ ሆቴሎች ስላሉ ነገ አንተ ራስህ ሚመችህን ትመርጣለህ።

- እኔ ብዙ ሥራ ስላለብኝ ራስህ ነገ መርጠህ ያዝልኝ፣ደስ ካለኝ እቀጥልበታለሁ ካልሆነም እንቀይራለን።

- እሽ እንደ ፈለግህ . . ባስም እጅግ በጣም አጥብቆ ነው አደራ ያለኝ፣እናም ሙሉ ጊዜ ልታዘዝህ ዝግጁ ነኝ።

- ባስም ለኔ የሚያደርገው እንክብካቤ የሚገርም ነው!

- በብዙ ምክንያት ነው ፦ አንተ እንግዳ ነህ፣ነብዩ [የአላህ እዝነትና ሰላም በርሳቸው ላይ ይወረድ] እንግዳ እንድናስተናግድ አዘውናል። አንተ እስላምን ለማወቅ የምትፈልግ ሰው ነህና እስላምን ልናሳውቅህ ግዴታ አለብን። አንተ የወንድሜ ወዳጅ ነህ፤አላህ ደግሞ ውለታ እንድንመልስና በቃላችን እንድንገኝ አዞናል።

- አንደኛ ፦ አንድ ነገር በተናገርኩ ቁጥር ነብዩ . . ነብዩ . . ለምን ትሉኛላችሁ? ሁለተኛ እስላምን ለማወቅ እያጠና ነው ያለህ ማነው?

- አንደኛ ፦ ተወዳጁ ነብይ [የአላህ እዝነትና ሰላም በርሳቸው ላይ ይወረድ] ዱካቸውን የምንከተል ታላቅ ምሳሌያችን ናቸው። ሁለተኛ በደስተኝነት መንገድ ፍለጋ ላይ መሆንህን የነገረኝ ወንድሜ ባስም ነው።

- ደስተኝነትን ፍለጋ እንጂ እስላምን ፍለጋ አይደለማ !

- እሰላም በሌለበት ደስተኝነት ስለማይኖር በሁለቱ መካከል ምንም ልዩነት የለም። ይህ ባይሆን ኖሮማ እናንተ ምዕራባውያን ከማንም በላይ ደስተኞች በሆናችሁ ነበር። ስዌድንን በመሰለ አገር 80% ያህሉ ሕዝብ ኤቲስት ወይም ሃይማኖት የለሽ መሆኑ ምስጢር አይደለም። አገሪቱ ከዓለም ዋነኞቹ ባለ ጸጋ አገሮች አንዷ ብትሆንም በዓለም ላይ ራስን መግደል በከፍተኛ ደረጃ ከሚፈጽምባቸው አገሮች ዋነኛዋ ነች። ራንስን ማጥፋት የደስተኝነት ማጣትና የተስፋ ቢስነት ዋነኛ መገለጫ አይደለም ወይ? !

- ሙስሊሞችም ራሳቸውን ያጠፉ የለም?

- አዝናለሁ ልክ ነህ ! ግና በከፍተኛ ልዩነት ቁጥራቸው ከሁሉም አነስተኛ ነው። ሃይማኖት ራስን ከማጥፋት ጋር ያለውን ግንኙነት በሚመለከቱና በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በተጠናቀሩ ሰነዶች ላይ በመመርኮዝ ዶክተር ጆስ ማንዌልና ተመራማሪ አሌሳንድራ ፊሊሽማን ባካሄዱት አጠቃላይ የሆነ ሳይንሳዊ ጥናት መሰረት፣ራስን የማጥፋት በከፍተኛ ቁጥር የሚፈጸመው በኤቲስቶች ዘንድ መሆኑን የደረሱበት ሲሆን፣ራሳቸውን ከሚገድሉ ሰዎች መካከል 25% ያህሉ ኤቲስቶች፣ከነሱ ቀጥሎ ቡድሂስቶች፣ከዚያ ክርስቲያኖችና ህንዱዎች ሲከተሉ ሙስሊሞች ከ1% ባነሰ ቁጥር መጨረሻ ላይ ይመጣሉ። ይህም ብቻ ሳይሆን{የእስላም ሃይማኖት ራስን መግደል አጥብቆ የሚከለክል በመሆኑ በሙስሊም አገሮች ውስጥ ራሳቸውን የሚያጠፉ ሰዎች መቶኛ ከሌሎች አገራት በተቃራኒ ወደ ዜሮ የቀረበ ነው} ብለዋል ሁለቱ ተመራማሪዎች።

- እስላም ራስን መግደል እርም አድርጎ ይከለክላል?

- በትክክል፣ይህ ብቻ ሳይሆን ለሰው ልጅ ጎጂ የሆኑ ነገሮችን ሁሉ ይከለክላል። በጣም የሚገርመው ነብዩ (የአላህ እዝነትና ሰላም በርሳቸው ላይ ይሁንና) በአኃዛዊ መረጃዎች መሰረት ራስን ማጥፋት ከሚፈጽምባቸው ነገሮች 90% ውን ቃል በቃል የተናገሩ መሆኑ ነው፤እንዲህ በማለት ፦{ራሱን በብረት የገደለ ሰው፣ብረቱ በእጁ ሆኖ ሆዱን እየወጋና እየተሰቃየ ለዘላለም በገሀነም እሳት ውስጥ ዘውታሪ ሆኖ ይኖራል፤መርዝ ጠጥቶ ራሱን የገደለ ሰው መርዙን ፉት እያለ በገሀነም እሳት ውስጥ ዘውታሪ ሆኖ ይኖራል፤ከገደል አፋፍ ራሱን ወርውሮ የሞተ ሰው በገሀነም እሳት ውስጥ ራሱን ወደ ገደል እንደወረወረ ዘውታሪ ሆኖ ይኖራል።}

- ሙያህ ተጽእኖ ያሳደረብህ ትመስላለህ! ለዚህ ነው አኃዞችን በጣም የምትወደው!

- ለአስተያየትህ አመሰግናለሁ። በእርግጥ ወንድሜ እንደ ነገረህ ያጠናሁት ማቴማቲክስ ነው። ማቴማቲክስ ለሎጂካዊ አስተሳሰብ አጋዥ መሆኑ ጥርጥር የለውም። ሳይንሳዊ ስልትን የተማርኩት ግን መጀመሪያ ከሃይማኖቴ ነው።

- ሁሉም ነገር ከነብዩና ከሃይማኖታችሁ ነው! ታበዙታላችሁ!

- ሊሆን ይችላል፤ይሁንና ሳይንሳዊው ስልት ያበዛሁት ምኑ ላይ መሆኑን ለይተህ ማስቀመጥን እንጂ በቀጥታ እኔን መውቀስ የማይጠይቅ መስሎ አይታህም?

- ተረትቻለሁ! ሃይማኖታችሁ ሳይንሳዊ ስልትን እንዴት ነው የሚያበረታታው?

- ከሳይንሳዊ ስልትና አቀራረብ ጋር ትስስር ያላቸው አንዳንድ የእስላም ጥሬ እውነታዎችን እንመልከት። ለምሳሌ ያህል እስላም ከጭፍን ተከታይነት ያስጠነቅቃል። ኃያሉ አላህ ስለ አጋሪዎች እንዲህ ይላል፦

{ለነርሱም አላህ ያወረደውን ተከተሉ በተባሉ ጊዜ፣ አይደለም አባቶቻችንን በርሱ ላይ ያገኘንበትን ነገር እንከተላለን ይላሉ፣አባቶቻቸው ምንም የማያውቁና (ወደ እውነት) የማይመሩም ቢኾኑ (ይከተሉዋቸዋልን?)} [አል በቀራ፡170]

ያለ ሳይንሳዊ ስልት ግምትን መከተለን አስመልክቶ እንዲህ ይላል፦ { . . ጥርጣሬን እንጅ ሌላን አይከተሉም። እነርሱም የሚዋሹ እንጂ ሌላ አይደሉም።} [አል አንዓም፡116][

ሳይንስን፣ሎጂክን፣አእምሮንና ምርምርን ስለሚጻረረው የግል ዝንባሌ ተከታይነት እንዲህ ይላል፦{ . . ብዙዎቹም ያለ ዕውቀት በዝንባሌዎቻቸው ያሳስታሉ፤} [አል አንዓም፡119]

ከፍትህ አስተካካይነት የሚያርቀውን ጥላቻ አስመልክቶ እንዲህ ይላል፦{ . . ሕዝቦችንም መጥላት ባለማስተካከል ላይ አይገፋፋችሁ፤አስተካክሉ፤እርሱ (ማስተካከል) ለአላህ ፍራቻ የቀረበ ነው። አላህንም ፍሩ። አላህ በምትሠሩት ሁሉ ውስጠ ዐዋቂ ነው።} [አል ማኢዳህ፡8][ ስለ ሳይንሳዊ ተጨባጭነትም እንዲህ ይላል፦{ከነዚያ ይሁዳውያን ከኾኑት ሰዎች ንግግሮችን ከስፍራዎቹ የሚያጣምሙ አልሉ፤ሰማንም አመጽንም . . ይላሉ፤} [አልኒሳእ፡46]ወሰን ማለፍን፣ግፍንና ጥፋትን በመጻረር እንዲህ ይላል፦ {(የወቀሳ) መንገዱ በነዚያ ሰዎችን በሚበድሉት በምድርም ውስጥ ያለ ሕግ ወሰን በሚያልፉት ላይ ብቻ ነው፤ . . } [አል ሹራ፡42] ለእውቀት መታመንን እና ፍትሐዊነትን አስመልክቶ እንዲህ ይላል፦{ . . በሰዎችም መካከል በፈረዳችሁ ጊዜ በትክክል እንድትፈርዱ (ያዛችኋል)፤} [አልኒሳእ፡58] ፍትሕ ማስፈንን በሐቅ መመስከርንና አለማዳላትን በሚመለከትም እንዲህ ይላል፦{እናንተ ያመናችሁ ሆይ! በትክክል (ፍትሕ) ቀዋሚዎች፣ በነፍሶቻችሁ ወይም በወላጆችና በቅርብ ዘመዶች ላይ ቢኾንም እንኳ ለአላህ መስካሪዎች ኹኑ።} [አል ኒሳእ፡135] ማስረጃ የመጠየቅን አስፈላጊነት በሚመለከትም እንዲህ ይላል፦{ . . እውነተኞች እንደ ኾናችሁ አስረጃችሁን አምጡ በላቸው።} [አል ነምል፡64]

ስለ . .

 

- አሳማኝ ነው . . ይበቃኛል። አንተም እንደ ወንድምህ የሃይማኖት መሪ ነህ?

- እኔም ሆንኩ ወንድሜ እናንተ ዘንድ ባለው ዓይነት ቤተ ክህነታዊ ትርጉሙ የሃይማኖት መሪዎች አይደለንም። የወንድሜ የትምህርት መስክ እስላማዊ ጥናትና ምርምር ሲሆን የኔ ደግሞ ማቴማቲክስ ነው . . በነገራችን ላይ ከኣደም ወንድም ከሙሐመድ የእራት ግብዣ ተጠርተሃል . . የግብጽን የባህል ምግብ ወይም የፈረንጆችን ፈጣን ምግብ ትፈልግ እንደሆነ ማወቅ ይፈልጋል።

- ቀለል ያለ የግብጽ ምግብ ይሁን።

- (ኮሽሪ) የምንለው የምግብ ዓይነት አለን፤ይስማማሃል?

- ኮሸሪ! አላውቀውም፣ለማንኛውም እንሞክረው።

- ኮሸሪ ከፓስታ ከሩዝ ከሽንኩርት ከትማቲምና ከሌሎች ነገሮች የሚሠራ ምግብ ነው፤ለማንኛውም በጣም ጣፋጭና በጣም ታዋቂ የሆነ ምግብ ነው። እንሻአላህ አስደሳች ሆኖ ታገኘዋለህ፣ይህ ልዩ የሆነ ምርጥ የኮሸሪ ቤት ነው።

- የጀማል ምርጫ ያላስደሰተው ሙሐመድ “ጀማል ከውጭ የመጣ እንግዳችንን ኮሸሪ እንጋባዛለን! ምን ማለትህ ነው? ይህማ ተገቢ መስተንግዶ አይደለም” አለው።

- አይደለም ሙሐመድ ይህ የራሱ ፍላጎት ነው . . ጆርጅ ሰማህ! ሙሐመድ እንዴት በተራና ርካሽ ሬስቶራንት እንግዳችንን እንጋብዛለን?ትልቅ ሬስቶራንት መምረጥ አለብን ይላል፣ምን ትላለህ?

- በጣም አመሰግነዋለሁ፣ይህን የመረጥኩት እኔ ነኝ፣በጣም ያስደስተኛል በለው።

- ይኸው ነግሬህ የለ!

- ከይቅርታ ጋር ፍላጎትህን እናከብራለን፤እንግዳን ማክበርና ማስተናገድ ልማዳችን ነው፤ባህላችንና ሃይማኖታችንም በዚህ ያዘናል በለው።

- እናንተ ዘንድ ሁሉም ነገር በእስላም ወይም በሙሐመድ ምክንያት ነው! እናንተ ሙስሊሞች ከኛ ከክርስቲያኖች ይበልጥ ሃይማኖተኞች ሳትሆኑ አትቀሩም።

- እንዴት ማለት? አልገባኝም።

- እኛ በሳምንት አንድ ቀን እሁድ ብቻ በመጸለይ እንወሰናለን፣እናንተ ግን በቀን ከአንድ ጊዜ በላይ ትጸልያላችሁ። ለሃይማኖታችሁና ለነብያችሁም ልዩ አድናቆትና ግምት ትሰጣላችሁ። እኛ ዘንድ ግን ነብያት እንኳ በተጨባጭ አክብሮት አይቸራቸውም። እናንተ ሃይማኖትን የተሟላ የሕይወት መመሪያ አድርጋችሁ ስትወስዱ እኛ ግን መንፈሳዊ ትስስር ብቻ አድርገን እናያለን።

- በምትለው ነገር ሙስሊሞችን እያወደስክ ነው ወይስ እየነቀፍከ ነው?

- እህህ፣ገለጻ ብቻ ነው። እናንተ የተቀደሱ ነገሮቻችሁ ሲነኩ ትገነፍላላችሁ፤ቁጣችሁም ገደብ የለውም። አሜሪካኖች መጽሐፋቸውን ሲያዋርዱና ሲያቃጥሉ አፍጋኖች የሰሩትን መጥቀሱ ብቻ በቂ ነው!

- ለራሱ የተቀደሱ እሴቶች ግድ የሌለውና ነብዮቹን የማያከብር ምንም መሆን አይችልም። እንግሊዞች መላእክትን ታከብሩ የለ? አሜሪካኖች መስራች ፕሬዚዳንቶቻቸውን ያከብሩ የለ? ኮሙኒስቶች ማርክስና ሌኒንን ያከብሩ የለ? ናዚዎች ሂትለርን ያከብሩት የለ? ሌሎችም . . እኛም ነብያትን በሙሉ እናከብራቸዋለን፣ይልቁንም ከክርስቲያኖች እንኳ በበለጠ ነብዩ ዒሳን [የአላህ ሰላም በርሳቸው ላይ ይወረድ] እናከብራለን፤ከናንተ ይበልጥም እንወዳቸዋለን። ግን የአላህ አገልጋይና መልክተኛው ናቸውና ከዚህ ደረጃቸው በላይ አናስቀምጣቸውም።

- አዎ፣ልክ ነህ ግን ታጋንናላችሁ!

- ማጋነንማ እናንተ እንደምታደርጉት ዓይነት ሙሐመድ አምላክ ናቸው ብንል ኖሮ ነበር!

- ታጋንናላችሁ ስል ሃይማኖትን ከሁሉም የሕይወት ፈርጆች ጋር በማስተሳሰር ረገድ ማለቴ ነው።

- በእግዚአብሔርና በሕይወት መካከል ያለውን ትስስር በተመለከተ፣በፈጣሪ አምላክና በአገልጋዩ መካከል ያለውን ግንኙነት ጊዜያዊ የጸሎት ግንኙነት ብቻ ነው፣የተቀረው የሕይወት ዘርፍ እግዚአብሔርን አይመለከተውም የሚል ሰው፣ሕይወትን ሃይማኖትንም ሆነ እግዚአብሔርን የማይረዳ ሰው ነው የሚል እምነት አለኝ። ይቅርታ አድርግልንና እንዲህ ያለው ሰው መታደልን አያገኝም፤ሁሌም በጭንቀትና በውጥረት ውስጥ ይኖራል፤ፍጻሜው ከፍ ሲል የተጠቀሰው ዓይነት የራስን ሕይወት በገዛ እጅ ማጥፋት ይሆናል። ቋሚ ትስስርና ግንኙነት በመካከከላቸው ከሌለ ሕይወት ሃማኖትም ሆነ አምላክ ትርጉም አልባ ይሆናሉ።

ኮሸሪ ወደሚያቀርብ ሬስቶራንት ገቡ፣የጆርጅን ትኩረት የሳበች አንዲት ጠረጴዛ መርጠው ተቀመጡ። ሬስቶራንቱ በተመጋቢዎች የተጨናነቀ ሲሆን አስተናጋጆቹ የደንበኞቻቸውን ፍላጎት ለማሟላት ደፋ ቀና ይላሉ . . ሦስት ኮሸሪ
አዘው
በደቂቃዎች ውስጥ አስተናጋጁ ይዞላቸው መጣ . .

- ወዳጄ በአላህ ስም ይጀምሩት፣ኮሸሪው ቀርቧል።

- አስተናጋጁ ምን እያለ ነው?

- መብላት ከመጀመሬ በፊት በአላህ ስም እንድጀምር እያስታወሰኝ ነው።

- ለምን?!

- ቅድም የጀመርነውን ሀሳብ ለመቀጠል አንድ ሙስሊም ሕይወቴ በሙሉ የአላህ ነው ብሎ ስለሚያስብ መመገብ ከመጀመሩ በፊት (ብስምላህ) ይላል። በአላህ ስም ታግዤ በረከትና ረድኤቱን ከርሱ ጠይቄ እጀምራለሁ ማለቱ ነው።

- ግሩም ነው!

- እስላም ማንኛውንም ነገር ትንሹንም ትልቁንም የሚመለከት ድንጋጌ አሰፍሯል። አላህ እንዲህ ብሏል፦

{ . . በመጽሐፉም ውስጥ ምንም ነገር አልተውንም፤ . . }</strong ]አል ነምል፡38][

- ማንኛውንም ነገር!

- እህህ፣በነብዩ [የአላህ እዝነትና ሰላም በርሳቸው ላይ ይወረድ] ዘመን ስለሆነው ነገር የተላለፈውን ዘገባ አስታወስከኝ። አንድ ሙስሊም ያልሆነ ሰው ወደ ነብዩ ባልደረቦች መጥቶ (ነብያችሁ ስለ ዓይነ ምድር እንኳ ሳይቀር ሁሉንም ነገር አስተምሯችኋላ!) ሲል አሾፈባቸው። ባልደረቦቹ (አዎ፣ከሽንት ወይም ከዓይነ ምድር በኋላ ቦታውን ለማጽዳት በቀኝ እጃችን እንዳንጠቀም ከልክለውናል፤በፋንድያ ወይም በአጥንት መጸዳዳትንም ከልክለዋል፤አንዳችሁ ከሦስት ባላነሱ ድንጋዮች አይጽዳዳ ብለዋልም።) አሉት።

- የነብያችሁ ባልደረባ ያለው ነገር ትክክለኛ ነው ወይስ ሙስሊም ያልሆነውን ሰውየ ለመከራከር ብቻ እንዳው የተናገረው ነው?! እውን እስላም ውስጥ ዝርዝር የስነ ምግባር ስርዓቶች አሉ?

- አዎ ትክክለኛ ነገር ነው። እርሱ የተመሰገነ ይሁንና አላህ ሃይማኖትን ምሉእ አድርጎታል። አላህ እንዲህ ብሏል፦{ . . ዛሬ ሃይማኖታችሁን ለናንተ ሞላሁላችሁ። ጸጋዬንም በናንተ ላይ ፈጸምኩ። ለእናንተም እስላምን ከሃይማኖት በኩል ወደድኩ . . } [አል ማኢዳህ፡3] ነብዩ [የአላህ እዝነትና ሰላም በርሳቸው ላይ ይወረድ] የተላኩትም መልካም ስነ ምግባራትን ምሉእ ለማድረግ ነው።

 

- የተሟሉ መልካም ስነ ምግባራት ባለቤቶች እናንተ ብቻ እንደ ሆናችሁ አድርጋችሁ የምታምኑት ለምንድነው?

- ልብ አላልክም ይሆናል እንጂ አሁን ጠቅሼልህ ነበር፤ነብዩ [የአላህ እዝነትና ሰላም በርሳቸው ላይ ይወረድ]«የተላክሁት መልካም ስነ ምግባራትን የተሟሉ ለማድረግ ነው» ብለዋል። ማሟላት ማለት ቀደም ሲል በህዝቦች ዘንድ የነበሩትንና ሙሉ ያልነበሩትን መልካም ስነ ምግባራት ምሉእ ማድረግ ማለት ነው። ይህም ከእስላም ልዩና ድንቅ ገጽታዎች አንዱ ነው።

- ምን ማለትህ ነው?

- እስላም መልካም ስነ ምግባራትን፣ሃይማኖቶችንና ሕግጋትን የማሟላት ትልእኮ ይዞ ነው የመጣው።የኣደምን የሙሳና የዒሳን [በሁሉም ላይ የአላህ ሰላም ይወረድ] መልእክት የሚያሟላ የማጠቃለያው የአላህ መልእክት ነው። መልካም ጸባይና ውብ ስነ ምግባር እስላም ውስጥ ተራ ነገር ሳይሆን የሃይማኖታችን አቢይ አካል ነው።

- ኮሸሪም የሃይማኖታችሁ አብይ አካል ይሆን?

- እህህ፣ለእስላም ሳይሆን ለግብጽ አብይ ነገር ነው፤ለድሆችና ለሀብታሞችም የጋራ ምግብ ነው።

- ኦ ኮሸሪ እውነትም ጣፋጭ ምግብ ነው።

- መልካም እራት፣እንግሊዝኛ አጣርቶ ስለማይናገር በዝምታ የተዋጠውን ጋባዣችን ሙሐመድን እናመሰግናለን።

- ሙሐመድን በሚገባ አመስግንልኝ። እስከ ዛሬ ከተመገብኳቸው ምርጥ ምግቦች አንዱ መሆኑንም ንገርልኝ።

- መህበሊያ በወተት ይቀራናል፣አዝዣለሁ።

- ሙሐመድ መህበሊያ በወተት ይቀራናል ይለሃል። መህበሊያ ከግብጽ ባህላዊ የጣፋጭ ዓይነቶች አንዱ ነው።

በልተው
ከጨረሱ
በኋላ
ለጆርጅ
ወደ
ተያዘለት
የአይሮፕላን
ማረፊያ ሆቴል አመሩ። ጆርጅ የሆቴሉን አስፈላጊ ፎርማሊቲ አጠናቆ ከገባ በኋላ ጀማል ነገ ጧት ተመልሶ እንደሚመጣ ነግሮት ተሰናብቶ ሄደ . .
ጆርጅ ወደ ክፍሉ ገብቶ እቃዎቹን ቦታ ቦታ ካስያዘ በኋላ ፈጣን ሻወር ወሰደ . . ከዚያም ኢሜይሉን ከፈተና ከወዳጆቹ የተላኩለትን ምላሾች አነበበ . . ጠቅለል አድርጎ ካዘጋጀ በኋላ ለሁሉም መልሶ ላከላቸው . .

“የላካችሁልኝ መልሶች ለኔ አስደናቂና ጠቃሚ ነበሩ፤እነሱም የሚከተሉት ናቸው፦

ሐቢብ ፦ ብዙዎቹ የእስላም አቀራረቦች ሳይንሳዊ ቢሆኑም እስላምን አልወደውም፤እናም የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያንን እንድትጎበኝ እመክረሃለሁ።

ሌቪ ስለ እስላም ስንናገር ስለ ጭካኔ፣ስለ አክራሪነት፣ስለ ኋላቀርነትና ስለ አጥፊነት መነጋገር የግድ ይላል።

ካትሪና ይህ ሃይማኖት እንዲህ ያለ መስህብነት እንዴት ሊኖረው እንደቻለ ምስጢሩ አይገባኝም! ምናልባት ለኢየሱስ ያላቸውን ፍቅርና ለሴቶች ያላቸውን አክብሮት አስረግጦ መናገር ጠቃሚ ሳይሆን አይቀርም።

ኣደም ፦ ከሁሉም በላጩ ዋቢ ማጣቀሻ የአላህ መጽሐፍ ቁርኣን ነው። ከቁርኣን ያልተማረና ያላጠናው ሰው ስለ እስላም ባይናገር ምኞቴ ነው።

ጃኖልካ እስላም ጥልቀት ያለው ገርነት፣ቅለት ያለው ጥልቀትም ነው። የዚህ እምነት ማራኪነትና መስህብነቱ ለመናገር የሚቸግር ነው። ሚዛናዊ የሆኑ አንዳንድ ምዕራባውያን ስለ እስላም የጻፏቸውን ነገሮች ማንበብ ተመራጭ ነው።

እኔ ጆርጅ የሚከተለውን ላክሁላችሁ እሰላም ውስጥ አስገራሚ የሆኑ ምስጢራት ማለትም ተውሒድ፣አጠቃላይነት፣እርጋታ፣መንፈሳዊነት፣ሳይንሳዊነት፣ሽብር፣ሴት፣ዋቢነት፣ ተአማኒነትና ታሪክ ይገኛሉ።

ከዚህ የሚቀጥለው መልእክት በነዚህ በዘረዘርኳቸው ጉዳይ ዙሪያ ያለውን ጭጋጋማ ሁኔታ የሚያጠራ እንዲሆን ሀሳብ አቀርባለሁ። ማብራሪያ ያለው ሰው ሀሳቡን ያካፍለን።

ጆርጅ”

ደብዳቤውን ከላከ በኋላ . . ከሌቪ የተላከ መልእክት አገኘ።

“ወዳጄ ጆርጅ

በሰላም በጤና ወደ ግብጽ እንድትደርስ እመኛለሁ፤ቀደም ሲል አይሁዳዊነትንና ክርስትናን በተመለከተ ካደረግሃቸው ጥናቶች በተቃራኒ በከፍተኛ ኃይልና በጠንካራ ጉልበት ወደ እስላም እየተንደረደርክ መሆንህ ይሰማኛል . . እባክህን እነዚህን ሙስሊሞች ተጠንቀቃቸው፤አደጋ እንዳያደርሱብህ አሰጋለሁ።

ሌቪ”

መልስ ላከላት . .

“ወዳጄ ሌቪ

ለእውነተኛ ስሜትሽ ምስጋናዬ የላቀ ነው፤አስፈላጊውን ጥንቃቄ አደርጋለሁ። ያለውን ሁኔታም በየጊዜው አሳውቅሻለሁ። ያልሽውን መስየሽ ሊሆን ይችላል፣ግን እርግጠኛ ሁኚ ሙሉ በሙሉ አሳማኝ ሆኖ ሳላገኘው ወደ የትኛውም ሃይማኖት ፈጽሞ አልንደረደርም፣ከናንተ ጋር እመካከራለሁ፤ስለ በጎ አስተያየትሽ አመሰግናለሁ።

ጆርጅ”

ከካኽ መልእክት ደረሰው . . ከፍቶ አየው . .

“ወዳጄ ጆርጅ

ከኩባንያው መራቅህና ተስማምተህ ከመቀበልህ በፊት የማታውቀውን ተልእኮ በመቀበልህ ደስተኛ ነኝ፤እንዲሳካልህ ምኞቴ ነው። ሁሉንም ነገር አመቻችቼልሃለሁ፤በስኬት ባትወጣው ግን ኃላፊነቱን አንተው ትሸከማለህ። ስኬትህን እጠባበቃለሁ።

ካኽ”

ጆርጅ ጧት አንድ ሰዓት ላይ ለቁርስ ከክፍሉ ወጣ፤በተለያዩ ዓለም አቀፍና የግብጽ የቁርስ ዓይነቶች የተሞላውን የሆቴሉን ቡፌ ወዶታል፤የማያውቃቸውን አዳዲስ ምግቦች መቀማመስ ያዘ . .
“የሚያስፈልግዎት ነገር ይኖራል?” አስተናጋጁ በተሰባበረ እንግሊዝኛ ጠየቀው . .

- በጣም አመሰግናለሁ . .

- ጌታዬ ከየት ነው የመጡት?

- ከእንግሊዝ አገር።

- አንተሳ?

- ከግብጽ . . ከእስክድርያ ነኝ።

- ስለ እስክድርያ ልትነግረኝ ትችላለህ?

- እስክድርያ ከግብጽ ታላላቅ ከተሞች አንዷ ስትሆን በመቄዶኒያዊው ታላቁ እስክንድር ከልደት በፊት በ332 ዓመት የተቆረቆረች ጥንታዊት ከተማ ነች።

ጆርጅ እስክድር በስሙ እንዲትጠራ ስለ ፈለጋት ስለዚች ታሪካዊት ከተማ ያነበባቸው ነገሮች ታወሱት። እስክድር የቆረቆራት የንግድና የሄሌኒዝም ሥልጣኔ ማእከል እንድትሆን በማሰብ ሲሆን በኋላ ላይ ብዙ ዘመናትና ሥልጣኔዎች ተፈራርቀውባታል። በውስጧም ከጥንታዊው ዓለም አስደናቂ ነገሮች አንዱ የሆነው የእስክንድርያ የብርሃን ማማንና የእስክንድርያን ቤተ መጽሐፍት የመሳሰሉ ታሪካዊ ቅርሶችን ይዛለች። ክርስትና ወደ ከተማይቱ የደረሰው በ45
ዓመተ ልደት በሐዋርያው ቅዱስ ማርቆስ አማካይነት ነበር።
ለክርስቲያኖች አንደኛዋ የትምህርት ማበልጸጊያ ማእከል ከመሆኗም በላይ የአዲሱ ፍላጦናዊነት ፍልስፍና
ፈለግ መገኛ በመሆኗ በፍልስፍና ረገድም የራሷ የሆነ አሻራ ነበራት። በዓለም ላይ የክርስትናን ነገረ መለኮትና እሳቤ የቀረጸው የእስክንድርያ ስነ መለኮት ትምህርት ቤት እምብርትም ነበረች . . ከእስላም መምጣት በኋላ የነበራትን ሚና ማስታወስ ሞከረ፤በዘመነ እስላምም የዕውቀት መናኸሪያ ሆና በመዝለቋ፣ወደ አገራቸው ተመልሰው ከመሄዳቸው በፊት የምዕራብና የአንዱሉስ ሊቃውንት ዕውቀት የሚቀስሙባት ማእከል ሆና አገልግላች . .
አስተናጋጁ አቋረጠው፦

- ጌታዬ እኔን ረስተው በሀሳብ የነጎዱ ይመስላል፣ይፍቀዱልኝ ልሂድ . .

ጆርጅ ብንን ብሎ ከነጎደበት ዓለም ተመለሰና፦

- አይደለም፣ስለ እስክድርያ ጥንታዊ ታሪክ ሳሰላስል ነበር።

- እኔ መሰረታዊ ትምህርት እንኳ አላጠናቀኩም፣የምጥፈውና የማነበበውም በግድ ነው። ይሁን እንጂ ግብጽን አወዳለሁ በተለይም እስክድርያን። እስክድርያ ያለ ጥርጥር የታሪክ ከተማ ናት። ከዚህ በፊት ጎብኝቷት ያቃሉ?

- እንድጎበኛት አጓጓኸኝ፤አንተ ሙስሊም ነህ?

- የለም፣ክርስቲያን ነኝ . .

- በሙስሊሞችና በክርስቲያኖች መካከል ያለው ግንኙነት እንዴት ነው? እስላም ወደ ግብጽ የገባው እንዴት ነው?

- በሙስሊሞችና በዘመኑ ግብጽን ይገዙ በነበሩት ቤዛንታውያን መካከል ጦርነት ተደረገ። የግብጽ ክርስቲያኖች ከሙስሊሞች ጎን ሆነው ይዋጉ ነበር።

- የግብጽ ክርስቲያኖች?!

- ኮፕቲኮች የግብጽ የመጀመሪዎቹ ነዋሪዎች ናቸው። ሁሉም ክርስቲያኖች ናቸው ማለት ግን አይደለም . . ሙስሊሞች በድል አድራጊነት ወደ እስክድርያ ሲገቡ ነዋሪው ሕዝብ የእምነት ነጻነት ተጎናጸፈ። ለአይሁድ ማህበረሰብም ነጻነቱን ጠብቆለት በሰላም ኖሩ። በአንድም ቤተክርስቲያን ላይ ጥቃት አልሰነዘሩም።

- ለሙስሊሞች ይህን ያህል አድናቆት ካለህ ለምን አልሰለምክም?

- እንዲህ ሆኘ ነው የተወለድኩት። ሃይማኖቴን ያባቴንና የአያቶቼን ሃይማኖት ለምን እለውጣለሁ? እርስዎ ሃይማኖትዎን መለወጥ ይችላሉ?

- ምን የሚከለክል አለ? ልለውጥ እችል ይሆናል . . በነበረው መጽናቱ ለአሳማኝነቱ እስካልሆነ ድረስ አሳማኝ ሆኖ ወዳገኙት መለወጥ የበለጠ ተገቢነት አለው።

- እኔ እንኳ መለወጥን አልወድም፤የሙስሊሞችን አስቸጋሪ ግዴታዎችም አልወድም።

- የሙስሊሞች አስቸጋሪ ግዴታዎች ስትል?!

- በቀን አምስት ጊዜ መስገድ፣ዘካ መክፈል፣የረመዷን ወር መጾም፣ወደ መካ ለሐጅ መሄድ . . አትዋሽ . . አትስረቅ . . አትቆጣ . . ዝሙት አትፈጽም . . ወዘተ.

- እነሱ ግን በዚህ ይደሰታሉ። የላቀ ሕይወትና መታደል ነው ብለው ያምናሉ።

- እነሱ ይደሰቱበት ይሆናል። ለኔ ግን አስቸጋሪ ነው፤ይቅርታ ብዙ አወራሁ።

- የለም፣እኔም ተመግቤ ጨርሻለሁ፣ለሰጠኸኝ ጊዜ አመሰግናለሁ።

ጆርጅ ከዚህ ሆቴል ወደ ሌላ ለመዛወር ወደ ክፍሉ ሄዶ ሻንጣዎቹን አዘጋጀ፤ሻንጣዎቹ እንዲወርዱለት ጠይቆ ወረዱ።እርሱም ጀማልን ለመጠበቅ ክፍሉን ለቆ ወደ እንግዳ መቀበያው ሄደ። የመልቀቂያ ሂደቱን እንደጨረሰ ጀማል ደረሰ . .

- ዝግጁና ለሥራው ጉጉ ትመስላለህ።

- ልክ ነህ . . ዛሬ ማጠናቀቅ ያለብኝ ብዙ ሥራዎች አሉብኝ።

- መጀመሪያ ሻንጣዎችህን ወደ ሆቴሉ እናደርስና ከዚያ ወደምትፈልገው ቦታ እወስደሃለሁ።

- አዲሱ ሆቴል የት አካባቢ ነው?

- አልመዓዲ በሚባል አካባቢ አባይ ወንዝ ዳርቻ የሚገኝ ሆቴል ነው።

- ለሥራዬ ቅርበት ይኖረው ይሆን?

- ካይሮ ትልቅ ከተማ ነች። ሥራህ በትክክል የት እንደሆነ አላውቅም፤እንሻ አሏህ ምቹና ለሥራህም ቅርብ ይሆናል፤ካልተመቸህም መቀየር ይቻላል።

ወደ አዲሱ ሆቴል ደርሰው ክፍል የመያዙን ሂደት አጠናቀቁ . .

- ወደ ክፍልህ ሄደህ አረፍ ብለህ እስክትመጣ እጠብቃሃለሁ።

- እረፍት እንኳ አያስፈልገኝም፤ወደ ክፍሉ ደርሼ ብቻ እመለሳለሁ።

ጆርጅ በፈገግታና በንቁ መንፈስ በፍጥነት ተመልሶ መጣ . .

- መልካም ፈቃድህ ከሆነ ወደዚህ አድራሻ መሄድ እፈልጋለሁ . . ከኛ ጋር ሲጻጻፍ የነበረ የሠራተኛ ኤጀንሲ ኩባንያ ነው።

- ኩባንያው አልጂዛ ውስጥ ስለሆነ ከዚህ ብዙ ርቀት የለውም፤ከፒራሚዶቹም ቅርብ ርቀት ላይ ይገኛል።

- መልካም፣ፒራሚዶቹንም ለማየት ከፍተኛ ጉጉት አለኝ።

- ልክ ነህ፤ግብጽን ጎብኝተህ ፒራሚዶችን ሳታይ መቅረት ተገቢ አይሆንም።

- ፒራሚዶቹም በሃይማኖታችሁ ምክንያት የተገኙ ናቸው?

- ፒራሚዶቹ የተገነቡት በፈረዖዎቹ ዘመን ነው፤ ነብያችንና ነብዩ ዒሳም [የአላህ እዝነትና ሰላም በሁለቱም ላይ ይወረድ] ከመላካቸው ረዥም ዘመናት አስቀድሞ ነው። አንዳንዶቹ ፈርዖዎች በአላህ ያምኑ የነበሩ ሲሆን ከፊሎቹ ደግሞ ከሃዲዎች ነበሩ። ለነብዩ ሙሳ [የአላህ ሰላም በርሳቸው ላይ ይወረድ] “እኔ ታላቁ ጌታችሁ ነኝ” ያለውንና ቤተ እስራኤላውያንን ያሰቃየውን ፈርዖ ታውቁት የለም?

- የሚገርመው ታሪኩን በብሉይ ኪዳንና በቁርኣንም ውስጥ ያነበብኩት መሆኑ ነው።

- ግሩም . . እውነቱን ንገረኝና ከሁለቱ መጽሐፎች ለሙሳ [የአላህ ሰላም በርሳቸው ላይ ይወረድ] የበለጠ ከበሬታ የሚሰጠው የትኛው ነው?

- ስለ እውነት . . የአይሁድ ነብይ ከመሆኑም ጋር ቁርኣን ነው የበለጠ ከበሬታ የሚሰጠው፤ይሁንና . .

- ይቅርታ፣እውነቱን ንገረኝና ከአዲስ ኪዳንና ከቁርኣን ለነብዩ ዒሳ [የአላህ ሰላም በርሳቸው ላይ ይወረድ] የበለጠ ከበሬታ የሚሰጠው የትኛው ነው?

- በአንድ መልኩ ካየን ወንጌል ነው፣በሌላ መልኩ ካየን ግን ቁርኣን ነው።

- እንዴት?

- ቁርኣን በኢየሱስ አወላለድ ትረካው፣ስለ ተሟላ ባህሪያው፣ከጉድለት በጠራና ክብሩን በጠበቀ መልኩ ባማቅረብ ረገድ የበለጠ ከበሬታ ይሰጠዋል። አዲስ ኪዳን ደግሞ ከፍ አድርጎት የአምላክነት ደረጃ በመስጠት ያከብረዋል።

- የሰውን ልጅ አምላክ አድርጎ ማቅረብ ከበሬታ ነው ብለህ ታምናለህ ወይስ ያልሆነውን አድርጎ በማቅረብ በርሱ ላይ ቅጥፈት መንዛት ነው ትላለህ?!

- ማለት የፈለከውን በሚገባ እረዳለሁ፤በአንዳንድ የወንጌል ቅጂዎች የእግዚአብሔር አገልጋ እንጂ አምላክ አለመሆኑ ተጠቅሷል። ይህንና ሌላ ሌላም ማለት ትችላለህ። ተገቢ መብትህም ነው፤ግና ሀሳቤን የጠየከኝ በተወሰነ ነጥብ ላይ ነው።

- “ኢየሱስ ሙስሊም ነበርን?” በሚል ርእስ አሜሪካ በሚገኘው የሉተር ዩኒቨርሲቲ የሃይማኖቶችና የእምነቶች ክፍለ ትምህርት ፕሮፌሰር በሆኑት ሮበርት ሽዲንገር የቀረበውን ጥናት አንብበሃል ብዬ እገምታለሁ።

- አዎ . . ገረፍ ገርፍ አድርጌ አይቸዋለሁ፤በጣም የተጋነነ ይመስለኛል። እስላም ከርሱ በኋላ የመጣ እየሆነ ኢየሱስ እንዴት ሙስሊም ሊሆን ይችላል?!

- ያልለመዳችሁትን የሚናገር ሰው ሁሉ፣ ወይ ያጋንናል ወይ ከሃዲ ነው፤ወይ ደግሞ ሳይንሳዊ አቀራረብን ይቃረናል ትሉታላችሁ። ሰውየው ታዋቂ በሆነ ዝነኛ ዩኒቨርሲቲ የስነ መለኮት ዴፓርትመንት ሊቀ መንበር ነው፤ቃሉን አላጠፈም ዩኒቨርሲቲውም ደግፎታል። እናም የሰው ልጅ ሕሊናዊ ነጻነትና ምሁራዊ ጀግንነት ኖሮት አንዳንድ ውሳኔዎች ላይ መድረስ አያስፈልገውም ትላለህ?!

- ምናልባት . . ባልከው ላይ በከፊል እስማማለሁ።

- መልካም አሁን ደርሰናል። ካንተ ጋር እንድገባ ትፈልጋለህ ወይስ እዚህ ቆይቼህ መቼ መጥቼ እንደምወስድህ ታሳውቀኛለህ?

- እኔ እንጃ . . ለማንኛውም አብረን እንግባና የሚሆነውን አይቼ እወስናለሁ።

ወደ ዓለም አቀፉ የሰራተኛ ኤጀንሲ ኩባንያ ገብተው ሥራ አስኪያጁን ለማግኘት ጠየቁ። ሥራ አስኪያጁ ዶ/ር ገጊዮርጊስ ወጣ ማለታቸውንና ከሁለት ሰዓት ያህል በኋላ እንደሚመለስ ጸሐፊው ነጋራቸው . . ከሁለት ሰዓት በኋላ ተመልሰው እንደሚመጡ ነግረውት ወጡ . .

- ሁለት ሰዓቶች አለን፣የምንገኘው ከፒራሚዶች በቅርብ ርቀት ላይ ነውና በሁለቱ ሰዓት ውስጥ ትጎበኛቸዋለህ ወይስ ሌላ ቀጠሮ አለህ?

- ወደ ፒራሚዶቹ እንሂድና ተመልሰን እንመጣለን።

- መልካም ነው፣በነገራችን ላይ የኩባንያው ሥራ አስኪያጅ እንዳንተው ክርስቲያን ነው፤ግን ፕሮቴስታንት ሳይሆን ኦርቶዶክስ ነው።

- እንዴት አወቅህ? ትተዋወቃላችሁ?

- አንተዋወቅም። ጸሐፊው እንደ ነገረን ከስሙ ነው ያወቅኩት። እኛ ዘንድ ጊዮርጊስ የሚለውን ስም የሚጠቀሙት ክርስቲያኖች ብቻ ናቸው። ኦርቶዶክስ ነው ያልኩህ እዚህ ያሉት ብዙኃኑ ክርስቲያኖች ኦርቶዶክሶች እንጂ ፕሮቴስታንት ባለመሆናቸው ነው . . እርስ በርሳችሁ አንዱ ሌላኛውን በክህደትና በመናፍቅነት እንደምትወነጃጀሉም አውቃለሁ።

- እስላም ውስጥ በክህደትና በመናፍቅነት የሚወነጃጀሉ ቡድኖች የሉም?!

- ያሳዝናል ግን አሉ።

- እንዴት ያሉት ናቸው?

- የቁርኣንን ምሉእነት የሚክዱ፣የነብዩን [የአላህ እዝነትና ሰላም በርሳቸው ላይ ይወረድ] ባልደረቦችና ንጹሃት ባለቤቶቻቸውን የሚወነጅሉና የሚዘልፉ . . በብዙ መሰረት የለሽ አፈተረታዊ ተግባሮች ላይ የተሰማሩ ተስፈንጣሪዎች ይገኛሉ።

- የትነው የሚገኙት?

- በሙስሊሙ ዓለም ውስጥ አነሶች ሲሆኑ መሰረታቸው በኢራንና እራቅ ሲሆን በሌሎች አገሮችም ይገኛሉ።

- ሺዓ ማለትህ ነው!

- በትክክለኛ ስማቸው “ራፍዷ” ወይም ሙሉውን ቁርኣንና ሙሉውን የነብዩን [የአላህ እዝነትና ሰላም በርሳቸው ላይ ይወረድ] ሱና ስለማይቀበሉ “እምቢተኞች” ናቸው። ሌሎች ራሳቸውን ከእስላም ጋር ለማያያዝ የሚሞክሩ እንደ በሃኢዝም፣ቃድያኒዝምና የመሳሰሉ ቡድኖችም አሉ።

- እንግዲያውስ እንደኛው አንዱ ሌላውን ከሃዲ አድርጎ የሚመለከት ተጻራሪ ቡድኖች ሆናችኋል ማለት ነዋ?!

- የለም፤፣እንደ እናንተ እንኳ አልሆንም። ብዙኃኑ ሙስሊሞች ቁርኣን በአመጣጡ፣በአስተላለፉ፣በአረዳዱና በቃላቱ በተሟላና በተረጋገጠ መንገድ ወደኛ የደረሰ መሆኑን ሙሉ በሙሉ ይቀበላሉ። እናንተ ዘንድ ግን ኦርቶዶክሱም፣ካቶሊኩም፣ፕሮቴስታንቱም ሆነ የተቀሩት ቡድኖች ፈጽሞ ያልተበረዘና ያልተዛባ ወንጌል አለን ማለት አይችሉም፤ይህንን በሚገባ ታውቃላችሁ ብዬ አስባለሁ።

- የምትለውን ልየነት አውቃለሁ፣ግን የሚመሳሰሉበት መንገድ ይታየኛል። ዋናው ነገር ግብጽ ውስጥ ሺዓዎች አሉ?

- ለተወሰኑ ዘመናት ግብጽን ገዝተው የነበሩ ቢሆንም፣ዛሬ ግን የሉም ማለት ይቻላል።

- ከዚያ በኋላ ፈጃችኋቸው?

- እኛ እንደ እናንተ አይደለንም። ስርወ መንግስታቸውና ዘመናቸው አለፈ፣አበቃ። ብዙኃኑ ሕዝብ ግን በትክክለኛው ሱና ላይ ተፈጥሯዊ ንጽህናውን እንደጠበቀ ኖረ። የተቀሩትም ወደ ሱና እና ወደ እስላም ተመለሱ።

- “እኛ እንደ እናንተ አይደለንም” ስትለኝ ምን ማለትህ ነው?

- ማለት የፈለኩትን በተሳሳተ መንገድ እንደማትረዳው ተስፋ አለኝ። ለምሳሌ ያህል ነባሮቹ የአውስትራሊያ ሕዝቦች የት ናቸው?! የአሜሪካ ነባር ነዋሪ ቀይ ሕንዶችስ የት ገቡ?!

- የበለጠ ልታብራራው ትችላለህ?

- ሕዝቦቹ እንዴት እንደ ተበደሉና ከነአካቴው እንዴት እንደ ተፈጁ ታውቃለህ! ነባር ህዝቦች በመጤዎቹ ነጮች እጅ ሙሉ በሙሉ ጠፍተዋል። እስላም ግን ግፍን አርም አድርጎ ፍትህ ማስፈንን ግዴታ አድርጎ ደንግጓል . . ተመልከት! ፕራሚዶቹ ከሩቅ መታየት ጀመሩ።

- እንዴት ይገዝፋሉ!

- ግዝፈታቸውና የኪነ ህንጻ ውበታቸው ስትቀርባቸው የበለጠ ጎልቶ ይታያል። እዚህ እንወርድና በፈረስ ጋሪ እንሳፈራለን፤የማሳስብህ ነገር ቢኖር ኪስህንና እቃህን በሚገባ እንድትጠብቅ ነው።

- ምን ማለትህ ነው?!

- የቱሪስት መዳረሻ ስፍራዎች በብዙዎቹ የዓለም አገራት ውስጥ የስርቆትና የዘረፋ ቦታዎች ናቸው። እናም የስርቆቱ ዘዴ የተለያየ ቢሆንም ይህ የኛ ብቻ የተለየ ችግር አይደለም ማለቴ ነው።

- እናንተ እንደምትሉት ሙስሊሞች አይሰርቁም ተብሎ መገመት የለበትም?

- ሙስሊም ሰው እንጅ መልኣክ አይደለም። እንደ ሌላው ሁሉ የራሱ የሆኑ ስህተቶች፣ድክመቶችና ጉድለቶች ይኖሩታል። ይሁን እንጂ ሃይማኖቱ ከዚህ ሁሉ ይከለክለዋል፤ሌላውን ግን ሃይማኖቱ እነዚህን ነገሮች እንዲፈጽም ሊያበረታታው ይችላል።

- እንዴት?

- አንዳንድ ሃይማኖቶች - ስረ መሰረታቸው ትክክለኛ የነበረ ቢሆንም እንኳ- በሌሎች ላይ ግፍ እንዲፈጸም፣እንዲገደሉና እንዲሰረቁ ያዛሉ። እስላም ግን ይህን ሁሉ ሐራም አድርጎ አጥብቆ ይከለክላል። ሰዎች ግን ከሃይማኖታቸው በራቁ መጠንና ከእስላማዊ ስነ ምግባርና ከመንፈሱ በሚኖራቸው ርቀት ደረጃ ሃይማኖቱ በከለከላቸውና እንደ ስርቆት፣ዝሙት፣መጠጥ፣መዋሸት፣ቃልን ማጠፍና ራስ ወዳድነት በመሳሰሉ እኩይ ተግባራትና ባህርያት ውስጥ ይዘፈቃሉ . . ደረስን በል ውረድ።

- ድንቅና አስደሳች ጉዞ ሳይሆን አይቀርም።

በፒራሚዶቹ ስፍራ ለመዘዋወር ሚቀመጡባቸውን ሁለት ፈረሶች ጀማል ተከራየ . . ፈረሶቹን የሚመሩ ሁለቱ ሰዎች እንግሊዝኛ በደንብ የማይናገሩ በመሆናቸው ጉብኝቱን በሁለት ሰዓት ውስጥ መጨረስ ይችሉ ዘንድ እንዲፈጥኑ እንዲነግራቸው ጆርጅ ጀማልን ጠየቀ . . ጉብኝቱ ሲጠናቀቅ ለቀጠሮው ለመድረስ ወደ መኪናቸው አመሩ . .

- ጀማል ከልብ ነው የማመሰግነው። በእውነት አስደሳች ጉዞ ነበር። ወደ ቅድሙ ቢሮ ተመልሰን መሄድ እንችላለን?

- ይቻላል፤ከፈለክም ወደ ሆቴልህ እንዲመጣ ደውልህ ልትነግረው ትችላለህ፤አሁን ሰባት ሰዓት ነው።

- መልካም፣እደውልለታለሁ።

የእጅ ስልኩን ለማውጣት ጆርጅ እጁን ወደ ኪሱ ሲከት ኪሱ ውስጥ የነበረው ገንዘብ የለም! በደንብ ቢፈልግም አላገኘውም . .

- ተሰረቅሁ መሰለኝ!

- እንሻ አሏህ በጎው ነው የሚሆነው፤ምናልባት ወድቆብህ ሊሆን ይችላል።

- አይደለም፣ፈረሱን ይመራ የነበረው ሰውየ ከፈረሱ ላይ ስወርድ ኪሴ ገብቶ ወስዶት ይሆናል። በጎው ነገር የክሬዲት ካርዶች ያሉበት ቦርሳዬ ያለበትን ሌላኛው ኪስ አለመግባቱ ነው።

- አላህ ይመስገን። ነቃ በል ተጠንቀቅ ብየህ አልነበረም!

- ብዙ ገንዘብ አይደለም፤ዋናው ነገር ለሰራተኛ ኤጀንሲ ኩባንያው ሥራ አስኪያጅ ለዶ/ር ጊዮርጊስ ልደውል።

ከኩባንያው ሥራ አስኪያጅ ጋር ስምንት ሰዓት ገደማ ላይ ሆቴል ለመገናኘት ተስማሙና ጆርጅ ይህንኑ ለጀማል ነገረው። ወደ ሆቴሉ ሲደርሱ ጭውውታቸውን ለመቀጠል አብሮት ወደ ክፍሉ እንዲሄድ ጀማልን ጠየቀው . .

- ከጊዮርጊስ ጋር የሥራ ስብሰባ ላይ ስትሆኑ ልረብሻችሁ አልፈልግም።

- አጭር ስብሰባ ይሆናል ብዬ ነው የምጠብቀው። ነገ ለሚኖረን ረዥም ስብሰባ ዝግጅት ብቻ ነው የሚሆነው። ጉዳይ ከሌለህ በጣም አስፈላጊ በሆነ ጉዳይ ላይ ካንተ ጋር መነጋገር እፈልጋለሁ።

- ጉዳይ የለብኝም፣መቀጠል ትችላለህ።

ወደ ክፍሉ አብረው ሄዱ፤ጆርጅ ከክፍሉ የመስተንግዶ ባልኮኒ ሁለት ሲኒ ሻይ አዘጋጅቶ ቁጭ ብለው ለደቂቃዎች እየተነጋገሩ ከቆዩ በኋላ የክፍሉ ስልክ አቃጨለ። የአቀባበል ሰራተኛው የሠራተኛ ኤጀንሲ ኩባንያው ሥራ አስኪያጅ እየጠበቀው መሆኑን ለጆርጅ ነገረው።
ጆርጅ በችኮላ አንዳንድ ወረቀቶችን ወሳሰደና ጀማልን አስፈቅዶት ዶ/ር ጊዮርጊስን ለመገናኘት ወደ እንግዳ መቀበያ አመራ። ሲጠብቀው የነበረው እንግዳ መካከለኛ ቁመና ያለውና በሃምሳዎቹ የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኝ ሲሆን ጆርጅ አስቀድሞ ሰላምታ በማቅረብ እንኳን ደህና መጣህ አለው . .

- የሚመችህ ከሆነ ለአፍታ ያህል አብረን እንቀመጥና ነገ በሚኖረን ስብሰባ ቅድመ ዝግጅት ላይ እንነጋገራለን።

- በጣም ይመቸኛል።

- በኢሜይል እንደጠቀስኩልህ እዚህ ካይሮ ሆነው የሚሰሩ ብዙ የቴክኒክ ባለሞዎችን ለኩባንያችን መቅጠር እፈልጋለሁ። የምፈልጋቸው ባለሞያዎች ግን የላቀ ብቃት ያላቸው ብቻ መሆን ይኖርባቸዋል።

- ብዙ አመልካቾችን ያዘጋጀሁልህ ስለሆነ ከፈለግህ ነገ ቃለ መጠይቅ ልታደርግላቸው ትችላለህ።

- በናንተ በኩል በአመራረጡ ላይ ምን ልታግዙኝ ትችላላችሁ?

- የምታገኛቸው ካመለከቱት በርካታ ሰዎች መካከል እኛ የመረጥንልህ እጩዎች ናቸው።

- በምን መመዘኛ ነው የተመረጡት?

- በሙያዊ መመዘኛ መሰረት ነዋ! ማለት የፈለከው አልገባኝም።

- አንዱ መመዘኛ እንደኛው ክርስቲያን መሆን አልነበረም?

ጊዮርጊስ ፊቱን ቅጭም አደረገ . .

- በመጀመሪያ እኔ ክርስቲያን መሆኔን እንዴት አወቅክ? ሁለተኛ የኩባንያው ባለቤት ሙስሊም ሲሆን እኔ የኩባንያው ሥራ አስኪጅ ብቻ ነኝ። ሦስተኛ ተመልማዮቹ አስር ሲሆኑ አንዱ ብቻ ክርስቲያን ሲሆን የተቀሩት ሙስሊሞች ናቸው። አራተኛ . .

- ይቅርታ ምንም ፈልጌ አይደለም፣እንዳው በመካከላችሁ ውጥረት ብጤ ሊኖር ይችላል ብዬ ስለጠበቅኩ ብቻ ነገሮችን ለማጣራት ፈልጌ ነው።

- በመካከላችን ያለው ግንኙነት በጣም ጥሩ ነው። በምዕራቡ ዓለም እንደምትገምቱት ወይም እንዲሆን እንደምትሹት አይደለም። ለአናሳው የክርስቲያን ማህበረሰብ ከእስላማዊው አስተዳደር ይበልጥ በቂ ጥበቃ ያደረገ አልነበረም፤በዚህ የተነሳም ከታሪክ አንጻር ሁሌም ከሙስሊሞቹ ጦር ጎን ተሰልፈው ጠላትን በጋራ ሲዋጉ መኖራቸውን እንረዳለን።

- መልካም፣በአመራረጡ ላይ ወገንተኝነት መመዘኛ ላለመሆኑ እርግጠኛ መሆን ስለፈለኩ ብቻ ነው።

- እርግጠኛ ሁን . . በቀረቡት እጩዎች መካከል የክርስቲያኖች መቶኛ ከተጨባጩ አኃዝ የበለጠ ከመሆኑ ውጭ ምርጫው የተካሄደው በሙያዊ መመዘኛ ብቻ ነው።

- እንዴት?

- ከአስር አንድ ማለት ክርስቲያኖች ከጠቅላላው ሕዝብ ከሚወክሉት መቶኛ የበለጠ ነው ማለት ነው። ለማንኛውም ነገ በዚህ ረገድ ተጨማሪ ነገር እነግርህ ይሆናል . . ደስ ይልህ ወይም ያስከፋህ እንደሆነ ግን አላውቅም።

- በጣም ጥሩ፣አንድ ወዳጄ ላይ ክፍሌ ሆኖ እየጠበቀኝ ስለሆነ ለመሄድ እገደዳለሁ . . በነገራችን ላይ ይህ ወዳጄ ግብጻዊ ሙስሊም ነው። ቀጠሯችን ነገ ሦስት ሰዓት በኩባንያው ቢሮ ነው። ከመካከላቸው መምረጥ እችል ዘንድ በተቻለ መጠን ብዙ ሰዎችን ማግኘት ምኞቴ ነው።

- መልካም፣ተስማምተናል። ነገ እንጠብቀሃለን፣ እንሻአላህ የሚያረካህ ነገር ታገኛለህ። ግብጽ ብቃት ባለው የሰለጠነ የሰው ኃይል የበለጸገች አገር ናት።

ጆርጅ ወደ ክፍሉ ወጣ፣በመዘግየቱ ጀማልን ይቅርታ ጠየቀው . . ወደ ሆቴሉ ሬስቶራንት ሄደው አብረው ምሳ ለመብላት ጥያቄ አቀረበለት . .

- ቀጥተኛ የሆነ ጥያቄ ላቀርብልህ እችላለሁ?

- ጠይቅ።

- ለግልጽነቴ ይቅርታ አድርግልኝ . . ከኔ ጋር በመሆንህ፣እኔን በመኪና በማመላለስህና ከኔ ጋር በመልፋትህ የምታገኘው ጥቅም ምንድነው?

- የማገኘው ጥቅም ብዙና ግልጽ ነው።

- ምንድነው?

- በሃይማኖታችን ውስጥ ሰዎችን ማገልገልና መጥቀም ከፍተኛ ቦታ አለው። ወደ አላህ ከሚያቃርቡ ምርጥ የትሩፋት ተግባራትም አንዱ ነው።

- የምታገኘው ጥቅም በቃ ይኸው ብቻ ነው ማለት ነው?!

- አይደለም፣የወንድሜን ወዳጅ ማገዝ የመሳሰሉ ሌሎች ጥቅሞችም አሉ። ከዚህ ሁሉ የላቀ ነገርም አለበት፣እሱም አንተን ወደ እስላም መጥራት (ደዕዋ) ነው።

- ይቅርታ፣የመጨረሻውን ጥቅም በተመለከተ የሚኖር አይመስለኝም። ግና ቁሳዊ ጥቅምህ ምንድነው? ለዚህ ሥራህ ስንት እንዲከፈልህ ትፈልጋለህ?

- እመነኝ ይህን ፈጽሞ አላሰብኩትም። የምትፈልገውን ያህል ገንዘብ ወስን። ግን መክፈል የምትጀምረው እንግዳ ከመሆንህ አንጻር መብትህ ከሆኑት ከመጀመሪያዎቹ የሦስት ቀናት ቆይታህ በኋላ ነው።

- ሰዓቱ ገና ቢሆንም የዛሬ ውሎ አስደሰች ነው። ይሁን እንጂ ወደ ክፍሌ ገብቼ አንዳንድ ሥራዎችን ማጠናቀቅና በጊዜ መተኛት ይኖርብኛል። በጣም ነው የማመሰግነው . . ቀጠሯችን ነገ ሁለት ሰዓት ነው። ከጊዮርጊስ ጋር ያለን ቀጠሮ ሦስት ሰዓት በመሆኑ አብረን ወደ ኩባንያው እንሄዳለን።

- መልካም ነው፣እንሻአላህ ይመቸኛል።

ሂሳቡን ለመክፈል ጆርጅ እጁን ወደ ኪሱ ሲከት ገንዘብ የያዘ ቦርሳውን አልነበረም . .

- ቦርሳዬን ላይ ረስቼ ሳልመጣ አልቀረሁም። ሄጄ ይዤ ልመለስ ጥቂት ደቂቃዎች ትጠብቀኛለህ።

- አሁን ለምን ፈለከው?

- አገልግሎት ለሰጠን አስተናጋጅ ጉርሻ ነገር ልሰጠው እፈልጋለሁ።

- አሁን አስራ አንድ ሰዓት ገደማ ነው። ጊዜህን ከማባከንና ወጥተህ በመውረድ ከምትለፋ፣የግብጽ ፓውንድም ስለማይኖርህ ይህን መቶ ፓውንድ ያዝና እንሻአላህ ነገ ዘርዝረን ትመልስልኛለህ።

- ጀማል በጣም አመሰግናለሁ።

ስርቆቱ . . (4)

ጆርጅ ወደ ክፍሉ ሄዶ ሥራዎቹን ለማከናወን ኮምፒውተሩን ከፈተ። ቦርሳው ትዝ ብሎት ቢፈላልግ አጣ። ክፍሉን ሙሉ በሙሉ ቢበረብርም ምንም ነገር ማግኘት አልቻለም። ጠፍቷል ብሎ ስለቆረጠ በጭንቀት ተወጠረ። ቦርሳው የክሬዲት ካርዶቹና ያለውን ጥሬ ገንዘብ ሁሉ የያዘ በመሆኑ ብዙ ከተረበሸ በኋላ ለጀማል ደወለ . .

- ቦርሳዬ የትነው ያለው?

- ክፍሌ ውስጥ ትቻለሁ ብለህ የለ?

- እባክህን የበለጠ ግልጽ ሁን። ቦርሳዬንና አንተንም ክፍሉ ውስጥ ትቼ ነበር የሄድኩት፣ስመለስ ግን አላገኘሁትም።

- ምን ማለትህ ነው?

- በሰጠኸኝ መቶ ፓውንድ ልትሸነግለኝ አትሞክር። አሁን ቦርሳዬን መልስልኝ።

- ይቅርታ እኔ አልወሰድኩም።

- ቦርሳው ክፍሉ ውስጥ ነበር። ክፍሉ ወስጥ አንተን ብቻ ትቼ ነው የወጣሁት። ታድያ ማን ወሰደው?

- እደግማለሁ እኔ ፈጽሞ አልወሰድኩም።

- ከአላህ ምንዳ አገኛለሁ፤የወንድሜን ወዳጅ አግዛለሁ ነው የምትለኝ። አሁን ነገሮች ሁሉ በግልጽ ታዩ፤ሃይማኖታችሁ የስርቆት ሃይማኖት ሳይሆን አይቀርም መስለኝ። በአንድ ቀን ሁለቴ ልሰረቅ!

- በእስላም ላይ ድንበር እንዳታልፍ እጠይቀሃለሁ፣እኔ ፈጽሞ አልወሰድኩም።

- ታድያ ዬት ሄደ? በኖ ጠፋ?!

- በዚህ ሁኔታ ለምንድነው የምታናግረኝ?!

- ቦርሳው ነገ ጧት ከሦስት ሰዓት በፊት ካልመጣልኝ ለፖሊስ አመለክታለሁ። ደሞም ሰዎችን ማገልገል ሃይማኖታዊ ትእዛዝ ነው ትለኛለህ! እናንተ ዘንድ ስርቆት የሃይማኖት አንዱ አካል ነው መሰለኝ። ለማንኛውም ጭቅጭቅ ሳላበዛ ቀጠሯችን ቦርሳዬን ይዘህ ነገ ሁለት ሰዓት ነው። ይህ የመጨረሻ ቃሌ ነው።

ጆርጅ የስልክ ጥሪውን አቋረጠ። ንድድ እያለውና ግራ እየተጋባ ወደ አልጋው ተወረወረ . .

- ካኽ በኔ ላይ ድል ሊቀዳጅ ነው መሰለኝ! ወደዚህ አገር ምን አመጣኝ? እስላምን የስርቆት ሃይማኖትን ለማወቅ? በአንድ ቀን ሁለት ጊዜ ተሰርቄአለሁ . . ጀማል ተብየው መጣና እንድትሰልም እመኛለሁ ይበለኝ!! ምን የሚሉት ሹፈት ይሆን?!!

ጆርጅ በከፍተኛ ንዴትና ውጥረት ተይዞ ስለነበር ለአንድ ሰዓት ያህል በሀሳብ ዋዠቀ። ውጥረቱና ብሽቀቱ ከአስፈላጊነታቸውም ጋር ቦርሳው ውስጥ ባሉት ካርዶችና ገንዘብ ምክንያት ሳይሆን ሌሎች በሃይማኖት ስም እንደ ሕጻን ልጅ እየሸነገሉኝ ነው የሚል ስሜት ስላደረበት መሆኑን በእርግጠኝነት ይረዳል። የክሬዲት ካርዶቹን ለማሳገድ ደብዳቤ ለመላክ አሰበ፤ግና ነገ ጀማል ይመልስልኝና ይህ ቆሻሻ ጨዋታ ያበቃል ብሎ ተስፋ ስላደረገ ሀሳቡን ቀየረ . . የነገውን ቀጠሮ አስታውሶ ከራሱ ጋር አወራ . .

- የነገ ቀጠሮዬ ከሙስሊም ጋር ሳይሆን ከክርስቲያን ጋር መሆኑ መልካም ነገር ነው። ለኔ የበለጠ ቅንነት እንዲኖረው ያደርገዋል . . ለጊዮርጊስ ደውሎ የሆነውን ነገር ልነግረው ወሰነና ደወለ።

- ሃሎ፣ቀጠሮው ተለወጠ እንዴ?

- የለም አልተለወጠም። ካንተ ጋር ለመገናኘት በመጣሁበት ጊዜ ክፍሌ ውስጥ ትቼ የነበረው ሙስሊሙ ወዳጄ ስርቆት ፈጽሞብኝ ምን እንደማደርግ ላማክርህ ነው የደወልኩት።

- እርግጠኛ ነህ እርሱ ነው የሰረቀህ?

- እያዘንኩ አዎ፤ቦርሳዬንና እርሱን ክፍሌ ውስጥ ትቼ ስመለስ ቦርሳውን አላገኘሁም።

- ክፍሉ ውስጥ በደንብ መፈለግ ሊኖርብህ ይችላል፤አሊያም ሆቴሉ ውስጥ ወድቆብህ ይሆናል።

- እርግጠኛ ነኝ፤በሃይማኖት ስም ሲሸነግለኝ ምነኛ እንደ ተጃጃልኩ አላውቅም። ነገ ጧት ካላመጣልኝ ለፖሊስ እንደማመለክት አስጠንቅቄዋለሁ።

- እንዲመጣልህ ምኞቴ ነው። ከአነጋገርህ እንደተረዳሁ ግን ማስረጃ ስለማይኖርህ የፖሊሱ ነገር እንኳ ምንም አይጠቅምህም።

- ልክ ነህ፤ምንም ማስረጃ የለም። ታድያ መፍትሔው ምንድነው?

- ከርሱ ጋር የነገ ቀጠሮህ ስንት ሰዓት ነው?

- ሁለት ሰዓት ነው።

- መልካም፤እኔ ደውዬ እንድሞክር የስልክ ቁጥሩን ልትሰጠኝ ትችላለህ?

- አዎ ይኸውልህ ቁጥሩ . .

- አሁን እረፍት ውሰድ። መሆን የሚችለውን ነገር ነገ እንመካከራለን። ለማንኛውም ግን ወስዶ ከሆነ ያመጣዋል የሚል ተስፋ አለኝ።

ጆርጅ የስልክ ጥሪውን ሲቋጭ የተወሰነ እርጋታ ተሰማው . . ኢሜይሉን ከፈተና የሚከተለውን መልእክት ከጃኖልካ አገኘ ፦

“ወዳጄ ጆርጅ

እኔ ሊብያ ውስጥ እንደተደሰትኩ አንተም በግብጽ ቆይታህ ደስተኛ እንደምትሆን ተስፋ አደርጋለሁ። እዚህ ሕዝቡ እንግዳ ተቀባይና ሰው ወዳድ ነው። እጅግ በጣም በስነ ምግባር የታነጸና በጣም ሃይማኖተኛ ነው። ምናልባት በምዕራባውያኑና በነዚህ ዐረቦች መካከል ያለው ዋነኛው የባህሪ ልዩነት ስነ ምግባርና ግብረ ገብነት የሃይማኖታቸው አንድ አካል እንጂ እኛ ዘንድ እንደተለመደው ከሌሎች ዋጋና አጸፋ ጥቅም ሚጠበቅበት ነገር አለመሆኑ ነው። እንዴት ይዞሃል? ስለ ጤንነትህና ስለ ሁሉም ነገር ካንተ መስማት እንሻለን።

ጃኖልካ”

መልስ ጻፈለት ፦

“ወዳጄ ጃኖልካ

በሊብያ መደሰትህ አስደስቶኛል፤እነዚህን ሙስሊሞች ግና አጥብቀህ እንድትጠነቀቃቸው ምኞቴ ነው። እኔን በተመለከተ እስካሁን በግብጽ ሙስሊሞች ሁለት ጊዜ ስርቆት ተፈጽሞብኛል። አንደኛው ጊዜ ወደ እስላም እንድገባ ጥሪ ሲያደርግልኝ በነበረ ሰው ሲሆን በችግሬ ጊዜ ከጎኔ የቆመው እንደኔ ያለው አንድ ክርስቲያን ብቻ ነው። ሥራዬን አጠናቅቄ ወደ እንግሊዝ ለመመለስ እንዴት እንደ ጓጓሁ ልነግርህ አልችልም።

ጆርጅ”

በመቀጠልም
ከሙስሊሞች
እንዲጠነቀቅ
በማሳሰብ ለላከችለት ደብዳቤ ምላሽ ለሌቪ ጻፈ

“ወዳጄ ሌቪ

ያሳዝናል ያስጠነቀቅሽኝ ነገር አልቀረም ደርሶብኛል፤ግብጽ ውስጥ ስርቆት ተፈጽሞብኛል። ቀደም ሲል እንደጠቀስሽው ሁሉ በፍጥነት ወደ እስላም ስንደረደር የነበርኩ ቢሆንም አሁን ግን ስነ ምግባር የጎደለው ሃይማኖት መሆኑን እየተረዳሁ ነኝ። ምናልባት ይሁዳዊነትና ክርስትና የተዛቡና የተከለሱ ሊሆኑና እስላም ግን ያልተዛባና ያልተከለሰ ሊሆን ይችላል፤ግና ስነምግባራዊነት ፍጹም የጎደለው ሃይማኖት ነው። ስለ ሌላው ጉዳይ በቅርቡ እጽፍልሻለሁ። አሁን የጻፍኩልሽ በማስጠንቀቂያሽ አለመጠቀሜን በማስታወሴ ነው።

ጆርጅ”

ኢሜይሉ ላይ ቀደም ሲል ለላከላቸው ጥቄዎቹ የተላኩለት ምላሾችን ቢያገኝም፣አንዱንም የማንበብ አምሮት ስላልነበረው ኮምፒውተሩን ዘጋ . . ለመተኛት በመሞከር አልጋው ላይ ቢዘረገፍም እንቅልፍ አልመጣልህ አለው። ብድግ ብሎ ቲቪውን ከፈተና የእንግሊዝኛውን ቢቢሲ ቻናል ዜና ጥቂት ከተከታተለ በኋላ ቻናሎችን ሲቀያይር በእንግሊዝኛ ቋንቋ የሚተላለፍ እስላማዊ ቻናል አጋጠመው።
ፕሮግራሙ እስላም ውስጥ ስላለው መልካምና ምስጉን ባህርያት የሚወያራና ሙሐመድ

[የአላህ እዝነትና ሰላም በርሳቸው ላይ ይወረድ]

የተላኩት መልካ ስነ ምግባርን የተሟላ እንዲሆን ለማድረግ መሆኑን የሚናገር ነበር . . ለራሱ እንዲህ አለ

- እነዚህ እስላማዊ ሕዝቦች በሰብእና መከፋፈልና በጣምራዊነት የተጠቁ ሳይሆኑ አይቀሩም . . ጣምራ መስፈርት የሚጠቀመው ይህ ሃይማኖት እንዴት ያስጠላል!

የንዴቱ ብዛት ፕሮግራሙን እስከ መጨረሻው መከታተል አላስቻለውም። እንደገና ለማንቀላፋት ሞከረ። ሲገለባበጥ ከቆየ በኋላ እንቅልፍ ወስዶት ጭልጥ አለ . . ዘጠኝ ሰዓት ገደማ ከእንቅልፉ ብንን ብሎ ተነሳና ወደ መጸዳጃ ቤት ሄደ። ሲወጣ ፊት መታጠቢው አጠገብ ዓይኑ በጠፋ ቦርሳው ላይ አረፈ! ቀትር ላይ ዶ/ር ጊዮርጊስን ለመገናኘት ከመሄዱ በፊት መጸዳጃውን መጠቀሙ ትዝ አለው። ተቻኩሎ ስለ ነበር ሰነዶቹን ብቻ ወስዶ የገንዘብ መያዣ ቦርሳውን እዚያ መርሳቱን ልብ አላለም ነበርና በዚህ ሁሉ ውጥንቅጥ ውስጥ ሊገባ ቻለ!
ስሜቱ ክፉኛ ተጎድቶ አልጋው ላይ ቁጭ አለ። ያዞረውና ያጥወለውለው ጀመር . . ለሆነው ነገር ጀማልን ምን ብሎ ይቅርታ ይጠይቅ? ምንም ማረጋገጫ ሳይኖረው በስርቆት የወነጀለው በመሆኑ በድሎታል . . ኣደም ግልፍተኛ እንዳይሆንና በችኮላ እንዳይወስን ብዙ ጊዜ አስጠንቅቆታል . . አሁን ምን ማድረግ ይችላል?

ስርቆቱ . . (5)

ጧት ሁለት ሰዓት ላይ ጀማል ወደ ሆቴሉ ደርሶ የእንግዳ መቀበያው ሰራተኛውን ለጆርጅ እንዲደውልና መምጣቱን እንዲነግረው ጠየቀ . .

- እንግሊዛዊው ጆርጅን ነው?

- አዎ።

- ዛሬ ንጋት ላይ ደሙ በከፍተኛ ደረጃ ወርዶ በአንቡላንስ ወደ ሆስፒታል ተወስዶ ነበር።

- ተመልሷል?

- አዎ፣ከሁለት ሰዓት ገደማ በፊት ተመልሷል። ይተኛ አይተኛ ግን አላውቅም።

- እባክህን ደውልለትና ሊጠይቅህ የመጣ ጀማል የሚባል ሰው መምጣት ይፈልጋል በለው።

ሰራተኛው ደውሎ ሲነግረው ይምጣ አለውና ጀማል ወደ ክፍሉ ሲደርስ ድካምና መንገላታት ከፊቱ በጉልህ የሚስተዋለው ጆርጅ በሩን ከፈተለት . .

- ጆርጅ ይቅርታ አድርግልኝ፤ፈጽሞ አንተን የማስከፋት ፍላጎት አልነበረኝም። ይህ የባለቤቴ የወርቅ ማስቀመጫ ቦርሳ ነው። ባንኮች ተከፍተው ሄጄ ገንዘብ እስካመጣልህ ድረስ በአደራ አንተ ዘንድ ይቀመጥ። ያንተን ቦርሳ ላመጣልህ አልቻልኩም፣ ስንት እንዳለበትም አላውቅም!

- ይህ ሁሉ ለፖሊስ እንዳላመለክት በመፍራት ነው?

- በተከሰተው ነገር በጣም አዝናለሁ። ፖሊስ እንኳ ማድረግ የሚችለው ምንም ነገር አይኖርም።

- ታድያ የባለቤትህን ወርቅ ለምን ታመጣለህ?

- አንተ እንግዳ ነህ፤መስተንግዶ የማግኘት መብት አለህ። በተጨማሪም መንገደኛ እንግዳ ሆነህ ችግር የደረሰብህ ሰው ስለሆንክ ልናግዝህ ግዴታ ነው። በተጨማሪም ስለ እስላም የተዛባ እይታ እንዳይኖርህ እፈልጋለሁ።

- አሁንም እኔ አልወሰድኩም በሚለው ላይ እንደጸናህ ነው ማለት ነው?

- ያለ ምንም ጥርጥር እኔ አልወሰድኩም። ይሁን እንጂ እንዳይደክምህ አሁን ይህን ማንሳት አልፈልግም።

- በኔ ቦታ ብትሆን ምን ታደርግ ነበር?

- እውነቱን ለመናገር አላውቅም። ይህ ቦርሳው ለኔ በሚኖረው አስፈላጊነት ደረጃና በሚኖረኝ ስነ ልቦናዊ መረጋጋት ላይ የሚሞረከዝ ይሆናል። ምናልባት የሂሳብ ባለ ሞያነቴ ሁሉንም ነገር ወደ አኃዞች ለውጬ እንድመለከት ያደርገኝ ይሆናል።

- አንተ በኔ ቦታ ብትሆንና እኔ በአንተ ቦታ ብሆን ከኔ ምን ትጠብቃለህ?

- ይቅርታ አድርግልኝ መልስ አልሰጥም።

- አንተ ያደረከውን ያደርጋል ብለህ ትጠብቀኛለህ?

- እውነቱን ለመናገር አልጠብቅም፤ላንተ ግን ይገባሃል።

- ያደረኩትን ካደረኩ በኋላ ቦርሳዬን ባገኘው ለዚህ ሰው ምን ትለዋለህ?

- አግኝተሃል?!

- እንዲሁ ቢሆን ማለቴ ነው፣ይሆናል ብለህ አስበውና መልስልኝ።

- የግድ ወዳጄን ይቅርታ እጠይቀዋለሁ። ነገሩ በጣም ከባድና አስቸጋሪ በመሆኑ ተዝለፍልፌ ልወድቅም እችላለሁ ብዬ አምናለሁ።

- ይቅርታ ጠይቀህ አልቀበልም። ሥራህን አልረሳውም ቢልህስ?

- አላህ ይቅር ባይና ይቅር ባዮችን የሚወድ በመሆኑ፣ለሰው ልጅ ይበልጥ ተገቢው ነገር ይቅር ባይነትና ሆደ ሰፊነት ቢሆንም፣እንደዚያ ቢል እንኳ እውነት አለው።

- እንግዲያውስ እኔም ይቅርታ እጠይቀሃለሁ። ቦርሳዬን አግኝቻለሁ . . በዚህ ምክንያት ነው የደም ግፊቴ ወርዶ ወደ ሆስፒታል የተወሰድኩት፣ምን እንደማደርግ አላውቅም። እንዳልከው አላህ ይቅር ባይነትን የሚወድ ነውና ደጋግሜ ይቅር እንድትለኝ እለምንሃለሁ።

ጀማል ሳይፈልግ የወረደ እንባውን አባበሰ . .

- ይቅር ብየሃለሁ። ልነግርህ የምችለው ነገር ቢኖር ከትናንት ጀምሮ እስካሁኑ ደቂቃ ድረስ እኔም ሆንኩ ባለቤቴ፣እንግሊዝ አገር የሚገኘው ወንድሜ ባስምም ሆነ ኣደም መተኛት ያልቻልን መሆናችንን ብቻ ነው።

- ነግረሃቸዋል ማለት ነው?!

- መሬት ጠባኝ መፍትሔ ፍለጋ ስኳትን፣የእስላም ስነ ምግባር ምን መሆን እንዳለበት ሊመክረኝና ሊያስተምረኝ ጊዮርጊስ ሲደውልልኝ ለአንተ መፈተኛ መሆን አልፈለኩም። ኃያሉ አላህ እንዲህ ይላል ፦{ጌታችን ሆይ! ለነዚያ ለካዱት ሰዎች መሞከሪያ አታደርገን፤ . . } [አል ሙምተሒና፡5[

- እጅግ በጣም ነው የማዝነው።

- ነገሩ አሳማሚ ቢሆንም አልፏልና ምንም እንዳልተፈጠረ አድርገህ ቁጠረው። አሁን ጤንነትህ እንዴት ነው?

- እኔ ደህና ነኝ፤ግን በአንተ ላይ ጥፋት ሰርቻለሁ፤ከባድ በደል ፈጽሜአለሁ።

- እኔ ይቅር ብየሃለሁ፣፤ግን ከግዴታ ጋር ነው።

- ምንድነው?

- የሆነውን ነገር እርግፍ አድርገህ ረስተህ ለራስህ ጤንነት ጥንቃቄ ከማድረግ ግዴታ ጋር ነው። አለዚያ ይቅር አልልህም።

- ግዴታውን እቀበላለሁ፤ተስማመቻለሁ። ግን አንተም ጥፋቴን እርግፍ አድርገህ ለመርሳት ቃል ከገባህልህኝ ነው።

- ተስማምተናል። ቁርስ አድርገሃል?

- አላደረኩም።

- አብረን ቁርስ ለመብላት ራሴን ጋብዣለሁ፤ግን ከጊዮርጊስ ጋር ላለህ ቀጠሮ እንዳትዘገይ በፍጥነት መሆን ይኖርበታል። ወደ ሬስቶራንቱ ቀድሜ ወርጀ ታች እጠብቀሃለሁ።

- በአምስት ደቂቃ ውስጥ ካንተ ጋር እሆናለሁ።