.የቁርኣንና የሱንና ታአምራት

.የቁርኣንና የሱንና  ታአምራት

እያንዳንዱ ነቢይና መልክተኛ ከአላህ አላህ (ሱ.ወ.) ለመላኩ አስረጅ የሚሆን ተአምር ይሰጠዋል። ለምሳሌ ያህል የሙሳ  ተአምር በትራቸው ነበር። የዒሳ  ተአምር ደግሞ ዕውርም ኾኖ የተወለደንና ለምጻምን መፈወስ፣በአላህ ፈቃድም ሙታንን ከመቃብራቸው ማስነሳት ነበር። የነቢያት መደምደሚያና የመልክተኞች መቋጫ የሆኑት የሙሐመድ  ታአምር ደግሞ መልክታቸው እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ የሚቆይና ለሁሉም ዘመንና ስፍራ ምቹ የተደረገ ከመሆኑ ጋር በተጣጣመ መልኩ ዘላለማዊ ሕያው መጽሐፍ የሆነው ታላቁ ቁርኣን ነው። ቁርኣን የሕይወት መመሪያ መጽሐፍ ከሆነ ዘንዳ፣ይህ መጽሐፍ በሁሉም ነገሩ ተአምራዊ ነው። የዚህ ቁርኣን ታምራዊነትና አሸናፊነት ለነቢዩ  መልክት እውነተኛነትና ለነቢዩ ፍጹም ሐቀኝነት ዛሬም አስረጅ ተአምር ሆኖ ቀጥሏል። ሲሳይ ሰጭ፣ሕያውና ከሁሉም የተብቃቃ ከሆነው ፈጣሪ በነቢያት መደምደሚ አማካይነት የተላለፈ፣ለሁሉም ዘመንና ቦታ ምቹና ተስማሚ የሆነ መጽሐፍ ነው። ቀደም ሲል ከተገለጹት የተአምራዊነት ገጽታዎቹ በተጨማሪ፣ከዘመናችን ተመራማሪ ሳይንቲስቶች ጥረት መረዳት እንደ ተቻለው፣ቁርኣን እግረ መንገዱን በሚያነሳቸው ሳይንሳዊ ጉዳዮች ላይም ተአምራዊ ነው። ሳይንቲስቶች ባደረጉት ጥናት እንደ ደረሱበት ቅዱስ ቁርኣን በቅርቡ እንጂ ዘመናዊው ሳይንስ ያልደረሰባቸውን ብዙ ሳይንሳዊ እውነታዎችን ያከተተ መሆኑ ተረጋገጧል። ከነዚህም መካከል ለአብነት ያህል፦ የሰው ልጅ ጽንስ ዕድገት ደረጃዎችን ሰዎች ስለዚህ ጉዳይ ምንም ነገር ከማያውቁበት ከበርካታ ምእተ ዓመታት በፊት በተራቀቀ ሁኔታ መግለጹ አንዱ ነው። አላህ (ሱ.ወ.) ይህን በማስመልከት እንዲህ ብሏል፦

{በእርግጥም ሰውን ከነጠረ ጭቃ ፈጠርነው። ከዚያም በተጠበቀ መርጊያ ውስጥ፣የፍትወት ጠብታ አደረግነው። ከዚያም ጠብታዋን (በአርባ ቀን) የረጋ ደም አድርገን ፈጠርን፤የረጋውንም ደም ቁራጭ ሥጋ አድርገን ፈጠርን፤ቁራጭዋንም ሥጋ አጥንቶች አድርገን ፈጠርን፤አጥንቶቹንም ሥጋን አለበስናቸው፤ከዚያም (ነፍስን በመዝራት) ሌላ ፍጥረትን አድርገን አስገኘነው፤ከሰዓሊዎችም ሁሉ በላጭ የኾነው አላህ ላቀ።}[አል ሙእምኑን፡12-14]

በተጨማሪም አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{በእናቶቻችሁ ሆዶች ውስጥ፣በሦስት ጨለማዎች ውስጥ (በሆድ በማሕጸንና በእንግዴ ልጅ) ከመፍጠር በኋላ፣(ሙሉ) መፍጠርን ይፈጥራችኋል፤ይሃችሁ ጌታችሁ አላህ ነው። ሥልጣኑ የርሱ ብቻ ነው፤ከርሱ ሌላ አምላክ የለም፤ታዲያ ወዴት ትዞራላችሁ?}[አል ዙመር፡6]

ሳይንቲስቶችና ሐኪሞች ይህንን ከራሳቸው ግኝቶችና ማመሳከሪያ ዋቢዎች ጋር አነጻጽረው ሲያጠኑ ሙሉ በሙሉ ውስጠ ዐዋቂው አላህ (ሱ.ወ.) እንዳለው ሆኖ ነበር ያገኙት። በተጨማሪም የመዳሰስ ስሜት መነሻ ስፍራን በተመለከተ አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{እነዚያን በታምራታችን የካዱትን በእርግጥ እሳትን እናገባቸዋለን፤ስቃይን እንዲቀምሱ ቆዳዎቻቸው በተቃጠሉ ቁጥር ሌሎችን ቆዳዎች እንለውጥላቸዋለን፤አላህ አሸናፊ ጥበበኛ ነውና።}[አል ኒሳእ፡56]

የጠፈርን መስፋፋትና እየተዘረጋጋ መሄድ ሲገልጽም አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{ሰማይንም በኃይል ገነባናት፤እኛም በእርግጥ [ለማስፋት] ቻዮች ነን።}[አል ዛሪያት፡47]

ፀሐይ በራሷ ምሕዋር የምትጓዝ መሆኑን ሲገልጽ አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

‹ሌሊቱም ለነሱ ምልክት ነው፤ከርሱ ላይ ቀንን እንገፍፋለን፣ወዲያውኑም እነሱ በጨለማ ውስጥ ይገባሉ። ፀሐይም ለርሷ ወደ ኾነው መርጊያ ትሮጣለች፤ይህ የአሸናፊው፣የዐዋቂው፣አምላክ ውሳኔ ነው።}[ያሲን፡37]

የነቢዩ ሱንናም ከዚህ ተአምር የራቀ አይደለም። ከእመ ምእመናን ዓእሻ (ረ.ዐ.) በተላለፈው መሰረት፣የአላህ መልክተኛ  እንዲህ ብለዋል፦ { እያንዳንዱ የኣደም ልጅ ሦስት መቶ ስልሳ የአጥንት መገጣጠሚያዎች ይዞ ነው የተፈጠረው፤በነዚያ ሦስት መቶ ስልሳ አጥንቶች ቁጥር፣‹አልሏሁ አክበር›፣አልሐምዱ ሊልላህ›፣‹ላእላሀ እልላልሏህ›፣‹ሱብሓነልሏህ› እና ‹አስተግፍሩልሏህ› ያለ ሰው፣ሰዎች ከሚሄዱበት መንገድ ላይ ድንጋይ ወይም እሾህ፣ወይም አጥንት ያስወገደ፣በበጎ ነገር ያዘዘ፣ወይም ከክፉ ነገር የከለከለ ሰው በዚያ ዕለት ራሱን ከእሳት ያረቀ ሆኖ ይውላል።}[በሙስሊም የተዘገበ]

ዛሬ በሳይንስ እንደ ተረጋገጠው የሰው ልጅ እነዚህ አጥንቶችና መገጣጠሚያዎች ባይኖሩት ኖሮ፣ሕይወቱን መምራትና ኑሮን ማጣጣምም ሆነ የተጣለበትን በምድር ላይ የምትክነት ተልእኮ መወጣት ባልቻለ ነበር። ከዚህ ስንነሳም የፈጣሪን ታላቅ ጥበብና ድንቅ ውሳኔ ለሚመሰክረው ለዚህ ትልቅ ጸጋ የሰው ልጅ በየቀኑ ምስጋና የማድረስ ግዴታ ይኖርበታል። በዚህ ሐዲስ ውስጥ ተአምራዊው ነገር ነቢዩ  እንዲህ ዓይነቱ ዕውቀት የትምና ማንም ዘንድ ባልነበረበት ሰባተኛው መቶ ክፍለ ዘመን እንዲህ በረቀቀ ሁኔታ የሰው አጥንት መገጣጠሚያዎችን መግለጻቸው ነው። እንኳ በዚያ ዘመን ዛሬ በሃያ አንደኛው ክፍለ ዘመን አብዛኛው ሕዝብ ብቻ ሳይሆን ብዙ የሕክምና ሳይንስ መምሕራን ጭምር ይህን አያውቅም!! ዛሬ ዘመናዊው ሳይንስ ልክ ነቢዩ  ከአስራ አራት ክፍለ ዘመናት በፊት እንደተናገሩት ባረጋገጠው መሰረት፣በሰው አካል ውስጥ ሦስት መቶ ስልሳ የአጥንት መገጣጠሚያዎች ይገኛሉ። 147ቱ በጀርባ አከርካሪ አጥንት ሲገኙ፣24ቱ በደረት፣86ቱ ከወገብ በላይ ባለው ክፍል፣88ቱ ከወገብ በታች ባለው የሰውነት ክፍል፣15ቱ ደግሞ በዳሌ ገንዳ ይገኛሉ።

እዚህ ላይ የግድ መነሳት ያለበት ጥያቄ ፦ ከፈጣሪው አላህ (ሱ.ወ.) በስተቀር ይህንን የሰው ልጅ ዕውቀት በሃያኛው ክፍለ ዘመን መጨረሻዎች ላይ እንጅ ያልደረሰበትን ልዩ የሆነ ሳይንሳዊና ሙያዊ እውነታ ለነቢያትና ለመልክተኞች መደምደሚያ  ማን ሊያስተምር ይችላል?! የሚለው ነው።

ነቢዩን  ከሰው ግንዛቤ በላይ የሆነውን እንዲህ ያለውን ጉዳይ እንዲያነሱ ሊያደርጋቸው የሚችለውስ ማን ሊሆን ይችላል?! አላህ (ሱ.ወ.) በገደብ የለሽ ዕውቀቱ የሰው ልጅ አንድ ቀን በዚህ የአቶኖሚ ግኝት ላይ ሊደርስ እንደሚችል ስለሚውቅም ነቢዩን  አሳውቋቸዋል። ከዚህ ነቢያዊ ሐዲሥ የሚንጸባረቀው የሐቅ ብርሃን ለእኚህ የመልክተኞች መደምደሚያ ነቢይ እውነተኛነትና ከመለኮታዊ ራእይ ጋር ስላላቸው ትስስር እርግጠኝነት የጸና ማስረጃ ነው።

የሳይንስና የስልጣኔ መንገድ ግን የመልካም ስነምግባር መንገድ ካልሆነ፣ለሰው ልጆች ተድላና ደስታ የማያገለግል፣ለጥፋትና ለዕድለ ቢስነት የሚያጋልጣቸው የመከራና የዋይታ አጥፊ ስልጣኔና አውዳሚ ዕውቀት እንጂ ሌላ ምንም ሊሆን አይችልም! ስለዚህም የስልጣኔና የዕውቀት መንገድ የመልካም ስነምግባርና የሞራላዊ እሴቶች መንገድም ጭምር ነው። ዕውቀትና ስልጣኔ የሌለበት የደስተኝነትና የመታደል መንገድ ቅዠትና ከንቱ ተረት እንደሆነ ሁሉ፣መከመልካም ስነምግባርና ከሞራላዊ እሴት የተራቆተ የዕውቀትና የስልጣኔ መንገድም ግለሰቦችን፣ማህበረሰቦችንና መላውን የሰው ልጅ ለጥፋትና ለውድመት የሚያጋልጥ መንገድ ነው።