ደስተኝነትን የምትፈልግ ሰው ሆይ!!

ደስተኝነትን የምትፈልግ ሰው ሆይ!!

አላህ (ሱ.ወ.) እንዳለው ሁሉ፣ወደዚህ ሕልውና ከመምጣትህ በፊት፣ከመኖርህ አስቀድሞ ፍጽሞ ያልሆንክ አልቦ ነበርክ።

{ሰው፣ ከአሁን በፊት ምንም ነገር ያልነበረ ሲኾን፣እኛ የፈጠርነው መኾኑን አያስታውስምን?}[መርየም፡67]

ከዚያ በኋላ አላህ (ሱ.ወ.) ከአፈር፣ከዚያም ከፍትወት ጠብታ ፈጠረህና ሰሚ ተመልካችም አደረገህ። አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{በሰው ላይ የሚታወስ ነገር ሳይኾን፣ከዘመናት የተወሰነ ጊዜ በእርግጥ አልፎበታል። እኛ ሰውን፣(በሕግ ግዳጅ) የምንሞክረው ስንኾን፣ቅልቅሎች ከኾኑ የፍትወት ጠብታ ፈጠርነው፤ሰሚ ተመልካችም አደረግነው።}[አልደህር፡1-2]

ከዚያም በሂደት ከደካማነት ወደ ብርቱነት ተሸጋገርክ፤በመጨረሻም ከብርታት በኋላ ወደ ሽምግልና እና ወደ ድክመት መመለስ ዕጣ ፈንታህ ይሆናል። አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{አላህ ያ ከደካማ (ፍትወት ጠብታ) የፈጠራችሁ ነው፤ከዚያም ከብርቱነት በኋላ ደካማነትንና ሽበትን አደረገ፤የሚሻውን ይፈጥራል፤እርሱም ዐዋቂው ቻዩ ነው።}[አልሩም፡1-2]

ምንም ጥርጣሬ የሌለበት ፍጻሜህም ሞት ነው። በነዚያ የዕድገት እርከኖች ውስጥ፣አላህ (ሱ.ወ.) በሰጠህ የኃይል የአቅምና የምግብ ጸጋ ካልታገዝክ በስተቀር ራስህን ከጉዳት መከላከልም ሆነ ራስህን መጥቀም የማትችል፣በተፈጥሮህ ችግረኛና አቅም የለሽ ሆነህ ከድክመት ወደ ድክመት ትሸጋገራለህ።ራስህን በሕይወት ለማቆየት አስፈላጊ የሆኑ ግን በእጅህ የሌሉ፣አንዴ ስታገኛቸው ሌላ ጊዜ ደግሞ የምትነፈጋቸው አያሌ ነገሮች አሉ።የምትፈልጋቸውና የሚጠቅሙህ ግን ለማግኘት ከአቅምህ በላይ የሚሆኑ አንዳንዴ ልታገኛቸው የምትችል፣ሌላ ጊዜ ደግሞ የማታገኛቸው ብዙ ነገሮችም ይኖራሉ። እንደዚሁም ሊጎዱህና ተስፋ የሚያስቆርጡህ፣ድካምና ልፋትህንም ከንቱ የሚያስቀሩ፣ለችግርና ለመከራ የሚዳርጉና አንዳንዴ ለማስወገድ ፈልገህ ሲሳካልህ ሌላ ጊዜ ደግሞ የማትችላቸው ብዙ ነገሮችም ይኖራሉ። ታድያ አንተ አቅመ ቢስ ደካማና አላህን ብቻ የምትከጅል ችግረኛ መሆንህ አይሰማህምን?! አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{እላንተ ሰዎች ሆይ! እናንተ (ሁል ጊዜ) ወደ አላህ ከጃዮች ናችሁ፤አላህም እርሱ ተብቃቂው ምስጉኑ ነው።}[ፋጢር፡15]

በባዶ ዓይን ሊታይ የማይችል ደካማ ቫይረስ ያጠቃህና የአልጋ ቁራኛ ያደርገሃል። ለመታከምም እንዳንተው ደካማ ፍጡር ወደሆነ ሰው ትሄዳለህ። አንዳንዴ ፈውስ ታገኛለህ፣ሌላ ጊዜ ደግሞ ሐኪሙ ማዳን ያቅተውና በሽተኛውም ሐኪሙም ግራ ይጋባሉ . . ሰው ሆይ! ምንኛ ደካማ ነህ!! ዝንብ እንኳ አንድ ነገር ቢነጥቅህ ማስመለስ ይሳነሃል!! አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{እላንተ ሰዎች ሆይ! አስደናቂ ምሳሌ ተገለጸላችሁ፤ለርሱም አድምጡት፤እነዚያ ከአላህ ሌላ የምትገግገዟቸው (ጣዖታት)፣ዝምብን ፈጽሞ አይፈጥሩም፤ለርሱ (ለመፍጠር)፣ቢሰበሰቡም እንኳ፣(አይችሉም)፤አንዳችንም ነገር ዝንቡ ቢነጥቃቸው ከርሱ አያስጥሉትም፤ፈላጊውም ተፈላፊውም ደከሙ (ገዥውም ተገዥውም ደካሞች ናቸው)።}[አልሐጅ፡73]

ዝንብ የነጠቀህን ነገር ማስጣል የማትችል ከሆንክ፣ካንተ ጉዳይ በእጅህ ያለውና የምትወስንበት ምን ይኖረሃል?! አናትህ በአላህ እጅ ነው። ነፍስህ በአላህ እጅ ናት። ልብህ በአልረሕማ ሁለት ጣቶች መካከል ነውና እንዳሻው ይገለባብጠዋል።ሕይወትህና ሞትህም በርሱ እጅ ነው። መታደልህና ዕድለ ቢስ መሆንህም በርሱ እጅ ውስጥ ነው። እንቅስቃሴህና እርጋትህ፣አንደበትህና ቃላትህ በርሱ መሻት ስር ናቸው፤ከርሱ ፈቃድና ይሁንታ ውጭ አትንቀሳቀስም። ከርሱ መሻት ውጭ ምንም አትሠራም፤አንተን ለራስህ ከተወህ ለድክመትህ፣ለአቅመ ቢስነትህ፣ለጥፋትህና ለኃጢአትህ ተወህ ማለት ነው። ጉዳይህን ለሌላ ሰው አሳልፎ ከሰጠብህ ደግሞ መጥቀምም ሆነ መጉዳት፣መግደልም ሆነ ማስነሳት ለማይችል ተወህ ማለት ነው። ስለዚህም ለአንዲት ሰከንድ እንኳ ከርሱ መብቃቃት አትችልም። እናም በትንፋሽህ ልክ በግልጽም ሆነ በስውር እርሱን ለመፈለግ ትገደዳለህ፤እርሱ ጸጋዎቹን ሲዘረግፍልህ አንተ ግን በሁሉም መስክ እንዲህ በጽኑ አስፈላጊህ እየሆነ በኃጢአትና በክሕደት ከርሱ ለመጣላት ትጣደፋለህ። ዞሮ መግቢያህ፣መጨረሻህና መመለሻህ ወደርሱ ብቻ ሆኖ ሳለ ነገ እፊቱ የምትቆም መሆንህን ትረሳለህ።

ሰው ሆይ! የኃጢአቶችህን ምርትና የሚያስከትለውን አደጋ ለመሸከም አቅመ ቢስ ደካማ ነህ። አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{አላህ ከናንተ ሊያቃልልላችሁ ይሻል። ሰውም ደካማ ኾኖ ተፈጠረ።}[አልኒሳእ፡28]

አላህ (ሱ.ወ.) ነቢያትን ልኮ መጻሕፍትን አስተላልፎአል፤ሕግጋትንም ደንግጓል። ከፊት ለፊትህም ቀጥተኛውን መንገድ ዘርግቷል። ማብራሪያና ማስረጃዎችንም አቅርቧል። በያንዳንዱ ነገር ውስጥም አንድነቱን፣ጌትነቱንና አምላክነቱን የሚያመለክት ምልክት አኑሮልሃል። ይህ ሁሉ ሆኖ ግን አንዳንድ ሰዎች እውነትን በሐሰት ሲመክቱ፣ሰይጣንና ሌላውንም ከአላህ ሌላ ወዳጅ አድርገው ሲይዙና በሐሰት ሲከራከሩ ታገኛቸዋለህ፦

{በዚህም ቁርኣን ውስጥ፣ከየምሳሌው ሁሉ፣ለሰዎች መላልሰን ገለጽን፤ሰውም ከነገሩ ሁሉ ይበልጥ ክርክረ ብዙ ነው።}[አልከህፍ፡54]

የምትቀጨው የአላህ (ሱ.ወ.) ጸጋ መጀመሪያህንና መጨረሻህን አስረስቶህ ይሆን?! ከፍትወት ጠብታ የተፈጠርክ መሆንህ፣መግቢያህ ወደ አፈር፣ከሞት ስትቀሰቀስ ደግሞ መሄጃህ ወደ ጀነት ወይም ወደ ጀሀነም እሳት መሆኑን አታስታውስምን?! አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{ሰው እኛ ከፍትወት ጠብታ የፈጠርነው መኾናችንን፣አላወቀምን? ወዲያውም እርሱ (ትንሣኤን በመካድ) ግልጽ ተከራካሪ ይኾናልን? ለኛም ምሳሌን አደረገልን፤መፈጠሩንም ረሳ፤አጥንቶችን፣እነርሱ የበሰበሱ ሲኾኑ ሕያው የሚያደርጋቸው ማነው? አለ።› ያ በመጀመሪያ ጊዜ (ከኢምንት) ያስገኛት ሕያው ያደርጋታል፤እርሱም በፍጡሩ ሁሉ (ኹኔታ) ዐዋቂ ነው፣በለው።›[ያሲን፡77-79]

አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{አንተ ሰው ሆይ፣በቸሩ ጌታህ ምን አታለለህ? በዚያ በፈጠረህ፣አካለ ሙሉም ባደረገህ፣ባስተካከለህም።}[አልኢንፊጣር፡6-7]

ሰው ሆይ! የአላህን ተውሒድና እርሱን የማላቅ ጥዑመ ለዛ . . ከድህነት ወደ መብቃቃት፣ከበሽተኝነት ወደ ጤንነት፣ከጭንቀት ወደ መረጋጋት ያወጣህ ዘንድ፣ኃጢአትህን ይምርህ ዘንድ፣ችግርህን ያስወግድል ዘንድ፣ተበድለህ ከሆነ ረድኤቱን ይለግስህ ዘንድ፣ግራ ተጋብተህ ጠመህ ከሆነ ይመራህ ዘንድ፣ያላወቅኸውንም ያስተምርህ ዘንድ፣ስትፈራ መድህን ይሰጥህ ዘንድ፣ድክመት ውስጥ ስትሆን ይራራልህ ዘንድ፣ጠላቶችህን ካንተ ይመክትልህ ዘንድ፣ሲሳይ ይከፍትልህ ዘንድ . . እርሱ ፊት ቆመህ እርሱን መለመንና መማጸንን ራስህን ለምን ትነፍጋለህ?!

ሰው ሆይ! ከሃይማኖት ጸጋ በኋላ አላህ (ሱ.ወ.) ለሰው ልጅ የዋለለት ታላቁ ጸጋ የአእምሮና የማሰብ ችሎታ ጸጋ ነው። በዚህ የማሰብ ታላቅ ተወህቦም የሚጎዳውን ከሚጠቅመው ለይቶ ያውቃል። የአላህን ትእዛዛትና እገዳዎቹን ይረዳል። ዋነኛውን የሕይወት ተልእኮና ዓለማ የሆነውን አንድ አላህን ብቻ ያለ ምንም ሸሪክ ማምለክንም በዚህ ታላቅ ጸጋ አማካይነት ማወቅ ይችላል። አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{ማንኛውም በናንተ ላይ ያለው ጸጋ ከአላህ ነው፤ከዚያም ችግር በደረሰባችሁ ጊዜ፣ወደርሱ ብቻ ትጮኻላችሁ። ከዚያም ከናንተ ላይ ችግርን ባነሳላችሁ ጊዜ፣ከናንተው የኾኑ ጭፍሮች ወዲያውኑ በጌታቸው (ጣዖትን) ያጋራሉ።}[አልነሕል፡53-54]

ሰው ሆይ! አስተዋይ አእምሮ ያለው ሰው ሰናይ ነገሮችን ይወዳል፣ወራዳ ነገሮችን ይጠላል። የሁሉንም ነቢያት፣የደጋግ ትጉሃን የአላህ አገልጋዮችን ዱካ ይከተላል፤በአርአያቸው መመራትን ይመርጣል። ከነርሱ ባይሆንም፣ከደረጃቸው ባይደርስም ወደዚያ ለመቅረብ ነፍሱ ትጓጓለች። ለዚህ ደግሞ መንገዱን አላህ (ሱ.ወ.) በሚከተለው ቃሉ አሳይቶናል። አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{በላቸው፦ አላህን የምትወዱ እንደ ኾናችሁ፣ተከተሉኝ፤አላህ ይወዳችኋልና፤ኀጢአቶቻችሁንም ለናንተ ይምራልና፤አላህም መሓሪ አዛኝ ነው።}[ኣሊዒምራን፡31]

ይህን ከፈጸመ አላህ (ሱ.ወ.) በቸርነቱ ከነቢያት፣ከመልክተኞች፣ከሰማእታትና ከደጋጎች ባሮቹ ጎራ ያሰልፈዋል። አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{አላህንና መልክተኛውንም የሚታዘዝ ሰው፣እነዚህ ከነዚያ አላህ በነሱ ላይ ከለገሰላቸው ከነቢያት፣ከጻድቃንም፣ከሰማዕታትና ከመልካሞቹ ጋር ይኾናሉ። የነዚያም ጓደኝነት አማረ!}[አልኒሳእ፡69]

ሰው ሆይ! ምክሬ ከራስህ ብቻ ጋር ሆነህ የመጣልህን እውነት እንድታስተውል፣ማስረጃዎቹን እንድትመለከት፣ማረጋገጫዎቹን እንድታስተነትን ብቻ ነው። ትክክለኛ ሆኖ ካገኘኸው ለመከተል ተጣደፍ፣የወግና የልማድ ምርኮኛ አትሁን። ነፍስህ ከወዳጆችህ፣ከጓደኞችህ፣ከአብሮ አደጎችህና ከአያቶችህ ውርስ ይበልጥ ለአንተ ውድ መሆኗን ዕወቅ። አላህ (ሱ.ወ.) ካፍሮችን በዚህ የመከራቸው ሲሆን እንዲህ ብሏል፦

{የምገሥጻችሁ ባንዲት ነገር ብቻ ነው፤(እሷም) ሁለት ሁለት፣አንድ አንድም ኾናችሁ ለአላህ እንድትነሱ፣ከዚያም በጓደኛችሁ (በሙሐመድ) ምንም ዕብደት የሌለበት መኾኑን መርምራችሁ እንድትረዱ ነው፤እርሱ ለናንተ ከብርቱ ቅጣት በስተፊት አስጠንቃቂ ነው እንጂ ሌላ አይደለም፣በላቸው።}[ሰበእ፡46]

ሰው ሆይ! በምትሰልምበት ጊዜ የምታጣው ምንም ነገር የለም። አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{በአላህና በመጨረሻውም ቀን ባመኑ፣አላህ ከሰጣቸውም (ሲሳይ) በለገሱ ኖሮ፣በነርሱ ላይ ምን (ጉዳት) ነበረ? አላህም በነርሱ (ኹኔታ)?ዐዋቂ ነው።}[አልኒሳእ፡39]

በአላህ (ሱ.ወ.) እና ከርሱ በተላለፈው ሁሉ ቢያምኑ ምን ይጎዳሉ?! እያለን ነው። እናም በወዲያኛው የኣኽራ ሕይወት ለበጎ ሠሪ የገባውን ቃል ኪዳን በማሰብ ቢያምኑ ምን ይጎዳሉ?! እርሱ ጥሩና ጥሩ ያልሆነውን ንይያቸውን ውስጠ ዐዋቂ ነውና ከሰጣቸው ሀብት አላህ (ሱ.ወ.) በሚወደው መንገድ ቢለግሱ ምን ይጎዳሉ?! እርሱ ለበጎ ሥራ ማን ተገቢ እንደሚሆን፣እርሱ ዘንድ ቀቡልነት ላለው በጎ ሥራ ማን እንደሚገራ፣ለዚህም መመራትን ማን እንደሚታደል ከሁሉም በላይ ያውቃል። በሌላው አንጻርም ለውርደትና ከመለኮታዊ በረከቱ ኬላ ተባርሮ ለመርገምት ማን እንደሚዳረግም እርሱ ከማንም በላይ ያውቃል። ከርሱ በር የተባረረ መናጢም በዱንያም ሆነ በኣኽራም ለከፋ ኪሳራ ተዳርጓል!

እስላምን ተቀብለህ መከተልህና መስለምህ አላህ ሐላል አድርጎ ከፈቀደለህና መስራት ከምትፈልገው ወይም ማግኘት ከምትሻው ማንኛውም ነገር አያግድህም። ይልቅዬም እርሱን በማሰብና ሽልማቱን ተስፋ በማድረግ በምትሠራው ማንኛውም ሥራ፣ሥራው ሀብትን ስልጣንህንና ክብርህን የሚጨምር ዓለማዊ ጠቀሜታ የሚሰጥህ ቢሆን እንኳ አላህ ምንዳ ይጽፍልሃል። ከሐራም በሐላል መብቃቃትን በማሰብ የምትፈጽማቸው የተፈቀዱ ነገሮች ቢሆኑ እንኳ አላህ (ሱ.ወ.) የዕባዳ አጅር ይሰጠሃል።

የሰው ልጅ ሆይ! የአላህ (ሱ.ወ.) መልክተኞችና ነቢያት እውነትን ይዘው መጥተዋል፤የአላህን ፍላጎትም ለሰዎች አድርሰዋል። ስለዚህም የሰው ልጅ በዚህ ሕይወቱ ዕውቀትና ግንዛቤን ተመርኩዞ ለመጓዝና በወዲያኛው የኣኽራ ሕይወቱም ከሚታደሉት ጋር ለመሆን፣የአላህን (ሱ.ወ.) ሸሪዓ ማወቅ አስፈላጊው ነው። አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{እላንተ ሰዎች ሆይ! መልክተኛው እውነትን ከጌታችሁ አመጣላችሁ፤እመኑም፤ለናንተ የተሻለ ይኾናል፤ብትክዱም (አትጎዱትም)፤በሰማያትና በምድር ያለው ሁሉ የአላህ ነውና፤አላህም ዐዋቂ ጥበበኛ ነው።}[አልኒሳእ፡170]

በተጨማሪም አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{፦ እላንተ ሰዎች ሆይ! እውነቱ ከጌታችሁ በእርግጥ መጣላችሁ፣(በርሱ) የተመራም ሰው፣የሚመራው ለራሱ ነው፤የተሳሳተም ሰው፣የሚሳሳተው (ጉዳቱ) በራሱ ላይ ነው፤እኔም፣በናንተ ላይ ተተባባቂ አይደለሁም፣በላቸው።}[ዩኑስ፡108]

የሰው ልጅ ሆይ! ከሰለምክ የምትጠቅመው ራስህን ነው፤ከሓዲ ከሆንክም የምትጎዳው ራስህን ነው። አላህ (ሱ.ወ.) ከባሮቹ የተብቃቃ ጌታ ነውና የአጥፊዎች ኃጢአት አይጎዳውም፤የትጉሃን አገልጋዮቹ ዕባዳም አይጠቅመውም። ከርሱ ዕውቀት ውጭ ትእዛዙ ተጥሶ ኃጢአት አይፈጸምም፤ከርሱ ፈቃድ ውጭም ትእዛዛቱ አይፈጸሙም። አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{፦ ከጌታችሁ ዘንድ ብርሃኖች በእርግጥ መጡላችሁ፤የተመለከተም ሰው (ጥቅሙ) ለነፍሱ ብቻ ነው፤የታወረም ሰው (ጉዳቱ) በራሱ ላይ ብቻ ነው፤እኔም በናንተ ላይ ጠባቂ አይደለሁም፣(በላቸው)።}[አልአንዓም፡104]

ከአላህ (ሱ.ወ.) በተላለፈላቸው መሰረት ነቢዩ  ጌታቸው እንዲህ ማለቱን ነግረውናል፦ {ባሮቼ ሆይ! እኔ ግፍን በራሴ ላይ እርም አድርጌ በናንተ መካከልም ሐራም አድርጌያለሁና አትበዳደሉ። ባሮቼ ሆይ! እኔ የመራሁት ካልሆነ በቀር እያንዳንዳችሁ በጥመት የምትመሩ ናችሁ፡፡ ስለዚህ አመራርን ከኔ እሹ፤እኔም አመራሬን እሰጣችኋለሁና፡፡ አገልጋዬቼ ሆይ! እኔ የማበላው ካልሆነ በቀር ሁላችሁም የተራባችሁ ናችሁና ሲሳይን ከኔ ለምኑ፤እኔም እመግባችኋለሁና፡፡ አገልጋዮቼ ሆይ! እኔ የማለብሰው ካልሆነ በቀር ሁላችሁም የታረዛችሁ ናችሁና ልብስን ከኔ ለምኑ፤እኔም አለብሳችኋለሁ፡፡ አገልጋዮቼ ሆይ! ቀንም ሆነ ማታ ኃጢኣትን ትሰራላችሁ፤እኔም ኃጢኣቶችን በሙሉ ይቅር የምል ነኝና ይቅርታን ከኔ ለምኑ፤እኔም ይቅር እላችኋለሁና፡፡ አገልጋዮቼ ሆይ! ልትጎዱኝ አይቻላችሁም፤ልትጠቅሙኝም አይቻላችሁም፡፡ አገልጋዮቼ ሆይ! ከናንተ የቀደሙት (ትውልድ) እና የሚከተሉት፣ሰዎቻችሁና ጅኖቻችሁ በመካከላችሁ ካለውና ልቡ እጅግ የጠራ በሆነው በኩል ብትሰባሰቡ እንኳ በግዛቴ ላይ አንዳችም ነገር አትጨምሩም፡፡ አገልጋዮቼ ሆይ! ከናንተ የቀደሙትም ሆኑ የሚከተሉት፣ሰዎቻችሁም ሆኑ ጅኖቻችሁ፣ከመካከላችሁ እጅግ የከፋ ልብ ካለው በኩል ብትተባበሩ ከግዛቴ ቅንጣት አትቀንሱም፡፡ አገልጋዮቼ ሆይ! ከናንተ የቀደሙትም ሆኑ የሚከተሉት፣ሰዎቻችሁና ጅኖቻችሁ፣በአንድ አደባባይና ሥፍራ ሆነው ቢለምኑኝና ለያንዳንዳቸው የሚፈልጉትን ሁሉ ብሰጥ መርፌ ከውቅያኖስ ብትገባ የምታጎድለውን ያህል እንኳ እኔ ዘንድ ካለው ላይ አይጎድልብኝም፡፡ አገልጋዮቼ ሆይ! ለናንተ እኔ ዘንድ የምቆጥርላችሁና ከኔ ምንዳ የሚያሰጧችሁ ሥራዎቻችሁ እንጂ ሌላ አይደለም፤ስለዚህ ጥሩ ያገኘ ሰው አላህን ያመስግን፤ከዚህ ውጪ የሚመኝ ግን ማንንም ሳይሆን ራሱን ይውቀስ፡፡} [በሙስሊም የተዘገበ]

የሰው ልጅ ሆይ! . . እነሆ መንገዱ ይህ ነው፤ከዚህ ውጭ ለዛሬው የዱንያ ሕይወትና ለመጪው የኣኽራ ዘላለማዊ ሕይወት ደስተኝነትን ለማግኘትና ለመታደል ለመብቃት ከቶም ሌላ መንገድ የለም። የተቀሩት መንገዶች ግን የዕድለ ቢስነት የውድመትና የመከራ አስከፊ መንገዶች ናቸው። አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{ይህም ቀጥተኛ ሲኾን መንገዴ ነው፤ተከተሉትም፤(የጥመት) መንገዶችንም አትከተሉ፤ከ(ቀጥተኛው) መንገዱ እናንተን ይለያዩዋችኋልና። ይኻችሁ ትጠነቀቁ ዘንድ በርሱ አዘዛችሁ።}[አልአንዓም፡153]

የደስተኝነትና የመታደልን መንገድ የያዘ ሰው ለመታደል ይበቃል፤የተቀሩትን ሌሎች መንገዶች የያዘ ሰው ግን ከአላህ (ሱ.ወ.) መንገድ ወጥቶና አፈንግጦ ይርቃል እንጂ ወደ ደስተኝነትና የመታደል መንገድ አይገባም።