እነሆማ ይህ ነው መንገዱ . .

እነሆማ ይህ ነው መንገዱ . .

ማንኛውም አስተዋይ የሆነ አመዛዛኝ ሰው፣በግልጽ ማወቁን ቢያስተባብለው እንኳ የዘላለማዊ ደስታና የመታደል መንገድ ይህ መሆኑን ያውቃል። እንዲህ ዓይነቱ አስተባባይ ግን ሙሳ  ተአምራትን ይዘውላቸው ቢመጡም ነቢይነታቸውን እንደካዱት ሰዎች ዓይነት ነው። አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{ነፍሶቻቸውም ያረጋገጧት ሲኾኑ ለበደልና ለኩራት በርሷ ካዱ፤የአመጸኞችም ፍጻሜ እንዴት እንደ ነበረ ተመልከት።}[አልነምል፡14]

አስተዋይ አእምሮና አመዛዛኝ ልቦና ያላቸው ብዙ

ሰዎች ግን ባይሰልሙ እንኳ፣መላው የሰው ዘር በዱንያም ሆነ በኣኽራ መታደልን ከፈለገ ብቸኛው የመድህን መንገድ ይህ መሆኑን ያውቃሉ።

እናም መንገዱ ይህ ነው . . ነጻና ከራሱ ጋር ድፍረትና ጀግንነት ያለው ሰው ሁሉ፣ያለውን ጫና እና አፈና ተቋቁሞ የገዛ ራሱን ወይም ሌሎች ሰዎችን መፍራት ሳያግደው፣አዲስ ነገርን መፍራት ወይም በየሚዲያው የሚካሄደው የማጠልሸት ዘመቻ አስቀድሞ አእምሮው ውስጥ የተቀረጸው የተዛባ ምስል . . ይህን ሃይማኖት ከመደገፍ ወይም ከመከተል ያላቀበውና ሀሳቡን በድፍረት መግለጽ የሚችል ሰው ሁሉ መንገዱ ይህ መሆኑን ያረጋግጣል። በዚህ ረገድ ድፍረትና ወኔ ማጣት፣እንደዚሁም ማህበራዊ ትስስሮች፣ ግንኙነቶችና ስጋቶች ከይሉኝታ ጭምር፣ብዙ ሰዎችን የመታደልን መንገድ እንዳይከተሉ ከልክሏቸዋል። አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{አትፍሯቸውም፤ምእመናንም እንደ ኾናችሁ ፍሩኝ።}[ኣሊ ዒምራን፡175]

እነሆማ መንገዱ ይህ ነው . . የሕይወት ሕግ የሆነው መሞከር፣እውነተኛውን ከአስመሳዩ የሚለይ መፈተን ቢኖርበትም፣አዎ ይህ የደስተኝነት መንገድ ነው። የመታደል መንገድ ነው። የሰብአዊ ክብር መንገድ ነው። የእዝነትና የርኅራሄ መንገድ ነው። የዕውቀትና የሳይንስ መንገድ ነው። የስልጣኔ መንገድ ነው። የሞራላዊ ግብረ ገብነትና የመልካም ስነምግባር መንገድ ነው። አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{ያ የትኛችሁ ሥራው ይበልጥ ያማረ መኾኑን ሊሞክራችሁ፣ሞትንና ሕይወትን የፈጠረ ነው፤እርሱም አሸናፊው መሓሪው ነው።}[አልሙልክ፡2]

እነሆማ መንገዱ ይህ ነው . . ከኛ በፊት ነቢዮችና መልክተኞች የተጓዙበት መንገድ፣ክቡራን ሶሓቦችና ከሁሉም ሕዝቦች፣ዘሮችና ቋንቋዎች እነሱን በመልካሙ ነገር ሁሉ የተከተሉ ተከታዮች (ታብዑን) የተጓዙበት የመታደል መንገድ ይህ ነው። በመጻኢው ቅርብ ዘመን የበላይነቱን ይዞ የሚመራው መንገድም ይህ ነው። የአላህ መልክተኛ  እንዲህ ይላሉ፦ {ይህ ጉዳይ (እስላም) ሌሊትና ቀን ከደረሱበት ቦታ ሁሉ በእርግጥ ይዳረሳል፤የጭቃም ሆነ የሱፍ ቤትን (ከተማና ገጠርን ሁሉ)፣በክቡር ሰው ከበሬታ ወይም በተዋራጅ ውርደት፣አላህ እስላምን ልዕልና በሚያላብሰው ከበሬታ ወይም ክሕደትን በሚያዋርድበት ውርደት፣አላህ ይህን ሃይማኖት ሳያስገባበት የሚቀር ቦታ አይኖርም።} [በአሕመድ የተዘገበ] ስለዚህም ዘላለማዊ ደስታና ተድላን ለመጎናጸፍ በዚህ መንገድ ከሚጓዙ ክቡራን ተጓዦች ቅፍለት ጋር ተቀላቀል።

እነሆማ መንገዱ ይህ ነው . . የተጓዘበትን ሰው ልብ በሐሴት የሚሞላ መድህን ነው . . መታደል ነው . . ይህ የደስተኝነት መንገድ ነው . . እናም ከዚህ ሳትቋደስ ቀርተህ ራስህን አትበድል፤ነፍስህን ከመጉዳትና ከመበደልም ተጠንቀቅ፤የደሰተኝነትን መንገድ፣የዘላለማዊ መታደልን መንገድ ያዝ። አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{ከወንድ ወይም ከሴት፣እርሱ አማኝ ኾኖ በጎን የሠራ፣መልካም ኑሮን በእርግጥ እናኖረዋለን፤ ይሠሩትም ከነበሩት ነገር በመልካሙ ምንዳቸውን እንመነዳቸዋለን።}[አልነሕል፡97]

እነሆማ ይህ ነው መንገዱ . . ጠበቅ አድርገህ ያዘው፤የዱንያ ሕይወትህን በደስተኝነት ምልዓት፣በእርጋታ፣በእፎይታና በእርካታ ኑር። አላህ (ሱ.ወ.) ዘንድ ያለው በላጭና ዘላለማዊ መሆኑንም አትርሳ። የወዲያኛው የኣኽራ ሕይወት እርካታና እፎይታ ዘላለማዊው እርካታና እፎይታ ነው። በዱንያ የመታደልንና በኣኽራም የመታደልን መንገድ ጌታችንና አምላካችን አላህ (ሱ.ወ.) አንድ ብቸኛ መንገድ አድርጎታል። የተቀሩት ሌሎች መንገዶችን በዱንያ እድለ ቢስነትን በኣኽራ እሳተ ገሀነምን ያካተቱ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል።

{ከግሣጼየም የዞረ ሰው፣ለርሱ ጠባብ ኑሮ አልለው፤በትንሣኤም ቀን ዕውር ኾኖ እንቀሰቅሰዋለን። ፦ ጌታዬ ሆይ! ለምን ዕውር አድርገህ አስነሳኸኝ? በእርግጥ የማይ የነበርኩ ስኾን ይላል።} [ጣሃ፡124-125]

በተጨማሪም አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{(ነገሩ) እንደዚሁ ነው፤ታምራታችን መጣችልህ፤ተውካትም፤እንደዚሁም ዛሬ ትትተዋለህ፤ይለዋል።}[ጣሃ፡126]

ይህን መንገድ ከመርሳት ወይም ሆን ብለህ ከመዘናጋት በእጅጉ ተጠንቀቅ . . የደስተኝነትና የመታደል መንገድ ይህ ነውና።

እነሆማ መንገዱ ይህ ነው . . ጉዞው በአላህ ተውሒድና ተውሒዱን በአካላዊ ተግባራት በማረጋገጥ፣በሁሉም ነቢያትና መልክተኞችም በማመን ልብ ውስጥ የሚጀምር፣ከዚህ ተነስቶ በኣኽራ ዘላለማዊ ተድላና ደስታ የሚያበቃ ጉዞ ነው። የጉዞው መነሻ ሁለቱን ቃላተ ምስክርነት በልብ አምኖ በአንደበት መናገር ነው። እነሱም {አሽሀዱ አን ላ እላሀ እልላሏህ ወአንነ ሙሐመደን ረሱሉሏህ} የሚሉ ቃላት ናቸው። ከአላህ በስተቀር ሌላ እውነተኛ አምላክ አለመኖሩንና ሙሐመድም የአላህ መልክተኛ መሆናቸውን እመሰክራለሁ ማለት ነው። ጉዞው በዚህ ቃለ ምስክርነት ተጀምሮ ከነቢዩ  አብሮነት ጋር ጀነት ውስጥ ወደ አላህ (ሱ.ወ.) ፊት በመመልከት ተድላና ደስታ የሚጠናቀቅ ጉዞ ነው። እናም አሁኑኑ፦ {አሽሀዱ አን ላ እላሀ እልላሏህ ወአንነ ሙሐመደን ረሱሉሏህ} በል . . ሕይወትህን በደስተኝነት ኑር፤በደስተኝነትም ሙት፤ከመቃብርህም ተነስተህ ወደ ዘላለማዊ ተድላና ደስታ ጀነቶች አቅና . . እነሆማ መንገዱ ይህ ነውና . . ይዘህ ካልተጓዝክበት ግን መልክተኛው ያለበት ግልጥ ባለ ሁኔታ የአላህን መልክት (ሱ.ወ.) ማድረስ ብቻ ነው። አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{ብትዞሩም፣በርሱ ወደ እናንተ የተላክሁበትን ነገር በእርግጥ አድርሼላችኋለሁ፤ጌታዬም ሌላችሁን ሕዝብ ይተካል፤ምንም አትጎዱትምም፤ጌታ በነገሩ ሁሉ ላይ ተጠባባቂ ነውና (በላቸው)።}[ሁድ፡57]