የደስተኝነት ጽንሰ ሐሳብና ትክክለኛ ምንነቱ

የደስተኝነት ጽንሰ ሐሳብና ትክክለኛ ምንነቱ

መታደል ወይም ደስተኝነት በሚለው ቃል ምንነት ላይ በሰዎች መካከል ልዩነት ይታያል። አንዳንዶቹ ከእርካታ፣ከምቾት፣ወይም ከገንዘብ፣ከሥልጣንና ከዝና . . ጋር የተቆራኘ አድርገው ይመለከቱታል። ለዚህም ሲሉ ብዙ ሰዎች በተለያዩ መንገዶች ደስተኝነትንና መታደልን በመፍለግ ሕይወታቸውን ያሳልፋሉ። እርግጥ ነው . . ደስተኝነት ወይም መታደል ውስጣዊ እርካታ፣ምቾት፣መረጋጋትና ሕሊናዊ እፎይታ ሲሰማ ከውስጥ የሚመነጭ ስሜት ነው። ይሁን እንጂ ሰዎች ስለ ደስተኝነት ያላቸው አመለካከት እንደ ባሕርያቸውና እንደ ዝንባሌያቸው፣እንደ ትልማቸውና እንደ ምኞቶቻቸው፣ሌላው ቀርቶ እንደ ማሕበረሰባዊ ልዩነቶቻቸውም መለያየት የተለያየ ነው። አንዳንዶቹ ደስተኝነትን በገንዘብና በሀብት፣በተንደላቀቀ ቤትና ኑሮ፣በክብርና በሥልጣን ውስጥ ሲመለከቱት፤ሌለሎቹ ደግሞ በጥሩ ሚስት ወይም ባል፣በልጆችና መልካም ቤተሰብ፣በሥራ ወይም በትምሕርት ደረጃ ውስጥ ያዩታል። ምናልባትም ደስተኝነትን ከሚወዱት ጋር በመገናኘት ወይም ከሚጠሉት በመገላገል፣ከዓለማዊ ደስታ ርቀው የምናኔ ሕይወት በመምራት፣ወይም ድሆችና ችግረኞችን በመርዳት ውስጥ የሚመለከቱም ይኖራሉ። በጣም አስገራሚው ግን ከነዚህ አንዳቸውን በእውነትና በእርግጠኝነት አንተ ደስተኛ ነህ ወይ? ብለን ስንጠይቅ መልሱ አሉታዊ መሆኑ ነው!!

ስለዚህም ለደስተኝነት የሚሰጠው ትርጓሜ እንደየሰውና እንደየሕብረተሰቡ የሚለያይ መሆኑን እንረዳለን። ለዚህም ይመስላል አንዳንድ ዓለም አቀፋዊ ድርጅቶች ‹‹የሕዝቦች የደስተኝነት መሰላል›› የተሰኘ መለኪያ በማስቀመጥና የተለያዩ መጣኞችን በመተንተን ለመሰላሉ ደረጃዎችን መድበው የትኞቹ ሕዝቦች ይበልጥ ደስተኞች እንደሆኑ ለማወቅ የፈለጉት። ውጤቱ ግን ለሁሉም ያልተጠበቀ ዱብ እዳ ነበር የሆነው። ሁላችንም እንደምናውቀው እያንዳንዱ አሜሪካዊ ከሚመራው ከፍተኛ የብልጽግና ሕይወት ተቃራኒ በሆነ ሁኔታ፣በመመዘኛው መሰረት ያሽቆለቆለ ነጥብ ያገኘው የዩ.ኤስ. አሜሪካ ሕዝብ ከሁሉም በላይ ደስተኛ ሳይሆን፣ከሁሉም ይበልጥ ደስተኝነት የራቀው ሆኖ ነበር የተገኘው። በጣም አስደናቂው ሆኖ የተስተዋለው በከባድ ድህነት ውስጥ ኑሮውን የሚገፋው የናይጄሪያ ሕዝብ ከዓለም ሕዝቦች ሁሉ ከፍተኛውን የደስተኝነት ነጥብ ያስመዘገበ፣ከሁሉም ይበልጥ ደስተኛ ሕዝብ ሆኖ መገኘቱ ነው!! 

ይህ የአሜሪካው ኒውዝዊክ መጽሔት የዓለማችን ይበልጥ ደስተኛው ሕዝብ የትኛው እንደሆነ ለማወቅ ያደረገው ዳሰሳ ውጤት ሲሆን፣በአብላጫው ሙስሊም የሆነው ደሃው የናይጄሪያ ሕዝብ ጥናቱ ውስጥ ከተካተቱ ስልሳ አምስት አገሮች ውስጥ በደስተኝነት የአንደኝነቱን ቦታ ይዟል። ቀጣዮቹን ደረጃዎች ሜክሲኮ፣ቬንዙዌላና ሰልቫዶር ሲይዙ፤የበለጸጉ አገሮች ግን - ዘገባ አቅራቢውን ባስደመመ ሁኔታ- በደስተኝነት መሰላሉ ዝቅተኛ ደረጃዎችን ይዘዋል። እዚህ ላይ ጥናቱ ያካተታቸው አብዛኞቹ አሜሪካውያን ደስተኝነት ከሀብትና ከገንዘብ1 ጋር የማይገናኝ መሆኑን አምነው የተቀበሉ መሆናቸውን ቆም ብለን ማየት ያስፈልግ ይሆናል። ይህ ተጣጣፊ በሆነና ከሁሉም ይበልጥ ተስፈንጣሪ በሆነ የካፒታሊዝም ዓይነት ላይ በተመሰረተ ሕብረተሰብ ውስጥ ያልተለመደ እንግዳ ነገር መስሎ ይታያል። አሜሪካ ውስጥ2 እየተስተዋለ ያለውን የሃይማኖትን ዳግም ተመልሶ መስፋፋት ክስተትን እንዲዳስስ ኋላ ላይ መጽሔቱን የገፋፋውም ይኸው ጉዳይ ነው። በዚህም አሜሪካውያን ደስተኝነትን ለማግኘት ሲሉ ለታከታዮቻቸው ነፍሶች ማከሚያነት በሚወሰዱት ጊዜያዊ ትኩረትን የማሰባሰብና የአስተውሎት ሕክምና አማካይነት ስለሚያደርጉት ብርቱ ጥረት ጥያቄዎች መነሳት ጀምረዋል።

ምናልባትም ስለ ደስተኝነት ምንነትና እንዴትስ ማገኘት እንደሚቻል ትርጓሜና ትንተና በሰጡት ብዙዎቹ ዘንድም ይህንኑ ችግር እናስተውላለን። በአፍላጦን አመለካከት ደስተኝነት የሰብእና ትሩፋቶች (ጥበብ፣ጀግንነት፣ቁጡብነትና ፍትሕ) ናቸው። በርሱ እምነት የሰው ልጅ ምሉእ የሆነ ደስተኝነት የሚያገኘው ነፍሱ ወደ ሌላኛው ዓለም ስትመለስ ብቻ ነው። አርስቶትል ደግሞ ደስተኝነትን ከአላህ የሚለገስ ችሮታ አድርጎ የሚመለከት ሲሆን፣አምስት ገጽታዎች አሉት ይላል። እነሱም፦ የአካልና የስሜት ሕዋሳት ደህንነት፣ሀብትን ማግኘትና በአግባቡ መጠቀም፣በሥራ ስኬታማ መሆንና ዓለማን እውን ማድረግ፣የአእምሮ ጤንነትና ትክክለኛ እምነት፣መልካም ዝና እና በሰዎች ዘንድ ተቀባይነትን ማትረፍ ናቸው። በስነልቦና ሳይንስ ደስተኝነትን የኑሮ ስኬት ደረጃ ነጽብራቅ ወይም የአስደሳች ነገሮች ሁነቶች ድግግሞሽ አማካይ ነጸብራቅ3 አድርጎ መረዳት ይቻላል። ይሁን እንጂ በደስተኝነት ጽንሰ ሐሳብ ግንዛቤ ዙሪያ ያለው ይህ ልዩነት ‹‹ደስተኝነት ምንድነው? እንዴትስ ደስተኛ መሆን እችላለሁ? ደስተኝነት እርካታን በማግኘት ብቻ እውን ሊሆን ይችላል?›› የሚሉ ጥያቄዎች በጥያቄነት እንዲቀጥሉ ያደርጋል። 

ደስተኝነት ከእርካታ የተለየ ነው፦

ሰው ብዙ ጊዜ የተለያዩ እርካታዎችን ፍለጋ ይባዝናል፤በለስ ቀንቶት ያገኘውን እርካታ ከማጣጣም አያመነታም። አርኪ ነገሮችን ሁሉ ቢያገኝ ደስተኝነትን አገኛለሁ ብሎ ይገምታል። ግና ከደስተኝነት ከማንም ይበልጥ ሩቅ መሆኑን በድንገት ይገነዘባል። ቁሳዊ እርካታዎች በዓይነት የተለያዩና በቅርጽና ይዘታቸውም ተለዋዋጮች ናቸው። ይሁን እንጂ ሁሉም እርካታና ሁሉም አርኪ ነገር ደስተኝነትን አያጎናጽፍም። በዚህ ምክንያት ነው በደስተኝነት ጽንሰ ሐሳብና በእርካታ ጽንሰ ሐሳብ መካከል መምታታት የሚፈጠረው። ትክክለኛው ግንዛቤ ሁለቱ በአንድ በኩል ሲገናኙ በሌላ በኩል ደግሞ የሚለያዩ መሆናቸው ነው። አንድነታቸው ሁለቱም እርካታን የሚሰጡ ከመሆናቸው አንጻር ነው። የሚለያዩት ደግሞ እርካታ ወዲያው መጥቶ መንስኤው ከሄደ በኋላ ወዲያውኑ አብሮት የሚጠፋ ብቻ ሳይሆን ቁጭትና ብርቱ ጸጸትን ትቶ ሊያለፍ የሚችል በመሆኑ ሲሆን፣ደስተኝነት ግን ለረዥም ጊዜ አብሮ የሚቆይ ከመሆኑ አንጻር ነው።

በእርካታና በደስተኝነት ግንዛቤዎች መካከል ያለው ይህ የመደበላለቅ ሁኔታ፣አንዳንድ ጊዜ ከራሱ ከግለሰቡ በኩል የሚመጣ ሲሆን፣ሁሉንም እርካታዎች ደስተኝነት አድርጎ የመመልከት አዝማሚያን ያሳያል። ዝነኛ መሆን በሰው ዘንድ ታዋቂ መሆንን፣ቅድሚያ ማግኘትንና ተቀባይነትን . . ስለሚያስገኝ ወደር የሌለው እርካታ ይሰጣል። ይህ ሁሉ የእርካታ ዓይነት ነው። ይሁን እንጂ ዝና እና ታዋቂነት፣ሀብትና ሥልጣንም ኖሮት ይህን ሁሉ ይዞ በጭንቀትና በውጥረት እየተሰቃየ ደስተኝነትን የተነፈገና ስነልቦና ሐኪሞች ዘንድ ለሕክምና የሚመላለስ፣ወይም ከጭንቀቱ ለመገላገል ሲል ራሱን በመግደል ሕይወቱን የቋጨ ሰው ቁጥሩ እጅግ ብዙ ነው!! ስንቶቹ ታዋቂና ዝነኛ ግለሰቦች ከጭንቀት ለመገላገል ሲሉ ራስን ማጥፋት እንደ መፍትሔ እንደወሰዱ ሁላችንም እናውቃለን!! ብዙዎች ደስታን ፍለጋ ከልክ ባለፈ ሥጋዊ ፍላጎት ውስጥ ተዘፍቀው በዝሙት የሚጠመዱ ሲሆን፣ከጥቂት ጊዜ በኋላ ግን የኤድስ ሰለባ ሆነው መቀጠፋቻውን እንሰማለን!! ሕገወጥ ወሲብ ጊዜያዊ እርካታ ሊሰጥ ይችል ይሆናል፤ግና በቋሚነት ቤተሰብን ያፈርሳል፣ለሕብረተሰቡም ጠንቅ ይሆናል። ወሲብ ነክ ፊልም አንድ ዓይነት ጊዜያዊ እርካታን ይሰጥ ይሆናል፤ግና የግለሰቡን ሰብእና ያወድማል፣የተቀደሰውን ትዳራዊ ትስስር ያናጋል፤የማሕበረሰቡን ደህንነትም አደጋ ላይ ይጥላል። ከሌሎች ፍላጎቶችና እርካታዎች ምግብ አንዱ ሲሆን፣ከመጠን ያለፈ የምግብ ፍላጎትም የሐኪሞችና የጤና ተቋማት ቋሚ እንግዳ መሆንን ያስከትላል!!

በሁለቱ ጽንሰ ሐሳቦች መካከል ያለው መምታታት አንዳንዴ ከተወሰኑ ወገኖች በኩል ሆን ተብሎ የሚደረግ ሲሆን፣ብዙዎች የተለያዩ የፍላጎት ማርኪያዎችን ደስተኝነትና የእውነተኛ ደስታ ምጭ እንደሆኑ አድርገው ለማሻሻጥ ሲጥሩ ይስተዋላሉ። ዓላማቸውም የሰውን ትኩረት በመቆጣጠር ወደ ተለያዩ አቅጣጫዎች መውሰድ ነው። እጽ ተጠቃሚ ወጣት መጀመሪያ ላይ መጠቀም የሚጀምረው ለጊዜያዊ እርካታው ሲሆን፣በኋላ ግን እጹን የሚያቀርብለት ሰው እንዳሻው የሚጫወትበት አሻንጉሊት ወደ መሆን ይሸጋገራል!

የተለያዩ ሸቀጦችን ለማሻሸጥ የሚቀርቡ ማስታወቂያዎችም የሰዎችን ትኩረት ስበው አእምሮን ስለሚቆጣጠሩ ሸማቹን ያደናግራሉ።

እናም ደስተኝነት አንድ ሰው የሚፈልገውን ሁሉ በማግኘቱ የሚደረስበት ነገር አይደለም ማለት ነው። እንዲህ ቢሆን ኖሮ የናጠጡ ሀብታሞችና መሪዎች ከሰው ሁሉ በላይ ደስተኞች በሆኑ ነበር። ሳይንሳዊ ጥናቶችና ተግባራዊ አስተውሎዎች ግን ይህንን ያስተባብላሉ። ምናባትም እንዲህ መሆኑ አላህ (ሱ.ወ.) በዚህ ዩኒቨርስ ውስጥ ያኖረው ምሉእ ፍትሑ አንዱ መገለጫ ሊሆን ይችላል። ብዙ ድሆችና ችግረኞች ደስተኞች መሆናቸውን መመልከት ይቻል የለም! ብዙ የተንደላቀቁ ሀብታሞች እነርሱ ዘንድ በሌሉና ድሆች ዘንድ በሚገኙ ብዙ ሕሊናዊ እርካታዎች ይቀኑ የለም!! ደስተኝነት ምናልባት በእረፍት ውስጥ ይገኝ ይሆን?! እስኪ እንመልከት።

ፈጽሞ. . ደስተኝነት እረፍት ውስጥ አይገኝም!!

ብዙ ሰዎች እረፍት ማለት ደስተኝነት ነው ብለው ስለሚገምቱ እረፍት ለማግኘት ይጥራሉ። እረፍት ግን ለጭንቀት፣ለሀሳብ፣ለድብርትና ለብቸኝነት ሊዳርግ ይችላል። ሰው ብዙ ጊዜ አካሉን እያደከመም ደስተኝነት የሚሰማው መሆኑንና አልፎ አልፎም ድካምና ችግር ራሱ ደስታና እርካታ የሚሆንበት ሁኔታ መኖሩን ይረሳል። ውሃ ጉድጓድ ውስጥ የወደቀ ሕጻን ሕይወት ለማትረፍ ራሱን ወደ ጉድጓዱ ለመወርወር የተገደደ ሰው ሊደርስበት የሚችለው የአካል ጉዳትና ስብራት፣የሚያስከትለው ሕመምና ስቃይ እንዳለ ሆኖ የሕጻኑን ሕይወት ለማትረፍ በመቻሉ ብቻ ደስተኝነት ይሰማዋል። ምሁራንና ተመራማሪዎች በጥናትና ምርምራቸው ላይ የሚገጥማቸው ችግር፣ድካምና ልፋት ከባድ ቢሆንም ወደ ከፍተኛ ደረጃ የሚያደርሳቸው በመሆኑ ልፋቱ ደስታና እርካታን ይሰጣቸው የለም?!! እስፖርተኛም እንዲሁ ላቡን እያንጠፈጠፈና ከከባድ ድካም ጋር እየታገለ ደስተኝነት ይሰማዋል። ድሆችንና ችግረኞችን ለመርዳት የተሰማራ በጎ አድራጊም ከድካሙና ከልፋቱ ጋር በሚሰጠው አገልግሎት ተደሳች ይሆናል። የሚወደውን ገንዘብና ንብረት ሌሎችን ለመርዳት ሲል የሚለግስ፣ጊዜውን፣ዕረፍቱንና የሚወደውን ነገር የሚሰዋ ሰውም ሕሊናዊ እርካታና ደስተኝነትን ያገኛል።

በዚህ የመጠለለፍ ሁኔታና ለደስተኝነት በሚሰጡ የተለያዩ ትርጓሜዎች ምክንያት፣የደስተኝነትን ምንነትና እውነተኛውን መታደል እንዴት ማግኘት እንደሚቻል ለማወቅ ያላሰለሰ ጥረት የሚያደርግ ሰው ግን ግራ መጋባቱን ይቀጥላል።