በቅርቢቱ ሕይወት ለደስተኝነት የሚያበቁ መረማመጃዎች በእስላም፦

በቅርቢቱ ሕይወት ለደስተኝነት የሚያበቁ መረማመጃዎች በእስላም፦

ዛሬ በምንኖረው ሕይወት ለመታደልና ደስተኝነትን ለማግኘት በእስላም ውስጥ በርካታ መረማመጃዎችና ምክንያቶች ይገኛሉ። ከነዚህም መካከል፦

1- በተውሒድና በአላህ በማመን የሚገኝ ደስተኝነት፦

ተውሒድ የሚያስገኘውን እፎይታ የሚመስል እፎይታ፣ተውሒድ የሚያላብሰውን ውስጣዊ መረጋጋት የመሰለ ውስጣዊ መረጋጋትም የለም። አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{እነዚያ ያመኑና እምነታቸውን በበደል ያልቀላቀሉ፣እነዚያ ለነርሱ ጸጥታ አላቸው፤እነሱም የተመሩ ናቸው።}[አል አንዓም፡82]

እናም በሚኖረን የተውሒድ ምሉእነት ደረጃና መጠንም በዱንያና በኣኽራም መድህንና መረጋጋትን፣መታደልና ደስተኝነትን እናገኛለን። አላህ (ሱ.ወ.) በተውሒዱ ልክ የባለቤቱን ልብ የሚያሰፋና ደስተኝነትን የሚያሰገባበት ሲሆን፣አላህ ይጠብቀንና ሽርክ ደግሞ በባለቤቱ ላይ ወደ ከፍታ ቦታ የሚወጣ ሰውን እንደሚያጋጥመው ዓይነት የልብ ጥበንና ጭንቀት ያስከትልበታል። አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{አላህም ሊመራው የሚሻውን ሰው፣ደረቱን (ልቡን) ለእስላም ይከፍትለታል፤ሊያጠመውም የሚሻውን ሰው፣ደረቱን ጠባብ፣ቸጋራ፣ወደ ሰማይ ለመውጣት እንደሚታገል፣ያደርገዋል። እንደዚሁ አላህ በነዚያ በማያምኑት ላይ ርክሰትን ያደርጋል።}[አል አንዓም፡125]

አላህ (ሱ.ወ.) ልቡን ለእስላም አስፍቶለት ከርሱ ዘንድ የሆነ ብርሃን የፈነጠቀለት ሰውና፤ በሽርክና፣በጣዖታዊነት፣በግልጽ ጥመትና አላህን (ሱ.ወ.) በመርሳት ጽልመት ውስጥ የሚዳክር ሰው ፈጽሞ እኩል አይደሉም። አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{አላህ ደረቱን ለእስላም ያሰፋለትና እርሱም ከጌታው ዘንድ በብርሃን ላይ የኾነ ሰው፣(ልቡ እንደ ደረቀ ሰው ነውን?) ልቦቻቸውም ከአላህ መውሳት ለደረቁ ሰዎች ወዮላቸው፤እነዚያ በግልጽ መሳሳት ውስጥ ናቸው።}[አል ዙመር፡22]

በሽርክ ጨለማ ውስጥ ሙት የነበረና አላህ (ሱ.ወ.) በቸርነቱና በእዝነቱ በተውሒድ ሕያው ያደረገው ሰው፣ፈጽሞ በማይወጣ ሁኔታ በሽርክ ጨለማ ውስጥ ሰምጦ እንደቀረ ሰው አይደለም። አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{ሙት የነበረና ሕያው ያደረግነው፣ለርሱም በሰዎች መካከል በርሱ የሚኼድበትን ብርሃን ያደረግንለት ሰው፣በጨለማዎች ውስጥ ከርሷ የማይወጣ ኾኖ እንዳልለ ሰው ብጤ ነውን? እንደዚሁ ለከሃዲዎች ይሠሩት የነበሩት ነገር ተጌጠላቸው።}[አል አንዓም፡122]

2- የአላህ (ሱ.ወ.) ውዳሴ፣እርሱን መማጸንና ወደርሱ መቃረብ፦

የሰው ልጅ የፈለገውን ያህል ዓለማዊ መጠቀሚያና መደሰቻ ቢሰጠው፣ያሻውን ያህል የመደሰቻና የእርካታ ማግኛ መንገዶችን ቢታደል፣ከአላህ (ሱ.ወ.) መንገድ የራቀ እስከሆነ ድረስ እውነተኛውን ደሰተኝነት ማግኘት አይችልም። እውነተኛ ደስተኝነትና እርካታ ማግኘት የሚችለው ወደ አላህ (ሱ.ወ.) ሲቀርብ፣በውዳሴው ጥላ ስርና በርሱ አፀድ ውስጥ ሲሆን ብቻ ነው። አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{(እነሱም) እነዚያ ያመኑ፣ልቦቻቸውም አላህን በማውሳት የሚረኩ ናቸው፤ንቁ አላህን በማውሳት ልቦች ይረካሉ።}[አል ረዕድ፡28]

ለምን ቢባል፦ {ልብ ውስጥ ወደ አላህ (ሱ.ወ.) ፊትን መመለስ ብቻ የሚያሰባስበው መዋለል ይገኛል። ለብቻው ገለል ሲልም በርሱ መጽናናት ብቻ የሚያስወግደው ብቸኝነትና መቦዘንም አለበት። እርሱን የማወቅና በፍጹምነት እርሱን የመግገዛት ደስተኝነት ብቻ የሚያስወግደው ሐዘንም ይገኝበታል። ወደርሱ መሰባሰብና ከርሱ ወደርሱ መሸሽ ብቻ የሚያረጋጋው ጭንቀትም አለበት። ትአዛዙን፣እገዳውንና ውሳኔውን ወዶ መቀበልና ከርሱ ጋር እስከሚገናኝበት ጊዜ ድረስ በዚያ ላይ መታገስ ብቻ የሚያጠፋው የቁጭት እሳትም አለበት። ተፈላጊው እርሱ ብቻ እስኪሆን ድረስ የማይገታ ብርቱ ፍላጎትም አለበት። በርሱ ፍቅር፣ወደርሱ በመመለስ፣ዘውትር እርሱን በማውሳትና በእርግጠኝነት ለርሱ ፍጹም በመሆን ብቻ የሚሸፈን እጦትም ይገኝበታል፤ዱንያና በርሷ ውስጥ ያለው ሁሉ ቢሰጠው እንኳ ያንን እጦት ፈጽሞ መሸፈን አይችልም።}1

3- መልካም ሥራ፦

አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{እነዚ ያመኑትና መልካም ሥራዎችን የሠሩት፣ለነሱ ደግ ኑሮ፣መልካም መመለሻም አላቸው።}[አል ረዕድ፡29]

እነዚያ ከልቦቻቸው በአላህ፣በመላእኮቹ፣በመጽሐፎቹ፣በመልክተኞቹና በመጨረሻው ቀን ያመኑና ይህን እምነት በመልካም ሥራዎች ማለትም አላህን መውደድ፣እርሱን መፍራት፣እርሱን ብቻ ተስፋ ማድረግ በመሳሰሉ የልብ ሥራዎችና ሶላትን በመሳሰሉ አካላዊ ሥራዎች በተግባር ያረጋገጡ ሰዎች የተሟላ እፎይታና የተሟላ መረጋጋት ይታደላሉ። ይህም በዱንያና በኣኽራ ሕይወታቸው ከአላህ (ሱ.ወ.) ውዴታና ከበሬታውን የተቸሩ በመሆናቸው ነው። ስለዚህም ከኢማን ጋር በመልካም ሥራ ላይ መሰማራት ይኖርብናል። አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{እነዚያ ያመኑና እነዚያም ይሁዳውያን የኾኑ፣ሳቢያኖችም፣ክርስቲያኖችም፣(ከነርሱ) በአላህና በመጨረሻው ቀን ያመነና መልካምን ሥራ የሠራ ሰው፣በነርሱ ላይ ፍርሃት የለባቸውም፤እነርሱም አያዝኑም።}[አል ማእዳህ፡69]

ነቢዩ  እርካታና እፎይታቸውን በሶላትና በአምልኮተ-አላህ (በእባዳ) ውስጥ ያገኙ የነበረ ሲሆን ይህንኑ በማስመልከት እንዲህ ብለዋል፦ {ቢላል ሆይ! ለሶላት የመጨረሻውን ጥሪ (እቃማህ) አድርግና በርሱ እፎይ አሰኘን፣አርካን፡፡} 

4- ልገሳ የደስተኝነት ምስጢር ነው፦

ይህ በተግባር የታየና የተረጋገጠ ጉዳይ ነው። ለሌሎች በጎ የሚሠራ ሰው ከሰው ሁሉ ደስተኛ መሆኑና በምድር ላይ ከሌሎች ይበልጥ ተቀባይነት የሚቸረው ሰው መሆኑን እናውቃለን። አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{የምትወዱትን እስከምትለግሱ ድረስ በጎ ሥራን አታገኙም። የምትለግሱትን ማንኛውንም ነገር፣አላህ ያውቀዋል።}[ኣሊ ዒምራን፡92]

ልገሳ የተለያዩ ገጽታዎች አሉት። ገንዘብ መስጠትን አላህ (ሱ.ወ.) አንዱ የእስላም ማእዘን አድርጓ ከሀብታሙ ተወስዶ ለድሃው የሚከፈለውን ዘካ በግዴታነት ደንግጓል። ይህ ልገሳም ጉራና መመጻደቅ በማይኖርበት ሁኔታ ለአላህ (ሱ.ወ.) ልቦናን ፍጹም በማድረግ ከሚወዱት ነገር እንዲሆንም ደንግጓል። አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{እናንተ ያመናችሁ ሆይ! . . ምጽዋቶቻችሁን በመመጻደቅና በማስከፋት አታበላሹ።}[አል በቀራህ፡264]

ልገሳውም በገንዘብ ላይ ብቻ የሚወሰን ሳይሆን ወደ ሁሉም ዓይነት ልገሳ በመስፋት ገንዘብን፣ምግብን፣ዕውቀትና ጉልበትንም ያጠቃልላል። አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{ምግብንም፣ከመውደዳቸው ጋር ለድኻ፣ለየቲምም፣ለምርኮኛም፣ለእስረኛም ያበላሉ። የምናበላችሁ ለአላህ ውዴታ ብቻ ነው፤ከናንተ ዋጋንም ማመስገንንም አንፈልግም።}[አል ደህር፡8-9]

ምጽዋትና ልገሳ ሌላው ቀርቶ በፈገግታና በጥሩ ፊት ብቻ እንኳ ሊገለጽ ይችላል። ነቢዩ  ፦ {ወንድምህን በፈካ ፊት በፈገግታ መቀበል ሶደቃ (ምጽዋት) ነው።} [በትርምዚ የተዘገበ] ብለዋል። በተጨማሪም ነቢዩ  ፦ {የወንድሙን ጉዳይ ለማሳካት የተሰማራን ሰው አላህ የርሱ ጉዳይ አስፈጻሚ ይሆንለታል። ለአንድ ሙስሊም አንድን ችግር የፈታለት ሰው፣በዚያ ከትንሳኤው ቀን ችግሮች አንዱን ችግር ያስወግድለታል። የአንድን ሙስሊም ገበና የሸፈነለትን ሰው፣አላህ በትንሳኤው ቀን ገበናውን ይሸፍንለታል።} ብለዋል። [በአቡ ዳውድ የተዘገበ] ይህ ልገሳ በዓለማዊ ሕይወትም ደስተኝነትን የሚያጎናጽፍ መሆኑ ጥርጥር የለውም። አንዳች ቁሳዊ ጥቅም ለማግኘት ወይም ለጉራና ለመመጻደቅ የሚለገስ ከሆነ ግን መስሎ ቢታይ እንኳ ምንም ዓይነት ደስተኝነት አያስገኝም።

5- በአላህ (ሱ.ወ.) ላይ መመካት (ተወኩል) የደስተኝነት መክፈቻ ቁልፍ ነው፦

ሰው ብዙ ጊዜ አንድ ነገር ለማድረግ ፈልጎ የአቅም ማነስ ወይም ያለመቻል ስሜት ይጠናወተውና የፈለገውን ለማድረግ ይችል ዘንድ አቅም ባለውና በሚተማመንበት ሌላ ወገን መታገዝን አስፈላጊ ሆኖ ያገኛል። ለዚህ ከአላህ (ሱ.ወ.) የበለጠ ብርቱ ኃይልና ረዳኢ ከቶም የት አለና?! የሰማያትና የምድር ግዛት በእጁ ወደ ሆነው፣የሻውን ነገር የማድረግ ፍጹማዊ ሥልጣን የርሱ ብቻ ወደ ሆነው ኃያሉ ቻይ ጌታ ወደ አላህ መጠጋትና በርሱ ላይ መተማመን የደስተኝነት መክፈቻ ቁልፍ ነው። አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{ነገሩም፣አንዳችን በሻ ጊዜ፣ኹን ማለት ነው፤ወዲውኑ ይኾናልም።}[ያሲን፡82]

ለዚህም ነው አላህ (ሱ.ወ.) በርሱ ላይ ብቻ እንድንተማመንና በርሱ ብቻ እንድንመካ ያዘዘን። አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{ምእመናንም እንደ ኾናችሁ በአላህ ላይ ተመኩ አሉ።}[አል ማእዳህ፡23]

ከርሱ ወዲያ መተማመኛ የለም፤መጠጊያና መመኪያም በርሱ በቃ። አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{በአላህም ላይ ተጠጋ፤መጠጊያም በአላህ በቃ።}[አል ኒሳእ፡81]

ይህን ማድረግ ያለ ጥርጥር እርካታን፣እፎይታን፣መረጋጋትን፣መብቃቃትን፣ደስተኝነትንና ሞክረው ያዩት ብቻ የሚያውቁትን ስኬታማነት ያስጨብጣል። አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{አላህንም የሚፈራ ሰው፣ለርሱ መውጫን ያደርግለታል። ከማያስበውም በኩል ሲሳይን ይሰጠዋል፤በአላህም ላይ የሚጠጋ ሰው፣እርሱ በቂው ነው፤አላህ ፈቃዱን አድራሽ ነው፤አላህ ለነገሩ ሁሉ የተወሰነ ጊዜን በእርግጥ አድርጓል።}[አል ጦላቅ፡2-3]

ተወኩል በተጨማሪም ከተረገመው ሰይጣን በአላህ (ሱ.ወ.) መጠበቅንም ያስገኛል። አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{እርሱ በነዚያ ባመኑትና በጌታቸው ላይ በሚጠጉት ላይ ለርሱ ሥልጣን የለውምና።}[አል ነሕል፡99]

ከጠላት ጥቃትም ይከላከላል። አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{እነዚያ ሰዎቹ ለነርሱ፦ ሰዎች ለናንተ (ጦርን) አከማችተዋልና ፍሩዋቸው ያሉዋቸውና (ይህም) እምነትን የጨመረላቸው፣በቂያችንም አላህ ነው፣ምን ያምርም መጠጊያ! ያሉ ናቸው። ከአላህም በኾነ ጸጋና ችሮታ ክፉ ነገር ያልነካቸው ኾነው ተመለሱ፤የአላህንም ውዴታ ተከትተሉ፤አላህም የታላቅ ችሮታ ባለቤት ነው። ይሃችሁ፣ሰይጣን ብቻ ነው፣ወዳጆቹን ያስፈራራችኋል፤አትፍሩዋቸውም፤ምእመናንም እንደኾናችሁ ፍሩኝ።}[ኣሊ ዒምራን፡173-175]

የተወኩል ምስጢርና እውነታው የልብ በአላህ ላይ ብቻ መተማመንና በርሱ ብቻ መመካት ነው። ልቡ ከርሱ በስተቀር በሌላ ላይ ከመተማመንና ከመጠጋት የጸዳ እስከሆነ ድረስ ውጤትን ከሳቢያ ለመጠበቅ መረማመጃ ምክንያቶችን (አስባብ) ሁሉ መጠቀም ጉዳት አያስከትልበትም። በተመሳሳይ መልኩም ልቡ በሌላ ላይ እየተንጠላጠለ፣በሌላ እየተመካና ወደ ሌላ እየተጠጋ በአንደበቱ {ተወከልቱ ዐለልሏህ}፣በአላህ ላይ እተማመናለሁ ማለቱ ምንም አይጠቅመውም። በምላስ መተማመንና በልብ መተማመን የተለያዩ ነገሮች ናቸውና። (17)

6- ደስተኝነት በእርግጠኝነት (የቂን) እና በአላህ ላይ በመተማመን ውስጥ ነው፦

ኢማን ለአማኙ ሰው እርግጠኝነትንና ሙሉ በሙሉ በአላህ (ሱ.ወ.) ላይ መተማመንን እውን ያደርግለታል። ይህም በራስ መተማመንን ስለሚያላብሰውና ነገሩ ሁሉ በአላህ (ሱ.ወ.) እጅ መሆኑን ስለሚረዳ በዚህ ሕይወቱ ውስጥ ምንም ነገር አያሰጋውም። አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{አላህም በጉዳት ቢነካህ፣ለርሱ (ለጉዳቱ) ከርሱ በቀር ሌላ አስወጋጅ የለም፤በበጎም ነገር ቢነካህ እርሱ በነገሩ ሁሉ ላይ ቻይ ነው።}[አል አንዓም፡17]

ሙእምን ሰው፣ለርሱ የተጻፈው ሲሳይም በአላህ (ሱ.ወ.) እጅ ውስጥ ብቻ መሆኑንም በእርግጠኝነት ይገነዘባል። አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{ከአላህ ሌላ የምትግገዙት፣ጣዖታትን ብቻ ነው፤ውሸትንም ትቀጣጥፋላችሁ፤እነዚያ ከአላህ ሌላ የምትግገዟቸው ለናንተ ሲሳይን ሊሰጧችሁ አይችሉም፤ስለዚህ ሲሳይን ከአላህ ዘንድ ብቻ ፈልጉ፤ተገዙትም፤ለርሱም አመስግኑ፤ወደርሱ ትመለሳላችሁ።}[አል ዐንከቡት፡17]

በምድር ላይ የሚንቀሳቀስ ማንኛውንም ፍጥረት የመመገብ ዋስትናን አላህ (ሱ.ወ.) ለራሱ ወስዷል። አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{በምድርም ላይ ምንም ተንቀሳቃሽ የለችም፣ምግቧ በአላህ ላይ ቢኾን እንጂ፤ማረፊያዋንም፣መርጊያዋንም፣ያውቃል፤ሁሉም ግልጽ በኾነው መጽሐፍ ውስጥ ነው።}[ሁድ፡6]

ምግቡን ራሱ ተሸክሞ ማምጣት የማይችል ፍጥረት ቢሆን እንኳ አላህ (ሱ.ወ.) ይመግበዋል። አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{ከተንቀሳቃሽም ምግቧን ለመሸከም የማትችለው ብዙ ናት፣አላህ ይመግባታል፤እናንተንም፣(ይመግባል)፤እርሱ ሰሚው ዐዋቂው ነውና።}[አል ዐንከቡት፡60]

ለርሱ የተመደበው ሲሳይ የግድ የሚመጣለት መሆኑንና ይህም ምንም ጥርጣሬ የሌለበት እውነት ስለመሆኑም እርግጠኛ ይሆናል። አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{ሲሳያችሁም፣የምትቀጠሩትም (ፍዳና ምንዳ) በሰማይ ውስጥ ነው። በሰማይና በምድር ጌታም እምላለሁ፣እርሱ እናንተ እንደምትናገሩት ብጤ እርግጠኛ ነው።}[አል ዛርያት፡23]

አላህ (ሱ.ወ.) ሲሳይን ለሰዎች ሁሉ ወስኖና መጥኖ የከፋፈለላቸው መሆኑንም በእርግጠኝነት ይገነዘባል። አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{በላቸው፦ ጌታዬ ሲሳይን ለሚሻው ሰው ያሰፋል፤ያጠባልም፤ግን አብዛኛዎቹ ሰዎች አያውቁም።}[ሰበእ፡36]

አላህ (ሱ.ወ.) ሁሌም በጥሩውና በመጥፎውም የሚፈትነው መሆኑንም የማያወላውልና የጸና እምነት ያምናል። አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{ነፍስ ሁሉ ሞትን ቀማሽ ናት፤ለመፈተንም በክፉም በበጎም እንሞክራችኋለን፤ወደኛም ትመለሳላችሁ።}[አል አንቢያ፡35]

የአላህ (ሱ.ወ.) ርህራሄና እዝነቱ ባይኖር ኖሮ በአስከፊ ሁኔታ እንደሚጠፋም ይረዳል።

ዕድሜው ረዘመም አጠረ፣በዚህች ዓለም ላይ ተላላፊ እንግዳ መሆኑን፣ያለ አንዳች ጥርጥር ወደ ወዲያኛው ዓለም እንደሚሸጋገርም ያውቃል። ስለዚህም በዚህ ዓለም ላይ ሕይወቱን የሚመራው ከዚህ መሰረታዊ መርህ በመነሳት ነው። የኑሮ ውጣ ውረዶችን አይፈራም፤ጠላቱ በአንድ ክንድ ወይም ከዚያ ባነሰ ርቀት ወደርሱ የቀረበ ቢሆን እንኳ ከአላህ (ሱ.ወ.) በስተቀር ማንንም አይፈራም። ፈርዖንና ሰራዊቱ ወደ ነቢዩ ሙሳ  የደረሱበትን ቅጽበት አስመልክቶ አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{ሁለቱ ጭፍሮችም በተያዩ ጊዜ፣የሙሳ ጓዶች እኛ (የፈርዖን ሰዎች) የሚደርሱብን ነን፣አሉ። (ሙሳ)፦ ተውዉ! ጌታዬ ከኔ ጋር ነው፤በእርግጥ ይመራኛል አለ። {ወደ ሙሳም ባሕሩን በበትርህ ምታው ስንል ላክንበት፣(መታውና) ተከፈለም፤ክፍሉም ሁሉ እንደ ታላቅ ጋራ ኾነ። እዚያም ዘንድ ሌሎችን አቀረብን። ሙሳንና ከርሱ ጋር ያሉትንም ሰዎች፣ሁሉንም አዳን። ከዚያም ሌሎቹን አሰጠምን። በዚህ ውስጥ ታላቅ ታምር አለበት፤አብዛኞቻቸውም አማኞች አልነበሩም።}[አል ሹዐራ፡61-67]

የእርግጠኞች ሁሉ ቁንጮ የሆኑት ሙሐመድ  ጠላታቸው ወደ እግሮቹ ቢመለከት ሊያገኛቸው በሚችልበት ሁኔታ ውስጥ ሆነው፣ሙሽሪኮቹ ሊገድሏቸው እያሳደዷቸው፣አብሯቸው ዋሻው ውስጥ ለሚገኙት ባልደረባቸው ለአቡበክር (ረ.ዐ.) የተናገሩትን በማስመልከት አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{አትዘን፣አላህ ከእኛ ጋር ነውና ባለ ጊዜ፣አላህ እርካታውን በርሱ ላይ አወረደ፤ባላያችኋቸውም ሰራዊት አበረታው፤የነዚያንም የካዱትን ሰዎች ቃል ዝቅተኛ አደረገ፤የአላህም ቃል እርሷ ከፍተኛ ናት፤አላህም አሸናፊ ጥበበኛ ነው።}[አል ተውበህ፡40]

አማኝ ሰው የሞት ቀጠሮና ውሳኔው በአላህ (ሱ.ወ.) እጅ ብቻ መሆኑን በእርግጠኝነት ስለሚያውቅ ሞትን አይፈራም። አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{አላህ ነፍሶችን በሞታቸው ጊዜ ይወስዳል፤ያችንም ያልሞተችውን በእንቅልፏ ጊዜ፣(ይወስዳታል)፤ታዲያ ያችን ሞትን የፈረደባትን ይይዛታል፤ሌላይቱንም እስከ ተወሰነ ጊዜ ድረስ ይለቃታል፤በዚህ ውስጥ ለሚያስተነትኑ ሕዝቦች ምልክቶች አሉበት።}[አል ዙመር፡42]

ሙእምን ሰው፣ሞት ፈጽሞ ሊሸሹት የማይቻልና የማይቀር እውነታ መሆኑንም በእርግጠኝነት ያውቃል። አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{ያ ከርሱ ምትሸሹት ሞት፣እርሱ በእርግጥ አግኛችሁ ነው፤ከዚያም ሩቁንና ቅርቡን ዐዋቂ ወደኾነው (ጌታ) ትመለሳላችሁ፤ትሠሩትም የነበራችሁትን ሁሉ ይነግራችኋል በላቸው። }[አል ጁሙዓ፡8]

ሞት ተወስኖ በተጻፈለት ቀነቀጠሮ እንጂ የማይመጣ መሆኑንም ይረዳል። አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{አላህም ሰዎችን በበደላቸው በያዛቸው ኖሮ፣በርሷ (በምድር) ላይ ከተንቀሳቃሽ ምንም ባልተወ ነበር፤ግን እስከ ተወሰነ ጊዜ ድረስ ያቆያቸዋል፤ጊዜያቸውም በመጣ ወቅት፣አንዲትን ሰዓት አይቆዩም፤አይቀደሙምም።}[አል ነሕል፡61]

7- ወዶ መቀበልና በተሰጡት መርካት (ሪዷ) የደስተኝነት መግቢያ በር ነው፦

ደስተኝነት አላህ (ሱ.ወ.) የሰጠውን ወዶ መቀበልና ባለው መርካት ነው። መብሰልሰል፣መቆጨትና መከፋት ግን የሰውን ሕይወት፣መንፈሱንና ስሜቱን የሚበክል መርዝ ነው። በተሰጡት ዕጣ ፈንታ ረክቶ የአላህን ውሳኔና እርሱ የመረጠውን ወዶ መቀበል (ሪዷ) የደስተኝነት፣የእርካታ፣የእፎይታና የመታደል መግቢያ በር ነው። ይህ እርካታ የሰው ልጅ የሚያጋጥመውን ሁሉ በጎ፣አስደሳች፣ገንቢና ጠቃሚ እንዲሆን ያደርጋል። ይህ ሲሆንም ነፍሱ ከፈጣሪ ጌታዋ በስተቀር ከሌላ ምንም አትከጅልም፤ባመለጣት ዓለማዊ ደስታም አትቆጭም። በአላህ ውሳኔ ረክቶ ጥረትና ትጋቱን እየቀጠለ መልካሙን ሁሉ ከጌታው ይለምናል። ሪዷ የተለያዩ መልኮች ያሉት ሲሆን፣አንዳንዶቹ የሚከተሉት ናቸው፦

ሀ) አላህን በጌትነት፣እስላምን በሃይማኖትነት፣ሙሐመድን  በነቢይነትና በመልክተኛነት ወዶና ረክቶ መቀበል አንዱ ነው። ይህን ወዶና ረክቶበት ያልተቀበለ ሰው፣በማያቋርጥ ጭንቀትና የግራመጋባት ሁኔታ ውስጥ ይኖራል። ነቢዩ  እንዲህ ብለዋል፦ {አላህን በጌትነት፣እስላምን በሃይኖትነት፣ሙሐመድን  በመልክተኛነት ወዶና ረክቶ የተቀበለ ሰው የኢማንን ጣዕም ቀምሷል።} [በቡኻሪ የተዘገበ] የኢማንን ጥፍጥና ያልቀመሰ ሰውም የደስተኝነትን ጣዕም አልቀመሰም፤ሕይወቱ የመከፋትና የጭንቀት ሕይወት እንደሆነ ይቀጥላል። የአላህን ጌትነት ወዶ መቀበል ማለት በአላህ (ሱ.ወ.) መኖር ማመን፣የፈጣሪ አምላክን ኃያልነት፣ጥበቡን፣ችሎታውን፣ፍጹማዊ ዕውቀቱን፣መልካሞቹን ስሞቹን ማወቅ ማለት ነው። በርሱ ማመንን፣አምልኮቱንና ለርሱ ብቻ ተገዥ መሆንን በእርካታ መቀበል ማለት ነው። ይህን ያላደረገ ሰው፣አላህ ይጠብቀንና በጥርጣሬና በግራ መጋባት፣በሕመምና በጭንቀት ውስጥ የሚኖር ነው።

ለ) የአላህን ፍርድና ሸሪዓውን በእርካታ ወዶ መቀበል ሌላው የሪዷ ገጽታ ነው። አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{በጌታህም እምላለሁ (አላህ በራሱ መማሉ ነው)፣በመካከላቸው በተከራከሩበት ፍርድ እስከሚያስፈርዱህ፣ከዚያም ከፈረድከው ነገር በነፍሶቻቸው ውስጥ ጭንቀትን እስከማያገኙና ፍጹም መታዘዝን እስከሚታዘዙ ድረስ አያምኑም (ምእመን አይኾኑም)።}[አልኒሳእ፡65]

የሰው ልጆች፣የሚበጃቸውን ሁሉ የሚያውቀው ፈጣሪያቸውን ሕግጋት ትተው ሰው ሠራሽ በሆኑ ጎጂና ጎደሎ ሕግጋትና ሥርዓቶች በመተዳደራቸው፣ብዙ አስከፊ ችግሮችንና የሕይወት ፈተናዎችን ለመጋፈጥ፣ስቃይ አበሳቸውንም ለመጋት ተገደዋል። አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{የፈጠረ አምላክ እርሱ ዕውቀተ ረቂቁ፣ውስጥ ዐዋቂው ሲኾን (ምስጢርን ሁሉ) አያውቅምን?)}[አል ሙልክ፡14]

ሐ) የአላህን (ሱ.ወ.) ፍርድና ቅድመ ውሳኔውን ወዶ በእርካታ መቀበልም ሌላው የሪዷ ገጽታ ነው። እናም ሙስሊም ሰው ከአላህ (ሱ.ወ.) መሻትና ቅድመ ውሳኔ ውጭ ምንም ነገር እንደማያገኘውና እርሱ ልቡን እንደሚመራው በውስጡ እርግጠኝነትን ስለሚያሳድር የአላህን ቀዷእና ቀደር በጸጋና በውዴታ ይቀበላል። አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{ከመከራም (ማንንም) አይነካም፣በአላህ ፈቃድ ቢኾን እንጅ፤በአላህም የሚያምን ሰው፣ልቡን (ለትዕግስት) ይመራዋል፤አላህም ነገሩን ሁሉ ዐዋቂ ነው።}[አል ተጋቡን፡11]

ሙስሊሙ ችግርና መከራን ከአላህ በስተቀር ማስወገድ የሚችል አለመኖሩን በእርግጠኝነት ስለሚያውቅ የአላህን ቀዷእና ቀደር (ሁሉም ነገር በርሱ ዕውቀት፣በርሱ መሻትና ቅድመ ውሳኔ ብቻ የሚፈጸም መሆኑን) በጸጋና በእርካታ ይቀበላል። አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{አላህም ጉዳትን ቢያደርስብህ፣ከርሱ ሌላ ለርሱ ገላጭ የለውም፤በጎንም ነገር ቢሻልህ፣ለችሮታው መላሽ የለም፤ከባሮቹ የሚሻውን በርሱ ይለይበታል፤እርሱም መሓሪ አዛኝ ነው።}[ዩኑስ፡107]

በጣም አስደናቂው ነገር፣እምነት አማኙ ከአላህ (ሱ.ወ.) የተወሰነለትን ዕጣ ፈንታ ወዶ በእርካታ እንዲቀበል፣ችግርና መከራን በትዕግስት እንዲያሳልፍ፣የአላህን (ሱ.ወ.) ጸጋና ቸርነቱን እንዲያመሰግን የሚያደርገው መሆኑ ነው። ይህን ውስጣዊ እርካታ ማግኘት የሚችሉት ምእመናን ብቻ ናቸው። ነቢዩ  እንዲህ ብለዋል፦ {ሙእምን ሰው ነገሩ ሁሉ አስደናቂ ነው። የርሱ ነገር ሁሉ ለበጎ ነው፤ይህ ለማንም ሳይሆን ለአማኝ ሰው ብቻ የሚሆን ነው። አስደሳች ነገር ሲያጋጥመው ያመሰግናል፣በጎም ይሆንለታል። ክፉ ነገር ቢያጋጥመውም ይታገሳል፣በጎም ይሆንለታል።}[በሙስሊም የተዘገበ] ሌላው ቀርቶ በዓለማዊ ጸጋና ሀብት ከኛ በላይ የሆኑትን ስናይ በተሰጠን እንዴት እንደምንረካም ነቢዩ  ሲያስተምሩን እንዲህ ብለዋል፦ {አላህ የዋለላችሁን ጸጋ እንዳትንቁ ለማድረግ ይበልጥ የተገባ ነውና፣(በቁሳዊ ሀብት) ከናንተ በታች የሆኑትን ተመልከቱ እንጂ ከናንተ በላይ የሆኑትን አትመልከቱ።} [በቡኻሪና ሙስሊም የተዘገበ]