የእውነተኛ ሃይማኖት መመዘኛዎች-1

የእውነተኛ ሃይማኖት መመዘኛዎች

የአንድ እምነት ተከታይ የሆነ ሰው የርሱ እምነት ከተቀሩት እምነቶች ሁሉ ትክክለኛውና ዓይነተኛው እምነት ስለመሆኑ ሁሌም ሙሉ በሙሉ እርግጠኛ ሆኖ እናገኘዋለን። የያንዳንዱ እምነት ተከታይም ይህን የሚተነትንበት የራሱ የተለየ መንገድ አለው። የብልሹ ሰው ሠራሽ ወይም የተዛቡ ሃይማኖቶች ተከታዮች የእምነታቸውን ትክክለኛነት የሚተነትኑት አባቶቻቸው ይህንኑ ሲከተሉ ያኟቸው መሆኑንና የነሱን ዱካ የሚከተሉ መሆናቸውን በመግለጽ ነው። አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{(ነገሩ) እንደዚሁም ነው፤ከበፊትህ በማንኛይቱም ከተማ ውስጥ አስፈራሪን አልላክንም፣ቅምጥሎችዋ፣እኛ አባቶቻችንን በሃይማኖት ላይ አገኘን፤እኛም በፈለጎቻቸው ላይ ተከታዮች ነን ያሉ ቢኾኑ እንጅ። (አስፈራሪው) አባቶቻችሁን በርሱ ላይ ከአገኛችሁበት ይበልጥ ቀጥተኛን (ሃይማኖት) ባመጣላችሁም? አላቸው፤እኛ በርሱ በተላካችሁበት ነገር ከሓዲዎች ነን አሉ።}[አል ዙኽሩፍ:23-24]

በተጨማሪም አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{ለነርሱም አላህ ያወረደውን ተከተሉ በተባሉ ጊዜ፣አይደለም አባቶቻችንን በርሱ ላይ ያገኘንበትን ነገር እንከተላለን ይላሉ፤አባቶቻቸው ምንም የማያውቁና (ወደ አውነት) የማይመሩም ቢኾኑ (ይከተሉዋቸዋልን?) የነዚያም የካዱት(ና ወደ ቅን መንገድ የሚጠራቸው ሰው) ምሳሌ እንደዚያ ድምጽንና ጥሪን በስተቀር ሌላን በማይሰማ (እንስሳ) ላይ እንደሚጮኽ ብጤ ነው፤(እነርሱ) ደንቆሮዎች፣ዲዳዎች፣ዕውሮች ናቸው፤ስለዚህ እነርሱ አያውቁም።}[አል በቀራህ:170-171]

አቋማቸው አእምሮን ማሰራት ወይም ማሰብና ማስተዋል ሳያስፈልግ በአስጠሊው ጭፍን ተከታይነት ላይ የሚሞረኮዝ ነው። ወይም በተሳሰቱ፣በተጣመሙና እርስ በርሳቸው የሚጋጩ፣ትክክለኛ ስለ መሆናቸው ማስረጃም ሆነ ማረጋገጫ በሌላቸው ዘገባዎች ላይ ይሞረኮዛሉ። በእርግጥ እንዲህ ያሉ ነገሮችን ሃይማኖቶችንና እምነቶችን በሚመለከት በማስረጃነት ማቅረብ ስሕተት ነው።

እውነት የማከፋፈል አንድ ብቻ በመሆኑ እነዚያ እምነቶች ሁሉ በአንድ ጊዜ ትክክለኞች ይሆናሉ ማለት ፈጽሞ የማይቻል ነው፤አሊያ እውነት እርስ በርሱ የሚጻረር ሊሆን ነው፤ይህ ደግሞ ጤናማ አእምሮ የማይቀበለው ነገር ነው።

{ከአላህ ሌላ ዘንድ በነበረ ኖሮ፣በርሱ ውስጥ ብዙን መለያየት ባገኙ ነበር።}[አል ኒሳእ፡82]

ታድያ እውነተኛው ሃይማኖት ምንድነው? ከነዚህ እምነቶች መካከል አንዱ ብቻ እውነተኛው እምነት ነው መመዘኛውን የማያሟሉ የተቀሩት እምነቶች ብልሹና የተሳሳቱ ናቸው ለማለት የሚያስችሉን መመዘኛዎች የትኞቹ ናቸው?!

መመዘኛዎቹ የሚከተሉት ናቸው፦

አንደኛ ፦ የሃይማኖቱ ምንጭና መገኛ መለኮታዊነት ማለትም ከአላህ (ሱ.ወ.) ዘንድ የተላለፈ መሆን ነው።

ይህም ለአገልጋዮቹ ያደርስ ዘንድ በመልኣክ አማካይነት ከአላህ መልክተኞች ወደ አንዱ የተላለፈ መሆን ማለት ነው። እውነተኛው ሃይማኖትም ይህን ዩኒቨርስ ከፈጠረው አላህ (ሱ.ወ.) የተላለፈ ሃማኖት ሲሆን፣ባስተላለፈላቸው ሃይማኖት መሠረት ፍጡራንን በትንሣኤው ቀን የሚጠይቃቸውና የሚመረምራቸው አላህ (ሱ.ወ.) ብቻ ነው። አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{እኛ ወደ ኑሕና ከርሱ በኋላ ወደ ነበሩት ነቢያት እንዳወረድን፣ወደ አንተም አወረድን፤ወደ ኢብራሂምም፣ወደ እስማዒልም፣ወደ እስሓቅም፣ወደ የዕቁብም፣ወደ ነገዶቹም፣ወደ ዒሳም፣ወደ አዩብም፣ወደ ዩኑስም፣ወደ ሃሩንና ወደ ሱለይማንም አወረድን፤ለዳውድም ዘቡርን ሰጠነው። ከዚህም በፊት በአንተ ላይ በእርግጥ የተረክናቸውን መልክተኞች፣ባንተ ላይም ያልተረክናቸውን መልክተኞች (እንደላክን፣ላክንህ)። አላህም ሙሳን ማነጋገርን አነጋገረው።}[አል ኒሳእ፡163-165]

በዚህ መሠረት ከአላህ ጋር ሳይሆን ከራሱ ጋር የተዛመደ ሃይማኖት ይዞ የሚመጣ ማንኛውም ሰው ሃይማኖቱ የግድ ውድቅ የሆነ ሃይማኖት ነው።

ሰዎች የሚፈጥሩትና እየጨመሩበትና እየቀነሱበት የሚያሻሽሉት ሃይማኖትም እንዲሁ ውድቅና ተቀባይነት የለውም። ሃይማኖትን የሚያሻስሉትና የሚለዋውጡት ለፈጠራቸው ሰዎች የሚበጀውን ከማንም በላይ ከሚያውቀው አላህ የሚያውቁ አይደሉም።

{የፈጠረ አምላክ እርሱ ዕውቀተ ረቂቁ፣ውስጥ አዋቂው ሲኾን (ምስጢርን ሁሉ) አያውቅምን።}[አል ሙልክ፡14]

አለዚያማ አሻሻዩና ለዋዋጩ ራሱን ለፈጠራቸው ሰዎች የሚበጀውን ከማንም በላይ የሚያውቅ ፈጣሪ ጌታ አድርጎ ሾሟል ማለት ነው። አላህ (ሱ.ወ.) ግን ይህን ከመፍቀድ የጠራና ላቀ ነው። አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{በሰማያትና በምድር ያሉ ሁሉ፤በውድም በግድም ለርሱ የታዘዙ፣ወደርሱም የሚመለሱ ሲኾኖኑ (ከሓዲዎች) ከአላህ ሃይማኖት ሌላን ይፈልጋሉን?}[ኣሊ ዒምራን፡83]

በተጨማሪም አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{በጌታህም እምላለሁ (አላህ በራሱ መማሉ ነው) በመካከላቸው በተከራከሩበት ፍርድ እስከሚያስፈርዱህ፣ . . ድረስ አያምኑም፤(ምእመን አይኾኑም)።}[አል ኒሳእ፡65]

ሁለተኛ፦ ሃማኖቱ አንድ አላህን ብቻ ለመገዛትና እርሱን ብቻ ለማምለክ ጥሪ የሚያደርግ፣በርሱ ማጋራትን (ሽርክን) የሚከለክል መሆን። ለተውሒድ ጥሪ ማድረግ የሁሉም ነብያትና መልክተኞች ጥሪ መሠረት ነው። ሽርክ፣ባእድ አምልኮና ጣዖታዊነት ደግሞ ከጤናማ ተፈጥሮና ከአስተዋይ አእምሮ ሀሁ ጋር የሚጣረስ ነው።

አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{ከአንተ በፊትም፣እነሆ ከኔ ሌላ አምላክ የለምና ተገዙኝ በማለት ወደርሱ የምናወርድለት ቢኾን እንጅ ከመልክተኛ አንድንም አልላክንም።}[አል አንቢያ፡25]

እያንዳንዱ ነብም ለሕዝቦቹ እንዲህ ብሏል፦

{አላህን ተገዙ፤ለናንተ ከርሱ ሌላ ምንም አምላክ የላችሁም፤እኔ በናንተ ላይ የከባድ ቀንን ቅጣት እፈራላችኋለሁ።}[አል አዕራፍ፡59]

በመሆኑም ሽርክን የሚቀበል፣ነብይንም ይሁን መልኣክን ወይም ጻድቅን (ወሊይ)፣ሰብአዊ ፍጡርንም ይሁን ግኡዝ ነገርን በአላህ አምልኮ የሚያጋራ ማንኛውም ሃይማኖት ተቀባይነት የሌለው ውድቅ ሃይማኖት ነው። አምልኮ (ዕባዳ) ተጋሪ ለሌለው ለአንድ አላህ ብቻ የተገባ ሲሆን፣ሽርክና ጣዖታዊነት ግልጽ ጥመት ነው። መሰረቱ ከአላህ ዘንድ ቢሆን እንኳ ሽርክ ብክለት የገባባት ማንኛውም ሃይማኖትም ውድቅና ተቀባይነት የሌለው ሃይማኖት ነው። አላህ (ሱ.ወ.) ለዚህ አስደናቂ ምሳሌ ሲገልጽልን እንዲህ ብሏል፦

{እላንተ ሰዎች ሆይ! አስደናቂ ምሳሌ ተገለጸላችሁ፤ለርሱም አድምጡት፤እነዚያ ከአላህ ሌላ የምትገግገዟቸው (ጣዖታት)፣ዝምብን ፈጽሞ አይፈጥሩም፤ለርሱ (ለመፍጠር)፣ቢሰበሰቡም እንኳ፣(አይችሉም)፤አንዳችንም ነገር ዝንቡ ቢነጥቃቸው ከርሱ አያስጥሉትም፤ፈላጊውም ተፈላፊውም ደከሙ (ገዥውም ተገዥውም ደካሞች ናቸው)። አላህን ተገቢ ክብሩን አላከበሩትም፤አላህ በጣም ኃያል አሸናፊ ነው።}[አል ሐጅ፡7374]

ሦስተኛ፦ ከሰው ልጅ ትክክለኛና ጤናማ ተፈጥሮ ጋር የሚጣጣም መሆን። አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{ወደ እውነት ተዘንባይ ኾነህ ፊትህን ለሃይማኖት ቀጥ አድርግ፤የአላህን ፍጥረት ያችን አላህ ሰዎችን በርስዋ ላይ የፈጠረባትን (ሃማኖት ያዙዋት)፤የአላህን ፍጥረት መለወጥ የለም፤ይህ ቀጥተኛ ሃይማኖት ነው፤ግን አብዛኛዎቹ ሰዎች አያውቁም።}[አል ሩም፡30]

ተፈጥሮ የሰዎች ፈጣሪ ሰዎችን የሕልውናቸው አካል አድርጎ የፈጠራባቸውን ሁሉ የሚያካትት ሲሆን፣ሃይማኖት ከሰው ልጅ ተፈጥሮ ጋር የማይጣጣም ሊሆን አይችልም። አለዚያ ፈጣሪ ሃይማኖቱን አልደነገገም ማለት ሲሆን ይህ ደግሞ ሊሆን የማይችልና ሽርክም ነው።

አራተኛ፦ ከትክክለኛ አእምሮ ጋር የጠጣጣመ መሆን። ይህም ትክክለኛ ሃይማኖት የአላህ ሕግ፣ትክክለኛ አእምሮም የአላህ ፍጡር በመሆናቸው የአላህ ሕግ ከአላህ ፍጡር ጋር ፈጥሞ ሊጣረስ አይችልም። አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{ለነርሱም፣በነርሱ የሚያውቁባቸው ልቦች፣ወይም በነርሱ የሚሰሙባቸው ጆሮዎች፣ይኖሩዋቸው ዘንድ፣በምድር ላይ አይኼዱምን? እነሆ ዓይኖች አይታወሩም ግን እነዚያ በደረቶች ውስጥ ያሉት ልቦች ይታወራሉ።}[አል ሐጅ፡46]

በተጨማሪም አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{በሰማያትና በምድር ውስጥ ለምእመናን ሁሉ (ለችሎታው) እርግጠኛ ምልክቶች አልሉ። እናንተንም በመፍጠር፣ከተንቀሳቃሽም (በምድር ላይ) የሚበትነውን ሁሉ (በመፍጠሩ) ለሚያረጋግጡ ሕዝቦች ታምራቶች አልሉ። በሌሊትና መዓልት መተካካትም፣ከሲሳም (ከዝናም) አላህ ከሰማይ ባወረደው፣በርሱም ምድርን ከሞተች በኋላሕያው በማድረጉ፣ነፋሶችንም (በያቅጣጫቸው) በማዘዋወሩ፣ለሚያውቁ ሕዝቦች ማስረጃዎች አልሉ። እነዚህ፣ ባንተ ላይ የምናነባቸው ሲኾኑ፣የአላህ ማስረጃዎች ናቸው፤ከአላህና ከማስረጃዎቹም ወዲያ በየትኛው ንግግር ያምናሉ?}[አል ጃሢያ፡3-6]

እውነተኛ ሃይማኖት በአፈተረት፣በቅዠት ሀሳቦችም ሆነ አንዱ ሌላውን በሚጻረር ሁኔታ በቅራኔዎች የተሞላ ሊሆን አይችልም። ይህ ከጤናማ አመዛዛኝ አእምሮ ጋር የሚጻረር ነው። አንድን ትእዛዝ አስተላልፎ በሌላ ትእዛዝ ደግሞ ተቃራኒውን አያዝም። ለአንዱ ቡድን አንድን ነገር ፈቅዶ ለሌላው ቡድን ያንኑ ነገር እርም አያደርግም፤በተመሳሳይ ጉዳዮች ላይ የተለያየ ብያኔ አይሰጥም እርስ በርሳቸው የሚጣረሱ ውሳኔዎችን አያስተላልፍም።

አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{ቁርኣንን አያስተነትኑምን? ከአላህ ሌላ ዘንድ በነበረ ኖሮ፣በርሱ ውስጥ ብዙን መለያየት ባገኙ ነበር።}[አል ኒሳእ፡82]

ይልቁንም በግልጽ ማስረጃዎች ላይ የተመሰረተ መሆኑም የግድ ነው። አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{እውነተኞች እንደኾናችሁ አስረጃችሁን አምጡ፣በላቸው።}[አል በቀራህ፡111]