የሰው ልጅ ሃይማኖት ያስፈልገዋል?

የሰው ልጅ ሃይማኖት ያስፈልገዋል?

የሰው ልጅ በምንም ዓይነት ያለ ሃይማኖት መኖር አይችልም።

የሰው ልጅ በተፈጥሮው ከሕብረተሰቡ ተነጥሎ ለብቻው መኖር የማይችል ማሕበራዊ ፍጠር እንደሆነ ሁሉ፣በተፈጥሮው ያለ ሃይማኖት ትክክለኛ የሆነ ጤናማ ሕይወት መኖር የማይችል ፍጡር ነው። ስለዚህም ሃይማኖተኝነት ለሰው ልጅ ተፈጥሯዊ የሆነ ባሕርይ ነው።

የሰው ልጅ ሲጨነቅና መከራ ሲገጥመው ወደ አላህ (ሱ.ወ.) ተመልሶ የሚማጸነው ከመሆኑ የበለጠ ማስረጃ የለም።አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{በመርከቦች ውስጥ በተሳፈሩ ጊዜም፣አላህን፣መግገዛትን ለርሱ ብቻ ያጠሩ ኾነው ያጠሩታል፤ወደ የብስ (በማውጣት) ባዳናቸው ጊዜም ወዲያውኑ እነርሱ (ጣዖትን) ጋራሉ።}[አል ዐንከቡት፡14]

አንድን ዕቃ የሚሰራ ወገን ዕቃውንና የሚያስፈልጉትን ነገሮች ከማንም በላይ እንደሚያውቅ ሁሉ፣ፈጣሪ አምላክ ስለ ፍጡራኑና አስፈላጊያቸው ስለሆኑ ነገሮች ሁሉ ከማንም በላይ ያውቃል። አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{የፈጠረ አምላክ እርሱ ዕውቀተ ረቂቁ፣ውስጥ አዋቂው ሲኾን (ምስጢርን ሁሉ) አያውቅምን።}[አልሙልክ፡14]

ፈጣሪ ርህሩህ መሓሪና ቸር በመሆኑ፣የሰዎች መንፈስ ሕያው ሆኖ ሕይወታቸውን በሥርዓት ይመሩ ዘንድ ጃይማኖትን ደንግጎላቸዋል።አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{እላንተ ያመናችሁ ሆይ! (መልክተኛው ሕያው ወደሚያደርጋችሁ እምነት በጠራችሁ ጊዜ፣ለአላህና ለመልክተኛው ታዘዙ፤)}[አል አንፋል፡24]

በመሆኑም ተፈጥሮን በመጻረር የአላህን ሕልውና እንክዳለን የሚሉ ወገኖች እንኳ በውስጣቸው ውሸታቸውንና ክህደታቸውን ያውቃሉ። አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{ነፍሶቻቸውም ያረጋገጧት ሲኾኑ ለበደልና ለኩራት በርሷ ካዱ፤የአመጸኞችም ፍጻሜ እንዴት እንደ ነበረ ተመልከት።}[አልነምል፡14]

በጭንቅና በመከራ ሰዓት አስገዳጅ ሁኔታ ሲያጋጥመው ይህን በግልጽ ያያል። አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{የአላህ ቅጣት ቢመጣባችሁ ወይም ሰዓቲቱ (ትንሣኤ) ብትመጣባችሁ፣ከአላህ ሌላን ትጠራላችሁን? እውነተኞች እንደ ኾናችሁ ንገሩኝ በላቸው። አይደለም እርሱን ብቻ ትጠራላችሁ፤ቢሻም ወደርሱ የምትጠሩበትን ነገር ያስወግዳል፤የምታጋሩትንም ነገር ትተዋላችሁ (በላቸው)።}[አል አንዓም፡41-42]

በተጨማሪም አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{ሰውንም ጉዳት ባገኘው ጊዜ፣ጌታውን ወደርሱ ተመላሽ ኾኖ ይጠራል። ከዚያም ከርሱ ዘንድ ጸጋን በሰጠው ጊዜ ያንን ከዚያ በፊት ወደርሱ ይጸልይበት የነበረውን (መከራ) ይረሳል፤ከመንገዱ ለማሳሳትም ለአላህ ባላንጣዎችን ያደርጋል፤በክሕደት ጥቂትን ተጣቀም፤አንተ በእርግጥ ከእሳት ጓዶች ነህ በለው።}[አል ዙመር፡8]

መላው የሰው ዘር አላህ በፈጠራቸው ንጹሕ ተፈጥሯቸው፣በጥቀምም ሆነ መጉዳት በእጁ የሆነውን፣ያሻውን የሚሰራና የፈለገውን የሚወስን የሆነውን አንድ አምላክ የማምለክ ባሕርይ ይዘው ተወልደዋል። አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{አላህም በጉዳት ቢነካህ ለርሱ (ለጉዳቱ) ከእርሱ በቀር ሌላ አስወጋጅ የለም፤በበጎም ነገር ቢነካህ እርሱ በነገሩ ሁሉ ላይ ቻይ ነው።}[አል አንዓም ፡14]

በተጨማሪምአላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{አላህ ለሰዎች ከችሮታ የሚከፍታት ለርሷ ምንም አጋጅ የላትም፤የሚያግደውም ከርሱ በኋላ ለርሱ ምንም ለቃቂ የለም፤እርሱም አሸናፊው፣ጥበበኛው ነው።}[ፋጢር፡2]

ሰው ሁለት ኃይሎች አሉት፤አንደኛው የዕውቀት ኃይል ሲሆን ሌላው የፍላጎት ኃይል ነው።

ሁለቱን እውን ለማድረግ በሚያደርገው ጥረት መጠንም ከፈለገው ግብ ይደርሳል። የመጀመሪያውን ማለትም የዕውቀትን ኃይል በተመለከተ፣ለአላህ ለስሞቹና ለባህርያቱ፣ለትእዛዛቱና ለእገዳዎቹ ግዴታ የሆነበትን በማወቁ ረገድ በሚኖረው ዕውቀት መጠን፣በተግባራዊ ስነምግባሩና በጸባዩ፣ወደ አላህ የቀረቡ ደጋግ አገልጋዮቹን መንገድ እንዴት እንደሚከተል፣በተጓዦቹየመወጣጫደረጃዎች ላይ እንዴት ከፍ እንደሚል፣ስለ ሰው ልጅ ነፍስያ ውስጣዊ ተፈጥሮ፣ስለ ደዌዎቿና ስለ ቆሻሻዎቿ፣እንዴት ሊረታትና ሊገራት እንደሚችል፣በጠላቶቿና እርሷን ከጌታዋ በሚያግዱት ሁሉ ላይ እንዴት ድል መቀዳጀት እንደሚቻል በሚኖረው እውቀት ደረጃ፤ወደ መጠቀ መንፈሳዊ ደረጃና ወደ ላቀ መንፈሳዊ ግብ በሚያደርሰው መልኩ ራሱን ከርካሽ ቁሳዊ ፍላጎቶችና የወረዱ ስሜታዊ ዝንባሌዎች በራቀ ሁኔታ በውብ ስነምግባርና በምስጉን ባሕርያት ከማነጽና ከመግራት ጎን ለጎን . . ለአላህ የሚኖረው ተገዥነትና ተመሪነት፣አላህ ዘንድ የሚኖረው ደረጃና ስፍራም፣የወዳኛው ሕይወት ተድላና በደስታ ብቻ ሳይሆን የዚች ዓለም ተድላና ደስታውም ጭምር በዚህ መጠን ይሆናል።

ይልቁንም ይህ የዕውቀት ኃይልና አቅም ከጽናትና ከቀጥተኝነት በተጨማሪ በውስጡ ባካተተው ቅን መመሪያ፣የፍላጎት ኃይል መጋቢና ስንቅ ነው። አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{እላንተ ያመናችሁ ሆይ! (መልክተኛው) ሕያው ወደሚያደርጋችሁ እምነት በጠራችሁ ጊዜ፣ለአላህና ለመልክተኛው ታዘዙ፤}[አል አንፋል፡24]

ይኸውና የኤቲዝም ጎራዎች የመንፈስ እርካታን ማስገኝት ቀርቶ የአካልን እርካታ ማስፈን ስለተሳናቸው ክስረታቸውን እያወጁ ነው። ያሻቸውን ያህል ብልጭልጭ የማታለያ ቃላቶቻቸውን እርስበርሳቸው ቢለዋጡና አሰማምረው ቢነዙ እውነተኛውን ደስተኝነት ለሰውልጆች ለማቅረብ ሳይችሉ መክነዋል።

የሰው ልጅ በአደጋና በመከራ ወቅት ወደማነው የሚማጸነውና የሚወተውተው?! ወደ ብርቱው ማእዘን ነው የሚጠጋው፤ኃይልና ተስፋ፣ክጀላና ትዕግስት፣በጎ መተማመንና ነገሮችን ሁሉ ለርሱ መስጠት ወዳለበት ወደ ኃያሉ አላህ ነው የሚሸሸው። አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{(እነሱም)እነዚያያመኑ፣ልቦቻቸውም አላህን በማውሳት የሚረኩ ናቸው፤ንቁ አላህን በማውሳት ልቦች ይረካሉ።}[አል ረዕድ፡28]

በግፍና በጭቆና እሳት ተለብልቦ ምሬት ሲሰማው ይህ ዩኒቨርስ ፈጣሪ ጌታ እንዳለው፣ቆይቶም ቢሆን ለጭቁን ተጎጂው ረድኤቱ እንደሚመጣ፣እያንዳንዱ ሰው እንደሥራው ዋጋውን የሚያገኝበትና በጎ የሠራም ሆነ ክፉ የሠራው ፍርዱን የሚያይበት የትንሣኤ ቀን ስለመኖሩ እርግጠኛ ይሆናል። በዚህም በአላህ (ሱ.ወ.) ላይ በሚኖረው መተማመንና እርግጠኝነት ልቡ ይረካል። አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{የአላህን ውዴታ የተከተለ ሰው፣ከአላህ በኾነ ቁጣ እንደ ተመለሰና መኖሪያው ገሀነም አንደ ኾነ ሰው ነውን? መመለሻውም ምን ይከፋ!}[ኣሊ ዒምራን፡162]

በተቃራኒው ደግሞ አላህን (ሱ.ወ.) ማወቅና በርሱ ማመንን ያጣ ሰው ሁሉንም ኃይል ያጣ፣

የመንፈስ እርካታና ውስጣዊ መረጋጋትን፣ደስተኝነትም ተነፍጎ በጭንቀት በውጥረትና በሀዘን ማእበል ውስጥ የሚኖር ሰው ነው። የተረጋጋ አእምሮም ሆነ ውስጣዊ ሰላም የሌለው ሲሆን፣ብቸኛ ግቡ ሥጋዊ መደሰቻንና ስሜታዊ ፍላጎቶችን ለማርካት ገንዘብ ማሳደድ ነው። የሚኖርለት ዓላማም ሆነ የሕይወት ግብ የሌለው፣ደስተኝነትን ፍለጋ ሲለፋና ሲባዝን የሚኖር፣የስጋዊ ፍላጎቶቹ ተገዥ ሆኖ የሚኖር በመሆኑ ከሰውነት እየወረደ ወደ አንስሳዊነት ብቻ ሳይሆን ከዚያም ወደ ከፋ ይዘቅጣል።አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{ይልቁንም አብዛኞቻቸው የሚሰሙ፣ወይም የሚያውቁ፣መኾናቸውን ታስባለህን? እነርሱ እንደ እንስሳዎች እንጂ ሌላ አይደሉም፣ከቶውንም እነሱ ይልቅ መንገድን የተሳሳቱ ናቸው።}[አል ፉርቃን፡44]

ስቃይና መከራ ስለወረረው የስነልቦና ውድመትና የውስጣዊ ጭንቀት ሰለባ ይሆናል። አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{ከግሣጼም የዞረ ሰው፣ለርሱ ጠባብ ኑሮ አልለው፤በትንሣኤም ቀን ዕውር ኾኖ እንቀሰቅሰዋለን።}[ጣሃ፡124]

ጌታው ያወቀ፣ኃያልነቱን የተገነዘበ፣ለርሱ መፈጸም የሚገባቸውን ግዴታዎችም የተረዳ፤ሸሪዓውን በመከተል ለትእዛዛቱ ታዛዥ በመሆንና ከእገዳዎቹ በመከልከል የርሱን ውዴታ ለማግኘት የጓጓ፤ጌታው በትንሹም በትልቁም፣በግልጹና በስውሩም፣በሁሉም ጊዜና ስፍራም ለርሱ ወሳኝና የዘውትር አስፈላጊው መሆኑን ያወቀ ሰው ይህን ሁሉ ከማያውቀው ሰው የተለየ ነው። አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{እላንተ ሰዎች ሆይ! እናንተ (ሁል ጊዜ) ወደ አላህ ከጃዮች ናችሁ፤አላህም እርሱ ተብቃቂው ምስጉኑ ነው።}[ፋጢር፡15]

ልቡ በጥርጣሬና በግራመጋባት ተሞልቶ እርግጠኝነትን ማጣትና ባዶ ግምቶች ወደ መከፋትና ተስፋ መቁረጥ ጨለማ የወሰዱት ሰው፣ዓለማዊ መደሰቻዎችንና ጊዜያዊ ማርኪያዎችን ቢያገኝም፣ከፍተኛ ሹመትና ማእረግ ማግኘት ቢሳካለትም እንኳ እውነተኛ ደስተኝነትንና ውስጣዊ እርካታን የማግኘት ጥረቱ ከንቱ ይሆናል። አላህን ለማግኘት ያልታደለ ምን አግኝቶ?! አላህን ያገኘ ምን አጥቶ?!