የአላህን (ሱ.ወ) አምላክነት የሚያረጋግጡ ማስረጃዎች

የአላህን (ሱ.ወ) አምላክነት የሚያረጋግጡ ማስረጃዎች

የአላህን (ሱ.ወ) አምላክነት የሚያረጋግጡ ማስረጃዎች

ጤናማ ተፈጥሮና አመዛዛኝ አእምሮ ይህ ዩኒቨርስ ጌታ እንዳለው፣ይህ ፍጥረተ ዓለም ያስገኘው ፈጣሪ እንዳለው ካረጋገጡ፣በጌትነቱ ላይም ከተስማሙ፣ለርሱም ጌትነት ብቻ ተገዥ ከሆኑ . . በአምላክነቱ ተጋሪም ሆነ ተፎካካሪ ባላንጣ የሌለው አንድ አምላክ ብቻ መሆኑን በከፍተኛ ድምጽ ያውጃሉ። ለዚህ ጉልህ አስረጅ ከሆኑ አያሌ ምልክቶች ውስጥ የሚከተሉትን እናገኛለን፦

1.ይህ ዩኒቨርስ ሁለት አምላኮች እንዴት ሆኖ ሊኖረው ይችላል?!

የሰው ልጅ አእምሮ አንድ አምላክ ብቻ መኖሩን መቀበልን ግድ ይላል። አለበለዚያ ግን - ለክርክር ያህል- ሁለት አምላኮች ቢሆኑና ተጋጭተው ልዩነት ቢፈጥሩ፣እያንዳንዱ የየራሱን ፍላጎት ማስፈጸም ቢፈልግ፣አንደኛው አንድ ነገር ሲፈልግ ሌላኛው ተቃራኒውን ቢሻ ምንድነው የሚኮነው?! አንዱ ከሌላኛው በላይ መሆኑና ሌላኛው የበታች ደካማ መሆኑ የግድ ነው። በዚህ ሁኔታ የበታቹ ደካማ አምላክ ሊሆን ይችላልን?! ስለዚህም ሊኖር የሚችለው እውነተኛ አምላክ አንድ ብቻ ይሆናል። አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ብሏል፦

{አላህ ምንም ልጅን አልያዘም (አልወለደም)፤ከርሱም ጋር አንድም አምላክ የለም፤ያን ጊዜ፣(ሌላ አምላክ በነበረ)፣አምላክ ሁሉ በፈጠረው ነገር በተለየ ነበር፤ከፊላቸውም በከፊሉ ላይ በላቀ ነበር፤አላህ ከሚመጥኑት ሁሉ ጠራ። ሩቁንና ቅርቡንም ሁሉ ዐዋቂ ነው፤(በርሱ) ከሚያጋሩትም ሁሉ ከፍ አለ።}[አል ሙእሚኑን፡91-92]

2.አቅምም ሆነ መላ የሌለውን፣የሰማያትና የምድር ባለቤት ያልሆነውን፣ምንም ያልፈጠረውን እና የማይፈጥረውን፣እንኳን ለሌላው ለራሱም ቢሆን ጥቅምም ሆነ ጉዳት፣ሞትም ሆነ ሕይወት ወይም ዳግም መቀስቀስን ማስገኘት የማይችል ደካማ አምላክ የሚያመልክ ሰው አስገራሚ ፍጡር ነው። አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ብሏል፦

{ያ ፉርቃንን (ውነትን ከውሸት ለይውን መጽሐፍ ቁርኣንን) በባሪያው ላይ፣ለዓለማት ማስፈራሪ ይኾን ዘንድ ያወረደው (አምላክ) ክብርና ጥራት ተገባው። (እርሱ) ያ የሰማያትና የምድር ንግሥና የርሱ ብቻ የኾነ፣ልጅንም ያልያዘ፣በንግሥናውም ተጋሪ የሌለው፣ነገሩንም ሁሉ የፈጠረና በትክክልም ያዘጋጀው ነው። (ከሐዲዎች) ከርሱም ሌላ ምንንም የማይፈጥሩን፣እነሱም የሚፈጠሩን፣ለነፍሶቻቸቸውም ጉዳትን ለመከላከል፣ጥቅምንም ለማምጣት የማይችሉን አማልክት ያዙ።}[አል ፉርቃን፡1-3]

ይህ ባይሆን ኖሮና አጋሪ ሙሽሪኮች እንደሚሉት ከአላህ ጋር ወደርሱ ለማቃረብና ለማማለድ የሚመለኩ አማልክት ቢኖሩ ኖሮ፣እነዚያ አማልክት እርሱን ባመለኩና ወደርሱ መቃረቢያ መንገድን በፈለጉ ነበር። አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ብሏል፦

{(ሙሐመድ ሆይ) በላቸው፦ እንደምትሉት ከርሱ ጋር አማልክት በነበሩ ኖሮ ያን ጊዜ ወደ ዐርሹ (ወደ ዙፋኑ) ባለቤት መንገድን በፈለጉ ነበር። ጥራት ይገባው፤ከሚሉትም ነገር ሁሉ ከፍ ያለን ልቅና ላቀ።}[አል እስራእ፡42-43]

እርሱ ግን ከማንምና ከምንም የተብቃቃ የሁሉም መጠጊያ፣ያልወለደና ያልተወለደ፣ምንም አምሳያ የሌለው አንድ አላህ ነው።

እነዚያ አማልክት ግን ምንንም ማድረግ የማይችሉና ምንም ሥልጣን የሌላቸው ደካሞች ናቸው። አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ብሏል፦

{እነዚያን ከአላህ ሌላ (አማልክት ብላችሁ) የምታስሰቧቸውን ጥሩ፤በሰማትም በምድርም ውስጥ የብናኝ ክብደት ያክል ምንንም አይችሉም፤ለነርሱም በሁለቱም ውስጥ ምንም ሽርክና የላቸውም፤ከነርሱም ለርሱ ምንም አጋዥ የለውም በላቸው። ምልጃም፣እርሱ ለፈቀደለት ሰው ብቻ ቢኾን እንጂ እርሱ ዘንድ ምንም አትጠቅምም፤ከልቦቻቸው ላይ ድንጋጤው በተገለጠም ጊዜ፣(ተማላጆቹ) ጌታችሁ ምን አለ? ይላሉ፤(አማላጆቹ) አውነትን አለ፤እርሱም ከፍተኛው ታላቁ ጌታ ነው፣ይላሉ።}[ሰበእ፡22-23]

መጥቀምም ሆነ መጉዳት የማይችሉትን ፍጡራን አማልክት አድርገው በአላህ የሚያጋሩትን ሙሽሪኮች፣አቅም የለሽነታቸውን በማሳመንና ፍጡራንን ማምለክ ውድቅ መሆኑን በማስረዳት፦ ጥሪያችሁ የሚጠቅም ከሆነ ከአላህ ጋር የምታጋሯቸውን አማልክቶቻችሁን ጥሯቸው፣በማንኛውም መልኩ መልስ መስጠት የማይችሉ አቅም የለሾች መሆናቸው ተረጋግጧልና ቅንጣት ያህል ሥልጣን በሰማያትም ሆነ በምድር ላይ በግላችሁም ሆነ በተጋሪነት የላችሁም፤እነዚያ የናንተ አማልክት በሰማያትም ሆነ በምድር ይብዛም ይነስ ምንም የሚጋሩት ነገር የላቸውም፤የግላቸውም ይሁን የጋራ ንግሥና የላቸውም፣በላቸው። ይህም ሆኖ ግን ለእውነተኛው የንግሥና ባለቤት ረዳቶችና ተጠሪዎች ሊሆኑ ስለሚችሉ እነሱን ማምለክ፣ንጉሡ ስለሚፈልጋቸው ለሚያመልኩባቸው ሰዎች በአማላጅነት ጉዳይ ያስፈጽማሉ ሊባል ይችል ይሆናል፤አላህ (ሱ.ወ) ግን ይህንንም ሲያስተባብል እንዲህ ብለዋል፦

ለርሱ

ለኃያሉ አንድ አላህ

ከነርሱም

ከነዚያ አማልክት

ምንም አጋዥ

ግዛቱን ለማስተዳደርና ለማቀናበር አጋዥም ሆነ ምንም ረዳት የለውም

3-በተቀናጀና በተቀነባበረ ብርቱና ተአምራዊ ወጥ ሥርዓት የሚመራውን ይህን ዩኒቨርስ መመልከቱ ብቻ፣እጅግ ዐዋቂና እጅግ ቻይ የሆነ የአንድ አምላክ ቅንብር ስለመሆኑ ከሁሉም የላቀ ማስረጃ ነው። አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ብሏል፦

{አምላካችሁም አንድ አምላክ ብቻ ነው፤ከርሱ በቀር ሌላ አምላክ የለም፤(እርሱ) እጅግ በጣም ርኅሩኅ አዛኝ ነው። ሰማትንና ምድርን በመፍጠር፣ሌሊትና ቀንንም በማተካካት በዚያችም ሰዎችን በሚጠቅም ነገር (ተጭና) በባህር ላይ በምትንሻለለው ታንኳ፣አላህም ከሰማይ ባወረደው ውሃና በርሱም ምድርን ከሞተች በኋላ ሕያው በማድረጉ፣በርሷም ውስጥ ከተንቀሳቃሽ ሁሉ በመበተኑ፣ነፋሶችንም (በየአቅጣጫው) በማገለባበጥ በሰማይና በምድር መካከል በሚንነዳውም ደመና ለሚያውቁ ሕዝቦች እርግጠኛ ምልክቶች አልሉ።}[አል በቀራህ፡163-164]

እናም ይህ ወጥ ቅንብርና አንዳች መዛነፍ ሳይኖርበት፣ለሰከንድ ሳይቆም - ቢቆም የዓለም ጥፋት ማለት ነውና - ለዘመናት የቀጠለው ሥርዓተ ዩኒቨርስ፣ይህን ማድረግ የሚችለው አላህ ብቻ እንደመሆኑ፣ይህን ድንቅ ቅንብር የፈጠረና ያስገኘ አምላክ አምሳያና ተጋሪ የሌለው አንድ ብቸኛ አምላክ አይደለምን?! አስተውሎ ማየት ለሚችል ሁሉ፣ይህ ግልጽና ቁልጭ ባለ ሁኔታ ሁለት አምላኮች ፈጽሞ ሊኖሩ እንደማይችሉ አያመለክትምን?! አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ብሏል፦

{በሁለቱ (በሰማትና በምድር) ውስጥ ከአላህ ሌላ አማልክት በነበሩ ኖሮ በተበላሹ ነበር፤የዐርሹ ጌታ አላህም ከሚሉት ሁሉ ጠራ።}[አል አንቢያ፡22]

በሰማያትና በምድር ከአላህ በስተቀር ሌሎች አማልክት ቢኖሩ ኖሮ ሁለቱም ከአቀፎአቸው ፍጥረታት ጋር በተበላሹና በጠፉ ነበር። ፍጥረተ ዓለም እንደሚስተዋለው ሁሉ በተሟላ ሁኔታ ተበጅቶ የተቀነባበረ ወጥ ሥርዓት በመሆኑ እንከንም ሆነ ጉድለት የለበትም። እርስ በርሱ መቃረንንም ሆነ መፋለስን አያስተናግድም። ይህም አቀነባባሪው አንድ፣ጌታውም አንድ፣አምላኩም አንድ መሆኑን ያመለክታል። ሁለት አቀነባባሪዎች፣ሁለት አስተዳዳሪዎች፣ሁለትና ከዚያም በሳይ ጌቶች ቢኖሩት ኖሮ ሥርዓቱ በተዛባና በተፋለሰ፣መሠረቱም በተናጋ ነበር። አንዱ አንድ ነገር ማድረግ ሲፈልግ ሌላው ተቃራኒውን ሲያደርግ እርስ በርስ ስለሚጋጩና ተጻራሪ ቅራኔ ውስጥ ስለሚገቡ የሁለቱን ፍላጎት ማጣጣምና ማስታረቅ ፍጹም አዳጋች ይሆናል። ያንደኛው ፍላጎት ብቻ ተፈጸሚ መሆን የሌላኛውን ደካማነትና አቅም የሌሽነት ሲያመለክት በሁሉም ነገር ላይ አንድ ፍላጎት ሊኖራቸው አይችልም። በመሆኑም ያለ ምንም ተቃውሞና ያለ አንዳች እምቢታ ፍላጎቱን ሁሉ የማስፈጸም ፍጹማዊ ኃይልና ችሎታ ያለው ምንም የማይሳነው ኃያሉ አምላክ አላህ ብቻ ይሆናል።

4- ከኣደም  አንስቶ ኑሕን፣ኢብራሂምን፣ሙሳን፣ዒሳንና ሙሐመድን  አጣቃሎ ሁሉም ነብያትና መልእክተኖች ከኀጢያት መጠበቅን፣አስተዋይና አመዛዛኝ አእምሮን፣እውነተኛነትን፣ታማኝ አድራሽነትን፣ቅንነትንና ቀጥተኛነትን ከአላህ (ሱ.ወ) የተቸሩ ሲኾኑ፣በአላህ አንድነት በተውሒድ እና ከአላህ በስተቀር ሊገዙት የሚገባ ሌላ እውነተኛ አምላክ ባለመኖሮ ላይ ሙሉ በሙሉ ተስማምተዋል። አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ብሏል፦

{ከአንተ በፊትም፣እነሆ ከኔ ሌላ አምላክ የለምና ተገዙኝ በማለት ወደርሱ የምናወርድለት ቢኾን እንጅ ከመልክተኛ አንድንም አልላክንም።}[አል አንቢያ፡25]

ኑሕን u አስመልክቶ አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ብሏል፦

{ኑሕን ወደ ወገኖቹ በእርግጥ ላክነው፤አላቸውም፦ ወገኖቼ ሆይ! አላህን ተገዙ፤ለናንተ ከርሱ ሌላ ምንም አምላክ የላችሁም፤እኔ በናንተ ላይ የከባድ ቀን ቅጣት እፈራላችኋለሁ።}[አል አዕራፍ፡59]

ስለ ነብዩ ዒሳም u አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ብሏል፦

{አልመሲሕም አለ፦ የእስራኤል ልጆች ሆይ! ጌታዬንና ጌታችሁን አላህን ተገዙ፤እነሆ! በአላህ የሚያጋራ ሰው፣አላህ በርሱ ላይ ገነትን እርም አደረገ፤መኖሪያውም እሳት ናት፤ለበዳዮችም ምንም ረዳቶች የሏቸውም።}[አል ማእዳህ፡72]

ነብዩ ሙሐመድን ለሕዝባቸው እንዲህ እንዲሉ አዟል፦

{ያ ወደኔ የሚወረደው፣አምላካችሁ አንድ አምላክ ብቻ ነው፣ማለት ነው፤ታዲያ እናንተ ፍጹም ታዛዦች ናችሁን? በላቸው።}[አል አንቢያ፡108]

የአመዛዛኝ አእምሮ ባለቤት የሆኑ ሰዎችም በዛሬው ዓለምና በወዲያኛው ዓለም ሕይወት መታደልን ያግኙ ዘንድ፣የነብዮቻቸውን ዱካ በመከተል የአላህን (ሱ.ወ) አንድነት ማረጋገጥ፣አላህ አንድዬ ጌታና አምላክ መሆኑን አምነው መቀበል ይገባቸዋል። አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ብሏል፦

{ከወንድ ወይም ከሴት፣እርሱ አማኝ ኾኖ በጎን የሠራ፣መልካም ኑሮን በእርግጥ እናኖረዋለን፤ይሠሩትም ከነበሩት ነገር በመልካሙ ምንዳቸውን እንመነዳቸዋለን።}[አል ነሕል፡97]

መልካም ሥራ ከእምነት ጋር ውጤቱ በዚህች ምድር ላይ ጥሩ ሕይወት ነው። ጥሩ ሕይወት ግን የግድ በገንዘብና በሀብት የተደላደለ ሊሆንም ላይሆንም ይችላል። መልካም ሕይወት ሆኖ ሀብትና ቁሳዊ ጸጋ የሌለበት ሊሆን ይችላል። በሰው ልጅ ሕይወት ውስጥ ከገንዘብ ውጭ ሕይወትን መልካምና በጎ የሚያደርጉ ብዙ ነገሮች አሉ። ከነዚህ መካከል ራስን ከአላህ (ሱ.ወ) ጋር ማስተሳሰር፣በርሱ ላይ መተማመን፣በርሱ ጥበቃና ረድኤት መጽናናትና መረጋጋት አንዱ ነው። ሌላው ጤንነት፣በተሰጠው ጸጋ መርካት፣በረከት፣የሕሊና እርካታ፣ቤተሰባዊ ደስታና ፍቅር፣በሰሩት በጎ ተግባር መደሰትና በሕሊና እና በአነዋነዋር ላይ የሚያሳድረው በጎ ተጽእኖ ሲሆን ገንዘብ ከነዚህ አንዱ አላባ ብቻ ነው። አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ብሏል፦

{ገንዘብና ወንዶች ልጆች የቅርቢቱ ሕይወት ጌጦች ናቸው፤መልካሞቹም ቀሪዎች (ሥራዎች)፣እጌታህ ዘንድ በምንዳ በላጭ ናቸው፤በተስፋም በላጭ ናቸው።}[አል ከህፍ፡46]

ልብ አላህ (ሱ.ወ) ዘንድ እጅግ ታላቅ፣ብጹእ እና ቋሚ ከሆነ ነገር ጋር ሲተሳሰር፣የሕይወት ጥሩነት ሌላ ትርጉም፣ደስተኝነትም ሌላ ትርጉም ይኖራቸዋል።

የሰው ልጅ እምቢኝ ብሎ ካፈነገጠ ግን፣ቀጣይነት ባለው ሁኔታ የሚዳክርበትን የአለመታደል እና የመረገምን ሁኔታ ለራሱ ወዶ ተቀብሏል ማለት ነው። በቁጭት ልብን በሚያደማ ሀሳብ፣በጭንቀትና በሀዘን ባህር ሰምጦ ብኩን ለመሆን ቆርጧል ማለት ነው። አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ብሏል፦

{አላህም ሊመራው የሚሻውን ሰው ደረቱን (ልቡን) ለእስላም ይከፍትለታል፤ሊያጠመውም የሚሻውን ሰው ደረቱን ጠባብ ቸጋራ፣ወደ ሰማይ ለመውጣት እንደሚታገል ያደርገዋል።}[አል አንዓም፡125]

አላህ ሸሪክ የሌለው አንድ አምላክ መሆኑን አረጋግጦ የተቀበለ ሰው፣የሕሊና እረፍት፣ውስጣዊ እፎይታና መረጋጋትን ያገኛል። አላህ ያጠመመው ሰው ግን - አላህ ይጠብቀንና - ልቡ የጠበበና የጨነቀው፣በሀዘንና በቁጭት የተወረረ፣ውስጣዊ ሰላምና መረጋጋት የራቀው ይሆናል። ይህም በተውሒድ ያመነና በአላህ አሻርኮ የጠመመ ሰው ምሳሌ ነው። አላህ (ሱ.ወ) ሌላ ምሳሌ ሲሰጥ እንዲህ ብሏል፦

{አላህ በርሱ ተጨቃጫቂዎች የኾኑ ተጋሪዎች ያሉትን ባሪያና፣ለአንድ ሰው ብቻ ንጹሕ የኾነን ባሪያ (ለሚያጋራና ባንድነቱ ለሚያምን ሰው) ምሳሌ አደረገ፤በምሳሌ ይተካከላሉን?፤ምስጋና ለአላህ ይገባው። በውነቱ አብዛኞቻቸው አያውቁም።}[አል ዙመር፡29]

የሙሽሪክ ሰው ምሳሌ፣አንዱ ሂድ ሌላው ተቀመጥ ሲለው ሦስተኛው ቁም የሚሉት ዓይነት ክፉ ዐመል የተጠናወታቸው ተጨቃጫቂ ጌቶች ያሉት ሰው ምሳሌ ሲሆን፣በዚህም የአካልም ሆነ የአእምሮ እረፍት አጥቶ እንደተረበሸ ይኖራል። በአላህ አንድነት የሚያምን ሰው ምሳሌ ደግሞ ለአንድ ጌታ ብቻ ታማኝ ተገዥና ታዛዥ የሆነ ሰው ምሳሌ ነው። ሁለቱ እኩል ሆናሉን?! አላህ (ሱ.ወ) አንድ ጌታ አንድ አምላክ ነው፤ከርሱ በስተቀር ሌላ እውነተኛ አምላክም ሆነ ሌላ እውነተኛ ጌታ የለም። ሁሉም ምስጋና እና የላቀ ውዳሴ ለርሱ ይሁን። እርሱን የማያውቁት ግን በከፍተኛ ውስጣዊ ግጭትና ቀውስ፣በሀሳብና በጭንቀት፣በግራ መጋባት፣በመደናበርና ራስን በማጥፋት አስከፊ ሁኔታ ውስጥ ይኖራሉ።