የነቢይነትና የመልክተኝነት እውነታ

የነቢይነትና የመልክተኝነት እውነታ

የአላህ (ሱ.ወ.) ጥበብ ሆኖ እያንዳንዱ መልክተኛ ከሚላክባቸው ወገን እንዲሆን ተደርጓል። አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{ከአንተም በፊት ወደነሱ ወሕይን (ራእይን) የምናወርድላቸውን፣ሰዎችን እንጂ ሌላን አልላክንም፤}[አል ነሕል፡43]

መልእክቱን እንዲያውቁትና እንዲረዱትም የሚላከው መልክተኛ የሚላክበት ሕዝብ ቋንቋ ተናጋሪ እንዲሆንም ተደርጓል። አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{ከመልክተኛ ማንኛውንም፣ለነርሱ ያብራራላቸው ዘንድ በወገኖቹ ቋንቋ እንጂ በሌላ አልላክንም፤አላህም የሚሻውን ያጠማል፤የሚሻውንም ያቀናል፤እርሱም አሸናፊው፣ጥበበኛው ነው።}[ኢብራሂም፡4]

ነቢዮችና መልክተኞች የምሉእ አእምሮና የጤነኛ ተፈጥሮ ባለቤቶች ሲሆኑ በእውነተኛነትና በታማኝነት የሚገለጹ፣ሰብአዊ ፍጡራንን ከሚጠናወቱ እንከኖችና ጉድለቶች ሁሉም የተጠበቁ ናቸው። እይታን ከሚስብና አመዛዛኝ ግምት ያላቸውን ሰዎች ሊያርቅ ከሚችል አካላዊ እንከንም የተጠበቁ ናቸው። ከሰዎች ሁሉ የላቀና የተሟላ የመልካም ስነምግባር ባለቤቶችም ናቸው። በሰብእናቸውና በባህርያቸው አላህ (ሱ.ወ.) ያጠራቸው ሲሆን፣ከሰው ሁሉ ቸሮችና ለጋሾች አድርጓቸዋል። በትእግስት፣በዕውቀት፣በገርነት፣በደግነት፣በጀግንነትና በፍትሐዊነት ባህርያት የተካኑ አድርጓቸዋል። በነዚህ ውብ ባሕርያት ከሕዝቦቻቸው ውስጥ አቻ የሌላቸው ሲሆኑ ተለይተው የሚታወቁባቸው መለያቸው ናቸው። መልክተኞች መልእክቱን ለመሸከምና አደራውን ለማድረስ አላህ (ሱ.ወ.) ከፍጥረታቱ ውስጥ ያላቃቸውና የመረጣቸው የርሱ ምርጦች ናቸው። አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{አላህ መልክቱን የሚያደርግበትን ስፍራ ዐዋቂ ነው፤}[አል አንዓም፡124]

በተጨማሪም አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{አላህ ኣደምን፣ኑሕንም፣የኢብራሂምንም ቤተሰብ፣የዒምራንንም ቤተሰብ፣በዓለማት ላይ መረጠ።}[ኣሊ ዒምራን፡33]

ስለ ነቢዩ ዒሳ [የአላህ ሰላም በርሳቸው ላይ ይሁን] አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{መላእክት ያሉትን (አስታውስ)፦ መርየም ሆይ! አላህ ከርሱ በኾነው ቃል፣ስሙ አልመሲሕ ዒሳ የመርየም ልጅ፣በዚህ ዓለምና በመጨረሻውም ዓለም የተከበረ፣ከባለሟሎችም በኾነ (ልጅ) ያበስርሻል፤በሕጻንነቱና በከፈኒሳነቱ (የበሰለ ሰው ዕድሜው ከ30-40 የኾነ) ሰዎቹን ያነጋግራል፤ከመልካሞቹም ነው (አላት)።}[ኣሊ ዒምራን፡45-46]

ሙሐመድ [የአላህ ሰላምና እዝነቱ በርሳቸው ላይ ይሁን] በነቢይነት ከመላካቸው በፊት በማሕበረሰባቸው ውስጥ {እውነተኛው፣ታማኙ} በመባል ይጠሩ የነበረ ሲሆን፣አላህም ታላቅ ስነምግባራቸውን ሲገልጽ እንዲህ ብሏል፦

{አንተም በታላቅ ጠባይ ላይ ነህ።}[አልቀለም፡4]

እነዚህን መልክተኞችና ነቢያት አላህ (ሱ.ወ.) በታላቅ ባሕርያትና በምጡቅ ስነምግባራት የገለጻቸውም ቢሆንም፣ሰብአዊ ፍጡራን በመሆናቸው አንደማናቸውም ሰው ይርባቸዋል፣ይታመማሉ፣ይተኛሉ፣ይበላሉ፣ይጠጣሉ፣ያገባሉ፣ይሞታሉ . . አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{ከአንተ በፊትም መልክተኞችን በእርግጥ ልከናል፤ለነርሱም ሚስቶችንና ልጆችን አድርገናል፤}[አልረዕድ፡38]

በተጨማሪም አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{አንተ ሟች ነህ፤እነርሱም ሟቾች ናቸው።}[አል ዙመር፡30]

ለነቢዩና ለመልክተኛው ለሙሐመድ [የአላህ ሰላምና እዝነቱ በርሳቸው ላይ ይሁን] አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{ . . አላህ ገላጩ የኾነን ነገር በነፍስህ ውስጥ የምትደብቅና . . }[አል አሕዛብ፡37]

በመሆኑም ነቢያት ጭቆና ሊደርስባቸው፣ሊገደሉ ወይም ከአገራቸው ሊሰደዱ ይችላሉ። አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{እነዚያም የካዱት ሊያስሩህ፣ወይም ሊገድሉህ፣ወይም (ከመካ) ሊያስወጡህ ባንተ ላይ በመከሩብህ ጊዜ፣(አስታውስ)፤ይመክራሉም፣አላህም ተንኮላቸውን ይመልስባቸዋል፤አላህም ከመካሪዎቹ ሁሉ በላይ ነው።}[አል አንፋል፡30]

ይሁን እንጅ መልካሙ ፍጻሜ፣ድልና መመቻቸት በዛሬውም ሆነ በመጪው ሕይወት የነርሱ ይሆናል።