የስልጣኔ መንገድ ፦

የስልጣኔ መንገድ ፦

የትኛውም ሕዝብ ወይም ማህበረሰብ፣ኋላ ቀርም ይሁን ያደገ፣የራሱ የሆነ መለዮ የሚያሰጠው የሆነ ባህል የግድ ይኖረዋል። ባህል የአነዋነዋር መንገድ፣ስለ ሕይወትና ስለ ፍጥረተ ዓለም የሚያዝ አቋም፣የሕይወት ገጽታዎችንና ነጠላ ጉዳዮችንም በጥቅሉ የሚገዛ ስነምግባራዊና ማህበራዊ እሴት ነው። በእንቅስቃሴና በተግባር መልክ የሚገለጽ ሲሆን ለማህበረሰቡ ማንነቱን የሚያላብስ፣አንድነቱንና ትስስሩንም ጠብቆ የሚያቆይ ነው። ስልጣኔ ግን በማህበረሰቡ ባህላዊ ሕላዌ ላይ ተጨማሪ ገላጭ የሆነ፣የዕድገትን ትርጓሜና የዓይነትና የብዛት ብልጫን የሚያመለክት፣ተጨባጭ የሆነ ስኬትን የሚያሳይ፣በታሪካዊ ስነምህዳር ላይ ግልጽ አሻራ ያለው፣ሁነቶቹን በማስገኘትና በመምራት ረገድ ከጊዜና ከቦታ አንጻር የአንጸባራቂ ለውጥና የሽግግር ወሳኝ ነጥብ እስከ መመስረት የሚደርስ ንቁ ተሳትፎ አለው። እያንዳንዱ ስልጣኔም በዚህ መልኩ የተፈጥሮ፣የስነምህዳር፣የፖለቲካ፣የሃይማኖት፣የባህል፣የትምህርትና የስነምግባር ቅንጅትና ስብጥር ነው። እነዚህ አለባዎች በጥምረት ተቀናጅተውና ተዋሕደው የዚህን ወይም የዚያን ሕዝብ ስልጣኔ ከልዩ መለያዎቹና መገለጫዎቹ ጋር ይመሰርታሉ።

እስላም የመጀመሪያዎቹን የምእመናን ስብስብ፣ጠባብ ብሔርተኝነትና ኋላ ቀርነት ከተንሰራፋበት የዘላንነት ሕይወት በማውጣት፣ለስልጣኔና ለትሩፋት መንፈስ ስርጸት ወደሚያበቃ የመጠቀ ስነምግባርና የላቀ መርሆ ከፍ አድርጓል። በጥቂት አስርት ዓመታት ውስጥም ሰው በሚኖርበት አብዛኛው የዓለም ክፍል በድል አድራጊነት ለመሰራጨት ችለዋል። ሙሐመድ  ይዘው የመጡት ሃይማኖት በነበረው ገርነት፣ፍትሐዊነትና እኩልነት ምክንያት እስላማዊው ስልጣኔ በወቅቱ በብዙ ሕዝቦች ዘንድ ተቀባይነት ለማግኘት ችሏል። የእስላም ስልጣኔ ብርሃን የፈነጠቀው፣ሰዎች በባርነትና በጭቆና ላይ የተመሰረተውን የቀድሞውን ስርዓት በተሰላቹበትና በጠሉበት፣በጨቋኝ አምባገነን አጼዎች፣በአውቶክራቶች፣በቀሳውስትና ካህናት ሥርዓት ስር የግፍና የሰቆቃ ሕይወት ካንገሸገሻቸው በኋላ ሰብአዊ ክብራቸውን የሚመልስላቸውንና እንደ ሰው የሚያከብራቸውን አዲስ ሥርዓት በናፈቁበት ወቅት ላይ ነበር። ለዚህም እስላም ወርቃማ ዕድል ይዞላቸው መጣ፤የብዙዎቹን ሁኔታ በአስደናቂ ፍጥነት ሲለውጥ ሲመለከቱም የናፍቁትን ሰብአዊ ክብርና ክቡር ሕይወት ለማየት በቁ። ከግፍ ከማይምነትና ከኋላ ቀርነትም አላቀቃቸው።

እስላማዊው ስልጣኔ ለሰው ልጅ ያለው አመለካከት በሰብአዊ ክብር ላይ የተመሰረተ በመሆኑ፣አንድም ቀን ሰብአዊ ፍጡርን ከመሰሉ ሌላ ሰብአዊ ፍጡር በዘሩ፣በቆዳ ቀለሙ፣ወይም በሚናገረው ቋንቋ ምክንያት አበላልጦ አያውቅም። በጥላው ስር ሁሉም ተመሳሳይ አያያዝና እኩል መብቶችን ተጎናጽፈዋል። እስላማዊው ስልጣኔ፣በዘርና በደም ትስስር ላይ የቆመውን የጎሳ ሥርዓት፣ዐቂዳና እሳቤን በሚጋራና ማሕበራዊ ትስስሩ በወንድማማችነትና በእኩልነት ላይ በተመሰረተ አንድ የጋራ ማሕበረሰብ ከለወጠ በኋላ፣ለሰው ልጆች ዕድገትና እርምጃ ወሳኝ የሆነ ታላቅ ድርሻ አበርክቷል።

በእስላም አመለካከት የመጀመሪያው ግብ ሰላምን መረጋጋትንና ደህንነትን ለሰው ልጆች ማረጋገጥ፣ዓይነተኛ የሆነ መልካም ሕብረተሰብ መገንባትና የሰው ልጆችን በመልካሙ ሁሉ ማስደሰት፣ክፉና እኩይ የሆነው ሁሉ መዋጋት ነው። ይኸውም በተለያዩ ገጽታዎቹ የስልጣኔ ዕድገት ማምጣት ብቻ በራሱ ተፈላጊው ግብ ባለመሆኑና የትክክለኛ ስልጣኔ ዓላማ መንፈሳዊ ደስታንና ሕሊናዊ እርካታን፣ከሰላምና ከልማት ጎን ለጎን ለሕብረተሰብና ለአገር እውን ማድረግ በመሆኑ ነው። ይህ እውን የሚሆነው በጎና ጠቃሚ የሆነውን ሁሉ በማስገኘትና ክፉና ጎጂ ከሆነው ሁሉ በማራቅ ነው።

በተጻራሪው ዘመናዊው ስልጣኔ የሰውን ልጅ እየጨመረ ለሚሄድ ጭንቀትና አለመረጋጋት የዳረገው ሲሆን፣በተንሰራፋው ቁሳዊ ጥመት ውስጥ ለመጥለቅ፣ከመልካም ስነምግባር፣ከሃይማኖትና ከሰብአዊ እሴቶችም ለመራቅ፣ኃይለኛው ደካማውን ወደሚደፍቅበት መንፈስ አልባ ግዑዝ መሳሪያነት ለመቀየር አደጋ የሰው ልጆችን አጋልጧል።