የሰው ልጅ መፈጠር ዓላማውና ምስጢሩ

የሰው ልጅ መፈጠር ዓላማውና ምስጢሩ

ዩኒቨርስ ውስጥ ያለው ሁሉ ለርሱ የተገራለትንና ከተቀሩት ፍጥረታት ሁሉ ክቡር የሆነው ይህን የሰው ልጅ፣አላህ (ሱ.ወ.) የፈጠረው ለታላቅ ጥበብና ለክቡር ዓላማ ነው፤እርሱ ከከንቱና ውድቅ ነገር ሁሉ የጠራ ጌታ ነውና። አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ብሏል፦

{ሰማያትንና ምድርን በመፍጠር፣ሌሊትና ቀንም በመተካካት፣ለባለ አእምሮዎች በእርግጥ ምልክቶች አሉ። (እነርሱም) እነዚያ ቆመው፣ ተቀምጠውም፣በጎኖቻቸው ተጋድመውም፣አላህን የሚያወሱ፣በሰማያትና በምድር አፈጣጠርም የሚያስተነትኑ ፦ ጌታችን ሆይ! ይኸን በከንቱ አልፈጠርከውም፤ጥራት ይገባህ፤ከእሳትም ቅጣት ጠብቀን፣የሚሉ ናቸው።}[ኣል ዒምራን፡190-191]

አላህ (ሱ.ወ) የከሓዲዎችን ክፉ ጥርጣሬ አስመልክቶ እንዲህ ብሏል፦

{ሰማይንና ምድርን፣በመካከላቸውም ያለውን ሁሉ ለከንቱ አልፈጠርንም፤ይህ የነዚያ የካዱት ሰዎች ጥርጣሬ ነው፤ለነዚያም ለካዱት ሰዎች ከእሳት ወዮላቸው!}[ሷድ፡27]

አላህ (ሱ.ወ) ሰውን እንደ ተቀሩት እንስሳት ሁሉ ለምግብና ለወሲብ ብቻ አልፈጠረውም። ክቡር ፍጡር አድርጎት ከፈጠራቸው ከብዙዎቹ ፍጡራን ያላቀው ቢሆንም ግን ብዙ ሰዎች ክህደትን መርጠዋል፤የተፈጠሩበትን ዓላማና ጥበቡን ቸል ብለው ወይም አስተባብለው ዋነኛ ተልእኮአቸውን መብላት፣መጠጣትና መደሰት ብቻ በማድረጋቸው ሕይወታቸውን ወደ እንስሳት ሕይወት ተርታ እንዲዘቅጥ ብቻ ሳይሆን ከዚያም የከፋ እንዲሆን አድርገዋል። አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ብሏል፦

{አላህ እነዚያን ያመኑትንና መልካሞችን የሠሩትን፣ከሥሮቻቸው ወንዞች የሚፈሱባቸውን ገነቶች ያገባቸዋል፤እነዚያም የካዱት፣(በቅርቢቱ ዓለም) ይጣቀማሉ፤እንስሳዎች እንደሚበሉ ይበላሉ፤እሳትም ለነርሱ መኖሪያቸው ናት።}[ሙሐመድ፡12]

በተጨማሪም አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ብሏል፦

{ተዋቸው፣ይብሉ፤ይጠቀሙም፤ተስፋም ያዘናጋቸው፤በእርግጥም (መጥፎ ፍጻሜያቸውን) ያውቃሉ።}[አል ሒጅር፡3]

አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ብሏል፦

{ከጋኔንም ከሰዎችም ብዙዎችን ለገሀነም በእርግጥ ፈጠርን፤ለነርሱ በርሳቸው የማያውቁባቸው ልቦች አሏቸው፤ለነሱም በሳቸው የማያዩባቸው ዓይኖች አሉዋቸው፤ለነሱም በሳቸው የማይሰሙባቸው ጆሮዎች አሉዋቸው፤እነዚያ እንደ እንስሳዎች ናቸው፤ይልቁንም እነርሱ በጣም የተሳሳቱ ናቸው፤እነዚያ ዘንጊዎቹ እነርሱ ናቸው።}[አል አዕራፍ፡179]

ሰዎች ሁሉ እያንዳንዱ የአካላቸው ክፍል ራሱን ለቻለ ጥበብና ምሥጢር እንደተፈጠረ በቁርጠኝነት ያረጋግጣሉ። ዓይን የተፈጠረው ለማየት፣ጆሮ ለመስማት ወዘተ. መሆኑን ያውቃሉ። እናም አካላቱ የተፈጠሩት ለጥበባዊ ዓላማ ሆነው እርሱ ራሱ ሰው ግን ለከንቱ የተፈጠረ እንዴት ሊሆን ይችላል?! ወይም ፈጥሮ ያስገኘው ጌታ የፈጠርኩህ ለታላቅ ዓለማና ጥበብ ነው ሲለው እምቢ ማለቱ እንዴት ሊታሰብ ይችላል?!

ታድያ አላህ (ሱ.ወ.) የፈጠረን ለምን ዓለማና ለምንስ ጥበብ ይሆን? ክቡር ፍጠራን ያደረገንና ነገሮችን ሁሉ ለኛ የተገሩ ያደረገውስ ለምን ይሆን? አላህ (ሱ.ወ) ራሱ መልሱን ነግሮናል። እንዲህ በማለት፦

{ጋኔንና ሰውንም፣ሊገዝዙኝ እንጅ ለሌላ አልፈጠርኳቸውም።}[አል ዛሪያት፡56]

በተጨማሪም አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ብሏል፦

{ያ ንግሥና በእጁ የኾነው አምላክ ችሮታው በዛ፤እርሱም በነገሩ ሁሉ ላይ ቻይ ነው። ያ የትኛችሁ ሥራው ይበልጥ ያማረ መኾኑን ሊሞክራችሁ፣ሞትንና ሕይወትን የፈጠረ ነው፤እርሱም አሸናፊው መሓሪው ነው።}[አል ሙልክ፡1-2]

አርቀው በሚያስወተውሉ ሰዎች ዘንድ እንደሚታወቀው ሁሉ አንድን ነገር የሠራው ከሌላው ይበልጥ የሠራበትን ዓለማ ያውቃል።አላህም (ሱ.ወ.) ሰውን የፈጠረበትን ጥበብና ምስጢሩን ከማንም በላይ ያውቃል። እዝህ ላይ መግገዛት ወይም ማምለክ የሚለው በመጸለይና በመጾም ብቻ ሳይሆን ዩኒቨርሱን በመላ ማልማትንና ለሰው ልጅ ጥቅም መግራትን የሚያካትት ስፋትና ጥልቀት ያለው ትርጓሜ አለው። አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ብሏል፦

{እርሱ ከምድር ፈጠራችሁ፤በውስጧ እንድታለሟትም አደረጋችሁ፤ምሕረቱንም ለምኑት፤ከዚያም ወደርሱ ተመለሱ፤ጌታዬ ቅርብ (ለለመነው) ተቀባይ ነውና አላቸው። }[ሁድ፡61]

አምልኮት ወይም ዕባዳ መላውን የሰው ልጅ ሕይወት የሚያካልል ነው። አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ብሏል፦

{ስግደቴ መገዛቴም፣ሕይወቴም፣ሞቴም፣ለዓለማት ጌታ ለአላህ ነው በል። ለርሱ ተጋሪ የለውም፤በዚህም (በማጥራት) ታዘዝኩ፤እኔም የሙስሊሞች መጀመሪያ ነኝ (በል)።}[አል አንዓም፡162-163]

ሰው ሆይ! ከዚህ በኋላስ . .

ሰው ሆይ! ዩኒቨርሱ በመላ ለአንተ አገልግሎት የተገራልህ ከሆነ፣ተአምራቱና ምልክቶቹ ግልጽ ሆነው ከአላህ በስተቀር ሌላ አምላክ አለመኖሩንና አላህ ተጋሪ የሌለው አንድዬ አምላክ መሆኑን ለመመስከር ከፊትህ ከቆሙ፣ከሞትክ በኋላ አንተን ዳግም መቀስቀስና ሕያው ማድረግ ለአላህ ሰማያትንና ምድርን ከመፍጠር የቀለለ መሆኑን ካወቅህ፣አላህ (ሱ.ወ.) በድንቅ አቋምና በአማረ ቅርጽ የፈጠረህ፣ክቡር ፍጡር ያደረገህ፣ዩኒቨርስን ለአንተ የገራልህ መሆኑንም ከተገነዘብክ ዘንዳ በቸሩ ጌታህ ምን አታለለህ?! አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ብሏል፦

{አንተ ሰው ሆይ፣በቸሩ ጌታህ ምን አታለለህ? በዚያ በፈጠረህ፣አካለ ሙሉም ባደረገህ፣ባስተካከለህም። በማንኛውም በሻው ቅርጽ በገጣጠመህ (ጌታህ ምን አታለለህ)።}[አል እንፍጣር፡8]

በመጨረሻም አንተ ከጌታህ ጋር ትገናኛለህና። አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ብሏል፦

{አንተ ሰው ሆይ! አንተ ጌታህን (በሞት) እስከምትገናኝ ድረስ ልፋትን ለፊ ነህ፤ተገናኚውም ነህ። መጽሐፉን በቀኙ የተሰጠ ሰውማ፣በእርግጥ ቀላልን ምርመራ ይመረመራል፤ወደ ቤተሰቦቹም ተደሳች ኾኖ ይመለሳል። መጽሐፉን በጀርባው ኋላ የተሰጠ ሰውማ፣(ዋ ጥፋቴ በማለት) ጥፋትን በእርግጥ ይጠራል። የተጋጋመች እሳትንም ይገባል።}[አል እንሽቃቅ፡6-12]

ለተፈጠርክበት ታላቅ ዓለማና ጥበብ በመኖር፣በዛሬው ሕይወትና በመጪው ዘላለማዊ ሕይወት የተድላና የደስታ መንገድ ተጓዝ። ይህን ስታደርግም በሕይወትህ ደስተኛ ትሆናለህና። ከሞትክ በኋላም ጌታህን ስትገናኘኝ የተረጋጋህና የታደልክ ትሆናለህና።

ፍጥረተ ዓለሙ በመላ እንዲሁ ለጌታው ተገዥና አምላኪ ነው። ሁሉም ፍጥረታት በየሁኔታቸው ጌታቸውን በማወደስ ያጠሩታል። አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ብሏል፦

{በሰማያት ያለው በምድርም ያለው ሁሉ ለአላህ ንጉሥ ቅዱስ አሸናፊ ጥበበኛ ለኾነው ያሞግሳሉ።} [አል ጁሙዓ፡1]

ከኃያልነቱ ፊትም ወድቀው ይሰግዳሉ። አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ብሏል፦

{አላህ በሰማያት ያለው ሁሉ፣በምድርም ያለው ሁሉ፣ፀሐይና ጨረቃም፣ከዋክብትም፣ተራሮችም፣ዛፎችም፣ተንቀሳቃሾችም፣ከሰዎች ብዙዎችም፣ለርሱ የሚሰግዱለት መኾኑን አታውቁምን? ብዙውም በርሱ ላይ ቅጣት ተረጋገጠበት፤አላህ የሚያዋርደውም ሰው ለርሱ ምንም አክባሪ የለውም፤አላህ የሻውን ይሠራልና።}[አል ሐጅ፡18]

ይልቁንም እነዚህ ፈጥረታት እንደየአግባቡና አንደሁኔታቸው ለጌታቸው ይሰግዳሉ። አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ብሏል፦

{አላህ በሰማያትና በምድር ያለ ሁሉ፣በራሪዎችም ክንፎቻቸውን (በአየር ላይ) ያንሳፈፉ ኾነው፣ለርሱ የሚያጠሩ (የሚያወድሱ) መኾናቸውን አላወቅህምን? ሁሉም ስግደቱንና ማጥራቱን በእርግጥ ዐወቀ፤አላህም የሚሠሩትን ሁሉ ዐዋቂ ነው።}[አል ኑር፡41]

ከዚህ አስፈሪና አስደማሚ ትእይንት ኋላ ቀርተህ ተዋራጅ መሆን ለአንተ ተገቢ ነውን?! አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ በማለት እውነት ተናግሯል፦

{አላህ በሰማያት ያለው ሁሉ፣በምድርም ያለው ሁሉ፣ፀሐይና ጨረቃም፣ከዋክብትም፣ተራሮችም፣ዛፎችም፣ተንቀሳቃሾችም፣ከሰዎች ብዙዎችም፣ለርሱ የሚሰግዱለት መኾኑን አታውቁምን? ብዙውም በርሱ ላይ ቅጣት ተረጋገጠበት፤አላህ የሚያዋርደውም ሰው ለርሱ ምንም አክባሪ የለውም፤አላህ የሻውን ይሠራልና።}[አል ሐጅ፡18]