ስለ ዩኒቨርስ አፈጣጠር አስበው ያውቃሉ?!

ስለ ዩኒቨርስ አፈጣጠር አስበው ያውቃሉ?!

ስለ ዩኒቨርስ አፈጣጠር አስበው ያውቃሉ?!

አላህ (ሱ.ወ.) የፈጠራቸውን ፍጥረታት ማስተዋልና ማስተንተን ወደ እምነት ከሚጠሩ፣ለሰው ልጅ እርግጠኝነትን ከሚጨምሩ፣የፈጣሪን ኃያልነትና የላቀ ጥበቡን ከሚያሳውቁት ዋነኛ መሳሪያዎች አንዱ ነው። አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ብሏል፦

{አላህ ሰማያትንና ምድርን እውነተኛ ኾኖ ፈጠረ፤በዚህ ውስጥ ለምእመናን ታምር አለበት።} [አል ዐንከቡት፡44]

በዚህ ዩኒቨርስ ውስጥ ስፍር ቁጥር የሌላቸው ፍጥረታት ይገኛሉ። ለመሆኑ እነዚህን ሁሉ ከመፍጠር ጀርባ ያለው ጥበብ ምን ይሆን?!

የአላህ (ሱ.ወ.) ገደብ የለሽ ችሎታና የኃያልነቱ ማስረጃዎች የምንጸባረቁባቸው አስደማሚ ምልክቶች በዩኒቨርስ ውስጥ ይገኛሉ። ዘመናዊው ሳይንስ የዚህን ጥበበኛ ኃያል ፈጣሪ ታላቅነት የሰውን ልጅ እንዲገነዘብ የሚያደርጉ አስረጅ ምልክቶችንንና ግኝቶችን ማቅረቡን እንደቀጠለ ይገኛል።

የሰው ልጅ ይህን ዩኒቨርስና ያቀፋቸውን ፍጥረታት በጥልቀት ቢያስተውል፣እጅግ በረቀቀ ገደብ የለሽ ኃያል ችሎታ የተፈጠረ፣አቅዶ ወስኖና አቀነባብሮ ባኖረው ጥበበኛ ዐዋቂ አምላክ የተገኘ መሆኑን በፍጹምነት አረጋግጦ ይቀበላል።

ይህ ዩኒቨርስና ጠፈራዊ አካላቱ፣ከዋክብቱ፣የፀሐያዊ ጭፍራ ስርዓቱና ያካካተታቸው ፕላኔቶቹ፣መሬትና በሕሮቿ፣ወንዞቸዋ፣ተራሮቸዋ፣እንስሳቱ፣እጽዋቱ . . እነዚህን ሁሉ አላህ (ሱ.ወ.) ከምንም ፈጥሮ ያስገኛቸው መሆኑን ማስተንተኑ ብቻ የአላህ (ሱ.ወ.) ችሎታ ዕውቀቱና ጥበቡ ምን ያህል ኃያል እንደሆነ ለመገንዘብ በቂ ነው። አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ብሏል፦

{እነዚያም የካዱት ሰማያትና ምድር የተጣበቁ የነበሩና የለያየናቸው መኾናችንን አያውቁምን? ሕያው የኾነንም ሁሉ ከውሃ ፈጠርን፤አያምኑምን? በምድርም ውስጥ በነሱ እንዳታረገርግ ጋራዎችን አደረግን፤ይመሩም ዘንድ በርሷ ውስጥ ሰፋፊ መንገዶችን አደረግን። ሰማይንም (ከመውደቅ) የተጠበቀ ጣራ አደረግን፤እነሱም ከታምራቶቿ ዘንጊዎች ናቸው። እርሱም ሌሊትንና ቀንን፣ፀሐይና ጨረቃንም የፈጠረ ነው፤ሁሉም በፈለካቸው (መዞሪያቸው) ውስጥ ይዋኛሉ።}[አልአንቢያ፡30-33]

አስተዋይ ሰው የአላህን ፍጡራን ሲያስተውል በዚህ ዩኒቨርስ ውስጥ ያለው ፍጥረት ሁሉ የጌታው አምላኪ መሆኑን፣ፍጥረታቱ በመላ እርሱን የሚያወድሱና የሚያጠሩት መሆኑን በእርግጠኝነት ይረዳል። አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ብሏል፦

{በሰማያት ያለው፣በምድርም ያለው ሁሉ ለአላህ፣ንጉሥ ቅዱስ አሸናፊ ጥበበኛ ለኾነው ያሞግሳሉ።} [አል ጁሙዓህ፡1]

ለኃያልነቱም ይሰግዳሉ። አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ብሏል፦

{አላህ በሰማያት ያለው ሁሉ፣በምድርም ያለው ሁሉ፣ፀሐይና ጨረቃም፣ከዋክብትም፣ተራሮችም፣ዛፎችም፣ተንቀሳቃሾችም፣ከሰዎች ብዙዎችም፣ለርሱ የሚሰግዱለት መኾኑን አታውቁምን? ብዙውም በርሱ ላይ ቅጣት ተረጋገጠበት፤አላህ የሚያዋርደውም ሰው ለርሱ ምንም አክባሪ የለውም፤አላህ የሻውን ይሠራልና።}[አል ሐጅ፡118]

በዚህ መልኩም ፍጥረታት ሁሉ ፈጣሪያቸውን ያወድሳሉ፤ይሰግዱለታልም። አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ብሏል፦

{አላህ በሰማያትና በምድር ያለ ሁሉ፣በራሪዎችም ክንፎቻቸውን (በአየር ላይ) ያንሳፈፉ ኾነው፣ለርሱ የሚያጠሩ (የሚያወድሱ) መኾናቸውን አላወቅህምን? ሁሉም ስግደቱንና ማጥራቱን በእርግጥ ዐወቀ፤አላህም የሚሠሩትን ሁሉ ዐዋቂ ነው።}[አል ኑር፡41]

እናም ለአማኝ ሰው መላው ዩኒቨርስ በጥቅሉ በአንድ ቅፍለት ወደ አንድ አቅጣጫ ወደ አላህ (ሱ.ወ.) እያመራ መሆኑ ይታየዋል። እርሱም በበኩሉ ከዚህ ብሩክ መልካም ጉዞ ጋር ራሱን ያጣጥምና ሕይወቱ አስደሳች ሆኖ ውስጣዊ መረጋጋት ያገኛል።

ከዩኒቨርስ መፈጠር ጀርባ ያለው ጥበብ

1- ለአላህ አንድነት አስረጅ መሆኑ፦

ወሰን የሌለው ይህ ዩኒቨርስ፣ያቀፋቸው ፍጥረታትና ታምራት ለአላህ (ሱ.ወ.) ኃያል ችሎታና ለድንቅ ጥበቡ ምሉእነት ትልቁ ማስረጃ ነው። አንድነቱን፣ከርሱ በቀር ሌላ አምላክና ሌላ ጌታ አለመኖሩንም በግልጽ ያመለክታል። አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{እናንተንም ከዐፈር መፍጥሩ፣ከዚያም እናንተ ወዲያውኑ የምትበታተኑ ሰዎች መኾናችሁ ከአስደናቂ ምልክቶቹ ነው። ለናንተም ከነፍሶቻችሁ (ከጎሶቻችሁ) ሚስቶችን ወደነርሱ ትረኩ ዘንድ መፍጠሩ፣በመካከላችሁም ፍቅርንና እዝነትን ማድረጉ፣ከአስደናቂ ምልክቶቹ ነው፤በዚህ ውስጥ ለሚያስተውሉ ሕዝቦች ታምራቶች አልሉ። ሰማያትንና ምድርንም መፍጠሩ፣የቋንቋዎቻችሁና የመልኮቻችሁም መለያየት ከአስደናቂ ምልክቶቹ ነው፤በዚህ ውስጥ ለዐዋቂዎች ታምራቶች አሉበት። በሌሊትና በቀንም መተኛታችሁ፣ከችሮታውም መፈለጋችሁ፣ከምልክቶቹ ነው፤በዚህ ውስጥ ለሚሰሙ ሕዝቦች ታምራቶች አሉበት።}[አል ሩም፡30-23]

በተጨማሪም አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{(ሙሐመድ ሆይ) በል ፦ ምስጋና ለአላህ ይግባው፤በነዚያም በመረጣቸው ባሮቹ ላይ ሰላም ይውረድ፤አላህ በላጭ ነውን? ወይስ ያ የሚያጋሩት? (ጣዖት)። ወይም ያ ሰማያትንና ምድርን የፈጠረና ከሰማይም ለናንተ ውሃን ያወረደው? (ይበልጣል? ወይስ ያ የሚያጋሩት?)፤ በርሱም ባለ ውበት የኾኑትን የታጠሩ አትክልቶችን፣ዛፍዋን ልታበቅሉ ለናንተ ችሎታ ያልነበራችሁን አበቀልን፤ከአላህ ጋር ሌላ አምላክ አለን? (የለም)፤ግን እነሱ (ከውነት) የሚያዘነብሉ ሕዝቦች ናቸው። ወይም ያ ምድርን መርጊያ ያደረገና በመካከሏም ወንዞችን ያደረገ፣ለርሷም ጋራዎችን ያደረገ፣በሁለቱ ባሕሮችም (በጣፋጩና በጨው ባሕር) መካከል ግርዶን ያደረገ፣(ይበልጣልን? ወይስ የሚያጋሩት?) ከአላህ ጋር ሌላ አምላክ አለን? ግን አብዛኞቻቸው አያውቁም። ወይም ያ ችግረኛን በለመነው ጊዜ የሚቀበል፣መከራንም የሚያስወግድ፣በምድርም ላይ ምትኮች የሚያደርጋችሁ፤(ይበልጣልን? ወይስ የሚያጋሩት?) ከአላህ ጋር ሌላ አምላክ አለን? ጥቂትንም አትገሠጹም። ወይም ያ በየብስና በባሕር ጨለማዎች ውስጥ የሚመራችሁ፣ነፋሶችንም ከዝናሙ በፊት አብሳሪ ኾነው የሚልክ? (ይበልጣልን? ወይስ የሚያጋሩት?) ከአላህ ጋር ሌላ አምላክ አለን? አላህ (በርሱ) ከሚያጋሩዋቸው ሁሉ ላቀ። ወይም ያ መፍጠርን የሚጀምር፣ከዚያም የሚመልሰው፣ከሰማይና ከምድርም ሲሳይን የሚሰጣችሁ አምላክ፣(ይበልጣልን? ወይስ የሚያጋሩት?) ከአላህ ጋር ሌላ አምላክ አለን? እውነተኞች እንደ ኾናችሁ አስረጃችሁን አምጡ በላቸው።}[አል ነምል፡59-64]

2- ዩኒቨርስን ለሰው ልጅ የተገራ ማድረጉ፦

አላህ (ሱ.ወ.) የሰውን ልጅ ለቁሳዊ ነገሮች ተገዥ ከመሆን ነጻ አውጥቶት፣በዚህ ዩኒቨርስ ውስጥ ያለውን ሁሉ፣በሰማያትና በምድርም ያለውን ከርሱ ብቻ በሆነ ችሮታና ቸርነቱ ለሰው ጥቅም የተገራና የተመቻቸ እንዲሆን አድርጎለታል። ይህም የሰው ልጅ ምድርን እንዲያለማና የተጠሪነት ግዴታውን ማለትም ለርሱ ያለው ተገዥነት ምሉእ ሆኖ ተልእኮው እንዲሳካ ለማድረግ ነው። መግራትና ማመቻቸት ማለት እዚህ ላይ ሁለት ትርጉሞች አሉት፦ አንደኛው አላህን (ሱ.ወ.)፣ችሮታውን፣ቸርነቱንና ኃያልነቱን ማወቅን መግራት ሲሆን፤ሌላው የሰውን ልጅ ለርሱ ከተገሩለት ሌሎች ፍጥረታት ሁሉ በላይ ደረጃውን ከፍ በማድረግ መግራትና ማመቻቸት ማለት ነው። አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{ለናንተም በሰማያት ያለውንና በምድርም ያለውን ሁሉ በመላ ከርሱ ሲኾን የገራላችሁ ነው፤በዚህ ለሚያስተነትኑ ሕዝቦች ታምራት አለበት።}[አል ጃሢያህ፡13]

በተጨማሪም አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{አላህ ያ ሰማያትንና ምድርን የፈጠረ፣ ከሰማይም ውሃን ያወረደ፣በርሱም ከፍሬዎች ሲሳይን ለናንተ ያወጣ፣መርከቦችንም በፈቃዱ በባሕር ላይ ይንሻለሉ ዘንድ ለናንተ የገራ፣ ወንዞችንም ለናንተ የገራ ነው። ፀሐይንና ጨረቃንም ዘውትር ኼያጆች ሲኾኑ ለናንተ የገራ፣ሌሊትንና ቀንንም ለናንተ የገራላችሁ ነው። ከለመናችሁትም ሁሉ የሰጣችሁ ነው፤ የአላህንም ጸጋ ብትቆጥሩ አትዘልቋትም፤ሰው በጣም በደለኛ ከሐዲ ነው።}[ኢብራሂም፡32-34]

3- ከጌታችሁ ጋር እንደምትገናኙ ታረጋግጡ ዘንድ

የሰውን ልጅ አፈጣጠር ትተን የሰማያትንና የምድርን አፈጣጠር ብናስተውል ከሞት በኋላ ዳግም መቀስቀስና ሌላ ሕይወት ስለመኖሩ ግልጽ ማስረጃ ማየት እንችላለን። የነበረውን መመለስ የሌለውን አዲስ ከመፍጠር የቀለለ አይደለምን?! አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{እርሱም ያ መፍጠርን የሚጀምር፣ከዚያም የሚመልሰው ነው፤እርሱም (መመለሱ) በርሱ ላይ በጣም ገር ነው፤}[አል ሩም፡27]

ይልቁንም ሰማያትንና ምድርን መፍጠር ሰውን ከመፍጠር በጣም የላቀ ነው። አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ብሏል፦

{ሰማያትንና ምድርን መፍጠር፣ሰዎችን ከመፍጠር ይልቅ ታላቅ ነው፤ግን አብዛኛዎቹ ሰዎች አያውቁም።}[አል ሙእሚን፡57]

በተጨማሪም አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{አላህ ያ ሰማያትን የምታዩዋት አዕማድ ሳትኖር ያነሳት፣ከዚያም በዐርሹ (ዙፋኑ) ላይ የተደላደለ፣ፀሐይንና ጨረቃንም የገራ ነው፤ሁሉም ለተወሰነ ጊዜ ይሮጣሉ፤ነገሩን ሁሉ ያስተናብራል፤በጌታችሁ መገናኘት ታረጋግጡ ዘንድ ታምራቶችን ይዘረዝራል።}[አል ረዕድ፡2]