ሰውን መፍጠሩና ክቡር ፍጡር ማድረጉ

ሰውን መፍጠሩና ክቡር ፍጡር ማድረጉ

ሰውን መፍጠሩና ክቡር ፍጡር ማድረጉ

ከዩኒቨርስ ግዝፈትና ከሰማያትና ከምድር ታላቅነት ጋር አላህ (ሱ.ወ.) ፍጥረተ ዓለሙን ሁሉ ለሰው ልጅ ጥቅም የተገራና የተመቻቸ እንዲሆን አድርጎታል። አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{ለናንተም በሰማያት ያለውንና በምድርም ያለውን ሁሉ በመላ ከርሱ ሲኾን የገራላችሁ ነው፤}[አል ጃሢያህ፡13]

ይህም የሰው ልጅ የርሱ ክቡር ፍጡር በመሆኑና ከተቀሩት ፍጥረታት ሁሉ በላይ ያላቀው በመሆኑ ነው። አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{የኣደምንም ልጆች በእርግጥ (ከሌላው ፍጡር) አከበርናቸው፤በየብስና በባሕርም አሳፈርናቸው፤ከመልካሞችም (ሲሳዮች ሰጠናቸው)፤ከፈጠርናቸውም ፍጡሮች በብዙዎቹ ላይ ማብለጥን አበለጥናቸው።}[አል እስራእ፡70]

አላህ (ሱ.ወ.) የመጀመሪያውን ሰው የኣደምን አፈጣጠርና እንዴት እንደ አከበረው፣ከዚያም በሰይጣን ጉትጎታና በጥፋቱ ከገነት ወደ መሬት እንዴት እንዳወረደው፣በኋላም አንዴት ይቅር ብሎ ምሕረት እንዳደረገለት ተርኮልናል። አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{በእርግጥም ፈጠርናችሁ፤ከዚያም ቀረጽናችሁ፤ከዚያም ለመላእክቶች ለኣደም ስገዱ አልን፤ወዲያውም ሰገዱ፤ኢብሊስ (ዲያብሎስ) ሲቀር፣ከሰጋጆቹ አልኾነም። (አላህ) ባዘዝኩህ ጊዜ ከመስገድ ምን ከለከለህ? አለው፤እኔ ከርሱ የበለጥኩ ነኝ፤ከእሳት ፈጠርከኝ፤እርሱን ግን ከጭቃ ፈጠርከው አለ። ከርሷ (ከገነት ወይም ከሰማያት) ውረድ፤በርሷ ውስጥ ልትኮራ አይገባምና፣ወጣም፣አንተ ከወራዶቹ ነህና አለው፤

፦ እስከሚቀሰቀሱበት ቀን ድረስ አቆየኝ አለ። አንተ ከሚቆዩት ነህ አለው።

፦ ስለ አጠመምከኝም ለነርሱ በቀጥተኛው መንገድ ላይ በእርግጥ እቀመጥባቸዋለሁ አለ። ከዚያም ከስተፊቶቻቸው፣ከኋላቸውም፣ከቀኞቻቸውም፣ከግራዎቻቸውም፣በእርግጥ እመጣባቸዋለሁ፤አብዛኞቻቸውንም አመስጋኞች ኾነው አታገኛቸውም (አለ)።

፦ የተጠላህ ብራሪ ስትኾን ከርሷ ውጣ፤ከነርሱ የተከተለህ ከናንተ ከመላችሁም ገሀነምን በእርግጥ እሞላታለሁ አለው። ኣደምም ሆይ! አንተም ሚስትህም በገነት ተቀመጡ፤ከሻችሁትም ስፍራ ብሉ፤ግን ይህችን ዛፍ አትቅረቡ፤(ራሳቸውን) ከሚበድሉት ትኾናላችሁና (አላቸው)። ሰይጣንም ከዕፍረተ ገላቸው የተሸሸገውን ለነርሱ ሊገልጥባቸው በድብቅ ንግግር ጎተጎታቸው፤ጌታችሁም መልኣኮች እንዳትኾኑ ወይም ከዘላለም ነዋሪዎች እንዳትኾኑ እንጂ ከዚች ዛፍ አልከለከላችሁም አላቸው። እኔ ለናንተ በእርግጥ ከሚመክሯችሁ ነኝ ሲልም ማለላቸው። በማታለልም አዋረዳቸው፤ከዛፊቱም በቀመሱ ጊዜ፣ዕፍረተ ገላቸው ለሁለቱም ተገለጠችላቸው፤ከገነት ቅጠልም በላያቸው ላይ ይደርቱ ጀመር፤ጌታቸውም ከዚቻችሁ ዛፍ አልከለከልኋችሁምን? ሰይጣንም ለናንተ ግልጽ ጠላት ነው አላልኋችሁምን? ሲል ጠራቸው።

፦ ጌታችን ሆይ! ነፍሶቻችንን በደልን፤ለኛ ባትምር ባታዝንልንም በእርግጥ ከከሳሪዎቹ እንኾናለን አሉ። (አላህ) ፦ ከፊላችሁ ለከፊሉ ጠላት ሲኾን ውረዱ፤ለእናንተም በምድር ላይ እስከ ተወሰነ ድረስ መርጊያና መጠቀሚያ አላችሁ፣አላቸው።}[አል አዕራፍ፡11-24]

አላህ (ሱ.ወ.) ሰውን እጅግ ባማረ ቅርጽ ፈጥሮት ከመንፈሱ ነፍቶበታል፤በዚህም የተስተካከለ ቁመና ያለው ሕያው፣የሚሰማ የሚያይ፣የሚናገርና የሚንቀሳቀስ ድንቅ ክቡር ፍጡር አደረገው፦

{ከሰዓሊዎችም ሁሉ በላጭ የኾነው አላህ ላቀ።} [አል ሙእምኑን፡12-16]

የሚያስፈልገውንም ሁሉ አስተማረው።ለሌሎች ፍጥረታት ያልተሰጡ እንደ አእምሮ፣ዕውቀት፣ንግግር፣ውብ ቅርጽ፣ያማረ ተክለ ሰውነት፣ክቡር ቁመና፣መካከለኛ አካል፣የማሰብ፣የመማርና የማገናዘብ ችሎታ . . የመሳሰሉ ተሰጥኦዎችና ባሕርያት ባለቤት አደረገው። ወደ መልካም ስነምግባራትና ውብ ጸባያትም መራው፤ከፈጠራቸው ብዙ ፍጥረታትም አላቀው። ከነዚህ የከበሬታዎቹ መገለጫዎች መካከል የሚኪሉትን እናገኛለን ፦

 

-አላህ (ሱ.ወ.) ከመጀመሪያው ኣደምን የፈጠረው በእጁ ነው፤ይህም ታላቅ ክብርና አቻ የሌለው ደረጃ ነው። አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{(አላህም) ኢብሊስ ሆይ! በሁለት እጆቹ ለፈጠርኩት ከመስገድ ምን ከለከለህ? (አሁን) ኮራህን? ወይስ (ፊቱኑ) ከትዕቢተኞቹ ነበርክ አለው።}[ሷድ፡75]

አላህ (ሱ.ወ.) ሰውን እጅግ ባማረ አቋም ፈጥሮታል። አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{ሰውንም በጣም በአማረ አቋም ላይ ፈጠርነው።}[አል ቲን፡4]

በተጨማሪም እንዲህ ብሏል፦

{ቀረጻችሁም፤ቅርጻችሁንም አሳመረ፤መመለሻችሁም ወደርሱ ነው።}[አል ተሃቡን፡3]

አላህ (ሱ.ወ.) መላእክትን በሙሉ ለሰው ልጆች አባት ለኣደም እንዲሰግዱ በማዘዝ ሰውን አክብሮታል። አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{ለመላእክትም ለኣደም ስገዱ ባልናቸው ጊዜ (አስታውስ)፤ወዲያውም ሰገዱ፤ኢብሊስ ብቻ ሲቀር፣ከጭቃ ለፈጠርከው ሰው፣እሰግዳለሁን? አለ።}[አል እስራእ፡61]

አላህ (ሱ.ወ.) ለሰው ልጅ ማሰቢያ አእምሮ፣ማስተዋልና ማገናዘብን፣መስማትና መናገርን የተቀሩትንም የግንዛቤ ሕዋሳት ያደለው በመሆኑ ክቡር ፍጡር አድርጎታል። አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{አላህም ከናቶቻችሁ ሆዶች ምንም የማታውቁ ሆናችሁ አወጣችሁ፤ታመሰግኑም ዘንድ፣ለናንተ መስሚያን፣ማያዎችንም፣ልቦችንም፣አደረገላችሁ።}[አል ነሕል፡78]

አላህ (ሱ.ወ.) ከራሱ የሆነ መንፈስ ነፍቶበት ሰውን ክቡርና የመንፈስ ምጥቀት የተቸረው ልዩ ፍጡር አድርጎታል። አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{ፍጥረቱንም ባስተካከልኩና ከመንፈሴ በነፋሁበት ጊዜ፣ለርሱ ሰጋጆች ኾናችሁ ውደቁ (አልኩ)።}[ሷድ፡72]

ይህ ለሰው ልጅ እጅግ የላቀ ክብር ነው።በመሆኑም ሰው ሰው በመሆኑ ብቻ ክቡር ስለሆነ መከበር አለበት። ከአላህ (ሱ.ወ.) መንፈስ የተነፋበትን ክቡር ፍጡር ማዋረድና መበደልም ፈጽሞ ተገቢ አይደለም።

በተጨማሪም አላህ (ሱ.ወ.) መላእክትንና ጋኔን ከልክሎ ሰውን መርጦ በምድሪቱ ላይ ተጠሪው አድርጎታል። አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{(ሙሐመድ ሆይ!) ጌታህ ለመላእክት ፦ እኔ በምድር ላይ ምትክን አድራጊ ነኝ፤ ባለ ጊዜ፣(የኾነውን አስታውስ፤እነርሱም) እኛ ከማመስገን ጋር የምናጠራህ፣ላንተም የምንቀድስ ስንኾን በርሷ ውስጥ የሚያጠፋንና ደሞችንም የሚያፈስን ታደርጋለህን? አሉ፤(አላህ) እኔ የማታውቁትን ነገር ዐውቃለሁ አላቸው።}[አል በቀራህ፡30]

ይህ ትእዛዙን የማይጥሱ፣ዘውትር እርሱን በማወደስ፣በማመስገን እና በማጥራት ላይ የተሰማሩት ቅን አገልጋዮቹ መላእክት እንኳን ያላገኙት ታላቅ ደረጃ ነው።

 

-አላህ (ሱ.ወ.) በዚህ ፍጥረተ ዓለም ውስጥ በሰማያትና በምድር ያሉትን ሁሉ፣ፀሐያትና ጨረቃዎችን፣ከዋክብት እና ፕላኔቶችን፣ጋላክሲዎችን እና ፀሐያዊ ጭፍራን . . ለዚህ ክቡር ፍጡር ለሰው ልጅ የተገሩለት እንዲሆኑ አድርጓል። አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{ለናንተም በሰማያት ያለውንና በምድርም ያለውን ሁሉ በመላ ከርሱ ሲኾን የገራላችሁ ነው፤}[አል ጃሢያህ፡13]

አላህ (ሱ.ወ.) መላውን የሰው ዘር የፈለገውን ያህል ክብርና ደረጃ ቢኖረው እንኳ ለማንኛውም ዓይነት ፍጡር ተገዥ ከመሆን ነጻ አውጥቷል። ይህም ከሰብአዊ ፍጡራን አምልኮና ተገዥነት ወደ ኃያሉ አላህ አምልኮና ተገዥነት የሚያሸጋግረው በመሆኑ ለሰው ልጅ ከምንም በላይ የሆነ የላቀ የነጻነት ደረጃ ነው። ለዚህም ነው አላህ (ሱ.ወ.) በራሱና በአገልጋይ ባሮቹ መካከል የሚገባ አማላጅም ሆነ አገናኝን የማይቀበለው። ይሁን እንጂ አንዳንዳንድ ወገኖች በሰው ልጅና በፈጣሪ ጌታው መካከል የአምላክነት ባህርያትና መብት የሰጧቸውን አማላጅ አገናኞችን ከራሳቸው ፈጥረው አቅርበዋል። አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ያሉትን አማላጆች ውድቅ በማድረግ የሰውን ልጅ አክብሮታል። አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{ከርሱ በቀር ሌላ አምላክ የሌለውን አንድን አምላክ ሊግገዙ እንጂ ያልታዘዙ ሲኾኑ፣ሊቃውንቶቻቸውንና መነኮሳታቸውን፣የመርየምን ልጅ አልመሲሕንም ከአላህ ሌላ አማልክት አድርገው ያዙ፤ከሚያጋሩት ሁሉ የጠራ ነው።}[አል ተውበህ፡31]

የሰውን ልጅ በቀዷእና በቀደር በማመንና ቁሳዊ ጥረትን ከውጤት ጋር በማያያዝ አማካይነት ከመጻኢው ጊዜ ስጋት፣ከጭንቀት፣ተስፋ ከመቁረጥና ከማዘን አላህ (ሱ.ወ) ነጻ አውጥቶታል። በቀዷእና በቀደር ማመን ማለትም አላህ (ሱ.ወ.) ሁሉንም ነገር ከመከሰቱ በፊት ወስኖ እርሱ ዘንድ የመዘገበው መሆኑንና ከርሱ ውሳኔና መሻት ውጭ የሚሆን ምንም ነገር አለመኖሩን ማመን፣አማኙን ሰው በሰላምና በእርጋታ፣በራስ በመተማመንና በከበሬታ፣በተገቢው መንገድ ሳቢያን ከውጤት በማገናኘት ማድረግ የሚገባውን ሁሉ እስከፈጸመ ድረስም የሆነው አላህ (ሱ.ወ.) የሻውና የወሰነው ነውና ባለፈውና ባመለጠው ነገር ባለ መቆጨትና ባለ ማዘን ሁኔታ ውስጥ እንዲኖር ያደርገዋል። አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{በምድርም፣በነፍሶቻችሁም፣መከራ (ማንንም) አትነካም፣ሳንፈጥራት በፊት በመጽሐፍ የተመዘገበች ብትኾን እንጅ፤ይህ በአላህ ላይ ገር ነው።}[አል ሐዲድ፡22]

ይህ እምነት ባለቤቱን ሚዘናዊ አእምሮ ኖሮት በእውነተኛ የስነልቦና መረጋጋትና በከፍተኛ የመተማመን ሁኔታ ውስጥ አንዲኖር ያደርገዋል። ችግርና መከራ ሚዛን አሳጥተውት ተጽእኖ የማያሳድሩበት፣ደሰታና ምቾትም ትእቢትና መንበጣረርን የማያስከትሉበት ሚዛኑን የጠበቀ ሰብእና እንዲላበስ ያስችለዋል።

አላህ (ሱ.ወ.) ለሰው ልጅ አእምሮና ለአስተሳሰቡ ከፍተኛ ዋጋ ሰጥቷል፤እንዲያስተውልና እንዲያስተነትንም አዞታል። የሰማያትንና የምድርንም አፈጣጠር ማስተንተንን፣ምክንያታዊ አስረጅና ትንተና ማቅረብንም ግዴታ አድርጓል። አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{፦ በሰማያትና በምድር ያለውን (ታምር) ተመልከቱ፣በላቸው፤ታምራቶችና አስፈራሪዎችም፣ለማያምኑ ሕዝቦች አይጠቅሙም።} [ዩኑስ፡101]

አእምሮ እንዲከበርና ትኩረት እንዲሰጠው፣እንዲሠራና እንዲያስተውል እንዲደረግ፣በጭፍን ተከታይነትና ወገንተኝነት አማካይነት ከሥራ ውጭ እንዳይደረግ አዟል። በሰው ልጅ ላይ የተጣለው ኃላፊነትና ግዴታ ከአእምሮ ጋር የተያያዘና ከርሱ ውጭ የማይሆን ከማድረጉም በላይ ለርሱ መኖር ማስረጃና ለአንድነቱም አመላካች አድርጎታል። የአመለካከት ልዩነት ሲኖርም በአእምሯዊ የማስረጃ አቀራረብ ስልት መዳኘትንም አዟል። አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ብሏል፦

{ገነትንም አይሁድን፣ወይም ክርስቲያኖችን የኾነ እንጂ አይገባትም አሉ፤ይህቺ (ከንቱ) ምኞታቸው ናት፣እውነተኞች እንደ ኾናችሁ አስረጃችሁን አምጡ በላቸው።}[አል በቀራህ፡111]

አእምሮን ከአፈተረት፣ከአባይ ጠንቋይ ማጭበርበር፣በጋኔንና በመናፍስት ከመታገዝና ከመሳሰሉት ነገሮችም ነጻ እንዲሆን አድርጎታል።

እያንዳንዱ ሰው በሠራውና በፈጸመው ነገር በግሉ ኃለፊና ተጠያቂ መሆኑን አረጋግጦ፣አንዱ በፈጸመው ነገር ሌላው ተጠያቂ አለመሆኑን ገልጾታል። አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{ኀጢአትን ተሸካሚም (ነፍስ) የሌላዋን ሸክም አትሸከምም፤}[ፋጢር፡18]

ቁርኣን በነዚህ የሰው ልጅ የክቡርነት መገለጫዎች፣የውርስ ኃጢአት ጽንሰ ሐሳብን ውድቅ አድርጎ በማስወገድ የሰውን ዘር ከሸክሙ ነጻ አድርጓል። (11)

ሴትን ከወንድ ጋር እኩል ማድረግ፦

ለሰው ልጅ የተሰጠው ከበሬታ በአንድ ጾታ ላይ ብቻ የተወሰነ አይደለም። ከበሬታው በመሰረቱ ልክ እንደ ወንዱ ሴቷንም ያጠቃለለ ነው። አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{ለነርሱም (ለሴቶች) የዚያ በነርሱ ላይ ያለባቸው (ግዳጅ) ብጤ በመልካም አኑዋኑዋር (በባሎቻቸው ላይ መብት) አላቸው፤}[አል በቀራህ፡228]

በተጨማሪም አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{ምእመናንና ምእመናትም ከፊሎቻቸው ለከፊሉ ረዳቶች ናቸው፤}[አል ተውባህ፡71]

በወዲያኛው ዓለም ሽልማትና ምንዳ ሴት ልጅ ፈጽሞ ከወንዱ አትለይም። አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{ጌታቸውም እኔ ከናንተ፣ከወንድ ወይም ከሴት፣የሠሪን ሥራ አላጠፋም፤ከፊላችሁ ከከፊሉ ነው፤በማለት ለነርሱ ልመናቸውን ተቀበለ፤}[ኣል ዒምራን፡195]

በተጨማሪም አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{ከወንድ ወይም ከሴት፣እርሱ አማኝ ኾኖ ከበጎ ሥራዎች አንዳችን የሚሠራም ሰው፣እነዚያ ገነትን ይገባሉ፤በተምር ፍሬ ላይ ያለችን ነጥብ ያክል እንኳ አይበደሉም።}[አል ኒሳእ፡124]

አላህ (ሱ.ወ.) ልክ እንደ ወንዱ ሁሉ ሴቷም ሙሉ ኃላፊነትንና ግዴታን ለመሸከም ብቁ፣ በሽልማትም ሆነ በቅጣትም ከወንዱ ጋር እኩል ሲያደርጋት ሴትን ክቡር ፍጡር አድርጓታል። ሌላው ቀርቶ ለሰው ልጅ የተላለፈው የመጀመሪያው መለኮታዊ ትእዛዝ ለወንዱና ለሴቷም ለመጀመሪያው ሰው ለኣደምና ለሐዋ በአንድ ላይ የተላለፈ ነበር። አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

‹ኣደም ሆይ! አንተ ከነሚስትህ በገነት ተቀመጥ፤ከርሷም በፈለጋችሁት ስፍራ በሰፊው ተመገቡ፤ግን ይህችን ዛፍ አትቅረቡ፤ከበደለኞች ትኾናላችሁና አልንም።}[አል በቀራህ፡35]

በተጨማሪም አላህ (ሱ.ወ.) የኣደምን ከገነት መውጣትና የዝርዮቹን መከራ፣በአንዳንድ ሃይማኖቶች ውስጥ እንደሚነገረው ዓይነት ተጠያቂነቱን በሔዋን ላይ አላደረገም። ይልቁንም አደምን ነው የመጀመሪያው ተጠያቂ አድርጎ የጠቀሰው። አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{ወደ ኣደምም ከዚህ በፊት ኪዳንን በእርግጥ አወረድን፤ረሳም፤ለርሱም ቆራጥነትን አላገኘንለትም።}[ጣሃ፡115]

{ከርሷም፣በልሉ፤ለነርሱም ሐፍረተ ገላቸው ተገለጸች፤ከገነትም ቅጠል በላያቸው ላይ ይለጥፉ ጀመር፤ኣደምም የጌታውን ትእዛዝ፣(ረስቶ) ጣሰ፤(ከፈለገው መዘውተር) ተሳሳተም። ከዚያም ጌታው መረጠው፤ከርሱም ጸጸቱን ተቀበለው፤መራውም።}[ጣሃ፡121-122]

እነሆም ሴቶችና ወንዶች በሰብአዊነት በዚህ መልኩ እኩል ተደርገዋል። አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{እላንተ ሰዎች ሆይ! እኛ ከወንድና ከሴት ፈጠርናችሁ፤እንድትተዋወቁም ጎሣዎችና ነገዶች አደረግናችሁ፤አላህ ዘንድ በላጫችሁ፣በጣም አላህን ፈሪያችሁ ነው፤አላህ ግልጽን ዐዋቂ፣ውስጥንም ዐዋቂ ነው።}[አል ሑጁራት፡13]

በዚህ መልኩም ወንዶችና ሴቶች በሚከተሉት ጉዳዮች እኩልና ተጋሪዎች ናቸው ፦

በግላዊ ቁሳዊ መብቶች የሕግ ኃላፊነት፦ የሴት ልጅ የሕግ ሰውነት የታፈረና የተከበረ ነው። ግዴታን በመወጣትና በመታዘዝ ብቁነት ላይ አላህ (ሱ.ወ.) ከወንዱ ጋር እኩል አድርጓት በመብቷ የመጠቀምን፣ንብረት የመያዝ፣ የማስተዳደርና ውል የመዋዋል፣መሸጥና መግዛትን የመሳሰሉትን ሁሉ አረጋግጦላታል። እነዚህ የሲቪል መብቶቿ በአፈጻጸም በወንዱም ላይ ከሚጣል ገደብ ውጭ ያለ ምንም ገደብ ሕጋዊ ተፈጻሚነት ይኖራቸዋል። አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{አላህም ከፊላችሁን በከፊሉ ላይ በርሱ ያበለጠበትን ጸጋ አትመኙ። ለወንዶች ከሠሩት ሥራ ዕድል አላቸው፤ለሴቶችም ከሠሩት ሥራ ዕድል አላቸው። አላህንም ከችሮታው ለምኑት፤አላህ በነገሩ ሁሉ ዐዋቂ ነውና። }[አል ኒሳእ፡32]

የውርስ መብቷን አስመልክቶም አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{ለወንዶች፣ወላጆችና የቅርብ ዘመዶች ከተውት (ንብረት) ፈንታ አላቸው። ለሴቶችም፣ወላጆችና የቅርብ ዘመዶች ከተውት ከርሱ ካነሰው ወይም ከበዛው፣ፈንታ አላቸው። የተወሰነ ድርሻ (ተደርጓል)።}[አል ኒሳእ፡7]

በሕግ ፊትም በደጉም ሆነ በክፉ ከወንድ ጋር ሙሉ በሙሉ እኩል ተደርጋለች። አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{ሰራቂውንና ሰራቂይቱንም በሠሩት ነገር ለቅጣት፣ከአላህ የኾነን መቀጣጫ፣እጆቻቸውን ቁረጡ፤አላህም አሸናፊ ጥበበኛ ነው።}[አል ማኢዳህ፡38]

በወዲያኛው ሕይወት ሽልማትና ቅጣትም ከወንዱ ጋር እኩል ነች። አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{ከወንድ ወይም ከሴት፣እርሱ አማኝ ኾኖ በጎን የሠራ፣መልካም ኑሮን በእርግጥ እናኖረዋለን፤ይሠሩትም ከነበሩት ነገር በመልካሙ ምንዳቸውን እንመነዳቸዋለን።}[አል ነሕል፡97]

በመረዳዳትና በመተጋገዝም እኩል ናቸው።አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ብሏል፦

{ምእመናንና ምእመናትም፣ከፊሎቻቸው ለከፊሉ ረዳቶች ናቸው፤በደግ ነገር ያዛሉ፤ከክፉም ይከለክላሉ፤ሶላትንም ይሰግዳሉ፤ዘካንም ይሰጣሉ፤አላህንና መልክተኛውንም ይታዘዛሉ፤እነዚያን አላህ በእርግጥ ያዝንላቸዋል፤አላህ አሸናፊ ጥበበኛ ነውና።}[አል ተውባህ፡72]

ለሴቶች እዝነትና ርህራሄን ማሳየት የታዘዘ ሲሆን በጦርነት ላይ ሴቶችን መግደል አላህ እርም አድርጎ ከልክሏል። በወር አበባዋ ሰሞን አብሯት መሆንንና አብሮ መብላትም ታዟል። አይሁዶች ይህን ሁሉ በመከልከል በወር አበባዋ ጊዜ በአካል ይርቋታል፤ጊዜው እስኪያልፍ ድረስም አብሯት መብላትን ይከለክላሉ። የሴት ልጅ ከአላህ መልክተኛም  ግሩም የሆነ ከበሬታ ተችሯታል። ነብዩ  እንዲህ ብለዋል፦ «በላጫችሁ ለቤተሰቡ ከሌላው ይበልጥ ጥሩ የሆነ ሰው ነው፤እኔ ከሁላችሁም ይበልጥ ለቤተሰቤ ጥሩ ነኝ።»[በትርምዚ የተዘገበ]

በዘመናቸው አንዲት ሴት በባሏ እንደ ተመታች ሲሰሙ ተቆጥተው እንዲህ ብለው ነበር ፦ «አንዳችሁ ባለቤቱን እንደ ባሪያ ይመታትና ከዚያ በቀኑ መጨረሻ ላይ ያቅፋታል!»[በቡኻሪ የተዘገበ]

ሴቶች ተሰብስበው ባሎቻቸውን ለመክሰስ ወደ አላህ መልክተኛ r ሲመጡ እንዲህ ነብዩ ብለዋል፦ «ባሎቻቸውን የሚከሱ ብዙ ሴቶች ወደ ሙሐመድ ቤተሰብ መጥተዋል፤እነዚያ (ሚስቶቻቸውን የሚጎዱ ወንዶች) ምርጦቻችሁ አይደሉም።»[በአቡ ዳውድ የተዘገበ]

ሴት እንደ እናት ወንድ ያላገኘውን ደረጃም አግኝታለች። አላህ (ሱ.ወ.) ከአባት በበለጠ ለእናት ደግ መሆንን አዟል። አንድ ሰው ወደ ነብዩ r መጥቶ ፦ «የአላህ መልክተኛ ሆይ! ለኔ መልካም አያያዝና ለደግነቴ ከሁሉም ይበልጥ ባለመብት የሆነው ማነው? ሲላቸው ፦ እናትህ ናት አሉት፤ከዚያስ? አላቸው፤እናትህ ናት፣አሉት፤ከዚያስ? አላቸው፤እናትህ ናት አሉት፤ከዚያስ? አላቸው፤አባትህ ነው አሉት።»[በቡኻሪና ሙስሊም የተዘገበ]

ለሴት ልጅ አስተዳደግም የሚሰተው ትኩረት ለወንዶች ልጆች አስተዳደግ ከሚሰጠው ትኩረት የበለጠ አላህ ዘንድ ምንዳ እንዳለው ሲገልጹም ነብዩ r እንዲህ ብለዋል ፦ «እነዚህ ሴት ልጆች ተሰጥተውት በነሱ የተፈተነና በጥሩ አያያዝ ደግ ለሆነላቸው ሰው፣ከገሀነም እሳት መከላከያ ይሆኑለታል።»[በቡኻሪና ሙስሊም የተዘገበ]

በተጨማሪም ነብዩ r እንዲህ ብለዋል ፦«አላህ ሆይ! የነዚህን የሁለቱን ደካሞች የሙት ልጅንና የሴትን መብት የጣሰውን ሰው ኃጢአተኛ አድርጌያለሁ።»[በነሳኢ የተዘገበ]