ሙሐመድ

ሙሐመድ

ነቢዩ ሙሐመድ  የነቢያትና የመልክተኞች መደምደሚያ ሲሆኑ፣የእስራኤል ቤት ነቢያት መደምደሚያ የሆኑት ነቢዩ ዒሳ  በነቢዩ ሙሐመድ  መምጣት ሕዝባቸውን አብስረዋል። ይህን በማስመልከት አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{የመርየም ልጅ ዒሳም፦ የእስራኤል ልጆች ሆይ! ፦እኔ ከተውራት በፊቴ ያለውን የማረጋግጥና ከኔ በኋላ በሚመጣው መልክተኛ፣ስሙ አሕመድ በኾነው የማበስር ስኾን፣ወደናንተ (የተላክሁ) የአላህ መለክተኛ ነኝ፣ባለ ጊዜ (አስታውስ)፤በግልጽ ታምራቶች በመጣቸውም ጊዜ፣ይህ ግልጽ ድግምት ነው፣አሉ።}[አል ሶፍ፡6]

ይህ የብስራት ትንቢትም በተውራትና በኢንጂልም ውስጥ ሰፍሮ ይገኛል። አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{ለነዚያ፣ያንን እነሱ ዘንድ በተውራትና በኢንጂል ተጽፎ የሚያገኙትን፣የማይጽፍና የማያነብ ነቢይ የኾነውን መልክተኛ የሚከተሉ ለኾኑት፣(በእርግጥ እጽፋታለሁ)፤በበጎ ሥራ ያዛቸዋል፤ከክፉም ነገር ይከለክላቸዋል፤መልካም ነገሮችንም ለነርሱ ይፈቅድላቸዋል፤መጥፎ ነገሮችንም በነሱ ላይ እርም ያደርግባቸዋል። ከነሱም ላይ ሸክማቸውንና እነዚያንም በነሱ ላይ የነበሩትን እንዛዝላዎች (ከባድ ሕግጋቶች) ያነሳላቸዋል፤እነዚያም በርሱ ያመኑ፣ያከበሩትም፣የረዱትም፣ያንንም ከርሱ ጋር የተወረደውን ብርሃን የተከተሉ፣እነዚያ እነሱ የሚድኑ ናቸው።}[አል አዕራፍ፡157]

ይልቅዬም በሕይወት እያሉ ነቢዩ ሙሐመድ  ቢላኩ እንዲያምኑባቸውና እንዲደግፉአቸው፣ይህንኑም ለሕዝቦቻቸው እንዲያሳውቁ አላህ (ሱ.ወ.) ሁሉንም ነቢያት ቃል ኪዳን አስገብቷል። አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{አላህ የነቢያትን ቃል ኪዳን፣ከመጽሐፍና ከጥበብ ሰጥቻችሁ ከዚያም ከእናንተ ጋር ላለው (መጽሐፍ) የሚያረጋግጥ መልክተኛ ቢመጣላችሁ በርሱ በእርግጥ እንደምታምኑበት በእርግጥም እንድትረዱት ሲል በያዘ ጊዜ (አስታውስ)፤አረጋገጣችሁን? በየሃችሁ ላይ ኪዳኔን ያዛችሁምን? አላቸው፤አረጋገጥን አሉ፤እንግዲያስ መስክሩ፤እኔም ከእናንተ ጋር ከመስካሪዎቹ ነኝ አላቸው።}[ኣሊ ዒምራን፡81]

ቅዱስ ቁርኣንም እነዚያን ብሥራቶች አውስቶ ለሙሐመድ  እውነተኛነት ማስረጃ አድርጓል። አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{እነዚያም የካዱት ሰዎች፣መልክተኛ አይደለህም ይላሉ፤በኔና በናንተ መካከል መስካሪ በአላህና እርሱ ዘንድ የመጽሐፉ ዕውቀት ባለው ሰው በቃ፣በላቸው።}[አል ረዕድ፡43]

በተጨማሪም አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{እርሱም (ቁርኣን) በቀድሞዎቹ መጻሕፍት ውስጥ (የተወሳ) ነው። የእስራኤል ልጆች ሊቃውንት፣የሚያውቁት መኾኑ፣ለነርሱ (ለመካ ከሓዲዎች) ምልክት አይኾናቸውምን?}[አል ሹዐራ፡196-197]

በብሉይና አዲስ ኪዳኖች ውስጥ ወደፊት እንደሚላኩ የተበሰረ ከመሆኑ አንጻር፣ልጆቻቸውን የሚያውቁትን ያህል ሙሐመድን  በማወቃቸው የመጀመሪያዎቹ አማኞች መሆን ይገባቸው ስለነበረው የመጽሐፉ ሰዎችም አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{እነዚያ መጽሐፍን የሰጠናቸው፣ወንዶች ልጆቻቸውን እንደሚያውቁ (በመጽሐፋቸው ምልክቱ ተነግሯልና ሙሐመድን) ያውቁታል፤ከነሱም የተለዩ ክፍሎች፣እነርሱ የሚያውቁ ሲኾኑ ውነቱን በእርግጥ ይደብቃሉ።}[አል በቀራህ፡146]

በተጨማሪም እንዲህ ብሏል፦

{እነርሱ ጋርም ላለው (መጽሐፍ)፣አረጋጋጭ የኾነ መልክተኛ ከአላህ ዘንድ በመጣላቸው ጊዜ፣ከነዚያ መጽሐፍን ከተሰጡት ከፊሉ እነርሱ እንደማያውቁ ኾነው የአላህን መጽሐፍ ከጀርባዎቻቸው ኋላ ጣሉ።}[አል በቀራህ፡101]

አላህ (ሱ.ወ.) በመጨረሻው ዘመን እንደሚላክ የተናገረው ነቢይ ሙሐመድ  መሆናቸውን ሁሉም ትንቢታዊ ብስራቶች በግልጽ ያመለከቱ ቢሆንም፣ከመጽሐፉ ባለቤቶች ከፊሎቹ ግን እያወቁ በቅዱሳን መጽሐፎቻቸው ውስጥ የሰፈረውን እውነታ በመደበቅ የማያውቁ ለመምሰል ይሞክራሉ።

ከርሳቸው በፊት የነበሩት ነቢያትና መልክተኞች ይዘው እንደመጡ ሁሉ፣ነቢዩ ሙሐመድም  አንድ አላህን ብቻ ያለ ምንም ማጋራት የማምለክን የተውሒድ ጥሪ ይዘው ነው የመጡት። አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{ከአንተ በፊትም፣እነሆ ከኔ ሌላ አምላክ የለምና ተገዙኝ፣በማለት ወደርሱ የምናወርድለት ቢኾን እንጅ ከመልክተኛ አንድንም አልላክንም።}[አል አንቢያ፡25]

የተላኩትም ከርሳቸው በፊት የነበሩትን ነቢያትና መልክተኞች ተልእኮ በማረጋገጥና ያለ ምንም ልዩነት በሁሉም በማመን ነው።

{ከነርሱ በአንድም መካከል የማንለይ ስንኾን አመንን፤}[አል በቀራህ፡136]

ይህ ብቻም ሳይሆን በሙሐመድ  አምኖ ከተቀሩት የአላህ ነቢያትና መልክተኞች ውስጥ በአንዱም እንኳ ሳያምን የቀረ ሰው፣በሙሐመድም ያላመነ ስለመሆኑ ቁርኣን ውስጥ ሰፍሯል፦

{ለናንተ ከሃይማኖት ያንን ኑሕን ያዘዘበትን ደነገገላችሁ፤ያንንም ወደ አንተ ያወረድነውን፣ያንንም በርሱ ኢብራሂምን፣ሙሳንና ዒሳንም ያዘዝንበትን፣ሃይማኖትን በትክክል አቋቁሙ፣በርሱም አትለያዩ፣ማለትን (ደነገግን)፤}[አል ሹራ፡13]

ነቢዩ  የአላህ መልክተኛና አገልጋይ ባሪው መሆናቸውንም አረጋግጧል፦

{፦ እኔ አምላካችሁ አንድ አምላክ ብቻ ነው ማለት ወደኔ የሚወረድልኝ ብጤያችሁ ሰው ብቻ ነኝ፤የጌታውንም መገናኘት የሚፈልግ ሰው፤መልካም ሥራ ይሥራ፤በጌታውም መግገዛት አንድንም አያጋራ፣በላቸው።}[አል ከህፍ፡110]

እርሳቸውን አስመልክቶ የመጽሐፎቹ ባለቤቶች ምልክታቸውን በግልጽ ያውቁ ዘንድ በቀደሙት ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ እንደ ሰፈረው ሁሉ፣ነቢዩ ሙሐመድ  የማያነቡና የማይጽፉ ነቢይ ነበሩ። አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{ለነዚያ፣ያንን እነሱ ዘንድ በተውራትና በኢንጂል ተጽፎ የሚያገኙትን፣የማይጽፍና የማያነብ ነቢይ የኾነውን መልክተኛ የሚከተሉ ለኾኑት፣(በእርግጥ እጽፋታለሁ)፤በበጎ ሥራ ያዛቸዋል፤ከክፉም ነገር ይከለክላቸዋል፤መልካም ነገሮችንም ለነርሱ ይፈቅድላቸዋል፤መጥፎ ነገሮችንም በነሱ ላይ እርም ያደርግባቸዋል። ከነሱም ላይ ሸክማቸውንና እነዚያንም በነሱ ላይ የነበሩትን እንዛዝላዎች (ከባድ ሕግጋቶች) ያነሳላቸዋል፤እነዚያም በርሱ ያመኑ፣ያከበሩትም፣የረዱትም፣ያንንም ከርሱ ጋር የተወረደውን ብርሃን የተከተሉ፣እነዚያ እነሱ የሚድኑ ናቸው።}[አል አዕራፍ፡157]

በቀደሙት ነቢያት እጅ አላህ (ሱ.ወ.) ተአምራትን እንዳሳየ ሁሉ፣በነቢዩ ሙሐመድ  እጅም ብዙ ቁሳዊ ተአምራቶችን አሳይቷል። ከተሰጧቸው ተአምራቶች ሁሉ ትልቁና ዋነኛው ሕያው ተአምር ግን፣የቀድሞዎቹና የመጪዎቹ ዜና ያለበት፣ማብራሪያ፣መመሪያ፣እዝነትና ብስራት የተካተተበት ታላቁ መጽሐፍ ቅዱስ ቁርኣን ነው።

{መጽሐፉንም፣ለሁሉ ነገር አብራሪ፣መሪም እዝነትም፣ለሙስሊሞችም አብሳሪ ኾኖ ባንተ ላይ አወረድነው።}[አል ነሕል፡89]

ቁርኣን ለምእመናን የልብ ብርሃን ነው፦

{ይህ (ቁርኣን) ለሰዎች የልብ ብርሃኖች ነው። ለሚያረጋግጡም ሕዝቦች መሪና እዝነት ነው።}[አል ጃሢያ፡20]

የማያነበውና የማይጽፈው ነቢይ  ሰዎች የተወዛገቡባቸውን ጉዳዮች በቁርኣን አብራርቶላቸዋል፦

{ባንተም ላይ መጽሐፉን አላወረድንም፣በርሱ የተለያዩበትን ለነርሱ ልታብራራላቸውና ለሚያምኑትም ሕዝቦች መሪና እዝነት ሊኾን እንጂ።}[አል ነሕል፡64]

እውነተኛው ሙሐመድ እያሉ ሲጠሯቸው የኖሩት የቁረይሽ ከሃዲዎች የነቢዩን  ታማኝነትና ሐቀኝነት ቢያውቁም አስተባበሉዋቸው። አላህም (ሱ.ወ.) ከመላው የሰው ዘር ጋር ብቻ ሳይሆን ከአጋኔንትም ጋር ጭምር ተሳባስበውና ተረዳድተው ቁርኣንን የመሰለ መጽሐፍ እንዲያመጡ ተፈታታኝ ጥያቄ አቀረበላቸው፦

{፦ ሰዎችም ጋኔኖችም የዚህን ቁርኣን ብጤ በማምጣት ላይ ቢሰባሰቡ፣ከፊላቸው ለከፊሉ ረዳት ቢኾንም እንኳ ብጤውን አያመጡም፤በላቸው።}[አል እስራእ፡88]

በዘመኑ የላቀ የስነጽሑፍና የቋንቋ አጠቃቀም አቅም የነበራቸው ቢሆንም ማምጣት አቅቷቸው ዋሹ። ጥያቄውን በማቅለል ከፈለጉት ኃይል ጋር ተባብረው መሰሉን አስር ምዕራፎች ብቻ እንዲያመጡ ጋበዛቸው፦፦

{ይልቁንም (ቁርኣንን) ቀጣጠፈው ይላሉን? እውነተኞች እንደ ኾናችሁ፣ብጤው የኾኑን ዐሥር የተቀጣጠፉ ሱራዎች አምጡ፤ከአላህም ሌላ የቻላችሁትን (ረዳት) ጥሩ፣በላቸው።}[ሁድ፡13]

አሁንም ማምጣት ተሳናቸው። አሁንም ጥያቄውን በማቅለል መሰሉን አንድ ምዕራፍ ብቻ እንዲያመጡ ተጠየቁ፦

{በባሪያችን ላይ ካወረድነው፣በመጠራጠር ውስጥ ብትኾኑ፣ከብጤው አንዲትን ምዕራፍ አምጡ፤}[አል በቀራህ፡23]

ታላላቅ ባለቅኔ ገጣሚዎችና የተባ አንደበት ያላቸው ተናጋሪዎች እያሏቸው የተባሉትን ማምጣት አሁንም ሳይችሉ ቀሩ። የቁረይሽ ከሓዲዎችም ነቢዩን ማስተባበል ገፉበት። አላህ (ሱ.ወ.) ግን እንደ ኢብራሂም፣ኑሕ፣ሙሳና ዒሳ ያሉ [የአላህ ሰላም በሁሉም ላይ ይሁን] ቁርጠኞቹ የትዕግስትና የጽናት ባለቤቶች (ኡሉል ዐዝም) ነቢያትና መልክተኞች እንዳደረጉ ሁሉ እንዲታገሱ ነቢዩን  አዘዛቸው፦

 

{ከመልክተኞችም የቆራጥነት ባለቤቶች የኾኑት እንደ ታገሡ ሁሉ ታገሥ፤።}[አል አሕቃፍ፡35]

ነቢዩም  በአንደበታቸውና በምጡቅ ስነምግባራቸው በትዕግስትና በጥበብ እያስተማሯቸውና እየመከሯቸው ደዕዋቸውን ቀጠሉ። ከከሓዲዎቹ ተንኮልም አላህ ጠበቃቸው፦

{አንተ ነቢዩ ሆይ! በቂህ አላህ ነው፤ለተከተሉህም ምእመናን፣(በቂያቸው አላህ ነው)።}[አል አንፋል፡64] {አላህ ባሪያውን በቂ አይደለምን?}[አል ዙመር፡36]

ነቢያቱንና መልክተኞቹን ድል እንዳጎናጸፈ ሁሉ አላህ (ሱ.ወ.) በከሓዲዎቹ ላይ ድል አቀዳጃቸው፦

{አላህ፦ እኔ በእርግጥ አሸንፋለሁ፤መልክተኞቼም (ያሸንፋሉ ሲል) ጽፏል። አላህ ብርቱ፣አሸናፊ ነውና።}[አል ሙጃደላህ፡21]

በተጨማሪም አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{(የርዳታ) ቃላችንም፣መልክተኞች ለኾኑት ባሮቻችን በውነት አልፋለች። እነርሱ ተረጂዎቹ እነርሱ ናቸው። ሰራዊቶቻችንም፣በእርግጥ አሸናፊዎቹ እነርሱ ናቸው።}[አል ሶፍፋት፡171-173] {እኛ መልክተኞቻችንን እነዚያንም ያመኑትን፣በቅርቢቱ ሕይወት፣ምስክሮችም በሚቆሙበት ቀን በእርግጥ እንረዳለን።}[አል ሙእሚን፡51]

ከሓዲዎቹ ተልእኮአቸውን ለመገደብና የደዕዋውን ብርሃን ለማጥፋት የቻሉትን ሁሉ አደረጉ፤አላህ (ሱ.ወ.) ግን ደዕዋቸውን ድል አድራጊ በማድረግ ጸጋውን አሟላ፦

{የአላህን ብርሃን በአፎቻቸው ሊያጠፉ ይሻሉ፤አላህም ከሓዲዎቹ ቢጠሉም እንኳ ብርሃኑን ገላጭ ነው። እርሱ ያ አጋሪዎቹ ቢጠሉም መልክተኛውን በመምሪያ (መጽሐፍ)፣በውነተኛው ሃይማኖትም (በእስላም)፣ከሃይማኖት ሁሉ በላይ ይፋ ሊያደርገው የላከ ነው።›[አል ሰፍ፡8-9]

አላህ (ሱ.ወ.) ጸጋውን ምሉእ በማድረግም እስላምን አሸናፊ አደረገ።በሁሉም መለኮታዊ ሃይማኖቶች ውስጥም የተውሒድን ወሳኝነት በአጽንኦት አሳወቀ። ለሰው ልጆች የዋለውን ታላቅ ጸጋም በዚህ መልክትና በዚህ ሃይማኖት አሟልቶ ደመደመ ፦

{ዛሬ ሃይማኖታችሁን ለናንተ ሞላሁላችሁ። ጸጋዬንም በናንተ ላይ ፈጸምኩ። ለናንተም እስላምን ከሃይማኖት በኩል ወደድኩ፤}[አል ማእዳህ፡3]

በተጨማሪም የሃይማኖቱን ጥበቃ ለራሱ ወስዶ ደዕዋው እስከ ትንሳኤ ቀን ድረስ ቋሚና ቀጣይ እንዲሆን አደርጓል፦

{እኛ ቁርኣንን እኛው አወረድነው፤እኛም ለርሱ ጠባቂዎቹ ነን።}[አል ሕጅር፡9]

እስላምንም የቀደሙት መለኮታዊ ሃይማኖቶች ሁሉ የመጨረሻው ማጠቃላያና መደምደሚያ መልክት አደረገው፦

{ሙሐመድ፣ከወንዶቻችሁ የአንድም ሰው አባት አይደለም፤ግን የአላህ መልክተኛና የነቢዮች መደምደሚያ ነው፤አላህም በነገሩ ሁሉ ዐዋቂ ነው+።}[አል አሕዛብ፡40]

እስላምን አላህ (ሱ.ወ.) ምድርንና በላይዋ ያሉትን እስኪወርስ ድረስ ቀሪና ቀጣይ መልክት አደረገው።

ለመሆኑ ይህ እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ በአላህ (ሱ.ወ.) ጥበቃ እየተደረገለት ቋሚና ቀጣይ የሆነው መልክት ምንድነው . . ?