የተንገዳገደውን ቤት መናድ

የተንገዳገደውን ቤት መናድ

ድካም ከተጫጫነው አጭር ዕረፍት በኋላ ሁለተሩ ወዳጆች ለመነቃቃት መቀመጫዎቻቸውን ተለዋወጡ። በመቀጠልም ማይክል ውይይቱን ጀመረ፦

በሙስሊም ሕብረተሰብ ውስጥ ፍች በብዛት ይስተዋላል፤ለዚህ መንስኤው እስላም ፍችን የተፈቀደ ማድረጉ ይመስለኛል።

ራሽድ፦ አንደኛ- የዚህን ድንጋጌ ውጤቶች በርሱ ላይ እስኪደፈደፍ፣ፍችን ሕጋዊ በማድረግ እስላም የመጀመሪያው አይደለም። ከእስላም በፊትም ፍች በመላው ዓለም ላይ ተስፋፍቶ ይገኝ ነበር። ባል ተገቢ ይሁን አይሁን በሆነ ነገር ሚስቱ ላይ ይናደድና ያለ ምንም መብትና ማካካሻ ፈቶ ከቤት ያበርራት ነበር። የግሪክ ስልጣኔ ባበበበት ዘመን ፍች ያለ ምንም ገደብና ግዴታ የተንሰራፋ ነበር። የአይሁድ ሃይማኖት ደግሞ ፍችን ሕጋዊ አድርጎ የሚፈቅድ መሆኑ የታወቀ ሲሆን፣ለወንዱ በነጠላ ፍላጎቱ ብቻ የሚጠቀምበት መብቱ ነው። ኤሁዶች ምክንያት ሲኖር ብቻ ፍች መፈጸምን የተሻለ አድርገው የሚመለከቱ ቢሆንም፣ይሁዲ ባል ሚስቱን ያለ ምንም ምክንያት የመፍታት መብት አለው። በተጨማሪም የተፈታች ሴት ሌላ ባል ካገባች ወደ መጀመሪያ ባሏ ዳግም መመለስ አትችልም።

ሁለተኛ- መንስኤው እስላም ፍችን መፍቀዱ ነው እንድንል፣እውን ፍች በሙስሊም ሕብረተሰቦች ውስጥ የተስፋፋ ነውን? ለማንኛውም ለማነጻጸር ያመቸን ዘንድ ከዓለም ዙሪያ ፍችን የሚመለከቱ አንዳንድ አኃዛዊ መረጃዎችን እስኪ እንመልከት፦

በአሜሪካ ከ1992 እስከ 1995 ባሉት ዓመታት ውስጥ አማካይ የፍች ብዛት ከያንዳንዱ 1000 ጋብቻ 502 ደርሷል። ይህ ቁጥር በከፍተኛ ደረጃ ይጨምራል ተብሎ ይጠበቃል። የአሜሪካ አስተዳደር ከ1999 ወዲህ ጋብቻን የሚመለከት አኃዛዊ መረጃን ይፋ ሲያደርግ ፍችን የሚመለከተው አኃዛዊ መረጃ ይፋ እንዳይወጣ ያደረገበት ምክንያትም ይህ ሳይሆን አልቀረም። በሩሲያ ፌድሬሽን ከ2001 እስከ 2004 ባሉት ዓመታት ውስጥ የፍች አማካይ ቁጥር ከ1000 ጋብቻዎች ውስጥ 750 ደርሷል። በስዊድን ደግሞ በተመሳሳይ ዓመታት አማካይ ቁጥሩ ከያንዳንዱ 1000 ጋብቻ 539 ፍች ነው። በእንግሊዝ ከ2000 እስከ 2003 ባሉት ዓመታት ውስጥ አማካይ የፍች ቁጥር ከያንዳንዱ 1000 ጋብቻ 538 ፍች ሆኗል።

በጃፓን ከ2000 እስከ 2004 ባሉት ዓመታት አማካይ የፍች ቁጥር ከያንዳንዱ 1000 ጋብቻ 366 ደርሷል።

ሙስሊም ሕብረተሰቦችን ስንመለከት ግን ከፍተኛው የፍች አማካይ ቁጥር የተመዘገበው በኩዌት ሲሆን፣ከ2000 እስከ 2004 ባሉት ዓመታት ውስጥ ከ1000 ጋብቻ 347 ደርሷል። በተቀሩት አገሮች ውስጥ አኃዙ ከዚህ በጣም ያነሰ ነው። በጆርዳን ከ2000 እስከ 2004 ባሉት ዓመታት ውስጥ የፍች አማካይ ቁጥር ከ1000 ጋብቻ 184 ነበር። በፍልስጥኤም በተመሳሳይ ዓመታት ውስጥ የፍች አማካይ ቁጥር ከ1000 ጋብቻ 142 ነበር።

በግብጽ ከ2000 እስከ 2003 ባሉት ዓመታት ውስጥ የፍች አማካይ ቁጥር ከ1000 ጋብቻ 347 ፍች ነበር። በሶሪያ ደግሞ ከ2000 እስከ 2002 ባሉት ዓመታት ውስጥ የፍች አማካይ ቁጥር ከ1000 ጋብቻ 84 ብቻ ነበር። በሊብያ ከ2000 እስከ 2004 ባሉት ዓመታት ውስጥ የፍች አማካይ ቁጥር ከ1000 ጋብቻ 51 ብቻ ነበር። በኢራን ከ2002 እስከ 2003 ባሉት ዓመታት ውስጥ አማካይ ቁጥሩ ከ1000 ጋብቻ 97 ፍች ነበር።

ከዚህ ሁሉ በኋላ ፍች በሙስሊም ሕብረተሰቦች ውስጥ የተስፋፋ ነው፣መንስኤውም እስላም ፍችን የተፈቀደ ማድረጉ ነው ማለት እንችላለን ወይ?!

ማይክል፦ ነገር ግን እስላም ከተቀሩት ሃይማኖቶችና ማሕበራዊ ስርዓቶች ጋር ሲነጻጻር ፍችን በቀላሉ የሚፈጸም በማድረግ የሚታወቅ ነው።

ራሽድ፦ ይህ ትችት ብዙ ነገሮችን የሚያካትት ነው፤ፍቀድልኝና በዝርዝር ላብራራው።

ማይክል፦ መቀጠል ትችላለህ።

ራሽድ፦ የመጀመሪያው ጉዳይ እስላም ፍችን በቀላሉ እንዲፈጸም ያደርጋል የሚል ጠቅለል ያለ እምነት ማሳደርን የሚመለከት ሲሆን፣በእርግጥ ፍችን የሚያበረታታ ሃይማኖትም ሆነ ማህበራዊ ስርዓት የለም። በእስላም ትምህርቶች የማይገዙና የተሰጣቸውን አንዳንድ መብቶች አለ አግባብ የሚጠቀሙ ወገኖች በዚህ ጉዳይ ላይ ቸልተኞች ሊሆኑ መቻላቸውን እኔም ካንተ ጋር ልስማማበት እችላለሁ። በተመሳሳይ መልኩ ግን የእስላም ትምህርቶች ከዚህ ተግባር ነጻ መሆናቸውን ማወቅ ይኖርብናል። ትምህርቶቹ የፍችን ቁጥር በማሳነስና የሚያስከትላቸውን አፍራሽ ተጽእኖዎች በሚያቃልል ሁኔታ ሥርዓት በማስያዝ ረገድ በጣም ግልጽ ናቸው። በአንዳንድ ሙስሊም ማህበረሰቦች ዘንድ የሚስተዋለው ከእስላም ሃይማኖት ትክክለኛ ሕግጋትና ከሥርዓቱ በመራቃቸው ምክንያት የሚከሰት ነው።

ማይክል፦ ይህን ነጥብ የበለጠ ልታብራራልኝ ትችላለህ?

ራሽድ፦ ጋብቻ እስላም ውስጥ፣በጊዜ ወስኖ መገደብ ፈጽሞ የማይፈቀድ ቋሚና የጸና ውል ነው። ይህም የባልና ሚስቱ ትዳራዊ ሕይወት በሞት እስኪለያዩ ድረስ ጸንቶ የሚቀጥል ነው ተብሎ ይታሰባል ማለት ነው። የጋብቻ ውል ቁርኣን ውስጥ ጥብቁና ከባዱ ቃል ኪዳን ተብሎ ነው የተገለጸው። ይህም ጋብቻ ክቡር መሆኑንና ለማፍረስ ሊታሰብ የማይገባ መሆኑን ያመለክታል። በተጨማሪም ፍች እስላም ውስጥ በአስገዳጅ ሁኔታዎች ውስጥ ብቻ ካልሆነ በስተቀር ሊፈጸም የማይገባ ያልተወደደ ጉዳይ ነው። ሌላ መፍትሔ ሊቀበሉ የማይችሉ አስገዳጅ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙ እንኳ ከመፈጸሙ በፊት የእርቅ ሙከራዎች ማድረግ ተገቢ መሆኑን እስላም አመልክቷል። የመፈጸሙን እድል ሊያጠቡ የሚችሉና መሟላት ያለባቸውን ቀዳሚ ሂደቶች ከማኖሩም በላይ ከተፈጸመም የሁሉንም ወገኖች ክብር በሚያረጋግጥና የተቀረውን ቤተሰብ በሚጠብቅ ስነምግባር የታጀበ እንዲሆን እስላም መመሪያ አስቀምጧል።

አንድ ባል እርሱ የማይወደው ጎን ስላላት ሚስቱን ቢጠላ እንኳ፣ሌሎች ጥሩ ጥሩ ባሕርያትና ጎኖች ሊኖሯት ስለሚችል እንዳይፈታትና አብሯት እንዲቆይ እስላም ጥሪ ያደርጋል። የጋብቻን ክቡርነት በማስጠበቅ ረገድም የፍች ቃልን በተራ ነገር ሁሉ እንደዋዛ ከመናገር እንዲቆጠቡ ሙስሊሞችን አስጠንቅቋል። ባል ሚስቱን በማረም ረገድ ራሱን የሚቆጣጠር ታጋሽ እንዲሆንና ከችኩልነት እንዲርቅ እስላም ያበረታታ ሲሆን፣ባልና ሚስት ችግራቻውን በራሳቸው መፍታት ካልቻሉ ጉዳዩ የሚያሳስባቸው ሌሎች ወገኖች ችግሩን ለመፍታት ጣልቃ እንዲገቡም አሳስቧል። ከዚህ ሁሉ ጥረት በኋላ ፍች አይቀሬ ሆኖ ከተገኘም፣ለሙከራና ለእርቅ ተጨማሪ ዕድል ለመስጠት ሲባል መማላስ የሌለበት የመጨረሻውን ፍች በአንዴ ሳይሆን በደረጃዎች እንዲፈጸም አድርጓል። የትዳር ጎጆው የግድ መፍረስ ካለበት ግን በሦስት ዙሮች እንዲፈጸም ያደረገ ሲሆን፣ከአንደኛውና ከሁለተኛ በኋላ ባል ሚስቱን የመመለስና ትዳሩን የማዳን መብት አለው። ከዚህም አልፎ እስላም ከሦስተኛው ዙር በኋላም እንኳ ባልና ሚስት ዳግም እንዲጣመሩ ዕድል የሰጠ ሲሆን፣የመጨረሻው ዕድል ግን በጣም ከባድና አሳማሚ ከሆነ እርምጃ ማለትም የተፈታችው ሚስት ሌላ ባል አግብታ ከዚያ ባል ከተፋታች ቦኋላ ብቻ እውን የሚሆን ነው።

ማይክል፦ ይህ የመጀመሪያው ነው፤ሌላኛው ነጥብስ?

ራሽድ፦ በጣም አስፈላጊ የሆነው ሌላው ነጥብ፣ሙስሊም ባልሆኑ ሌሎች ሕብረተሰቦች ዘንድ ያለው የተሳሳተ አመለካከት ሁኔታ ሲሆን፣እውነቱን ለመናገር በነዚህ ሕብረተሰቦች ውስጥ ፍች በተራ ነገሮች ምክንያት ይፈጸማል። ይህን አንተም በሚገባ ታውቃለህ። ለምሳሌ በአሜሪካ የፍርድ ቤት ውሎዎች እንደሚያመለክቱት ከባልና ሚስት አንዳቸው ኮምፒውተር የመጠቀም ወይም የቲቪ ፕሮግራሞችን ወይም ውድድሮችን የመከታተል ሱስ ካለበት ፍርድ ቤት የፍች ውሳኔ ሊሰጥ ይችላል። በካናዳ ደግሞ ከባልና ሚስት አንዱ በእንቅልፍ ሰዓት ሌላኛውን በማንኮራፋት የሚረብሸው መሆኑን በማረጋገጥ ብቻ ፍች መፈጸም ይቻላል። በጣሊያን ከባልና ሚስት አንዱ ሌላውን አንዳንድ የቤት ሥራዎችን እንዲሠራ ካስገደደ የፍች ብይን ማግኘት ይቻላል። በእንግሊዝ አገር ደግሞ ማስታወሻን በማጥፋት በመሳሰሉት ድርጊቶች አንደኛውን ወገን ማንቋሸሽ ለፍች ምክንያት ተደርጎ ሊቀርብ ይችላል።

በጀፓን የትዳር ጓደኛው እርሱን በማያስደስት መንገድ በመተኛቱ የፍች ጥያቄ ከቀረበለት ፍርድ ቤት የፍች ብያኔ ሊሰጥ ይችላል።

ማይክል፦ ወዳጄ ራሽድ የጠቀስካቸው ነገሮች በሙሉ በትክክል የሚፈጸሙ ናቸው። ይሁን እንጂ ይህ ከሃይማኖት ተነጥለው የወጡ ሴኩላር የፍትሕ ሥርዓቶች ውስጥ ያለው ተጨባጭ ሁኔታ ነው። ክርስትናን በተመለከተ ግን በፍች ላይ ያለው የከረረ አቋምና እገዳው በግልጽ የሚታወቅ ሲሆን፣በነባራዊው ዓለም ለማረጋገጥ አስቸጋሪ በሆኑ በተወሰኑ ጥቂት ምክንያቶች ብቻ እንጂ ፍች ፈጽሞ የተከለከለ ነው።

ራሽድ፦ እኔ ግን ይህ አክራሪ ቋም ከሰው ልጆች ተፈጥሮ ጋር ፈጽሞ አይጣጣምም ባይ ነኝ። በሙስሊሙ ዓለም የሚኖሩና በዚህ ረገድ በሁለቱ ሃይማኖቶች መካከል ከፍተኛ ልዩነት የሚያስተውሉ አንዳንድ ክርስቲያኖች፣በማህበራዊ ሕይወታቸው ውስጥ ወሳኝ ነጥብ ላይ ደርሰው ውስብስብ ለሆነው የሕይወት ባህሪ ሃይማኖታቸው ውስጥ መፍትሔና ምላሽ በሚያጡበት ጊዜ፣ከዚህ የከረረ አቋም ለመሸሽ ሲሉ ሃይማኖታቸውን ሊተው የሚችሉ የመሆኑ እውነታ ለዚህ ማብራሪያ ነው።

ይህ እስላምን የተለየ የሚያደርገው አንዱ ጎን ነው። እስላም የጋብቻ ውል በጊዜ ያልተገደበ ዘላለማዊ እንዲሆን ግዴታ አድርጎ ሲደነግግ፣ሕጉ የተሰጠው ምድር ላይ ለሚኖሩ፣የራሳቸው መለያ ባህርያት ላሏቸውና ሊለዋጡ በሚችሉ ሁኔታዎች ለሚኖሩ ሰብአዊ ፍጡራን መሆኑን ያውቃል። በሙከራ ብቻ እንጂ አስቀድሞ ሊታወቅ ለማይችል የምርጫ ስህተትም ቦታ ይሰጣል። የነዚህ ሁኔታዎች መለዋወጥ ወይም በዚህ ስህተት ላይ መውደቅ የተለያየ ደረጃ ያላቸው አፍራሽ ውጤቶችን ሊያስከትል እንደሚችልም ግንዛቤ ውስጥ ያስገባል። እነዚህ አፍራሽ ነገሮች አንዳንዴ በትዕግስት ሊታለፉ የሚችሉ ሲሆን፣ሌላ ጊዜ ደግሞ ከበድ ያሉ ስነልቦናዊ ማህበራዊና ቁሳዊ ኪሳራዎችን ሳያስከትሉና መራራ መስዋእትነትን ሳያስከፍሉ በትዕግስት የሚታለፉ አይሆኑም። ለዚህ ነው እስላም ኑሮ ሲደናቀፍ፣መውጫ ሲጠፋና ባለበት መቀጠል ፈጽሞ በማይቻልበት አጣብቅኝ ውስጥ ሲገባ፣እነዚህ ስህተቶች ሊታረሙና ሊስተካከሉ የሚችሉበትን መንገድ የቀየሰው። በዚህ ረገድ እስላም ነባራዊ ሁኔታን የሚያገናዝብ ሃይማኖት ሲሆን፣ለባል ለሚስትና ለመላው ቤተሰብ የተሟላ ፍትሕ ያሰፍናል። በመለያየትም ቢሆን እንኳ አካሄድን ማረምና አዲስ ተሞክሮ መጀመር፣የቤተሰቡን አባላት በሙሉ በአለመግባባትና በልዩነቶች እሳት ከመለብለብ፣ወይም የትዳርን ግብና ዓለማ እውን የማያደርግ ግንኙነት ከመቀጠል የተሸለ ይሆናል። ከጋብቻ አበይት ግቦችና ዓለማዎች አንዱ በፍቅርና በመተሳሰብ የሚገለጸው ስነ ልቦናዊ እርካታ፣ሕሊናዊ መረጋጋት፣የተረጋጋና የተሳካ ቤተሰባዊ ሕይወት መመስረት ነው . . እናም ፍች እስላም ውስጥ መድኃኒትና አካሄድን ማስተካከል፣ለለውጥ ዕድል በመስጠት የተሻለ ስኬታማ አዲስ ሕይወት የሚጀመርበት አጋጣሚ ነው።

በኔ እምነት ከላይ በተብራራው ሥርዓትና ማእቀፍ ውስጥ እስላም ፍችን መደንገጉ፣የሃይማኖቱን ምቹነትና ተጨባጭነት የሚያረጋግጥ ነው።

ማይክል፦ እሽ፣እስላም ፍችን ለወንዱ ብቻ የተሰጠ መብት ለምን ያደርጋል? ይህ ሴቷን መበደል አይሆንም?!

ራሽድ፦ ይህ ጉዳይ አሁንም በድጋሜ ሁሉንም ጎኖች በካተተ መልኩ አጠቃላይ በሆነ ማእቀፍ ውስጥ መታየት ይኖርበታል። ከአጠቃላዩ ማህበራዊ ሥርዓት አኳያ እንመርምረው ማለቴ ነው። ሥርዓቱ ከራሱ ከጋብቻና ከዓላማዎች ይጀምርና የቤተሰብን ጽንሰ ሀሳብ፣ሁሉም ወገኖች በቤተሰብ ውስጥ የሚጫወቱትን ሚና፣መብትና ግዴታዎቻቸውንም ያጠቃልላል።

እዚህ መጠቀስ ያለበት ሴት በተፈጥሮዋ ከወንድ ይበልጥ ስሜታዊ፣ተለዋዋጭና ችኩል መሆኗ ሳይንሳዊ እውነታ መሆኑ ነው። ወንድ ግን የዚህን ጉዳይ የመጨረሻ ውጤት በጥንቃቄ የመገመትና የመገንዘብ ብልጫ ያለው ከመሆኑም በላይ፣ስሜቱን የመቆጣጠር፣ሲናደድም ሆነ ሲረበሽ ራሱን ያዝ የማድረግ የተሻለ አቅም አለው።

በተጨማሪም የፍች ሁኔታ የገንዘብ ወጭና ኪሳራ የሚያስከትለው በወንዱ ላይ ብቻ ሲሆን፣ፍችን ተከትሎ መፈጸም የሚኖርበት ክፍያ ይጠብቀዋል። በፍች ውሳኔው ምክንያት የሚመጣው ይህ የክፍያ ግዴታ፣ባሎች ለፍች እንዳይቻኮሉ፣በደንብ ካልታሰበበት ወሳኔ ላይ እንዳይደርሱና እንዲታገሱ የሚደርጋቸው ተጨማሪ ምክንያት መሆኑም ጥርጥር የለውም።

ከዚህም ጋር፣እስላም ፍች የመፈጸምን መብት ለወንዱ ብቻ የሰጠ ቢሆንም፣በቂና ተገቢ የሆነ ምክንያት ካላት ፍች የምታገኝበትን መንገድ ለሴቷ ከማመቻቸት ችላ አላለም። ይህም ‹‹ኹልዕ›› በመባል የሚታወቀውና የሁሉንም ወገን መብት በሚጠብቁ ገደቦችና ሕግጋት መሰረት የሚፈጸም ራስን የማስፈታት ሂደት ነው።

ወዳጄ፣በናንተ አገር ስላለው የሴቶች ሁኔታ እንድንነጋገር ትፈቅዳለህ?!

ማይክል፦ ምሳ ብንበላ አይሻልም?