የሰው ነፍስያ በሁለት አመለካከቶች መካከል

የሰው ነፍስያ በሁለት አመለካከቶች መካከል

ራሽድና ማይክል ያረፉበት የወጣቶች እንግዳ ማረፊያ ማእከል በጣም ተመችቷቸዋል። ከዋጋው ርካሽነት በተጨማሪ የስፖርት ማዘውተሪያ ቦታዎችንና ጂሞችን፣የንባብና የመዝናኛ ክፍሎችን፣የመገኛኛና የኮሙኒኬሽን አገልግሎቶችን፣ . . ያካተተ ማእከል ነው። ከሁሉም በላይ ደግሞ ቁጥራቸው የበዛ የዕድሜና የትምህርት እኩዮቻቸው የሆኑ እንግዶች ያረፉበት መሆኑ በጣም አስደስቷቸዋል።

ማይክልና ራሽድ ወደ አንደኛው ማህበራዊ ሳሎን ገብተው የሚጠጡትን ነገር እንደምርጫቸው አዘው ተቀመጡ። ማይክል እንዲህ ሲል ቀጠለ፦

ባለፈው ውይይታችን የሃይማኖታችሁ ሊቅ ተናገረው ባልከው ነጥብ ላይ ነበር የቆምነው። የተናገረው ነገር ከተባለው ጋር የሚስማማ ነው ወይስ የሚቃረን ነው?

ራሽድ፦ የመስማማት ወይም የመቃረን ጉዳይ አይደለም። እስላም ራሱን የቻለ የተሟላና ከሌላው የተለየ፣ግልጽ በሆኑ መሰረቶች ላይ የቆመ ሥርዓት ነው። ይሁን እንጂ እነዚህን በማብራራት ላራዝምብህ አልፈልግም . . ያልኩህ ሊቅ እብን አልቀይም ይባላሉ። በመጽሐፎቻቸው ውስጥ በልብ (ልቦና) በነፍስያና በአእምሮ መካከል ስላለው ግንኙነት ተናግረዋል። መጀመሪያ ልጠቁምህ የምፈልገው ግን፣የተናገሩት ነገር እስላማዊ ስልጣኔ ከቆመባቸው መሰረቶች ጋር በሚጣጣሙ የእሴቶችና የጽንሰ ሀሳቦች ሥርዓት ማእቀፍ ውስጥ የሚወድቅ መሆኑን ነው። በመሆኑም ባለፈው ውይይት የጀመርኩትንና በዚህ እስላማዊ ሥርዓትና የዛሬውን የምዕራቡን ዓለም ህብረተሰብ ተጨባጭ ሁኔታና ስነምግባሮቹን በቀረጸው በፍሮይድ ንድፈ ሀሳብ መዘዞች መካከል ያለውን ልዩነት ማብራራት ልቀጥል።

ማይክል፦ ጊዜ ለመቆጠብ ያህል፣የንግግርህን የመጨረሻ ክፍል በአጭሩ እንዳብራራው ፍቀድልኝ፤ከምታምንበት የሚለይ ከሆነ ግን ታርመኛለህ።

ራሽድ፦ ቀጥል።

ማይክል፦ ከፍሮይድ ንድፈ ሀሳብ ብዙ የሰብእና ሞዴሎች የሚወጡ ሲሆን በሚከተሉት ይወከላሉ፦

ተራ ስሜቶችና ፍለጎቶች ወይም እንስሳዊ ፍላጎቶች ማለትም ‹‹እርሱ››ን፣ሙሉ በሙሉ በ‹‹እኔ›› በሰብእና ላይ ድል ከተቀዳጀ፣የሌሎችን መብት ከሚጋፋ፣የራሱን ግላዊ ስሜትና ፍላጎት ለማርካትና ለእንስሳዊ ጥሪዎቹ ብቻ መልስ ለማግኘት ከሚጥር፣እግረመንገዱን መልካም እሴቶችን፣ልማዶችንና ክቡር ተምሳሌቶችን ‹‹ከፍተኛው እኔ››ን ከሚደፈጥጥ ራስ ወዳድ ወይም ወንጀለኛ ሰብእና እናገኛለን።

እሴቶች መልካም ልማዶችና የተቀደሱ ተምሳሌቶች ማለትም ‹‹ከፍተኛው እኔ›› በ‹‹እኔ›› ላይ ድል ከተቀዳጀ ግን፣እግረ መንገዱን ሥጋዊ ስሜቶችንና መሰረታዊ ፍላጎቶችን የሚደፈጥጥ፣ከተጨባጭነት የራቀና ተምኔታዊ የሆነ ዓይነተኛ መነኩሴያዊ ሰብእና እናገኛለን።

አንድ ሰብእና ጤናማና የተረጋጋ የሚሆነው በአንድ በኩል ስሜታዊ ዝንባሌዎችንና ፍላጎቶችን፣በሌላ በኩል ደግሞ ወጫዊ እሴቶችንና ገደቦችን ማጣጣም ማመዛዘንና ማቻቻል ሲችል ነው። ይህ የሚፈጸመው በአንዳንዳንድ ሁኔታዎች ላይ ከነዚህ ስሜቶችና ፍላጎቶች ከፊሎቹን በማፈን፣ወይም በሌሎች ሁኔታዎች ደግሞ እንደ ሁኔታው ገደቦችንና እሴቶችን በመጣስ ነው።

ራሽድ፦ በጣም ጥሩ።እናም በዚህ ንድፈ ሀሳብና አንተ ማህበራዊ ገጽታውን በገለጽከው ምዕራባዊ ስልጣኔና በእስላማዊው ሥርዓት መካከል ያለውን ልዩነት ማወቅ ችለናል ማለት ነው . . ልዩነቱ በ‹‹እርሱ›› እና በ‹‹ከፍተኛው እኔ›› መካከል ያለው ጥልና ቅራኔ፣አንዳቸው በሌላው ሳይረታ በማብቃት የሚገለጽ ነው። ይህም ረቀቅ ባለ ማጣጣምና ማቻቻል፣በሁሉም የሕይወት መስኮች ሁሉንም የሰው ልጅ ገጽታዎች ሁለገብና ተደጋጋፊ በማድረግ ሲሆን፣የዚህ ምስጢር ደግሞ የመብቶች ተጋፊነት ብዬ በምጠራው ላይ ገደብ መጣል ነው።

ማይክል፦ የመብቶች ተጋፊነት የምትለውን ነገር ለመጀመሪያ ጊዜ መስማቴ ነው።መብት እንዴት ግፈኛ እንደሚሆን ታስረዳኛለህ። በቅድሚያ ግን አነጋገርህ የስነልቦና ሥርዓትን የሚመሰርቱ አሃዶች የመኖራቸውን እሳቤ አምኖ ይቀበላል ማለት ነው።

ራሽድ፦ የስነልቦና ሥርዓትን የሚመሰርቱ አሃዶች የመኖራቸው እሳቤ ቀደም ሲል ከሙስሊም ሊቃውንት አንደኛቸው ብቻ ሳይሆን አንዳንዶቻቸው ከብዙ መቶ ዓመታት በፊት ተመሳሳይ የሆነ እሳቤ ማንሳታቸውን የጠቀስኩልህ ነው። እብን አልቀይም የሚባሉ ሊቅ ከመጽሐፎቻቸው በአንደኛው ውስጥ የሚሉትን ተመልከት (ራሽድ መጽሐፍ አውጥቶ እያነበበ)፦ ‹‹ነገሮች አራት ሲሆኑ እነሱም፦ የሚጠላ ሆኖ ወደሚጠላ ነገር የሚያደርስ፣የሚጠላ ሆኖ ወደሚወደድ ነገር የሚያደርስ፣የሚወደድ ሆኖ ወደሚወደድ ነገር የሚያደርስና የሚወደድ ሆኖ ወደሚጠላ ነገር የሚያደርስ ናቸው። የሚወደድ ሆኖ ወደሚወደድ የሚያደርሰው አንድ ነገር እንዲደረግ የሚገፋፋ ነገር በሁለት መንገድ የተካተተበት ሲሆን፣የሚጠላ ሆኖ ወደሚጠላ ነገር የሚያደርሰው ደግሞ አንድ ነገር እንዳይደረግ የሚገፋፋ ነገር በሁለት መንገድ የተካተተበት ነው።

በሁለቱ ቀሪ ክፍሎች ደግሞ ሁለቱ [የመሥራትና የመተው] በርስ ይሳሳባሉ። ሁለቱ የመሞከሪያና የመፈተኛ መስክ ናቸው። ነፍሲያ በጉርብትና ከሁለቱ ይበልጥ የሚቀርባትን የምትመርጥ ስትሆን እሱም ጊዜያዊ የሆነው ነው። አእምሮና ኢማን ግን ከሁለቱ ይበልጥ ጠቃሚና ይበልጥ ዘውታሪ የሆነውን ይመርጣሉ። ልብ ደግሞ በሁለቱ ግፊቶች መካከል ሲሆን አንድ ጊዜ ወደ አንዱ ሌላ ጊዜ ወደ ሌላኛው ያጋድላል።›› ሙስሊም ሊቃውንት በቁርኣንና በነብዩ ﷺ ሐዲሦች ላይ በመንተራስ አእምሮ ‹‹ከፍተኛው እኔ›› ሲዘናጋ ስሜታዊ ፍላጎቶች ‹‹እርሱ›› ያለ ተቆጭና ያለ ተቆጣጣሪ እንደሚነቃቁና እንደሚነሳሱ ይገልጻሉ።

እናም በ‹‹ነፍሲያ›› እና በፍሮይድ ‹‹እርሱ›› መካከል፣በ‹‹አእምሮና ኢማን›› እና በ‹‹ከፍተኛው እኔ›› መካከል፣በ‹‹ልብ›› እና በ‹‹እኔ›› መካከል በሥራቸው ተመሳስሎ መኖሩን አላስተዋልክም?

ማይክል፦ በእርግጥም በሁለቱ መካከል ብዙ ተመሳስሎ መኖሩን አስተውያለሁ።

ራሽድ፦ በዚህና በፍሮይድ ሀሳብ መካከል መሠረታዊና ወሳኝ የሆነ፣ይህን ሥርዓት ከዚያኛው የተለየ የሚያደርግ መለያ አለ። መለያ ነጥቡ እብን አልቀይም ‹‹ሁለቱ የመሞከሪያና የመፈተኛ መስክ ናቸው›› በማለት በገለጹት አባባል የሚወከል ነው። የሰብእና ‹‹እኔ›› (እብን አልቀይም ዘንድ ‹‹ነፍሲያ››)ጤናማነት የ‹‹እርሱ››/‹‹ነፍሲያ›› ፍላጎቶችንና ስሜታዊ ዝንባሌዎችን በማርካት የሚገለጽ ነው።እስላማዊው ሥርዓት እነዚህን ከነፍሲያና ከግፊቶቿ የሚመጡ ፍላጎቶችንና የስሜታዊ ዝንባሌ ጥሪዎችን በተጨባጭ አላህ (ሱወ) ባሮቹን የሚፈትንባቸው መሞከሪያዎች አድርጎ ይወስዳል። ስለዚህም ‹‹እርሱ››ን/‹ነፍሲያ››ን ለማስደሰት ሲባል ለፍላጎቶቿ፣ለጥሪዋና ለግፊቶቿ ያልተገደበ ምላሽ መስጠት ትክክለኛ አይሆንም። በተመሳሳይ መልኩም ለ‹‹ከፍተኛው እኔ››/ለ‹‹አእምሮና ኢማን›› ተብሎ በምንኩስና ሥርዓት ውስጥ እንደሚስተዋለው ፍላጎቶቿን ሙሉ በሙሉ ማመቅና መጨፍለቅም ተፈላጊ አይደለም።

ይህ ከእስላም ውጭ በሌላ ማንኛውም ሥርዓት ውስጥ የማይገኝ ሚዛናዊነትና መካከለኛነት (ወሰጥያ) ነው። ፍላጎቶችንና ስሜታዊ ዝንባሌዎችን መቆጣጠር፣ከ‹‹አእምሮና ኢማን›› ጋር ሳይጋጩና የመብቶች ግፈኝነት ሳይኖር ለሰውን ልጅ ጤናማ ተፈጥሯዊ ፍላጎቶች ምላሽ መስጠት ነው።

ማይክል፦ የመብቶች ግፈኝነት ስትል ምን ማለትህ ነው?

ራሽድ፦ ማለት የተፈለገው፣ቁሳዊ ፍላጎቶችና ስሜታዊ ዝንባሌዎች መብት እንዳላቸው ሁሉ፣ታላላቅ እሴቶችና ምስጉን ስነምግባራትም መብት አላቸው ማለት ነው። እስላም ዘንድ እሴቶች፣ሞራላዊ ስነምግባሮች፣ፍላጎቶችና ስሜታዎ ዝንባሌዎች፣ይህ የላቀ እሴት ነው፣ያኛው ድንበር የጣሰ ፍላጎት ነው በሚል አንዱ የሌላውን መብት መጋፋት የተከለከለ ነው . . ይህን ነጥብ የበለጠ ለማብራራ ከእስላም ነብይ ﷺየተላለፈ አንድ ሐዲሥ እጠቅስልሃለሁ። የነብዩ ﷺ አምልኮተ አላህ (ዕባዳ) እንዴት እንደሆነ ለመጠየቅ ሦስት የሶሓባ ስብስቦች ወደ ነብዩ ﷺ ቤቶች መጡ።የተነገራቸው ዕባዳቸው ከጠበቁት ያነሰ ስለመሰላቸው ነብዩﷺ ከኛ የተለየ ብልጫስላላቸው ይሆናል፤እኛ ግን ኃፂጢአታችን የበዛ በመሆኑ ዕባዳ ማብዛት አለብን ብለው ደመደሙና ከተፈጥሮ ፍላጎቶቻቸው ጋር እስከመቆራረጥ ድረስ በዕባዳዎች ላይ ለመትጋት ወሰኑ። አንደኛቸው እኔ ሁሌ እጾማለሁ (ከምግብ ከመጠጥና ከወሲብ ከጎህ መቅደድ እስከ ጸሐይ መጥለቅ እታቀባለሁ) አለ። ሌላው እኔ ደግሞ ከሴት እርቃለሁ ዕድሜን በሙሉ አላገባም አለ። የአላህ መልክተኛ ﷺ መጡና፦ ‹‹እንዲህና እንደዚያ ያላችሁት እናንተ ናችሁ? በአላህ እምላለሁ እኔ ከሁላችሁም በላይ አላህን ፈሪና ተገዥው ነኝ፤ግና እጾማለሁ፣እፈስካለሁም። እሰግዳለሁ፣እተኛለሁም። ሴቶችንም አገባለሁ። ከኔ ሱንና (ፈለግ) ያዘነበለ ሰው ከኔ ጭፍራ አይደለም።›› አሏቸው። . . እነዚህ ሰዎች በመሰረቱ ትሩፋት፣እውነታና ተፈላጊ በሆነው ሃይማኖት ‹‹ከፍተኛው እኔ›› ትእዛዝ ላይ ተጨማሪ ነገር መደንገግ ነበር ያሰቡት። ይሁን እንጂ ያሰቡት ነገር የሌላውን መብት የ‹ነፍሲያ››/‹‹እርሱ››ን መብቶች ጭምር በመጋፋትና በመደፍጠጥ ብቻ የሚሆን ነበር። ይህን መርሕ ይበልጥ ጉልህ በሚያደርግ ሌላ ሐዲሥ ነብዩ ﷺ፦ ‹‹ . . ለጌታህ መፈጸም ያለብህ መብት ግዴታ አለብህ። ለገዛ ራስሀም መፈጸም ያለብህ ግዴታ አለብህ። ለቤተሰብህ (ሚስትህ) መፈጸም ያለብህ ግዴታ አለብህ። ስለዚህ ለያንዳንዱ ባለመብት ያለብህን ግዴታ ተወጣ . . ›› ብለዋል። ቅዱስ ቁርኣን ውስጥ በርካታ አንቀጾች ይህንኑ ያመለክታሉ። አላህ ﷻ እንዲህ ብሏል፦

{አላህም በሰጠህ ሀብት የመጨረሻይቱን አገር ፈልግ፤ከቅርቢቱም ዓለም ፋንታህን አትርሳ፤አላህም ወደ አንተ መልካምን እንደ አደረገ አንተም መልካምን አድርግ፤በምድርም ውስጥ ማጥፋትን አትፈልግ፤አላህ አጥፊዎችን አይወድምና፣(አሉት)።}[አልቀሶስ፡77]

በተጨማሪምአላህ ﷻእንዲህ ብሏል፦

{እጅህንም ወደ አንገትህ የታሠረች አታድርግ፣መዘርጋትንም ሁሉ አትዘርጋት፤የተወቀስክ፣የተቆጨህ፣ትሆናለህና።}[አልእስራእ፡29 ]. . ወዳጄ እስላም ብሕውትናን እና ምናኔን ሐራም አድርጎ የከለከለ መሆኑን አንተም ሳታውቀው አትቀርም።

እስላም ውስጥ የሰው ልጅ አእምሮውንና ሕሊናውን ያለ ምንም ግጭት ቅራኔም ሆነ መናጋት እያስደሰተ፣ ሃይማኖቱንም እውን ያደርጋል፤ተፈጥሯዊ ፍላጎቶቹንም ያረካል . .

ራሽድና ማይክል በውይይታቸው ተጠምደው እያሉ፣ቅርባቸው ያለውን ጠረጴዛ ይዞ ተቀምጦ የነበረ አንድ ወጣት ቀረብ ብሎ ከፊታቸው በመቆም እንዲህ አላቸው፦

ከናንተ ጋር እቀመጥ ዘንድ ትፈቅዱልኛላችሁ?

ማይክልና ራሽድ፦ በጣም ደስ እያለን . . እባክህን ተቀመጥ።

ወጣቱ፦ እውነቱን ለመናገር ውይይታችሁ በጣም ስቦኛል። ብንተዋወቅና በውይይቱ ላይ ብታሳትፉኝ ምስጋናዬ የላቀ ነው።

ማይክል፦ በእኔ በኩል ችግር የለብኝም።

ራሽድ፦ እንኳን ደህና መጣህ። ከወዳጄ ከማይክል ጋር ላስተዋውቅህ፣እንግሊዛዊ ሲሆን በመምህርነት ይሠራል። እኔ ራሽድ እባላለሁ፣ግብጻዊ ጸሐፊና ጋዜጠኛ ነኝ።

ወጣቱ፦ እንኳን ደህና መጣችሁ፣ከናንተ ጋር በመተዋወቄ ደስተኛ ነኝ። ራሴን ላስተዋውቅና ራጂቭ እባላለሁ፣ከሕንድ ነው የመጣሁት። ጀርመን ውስጥ ምህንድስና በማጥናት ላይ ነኝ። እዚህ ፓሪስ የተገኘሁት ወዳጆቼን ለመጎብኘት ነው።

ማይክልና ራሽድ፦ ራጂቭ ከአንተ ጋር መተዋወቃችን መልካም አጋጣሚ ነው።

ራሽድ፦ እንግዲህ በዚህ መልኩ ነው ምዕራባውያን የስነልቦና ጠበብት ነፍሲያን በጉድለቶች፣በእንከኖች፣በበሽታዎች . . ውስጥ እንጂ የማይመለከቱ መሆናቸውን የምንረዳው። እስላም ውስጥ ግን ነፍሲያ በውስጧ በጎና ክፉንም ያዘለች ስትሆን፣ከሰው ልጅ ተፈጥሮ ጋር ምንም ዓይነት መላተምና ግጭት ሳይኖርየነፍሲያን ሁኔታ በመሠረታዊ መልኩ መለወጥና ከእንስሳዊነት ጨለማ አውጥቶ ወደ መልካም ስነምግባራት ምሉእነት ቁንጮ ከፍ ማድረግ ይቻላል።

ራጂቭ፦ ከውይይታችሁ ማጠቃለል የምችለውየታፈኑ ፍላጎቶች ሁሌም ቀጥተኛ ወይም ቀጥተኛ ባልሆነ መንገድ እርካታን ለማግኘት ይፈልጋሉ። ይህ ደግሞ በፍሮይድ አመለካከት በመርህ፣በተምሳሌታዊ አብነትና በእሴቶች ላይ የሚታነጽ ሥልጣኔን የአፋና እና የእመቃ ሥልጣኔ አድርጎ መውሰድን ያስከትላል ማለት ነው።

የአውሮፓ ሥልጣኔ ስነምግባራዊ እሴቶችን የሚያመነጨው የዩኒቨርስ ጽንሰ ሀሳብን ገዥ በማድረግ አማካይነት ሲሆን፣ለሰው ልጅ ቀዳሚነትን የሚሰጠው የዚህ ዩኒቨርስ ጌታ አድርጎት ከመውሰድ አኳያ ነው። ይህ ሁሉ የመጣው የአምላክ መኖርን እሳቤ ከሥልጣኔው ውስጥ በማስወጣት ነው። በእስላም ሥልጣኔ ውስጥ ግን የአላህ መኖር ጽንሰ ሀሳብ ገዥው እሳቤ ነው፤ይሁን እንጂ እሳቤው የሰውን ልጅ ሕልውና የሚደመስስ አይደለም።

ራሽድ፦ በሰብአዊ ሕብረተሰቦች ውስጥ ስነምግባራዊ እሴቶች ምንጫቸው የግድ ወሕይ (መለኮታዊ መመሪያ) እንጂ አእምሮ መሆን የሌለበት ስለመሆኑ ይህ ቁርጥ ያለ ማስረጃ ነው። አእምሮ ብቻውን ከሆነ በእርግጠኝነት መዛነፍ የሚጠናወተው ሲሆን፣በወሕይ ማእቀፍ ውስጥ ከሆነ ግን የሚያመነጨው ተፈላጊውን ስነምግባር ይሆናል።

ማይክል፦ ራጂቭ ያንተ መገኘት ውይይታችን የሚያዳብርና የሚያጎለብት ነውና . . ነገ በዚሁ ቦታና ሰዓት አዲስ ውይይት ለመጀመር ቀጠሮ ብንይዝ ይመቻችኋል?

ራጂቭ፦ አዎ፣እኔ ይመቸኛል።

ራሽድ፦ በነገው ቀጠሮ ላይ ለአዲሱ ወዳጃችን ለራጂቭ መስተንግዶ ሁለታችሁንም የምሳ ግብዣ ጥሪዬን እንድትቀበሉ አክብሮት እጠይቃለሁ።

ማይክልና ራጂቭ፦ በጣም ደስ ይለናል።