የመንፈስ ሹክታ

የመንፈስ ሹክታ

የመንፈስ ሹክታ (1)

ጆርጅ እየተጫጫነው ከእንቅልፉ ተነሳ። የመሰላቸት ስሜት የሚሰማው በመሆኑ ቀኑን ሙሉ ከማንም ጋር ባይገናኝና ከክፍሉ ሳይወጣ ቢውል ምኞቱ ነው። ዳሩ ግን ከካኽ ጋር ፍጥጫ ውስጥ በመሆኑ ሊያሸንፈውና አስቸጋሪ ተልእኮውን በስኬት ሊያጠናቀቅ ቆርጧልና
ግላዊ ጉዳዮቹንና የሚጠናወቱትን የመሰላቸት፣የማመንታትና የመዛል ስሜቶች ማስወገድ የግድ ይላል፤ሥራውንና መጪ ዕድሉን እንዲያጨናግፉ መፍቀድ የለበትም።

ከጀማል ጋር ቀጠሮው ዛሬ አራት ሰዓት ላይ በመሆኑ ለቁርስና ኢሜይሉን ለማየት በቂ ጊዜ አለው

። ከክፍሉ ለመውጣት ስላልፈለገ ደውሎ ቁርስ ክፍሉ ድረስ እንዲመጣለት ጠየቀ፤ቁርሱ እስኪደርስ ቶሎ ተጣጥቦ

ለመውጣት

ባኞ ገባ . .
ከተወሰኑ ደቂቃዎች በኋላ አስተናጋጁ ቁርሱን አምጥቶ ጠረጴዛው ላይ ደርድሮለት ወጣ . . ጆርጅ ቁርሱን እየበላ ኢሜይሉን ከፍቶ ማየት ሲጀምር ከካትሪና የተላከለትን ደብዳቤ አገኘ . .

‹‹ፍቅሬ ጆርጅ

ከሄድክ ገና አጭር ጊዜ ቢሆንም ለምን በጣም እንደናፈኩህ ብቻ ሳይሆን ከአጠገቤ እንድትሆን ለምን በጣም እንዳስፈለገኝ አላውቅም። እስክትመጣ አንድ ወር መጠበቅ አይቻለኝም። ብዙ ግራ የሚያጋቡ ችግሮች ስላሉብኝ በእጅጉ ታስፈልገኛለህ። ግራ የመጋባቴን ደረጃ ለመጥቀስ ያህል እኔ ካቶሊካዊቷ ሃይማኖተኛ ቁርኣን የሚሉትን የሙስሊሞች ቅዱስ መጽሐፍ ትርጉም ሰምቼ አልቅሻለሁ እለሃለሁ። እናም በጣም በተረበሸ ሁኔታ ውስጥ እየኖርኩ ነውና ታስፈልገኛለህ።

አፍቃሪህ ካትሪና››

መልስ ጻፈላት . .

‹‹ፍቅሬ ካትሪና

በቅርቡ እመለሳለሁ የሚል እምነት አለኝ። ትናንትና የነበረኝ ቀጠሮ በጣም መጥፎና ስለ ሙስሊሞችም አፍራሽ ምስል የሚያንጸባርቅ ነበር። ችግሩ ከራሳቸው ከሙስሊሞቹ ወይም ከሃይማኖታቸው ይሁን አይሆን ግን አላውቅም፤ትናንት ከርሱ ጋር ቀጠሮ የነበረኝን ሙስጠፋ ግን እጠለዋለሁ። በቀናት ውስጥ ለመመለስ እሞክራለሁ። ከካኽ ጋር ባለኝ ፍጥጫ ተሸናፊ መሆን አልፈልግምና ጸልይልኝ።

አፍቃሪሽ ጆርጅ››

ከጃኖልካም ደብዳቤ ደረሰው . .

‹‹ወዳጄ ጆርጅ

ደብዳቤህ ደርሶኛል፤የሙስሊሞችን ስርቆት በተመለከተ ሀሳቤ ትክክለኛ በመሆኑ ተደስቻለሁ። ከእንግዲህ ከችኮላ መጠንቀቅ አለብህ። የሴቶችን ሁኔታ በሚመለከት ምንም ብዥታ የለብኝም፤ዋነኛው ብዥታዬ እስላም ውስጥ ነጻነት ያለውን ቦታ በተመለከተ ብቻ ነው፤ሀሳብ ወይም አመለካከት ካለህ አካፍለኝ።

ጃኖልካ››

ምላሽ ጻፈለት . .

‹‹ወዳጄ ጃኖልካ

በአጭር ጊዜ ውስጥ ሀሳቤን በመቀየሬ ትገረም ይሆናል!! ልክ ነህ እስላም ውስጥ ሴቶችን የሚጨቁን ምንም ነገር የለም።ሥርዓቱ በአውሮፓዊ ሕብረተሰባችን ውስጥ ያልለመድነውና ሙሉ በሙሉ የተለየ ቢሆንም፣እስላም ከሴት ልጅ ተፈጥሮና ስነ ሕወታዊ አፈጣጠሯ ጋር የሚጣጣሙ ድንጋጌዎችን ይዞላት ነው የመጣው። ይህ በሴቶች ጉዳይ ላይ ሰፊ ጥናትና ብዙ ውይይት ካካሄድኩ በኋላ የደረስኩበት ማጠቃለያ ሲሆን በነጻነት ጉዳይ ላይ ግን ብዙ ንባብም ሆነ ውይይት ገና አላካሄድኩም። የደረስክበት ነገር ካለህ ላክልኝና ለሁሉም ስብስብ መልሼ እልካለሁ፣በተጨማሪም በርእሱ ላይ ንባብና ውይይት አካሄዳለሁ።

ጆርጅ››

የኢሜይል መልእክቶቹን በመከታተል ላይ እያለ የክፍሉ ስልክ ጮኸ . . አንድ እንግዳ እየጠበቀው መሆኑን ለመንገር የደወለው የእንግዳ መቀበያ ሰራተኛው ነበር . . ሰዓቱን ተመለከተ፤ገና ሦስት ተኩል በመሆኑ ገረመው . . ጀማል ከቀጠሮው ግማሽ ሰዓት አስቀድሞ እንዴት መጣ? . .

- ይቅርታ ማነው የሚጠብቀኝ?

- አንዲት ወጣት ልጅ ናት።

- ማን ናት?

- እርሱ ያውቀኛል ብላኛለች፣ስሟን ግን አልነገረችኝም።

- መልካም እንግዳውስ መጣሁ።

ጆርጅ ወደ እንግዳ መቀበያው አመራ፣የምትጠብቀው ዲያና ናት። ቀለል ያለ ተራ ልብስ ለብሳ ጸጉሯን ወደ ኋላ አስራለች።ፊቷ ላይ ምንም ዓይነት ሜካፕ አይስተዋልም። በትናንቱና በዛሬ ሁኔታዋ መካከል ያለው ልዩነት በጣም ሰፊ ቢሆንም ከነተፈጥሮው ያለው የዛሬ ፊቷ ከትናንቱ ይበልጥ ውበትና ልስላሴን የተላበሰ
ይመስላል። እይታዋ ብስለትና ጠንቃቃነቷን የሚያሳብቅ ሲሆን ትላልቅ ዓይኖቿ ጎላ ጎላ ብለዋል . .
ጆርጅ በሰላምታ ከተቀበላት በኋላ እንድትቀመጥ ጋበዛት . .

- ምን ትጠጭያለሽ?

- ምንም አልፈልግም፤ጊዜህን መውሰድ አልሻም በአንድ ጉዳይ ላይ ላነጋግርህ ፈልጌ ነው።

ሁለት ጭማቂ እንዲያመጣላቸው ጆርጅ አስተናጋጁን አዘዘ . . ከዚያም ወደ ዲያና ፊቱን አዙሮ ለምን አንደመጣች ጠየቃት . . ለመደበቅ ብትሞክርም ዓይኖቿ እንባ ማቅረራቸውን አስተውሏል . .

- እሺ . .

- ትናንት ከውስጥ ከሚያወድሟትና ከሚገድሏት ጥያቄዎች ለመሸሽ ስትፈልግ የነበረችዋ ልጅ ነኝ! እኔ ትናንት ያዋረድካት ልጅ ነኝ! እኔ ኦርቶዶክሷ ፈርጣጭ ነኝ! አንተ እንደምትለውም እኔ ዝምተኛዋ ጭምቷ ምሁር ነኝ፤እኔ የታከተኝ ፍጡር ነኝ! . .

- በሚገባ አስታውስሻለሁ፣ግን ከኔ የሚፈለገው ምንድነው?

- ቆንጆ አይደለሁም ወይ?!

- ቆንጆ ነሽ በጣም፣ያውም ልብ የሚያዋልል ምስራቃዊ ውበት የታደልሽ! ይሁንና ቆንጆ ነሽ እንድልሽ ነው የመጣሽው?!

- ታድያ ትናንት ለምን አዋረድከኝ?

- ስጠይቅሽና ሳዋይሽ ነበርኩ እንጂ እኔ አላዋረድኩሽም።

- ጥያቄዎቹ እንደኔው እንዳታከቱህ ነበር የተናገርከው! ሽሽት የጥያቄዎቹን ጉዳይ እንደማይፈታ ነው የጠቀስከው። እናም የነዚህን አድካሚ ጥያቄዎች መልስ ልትነግረኝ ትችላለህ?

- ለዚህ ነው የመጣሽው?

- አዎ!

- መልስ አላገኘሁም፣እንዳውም በነዚህ ጥያቄዎች ምክንያት ራሴን ለማጥፋት ተቃርቤ ነበር ብልሽስ?!

- ያልከው ነገር እውነት ከሆነ ይህ ብስለትህንና ብልህንነትህን የሚያመለክት ማስረጃ ነው።

- ምላሽ አለማግኘቴ የብልህነቴ ማስረጃ ነው?!

- አለመሸሽህና መጋፈጥህ የብልህነት ማስረጃ ነው ማለቴ ነው።

- ታድያ አንቺ ለምንድነው የምትሸሽው?

- ሰዎች ነንና በድክመት ሁኔታዎች ውስጥ እናልፋለን።

- ለመሆኑ ለነዚህ ጥያቄዎች እውነተኛ መልሶች የሉምን?

- ያለ ጥርጥር አሉ።

- መልሶቹን ለማግኘትና ለማወቅ ያለኝን ጽኑ ፍላጎት ይህ ነው ብዬ ልነግርሽ አልችልም።

- እኔ ግን አውቃለሁ ግን ፈሪና ደካማ ነኝ።

- ታውቂያለሽ?!

- አዎ አውቃቸዋለሁ፤ይሁን እንጂ የሰው ልጅ የገዛ ራሱን ለመርታት በቂ ድፍረትና ጀግንነት ካልኖረው በስተቀር፣ህልውናውን ማረጋገጥ፣በሕይወቱ መታደልን ለማግኘትም ሆነ ራሱን ለመለወጥ አይችልም።

- የምትናገሪው ነገር አልገባኝም!

- አንዳንዴ ደሃ ደሃ ሆኖ የሚቀረው አንድ ሥራ ብጀምር እከስራለሁ ብሎ ስለሚፈራ ነው፤ላጤም አንዳንዴ እንደዚሁ ማግባትን ስለሚፈራ ላጤ ሆኖ ይቆያል፤ማይምም አንዳንዴ መማርን ስለሚፈራ ማይም ሆኖ ይቀራል።

- ትክክልና ግልጽም ነው፤ስለምን እንደምትናገሪ ግን አልገባኝም!

- ለነዚህ ጥያቄዎች አርኪና አሳማኝ መልስ አውቃለሁ፣ነገር ግን ልገደል ወይም ልታሰር እችላለሁ ብዬ ስለምሰጋ ባለሁበት ስቃይ ውስጥ እኖራለሁ።

- እኔ ግን ፈሪ አልሆንም! . . መልሱን ንገሪኝ፣ምንድነው?

- እስከዚህ ድረስ ጀግናና ደፋር ለመሆንህ እርግጠኛ ነህ?

- ምናልባት፤መልካም ፈቃድሽ ከሆነ ያለ ብዙ መፈላሰፍ ንገሪኝ።

- እኔም እንዳንተው እል ነበር፣በመጨረሻ ግን ፈሪ ሆኜ የምሸሽባቸውን መንገዶች ወደ ማሰላሰሉ ተመለስኩ።

- አንቺ የምትይውን ነገር አሳማኝ ሆኖ ካገኘሁት እስኪ ጀግንነቴን ልፈትሽበት! ለጥያቄዎቼ ምላሽ የማገኘው ከየት ነው?

- እኔ የመጣሁት ለጥያቄዎቼ እንዴት ምላሽ እንደማገኝ ካንተ ለማወቅ እንጂ አንተን ለማሳወቅ አይደለም።

- በተገላቢጦሽ እኔ ተማሪ ሆኛለሁና በይ ንገሪኝ።

- የምነግርህ ነገር ሊያስቆጣህ ይችል ይሆናል፤ዳሩ ግን ከረዥም ጥናትና ፍለጋ በኋላ ከርሱ በስተቀር ሌላ አላገኘሁም። እናም ሙስሊም ከመሆን ምንድነው የከለከለህ?

ጆርጅ ወደ ሰማይ አንጋጠጠ። ተመልሶ ለዲያና በደረቁ ፈገግ አለ። የመታደልን መንገድ ለመፈለግ ከቆረጠበት ጊዜ አንስቶ ያለፈባቸውን ሁኔታዎች ማጠንጠን ጀመረ . . ከሪሙሏህ፣ኣደም፣ሸይኽ ባስም፣ጀማል . . ያለፈበት ረዥም ጉዞ፣ያሳለፈው ብዙ ተሞክሮ፣ንባቡ፣ጥናቱና ውይይቱ . . የዚህ ሁሉ አድካሚ ጉዞ መዳረሻ እስላም ሊሆን? የመታደል መንገድ እስላም ራሱ ሊሆን?!
ደግሞስ የመታደልን መንገድ ካገኘ ያለ ምንም ማመንታት በቀጥታ እይዘዋለሁ፤እከተለዋለሁ ሲል የነበረውስ እርሱ ራሱ አልነበረምን? ኣደም ድፍረትና ሞራላዊ ጀግንነት ያስፈልገሃል ማለቱ ትክክል ይሆን እንዴ? እንዳለው ማሳየት የሚፈልገው ጀግንነትና ቁርጠኝነት ዝም ብሎ የማስመሰል ብቻ ይሆን? . .

- ረበሽኩህ መሰለኝ አዝናለሁ! ከዚህ የተለየ ሌላ ምላሽ አንተ ዘንድ ይኖራል የሚል ተስፋ ሰንቄ ነበር። ዝምታህ እንደኔው የፍርሃትና ድፍረት የማጣት እንደማይሆን ምኞቴ ነው።

- ይቅርታ . . የለም እንዳው ሳስብ ነበር!

- ስለምን ስታስብ ነበር?

- ስለ ጥያቄሽ።

- መልሱን አስቀድሜ አውቃለሁ . . ፈርተሃል።

- ምኑን ነው የምፈራው?

- በዙሪያህ ያሉ ሰዎችን . . የገዛ ራስህን።

- የለም አልፈራሁም . . መጀመሪያ ግን አንቺ ራስሽ እስላምን እስከዚህ ድረስ መፍራትሽ ለምን እንደሆነ ልትነግሪኝ ትችያለሽ?

- እኔ እስላምን አልፈራሁም!

- ታድያ ምንድነው የፈራሽው?

- የፈራሁት ቤተሰቦቼን ነው፤አባቴ ስለሞተ የምኖረው ከእናቴ ጋር በወንድሟ ቤት ነው። እኔ ብሰልም አጎቴ እብድ እንደሚሆን አውቃለሁ፤ሊገድለኝም ይችላል!

- ለምን?

- ቤተሰቦቼ ሙስሊሞች ያታልሉናል የሚል እምነት አላቸው።

- ይህ እንኳ ምናልባት እውነት ሊሆን ይችላል።

- አጎቴ ከክርስቲያኖቹ እንኳ ይልቅ ለሃይማኖታቸው ተገዥ ካልሆኑ ሙስሊሞች ጋር ብዙ ቅርርብ እንደኖረኝ ሁሌ ይጥራል። በሃይማኖት ጉዳዮች ላይ ከብዙ ክርስቲያኖች ጋር ስለምከራከር በሃይኖታችን ላይ ያለን እምነት እንዲሸረሽር ታደርጋለች ብለው ብዙ ጊዜ ይወቅሱኛል። ለሃይማኖታቸው ተገዥ ያልሆኑ ሙስሊሞች ከክርስቲያኖቹም የባሱ በመሆናቸው አጎቴ ከነሱ ጋር እንድቀራረብ ግፊት ያደርግብኛል።

- እንደ ሙስጠፋ ካሉት ጋር ማለትሽ ነው?

- አዎ፣እንዴት እጠላው መሰለህ!

- ግን እርሱ አርአያነት ያለው ሙስሊም አይደለም እንዴ?!

- ሴኩላሪስት በለው ሊብራል፣ግራ ዘመም ነው ሰይጣናዊ . . የፈለከውን ስም ስጠው የብልሹ ጋጠ ወጦች ዓይነተኛ ምሳሌ ነው። ግን እንዳትሰልም የሚያደርግህ ምንድነው? መልስልኝ።

- ይቅርታ በቅድሚያ የጀመርነውን መጨረስ እፈልጋለሁ። ብትሰልሚ አጎትሽ ሊገድልሽ የሚችለው ለምንድነው?

- ክርስትናን ለቆ የመሄዱ ሁኔታ ሁሌ እንዳይደጋገም ለመከልከልና ለመግታት።

- ይህማ ከተራ የሃይማኖት ነጻነትና ከሰብአዊ መብት ጋር የሚጋጭ ነው!

- የምን ነጻነት! እኔ እንዳንተው ክርስቲያን ነኝ። እናም አእምሮህ በማይቀበላቸው የቤተክርስቲያን ሚስጥራት ያለማመን ነጻነት አለህ?! በአንዳንዶቹ ወንጌሎች ውስጥ እንደሰፈረው ኢየሱስ አምላክ አይደለም ብለህ የማመን ነጻነትስ አለህ?!

- አሁን እነዚህን ወደ ጎን ተይአቸው። እኔ አሁን ቀጠሮ አለብኝ፤ወዳጄ እዚያ ጥግ ቁጭ ብሎ እየጠበቀኝ ነው፤ውይታችንን በኋላ ለመቀጠል እፈልጋለሁ! ፈቃደኛ ከሆንሽ ከሙስሊሙ ወዳጄ ጋር ላስተዋውቅሽ።

- እንደኔው ድፍረትና ጀግንነት ስላነሰህ የጠየኩህን ጥያቄ ከመመለስ እየሸሸህ መሰለኝ። ለማንኛውም ውሳኔው የራስህ ነው . . ከወዳጅህ ጋር ለመተዋወቅ ግን ደስተኛ ነኝ።

ጆርጅ ወደ ጀማል ሄዶ በመዘግየቱ ይቅርታ ጠየቀውና ስለ ዲያና ነገረው፤አብረው ወደሷ ተመለሱ . .

- ይህች መስለም የምትፈልገው ዲያና ናት።

- ዲያና እንኳን ደህና መጣሽ፣ጀማል እባላለሁ ከእስክንድሪያ ነኝ፤መስለምሽ ያስደስተናል።

- እኔም ከእስክንድሪያ ነኝ፣ግን ኦርቶዶክስ ነኝ። ለጆርጅ መስለም እፈልጋለሁ አልልኩትም፤ያልኩት ነገር የብዙዎቹ አሳሳቢ ጥያቄዎቻችን ምላሽ እስላም ውስጥ ይገኛል ነው።

- መልካም . . ጭንቀትና ድብርትን የሚወድ ወይም ለጥያቄዎቹ ምላሽ ማግኘት የማይፈልግ ማንም ሰው ስለሌለ፣ይህ ራሱ አንቺ እስላምን ትፈልጊያለሽ ማለት ነው።

- ትክክል ነው . . ለዚህም ነው ለምን አትሰልምም? የሚል ጥያቄ ለጆርጅ ያቀረብኩለት።

- እኔም መልስ አልሰጠኋትም . . የግብጻውያን ጭካኔ ግን በጣም አስበርግጎኛል። ዲያና ብትሰልም እንደምትታሰር ወይም እንደምትገደል ነው የምትናገረው!

ዲያና ብሶት እየተነፈሰች ቀና አለች . .

- አዝናለሁ . . ግብጾችን ብቻ እንዳትወቅስ እጠይቃለሁ! እናንተ አውሮፓውያንና አሜሪካውያን በጭካኔ ረገድ ከኛ በብዙ ደረጃ ትበልጣላችሁ። ኢራቅ ውስጥ በአቡ ጉረይብ የፈጸማችሁትን ረሳህ? ግፍ ጭካኔ ጥቃትና ማንአህሎኛነት በከፋ መልኩ እናንተ ዘንድ የተንሰራፋ ነው፣በተለይም በሴቶች ላይ። በምዕራቡ ዓለም ሴቶች ከወንዶች ይበልጥ በስድሰት እጥፍ ለመመታትና ለጥቃት እንደሚጋለጡ መካድ ትችላለህ? በአሜሪካ 33% የሚሆኑ፣በእንግሊዝ 77% የሚሆኑ ባሎች ያለ ምንም ምክንያት ሚስቶቻቸውን እንደሚመቱ ማስተባበልስ ትችላለህ?

- የተናገርኩት ነገር ያስቆጣሽና የረበሸሽ ይመስላል!

- አይደለም፣ግን ግብጻዊት ነኝና ወቀሳህን ከአገሬ እከላከላለሁ።

- አገርን መውደድ መልካም ነገር ነው . . በጣም ጥሩ ነገር ነው! ይሁን አንጂ መርህን መውደድ ይበልጥ ተገቢ ነው። እኛ ዘንድ በምዕራቡ ዓለም ትምክህትና ጭካኔ መኖራቸውን ብቀበልም እናንተም ዘንድ መኖራቸው ግን አስገርሞኛል። በሃይማኖትና በእምነት ነጻነት ረገድ ግን እኛ የተሻልን ነን። ያለ አንዳች ችግርና ባሰኘሽ ጊዜ ክርስቲያን፣ሙስሊም፣ይሁዲ ወይም ቡድሂስት . . መሆን ትችያለሽ።

ጀማል ስቆ ቀጠለ . .

- እህህ፣ለዚህ ነዋ ሕጃብ ፈረንሳይ ውስጥ የተከለከለው!! አዛንና ሚናሬት መስራት ስዊዘርላንድ ውስጥ የተከለከለው በዚህ ነጻነት ነዋ!! ስለ የትኛው ነጻነት ነው የምታወራው?

- ጀማል ልክ ነህ። ግን እኛ አንድ ሰው መስለም ቢፈልግ አናስረውም ወይም አንገድለውም!

- እኛም ብንሆን መስለም የፈለገ ሰው አንገድልም!

- ጀማል ትክክል ነህ . . ይህ እኛ ዘንድ ያለው የክርስቲያናዊ ጠባብ ወገንተኝነት አካል ነው የሚል እምነት አለኘኝ። ይሁንና እስላምም እንደዚሁ በሰይፍና በጉልበት አይደለም የተስፋፋው?

- እስላምን በኢንዶኔዥያ፣በናይጄሪያ፣በኢትዮጵያ . . እንዲስፋፋ ያደረገ የጦር መሪ ማን ነበር? አብዛኞቹ የእስላም አገሮችና ሙስሊሞች በብዛት የሚኖሩባቸው አገሮች፣እስላምን ያለ ምንም ሰይፍ በደዕዋና በትምህርት ብቻ ነው የተቀበሉት፣ማንም ሰው እስላምን እንዲቀበል አልተገደደም። ይህ ታሪክ ያረጋገጠው እውነታ ነው . . ይቅርታ፣በብዙዎቹ የእስላም አገሮች ውስጥ ክርስቲያኖች ለ1400 ዓመታት ያህል ክርስትናቸውን ይዘው ሲኖሩ እምነታቸውን እንዲለውጡ ማንም አላስገደዳቸውም። ሕንዶች ከአንድ ሺ ዓመታት በላይ በእስላም አስተዳደር ስር ሲኖሩ እስላምን እንዲቀበሉ ተገደው ያውቃሉ? ሙስሊሞች አንደሉስን ወይም የዛሬዋን እስፔይንን ሲገዙ እንዲሰልሙ ክርስቲያኖችን አስገድደው ያውቃሉ? በኋላ ላይ ግን በተቃራኒው ክርስቲያኖቹ ነበሩ ከመገደልና ክርስትናን ከመቀበል አንዱን እንዲመርጡ ሙስሊሞችን ያስገደዱት።

ውይይትና ክርክሩ ሰፍቶ እተንዛዛ መሆኑ የተሰማው ጆርጅ ከቀጠሮው እንዳይስተጓጎል ለመቋጨት ፈለገ . .

- በጣም ዘግይተናል፤እርስ በርሳችሁ እንድትተዋወቁ ፈልጌ ነው . . ዲያና ይህ ቢዝነስ ካርዴ ነው፣የስልክ ቁጥርሽን እፈልጋለሁ።

- ቢዝነስ ካርዴን እንካ፤ጀማል አንተም ያዝ።

- ችግር ከሌለው ምናልባት ዛሬ ወይም ነገ እደውልልሽና ውይይታችን እንቀጥልበታለን።

- ዋናው ነገር አጎቴ እንዳያውቅ ብቻ ነው። ካወቀ ግን እንደ ወፋእ ቆስጠንጢን፣ወይም ክሪስቲን መስሪ፣ወይም እንደ ሚርና ዓድልና እንደ ሌሎቹ መሆኔ ነው . . ልብ በል እስካሁን ጥያቄየን አልመለስክም!

- ዛሬ ወይም ነገ እደውልልሻለሁ፤ጥያቄው አስቸጋሪ ቢሆንም መልስ እሰጣለሁ! በይ አሁን ፍቀጅልን እኛ እንሂድ።

የመንፈስ ሹክታ (2)

ወደ መኪና ከገቡ በኋላ ጆርጅ ወደ ጀማል ዞር ብሎ በአግራሞት ጥያቄ አቀረበለት . .

- ዲያና በመጨረሻ የደረደረቻቸው ስሞች ምንድናቸው?

- ወፋእ ቆስጠንጢን፣ክሪስቲንና ሚርናን . . እና የመሳሰሉትን ማለቷ ነው። ሁሉም የሰለሙ ክርስቲያኖች ሲሆኑ ታግተው ብዙ ሰቆቃ የተፈጸመባቸውና አንዳንዶቹም የተገደሉ ናቸው! የነርሱ እጣ ፈንታ እንዳይደርሳት ስጋቷን እየገለጸች ነው።

- ሽብርና ጭካኔ ነው። ለማንኛውም የካይሮ ቆይታዬን ነገ አበቃለሁ፤ለተወሰኑ ቀናት ወደ እንግሊዝ ሄጄ ወደ ካይሮ እመለሳለሁ። ባለቤቴ የኔን በአጠገቧ መገኘት በሚያስፈልጋት ሁኔታ ውስጥ ትገኛለች።

- መልካም፣ዛሬ ከመጨረሻው ኩባንያ ጋር ቀጠሮ አለህ፤ከዚያ በኋላ የምትፈልጋቸውን ነገሮች ጠቅለል ባለ መልኩም ቢሆን መልክ መልክ አስይዛቸው።

- ልክ ነህ ይህንኑ ነው የማደርገው። ከሄድኩ በኋላ ሥራው ቀጣይነት እንዲኖረው የሚያደርግና ለክትትል የሚያመች የሥራ ማእቀፍ መፍጠርም ያስፈልገኛል።

- ከመጨረሻው ኩባንያ ጋር ከምታደርገው ግንኙነት በኋላ አንደኛቸውን ለዚህ ኃላፊነት ብቁ ሆኖ ልታገኝ ትችላለህ . . ደርሰናል፣መቼ እንድመጣልህ ነው የምትፈልገው?

- አብረን እንግባና ከዚያ በኋላ እንወስናለን።

ወደ ኩባንያው ሕንጻ ደርሰው ከሥራ አስኪያጁ ጋር ለመገናነት ጸሀፊዋን ጠየቁ፤ባለ ቀጠሮዎቹ መድረሳቸውን ደውላ ነገረችው . .

- ዶክተር ኻሊድ እየጠበቃችሁ ነው ግቡ።

እንኳን ደህና መጣችሁ ብሎ ከተቀበላቸው በኋላ ወደ ስብሰባ ክፍሉ አስገባቸው . .

- በተጻጻፍነው መሰረት ዛሬ ማነጋገር የሚቻል ባለሞዎች ይኖራሉ ብዬ እጠብቃለሁ።

- አዎ ለዛሬ አራት ሰዎች አሉ። የቴክኒክ ሞያተኞችንና የዕውቀትና ቴክኖሎጂ አመራር ባለሞያዎችን በሁለት መደብ ስለ ከፈልኳቸው፣ሌሎቹን ከፈለክ ነገ ልታገኛቸው ትችላለህ።

- በጣም ጥሩ . . የዕውቀትና ቴክኖሎጂ አመራር ባለሞያዎችንስ?

- እንደ ነገርኩህ አራት ናቸው ዛሬ ለቃለ መጠይቅ ታገኛቸዋለህ፤ካመንክባቸው በኋላ እነርሱ ራሳቸው በአንተ ቦታ ሆነው የቴክኒክ ባለሞያዎችን ቃለ መጠይቅ ማድረግ ይችላሉ ብዬ አስባለሁ። በመሰረቱ የቴክኒክ ሞያተኞችና ፕሮግራመሮች ሲሆኑ በተጨማሪም የቴክኒክና ፕሮግራሚንግ ኦፕሬሽን አመራር ትምህርት የቀሰሙና ክህሎትም ያላቸው ናቸው።

- መቼ ላገኛቸው እችላለሁ?

- ሻዩን ከጠጣህ በኋላ በነጠላ ወይም አንድ ላይ እንደፈለክ ማግንት ትችላለህ።

- መልካም ፈቃድህ ከሆነ አራቱንም አንድ ላይ ማግነት እፈልጋለሁ።

- እንዳሻህ፣ሻይ እስክትጠጣ ዝግጁ መሆናቸውን ላረጋግጥ . . ከቃለ መጠይቁ በፊት ልታውቃቸው ስለሚገባ እነዚህ ሲቪዎቻቸው ናቸው። ይቅርታ መጣሁ . .

ጆርጅ ሲቪዎቹን በችኮላ አያቸው። የሰዎቹ ልምድና ክህሎት ትኩረቱን ስቧል፤ይሁን አንጂ እስኪያነጋግራቸው ድረስ መቸኮል አልፈለገም። መረጃዎቻቸውን በትንሽ ወረቀት ላይ ጠቅለል አድርጎ አሰፈረ . .

•ሙሐመድ ዐሊ - ሙስሊም - 38 ዓመት፣የግብብጽን የኤሌክትሮኒክስ መንግስት ፖርታል ፕሮጄክቶችን የመራ ሲሆን ፕሮግራሙ ግን ፍጻሜ አላገኘም።

•አሚር እስሐቅ - ክርስቲያን - 37 ዓመት፣የተባበሩት መንግስታት ድርጅትና የግብጽ መንግስት የቴክኖሎጂ የጋራ ፕሮጄክቶችን እንዲሁም የግብጽን የኢንፎርሜሽን ማእከል መርቷል።

•ሰልዋ ሐሰን - 39 ዓመት - ሙስሊም፣በስማርት ፎን መስክ በተሰማራ ኩባንያ ውስጥ የቴክኖሎጂ ፕሮጄክቶችን መርታለች።

•ማዝን ከማል -

39 ዓመት - ሙስሊም፣ሁለት የፕሮግራሚንግና የድረ ገጽ ዲዛን ኩባንያዎችን መርቷል።
ጽፎ እንደጨረሰ ዶክተር ኻሊድ ተመልሶ መጣ . .

- ጨርሰህ ከሆነ ወደ ስብሰባ ክፍል እንዲገቡ እጠራቸዋለሁ።

- ዝግጁ ነኝ።

- እሽ ጆርጅ፣እኔ መሄዴ ነው፣መቼ እንድመጣልህ ነው የምትፈልገው?

- ጀማል አመሰግናለሁ፣ከአንድ ሰዓት በላይ የሚያቆየኝ አይመስለኝም፣እጠበቀሃለሁ አብረን የምንሄድበት ቦታ አለ።

- መልክም፣ደህና ሁን።

ዶክተር ኻሊድ ባለ ሲቪዎቹን ጆርጅ ቁጭ ብሎ ወደ ሚጠብቃቸው ስብሰባ ክፍል እንዲገቡ ጠየቃቸው . .

- የናንተንም ሆነ የኢንጂነር ጆርጅን ጊዜ መሻማት አልፈልግም፣እርሱ የሚፈልገውን አብራርቼላችኋለሁ፣ሲቪዎቻችሁንም ተመልክቷል። ጊዜ ለማሳጠር ሲባል አንድ ላይ ነው የሚያነጋግራችሁ፤ጆርጅ መቀጠል ትችላለህ።

- የሁላችሁንም ሲቪዎች ተመልክቻለሁ፣ሁሉም በእጄ ይገኛሉ፤ለሁላችሁም አድናቆት አለኝ። እያንዳንዱ ሰው ለኩባንያችን ምን ማበርከት እንደምችልና ለምን እንደተስማማ ይንገረኝ።

የተናገሩትን አዳምጦ አብሯቸው ተወያየ፤ለሁሉም ያለውን አድናቆት ገልጾ የሚፈለግባቸውን ነገራቸው . . ከመካከላቸው ሦስቱን (አሚር፣ሰልዋና ማዝንን) ለመምረጥ መወሰኑን ገልጾ ሙሐመድ ሥራው ብዙ የማይመጥነው መሆኑን አስረዳ። ከመካከላቸው አንድ ሥራ አስኪያጅ እንዲመርጡ ጠይቋቸው አሚር እንዲሆን ወሰኑ . .

- ሥራ አስኪያጃችሁ ክርስቲያን በመሆኑ ችግር የለባችሁም?

- አንተም ክርስቲያን ነህ ምን ችግር አለው?

- አሚር ከሁለተኛ ደረጃ ጀምሮ ጓደኛዬ ነው፤እፊቱ እናገራለሁ፣የአመራር ብቃት አለው፤እንዲሰልም እመኝለታለሁ፤ባይሰልምም ግን ወዳጄ ሆኖ ይቀጥላል።

- የናንተ ዓይነቱን የምዕራባውያን ችግር እኛ ከሙስሊሞች ጋር የለንም፤እኔም ማዝን ከኔ የተሻለ የአመራር ብቃት አለው የሚል እምነት ነበረኝ።

- እኔ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ቀጠሮ አለብኝ፣ስብሰባችሁን ቀጥላችሁ የኩባንያው የቢሮ ሥራ የሚጀመርበትን የተሟላ ዝርዝርና የመጀመሪያ ዓመት እቅድ እንድትነድፉ እፈልጋለሁ። በእቅዱ ላይ ተወያይተን ለማጽደቅና ሥራ ለመጀመር ነገ ጧት አንገናኛለን። በተጨማሪም በዓለም አቀፍ ሠራተኛ ኤጀንሲ ኩባንያ ዘንድ ምርጥ ከሆኑ የቴክኒክ ሠራተኞች ስብስብ ጋር ተገናኝቼ ቃለ መጠይቅ ማካሄዴን ስነግራችሁ በደስታ ነው።

- ዶክተር ጊዮርጊስ የሚመራውን ነው?

- አዎ አሚር . . ታውቀዋለህ እንዴ?

- ዶክተር ጊዮርጊስ ለኔም ለማዝንም ጓደኛችን ነው . . ምርጥና የሰለጠነ የሰው ኃይል ያቀርባል።

- እንደዚሁም በሌላ ኤጀንሲ ያገኘኋትና ዲያና ሳምሕ የምትባል በጣም ድንቅ የሆነች ፕሮግራመርም አለችኝ።

- እህህ፣ፕሮግራመርዋ ዲያና ሳምሕ?

- ታውቃታለህ?

- የእህቴ ልጅ ናት።

- አንተ አጎቷ ነህ ማለት ነው?

- አዎ።

- ሊሆን አይችልም!

- ምኑ ነው መሆን የማይችለው?!

- ዛሬ ማታ የግድ አንተን ማግኘት አለብኝ። ምሽት አንድ ሰዓት ላይ ለእራት ግብዣ ብጠራህ ትቀበላለህ?

- ሁላችንም ነው?

- አይደለም፣ከሥራው ጋር ግንኙነት በሌለው የግል ጉዳይ ነው የፈለኩህ።

- መልካም፣የትነው?

- ባረፍኩበት ሆቴል ውስጥ፣አድራሻውን እንካ ያዝ።

የመንፈስ ሹክታ (3)

- ወደ ሆነ ቦታ እንድትወስደኝ እፈልጋለሁ፣አትቃወም።

- ችግር የለውም፣ግን ወዴት ነው?

- ከድሆችና ከተራ ነዋሪዎች ጋር መቀመጥና መነጋገር እፈልጋለሁ።

- በጣም እንግዳ የሆነ ጥያቄ ነው፤አልቃወምም፣ለምን እንደሆነ ግን ማወቅ እችላለሁ?

- አንዳንድ ነገሮችን ከራሳቸው አንደበት መስማትና ሕይወትን እንዴት አንደሚመለከቱ ማወቅ እፈልጋለሁ።

- አሳማኝ ምክንያት ነው።

- በነገራችን ላይ ከሰለመች ሊገድላት ከሚችለው የዲያና አጎት ጋር ተዋውቄአለሁ፣የሆነ ነገርም አስቤአለሁ።

- የት ተዋወቅከው?

- የኩባንያችን ቢሮ ሥራ አስኪያጅ እንዲሆን ያጨሁት ሰው እርሱ ነው።

- እንዲህ ያለው ሰው ለዚህ ተገቢ አይደለም፣ጆርጅ ምነው ጭፍን ወገንተኝነት!

- ከተስማማሁና ሥራ አስኪያጅ እንዲሆን ከወሰንኩ በኋላ በአጋጣሚ እንጂ አጎቷ መሆኑን አላወቅኩም።

- ይሄ ሀሳብህን እንድትቀይር የሚያደርግ ነውርና የስነ ምግባር ሕጸጽ ነው።

- ልክ ነህ፣ይሄ የማደርገው ነገር ነው፤ግን ዛሬ ማታ አንተም ከምታየውና ከማደርገው ሙከራ በኋላ የሚሆን ነው። ዛሬ በኔ ሆቴል አብረን እራት እንድንበላ ተጋብዘሃል።

- ምን አሰብክ?

- ማታ ታየዋለህ።

- መልካም፣እነሆ ወደ ተራ ሰዎች ሰፈር ደርሰናል . .

- የሆነን ሰው እቤቱ ድረስ ሄጄ መጎብኘት እፈልጋለሁ።

- እቤቱ ገብተህ መጎብኘት! ግድ የለም የማውቀው ሰው አለ፣ግን በዛኛው የመንገድ ጎን ነው። እስኪ ልደውልለትና መኖር አለመኖሩንና ጉብኝታችንን ይቀበል እንደሆነም ላረጋገጥ።

- ጥሩ፣እኔም ለዲያና ልደውል።

ጆርጅ ለዲያና ደውሎ አንድ ሰዓት ላይ በሆቴሉ ለመገናኘት ቀጠራት . . ጀማልም ለጋሼ ሰዒድ ከጆርጅ ጋር እንደሚጎበኙት ለመንገር ደወለላቸው . .

- የተዘጋጀ ምግብ ገዝተን ይዘን መሄድ ይኖርብናል።

- ለምን?

- አስቀድሞ ቀጠሮ ሳይኖረን በምሳ ሰዓት እየሄድን በመሆኑና ጋሼ ሰዒድ እኛን ለማስተናገድ አቅም እንደሌላቸው ስለማውቅ ለምን እናሸማቅቃቸዋለን?

- መልካም ብለሃል፣በጣም ምርጥ የሆነ ምግበና ጣፋጮችን ከሚያስፈልጉ ነገሮች ሁሉ ጋር እንግዛ።

ወደ ጋሼ ሰዒድ ቤት ደረሱ። በጣም ያረጀና ንጽሕናው ባልተሟላ ጠባብ ጎደና የሚገኝ ቤት ነው . . ጀማል በሩን አንኳኳ፤ጋሼ ሰዒድ እንኳን ደህና መጣችሁ ብለው በፈገግታ በሩን ከፍተው ተቀበሏቸው። ምግብ፣አትክልትና ጣፋጮቹን ይዘው አብረው ወደ ውስጥ ገቡ . . በጣም ያረጀ ግን በጣም ንጹህ ወደ ሆነ አሮጌ ክፍል ወሰዷቸው። የተዘጋጀው የመሬት መቀመጫ አሮጌ ፍራሽ ሲሆን መሀል ላይ ዳቦ፣ጥቂት አትክልትና አንድ ሳህን ሩዝ የተደረደረበት የምግብ መብያ ላስቲክ ተነጥፏል . .

- እባካችሁን አረፍ በሉና ጀምሩ።

- ምግብ ይዘን መጥተናል፣እንኩ ያዙ።

- አመሰግናለሁ፣አስፈላጊ አልነበረም፤እኔ ላስተናግዳችሁ ተዘጋጅቻለሁ፤እንዲያዘጋጁልን አንዴ ወደ ውስጥ ላስገባ።

ጋሼ ሰዒድ ወደ ውስጥ ገቡ። ጆርጅ የተነጋገሩትን በትክክል እንዲነግረውና ጋሼ ሰዒድ የሚናገሩትን እያንዳንዱን ቃል እንዲተረጉምለት ጀማልን ጠየቀው፣አንድም ቃል ሳይተረጉምለት እንዳያልፍ አሳሰበው . . ከደቂቃዎች በኋላ ጋሼ ሰዒድ እንግዶቹ ያመጡት ምግብ በየሳህኑ የተደረደረበትን ትልቅ ሳፋ ይዘው ተመለሱ . .

- በሉ ጀምሩ፣አክብራችሁናል።

- ጀማል . . በዚች ዓለም ላይ ምኞታቸው ምን እንደሆነ ጠይቃቸው።

- የኔ ልጅ ከችግር መሰወርንና ጤንነትን ነው።

- በሕወታቸውስ ደስተኛ ናቸው?

- ልጄ ጌታችን የዋለልን ውለታ ከባድ ነው፣እቤት ውስጥ እኖራለሁ ልጆች አሉኝ፣የእለት ጉርሴን አገኛለሁ፤ከዚህ በላይ ምን እፈልጋለሁ?

- ገንዘብና ንብረት እንዲኖራቸው አይመኙም?

- ጌታችን ሲሳይ ይስጠን ይጨምርልን፤ግን ገንዘብ ብቻ አይደለም፣ገንዘብም ጤንነትም የሕሊና ሰላምና እርጋታም ይጨምርልን።

- የሕሊና እርጋታና ሰላም ሲሉ ምን ማለታቸው እንደሆነ ጠይቃቸው።

- ጀማል ወዳጅህን እንዴት እንደሚኖር ጠይቀው፤የሕሊና እርጋታን የማያውቅ ሰው ሕይወቱ የመከራ ሕይወት ነው።

- እንደገና ጠይቅልኝ፣እንዴትና መቼ ነው የሕሊና መረጋጋትና እፎይታ የሚሰማቸው?

- የሕሊና መረጋጋትና እፎይታ የሚሰማኝ ዐስር (አስር ሰዓት) አካባቢ ከልጆቼ ጋር ሻይ ስጠጣ፣የአምላኬን ትእዛዝ ሳልጥስ ውዬ፣ያለብኝን ግዴታ ተወጥቼ ማንንም ሳላውክ ለመተኛት ሌሊት ጎኔን ሳሰርፍና ነው። ሶላት ከሰገድክ በኋላ የሕሊና መረጋጋትና እፎይታ አይሰማህም ወይ? በልልኝ።

ጀማል ያሉትን ሲተረጉምለት ጆርጅ አቀርቅሮ ለረዝም ጊዜ ዝም አለ . .

- አዝናለሁ፣እናንተ እንግዶቼ ናችሁና ልትከበሩ ይገባል፣ የማይገባ ተናግሬ አስቀይሜአችሁ እንዳልሆን።

- ይቅርታ መጠየቅ አያስፈልጋቸውም፣ይቅርታ መጠየቅ ያለብኝ መልስ ባለመስጠቴ እኔ ነኝ። መልካም ፈቃዳቸው ከሆነ መልሱን ይለፉኝ። የመጨረሻ ጥያቄ ላቀርብላቸው እፈልጋለሁ፣ለምንድነው የሚኖሩት?

- ጥያቄዎቻችሁ የሚገርሙ ናቸው! ለምን እንደሚኖር የማያውቅ ሰው አለ እንዴ?! ልጄ ጌታችን የፈጠረን እንድናመልከው ነው፤የሚመግበንና ሲሳይ የሚቸረንም እርሱ ነው፤ችሮታና ቸርነት በርሱ እጅ ነው። እኔ የምለው ግን የክቡር ጉብኝታቸው ምክንያት ምንድነው?

- ከርስዎ ለመማርና ከርስዎ ጋር ለመተዋወቅ ነው በላቸው።

- አላህ ብሩክ ያደድርጋችሁ፣ተባረኩ።

ጋሼ ሰዒድ እነሱ ካመጡት ምርጥ ምግብ ይልቅ የራሳቸውን ቤት ያፈራውን ምግብ እየበሉ መሆናቸውን ጆርጅ አስተውሏል . .

- ጀማል እኛ ካመጣነው ምግብ ለምን እንደማይበሉ ጠይቃቸው።

- እናንተ እንግዶቼ በመሆናችሁ እናንተ ያመጣችሁት ቢሆንም ለናንተ ሰስቼ ነው . . እውነቱን ለመናገር ከተራው የኔ ምግብ እናንተ ከምግባችሁ የምታገኙትን ተመሳሳይ እርካታ አገኛለሁ። አንድ ሰው ደስተኛና ጤነኛ እስከሆነ ድረስ ሁሉም ምግብ ጣፋጭ፣አላህ ይመስገንና ሁሉም ሕይወት ተድላ ነው።

በልተው
ጨረሱና ጋሼ ሰዒድን ለመስተንግዷቸው አመስግነው ተሰነባብተው ወጡ . .

- መቼም ብዙ አስቸግሬሃለሁ፣አሁን ደግሞ ቤተክርስቲያን ወይም የተራ ክርስቲያን ሰው ቤት መጎብኘት እፈልጋለሁ!

- እንግዳውስ የጋሼ ሰዒድ ጎረቤት ክርስቲያን ነውና ወርደን እንዲያስፈቅዱልን እንጠይቃቸው?

- መልካም . .

ጀማል ደውሎ ነገራቸው፤ወዲያው ነበር ጋሼ ሰዒድ ፈገግ እያሉ የወጡት . .

- ኑማ ተከተሉኝ።

- ወዴት?

- ወደ ጎረቤቴ ቤት . . በር ላይ መሆናችሁን ነግሬው እንኳን ደህና መጣችሁ ግቡ ብሏል።

ጋሼ ሰዒድ በሩን ሲያንኳኩ ራሳቸውን በሻሽ የተሸፋፈኑና ፊታቸው ብቻ የሚታይ ትልቅ አሮጊት በሩን ከፈቱ . .

- ግቡ፣ሳብርን ከእንቅልፍ ቀስቅሼው ፊቱን እየታጠበ ነው።

- አንዴ ወደ ቤቴ ሄጄ የሆነ ነገር ይዤ እመለሳለሁ።

- ጀማል ይህ የክርስቲያን ቤት ስለመሆኑ እርግጠኛ ነህ?

- አዎ፣እንደነገሩን የክርስቲያን ቤት ነው።

- ታድያ ሴትየዋ ለምንድነው ጸጉራቸውን የሸፈኑት?

- መልሱን ባውቀውም ከራሳቸው ብትሰማ እመርጣለሁ።

ጋሼ ሰዒድ ቡና እና የሚበሉ ነገሮችን ይዘው ተመለሱና ከእንግዶቹ ፊት አኖሩ . .

- ሁሉም ነገር እኔ ዘንድ ዝግጁ ስለሆነ ጎረቤቴ ምንም ነገር ለማዘጋጀት እንዳይለፋ ነግሬዋለሁ፤ድንገት የመጣንበት በመሆኑ የርሱ እንግዳ የኔም እንግዳ ነው።

- ለምግቡ ለቡናውና እንግዶችን ይዘህ በመምጣትህ አመሰግናለሁ።

- ጀማል፣ሁለቱ ከመቼ ጀምረው ጎረቤቶች እንደሆኑ ጠይቅልኝ።

- አባቴና አባቱ ጎረቤታሞች ከነበሩበት ከ12 ዓመቴ ጀምሮ ሰዒድ ጎረቤቴ ነው

- የአንድ ሃይማኖት ተከታዮች ግን አይደላችሁም!

- ልክ ነው፣ገን ጎረቤተትና ወዳጆች ነን . . ሰዒድ ሁል ጊዜ እንድሰልም ይመክረኛል።

- ስለ እስላምና ክርስትና ያለቸውን አመለካከትና በሁለቱ እምነቶች መካከል ስላለው ግንኙነት ጠይቅልኝ።

- የኔ ልጅ ኢዩሱስና መሐመድም ሁሉም የአላህ መልእክተኞች ናቸው። እኔና ወላጆቼ ከድሮም ክርስቲያኖች ስንሆን ሰዒድና ወላጆቹ ደግሞ ከጥንቱ ሙስሊሞች ናቸው። በመካከላችን ያለው ግንኙነትም ከጥንት ጀምሮ እጅግ በጣም ጥሩ ነው።

- ሙሐመድ የአላህ መልእክተኛ መሆኑን የሚያምኑ እስከሆነ ድረስ ለምን እንዳልሰለሙ ጠይቃቸው።

- እህህ፣ሰዒድም እኮ እንደዚሁ ዒሳ የአላህ መለእክተኛ መሆኑን ያምናል፤እናም ለምን ክርስትናን አልተቀበለም?!

- ሙስሊሞች ዒሳ የአላህ መልእክተኛ መሆኑን ስለሚያምኑና ክርስቲያኖች ግን ሙሐመድ የአላህ መልእክተኛ መሆኑን ስለማያምኑ ነው።

- ይህማ ራሱ ሰዒድ የሚናገረው ነገር ነው። ልጄ እውነቱን መስማት ትፈልጋለህ? አባቴና አያቶቼ የነበሩበትን መተው ስለምፈራ እንጂ ሰዒድ የሚለው ነገር አሳማኝ ነው፤ከአጎቶቼ ልጆች ይበልጥ እወደዋለሁ። እኔም ጥያቄ አለኝ፣ለመሆኑ አንተ ክርስቲያን ነህ ወይስ ሙስሊም?

- ለጊዜ ሲባል መልሱን ለራሴ ላቆይና ሌላ ጥያቄ አለኝ፣ባለቤትዎ እንደ ሙስሊሞች ለምን ይለብሳሉ?

- የኔ ባለቤት ብቻ ሳትሆን ሁሉም ግብጻውያት ክርስቲያኖችና ሙስሊሞች የሚለብሱት ነው።

- እኛ ዘንድ በአውሮፓ ክርስቲያኖች ጸጉራቸውን አይሸፍኑም።

- እኔ የማውቀው ግን እናንተ ዘንድ በአውሮፓም ሴቶች ጸጉራቸውን የሚሸፍኑ መሆናቸውን ብቻ ሳይሆን አልፎ አልፎም ፊታቸውን ጭምር ይሸፍኑ እንደነበረ ነው። ሁኔታው የተለወጠው ከጥቂት ምእተ ዓመታት ወዲህ ብቻ ነው! እስኪ የሴት ቅድመ አያቶችህን ፎቶግራፎች ፈትሽ። እኛም እንደዚሁ ነን፤ነገር ግን ትናንሽ ክርስቲያን ልጃገረዶች እናንተን መከተል ይወዳሉ፣በመልካሙ ነገር ቢሆን ባልከፋ ግን በጭፍኑ እናንተን ይኮርጃሉ።

- ለምን ክርስቲያኖቹ ብቻ?

- በሙስሊሞች ዘንድ ሃይማኖት ሕይወትን ሙሉ በሙሉ የሚያጠቃልልና አሻራውን በማሳረፍ የሚለውጥ በመሆኑና ኃጢአትን የሚየስተሰርየው ተጸጽቶ መመለስና ንስሀ በመሆኑ ነው። በክርስቲያኖች ዘንድ ግን የሰውን ልጅ ሕይወት የሚለወጠው በቤተክርስቲያን በሚሆን ነገር ነው . . እኛ ዘንድ የትኛውም ስህተት ቢሰራ ኢየሱስ አንዴ ከኃጢአቶች ሁሉ ነጻ ስለ አወጣን ነገሩ ቀላል ነው።

- ለሁለቱም ልባዊ ምስጋናዬን አቀርብልኝ፤ከሆቴሉ ቀጠሮ እንዳንዘገይ መሄድ ይኖርብናል።

ጋሽ ሰዒድንና ጋሼ ሳብርን ተሰናብተው ወጡ . . ወደ መኪናዋ አመሩ . .

- የፈለከውን ነገር አሳካህ?

- አዎ . . እኔ እንጃ፣አሁን ጭንቅላቴ ሊፈነዳ ምንም ያህል አልቀረውም . . በውስጤ የሚፈነዳ እሳተ ገሞራ እንዳለ ሆኖ ይሰማኛል። ከዲያና እና ከአጎቷ ጋር ቀጠሮ ባይኖረኝ ኖሮ ከነዚህ ተራ ሰዎች ጋር ረዥም ጊዜ ለማሳለፍ እሞክር ነበር። ጥልቀት ባለው ቅለትና ተራ ሁኔታ ነው ስለ ሕይወት የሚገልጹት . . ጀማል ይቅርታ . . የመናገር አምሮቴ ጠፍቷል።

- መልካም።

የጆርጅ ጭንቅላት በአንድ ጥያቄ ‹‹አንተን ከመታደል መንገድ ከልክሎ የያዘህ ምንድነው?›› በሚለው ሊፈነዳ ተቃርቧል። ፈራህ እንዴ? ወይስ የመታደል መንገድ አሁንም ገና አልተገለጸልህም?! ወይስ አንተ ያወቅከው ማወቅ የምትፈልገውን ሳይሆን ማወቅ የማትፈልገውን ሆኖ ይሆን? በውስጡ
በሚመላለሱ ግልጽ መረጃዎች ዓይነትና ብዛት የተነሳ መረጋጋት ከተሳነው አእምሮው የጥያቄው ጫና ምነው ፋታ በሰጠኝ ብሎ ተመኘ . .

የመንፈስ ሹክታ (4)

- ወደ ሆቴሉ ተቃርበናል፤ዲያናንና አጎቷን ለእራት ጋብዣለሁ።

- ምን ማድረግ ነው የፈለከው?

- ልጅቷ እንድትሰልምና ከአጎቷ ችግር እንዲትገላገል አደርጋለሁ።

- በጣም ጥሩ፣ወደ እስላም ጥሪ የሚያደርግ ዳዒ ሆንክ ማለት ነው፣አንተ ግን የምትሰልመው መቼ ይሆን?

- ለጋሼ ሳብር እንዳልኩት ሁሉ . . መልሱን ለራሴ አቆያለሁ። ጭንቅላቴ በዚህ ጥያቄ ምክንያት ሊፈነዳ ነው፣ምናልባትም ከጥያቄው ለመሸሽ እፈልግ ይሆናል፣ማን ያውቃል . .

- አንተ ዳዒው እንዴት ብለህ ይሆን እንድትሰልም ጥሪ የምታደርግላት?!

- ለሹፈትህ አመሰግናለሁ! እሷ መስለም ትፈልጋለች፣ነገር ግን አጎቷን ትፈራለች። እናም ይህን ፍርሃት ነው የማስወግደው።

- እንዴት?

- ታየው የለ? አሁን ደርሰናል።

- ይልቅስ ከአጎቷ በኩል በዲያና ላይ ችግር እንዳትፈጥርባት።

- በጊዜ ነው የደረስነው፤ወጥቼ ሻንጣዬን አስቀምጬ ሬስቶራንቱ ውስጥ ቶሎ ከናንተ እቀላቀላለሁ።

ጀማል ወደ ሬስቶራንቱ ሲገባ ዲያና እና አጎቷ አንድ ጠረጴዛ ይዘው ጆርጅን በመጠባበቅ ላይ ነበሩ፤አብሯቸው ቁጭ አለ . .

- ጆርጅ ሸንጣውን ለማስቀመጥ ነው ወደ ላይ የወጣው፣አሁን ይመጣል።

- ምን እንደሚፈልግ አላውቅም፣የዲያና አጎት መሆኔን እንዳወቀ ብቻ አብረን እራት ካልበላን አለኝ፤ምን እንደ ፈለገ ታውቃለህ?

- ምናልባት ዲያና ታውቅ ይሆናል! . .

- እኔ ምንም አላውቅም፤ለምን አልሰለምክም? ብዬ ላቀረብኩለት ጥያቄ መልስ ሊሰጠኝ እንደሚደውል ብቻ የነገረኝ ቢሆንም የደወለው ግን ሳልጠብቅ ለእራት ግብዣ ነው!

ጆርጅ ወደ ሆቴሉ ሬስቶራንት ደረሰ፤ዲያና ከሩቅ አይታው ምልክት ሰጠችው፤እነሱ ወደተቀመጡበት ጠረጴዛ አመራ . .

- ላስተዋውቃችሁ . . አሚር በግብጽ የኩባንያችን የቀጠና ሥራ አስኪያጅ ነው። ዲያና የኩባንያችን ምርጥ ፕሮግራመር ናት። ይሄ ሙስሊም ወዳጄ ደግሞ ፕሮግራመር ሳይሆን የፕሮግራሚንግ አባት የሆነው የማቴማቲክስ ባለሞያ ነው።

- አጎቴ የኩባንያችሁ ሥራ አስኪያጅ ነው?!

- ሙስሊም ባይሆንም፣በብቃትና በሁሉም ባልደረቦቹ ሙሉ ስምምነት የኩባንያው ሥራ አስኪያጅ ነው።

- ለጣልክብኝ እምነት አመሰግናለሁ።

- እስካሁን የሚገርመኝ ግን የሥራ ባልደረቦቹ ሙስሊሞች ሆነው እያለ እነሱ ራሳቸው ያጩት መሆኑ ነው!

ዲያና ፈገግ አለችና . .

- ምኑ ነው የሚያስደንቀው?!

- አስገራሚው አንዳንድ ክርስቲያኖች መስለም የሚፈልጉ ሰዎችን የሚከለክሉ መሆናቸው ነው።

አሚር በመደነቅ . .

- እስላምን በሚገባ ስላላወቁት ነው!

- አሚር፣አንድ ክርስቲያን ሰው ቢሰልም ችግር የለውም ትላለህ ማለት ነው?!

- ምናልባት መስማት የማትፈልገው ሊሆን ይችላል፣እኔ የማምንበትን ልንገርህ። ማንኛውም ክርስቲያን ፈልጎ ቢሰልም እኔ ምንም ችግር የለብኝም። ምናልባት ስለኔ የማታውቀው ከሦስት ሳምንታት ወዲህ ወደ አንድ እስላማዊ ማእከል እየተመላለስኩ መሆኔን ነው። ማን ያውቃል በቅርብ ጊዜ ውስጥ እሰልም ይሆናል!

- አጎትሽ ሊሰልም ይችላል፣እንግዳውስ አንቺን እንዳትሰልሚ የሚያደርግሽ ምንድነው?

- እህህ፣አሁን ገና ገባኝ።

- ምኑ ነው የገባሽ? ምን ነካሽ?

- አጎቴ አሚር የነገርኩህ አጎቴ አይደለም።

- እንዴት? የነገርሽኝ አጎትሽ ያንድ አባት ያንድ እናት ወንድም ነው ማለት አይደለም?

- አይደለም፤በምነግርህ ነገር ትገረም ይሆናል፤አያቴ ካንድ ሚስት በላይ ነበሩት።

- ክርስቲያን ሆኖ ከአንድ ሚስት በላይ?! ብዙ ማግባት ይፈቀዳል የሚል ክርስቲያን እኔ አላውቅም!

- ማነው ያለው? ወንጌል ከአንድ በላይ ማግባትን አይከለክልም የሚሉ ሰዎች አሉ፤ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ማርቆስ አምስተኛ የምእመናኑንና የከፊል ጳጳሳትን ፍላጎት በመጻረር ከአንድ በላይ ማግባትን በመቃወማቸው ታስረዋል። ሌላው ወገን እንደሚለው ይህ የሆነው በሙስሊሞች ተጽእኖ ምክንያትም ይሁን ወይም ከአንድ በላይ ማግባትን የሚደግፉ አንዳንድ ጳጳሳት እንደሚሉት ወንጌል የማይከለክለው በመሆኑ በመሆኑ፣አለዚያም ሚስቶች እንደሚሉት ቅምጥ ፍቅረኞችን ከመያዝ የተሻለ በመሆኑ . . ለማንኛውም አያቴ ሚስቱ ሞተችና ሌላ ሚስት አገባ። እናም አሚር አጎቴ ነው ግን የነገርኩህ አጎቴ ማርቆስ አይደለም፣ከአሚር ጋር በአባት ብቻ ነው የሚገናኙት።

- ይገርማል! ሕዝቡ ግን ከአንድ በላይ ማግባትን ይፈልጋል።

- እኔን ብቻ ለይተህ ለምን እንደጠራህ አሁን ገና ገባኝ። ዲያናን እንዳትሰልም የሚከለክለው አጎቷ እኔ መስየህ ኖሯል ማለት ነው።

- ልክ ነው።

ዲያና ከንፈሮቿን መጠጠችና በቁርጠኝነት ተናገረች . .

- እኔ ግን የጠራኸኝ ለምን እንዳልሰለምክ ልትነግረኝ ነው ብዬ ነበር ያሰብኩት።

ጀማል በመገረም . .

- ጣልቃ እንድገባ ፍቀዱልኝ፤ዲያና እርሱ እንዲሰልም መጓጓትሽ ትክክለኛ አቋም ነው፣አንቺ ራስሽ ግን ለምን አልሰለምሽም?

- ይህን ጥያቄ አቅርቤለት ከመመለስ ይሸሽ ስለነበረ መልሱን ሊነግረኝ ፈልጎ የጠራኝ መስሎኝ ነበር። አሁንሳ ልትነግረኝ ትችላለህ?

- ተገድጄ መመለስ እችላለሁ፤ብታልፉኝ ግን አመሰግናለሁ።

አሚር ፈገግ እያለ ቀጠለ . .

- እንግዳውስ አትመልስ። መልስ እንፈልጋለን፣ነገር ግን ያለ ምንም መሸማቀቅ ከሆነ ብቻ ነው።

ዲያና ጣርያ ጣርያውን እያየች . .

- አንተ መግለጽ እስካልፈለክ ድረስ አልናገርም እንጂ እኔ መልስህን አውቃለሁ።

- ሁላችሁንም አመሰግናለሁ . . ግን እውስጤ ያለውን ማንም የሚያውቅ አይመስለኝም።

- አንተ ሰብአዊ ፍጡር ነህና መታደልን ትፈልገዋለህ፣እኔ አጎቴና አሚርም እንዲሁ። ድፍረትና ጀግንነት ኖሮን ገልጸን ተናገርነው ወይም ፈርተን ከገዛ ራሳችን ሸሽተን ተደበቅን፣ እኛን እንዳናገኘው የሚከለክለን ነገር ራሱ ነው አንተንም የሚከለክለው። እኔ ለምሳሌ እንቅፋት የሆነብኝ አጎቴ ማርቆስ ነው ብዬ በሁኔታዎች እያሳበብኩ ራሴን እሸነግላለሁ! ድፍረትና ነጻነት ቢኖረኝ ኖሮ ግን እወስን ነበር።

- ግራ አጋባሽኝ! ታድያ ምንድነው የከለከለሽ?

ዲያና ጸጉሯን እየነካካች ቀጠለች . .

- እውነቱን ለመናገር የሚከለክለኝ አንተንና አሚርንም የከለከለው ነገር ነው። ውስጣዊ ግጭትህ እንዳይጋለጥ እንዳትነግረን እንደ ፈቀድንልህ ሁሉ አንተም በተራህ እንዳንናገር ለምን አትፈቅድልንም? እያንዳንዱ ሰው የየራሱን ቅራኔዎች፣ግጭቶች፣ዝንባሌዎችና ፍላጎtች እውስጡ አምቆ ይዟል። ለገዛ ራስ እውነተኛና ታማኝ መሆን ብዙ ያስቸግራል። በተለይ ደግሞ ጉዳዩ ከሕይወት መሰረት ጋር፣ከሕልውና ምንነትና ከመኖር ዓላማ ጋር የተያያዘ በሚሆንበት ጊዜ። ለዚህም ነው እኔ በፍርሃትና በሽንፈት እንደማደርገው ሁሉ፣ሰዎች በመጠጥና በጭፈራ . . ከዚህ የሚሸሹት!!

የዲያና አነጋገር ተጽእኖ ያሳደረበት አሚር በመደመም ስሜት ተውጦ ወደ ጫማው እየተመለከተ ቀጠለ . .

- የምትናገሪውን በሚገባ እረዳለሁ። የሰው ልጅ ደስተኛ ሆኖ መኖር ይኖርበታል። ፈጣሪ ጌታውን ለማወቅና ሕይወትን ለማጣጣም የመታደልን መንገድም ለራሱ ፈልጎ ማግኘት አለበት። ይህ ግን ነጻነትና ጀግንነትን የሚጠይቅ ውሳኔ ነው። ዲያና አንቺ ግን ከሁላችንም ይበልጥ ድፍረትና ጀግንነትን የተላበስሽ ነሽ፤ለዚህም ነው የተናገርሽውን መናገር የቻልሽው።

ጀማል ከመካከላቸው ሆኖ ግራ ቀኝ እየተመለከተ ግራ ተጋብቷል . .

- እኔ ምንም አልገባኝም፣ስለ የትኛው ጀግንነት ነው የምታወሩት?!

ዲያና ጥልቀት ባለው የተረጋጋ አነጋገር ቀጠለች . .

- ከሕሊና ደዌ የመላቀቅ ጀግንነት ነው። ከሕይወት ውጣ ውረዶች፣ከግላዊ ፍላጎቶች፣ከስሜታዊ ዝንባሌዎች እና ከውዥንብሮች በላይ ሆኖ የመገኘት ድፍረት ነው። የለመድከውን ወግና ልማድ ድንበር አልፎ የሚሄድ፣የሚነዙ ውዥንብሮችንና የሚሸረቡ ሴራዎችን በጣጥሶ የሚያልፍ ውሳኔ የመወሰን ጀግንነት ነው። ልቦናህ በሚገባ እያወቀው አንደበትህ ድፍረት አንሶት መናገር የተሳነውን እውነታ የመናገር ጀግንነት ነው።

- አሁንም ለመረዳት እየሞከርኩ ነው!

- አንተ ሙስሊም ሆነህ የተወለድክ በመሆንህ ምናልት መረዳት ሊያስቸግርህ ይችላል፤እኔ ግን ዲያና ማለት የፈለገችውን ተረድቻለሁ፣ጆርጅም እንደዚሁ ተረድቷል ብዬ እገምታለሁ።

የዲያና ዓይኖች እንባ አቀረሩ . . መናገር ቀጠለች . .

- አርሱም መረዳት የማይፈልግ ወይም መረዳቱ እንዲታወቅበት የማይፈልግ ካልሆነ በስተቀር ተረድቷል። ብዙ ሰዎች ደስተኞች መስለው ራሳቸውን ስለሚሸነግሉ ከራሳቸው ይሸሻሉ።

በፍለጋ ጉዞ ውስጥ ያለፈባቸው ደረጃዎች ሁሉ ጆርጅ አእምሮ ውስጥ በፈጣን ፊልም ሽው እያሉ አለፉ። ከቁርኣን ያነበባቸውን አንቀጾች ሁሉ አስታወሰ። ያሳለፋቸው ሁኔታዎች ሁሉ ከፊቱ ተደቀኑ። መልስ ሊያገኝላቸው የለፋባቸው ቅራኔዎችና ግጭቶች ሁሉ ትዝ አሉት። ግራ የተጋባ እይታው፣ በተቻለው ሁሉ ሊደብቀው ሞክሮ ባልተሳካለት ከባድ ፍንዳታ ውስጡ በመናጥ ላይ መሆኑን ያሳብቃል። እናም በሁለት ቃላት ብቻ ለማሳጠር ወሰነ . .

- አዎ ተረድቻለሁ።

- እኔም የምታወሩትን እንቆቅልሽ ተረድቻለሁ። የዛሬውን ዓለም ሕይወትና የወዳኛውን ሕይወት ተድላ ትጎናጸፉ ዘንድ፣መልካሙን ሁሉ ታገኙ ዘንድ፣የአላህን የተሟላ ሃይማኖት ተቀብላችሁ እንድትሰልሙ ለሁላችሁም እመኛለሁ። አላህ እንዲህ ብሏል፦ {ዛሬ ሃማኖታችሁን ለናንተ ሞላሁላችሁ። ጸጋዬንም በናንተ ላይ ፈጸምኩ። ለናንተም እስላምን ከሃይማኖት በኩል ወደድኩ} [አል ማኢዳህ፡3] በእስላም አማካይነት ጸጋ ሁሉ ተሟልቶ ሃይማኖትም ምሉእ ተደርጎ ተቋጭቷል።

- ለረዥም ጊዜ በፍለጋው ላይ የተሰማራሁትን ነገር በሚገባ የተረዳሁ ይመስለኛል።

- ስትፈልገው የነበረው ምንድነው?

- ራሴን ነበር ስፈልግ የነበረው። የመኖሬን ምንነትና የተፈጠርኩበትን ዓለማ ለማወቅ ነበር ፍለጋ ላይ የተሰማራሁት . . የተውሒድን ብርሃን፣የሕይወትን ውበት ስፈልግ ነበር . . የመንፈስን የአእምሮንና የነፍስን ደስታ ለማግኘት መታደልን ፍለጋ ላይ ነበርኩ።

ዲያና እንባዋን እያደራረቀች ተናገረች . .

- እኔም ስፈልገው የነበረው ይኸው ነው!

- ውብ የእንቁ ጌጥ ይሆን ዘንድ የሕይወቴን ዕንቁዎች አንድ ላይ አደራጅቶ የሚያያይዘውን ገመድ አግኝቻለሁ። አሁን ለምን እንደ ተፈጠርኩ፣ለምንስ ዓለማ እንደምኖር በሚገባ አውቄያለሁ!!

- እኔ ምንም አልገባኝም ! የገባህ ነገር ምን እንደሆነ ልትነግረኝ ትችላለህ?!

የዲያና ፊት በፈገግታዋ በራ . . ቀጠለች . .

- ስሜትህን እኔም በጥልቀት እጋራለሁ! ከሁላችንም ይበልጥ ነጻነትንና ጀግንነትን የተላበስክ ነህ። ከገዛ ራስ ጋር እውነተኛና ታማኝ ሆኖ መገኘት ግሩም ድንቅ ብቃት ነው።

- የምፈልገውን ተረድቻለሁ። አዳምንና ሙጢዕ አረሕማንን ተረድቻለሁ። ሌቪን፣ቶምን፣ካትሪናን፣ሐቢብን፣ኦርሜላን፣ማይክልን፣ጃኖልካንና ካኽንም ተረድቻለሁ። ከሁሉም በላይ ግን ጆርጅን ተረድቻለሁ . . የሕይወትን ትርጉምና ምንነት ተረድቻለሁ!

- ምንም አልገባኝም!! የጠቀስካቸው ስሞች ምንድናቸው?

አሚር ከእንባ ጋር እየተናነቀ . .

- ጆርጅ እኔም አሁን አንተን ተረድቻለሁ፤እጅግ በጣም ድንቅ ሰው ነህ!

- ሽማግሌው ስለ ደስተኝነት መንገድ፣ስለ መታደልን ፍለጋ የተናገረውን ተረድቻለሁ።

- ሽማግሌው?! የመታደልን መንገድ፣የደስተኝነትን ጎዳና ልታሳየን ትችላለህ?!

- መንፈሴ፣ነፍሴና ሕሊናዬ መልስ ሰጥተውኛል። የመንፈስ ሹክታን፣የሕሊናን ጥሪ እነሆ አሁን ሰማሁ! . . ሁላችሁም ባለ ውለታዎቼ ናችሁ!

- መንፈስህ መልስ ሰጠህ?!

- አዎ፣ከመንፈሴ ተለይቼ ነበር፤አእምሮዬና እውቀቴ መንገዱን አውቀው መንፈሴ ግን ሩቅ ነበር።

አሚር በመገረም ዓይኖቹን ከፈተ . .

- እኔን እየገለጽከኝ ነው መሰለኝ፤መንፈስህ ምን አለህ?

- ዓለማዊ ሕይወት ከወዳኛው ሕይወት ጋር እንዴት እንደሚጣጣም፣ነፍስ ለሕይወት ትርጉም ከሚሰጠው ተውሒድ ጋር እንዴት እንደምትቀናጅ ነገረኝ።

ስሜቷ በጥልቅ የተነካው ዲያና እንባዋን እየጠራረገች ቀጠለች . .

- ዓለማዊ ሕይወት ከወዳኛው ሕይወት ይጣጣማል?!

- መንፈስ ከዕውቀት ከአእምሮና ከነፍስ ጋር ይጣጣሙና እርስ በርስ ከመታገልና ከመጻረር ፈንታ ይቀናጃሉ። እርስበርስ መጻረራቸው የመከራዬ ምንጭ ነበር!

- ግሩም ነው፣የመንፈስ ጥራትና ምጥቀት የተሰማህ ጊዜ እጹብ ድንቅ ጊዜ ነው! መንፈስህ አሁን እንዴት ነው አብሮት የተቀናጀውና የተጣጣመው?

ጆርጅ ፊቱ እየበራና ፍልቅልቅ እያለ ቀጠለ . .

- የአካል ደስታ ከመንፈስ ደስታ ጋር ተገናኘ . . ቅለት ከጥልቀት ጋር ተጣመረ . . ዓለማዊ ሕይወት ከወዳኛው ሕይወት ጋር ተቀናጀ . . መርሕ ከጥቅም ጋር ተጣጣመ . .

- ድንቅ ነው . . እጹብ ድንቅ ነው . .

- ነገ ማታ ወደ ለንደን እጓዛለሁ። የመታደልን መንገድ የማግኘቴን የምስራች እነግረዋለሁ። ረዥም ጊዜ ራሴን በድያለሁ፤እድሜዬንም አባክኛለሁ።

- ለማነው የምትነግረው?

- የመታደልን መንገድ የሚያገኘው መንፈሴ መሆኑን ላረጋገጠልኝ ሽማግሌ ነው የምነግረው።

- እዚህ የምትከፍተው ኩባንያ ጉዳይስ?

- ሂደቶቹን ነገ ጧት አጠናቅቃለሁ። አይሮፕላን የያዝኩት ለተነገወዲያ ዓርብ ምሽት ሁለት ሰዓት ነው። የህሊናዬን ጥሪ በማዳመጤና የመንፈሴን ሹክታ በመስማቴ፣ሕይወቴና መንፈሴ ተጣጥመውና ተጣምረው መቀናጀታቸውን . . ለሽማግሌው እነግረዋለሁ። አሁን በዚህች አፍታ ከሁሉም ወዳጆቼ ጋር መገናኘት በጣም አምሮኛል። እኔ እነሆ ደስተኛ ሆኛለሁ፣በእርግጥ ታድያለሁ፤መንገዱን አግኝቻለሁ።

- ጆርጅ እንኳን ደስ አለህ እለሃለሁ።

- ይቅርታ አድርጉልኝና አሁን በቀጥታ ወደ ክፍሌ መሄድ እፈልጋለሁ።

ጆርጅ ወደ ክፍሉ ሄዶ ለወዳጆቹ ኢሜይል ጻፈላቸው . .

‹‹ በደስተኝነት መንገድ ፍለጋዬ ላይ ከኔ ጋር የተጓዛችሁ ወዳጆቼ . . እነሆ የመታደልን መንገድ አግኝቸዋለሁ . . አግኝቸዋለሁ . . ደስታዬ ወሰን የለውም . . ለአስቸጋሪዎቹ ጥያቄዎቼ ምላሽ አግኝቻለሁ . .

ለናንተ ለሁላችሁም የልብ ፍካትና የህሊና ብርሃን ይገባችኋል . . ሁላችሁም የመንፈስ እርካታና የተውሒድ ጸዳል ይገባችኋል . .

ለናንተ ለሁላችሁም የመንፈስ ደስታና መነቃቃት ይገባችኋል . .

ለናንተ ለሁላችሁም የዓለማዊ ሕይወት ስኬትና የሕይወት ለዛ ይገባችኋል . .

ለናንተ ለሁላችሁም የዓለማዊ ሕይወትና የወዳኛው ሕይወት ተድላ ይገባችኋል . .

እኔ የታደልኩትን የደስተኝነት መንገድና መልካሙን ሁሉ እናንተም ታገኙ ዘንድ ጥልቅ ፍላጎቴ ነው። እኔ አግኝቼዋለሁ፣አዎ አግኝቼዋለሁ። መንፈሴ አእምሮዬና ነፍሴ ጥምረት ፈጥረው ተጣጥመዋል። ዓለማዊ ሕይወት ከወዳኛው ሕይወት ጋር ተጣጥሟል። የአካል ደስታ ከመንፈስ ደስታ ጋር ተገጣጥሟል። ነፍሴ ብዙ ከተበታተነች በኋላ ተሰባስባ አንድ ሆናለች። ጥያቄዎቼ ሁሉ ምላሽ አግኝተዋል . . ይህ የደስተኝነት መንገድ ነው፣ይህ የመታደል መንገድ ነው።

አንተ ቸሩና ርህሩሁ አምላክ ምስጋና ላንተ ይሁን

ወዳጃችሁ/ ጆርጅ ኒሶን››