የመልካም ስነምግባር መንገድ

የመልካም ስነምግባር መንገድ

የደስተኝነትና የመታደል መንገድ፣ግብረ ገብነትና መልካም ስነምግባር የሚውለበለብበት መንገድ መሆኑ የግድ ነው። በዚህ መንገድ የሚጓዝ መንገደኛም መንገዱን በፍቅር፣በመቻቻል፣በቸርነት፣በይቅርታ፣በይሉኝታ፣በሰላም፣በትህትና፣በመተሳሰብ፣በፍትሕ፣በሐቀኝነት፣በምክክርና በተቀሩትም መልካም ስነምግባራት የተሞላ ሆኖ ማግኘቱም የግድ ነው። በተጨማሪም ከነፍሲያና ከፍላጎቶቿ በላይ በመሆን ወደ ከፍተኛው የሞራል ደረጃና ወደ ምሉእ ስነምግባር የሚመጠቅበት መንገድም ነው። መልካም ስነምግባር ሊያስቀሩት የሚቻል የቅንጦት እቃ ሳይሆን በሕይወት ውስጥ ወሳኝነት ካላቸው መሰረቶች ቀዳሚውን ቦታ የሚይዝ ነው። የግለሰቦች መልካም ጠባይና ጥሩ ግብረገብነት፣በራሳቸውና በሕብረተሰቦቻቸው የደስተኝነት ሕይወት ላይ ገንቢ ነፀብራቅ ይኖረዋል። መጥፎና ብልሹ ከሆነ ደግሞ የሁሉም ሕይወት ብልሹና ደስተኝነት የራቀው ይሆናል።

ለዚህ ነው እስላም በተከታዮቹ ዘንድ የመልካም ስነምግባር ቡቃያን ለመዝራት ከፍተኛ ትኩረት የሚሰጠውና እንዲላበሱት አጥብቆ የሚያሳስባቸው። የአላህ መልክተኛ  የተላኩበት ዓላማ መልካም ስነምግባራትን የተሟሉ ማድረግ መሆኑን ሲገልጹ እንዲህ ብለዋል፦ {የተላክሁት መልካም ስነምግባራትን ምሉእ ለማድረግ ነው።} [በበይሀቂ የተዘገበ] የሰው ልጅ ካወቃቸው ስልጣኔዎች ታላቁን ስልጣኔ በመገንባት ዘመናትን የተሻገረውና የመልክቱ ባለቤት ብርሃኑን ለማዳረስና ሰዎችን በዙሪያው ለማሰባሰብ ከፍተኛ ትግል ያደረጉበት የእስላም መልክት፣አቢይ ዓላማው የሰው ልጆችን ባሕሪ ማረቅ፣ስነምግባራቸውን ማነጽና የምሉእነት አድማስን ከፊታቸው ወለል አድርጎ መክፈት ነበር ማለት ይቻላል።

የነቢዩ  መላክም መልካም ስነ ምግባርን ለማጎልበት፣ነፍስን ለማጥራትና ለማነጽ ነበር። እሳቸው ሲላኩ ሰዎች ከነዚህ መልካም ስነ ምግባራት ብዙዎቹን የሳቱ፣ከፊሎቹን የማያውቋቸውና ምንም ግምት የማይሰጧቸው ነበሩ። አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{እርሱ ያ በመሃይሞች ውስጥ አንቀጾቹን (ቁርአንን)፣በነርሱ ላይ የሚያነብላቸው፣(ከማጋራት) የሚያጠራቸውም፣መጽሐፍንና ጥበብን የሚያስተምራቸው የኾነን መልክተኛ (ሙሐመድን) ከነሱው ውስጥ የላከ ነው፤እነርሱም ከርሱ በፊት በግልጽ ስሕተት ውስጥ ነበሩ።}[አልጁሙዓ፡2]

በተጨማሪም አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{በውስጣችሁ ከናንተው የኾነን በናንተ ላይ አንቀጾቻችንን የሚያነብላችሁና የሚያጠራችሁ፣መጽሐፍንና ጥበብንም የሚያስተምራችሁ፣ታውቁት ያልነበራችሁትንም ነገር የሚያሳውቃችሁ የኾነን መልክተኛ እንደላክን (ጸጋን ሞላንላችሁ)።}[አልበቀራህ፡151]

እምነት ከመልካም ስነ ምግባር ጋር የተሳሰረ መሆኑ፦

ኢማን አማኙን ወደ በጎ ነገሮች የሚገፋፋና ከክፉና ውጉዝ ነገሮችም የሚከለክለው ኃይል ነው። መልካም ስነምግባር የጠንካራ ኢማን ምልክት እንደሆነ ሁሉ፣የመልካም ስነ ምግባር መላሸቅም የኢማን ድክመት ምልክት ተደርጎ ይወሰዳል። የአላህ መልክተኛ  ጠንካራ ኢማን የግድ ጠንካራ መልካም ስነምግባርን እንደሚወልድ፣የመልካም ስነምግባር መዝቀጥ መንስኤም የኢማን መዳከም ወይም ጨርሶ አለመኖር መሆኑን አብራርተዋል። አማኝ ያልሆነ ሰው ምንም ግድ ሳይኖረው፣ይሉኝታና ወቀሳን ሳይፈራ፣በሚፈጽመው ኃጢአት እጠየቅበታለሁ ብሎ ሳይጨነቅ ወራዳ ተግባራትን ይፈጽማል። የአላህ መልክተኛ  እንዲህ ብለዋል፦ {ይሉኝታና ኢማን አንድ ላይ የተቆራኙ ናቸው፤አንደኛው ሲወገድ ሌላኛውም ይታጣል።} [በበይሀቂ የተዘገበ] ከጎረቤት ጋር በሚኖረው ግንኙነት ኢስነምግባራዊ መሆን ኢማንን የሚጻረር መሆኑን ሲያመለክቱም ነቢዩ  እንዲህ ብለዋል፦ {በአላህ እምላለሁ፣አያምንም፤በአላህ እምላለሁ፣አያምንም፤በአላህ እምላለሁ፣አያምንም፤} ሲሉ የአላህ መልክተኛ ሆይ! ምንድነው እርሱ? አሏቸው። {ጎረቤቱ ከርሱ ክፋት የመዳን መተማመኛ የሌለው ሰው ነው።} [በቡኻሪ የተዘገበ]

ከዚህም ስንነሳ፣አላህ (ሱ.ወ.) ባሮቹን ወደ በጎ ነገር ሲጠራ ወይም ከክፉ ነገር ሲያስጠነቅቃቸው ይህን የሚያደርገው በልቦቻቸው ውስጥ በጸናው ኢማን መሰረት መሆኑን እንገነዘባለን። አላህ (ሱ.ወ.) መጽሐፉ ውስጥ ብዙ ጊዜ እንዲህ ይላል፦

 

ከዚህ ዓይነቱ ሐረግ በማስከተልም የሚፈለግባቸውን ያወሳል። የሚከተለውን የመሳሰለ ማለት ነው፦

{እናንተ ያመናችሁ ሆይ! አላህን ፍሩ፤ከውነተኞችም ጋር ኹኑ።}[አልተውባህ፡119]

እንደዚሁም የአላህ መልክተኛ  ተከታዮቻቸውን ስለ መልካም ስነምግባር ሲያስተምሩ ከእምነት ጋር እያያዙ ያስተምሩ ነበር። ለአብነት የሚከተለውን የነቢዩን  ቃል እናገኛለን፦ {በአላህና በመጨረሻው ቀን የሚያምን ሰው፣እንግዳውን ያስተናግድ፤በአላህና በመጨረሻው ቀን የሚያምን ሰው፣የጎረቤቱን መብት ይጠብቅ፤በአላህና በመጨረሻው ቀን የሚያምን ሰው፣መልካም መልካሙን ይናገር ወይም ዝም ይበል። [በአሕመድ የተዘገበ] ምግባረ ሰናይነትን ነፍስ ውስጥ ለማነጽ በዚህ መልኩ ነው እስላም በእምነት እውነተኛነትና በምሉእነቱ ላይ የሚመረኮዘው።

ዕባዳዎችና ስነምግባር፦

ዕባዳ ወይም አምልኮተ አላህ እስላም ውስጥ እንዳው ስውር ቃላትና ትርጉም የለሽ እንቅስቃሴዎች ሳይሆን፣መንፈስን የሚያጠሩና ሕይወትን አስደሳች የሚያደርጉ ተግባራትና ቃላት መገለጫ ነው። እስላም ውስጥ የሃይማኖታዊ ግዴታዎች ግብ፣ሁኔታዎች የፈለጉትን ያህል ቢለዋወጡ እንኳ ሙስሊሙ ሁሌም ምስጉን ምግባራትን ተላብሶና በመልካም ባሕርያት ጸንቶ እንዲኖር ማድረግ ነው። ቅዱስ ቁርኣንና የጸዳው ነቢያዊ ሱንና ይህንኑ እውነታ ያረጋግጣሉ። አላህ (ሱ.ወ.) የሶላት ግዴታን ሲደነግግ ሶላት ከመጥፎ ስነምግባርና ከሚጠላ ነገር የሚከለክል መሆኑን በመግለጽ እንዲህ ብሏል፦

{ከመጽሐፉ ወደ አንተ የተወረደውን አንብብ፤ሶላትንም ደንቡን ጠብቀህ ስገድ፤ሶላት ከመጥፎና ከሚጠላ ነገር ሁሉ ትከለክላለችና፤አላህንም ማውሳት ከሁሉ ነገር በላጭ ነው፤አላህም የምትሠሩትን ሁሉ ያውቃል።}[አልዐንከቡት፡45]

ዘካም እንደዚሁ እስላም ውስጥ፣የእዝነትና የመተሳሰብን ቡቃያ የሚዘራ፣የትውውቅ የትብብርና የቅርርብ ግንኙነቶችን በሕብረተሰቡ የተለያዩ መደቦች መካከል የሚፈጥርና የሚያጠናክር የላቀ ግብ ያለው ዕባዳ እንጂ እንዳው ለድሆች ሊሰጥ ከሀብታሞች የሚወሰድ ተራ ግብር ብቻ አይደለም። የከፋዩን ነፍስ ከንፍገት ቆሻሻ ማጥራትና ሕብረተሰቡን ወደ ላቀ በይነሰባዊ ግንኙነት ደረጃ ከፍ ማድረግ የዘካ ቀዳሚ ጥበብ ነው። አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{ከገንዘቦቻቸው ስትኾን በርሷ የምታጠራቸውና የምታፋፋቸው የኾነችን ምጽዋት ያዝ፤ለነሱም ጸልይላቸው፤ጸሎትህ ለነርሱ እርካታ ነውና፤አላህም ሰሚ ዐዋቂ ነው።}[አልተውባህ፡103]

በመሆኑም ምጽዋት (ሶደቃ) ገንዘብ በመለገስ ብቻ ላይ የተወሰነ አልተደረገም። ሕብረተሰቡንና ግለሰቦችን ደስተኞች ለማድረግ አስተዋጽዖ የሚያደርጉ በርካታ መልካም ስነምግባሮችንም እንዲያካትት ተደርጓል። ነቢዩ  አንድ ሙስሊም መለገስ ያለበትን ሶደቃ ትርጓሜ ሰፋ አድርገው ሲያቀርቡ እንዲህ ብለዋል፦ {ከራስህ ባልዲ ወደ ወንድምህ ባልዲ ውሃ መገልበጥህ ሶደቃ ነው፤በበጎ ነገር ማዘዝህና ከክፎ ነገር መከልከልህም ሶደቃ ነው።} በሌላ ዘገባ ደግሞ {በወንድምህ ፊት ፈገግ ማለትህም ሶደቃ ነው፤ሰዎች ከሚሄዱበት መንገድ ላይ ድንጋይ፣እሾህና አጥንት ማስወገድህም ሶደቃ ነው፤በአሳሳች ቦታ ወንድምህን (መንገድ) መምራትህም ሶደቃ ነው} የሚል ተመልክቷል። [በበይሀቂ የተዘገበ]

እስላም ጾምንም እንደዚሁ ከምግብና ከመጠጥ መከልከል ብቻ አድርጎ አይመለከትም። የድሆችንና የአጦችን ስሜት ለመረዳት የሚያግዝ፣በተመሳሳይም ነፍስን ለማሰልጠንና ፍላጎቶቿንና ዝንባሌዎቿን ለመቆጣጠር የሚያስችል የመልመጃና የስልጠና ትምህርት ቤት አድርጎ ነው የሚመለከተው። አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{እላንተ ያመናችሁ ሆይ! ጾም በነዚያ ከናንተ በፊት በነበሩት (ሕዝቦች) ላይ እንደ ተጻፈ በናንተም ላይ ተጻፈ (ተደነባ)፤ልትጠነቀቁ ይከጀላልና።}[አልበቀራህ፡183]

የአላህ መልክተኛም  እንዲህ ብለዋል፦ {በሐሰት መመስከርን እና በዚያ መሰረት መስራትን እርግፍ አድርጎ ያልተወን ሰው፣ምግብና መጠጡን ከመተው አላህ ጉዳይ የለውም።} [በአሕመድ የተዘገበ] በተጨማሪም ነቢዩ  እንዲህ ብለዋል፦ {ጾም ምግብና መጠጥን መተው (ብቻ) አይደለም፤ከውዳቂ ዝባዝንኬና ከብልግና ቃል መጾም ነው እንጅ፤አንድ ሰው ቢሰድብህ ወይም ቢጣላህ፦ እኔ ጾመኛ ነኝ፣እኔ ጾመኛ ነኝ በልም።} [በእብን ኹዘይማ የተዘገበ]

ሐጅን በተመለከተም ሌሎች ሃይማኖቶች አንዳንዴ የማይታወቁ ሚስጥራዊ አምልኮዎችን የሚያካትቱ ከመሆናቸው አንጻር፣አንድ ሰው ስነምግባራዊ ይዘቶች የሌሉት ባዶ ጉብኝት አድርጎ ሊገምት ይችል ይሆናል። ይህ ፈጽሞ ስህተት ነው። ይህን ሥርዓተ ጸሎት አስመልክቶ አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{ሐጅ (ጊዜያቱ) የታወቁ ወሮች ናቸው፤በነርሱም ውስጥ ሐጅን (እንዲሠራ) ነፍሱን ያስገደደ ሰው፣በሐጅ ውስጥ ሴትን መገናኘት፣ማመጥም፣ክርክርም፣የለም፤ከበጎም ሥራ የምትሠሩትን ሁሉ አላህ ያውቀዋል፤ተሰነቁም፤ከስንቅም ሁሉ በላጩ ጥንቃቄ ነው፤የአእምሮዎችም ባለቤቶች ሆይ! ፍሩኝ።}[አልበቀራህ፡197]

ከላይ የቀረቡት ሁሉ በሃይማኖትና በመልካም ስነምግባር መካከል ያለው ትስስር በጣም የጠበቀ መሆኑን ያረጋግጣሉ። እስላም ውስጥ ሶላትን፣ጾምን፣ዘካንና ሐጅን የመሳሰሉ ዋነኞቹ የእስላም ማእዘናት፣የተቀሩት ሌሎች የመግገዛት ሥራዎችም፣በምስጉን ስነምግባርና በመጠቁ መርሆዎች ጥላ ስር፣የሰውን ልጅ ወደሚያልመውና በደስተኝነትና በመረጋጋት ወደታደለው ምሉእነት ሕይወት የሚወስዱ መንገዶች ናቸው። ዕባዳዎቹ በአፈጻጸማቸውና በቅርጻቸው የተለያዩ ቢሆኑም፣የአላህ መልክተኛ  {የተላክሁት መልካም ስነምግባራትን ምሉእ ለማድረግ ነው} በማለት ባስቀመጡት አንድ ግብ ላይ ሁሉም ይገናኛሉ። ስለዚህም የደስተኝነትና የመታደል መንገድ በስነምግባር ላይ የሚመረኮዝና በዚህ ምሕዋር ዙሪያ የሚሽከረከር፣ምስጉን ባሕርያትና ዕባዳ ፈጽሞ የማይነጣጠሉበት መንገድ ነው። 

ስነምግባር እስላም ውስጥ

የደስተኝነትና የመታደል መንገድ ሕጋዊ፣እነጻዊና ዐቂዳዊ መሰረቶቹ በሁሉም ነገር ውስጥ የሚቆሙት በስነምግባር መደላድል ላይ ነው። ከአላህ (ሱ.ወ.) ጋር የሚኖረውን ግንኘት ከሚመለከተው አደብና ስነምግባር አንስቶ ከራስ ጋር፣ከባልደረቦች ጋር፣ከዘመዶች ጋር፣ከጎረቤት ጋር፣ሌላው ቀርቶ ከሚዋጋህ ጠላትም ጋር፣ከእንስሳትና ከሁሉም ፍጥረታት ጋር፣ከዚህም አልፎ ከተፈጥሮ አካባቢ፣ከዛፎችና ከእጸዋትም ጋር . . በሁሉም ነገሮች ውስጥ መሰረቶቹ የሚቆሙት በስነምግባር መደላድል ላይ ነው። ይህ ሁሉ አንደበታዊ ስነምግባርን፣አካላዊና ተግባራዊ ስነምግባርንና ሕሊናዊና ውስጣዊ ልቦናንም የሚያጠቃልል ነው። አላህ (ሱ.ወ.) አንደበታዊ ከሆኑ የመልካም ስነምግባር መርሆዎች አንዱን ሲያረጋግጥ እንዲህ ብሏል፦

{ለሰዎችም መልካምን ተናገሩ፤}[አልበቀራህ፡83]

ተግባራዊ የስነምግባር መርህን ሲያስቀምጥም አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{በዚያች እርሷ መልካም በኾነችው (ጠባይ) መጥፎይቱን ነገር ገፍትር፤እኛ የሚሉትን ሁሉ ዐዋቂዎች ነን።}[አልሙእሚኑን፡96]

የአላህን መጽሐፍ አስተውሎ የተመለከተ ሰው፣በስነምግባራዊ ትእዛዛት የተሞላ መሆኑን ይረዳል። ቀጥሎ የሰፈሩትን ቁርኣናዊ አንቀጾች እናስተውል። አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{የበጎ ሥራ ዋጋ በጎ እንጅ ሌላ ነውን?}[አልረሕማን፡60]

በተጨማሪም (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{በመካከላችሁም ችሮታን አትርሱ፤}[አልበቀራህ፡237]

በተጨማሪም (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{ስለዚህ መልካም ትእግስት (ማድረግ አለብኝ) በምትሉትም ነገር ላይ መታገዣው አላህ ብቻ ነው።}[ዩሱፍ፡18]

በተጨማሪም አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{ሰዓቲቱም በርግጥ መጪ ናት፤መልካምንም ይቅርታ አድርግላቸው።}[አልሒጅር፡85]

በተጨማሪም አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{ገርን ጠባይ ያዝ፤በመልካምም እዘዝ፤ባለጌዎቹንም ተዋቸው።}[አልአዕራፍ፡199]

በተጨማሪም አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{ውድቅንም ቃል በሰሙ ጊዜ፣ከርሱ ይርቃሉ፤ለኛ ሥራዎቻችን አሉን፤ለናንተም ሥራዎቻችሁ አሏችሁ፤ሰላም በናንተ ላይ (ይኹን)፤ባለጌዎችን አንፈልግም ይላሉ፤}[አልቀሶስ፡55]

በተጨማሪም አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{መልካሚቱና ክፉይቱም (ጠባይ) አይተካከሉም፤በዚያች እርሷ መልካም በኾነችው ጠባይ (መጥፎይቱን) ገፍትር፤ያን ጊዜ ያ ባንተና በርሱ መካከል ጠብ ያለው ሰው፣እርሱ ልክ እንደ አዛኝ ዘመድ ይኾናል።}[ሓ ሚም አልሰጅዳህ፡34]

የአላህ መልክተኛ  ስነምግባርም ቁርኣናዊ ስነምግባር ነበር። አላህ (ሱ.ወ.) ታላቅ ስነምግባራቸውን ሲያሞግስ እንዲህ ብሏል፦

{አንተም በታላቅ ጠባይ ላይ ነህ።}[አልቀለም፡4]

ለዚህም ነው ነቢዩ ፣ከሌላው ነገር በተለየ ለመልካም ስነምግባር ልዩ ትኩረትና ትልቅ ደረጃ የሰጠ መልእክት ይዘው የመጡት። የአላህ መልክተኛ  እንዲህ ብለዋል፦ {ከምእመናን መካከከል ከሁሉም ይበልጥ ኢማኑ ሙሉ የሆነው ከሁሉም ይበልጥ መልካም ስነምግባር ያለው ነው፤ምርጥና በላጫቸውም ለሴቶቻቸው ከሌሎቹ ይበልጥ ጥሩዎቹ ናቸው።} [በበይሀቂ የተዘገበ] በተጨማሪም የአላህ መልክተኛ  እንዲህ ብለዋል፦ {በጎ ነገር መልካም ስነምግባር ነው፤ኃጢአት ልብህን የከነከነና ሰዎች እንዳያውቁት ብለህ የምጠላው ነገር ነው።} [በሙስሊም የተዘገበ] እንደዚሁም ነቢዩ  እንዲህ ብለዋል፦ {ብልግና እና መባለግ በእስላም ውስጥ ቦታ የላቸውም፤ከሰዎች ሁሉ እስልምናው ይበልጥ ያማረው ከሁሉም ይበልጥ መልካም ስነምግባር ያለው ነው።} [በአሕመድ የተዘገበ] በተጨማሪም ነቢዩ  እንዲህ ብለዋል፦ {በትንሣኤው ቀን በአንድ አማኝ (የሥራዎች) ሚዛን ከመልካም ስነምግባር ይበልጥ ክብደት ያለው ምንም ነገር የለም፤አላህ (ሱ.ወ.) ክፉ ባለጌን በእርግጥ ይጠላል።› [በበይሀቂ የተዘገበ]

የአላህ መልክተኛም  እንዲህ ብለዋል፦ {በኣኽራ ከሁሉም ይበልጥ ለኔ ተወዳጆቻችሁና ለኔ ከሁሉም ይበልጥ ቅርቦቻችሁ ከሁሉም ይበልጥ መልካም ስነምግባር ያላቸው ናቸው። ከሁላችሁም ይበልጥ እኔ ዘንድ የተጠሉትና ከሁሉም ይበልጥ ከኔ ሩቅ የሆኑት ደግሞ መጥፎ ስነምግባር ያላቸው፣ነገር ከልክ በላይ መናገርን የሚያበዙ (ለፍላፊዎች)፣ቀባጣሪዎችና ሲንጣጡ የሚውሉ ሰዎች ናቸው።} [በአሕመድ የተዘገበ] 

መልካም ስነምግባራት እስላም ውስጥ አጠቃላይና ምሉእ ሲሆኑ ቅደም ተከተላቸው እንደሚከተለው ነው፦

ከአላህ ጋር የሚኖር ግንኙነትን የሚመለከት መልካም ስነምግባር፦

ከአላህ (ሱ.ወ.) ጋር የሚኖረው አደብና መልካም ስነምግባር ሦስት ነገሮችን ያጠቃልላል፦

አንደኛ፦ በርሱ ማመንና ከርሱ ዘንድ የመጣውን ሁሉ ማረጋገጥ ነው። አላህ (ሱ.ወ.) ስለራሱ እንዲህ ብሏል፦

{አላህ ከርሱ በስተቀር አምላክ የለም፤ወደ ትንሣኤ ቀን በርሱ ጥርጥር የሌለበት ሲኾን፣በእርግጥ ይሰበስባችኋል። በንግግርም ከአላህ ይበልጥ እውነተኛ ማነው?}[አልኒሳእ፡87]

ከአላህ (ሱ.ወ.) የተላለፈ ቃሉን ማረጋገጥ፣አንድ ሰው በአላህና በነቢዩ  ንግግር ምንም ጥርጣሬና ውዥንብር ሳይገባበት የሚያምንበት፣የሚከላከልለት፣በርሱም መንገድ የሚታገልለት መሆንን ግዴታ ያደርጋል።

ሁለተኛ፦ የአላህን (ሱ.ወ.) ብያኔዎች በእሺታ፣በትግበራና በአፈጻጸም መቀበል፣አንድንም የአላህ ውሳኔና ሕግ እምቢ አለማለት ነው። ከአላህ ብያኔዎች (አሕካም) ውስጥ አንድም ነገር አለመቀበልና እምቢ ማለት ከአላህ (ሱ.ወ.) ጋር በሚኖረው ግንኙነት ያልተገባ አደብና መጥፎ ስነምግባር ማራመድ ማለት ነው። ለዚህም ነው የራሳችንን አስተያየትና ግላዊ ዝንባሌያችንን ከአላህ ንግግርና ከሕግጋቱ እንዳናስቀድም አላህ (ሱ.ወ.) የከለከለው። አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{እላንተ ያመናችሁ ሆይ! በአላህና በመልክተኛው ፊት (ነፍሶቻችሁን) አታስቀድሙ፤አላህንም ፍሩ፤አላህ ሰሚ ዐዋቂ ነውና።}[አልሑጁራት፡1]

ሦስተኛ፦ ፍርድና ውሳኔዎቹን በውዴታና በትዕግስት መቀበል። ቀዳእና ቀደሩን በተመለከተ ከአላህ ጋር የሚኖረው አደብና መልካም ስነምግባር፣አንድ ሰው ውሳኔውን በውዴታ ያለማጉረምረም መቀበል፣ለቀዷእና ለቀደሩ እጅ ሰጥቶ በእርካታ መውሰድ ነው። ለዚህ ነው አላህ (ሱ.ወ.) ታጋሾችን ያሞገሰው። አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{ታጋሾችንም (በገነት) አብስር። እነዚያን መከራ በነካቻቸው ጊዜ፣እኛ ለአላህ ነን፣እኛም ወደርሱ ተመላሾች ነን፤የሚሉትን፣(አብስር)።}[አልበቀራህ፡155-156]

ከሰዎች ጋር የሚኖር ግንኙነትን የሚመለከት መልካም ስነምግባር፦

አላህ (ሱ.ወ.) ለሰዎች ሁሉ በተለይ ደግሞ ለወላጆች፣ለቅርብ ዘመዶችና ለጎረቤቶች ደግ መሆንን አዟል። አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{የእስራኤል ልጆችንም ጥብቅ ኪዳን፦ አላህን እንጅ ሌላን አታምልኩ፤በወላጆችም በግጎን ሥራ (አድርጉ)፤በዝምድና ባለ ቤቶችም፣በየቲሞችም (አባት በሌላቸው ልጆች)፣በምስኪኖችም፣(በጎ ዋሉ)፤ለሰዎችም መልካምን ተናገሩ፤ሶላትንም ደንቡን ጠብቃችሁ ስገዱ፣በማለት በያዝንባቸው ጊዜ (አስታውሱ)፤ከዚያም ከናንተ ጥቂቶች ሲቀሩ ሸሻችሁ፤እናንተም (ኪዳንን) የምትተው ናችሁ።}[አልበቀራህ፡83]

በተጨማሪም አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{መልካም ሥራ፣ፊቶቻችሁን ወደ ምሥራቅና ምዕራብ አግጣጫ ማዞር አይደለም፤ግን መልካም ሥራ፣በአላህና በመጨረሻው ቀን፣በመላእክትም፣በመጻሕፍትም፣በነቢያትም ያመነ ሰው፣ገንዘብንም ከመውደዱ ጋር ለዝምድና ባለ ቤቶችና ለየቲሞች፣ለሚስኪኖችም፣ለመንገደኞችም፣ለለማኞችም፣ለጫንቃዎችም (ማስለቀቅ) የሰጠ ሰውና ሶላትንም ደንቡን ጠብቆ የሰገደ፣ዘካንም የሰጠ፣ቃል ኪዳንም በገቡ ጊዜ በኪዳናቸው የሞሉ (ሰዎች ሥራ) ነው፤በችግር፣በበሺታና በጦር ጊዜም ታጋሾችን (እናወድሳለን)፤እነዚህ እነዚያ እውነትን የያዙ ናቸው፤እነዚያም ተጠንቃቂዎቹ እነርሱ ናቸው።}[አልበቀራህ፡177]

በተጨማሪም አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{ምንን (ለማን) እንደሚለግሱ ጠይቁሃል፤ከመልካም ነገር የምትለግሱት፣ለወላጆችና ለቅርብ ዘመዶች፣ለየቲሞችም፣ለድኾችም፣ለመንገደኞችም ነው፤ከበጎ ነገርም ማንኛውንም ብትሠሩ አላህ እርሱን ዐዋቂ ነው በላቸው።}[አልበቀራህ፡215]

በተጨማሪም አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{እነዚያም ያመኑና የተሰደዱ፣በአላህም መንገድ ላይ የታገሉ፣እነዚያም ያስጠጉና የረዱ፣እነዚያ እነሱ በውነት አማኞች ናቸው፤ለነሱም ምሕረትና የከበረ ሲሳይ አላቸው። እነዚያም በኋላ ያመኑና የተሰደዱ፣ከናንተም ጋር ኾነው የታገሉ፣እነዚያ ከናንተው ናቸው፤የዝምድናዎች ባለቤቶችም በአላህ መጽሐፍ ከፊሎቻቸው በከፊሉ (መውረስ) የተገቡ ናቸው፤አላህ በነገሩ ሁሉ ዐዋቂ ነው።}[አልአንፋል፡74-75]

በተጨማሪም አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{አላህንም ተገዙ፤በርሱም ምንንም አታጋሩ፣በወላጆችና በቅርብ ዝምድና ባለቤትም፣በየቲሞችም፣በምስኪኖችም፣በቅርብ ጎረቤትም፣በሩቅ ጎረቤትም፣በጎን ባልደረባም፣በመንገደኛም፣እጆቻችሁም ንብረት ባደረጓቸው (ባሮች)፣መልካምን (ሥሩ)፤አላህ ኩራተኛ ጉረኛ የኾነን ሰው አይወድም።}[አልኒሳእ፡36]

በተጨማሪም አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{አላህ በማስተካከል፣በማሳመርም፣ለዝምድና ባለቤት በመስጠትም ያዛል፤ከአስከፊም፣(ከማመንዘር)፣ከሚጠላም ነገር ሁሉ፣ከመበደልም ይከለክላል፤ትገነዘቡ ዘንድ፣ይገሥጻችኋል።}[አልነሕል፡90]

በተጨማሪም አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{ጌታህም (እንዲህ ሲል) አዘዘ፤- እርሱን እንጂ ሌላን አትገዙ፤በወላጆቻችሁም መልካምን ሥሩ፤በአንተ ዘንድ ኾነው፣አንዳቸው ወይም ሁለታቸው፣እርጅናን ቢደርሱ፣ፎህ አትበላቸው፤አትገላምጣቸውም፤ለነርሱም መልካምን ቃል ተናገራቸው። ለሁለቱም ከእዝነትህ የመዋረድን ክንፍ ዝቅ አድርግላቸው፤ጌታዬ ሆይ! በሕጻንነቴ (በርኅራሄ) እንዳሳደጉኝ፣እዘንላቸውም በል። ጌታችሁ በነፍሶቻችሁ ውስጥ ያለውን ሁሉ ዐዋቂ ነው። ታዛዦችም ብትኾኑ፣(በመሳሳትም ብታጠፉ) እርሱ ለተመላሾች መሓሪ ነው። ለዝምድና ባለቤትም መብቱን ስጥ፤ለምስኪንና ለመንገደኛም (ስጥ)፤ማባከንንም አታባክን። አባካኞች የሰይጣናት ወንድሞች ናቸውና፤ሰይጣንም ለጌታው ብርቱ ከሓዲ ነው። ከጌታህም የምትከጅላትን ጸጋ ለማጣት፣ከነርሱ ብትዞር፣ለነርሱ ልዝብን ቃል ተናገራቸው።}[አልኢስራእ፡28]

በተጨማሪም አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{የዝምድናን ባለቤት ተገቢውን ስጠው፤ለድኻም፣(እርዳ)፤ይህ ለነዚያ የአላህን ፊት (ውዴታውን) ለሚሹ መልካም ነው፤እነዚያም እነሱ የፈለጉትንየሚገኙ ናቸው።}[አልሩም፡38]

በተጨማሪም አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{እላንተ ሰዎች ሆይ! ያንን ከአንዲት ነፍስ (ከአዳም) የፈጠራችሁን፣ከርስዋም መቀናጆዋን (ሔዋንን) የፈጠረውን፣ከነርሱም ብዙ ወንዶችንና ሴቶችን የበተነውን ጌታችሁን ፍሩ። ያንንም በርሱ የምትጠየቁበትን አላህንና ዝምድናዎቻችሁንም (ከመቁረጥ) ተጠንቀቁ፤አላህ በእናንተ ላይ ተጠባባቂ ነውና።}[አልኒሳእ፡1]

በተጨማሪም አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{ብትሽሾሙም በምድር ላይ ማበላሸትን፣ዝምድናችሁንም መቁረጥን፣ከጀላችሁን?}[ሙሐመድ፡22]

በተጨማሪም አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{እርሱ ከጌታህ ወዳንተ የተወረደው እውነት መኾኑን የሚያውቅ ሰው፣እንደዚያ እርሱ ዕውር እንደ ኾነው ሰው ነውን? የሚገሠጹት የአእምሮ ባለ ቤቶች ብቻ ናቸው። እነዚያ በአላህ ቃል ኪዳን የሚሞሉ፣የጠበቀውንም ኪዳን የማያፈርሱ ናቸው። እነዚያም አላህ እንዲቀጠል በርሱ ያዘዘውን ነገር የሚቀጥሉ፣ጌታቸውንም የሚያከብሩ፣መጥፎንም ቁጥጥር የሚፈሩ ናቸው። እነዚያም የጌታቸውን ውዴታ ለመፈለግ የታገሡ፣ሶላትንም አዘውትረው የሰገዱ፣እኛ ከሰጠናቸው ሲሳይም በምስጢርም ኾነ በግልጽ የመጸወቱ፣ክፉውንም ነገር በበጎ የሚገፈትሩ ናቸው፤እነዚያ ለነሱ መጨረሻይቱ ምስጉን አገር አለቻቸው። (እርሷም) የመኖሪያ ገነቶች ናት፤ይገቡባታል፤ከአባቶቻቸውም ከዝርያቸውም መልካም የሠራ ሰው፣(ይገባታል)፤መላእክትም በነሱ ላይ ከየደጃፉ ሁሉ ይገባሉ። ሰላም ለናንተ ይኹን፣(ይህ ምንዳ) በመታገሣችሁ ነው፣የመጨረሻይቱም አገር ምን ታምር! (ይሏቸዋል)። እነዚያም የአላህን ኪዳን ከጠበቀ በኋላ የሚያፈርሱ፣አላህም እንዲቀጠል በርሱ ያዘዘውን ነገር የሚቆርጡ፣በምድርም ላይ የሚያበላሹ፣እነዚያ ለነሱ ርግማን አለባቸው፤ለነሱም መጥፎ አገር (ገሀነም) አላቸው።}[አልረዕድ፡19-25]

መልካም ስነ ምግባር እስላም ውስጥ ከወዳጅ፣ከጓደኛ ከዘመድና ከጎረቤት ጋር በሚኖር ግንኙነት ላይ ብቻ የሚወሰን ሳይሆን፣ደመኛ ተዋጊ ቢሆን እንኳ ወደ ጠላትም ጭምር ይሸጋገራል! በዚህም መላውን የሰው ዘር ያካትታል። አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{መልካሚቱና ክፉይቱም (ጠባይ) አይተካከሉም፤በዚያች እርሷ መልካም በኾነችው ጠባይ (መጥፎይቱን) ገፍትር፤ያን ጊዜ ያ ባንተና በርሱ መካከል ጠብ ያለው ሰው፣እርሱ ልክ እንደ አዛኝ ዘመድ ይኾናል።}[ሓ ሚም አልሰጅዳህ፡34]

እኛን በመዋጋት ላይ ከሚገኙት ጋር እንኳ ቢሆን ወሰን እንዳናልፍ ሲያዘን አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{እነዚያንም የሚጋደሏችሁን (ከሓዲዎች)፣በአላህ መንገድ ተጋደሉ፤ወሰንንም አተለፉ፤አላህ ወሰን አላፊዎቸን አይወድምና።}[አልበቀራህ፡190]

ከተዋጊ ጠላት ጋር እንኳ ቢሆን እስላም የሚከተለውን መልካም ስነምግባር፣ጠላትን ለመዋጋት በአላህ መንገድ ለመታገል ለጅሃድ ለተሰማራው ጦራቸው ነቢዩ  በሰጡት ትእዛዞች ውስጥ እንመልከት። ነቢዩ  እንዲህ ብለዋል፦ {ቃል ኪዳን አታፈርሱ፤ምርኮን አትደብቁ፣አታሰቃዩ (አካላዊ ሰቆቃ አታድርሱ)፤ልጆችንም፣የገዳማት ሰዎችንም አትግደሉ።} [በአሕመድ የተዘገበ] በተዋጊ ጠላቶች አያያዝ ላይ እንዲህ ያለውን መልካም ስነምግባር የሚያዝ ሃይማኖት ነገር በጣም አስገራሚ ነው። ተዋጊ ያልሆኑትን በሚመለከትም - ጠላት እንኳ ቢሆን - ለነሱ ደግና ፍትሐዊ መሆንን ሲያበረታታ አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{ከነዚያ በሃይማኖት ካልተጋደሏችሁ፣ከአገሮቻችሁም ካላወጡዋችሁ (ከሃዲዎች)፣መልካም ብትውሉላቸውና ወደነርሱ ብታስተካክሉ አላህ አይከለክላችሁም፤አላህ ትክክለኞችን ይወዳልና።}[አልሙምተሕናህ፡8]

በእንስሳት አያያዝ ላይ የሚኖር መልካም ስነምግባር

እስላም ውስጥ መልካም ስነምግባር እንስሳትንም እስከማካተት ድረስ የሰፋ ነው። የአላህ መልክተኛ  እንዲህ ብለዋል፦ {አንዲት ሴት አስክትሞት ባሰረቻት ድመት ምክንያት ተቀጣች፤በዚያ ምክንያትም እሳት ገባች። ስታስራት አልመገበቻትም፣አላጠጣቻትምም፣ወይም የመሬት ነፍሳትንና ትላትል ትበላ ዘንድ ፈታ አልለቀቀቻትም።} [በቡኻሪ የተዘገበ] አላህ (ሱ.ወ.) በእንስሳት አስተራረድ እንኳ ደግነትና ርኅራሄን አዟል። ነቢዩ  እንዲህ ብለዋል፦ {አላህ በሁሉም ነገሮች ላይ ደግ መሥራትን ወስኗል፤እናም ስትገድሉ አገዳደልን አሳምሩ፤ስታርዱም አስተራረድን አሳምሩ፤አንዳችሁ (ሲያርድ) ቢላውን ይሞርድ፣የሚታረደውን እንስሳም (ቶሎ እንዲሞት በማድረግ) ያሳርፈው።} [በሙስሊም የተዘገበ]

ተፈጥሮና አካባቢ ጥበቃን የሚመለከት መልካም ስነምግባር

በተመሳሳይ መልኩም እስላም ለተፈጥሮ አካባቢ ጥበቃና ለአጠቃላይ ትእይንት እንክብካቤም ሳይቀር መልካም ስነምግባርን ይዞ መጥቷል። ማበከንን በማውገዝ የተፈጥሮ ሀብቶችን ማራቆትና ማበላሸት እንዲቆም ጥሪ አድርጓል። አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{ከአላህ ሲሳይ ብሉ፤ጠጡም፤አመጠኞችም ኾናችሁ በምድር ላይ አታበላሹ (አልናቸው)።}[አልበቀራህ፡60]

በተጨማሪም አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{የወሰን አላፊዎችንም ትዕዛዝ አትከተሉ፤የነዚያን በምድር ላይ የሚያጠፉትንና የማያበጁትን። }[አልሹዐራእ፡151-152]

ውሃና የተቀሩትን ሌሎች የተፈጥሮ ሀብቶችን በተመለከተም እስላም ታላቅ ትኩረት ሰጥቷል። አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{እነዚያም የካዱት ሰማያትና ምድር የተጣበቁ የነበሩና የለያየናቸው መኾናችንን አያውቁምን? ሕያው የኾነንም ሁሉ ከውሃ ፈጠርን፤አያምኑምን?}[አልአንቢያ፡30]

በተጨማሪም አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{አላህም ከሰማይ ውሃን አወረደ፤በርሱም ምድርን ከሞተች በኋላ ሕያው አደረገ፤በዚህ ውስጥ ለሚሰሙ ሕዝቦች በእርግጥ ታምር አልለ።}[አልነሕል፡65]

ከቅዱስ ቁርኣን ጎን ለጎን፣ነቢዩም  በፊናቸው ለአከባቢ ጥበቃና ለተፈጥሮ ሀበት እንክብካቤ ጥሪ ያደረጉ ሲሆን፣ነቢያዊው ሱንና የአፈር መሸርሸር፣የበረሃማነትና የድርቅ ተፈጥሯዊ አደጋዎች እንዳይከሰቱ ለአካባቢ ጥበቃ በተደጋጋሚ ጥሪ በሚያደርጉ ሐዲሶች የተሞላ ነው። ይህን በማስመልከትም ነቢዩ  እንዲህ ብለዋል፦ {ሦስቱን መርገምት ተጠንቀቁ፦ በውሃ መውረጃዎች (ቦይ)፣በመንገድ ላይና (ሰው በሚያርፍበት) ጥላ ቦታ መጸዳዳት ናቸው፡፡} [በአቡ ዳውድ የተዘገበ] በተጨማሪም ነቢዩ  እንዲህ ብለዋል፦ {ማንኛውም ሙስሊም ዘር ዘርቶ ወይም ችግኝ ተክሎ፣ወፍ ሰው ወይም እንስሳ ከተክሉ ቢበላ ሶደቃ ይሆንለታል።} [በሙስሊም የተዘገበ] እንደዚሁም ነቢዩ  እንዲህ ብለዋል፦ {የትንሳኤ ቀን ቢጀምርና በአንዳችሁ እጅ ችግኝ ቢኖር፣ከመነሳቱ በፊት ሊተክለው ከቻለ ያድርግ፡፡} [በአሕመድ የተዘገበ] የአላህ መልክተኛ  ሰዐድ ውዱእ ሲያደርጉ በአጠገባቸው አለፉና፦ {ይኸ ብክነት ምንድነው?} አሏቸው። ሰዐድም {በውዱእም ማባክ አለ እንዴ?!} ሲሉ ጠየቁ፡፡ ነቢዩም  ፦ {አዎ፣በሚፈስ ወንዝ ላይ ብትሆን እንኳ} አሉ፡፡ [በእብንማጃህ የተዘገበ] ይህ በጦርነት ጊዜ ጠላታቸውን በሚዋጉበት ወቅት እንኳ ሳይቀር የነቢዩ  ባልደረቦች አካባቢ ጥበቃን አስመልክተው ይከተሉት የነበረው መልካም ስነምግባር ነው፡፡ አቡ በክር ለጦርነት ላሰማሩት ጦር አዛዥ የሚከተለውን መመሪያ ሰጥተዋል፦ {ሕጻን አትግደል፤ሴትም፤አዘውንት ሽማግሌም፡፡ የሚያፈራ ዛፍም አትቁረጥ፤ፍየልም ሆነ ላም ለመብላት ካልሆነ በስተቀር አትግደል፡፡ ቤቶችን አታፈርስ፤የተምር ዛፍን አታጥለቀልቅ፣አታቃጥለውም፡፡} [በአሕመድ የተዘገበ (9)

ከመልካም ስነምግባር ትእዛዛት መካከል፦

እዚህ ላይ በአላህ መጽሐፍና በነቢዩ  ሱንና ውስጥ ከቀረቡት የመልካም ስነምግባር ትእዛዛት መካከል የተወሰኑትን መመልከቱ ጥሩ ይሆናል፡፡ ከነዚህ መካከል የሚከተሉት ይገኛሉ፦

ቅዱስ ቁርኣን ውስጥ፦

-

አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{አላህ አደራዎችን ወደ ባለቤቶቻቸው፣እንድታደርሱ ያዛችኋል። በሰዎችም መካከል በፈረዳችሁ ጊዜ፣በትክክል እንድትፈርዱ፣(ያዛችኋል)፤አላህ በርሱ የሚገሥጻችሁ ነገር ምን ምር! አላህ ሰሚ ተመልካች ነው።}[አልኒሳእ፡58]

-በተጨማሪም አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{፦ ኑ፤ጌታችሁ በናንተ ላይ እርም ያደረገውን ነገር (በርሱም ያዘዛችሁን) ላንብብላችሁ በላቸው፤በርሱ (በአላህ) ምንንም ነገር አታጋሩ፤ለወላጆችም በጎን ሥራ (ሥሩ)፤ልጆቻችሁንም ከድኽነት ፍራቻ አትግደሉ፤እኛ እናንተንም እነርሱንም እንመግባችኋለንና፤መጥፎ ሥራዎችንም ከርሷ የተገለጸውንም የተደበቀውንም ሁሉ አትቅረቡ፤ያችንም አላህ እርም ያደረጋትን ነፍስ በሕግ ቢኾን እንጅ አትግደሉ፤ይኻችሁ ታውቁ ዘንድ (አላህ) በርሱ አዘዛችሁ። የየቲምንም ገንዘብ፣ብርታቱን (አካለ መጠን) እስኪደርስ ድረስ በዚያች እርሷ መልካም በኾነች ኹኔታ እንጂ አትቅረቡ፤ስፍርንና ሚዛንንም በትክክል ምሉ፤ነፍስን ችሎታዋን እንጂ አናስገድድም፤በተናጋራችሁም ጊዜ፣በዘመዶቻችሁ ላይ ቢኾንም እንኳ፣(እውነትን በመናገር) አስተካክሉ፤በአላህም ቃል ኪዳን ምሉ፤ይኻችሁ ትገሠጹ ዘንድ በርሱ አዘዛችሁ። ይህም ቀጥተኛ ሲኾን መንገዴ ነው፤ተከተሉትም፤(የጥመት) መንገዶችንም አትከተሉ፤ከ(ቀጥተኛው) መንገዱ እናንተን ይለያዩዋችኋልና። ይኻችሁ ትጠነቀቁ ዘንድ በርሱ አዘዛችሁ።}[አልአንዓም፡151-153]

-በተጨማሪም አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{በምድርም ውስጥ ከተበጀች በኋላ አታበላሹ፤ፈርታችሁና ከጅላችሁም ተገዙት፤የአላህ ችሮታ ከበጎ አድራጊዎች ቅርብ ነውና።}[አልአዕራፍ፡56]

-በተጨማሪም አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{ታገሥም፤አላህ የበጎ ሠሪዎችን ምንዳ አያጠፋምና።}[ሁድ፡115]

-በተጨማሪም አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{እጅህንም ወደ አንገትህ የታሠረች አታድርግ፣መዘርጋትንም ሁሉ አትዘርጋት፤የተወቀስክ፣የተቆጨህ፣ትኾናለህና። ጌታህ ሲሳይን ለሚሻው ሰው ያሰፋል፤ያጠባልም፤እርሱ በባሮቹ ኹኔታ ውስጠ ዐዋቂ ተመልካች ነውና። ልጆቻችሁንም ድኽነትን ለመፍራት አትግደሉ፤እኛ እንመግባቸዋለን፤እናንተንም፣(እንመግባለን)፤እነሱን መግደል ታላቅ ኃጢአት ነውና። ዝሙትንም አትቅረቡ፤እርሱ በእርግጥ መጥፎ ሥራ ነውና፤መንገድነቱም ከፋ! ያችንም አላህ ያወገዛትን [መግደሏን ውጉዝ ያደረገውን] ነፍስ፣ያለ ሕግ አትግደሉ፤የተበደለም ኾኖ የተገደለ ሰው፣ለዘመዱ (በገዳይ ላይ) በእርግጥ ስልጣንን አድርገናል፤በመግደልም ወሰንን አይለፍ፤እርሱ የተረዳ ነውና። የየቲምንም ገንዘብ፣የብርታት ጊዜውን እስኪደርስ ድረስ በዚያች እርሷ መልካም በኾነች ኹኔታ እንጂ አትቅረቡ፤በኪዳናችሁም ምሉ፤ኪዳን የሚጠየቁበት ነውና። በሰፈራችሁም ጊዜ፣ስፍርን ምሉ፤በትክክለኛው ሚዛንም መዝኑ፤ይህ መልካም ነገር ነው፤መጨረሻውም ያማረ ነው። ለአንተም በርሱ ዕውቀት የሌለህን ነገር አትከተል፤መስሚያ፣ማያም፣ልብም፣እነዚህ ሁሉ (ባለቤታቸው) ከነሱ ተጠያቂ ነውና። በምድርም ላይ የተንበጣረርክ ሆነህ አትኺድ፤አንተ ፈጽሞ ምድርን አትሰረጉድምና፣በርዝመትም ፈጽሞ ጋራዎችን አትደርስምና። ይህ ሁሉ (ከሃያ አምስቱ ጠባዮች ውስጥ) መጥፎው (አስራ ሁለቱ ክልክሎች) እጌታህ ዘንድ የተጠላ ነው። ይህ ጌታህ ከጥበቡ ወደ አንተ ካወረደው ነገር ነው፤ከአላህም ጋር ሌላን አምላክ አታድርግ፤የተወቀስክ፣የተባረርክ ኾነህ በገሀነም ውስጥ ትጣላለህና።}[አልኢስራእ፡29-39]

-በተጨማሪም አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{ከጌታችሁ ወደ ኾነችም ምሕረትና፣ስፋትዋ እንደ ሰማያትና ምድር ወደ ኾነች ገነት፣አላህን ለሚፈሩ የተዘጋጀች ስትኾን ተቻኮሉ። ለነዚያ በድሎትም ኾነ በችግር ለሚለግሱት፣ቁጭትንም ገቺዎች፣ከሰዎችም ይቅርታ አድራጊዎች ለኾኑት (ተደግሳለች)፤አላህም በጎ ሠሪዎችን ይወዳል።}[ኣሊ ዒምራን፡133-134]

-በተጨማሪም አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{እላንተ ያመናችሁ ሆይ! ወንዶች ከወንዶች አይቀልዱ፤ከነርሱ የበለጡ ሊኾኑ ይከጀላልና፤ሴቶችም ከሴቶች (አይሳለቁ)፤ከነሱ የበለጡ ሊኾኑ ይከጀላልና፤ነፍሶቻችሁንም አታነውሩ (ከፊላችሁ ከፊሉን አይዝለፍ)፤በመጥፎ ስሞችም አትጠራሩ፤ከእምነት በኋላ የማመጥ ስም ከፋ፤ያልተጸጸተም ሰው፣እነዚያ እነሱ በዳዮቹ ናቸው። እናንተ ያመናችሁ ሆይ! ከጥርጣሬ ብዙውን ራቁ፤ከጥርጣሬ ከፊሉ ኃጢአት ነውና፤ነውርንም አትከታተሉ፤ከፊላችሁም ከፊሉን አይማ፤አንደኛችሁ የወንድሙን ስጋ የሞተ ኾኖ ሊበላው ይወዳልን? (መብላቱን) ጠላችሁትም፤(ሐሜትንም ጥሉት)፤አላህንም ፍሩ፤አላህ ጸጸትን ተቀባይ አዛኝ ነውና። እላንተ ሰዎች ሆይ! እኛ ከወንድና ከሴት ፈጠርናችሁ፤ እንድትተዋወቁም ጎሣዎችና ነገዶች አደረግናችሁ፤አላህ ዘንድ በላጫችሁ፣በጣም አላህን ፈሪያችሁ ነው፤አላህ ግልጽን ዐዋቂ፣ውስጥንም ዐዋቂ ነው።}[አልሑጁራት፡11-13]

-በተጨማሪም አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{ልጄ ሆይ! ሶላትን አስተካክለህ ስገድ፤በበጎ ነገርም እዘዝ፤ከሚጠላም ሁሉ ከልክል፤በሚያገኝህም መከራ ላይ ታገሥ፤ይህ፣በምር ከሚያያዙ ነገሮች ነው። ጉንጭህንም (በኩራት) ከሰዎች አታዙር፤በምድርም ላይ ተንበጥርረህ አትኺድ፤አላህ ተንበጣራሪን፣ጉረኛን ሁሉ አይወድምና። በአካኼድህም፣መካከለኛ ኹን፤ከድምጽህም ዝቅ አድርግ፤ከድምጾች ሁሉ አስከፊው የአህዮች ድምጽ ነውና።}[ሉቅማን፡19]

-በተጨማሪም አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{የአልረሕማንም ባሮች፣እነዚያ በምድር ላይ በዝግታ የሚኼዱት፣ባለጌዎችም (በክፉ) ባነጋገሩዋቸው ጊዜ፣ሰላም ሚሉት ናቸው።}[አልፉርቃን፡63]

-በተጨማሪም አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{አላህንም ተገዙ፤በርሱም ምንንም አታጋሩ፣በወላጆችና በቅርብ ዝምድና ባለቤትም፣በየቲሞችም፣በምስኪኖችም፣በቅርብ ጎረቤትም፣በሩቅ ጎረቤትም፣በጎን ባልደረባም፣በመንገደኛም፣እጆቻችሁም ንብረት ባደረጓቸው (ባሮች)፣መልካምን (ሥሩ)፤አላህ ኩራተኛ ጉረኛ የኾነን ሰው አይወድም።}[አልኒሳእ፡36]

-በተጨማሪም አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{ከአላህም በኾነች ችሮታ ለዘብክላቸው። ዐመለ መጥፎ ልበ ደረቅም በኾንክ ኖሮ ከዙሪያህ በተበተኑ ነበር። ከነርሱም ይቅር በል። ለነርሱም ምሕረትን ለምንላቸው። በነገሩም ሁሉ አማክራቸው። ቁርጥ ሐሳብም ባደረግህ ጊዜ በአላህ ላይ ተመካ። አላህ በርሱ ላይ ተመኪዎችን ይወዳልና።}[ኣሊ ዒምራን፡159]

ነቢያዊ ሱንና ውስጥ፦

ወደ ነቢያዊ ሐዲሶች ዐጸድ ከሄድን፣በምስጉን ስነምግባራትና በትሩፋት መርሆዎች የጎመሩ፣ልንቀጥፋቸው የምንችል ብዙ የኢማን ዛፎችን እናገኛለን። ከነዚህ ውስጥ፦

-ነቢዩ  እንዲህ ብለዋል፦ {ገር፣ለስላሳ፣የማያካብድና ለሰዎች ቅርብ የሆነ ሰው ሁሉ በእሳት ላይ እርም ተደርጓል።} [በትርምዚ የተዘገበ]

-የአላህ መልክተኛ  ለአንድ ሶሓቢይ እንዲህ ብለዋል፦ {አላህ የሚወዳቸው ሁለት ባሕርያት አሉህ፦ ቻይነት (ታጋሽነት) እና ረጋ ባይነት።} [በአሕመድ የተዘገበ]

-በተጨማሪም ነቢዩ  እንዲህ ብለዋል፦ {እኔ ዘንድ ያለውን ነገር ከናንተ ቆጥቤ አላስቀምጥም፤ራሱን ቁጥብ ማድረግ የፈለገን ሰው አላህ ቁጥብ ያደርገዋል፤ራሱን ማብቃቃት የፈለገን ሰውም አላህ የተብቃቃ ያደርገዋል፤ራሱን ማጽናናት የፈለገን ሰውም አላህ ያጽናነዋል፤ለማንም ሰው ከትእግስት የበለጠ መልካምና ሰፊ ስጦታ አልተሰጠም።} [በሙስሊም የተዘገበ]

-በተጨማሪም ነቢዩ  እንዲህ ብለዋል፦ {ሀብታምነት በንብረት ብዛት ሳይሆን፣ሀብታምነት የመንፈስ ሀብታምነት ነው፡፡} [በቡኻሪ የተዘገበ]

-የአላህ መልክተኛ  እንዲህ ብለዋል፦ {ሰዎችን የማያመሰግን አላህን አያመሰግንም፡፡} [በአሕመድ የተዘገበ]

-በተጨማሪም ነቢዩ  እንዲህ ብለዋል፦ {ራሳችሁን አስተናንሱ (ትሁት ሁኑ)፤አንዳችሁ በሌላኛው ላይ ወሰን አይለፍ የሚል ከአላህ ተላልፎልኛል፡፡} [በእብን ማጃህ የተዘገበ]

-በተጨማሪም ነቢዩ  እንዲህ ብለዋል፦ {ሁሉም መልካም ሥራ ሶደቃ ነው፤ከመልካም ሥራ ውስጥ አንዱ፣ወንድምህን በፈካ ፊት መቀበል ነው፤ከራስህ ባልዲ ወደ ወንድምህ ዕቃ ውሃ መገልበጥም ነው።} [በትርምዚ የተዘገበ]

በመጨረሻም በእውነተኛው ደስተኝነትና በመልካም ስነምግባራት መካከል ያለውን ግንኙነት፣በጣም ጥብቅ ጽኑና የተሳሰረ ጠንካራ ግንኙነት ሆኖ እናገኛለን። ግብረ ገብነትና መልካም ጠባይ ለሰው ልጆች ደስተኝነትና መታደል ብቸኛው ምንጭ ነው። ያለ ምስጉን ስነምግባር ደስተኝነት ፈጽሞ የሚታሰብ አይደለም። መልካም ስነምግባር በሌለበት ሁኔታ የሰው ልጅ በሕይወቱ ውስጥ ተስፋ መቁረጥን፣ጭንቀትን፣አበሳባና መከራን፣ውጥረትና መብሰልሰልን ብቻ ነው የሚያመርተውና የሚሰበስበው። በመሆኑም ደስተኝነትና መታደልን ፍለጋ፣የሰው ልጅ መልካም ስነምግባራትን እንዲላበስ ከሚገፋፉ አበይት ጉዳዮች ዋነኛው ነው። ምክንያቱም ያለ ምስጉን ስነምግባር ለአንዲት ሰከንድ እውነተኛውን ደስተኝነትንም ሆነ አንድም ቀን እርካታና መታደልን መጎናጸፍ እንደማይችል በእርግጠኝነት ያውቃልና።