እስላማዊ መንግሥት . . ለሰው ልጆች የግድ የሚያስፈልግ ሥርዓት

እስላማዊ መንግሥት . . ለሰው ልጆች የግድ የሚያስፈልግ ሥርዓት

ሦስቱ ወዳጆች ውይይታቸውን ለመቀጠል ሲገናኙ ማይክልና ራጂቭ ከራሽድ ድምጽ ጀርባ የሚረብሽ ባእድ ድምጽ መኖሩን አስተውለው ምን እንደሆነ ጠየቁ። ራሽድም ዜና እያዳመጠ መሆኑንና ለጥቂት ደቂቃ እንዲታገሱት ጠየቃቸው . . ከአፍታ በኋላ እንዲህ በማለት ቀጠለ፦

ይቅርታ፣በዚህ ሰሞን ዜናዎችን መከታተል ቢያንሰ ለኔ ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ እንደምትረዱልኝ ተስፋ አደርጋለሁ . . በዚህ ሰሞን በአገሬ በመከሰት ላይ ያሉትን ሁኔታዎች ትከታተላላችሁ?

ራጂቭ፦ አዎ፣ትኩረት የሚስቡ ዜናዎች ናቸው፤ክስተቶቹም ፈጣንና ተከታታይ ናቸው።

ማይክል፦ ምናልባት ትኩረቴን ይበልጥ የሳበው እስላማውያን የሚባሉት ወደ መድረኩ እየመጡ መሆናቸውና የመንግሥቱን ሥርዓት ወደ እስላማዊ መንግሥትነት ለመለወጥ ጥረት እያደረጉ የመሆናቸው ሁኔታ ሳይሆን አይቀርም . . በእርግጥ አሳሳቢ ነገር ነው።

ራሽድ፦ አሳሳቢነቱ ምኑ ላይ ነው?

ማይክል፦ የሰው ልጆች ሃይማኖታዊ መንግስትን ሞክረውት ውድቀት ገጥሟቸዋል። መራራ ተሞክሮ ነበር። እናም ሃይማኖታዊ መንግስት ያበቃለት ሲሆን ዘመኑም ከመካከለኞቹ ክፍለ ዘመናት ፍጻሜ ጋር ተደምድሟል።

ራሽድ፦ ለመሆኑ ሃይማኖታዊ መንግስት ስትል ምን ማለትህ ነው?

ማይክል፦ ገዥው መደብ በአምላክ ስም እንናገራለን የሚሉ የሃይማኖት መሪዎች የሆኑበት መንግሥት ነው . . ከሃይማኖታዊ መንግሥት አበይት አደጋዎች አንዱ በእግዚአብሔር ስም መብትና እውነታን ለራሱ በሞኖፖሊ የሚቆጣጠር መሆኑ ነው። ይህም ስዩመ እግዚአብሔር ነን፣በርሱ የተመረጥን ነን፣በርሱ ስም እንናገራለን በማለት ቅድስና እና አይነኬነትን ለራሳቸው ስለሚሰጡ ሲሆን፣እነርሱን መቃወም እግዚአብሔርን ተደርጎ ስለሚታይ ያሻቸውን ቢሰሩ ተጠያቂነት የለባቸውም።

ራሽድ፦ በጣም የሚያሳዝነው በእስላማዊ መንግሥት ላይ ያለውን የተሳሳተ እሳቤ ያመጣው ባህላዊ ብዥታ መሆኑ ነው። ሃይማኖታዊ መንግሥትን በተመለከተ በጠቀስከው ሁሉ ከአንተ ጋር እስማማለሁ። ይህም ቀሳውስትና ካህናት በአምላክ ወይም በጣዖታት ስም የሚገዙበት የመንግሥት ሥርዓትና ቲኦክራሲ (theocracy) በመባል የሚታወቀው ሲሆን፣ሥርዓቱ ሕግና ሥርዓቱን ብቻ ሳይሆን ኃይልና ሥልጣኑንም ከሃይማኖት ያመነጫል . . አውሮፓ በመካከለኞቹ ክፍለ ዘመናት በቤተክርስቲያን በተመራው በዚህ ሥርዓተ አገዛዝ የከፋ መከራ የደረሰባት ከሆነ፣እስላም ግን እንዲህ ያለውን አገዛዝ አላየም፣እውቅና ሰጥቶትም አያውቅም። እስላም ውስጥ የሃይማኖት መሪዎች አገዛዝ ሥርዓት ብቻ ሳይሆን የሃይማኖት መሪ ወይም የካህናት መደብ የሚባል የሕብረተሰብ ክፍልም የለም። ያለው ነገር ሊያጠፉና ሊያለሙ የሚችሉ፣ሊተቹ ሊጠየቁ፣ሊቀጡና አስፈላጊ ሲሆን ሊወገዱ በሚችሉ ሰብአዊ ፍጡራን አማካይነት የሚተገበር በሃይማኖትታዊ ርእዮት ላይ የሚመረኮዝ እስላማዊ አስተዳደር ብቻ ነው። እዚህ ላይ ያለው መሰረታዊ ልዩነት እስላማዊ መንግሥት ርእዮተ ዓለማዊ መሰረቱ እስላም የሆነ ምንም ዓይነት ቅድስናም ሆነ ተከህኖ በሌላቸው ሰዎች የሚመራ ሥርዓት መሆኑ ነው። ሕጋዊነቱንና ሥልጣኑን በመለኮታዊ ውክልና አገኘሁ የሚል መሪ እስላም ውስጥ የለም። እንዲገዛ ውክልና የሚሰጠው የግድ ሕዝቡ መሆን ይኖርበታል።

በተጨማሪም በሙስሊሙ ዓለም የታየው የእስላማዊ መንግሥት ተሞክሮ፣በአውሮፓ ከነበረው ሃይማኖታዊ ቤተክህነታዊ መንግሥት በተቃራኒ፣በዘመኑ የበለጸገና የተደላደለ መንግሥትን ያስገኘ የተሳካ ተሞክሮ ነበር።

ራጂቭ፦ በእስላማዊ መንግሥትና በሃይማኖታዊ መንግሥት መካከል ያለውን ልዩነት አውቀናል። በእስላማዊ መንግሥትና ሃይማኖታዊ ባልሆነው መንግሥት መካከል ያለው ልዩነትስ ምን ይመስላል?

ራሽድ፦ ልዩነቱ ሰፊና መሰረታዊ ነው። የማተኩረው ግን፣ዩኒቨርስን፣ሕይወትንና የሰውን ልጅ አስመልክቶ በእስላማዊው እሳቤና በዓለማዊው ሴኩላር እሳቤ መካከል ባለው የልዩነቱ መነሻ መሠረት ላይ ነው። እስላም ውስጥ የመንግሥት ሥርዓት የሚመነጨው፣ሃይማኖትና ሕይወት ተጣጥመውና ተቀናጅተው ሙስሊሙ የሚመራበትንና የሚኖርለትን፣የግለሰብ፣የሕዝብና የመንግሥት ሚና እርስ በርስ የሚደጋገፍበትንና ተጣጥሞ የሚቀናጅበትን የተሟላ ሥርዓት ከሚመሰርት፣እስላማዊ እሳቤ ነው።

ይህን ለመገንዘብ በአላህ ﷻ ግዛት ውስጥ እውነተኛው ቦታችን ምን እንደሆነ ማወቅ ይኖርብናል። የፈጠረን አላህ ﷻ ነው ብለን የምናምን ከሆነ፣ይህች መሬትና ሰማያቱ ሁሉ የርሱ ንብረት መሆናቸውን የምናረጋግጥ ከሆነ፣በዚህ ግዛቱ ውስጥ ሊተገበር የሚገባው ፍላጎት ሕግና ሥርዓት የርሱ ብቻ መሆን እንዳለበት ማረጋገጥ ይኖርብናል። የፈጠረንና ሲሳይ የሚሰጠን አላህ ﷻ ብቻ መሆኑን አምነን የምናረጋግጥ ከሆን፣የርሱ ተገዥ አገልጋዮች ከመሆን ውጭ ምንም ቦታ አይኖረንም . . አላህ ﷻ የኛና በዚህ ዩኒቨርስ ውስጥ ላሉት ሁሉ ብቸኛው ገዥና አስተዳዳሪ ከሆነ ዘንዳ፣ሙሉ በሙሉ ለርሱ ከመገዛትና ለርሱ ከመታዘዝ ውጭ በዚህ ዓለም ውስጥ ምንም እውነተኛ ስፍራ የለንም።

ማይክል፦ ይሁንና ግን፣ብዙ ችግሮች ያሉበትንና ብዙ የተወራበትን ተሞክሮ ዳግም እንድንጎትት የሚያደርገን ምንድነው? እንዴት መኖር እንዳለበት፣ደስተኛ ሕይወትን መምራት የሚያስችለው ምን እንደሆነ፣ሕይወቱን ለማደራጀትና ለመምራት የሚያስፈልገው ሥርዓትና ቅርጹ ምን እንደሆነ፣የሰው ልጅ በገዛ ራሱ መወሰን ይችላል። ከዚያም ነገሮችን ከተሞክሮው እያየ ማሻሻልን የሚከለክለው የለም።

ራሽድ፦ መሰረታዊው እውነተኛ ጥያቄ፣የሰው ልጅ ፍጹማዊ ጌታ የመሆን፣ወይም የሕግና የአስተዳደር ምንጭ የመሆን ብቃት አለውን? የሚለው ነው። ማንኛውንም መሳሪያ እንዴት እንደሚሠራ የማያውቅ ሰው፣የማሰራቱን ኃላፊነት ከወሰደ መሳሪያው ለብልሽት መዳረጉ አይቀሬ መሆኑን እናውቃለን . . ለምሳሌ መንዳት የማይችል ሰው መኪና ከነዳ የዚህ ጅል ሥራ ውጤት ምን ሊሆን እንደሚችል በእርግጠኝነት እናውቃለን። እንዲህ ያለውን አነስተኛ መሳሪያ ያለ ትክክለኛ ዕውቀት ማሰራት የማይቻል ከሆነ፣ፈርጀ ብዙ ገጸ ብዙ ውስብስብ የሆነውን፣ቁጥር ስፍር የሌላቸው ገጽታዎች ያሏቸው የሕይወትና የመኖር ጉዳዮች ያሉትን፣እያንዳንዱ ፈርጅ ቁጥር ስፍር በሌላቸው ውስብስብ ችግሮች የተተበተበ የሆነውን . . የሰብአዊ ፍጡር መሳሪያ የሆነውን ሰው፣ሌላው ቀርቶ ራሳቸውንም በሚገባ የማያውቁ መሰሉ የሆኑ ሰብአዊ ፍጡራን እንዴት አድርገው ሊያሰሩትና ሊመሩት ይችላሉ?!

ሌላው ነጥብ ደግሞ፣ፍትሕ ማግኘት የሚቻለው የሰው ልጆች የአነዋነዋር ሥርዓት፣መላውን የሰው ዘር እርሱ ዘንድ እኩል አድርጎ ከሚመለከት ፈጣሪ አምላክ የተሰጠ ከሆነ ብቻ ነው። መብቶቻቸውን ሊያረጋግጥላቸው የሚችለውም፣ከማንኛውም ዓይነት ግላዊ ዓላማና ግላዊ ጥቅም በላይ የሆነ፣ለአንድ የተለየ ግለሰብ፣ቤተሰብ፣መደብ፣አገር ወይም ሕዝብ ያልወገነ . . ፈጣሪ አምላክ ብቻ ነው። በምድር ላይ ፍትሕ ሊሰፍን የሚችለው በዚህና በዚህ መንገድ ብቻ ነው።

የሰው ልጅ ከግላዊ ዓለማና ጥቅም ሊጠራ አይችልም። ይህ በሁሉም ዘመንና ስፍራ የተቆራኘው ሰብአዊ ድክመት ነው። ፖለቲካ መሪዎችን፣የሃይማኖት መሪ በራህማዎችን፣ፓትርያርኮችን፣የሱፊ ጠሪቃ ሸይኾችን፣ተጽእኖ አሳዳሪ ባለሀብቶችን እንመልከት። ሁሉም ራሳቸውን በተጽእኖ የልዩ መብቶች ባለቤቶች ማድረጋቸውን እናስተውላለን። ከዚህ ስንነሳም በዓለም ላይ ያሉት ህጎችና ደንቦች ሁሉ በነርሱ ተጽእኖና በሥልጣናቸው ስር በመሆኑ ለተራው ሕዝብ የማይሰጡ መብቶች ይሰጣቸዋል። ይህንኑ በተለያየ መንገድ ደንብና ሥርዓት አድርገው ይደነግጋሉ፤በሚዲያዎቻቸው ይህ መደበኛው ሁኔታ እንደሆነ አድርገው ሕዝቦችን ያታልላሉ። እናም እንዲህ ያሉ ሰዎች በሚቆጣጠሩት ሕብረተሰብ ውስጥ ፍትሐዊ ለሆነ መንግሥትና ሚዘናዊ ለሆነ ሕብረተሰብ ግንባታ መሰረት መጣል ይቻላልን?!

በኃይላቸው በመመካት ሌሎች ሕዝቦችን በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ መንገድ ተገዥ ያደረጉ ኃያላን መንግስታትን እንመልከት። የትኛው ሕጋቸው፣የትኛው ተቋማቸውና የትኛው ሥርዓታቸው ነው በደም ስሩ ውስጥ ወገንተኝነትና አድልዖ የማይዘዋወርበት? እነዚህ በፍትሕና በእኩልነት መርሕ ላይ የተመሰረቱ ሕግጋትና ሥርዓቶችን ለሰው ልጆች ያኖራሉ ተብሎ ተስፋ ማድረግ ይቻላል?!

ራጂቭ፦ ወዳጄ ራሽድ፣ለመሆኑ ከእስላም የተለየ የተለያዩ እምነቶችን የሚከተሉና በአገራችሁ የሚኖሩ ንዑሳን ወገኖችን ምን ማድረግ ነው የምታስቡት? . . ለምሳሌ በኛ አገር ሕንድ ውስጥ በመቶዎች ሚቆጠሩ ንዑሳን ሃይማኖቶች ይገኛሉ። እናንተ የመንግሥትን ርእዮተ ዓለማዊ መሰረት እስላም በምታተደርጉ ጊዜ የራሳቸው ያልሆነውን ሃማኖት እንዲቀበሉ ታስገድዳላችሁ ማለት ነው።

ራሽድ፦ ይህን ጉዳይ ማንሳትህ መልካም ነው። በዚህ ረገድ ሦስት ነጥቦችን ማብራራት እፈልጋለሁ። እነሱም፦

አንደኛ፦ ሙስሊም ያልሆነ ሰው፣የራሱ የሆነ መንግስት ምድር ላይ እንዲመሰረት ሃይማኖቱ የማይጠይቀው እየሆነ፣ርእዮተ ዓለማዊ መሰረቱ እስላም በሆነ መንግስት ጥላ ስር መኖሩን ለምን እንደምትቃወሙ ይገርመኛል . . በሌላ በኩል ግን ሙስሊሙ በሴኩላር መንግስት ጥላ ስር ሲኖር፣ሃይማኖቱን የሚቃረኑ ሥርዓቶችን እንዲታዘዝ ታስገድዳላችሁ፤ሃይማኖቱ የማይፈቅድለት እየሆነ ዐቂዳውንና እምነቱን የሚጻረር ርእዮተ ዓለም እንዲቀበል ታደርጋላችሁ።

ሁለተኛ፦ እስላምን የመንግስት ርእዮተ ዓለማዊ መሰረት አድርጎ መውሰድ ሙስሊም ያልሆኑ ዜጎች እስላምን እንዲቀበሉ ማስገደድ ማለት አይደለም። ይህ ተቃውሞ የመነጨው ሃይማኖትን በግለሰባዊ እምነትና በውስጣዊ ስሜትነት ክልል ውስጥ አጥሮ ከሚያስቀረው ሴኩላሪዝም እሳቤ ነው። እስላም ግን ሃይማኖትን ከሰው ልጆች ሁለንተናዊ ሕይወት ነጥሎ በዚህ ጠባብ ክልል ውስጥ አይወስነውም። እስላም ለአንድ ሙስሊም አምልኮ፣ሕግጋትና የሕይወት መመሪያ (ሸሪዓ) ነው። የስልጣኔና የባሕል ርእዮተ ዓለማዊ መሰረት ነው። ሙስሊም ያልሆነው ዜጋ ግን፣ሃይማኖቱን መቀበል ሳይኖርበት እስላምን የስልጣኔና የባሕል ርእዮተ ዓለማዊ መሰረት አድርጎ ለሕጎቹና ለሥርዓቱ ተገዥ መሆን ይችላል . . ልክ ሊብራሊዝምን ወይም ሶሻሊዝምን የተለያዩ እምነቶችንና መንገዶችን በሚከተሉ ርእዮቶቹ ባልወጡባቸው ሕብረተሰቦች ውስጥ መተግበር ይቻላል እንደምትሉት ዓይነት ማለት ነው።

ሦስተኛ፦ መንግስትን በእስላማዊ ርእዮተ ዓለም ላይ መመሰረት ማለት የንዑሳን ዜጎችን መብቶች መድፈቅ ወይም በራሳቸው ሃይማኖታዊ ሕጎች ውስጥ ጣልቃ መግባት ማለት አይደለም። እስላም ለንዑሳን መብቶች መከበር ዋስትና ይሰጣል፤ግለሰባዊ ጉዳዮቻቸውን በተመለከተ በሃይማኖቶቻቸው መሰረት መዳኘታቸውንም አይከለክልም።

ማይክል፦ ዛሬ የምንኖረው ግን እስላም ከተነሳበትና የመንግስት ተሞክሮው ከተተገበረበት ዘመን በተለየ ዘመን ውስጥ ነው። ይህ ጥረት ቢሳካ ወደ ኋላ መቀልበስና የአድኃሪነት እርምጃ ተደርጎ የሚቆጠር ነው! . . እናንተ በዚህ አእምሯችንን ቆልፈን በዛሬው ዘመን አዲስ ሕይወት ውስጥ ተቀባይነትም ሆነ ምክንያታዊነት ወደ ሌለው ሁኔታ ልትወስዱን ትፈልጋላችሁ።

ለምሳሌ ያህል፣አራጣንና ወለድን ዛሬም ድረስ የተከለከለ ሐራም ማድረጋችሁን ቀጥላችሁበታል። ወለድና አራጣ ግን ለማንኛውም ዘመናዊ መንግስት ግዴታና አይቀሬ የሆነ የኢኮኖሚ ሥርዓቱ አካል ነው።

ራሽድ፦ ወዳጄ አነጋገርህ በዚህ ምሳሌና በሌሎቹም ምሳሌዎች እውነታ በጎደላቸው መነሻዎች ላይ የተመሰረተ፣የመንግስትን ቅርጽና ዓለም አቀፉን ሥርዓት በተመለከተም ከአንድ የተወሰነ እሳቤ የተንደረደረ ነው። ያም ዛሬ ራሱን በራሱ በኛ ላይ በተጨባጭ ሁኔታነት ጭኖ የምንኖርበት ዓለም አቀፋዊው ሥርዓት ሲሆን፣የኢኮኖሚ ሥርዓቱ ከወለድና ከአራጣ ጋር መቆራኘት፣በሰው ልጆች ላይ ያስከተላቸውን ጣጣዎችና የበዙ አፍራሽ ተጽእኖዎችን ችላ የሚል ምሳሌም ነው።

እርግጥ ነው እስላም አራጣና ወለድን እርም አድርጎ ይከለክላል፤ይሁን እንጂ አራጣና ወለድ ግን የኢኮኖሚ አይቀሬ ግዴታዎች አይደሉም።

ለአራጣና ለወለድ ጥሪ ሚያደርጉት በዓለም ያሉ ታላላቅ ካፒታሊስቶችና ሞኖፖሊስቶች ሲሆኑ፣አይቀሬ ግዴታ አስመስለው ሕዝቦችን ያጭበረብራሉ። እውነቱ ግን ግዴታነቱ በራሳቸው ካፒታሊስት ዓለም ውስጥ ብቻ መሆኑ ነው። ያም ሆኖ ግን በምዕራቡ ካፒታሊስት ዓለም ሚገኙ አንቱ የተባሉ ታላላቅ የምጣኔ ሀብት ኤክስፐርቶች፣የወለድ ሥርዓቱን በመኮነን አይቀሬ ውጤቱ፣በጊዜ ሂደት በከባድ የኢኮኖሚና የፋይናንስ ቀውሶች ውስጥ መዘፈቅና ሀብት በጥቂቶች እጅ ብቻ በመከማቸቱና ብዙኃኑ አጦች ቁጥራቸው እተበራከተ በመሄዱ የሚያስከትሉትን ማሕበራዊ ቀውሶች መጋፈጥ ብቻ መሆኑን ያስጠነቅቃሉ። በቅርቡ የተከሰተው ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ቀውስ፣ያስከተላቸው ዘርፈ ብዙ ችግሮችና አደጋዎች፣ባለፈው ክፍለ ዘመን ሰላሳዎቹ ውስጥ ተከስቶ የነበረው የኢኮኖሚ ቀውስ . . እነዚህን ሁሉ ካስተዋልን የአደጋውን ግዝፈት መገመት እንችላለን።

ከእስላማዊው ሥርዓት ተአምራት አንዱ የካፒታሊዝም ሁለት ማእዘናት የሆኑትን ወለድና ሞኖፖሊን፣የካፒታሊዝም ሥርዓት ከማቆጥቆጡ አንድ ሺ ዓመት ያህል አስቀድሞ እርም አድርጎ መከልከሉ ነው . . ወድ ወዳጄ፣ስለዚህም እስላማዊ መንግስት ሸሪዓዊ እስላማዊ ግዴታ ብቻ ሳይሆን ሰዋዊ ሰብአዊ ግዴታም ጭምር ነው።