ሰብአዊ ፍጡር . . እንዲገለል ሲደረግ

ሰብአዊ ፍጡር . . እንዲገለል ሲደረግ

ራጂቭና ራሽድ ከማይክል ቀድመው ወደ ውይይት ክፍሉ ገቡ። በራጂቭ የተጀመረው ቀጣዩ ምልልስ በሁለቱ መካከል ቀጠለ።

ራጂቭ፦ልንነጋገርበት የምፈልገውና በነገሩ ላይ እስላም ያለው አቋም ምን እንደሆነ ማወቅ የምሻው ጉዳይ አለኝ።

ራሽድ፦ በጣም ደስ እያለኝ፣ቀጥል . .

ራጂቭ፦በአገሬ በሕንድ የተገለለ (ካስት) በመባል የሚታወቅ የሕብረተሰብ መደብ ይገኛል። ዛሬ እንኳ ‹‹ሃሪጃን›› ወይም የእግዚአብሔር ልጆች የሚል መጠሪያ ተሰጥቷቸዋል። መጠሪያውን የሰጣቸው ታሪካዊው የሕንድ መሪ ማሃተማ ጋንዲ ነው . . የሕንድ መንግስት ከ1949 ዓል ጀምሮ ‹‹ካስት›› የሚለውን ቃል መጠቀም ያገደ ቢሆንም፣ተጨባጭ ሁኔታውና ጥናቶችም ጭምር በሕንድ የገጠር አካባቢዎችና በትናንሽ ከተሞች ማግለል ዛሬም ድረስ እንደቀጠለ መሆኑን ያመለክታሉ።

ራሽድ፦ ለመሆኑ የማግለል ችግር ምንድነው?

ራጂቭ፦ማግለል ተራ ችግር ሳይሆን አስከፊ ሰቆቃ ነው . . የሰው ልጅ ሰብአዊነትና መብቶቹ በአስከፊ ሁኔታ የሚረገጡበት ሰብአዊ ቀውስ ነው . .

እዚህ ላይ ማይክል ይቀላቀላቸውና ሰላምታ ያቀርብላቸዋል . .

ራሽድ፦ ሰላም ማይክል፣ራጂቭ ከአፍታ በፊት ውይይቱን ከፍቷል። ራጂቭ በመናገር ላይ እያለ ርእሰ ጉዳዩን ማወቅ ትችላለህ . . ራጂቭ ቀጥል . .

ራጂቭ፦የችግሩ መንስኤ ሕብረተሰቡን በመደቦች የሚከፋፍለው የሕንዱ ሃይማኖት ነው። ከሁሉም የበለጠ ከበሬታ የሚሰጠው መደብ የበራህሞች መደብ ሲሆን፣በእምነቱ መሰረት እነዚህን የፈጠራቸው በራህማ አምላክ በአፉ ነው። መምሕር፣ካህንና ዳኛ ከነርሱ መደብ ነው። በደረጃ የሚከተሉት ካሽተሮች ናቸው። እነዚህ ደግሞ አምላክ ከሁለት ክንዶቹ የፈጠራቸው ሲሆኑ፣ይማራሉ፤መስዋእቶችን ያቀርባሉ፤ለመዋጋት መሳሪያ ይታጠቃሉ። ከዚህ የሚቀጥለው ወይሾች ሲሆኑ፣አምላክ ከጭኑ የፈጠራቸው ናቸው። ያርሳሉ፤ይነግዳሉ፤ገንዘብ ይሰበስባሉ፤ለሃይማኖታዊ ትምህርት ቤቶች ወጭ ያወጣሉ። የታችኛውን ደረጃ የሚይዙት ደግሞ ሹደሮች ሲሆኑ፣አምላክ ከሁለት እግሮቹ የፈጠራቸው ናቸው። ከአገር በቀል ጥቁሮች ጋር የካስቶችን (የተገለሉትን) የሚወክሉት ሹደሮች ናቸው። የነርሱ ሥራ ከላይ የተጠቀሱ ሦስቱን የተከበሩ መደቦችን ማገልገል ሲሆን፣የተናቁና የወረዱ ሥራዎችን በመስራት ላይ ይሰማራሉ።

ራሽድ፦ ማለት ያሰብከው ገብቶኛል . .

ራጂቭ፦ይቅርታ፣ገና አላወቅህም።

ማይክል፦ ከዚህ የከፋ ሌላ ነገር አለ ማለት ነው? ይህ የመደብ ክፍፍል ዛሬም ድረስ ይሠራበታል?!

ራጂቭ፦አዎ፤ካስቶች በዚህ ክፍፍል መሰረት የሚስተናገዱበት ሁኔታ ዛሬም ድረስ በተለይም በገጠር አካባቢዎች መኖሩን ለራሽድ ነግሬ ነበር። በዚህ መደብ ላይ የሚፈጸመው ግፍና ኢሰብአዊ ጭቆና ለማሰብ የሚከብድ ነው። ከልደት በፊት በሦስተኛው ምእተ ዓመት የተጻፈው የሕንዱ መኖ ሕጎች የተመሰረቱት የሹደርና የካስቶችን መደብ በማንቋሸሽ ላይ ነው። በሕጎቹ መሰረት ለምሳሌ ያህል የሕንዱን ሃይማኖታዊ ጉዳዮችን ለሹደራዊ ያስተማረ ማንኛውም ሰው፣ከሹደራዊው ጋር ወደ ገሀነም ይሄዳል . . ካስቶችም ከመንደሩ ወጣ ብለው መኖር ሲኖርባቸው፣ያልተሰበሩ ደህና እቃዎችንም ከመጠቀም ይከለከላሉ። ከውሾችና ከአህዮች በስተቀር ምንም ዓነት ንብረት ሊኖራቸው አይችልም። የሙታን ሰዎችን ልብሶች ብቻ እንጂ ሌላ መልበስ አይችሉም። ሁሌም ያለ ጫማ መሄድ አለባቸው። የሴቶቻቸው ጌጣጌጥም ከብረት ብቻ የተሠራ መሆን ይኖርበታል። ሁሉም ግንኙነቶቻቸው እርስ በርሳቸው መካከል ብቻ የተወሰነ መሆን ይገባል። አንድ ሹደር ስለ ሃይማኖት ጉዳዮች ከተናገረ የፈላ ዘይት አፉ ውስጥ ይጨመራል!! . . ከዚህ ይበልጥ አስከፊውና መራራው ደግሞ፣ዛሬም ድረስ ከጧቱ ሦስት ሰዓት በፊትና ከሰዓት ከዘጠኝ ሰዓት በኋላ የካስቶች ጥላ በነዚህ ወቅቶች ረዥም ስለሚሆንና በራህማዎችን ጥላው አርፎባቸው እንዳያረክሳቸው ስለሚፈሩ ካስቶቹ ከቤቶቻቸው እንዳይወጡ ይከለከላሉ . . በራህማው የካስቱ ጥላ ከበከለው ከርክሰቱ ሳይታጠብ መብላትም ሆነ መጠጣት አይችልም!! . .

ማይክል፦ የማይታመን ነው! እንዲህ ያለ ነገር በዛሬው ዘመናችን ይከሰታል?! ከሕንድ ማህበረሰብ ምን ያህል መቶኛ ይይዛሉ?

ራጂቭ፦ካስቶች ከሕዝቡ ቀጥር 45% ማለትም ከሕንዱ እምነት ተከታዮች 80% ይሆናሉ። የተቀሩት ሦስቱ የሕንዱ መደቦች ግን 11% ብቻ ናቸው።

ራሽድ፦ ካለፈው ክፍለ ዘመን አርባዎቹ ጀምሮ የሕንድ መንግስት ‹‹ካስት›› የሚለውን ቃል መጠቀም ከልክሏል ብለህ ነበር። እናም ድርጊቱም የተከለከለና በሕግም የሚያስጠይቅ ነው ማለት ነው።

ራጂቭ፦ትክክል ነው። ችግሩ ያለው የጠራ ዘርና ያልጠራ ዘር በሚለው ላይ የሚመረኮዘው የዘረኝነት ቋጠሮ ከሕንዱ ሃይማኖት አበይት መሰረቶች አንዱ ተደርጎ የሚወሰድ በመሆኑ ላይ ነው። ከሕንዱና ከሦስቱ ‹ምርጥ› መደቦች ውጭ የሆነውን ሰው የረከሰና ያልጠራ አድርገው ይቆጥሩታል።

ራሽድ፦ በእርግጥ በግፍና የሰውን ልጅ ሰብእና በሚያራክስ፣በምንም መልኩ ሰው ተጠያቂ ባልሆነበት ነገር አድልዖ በማድረግ ላይ የቆመ አስቀያሚ ሥርዓት ነው። ይሁንና ያልከውን ነገር እስላም በዚህ ላይ ከሚኖረው እሳቤና ከሚያራምደው አቋም ጋር ምን ያያይዘዋል?

ራጂቭ፦የተገለሉ ካስቶች በተለይም ከነገርኳችሁ እገዳ በፊት የክርስትና ሃይማኖት ተከታይ በሆኑት እንግሊዞች ቅኝ አገዛዝ ስር እየኖሩ፣ክርስትናን የሚሰብኩ ቁጥራቸው የበዛ የሚስዮን ተቋማትም እያሉክርስትናን ሳይመርጡ አብዛኞቻቹ እስላምን መርጠው በመቀበል ይሰልሙ ነበር።

ራሽድ፦ ምናልባት እስላም ለሰው ልጅ ያለውን ከበሬታ በተግባር በማስተዋላቸው ሊሆን ይችላል።የእስላምን እውነታና ሰብአዊ መብት በሃይማኖቱ ውስጥ የሚይዘውን ደረጃ ያወቀ፣ትንሽና ትልቁን፣ደሃና ሀብታሙን፣ሁሉንም በእኩልነት የሚያስተናግድና ለሰው ልጆች የሚሰጣቸውን ነጻነቶች የተረዳ ሰው፣ወደዚህ ሃይማኖት ማቅናቱና ሃይማኖቱን መቀበሉ አይቀሬ ነው . . ከሙስሊሞች ጋር አብረው በመኖራቸው ይህን ሁሉ በተግባር ስለተመለከቱ ነው ብዬ አስባለሁ።

ማይክል፦ እስላም ነጻነቶችንና ሰብአዊ መብቶችን ያከብራል ብለህ ልታሳምነን ትፈልጋለህ? . . ነጻነቶችና ሰብአዊ መብቶች የታወቁት በሃይማኖቶች አማካይነት ሳይሆን፣መሰረታቸውን በጣሉት ምዕራባውያን ፈላስፎችና ርእዮተኞች አማካይነት ነው። እውን የሆኑትም ሕዝቦች ነጻነቶቻቸውንና መብቶቻቸውን ለማስከበር በግፍና በጭቆና ላይ ባካሄዱት ረዥምና መራራ ትግል ነው . . እነዚህ መብቶች እስላም ውስጥ የሉም፤የእምነት ነጻነትና እስላምን በመተው ወደ ሌላ ሃይማኖት የመለወጥ መብት የት አለ? ሀሳብን በነጻነት የመግለጽ መብትስ? የሴቶች መብትስ የት አለ? . . እባክህን በሃይማኖትህ ላይ ያለህ ጽኑ እምነት እውነቱን እንትሸሽግ አያድርግህ . .

ራሽድ፦ ውድ ወዳጄ፣የፍልስፍና ክርክር ሰፊ ግንባር ነው የከፈትከው . . ምዕራቡ ዓለም በሰብአዊ መብቶች ጥበቃ ወደ ፍጹማዊ ምሳሌነት ማማ የደረሰ ይመስል፣ሙሉ በሙሉ በራሱ በሚተማመን ድል አድራጊ ቅላጼ እየተናገርክ መሆንህን እየታዘብኩ ነው . . ምዕራቡ ዓለም ይህን ተምሳሌታዊ ደረጃ ተቆናጥጦ ከሆነ፣በአይሁዶች ላይ የተፈጸመውን ሰቆቃ ሰለባዎች ቁጥር አሳንሰው በማቅረብ ወይም ክስተቱን ከነጭራሹ በማስተባበል ‹‹ሀሳባቸውን በመግለጻቸው›› ብቻ፣በብዙ ተመራማሪዎች፣ጸሐፍትና የታሪክ ጠበብቶች ላይ በፍርድ ቤቶች የተላለፈባቸውን የጥፋተኝነት ውሳኔዎች ምን እንበላቸው? . . ይህ ሀሳብን በነጻነት የመግለጽ፣መረጃን የማግኘትና፣የምርምርና የጥናት መብቶችን መንፈግ አይደለምን?! በንጉሳዊቱ እንግሊዝ አንድ ሰው ሪፑብሊካዊ ፓርቲ የመመስረት፣ወይም በአገረ ጀርመን የናዚን ፓርቲ የማቋም መብት ሊኖረው ይችላልን? እኔ ሙስሊሙ ሃይማኖቴ መብት የሰጠኝ ቢሆንም እንኳ፣እንግሊዝ አገር ውስጥ ሕጋዊ በሆነ መንገድ ሁለተኛ ሚስት ማግባት እችላለሁን? መንግስት እነዚህን መብቶች ለማፈንና ነጻነቶችን ለመገደብ ጣልቃ ይገባ የለምን? . .

ማይክል፦ እነዚህ ነጻነቶችና መብቶች በመሰረቱ ከሰብአዊ መብቶች ጋር ይጻረራሉ። መብቶቹ ሁላችንም ልናከብራቸው በሚገቡ ሕጎችና ድንጋጌዎች መልክ ተቀርጸውና ተደራጅተው የጸኑ ናቸው። ሆሎኮስት መከሰቱን መጠራጠር ማለት በግልባጩ ጸረ ሴማዊነት ማለት በመሆኑ፣ዘረኝነትና ጥላቻን ማሰራጨት ነው። ‹‹ወንድማማችነትን›› እና ‹‹እኩልነትን››ም ይጻረራሉ። ሌሎች መብቶችን የሚገድቡ ቢሆኑ እንኳ ‹‹አይነኬ›› እና ‹‹የተቀደሱ መርሆዎች›› በመሆናቸው ከዚህ መዛነፍ አይቻልም። የጠቀስካቸውን ፓርቲዎች በነዚያ አገራት መመስረትን በተመለከተም ነገሩ ይኸው ነው። ሌላ ሚስት የማግባትህ ጉዳይም ከ‹‹ግላዊ ስሜትና ከራስ ሕሊና›› ማእቀፍ ገደብ ውጭ የሆነ፣የሕግ፣የማሕበራዊ ውልና አንተ የምትኖርበት ሕብረተሰብ አብላጫው ሕዝብ ወዶ የተቀበለውን ሥርዓት የመጣስ ሁኔታ በመሆኑ፣የሌሎች ግለሰቦችን (ፈቃደኛ ብትሆን እንኳ የሴትን) መብት የሚገፋ በመሆኑም ጭምር፣በ‹‹እምነት ነጻነት›› መብት ውስጥ የሚካተት አይደለም። በዚያውልክ ግን ካስፈለገህ ከጋብቻ ማእቀፍ ውጭ ፈቃደኞች እስከሆኑ ድረስ ከሌሎች ሴቶች ጋር የፍቅር ግንኙነት ማድረግ ይፈቀድልሃል . .

ራሽድ፦ በጣም ጥሩ . . እናም እኔ ጭቆና፣መብትና ነጻነቴን መጋፋት አድርጌ የምወስደውን አንተ ግፍና መጋፋት የሌለበት ደንብና ሥርዓት አድርገህ ትቆጥራለህ ማለት ነው። ይህ ደግሞ ወዳጃችን ራጂፍ የነገረንና ሁላችንም ተግባራቸውን ያጥላላን የሕንዱ ሃይማኖት ሰዎች በተጨባጭ የሚፈጽሙት ነገር ነው። አድራጎታቸውን የሌሎች ሰዎች መብት መጋፋት አድርገው ይቆጥራሉ ብለህ ታስባለህ? . . በእርግጥ አታስብም . .

ራጂቭ፦አነጋገርህ ድርጊታቸውና የሚፈጽሙት አስከፊ የመደብ ጭቆና ትክክለኛ ነው የሚል እንደምታ እንዳይኖረው እሰጋለሁ።

ራሽድ፦ በፍጹም . . የፈለግሁት መብቶችንና ነጻነቶችን ከመነጩበት የእሴትና የስነምግባር ሥርዓትም ሆነ ከሚቀርጻቸውና ከሚያደራጃቸው አጠቃላዩ የሕግ ማእቀፍ ነጥለን መመልከት እንደማንችል ማብራራት ነው። እነዚህን መብቶችና ነጻነቶች የምር ለማጤን ከፈለግን፣መመርመር ያለብን የቆሙበትን እሴቶችና መርሆዎች እንጂ፣መተግበሪያዎቻቸውንና የሰዎቹን አድራጎቶች መሆን የለበትም። በዚህ ከተስማማን በሰብአዊ መብትና በነጻነት መስኮች ውስጥ መንጸባረቁ አይቀሬ የሆነ . . መሠረታዊ ልዩነት በእስላማዊው እሳቤና በምዕራባዊው እሳቤ መካከል መኖሩን እንገነዘባለን። የዚህ ልዩነት መነሻ መሰረት፣የሰውን ልጅ፣ዩኒቨርስንና ሕይወትን በሚያካትተው አጠቃላዩ እይታ ውስጥ የ‹‹ሰው››ን ምንነት፣የ‹‹መብቶች››ን እና የ‹‹ነጻነትን›› እውነታ የሚመለከተው የእሳቤ ልዩነት ነው . . ወዳጄ ማይክል፣ምዕራባዊው ሰው መብቶችንና ነጻነቶችን አስመልክቶ በሚያራምደው እሳቤ መሰረት የ‹‹ሃይማኖት›› የ‹‹ወንድማማችነት›› እና የ‹‹እኩልነት›› ጽንሰ ሀሳቦችን፣‹‹የጸኑ›› እና ‹‹የተቀደሱ›› ብሎ ሲያቀርብ የሆነውም ይኸው ነው። እስላም ውስጥ ግን እነዚህ ጽንሰ ሀሳቦች ከዚህ የተለዩ ናቸው።

እስላም ውስጥ ስላለው የሰብአዊ መብቶችት መርሕ የምንነጋገን ከሆነ ደግሞ፣ከሃይማኖታዊ መንደርደሪያ በመነሳት ሕብረተሰቡ በሙሉ ሊወጣው ወደሚገባ ግዴታነት ደረጃ ከፍ የተደረገ ሆኖ እናገኛለን። እስላም ከሕግ ሥርዓቶቹና ከደንቦቹ በተጨማሪለመብቶቹ፣ከአጠቃላይ ስንምግባራት ከእዝነትና ከመልካም ፀባይ የተቀናጀ ማእቀፍ አኖሯል። ከዚህም አልፎ እስላም ውስጥ መብቶች በሰው ልጆች ብቻ ላይ የሚቆሙ ሳይሆን ወደ እንስሳትም ይሻገራሉ።

ማይክል፦ በሃይማኖታችሁ ውስጥ እንስሳት መብት ይኖራቸዋል ብዬ ጭራሽም አስቤ አላውቅም።

ራሽድ፦ በሰው ልጅ ላይ ጉዳት ማድረሱ የተረጋገጠ ወይም የሚጠበቅ እስካልሆነ ድረስ እንስሳትን መጉዳትና ማወክ እስላም ከልክሏል። ለዒላማ መለማመጃነት ወይም ለማታገል ሲባል እንደሚደረገው፣ለጨዋታና ለመዝናኛ ብሎ እንስሳትን መግደልም የተከለከለ ነው። ለምግብነት እንዲውል እንጂ እንዳይታረድም ታዟል። አንድ ሙስሊም እንስሳውን ለመብላት በሚያርድበት ጊዜ ያን መፈጸም የሚችለው በፈጣሪ አምላኩ ፈቃድ፣እርሱ በደነገገው መንገድና ስሙን በማውሳት መሆን ይገባል። አስተራረዱም ቢሆን የሚታረደውን እንስሳ ስሜት ግምት ውስጥ የሚያስገቡ ደንቦች ያሉት ሲሆን፣ሰዎች ከአላህ መንገድ ሲያፈነግጡና እርስ በርሳቸው ሲተራረዱ እንኳ ይህ ዓይነቱን ደንብ አናይም። የሚታረድበትን ቢላዋ ከፊቱ ሆኖ መሞረድ፣ሌላውን እንስሳ እያየው ማረድ . . የተከለከለ ነው። ለእንስሳት እንኳ ይህን ሁሉ መብት የሚሰጥ ሃይማኖት የሰው ልጆችን መብት ይጋፋል ብለህ ማሰብ ትችላለህ?!

ራጂቭ፦ጉዳዩ በሌላ ውይይት የበለጠ ማብራሪያ ሊሰጥበት የሚገባ ነው ባይ ነኝ።