የዘላለማዊነት ጉዞ

የዘላለማዊነት ጉዞ

ማይክል ወደ ቻት ሩም እንደገባ ለሁለቱ ወዳጆቹ ሰላምታ አቀረበ። ራጂቭ ሰላምታውን ሲመልስ ራሽድ ግን እንዲህ ሲል መናገር ቀጠለ፦

ትንሽ ታገሱኝማ! . . ትኩረት የሚስብ ትእይንት ትመለከቱ ዘንድ አዘጋጅላችኋለሁ . . የሊቮርኖ ቡድን ተጫዋች የሆነው ሞሪስኒ በኢጣሊያ ላሊጋ ከቢስካራ ክለብ ጋር ሲጫወቱ እንዴት እንደወደቀ አይታችኋል? . . ሜዳው ላይ ወድቆ ወዲያውኑ ሕይወቱ አልፋለች. . በሰላም ሲጫወት ቆይቶ በድንገት ወድቆ በመሞቱ ጨዋታውን ሲከታተሉ በነበሩ ተመልካቾች ላይ ትእይንቱ ከፍተኛ ድንጋጤ ፈጥሮ ነበር።

ማይክል፦ ከዚህ ይበልጥ የሚገርመው ግን የቦልተን ቡድን ተጫዋች የሆነው ምዋምባ በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ውድድር ከቶተንሃም ጋር ሲጫወቱ የወደቀው አወዳደቅ ነው። ተጫዋቹ ልቡ በመቆሙ ምክንያት ራሱን ስቶ ሲወድቅ ሁሉም ሰው ሞቷል ብሎ ደምድሞ ነበር። በጣም አልፎ አልፎ ብቻ በሚከሰት አጋጣሚ ልቡ ሥራውን ሙሉ በሙሉ ካቆመ ከ78 ደቂቃዎች በኋላ ዳግም መሥራት ቀጠለ። ሁኔታውን ሐኪሞች ለ78 ደቂቃ የቆየ ሞት አድርገው ሲወስዱት፣የቡድኑ ሐኪም ‹‹የማይታመን ነው፤ምዋምባ በዚህ ሁኔታ ይድናል ብለን ከቶም አልጠበቅንም ነበር›› በማለት አግራሞታቸውን ገልጸዋል። እናም ምዋምባ ከሞተ በኋላ ዳግም ወደ ሕይወት ተመልሷል!

ራሽድ፦ ሞት መላው የሰው ልጅ የሚስማማበትና እውቅና የሚሰጠው ብቸኛው እውነታ ነው . . ግና ከሞት በኋላ ምን ይኖር ይሆን? የሁሉም ነገር ፍጻሜ ይሆን ወይስ ብዙ ሰዎች እንደሚያምኑት የወዲያኛው የኣኽራ ዘላለማዊ ሕይወት መጀመሪያ ይሆን?

ራጂቭ፦ በወዲያኛው መጪ ሕይወት ማመን የሰው ልጅ ከተፈጠረበትና ምድር ላይ ከኖረበት ጊዜ ጀምሮ አብሮት የኖረ ጥንታዊ እምነት ነው። በቁፋሮ የተገኙ ቅርሶችና የታሪክ ማስረጃዎች ይህ እምነት በጥንታዊ ሥልጣኔዎች ውስጥ የነበረ መሆኑን ያመለክታሉ። የጥንት ግብጻውያን፣የማያ ነገዶች፣ሮማውያን፣በጤግሮስና ኤፍራጠስ ሸለቆ የኖሩ ሕዝቦችና ሌሎችም . . ያውቁት ነበር። እምነቱን በውስጣቸው ያካተቱት መለኮታዊ ሃይማኖቶች ብቻ ሳይሆኑ፣እንደ ሕንዱይዝም፣ቡድሂዝምም፣ ኮንፍሽያኒዝም፣ዞሪስትሪያኒዝምና ሳቢያኒዝም ያሉ . . ሰው ሠራሽ እምነቶችም ያውቁታል።

ራሽድ፦ ያልከው ትክክል ነው። የተቀሩት ነቢያትና መልእክተኞች ለሕዝቦቻቸው እንዳቀረቡት ሁሉ፣የእስላም ነቢይም ለዚህ እምነት ጥሪ አድርገዋል። በዚህ ዐቂዳ ማመን በሁሉም ዘመንና ስፍራ ከእስላም የእምነት ማእዛናት አንዱ ነው። ይህ እምነት በማይኖርበት ሁኔታ በአላህ፣በመለኮታዊ መጻሕቱና በመልእክተኞቹ ማመን ትርጉም የለሽ ይሆናል።

ማይክል፦ ይሁን እንጂ እምነቱ በሰዎች ሕይወት ውስጥ የሚያሳድረው ተጽእኖ የተለያየ መሆኑን ነው ያስተዋልኩት። በስነምግባራቸውና በግንዛቤያቸው ውስጥ የእምነቱ አሻራ የሚታይባቸው ሰዎች ቁጥርም አነስተኛ ነው።

ራሽድ፦ ልክ ነህ፤በንድፈ ሀሳባዊ እምነት ደረጃ ሰው ሁሉ አምኖ ይቀበለዋል፤የዚህን ዐቂዳ ተጨባጭ ሕያው ገጽታ አእምሯቸው ውስጥ የሚያመላልሱት ግን ጥቂቶች ብቻ ናቸው . . ለዚህ አስረጅ የሚሆነው፦ በጦርነት ወቅት የአየር ጥቃት መኖሩን የሚያስጠነቅቅ የአደጋ ሳይረን ሲያስተጋባ . . ጎዳናዎች በሙሉ ከእግረኞችና ከተሸከርካሪዎች ነጻ ይሆናሉ ተብሎ ይታሰባል። ይህን የማያደርግ ሰው ካለ እንኳ እንደ እብድ ሊቆጠር ይችላል . . ይህ ሁሉ ለዚች ዓለም ትንሹ አደጋ ለመጠንቀቅ ከሆነ፣ከዚህ እጅግ ለከፋና ለገዘፈ አደጋስ? መምጫው አይቀሬ መሆኑን ሰዎች ለሚያምኑበትና የዚህ ዩኒቨርስ ፈጣሪ አምላክ ያስጠነቀቀው፣በሁሉም ነቢያትና መልእክተኞቹ አንደበት ያሳወጀውና ያረጋገጠው አደጋ ጉዳይስ? ምክንያታዊ የሚሆነው ለዚህ የአምላክ ማስጠንቂቂያ የሚሰጠው ምላሽ ከሁሉም የላቀና የበረታ መሆን ያለበት መሆኑ ነው።

ማይክል፦ እንደሚመስለኝ የማስጠንቀቂያ ሳይረኖች የሚያስጠነቅቁትን አደጋ ሰዎች ያያሉ ይሰማሉ። በተግባር ባያዩት እንኳ በሌሎች ሁኔታዎችና ስፍራዎች በተከሰቱት አደጋዎች ውጤቱን አይተው አስተውለውትም ሊሆን ይችላል። መጪውን የወዲያኛ ዓለም በተመለከተ ግን እንዳናየው በመካከላችን ያለው የሞት መጋረጃ ስለሚጋርደን ዛሬ አይታየንም . . በሁለቱ ሁኔታዎች መካከል ያለውን የእርግጠኝነት ልዩነት የፈጠረው ይህ ነው።

ራሽድ፦ የተናገርከው ትክክል ነው። ነገር ግን የሰው ልጅ በስሜት ሕዋሳቱ ብቻ ሳይሆን በአእምሮውም ወደ እውነታዎች ደርሶ እርግጠኛ መሆን ይችላል ተብሎ ይታሰባል። በነዚህ ሰዎች ዘንድ ለሚስተዋለው እርግጠኛ ያለመሆን ድክመት፣መንስኤው አእምሯቸውን አለመጠቀማቸውና አለማስተንተናቸው ነው። ነገሮችን በአንክሮ ቢመለከቱ፣ቢያስተውሉና አእምሯቸውን አሰርተው ቢያስቡበት ግን፣በዓይናቸው የሚመለከቱት ከእይታቸው ከራቀው የበለጠ እርግጠኝነት እንደሌለው ይገነዘቡ ነበር።

በተጨማሪም በዓይን እነሱን ለመመልከት ወይም በተግባር ለመሞከር መጠበቅ ማለት፣አንዴ ብቻ ተከስተው ከማለፍ ውጭ ሌላ መሆን የማይችሉ በመሆናቸው ለባለቤቱ ጥፋትና አደጋ ማለት የሆኑ ብዙ ነገሮች አሉ። አንድ ሰው ለሌላው ሰው ከሰማይ ጠቀስ ሕንጻ ላይ ራሴን ወርውሬ ምንም ሳልሆን መሬት አርፋለሁ ቢለውና ሞክርና እንየው! ቢባል ሙከራው የመጀመሪያውና የመጨረሻው ከመሆኑም በላይ የሞካሪው ፍጻሜም ነው የሚሆነው። የሰውየውን አባባል ትክክለኛነት ወይም ስህተተኛነት የምናረጋግጠው በዚህ ሙከራ ሳይሆን፣አእምሮን በማሰራት፣በማስተንተን፣ በማስተዋል፣ከቀዳሚ ሙከራዎች ጋር በማነጻጸር፣ሊሆን የሚችለውን አስቀድመን በማስላት ሙከራውን ማድረግ ሳያስፈልግ ውጤቱ ምን እንደሚሆን በመገንዘብ ነው።

ራጂቭ፦ ስለዚህም ወደ እርግጠኝነት ለመድረስ ይህን ዐቂዳ በአእምሮ ማስረጃዎችና በሳይንሳዊ ንጽጽሮሽ በመጠቀም ማስረዳት ይኖርብናል ማለት ነው።

ራሽድ፦ ያን ማድረግ ችግር የለውም። እኔ 'ምለው ግን ከሁሉም የበለጠ ዋነኛው ማስረጃ ይህን በነገረን ወገን እውነተኛነት ላይ የሚኖረን መተማመን መሆኑን ነው። በመልእክተኞቹ አንደበት የነገረን አላህ ﷻ ነው። በአላህ ﷻ ማመን የሚጠይቀው ግዴታም የሚያስከትለው ውጤትም ይኸው ነው። እርሱ ከኛ ይበልጥ ለኛ የሚበጀውንና የሚጠቅመን የሚያውቅና ለጥቅማችን ከማንም በላይ የሚጓጓ ነውና።

የጠየቅኸውን የአእምሮ ማስረጃና ሳይንሳዊ ንጽጽሮሽ ብዛት ያለው ሲሆን፣ጥቂቱን ብቻ ቀጥዬ አቀርባለሁ፦

የመጀመሪያው ማስረጃ፦ መጀመሪያውኑ ከምንም ፈጥሮ ማስገኘትን ራሱን ዳግም ከሞት ለማስነሳት አስረጅ አድርጎ መውሰድ ነው። መጀመሪያ የፈጠረን አላህ ﷻ መሆኑን አምነን የምንቀበል ከሆነ፣መጀመሪያ ከምንም ፈጥሮ ያስገኘን ከሞት በኋላ ዳግም ሕይወት ዘርቶብን ሊቀሰቅሰን ቻይ ነው። ይህም ብቻ ሳይሆን የሁለተኛው ሕይወት መከሰት የመቻሉ ሁኔታ ከ‹ንድፈ ሀሳብ› አኳያ ከመጀመሪያው ሕይወት ይበልጥ የጠነከረ ነው . .

ሁለተኛው ማስረጃ፦ የቁሶችና የንጥረ ነገሮች ከአንድ ሁኔታ ወደ ሌላ ሁኔታ መለወጥ፣ከአንድ ባህርይ ወደ ሌላ ባህርይ መቀየር ነው። ቁርኣን ለዚህ ማንም ሰው በተግባር ማስተዋል የሚችለውን ምሳሌ አቅርቧል። ያም ከእርጥብ አረንጓዴ ዛፍ እሳት ማውጣት ሲሆን፣አንድን ነገር ከተቃራኒው የሚያስገኝ፣የፍጥረታት ሁሉ ቁሶችና ንጥረ ነገሮች የሚታዘዙለትና የሚገዙለት ምንም የማይሳነው ፈጣሪ ጌታ፣አጥንቶችን በስብሰው ትቢያ ከሆኑ በኋላ ዳግም ሕያው ለማድረግ ቻይ ነው።

ሦስተኛው ማስረጃ፦ ፍጥረታትን ካንዱ ወደ ሌላው ሁኔታ መገለባበጥ ነው። ሞት ከዚያ ሕይወት፣እንደገና ሞትና ከዚያ በኋላ ደግሞ ሌላ ሕይወት። ከግዑዝ ደረቅ የዘር ፍሬ በቅሎና ለምልሞ፣አብቦና ፍሬ የሚያፈራ ተክል ሆኖ ይወጣል፤ከዚሁ ፍሬ ደግሞ ግዑዝ የሆነ ደረቅ የዘር ፍሬ ይወጣል። ከሚያድጉ ሕያው አዕዋፍ ግዑዝ የሆነው እንቁላል ይወጣል፤ከዚህ ግዑዝ እንቁላል ዳግም ሕያውና ተንቀሳቃሽ የሆነ ጫጩት ይወጣል። ግዑዝና ሙት አድርገን በምንገምተው ነገር ውስጥ ሕይወት ሰርጾ እናገኛለን . . የሰው ልጅና የሁሉም እንስሳት ሁኔታም ይኸው ነው።

አራተኛው ማስረጃ፦ በሰው ልጅ በእንስሳትና በእጽዋት ውስጥ ያለውን የሕይወት ሕዳሴ ክስተት ማስተዋል ነው። መደበኛ የሰው ገላ በ260,000,000,000,000,000 ሕዋሳት የተገነባ ሲሆን፣ሕዋሳቱ በየሰከንዱ በመተካካት በፍጥነት ይቀንሳሉ። ጉድለቱ በምግብ አማካይነት የሚካካስ ሲሆን የሰው ገላ ልክ እንደ ወራጅ ውሃ ራሱን በራሱ ቀጣይነት ባለው ሁኔታ ይለውጣል። አንዲት ነባር ሕዋስ እንኳ በውስጣችን በማትቀርበት ሁኔታ የሰራ ገላችን በዚህ መልኩ በማያቋርጥ የለውጥ ሂደት ውስጥ ይኖራል . . ሂደቱ በወጣቶችና በሕጻናት ዘንድ በፍጥነት የሚደጋገም ሲሆን፣በጎልማሶች ዘንድ ግን በዝግታ ይቀጥላል . . ይህ ሙሉ ሕዳሴ በአማካይ በየአስር ዓመቱ አንድ ጊዜ ይከናወናል።

ከዚህ ሁኔታ የምንደርስበት ማጠቃለያ፣የሰው ልጅ ቁሳዊ አካላዊ ለውጥ ቀጣይነት ያለው ሲሆን፣ውስጣዊ ማንነቱና ሰብእናው የማይለወጥ መሆኑን ነው። ዕውቀቱ፣ልማዶቹ፣ ትውስታዎቹ፣ምኞትና ተስፋው፣ሀሳቦቹ . . ግን አይተካኩም፣አይቀያየሩም፣ሁሉም ባሉበት ይቀጥላሉ። የሰው ልጅ በገላው መጥፋትና በአካሉ መፍረስ የሚጠፋ ቢሆን ኖሮ፣ቢያንስ ቢያንስ የሕዋሳቱ መፍረስና ሙሉ በሙሉ መለወጥ የግድ ጫና ሊፈጥርበት ይገባ ነበር . . ይህም የሰው ልጅ ሕይወትና ሰብእናው ከአካሉና ከገላው የተለየ ነገር መሆኑን የሚያረጋግጥ ሲሆን፣በሕዋሳቱ መሞትና በማያቋርጥ ሁኔታ መለዋወጥ ገላው ቢጠፋና ቢፈርስ እንኳ እርሱነቱ ግን ቀሪ መሆኑን ያመለክታል።

አምስተኛው ማስረጃ፦ ዘመናዊው ሳይንስ፣የዩኒቨርስ የተፈጥሮ መሳሪያዎች የሰውን ልጅ ሥራዎች ሙሉ በሙሉ የሚመዘግቡና ቀርጸው የሚያስቀሩ መሆናቸውን የሚያመለክት መሆኑ ነው። ከወዲያኛው የኣኽራ ሕይወት አበይት ግቦች አንዱ፣ሰዎች በዚህ የዱንያ ሕይወታቸው በሠሩት ጥሩም ሆነ መጥፎ ሥራ፣ተመዝግቦ በተያዘባቸው መሰረት የሚሸለሙ ወይም የሚቀጡ መሆናቸው ነው። ምዝገባውና ቀረጻው የሰውን ቁርጠኛ ፍላጎት (ንይያህ)፣ቃልና ተግባሩን . . የሚያካትት ሲሆን፣እነዚህም ገጦች (dimensions) ጠፍተው በከንቱ የማይቀሩ መሆናቸው ብቻ ሳይሆን፣ካበቁ በኋላም ክስተቶቹን ዳግም መልሶ ማምጣትና ማጠንጠን እንደሚቻል ሳይንሳዊ ማስረጃዎች ያረጋግጣሉ።

የሆኑ ሀሳቦችና እቅዶች አእምሯችን ውስጥ ይመላለሱና ከዚያ እንረሳቸዋለን . . በሆነ ጊዜ ግን በሕልም እናያቸዋለን፤ራሳችንን ስንስት ወይም በቅዠት ሁኔታዎች ውስጥ ሆነን ሳናውቅ እናያቸዋለን ወይም ስለነሱ እንናገራለን። ይህም፣አእምሮ ወይም ትውስታ መዝጋቢ፣መኖሩን የምናውቀውና የምንገነዘብበት ብቻ አለመሆኑን፣መኖራቸው የማይሰማንና የራሳቸው ነጻ ሕልውና ያላቸው፣ዘመናዊው ሳይንስ ልንደመስሳቸው እንደማንችል ያረጋጋጠ የዚህ ትውስታ መዝጋቢ ሌሎች ገጽታዎች መኖራቸውን፣ቁርጥ ባለ ሁኔታ የሚያረጋግጥ ነው።

ዘመናዊው ሳይንስ የምንሰማቸው ድምፆች አየር ውስጥ የሚገኙ ሞገዶች መሆናቸውን የሚያረጋግጥ መሆኑን በተመለከተ፣እነዚህ የድምጽ ሞገዶች መጀመሪያ ከተፈጠሩ በኋላ ሕዋው ውስጥ ቀርተው የሚኖሩ መሆናቸው፣ ሳይንቲስቶች እስካሁን ድረስ መተግበር ባይችሉም፣ዘመናት ካለፉ በኋላ ድምጾቹን እንደገና መልሶ ማዳመጥ የሚቻል መሆኑ ሙሉ በሙሉ የተረጋገጠ ነው።

በተግባርም የወዲያኛው የኣኽራ ሕይወት መከሰት ስለ መቻሉ አስገራሚ በሆነ መልኩ እርግጠኛ መሆን ይቻላል። በብርሃንም ሆነ በጨለማ ጊዜ የምንፈጽማቸው ሁሉም እንቅስቃሴዎቻችንና ሁሉም ሥራዎቻችን በምሥል መልክ ሕዋው ውስጥ መኖራቸውንና እነዚያን ምስሎች በማንኛውም ጊዜ አንድ ላይ አሰባስቦ ማገጣጠም የሚቻል መሆኑን ዘመናዊው ሳይንስ ያረጋግጣል። ቋሚም ሆኑ ተንቀሳቃሽ ከሆኑ አካላት በማያቋርጥ ሁኔታ ሙቀት ይወጣል፤ከነሱ የሚመነጨው ሙቀት በተራው የአካላቱን ቅርጽና ቁመና የሚያንጸባርቅ ሲሆን፣ከማንኛውም ነገር የሚወጡትን የሙቀት ሞገዶች ፎቶ የሚያነሳ የተራቀቀ ካሜራም ተሰርቷል። ይሁን እንጂ መሳሪያው የሙቀት ሞገዶቹን መቅረጽ የሚችለው ክስተቱ በተፈጸመ በጥቂት ሰዓታት ውስጥ ብቻ ነው።

ማይክል፦ የመጨረሻው ቀንና ትንሣኤ መምጣቱ አይቀሬ ግዴታ ነው ብለን ከወሰድን፣እስላም ውስጥ ያለውን ስፍራም ካወቅን፣የዚህ እምነት ወይም ዐቂዳ አበይት መገለጫዎች ምንድናቸው?

ራሽድ፦ እስላም ውስጥ የዚህ እምነት ዝርዝር ጉዳዮች፣ በተቀሩት አብዛኞቹ ሌሎች ሃይማኖቶች ውስጥ ከተመለከቱት በብዙ ይለያሉ። በደምሳሳው ግን በሚከተሉት ነጥቦች ማጠቃለል ይቻላል፦

1) አላህ ﷻ ይህን ዓለምና በውስጡ ያሉትን ፍጥረታት ሁሉ የትንሣኤ (ቅያማ) ቀን በመባል በሚታወቅ ቀን ሙሉ በሙሉ ያጠፋል።

2) ከዚያም ዳግም ሕያው አድርጎ ይቀሰቅሳቸውና ለፍርድ ከፊቱ ያቆማቸዋል። ይህም ሕይወት ዘርቶ በመቀስቀስ መነዳት (ሐሽር) ነው።

3) ከዚያም ሰዎች በመጀመሪያው የዱንያ ሕይወታቸው የሠሯቸው በጎም ሆኑ እኩይ ሥራዎች ሁሉ ሳይቀንሱና ሳይጨምሩ አላህ ﷻ ፊት በመለኮታዊ ችሎቱ ለፍርድ ይቀርባሉ።

4) አላህ ﷻ የሰዎችን እያንዳንዷን በጎና እኩይ ሥራ ይመዝናል። መልካም ሥራው ሚዛን የደፋለት ሰው ምሕረት ያገኛል፤መጥፎ ሥራው ሚዛን የደፋ ሰው ደግሞ ይቀጣል።

5) ምሕረት የሚደረግላቸው ወደ ጀነት ይገባሉ፤የሚቀጡት ደግሞ ወደ እሳተ ጀሀነም ይገባሉ።

ራጂቭ፦ እውነቱን ለመናገር፣ነገሩ እጅግ በጣም አሳሳቢ ነው።