የእምነት አስፈላጊነት

የእምነት አስፈላጊነት

ወዳጆቹ በቀጠሮው መሰረት በወጣቶቹ ማእከል ሬስቶራንት ውስጥ ተገናኙ። ማይክልና ራሽድ ሜኑውን አይተው ምርጫቸውን ሲወስኑ፣ራጂቭ ግን ሜኔውን ሲያስተውል ቆይቶ እንዲህ አለ፦

ብዙ ሬስቶራንቶች የተሟላ የፍሬ-አትክልት ምግቦች ሜኑ አያቀርቡም፤ለማንኛውም የሚመቸኝን ምግብ አዛለሁ።

ማይክል፦ አንተ ቬጂቴሪያን ነህ ማለት ነዋ?

ራጂቭ፦ አዎ ነኝ፤ወደ 40 % የሚጠጋ የሕንድ ሕዝብ ቬጂቴሪያን ነው።

ራሽድ፦ በሃይማኖታዊ ምክንያቶች ወይስ ለጤንነት?

ራጂቭ፦ እውነቱን ለመናገር እከተለው የነበረው የህንዱ ሃይማኖት የእንስሳት ሥጋ መብላትን ሙሉ በሙሉ እርም ያደርጋል። ሕንድ ውስጥ የቬጂቴሪያን አመጋገብ ሥርዓት በሕንዱ እምነት ተከታዮች ዘንድ በጣም የተስፋፋ ነው። ይሁን እንጂ ሥርዓቱ አስቸጋሪ በመሆኑ አሁን አሁን ቁጥራቸው እየቀነሰ መጥቷል። እኔ የአትክልት ምግብን የምመርጠው በጤና እና በአካባቢ ጥበቃ ምክንያት ነው።

ራሽድ (አስተናጋጁን እየጠራ)፦ እባክህን ትእዛዝ ተቀበል።

ማይክል፦ ራጂቭ ለመሆኑ ሃይማኖትህን ትተህ ወደ የትኛው ሃይማኖት ነው የሄድከው?

ራጂቭ፦ ወደ የትኛውም አልሄድኩም። ጀርመን አገር መማሬ ብዙ እንዳነብና የህንዱን ሃይማኖት በሂስና አንክሮ እንድመረምረው ነጻነት ሲሰጠኝ ጥያቄና ጥርጣሬንም አውርሶኛል። ክርስትናንም አሳማኝ ሆኖ አላገኘሁትም። በመሆኑም ወደ ኤቲዝም ይበልጥ የቀረብኩ ነኝ።

ማይክል፦ በጥርጣሬው እኔም ወደ አንተ እቀርባለሁ፤ይሁን እንጂ የሰው ልጅ አንዳንድ ጊዜ ከአምላክ ጋር የሆነ ግንኙነት ያስፈልገዋል የሚል እምነት አለኝ። ግንኙነቱ ግን የሰውን ልጅ ሕልውና የሚደፈጥጥ ወይም የሚቆጣጠረው መሆን አይገባም።

ራሽድ፦ እኔ ግን ይህ አባባል ክርክርና ማጥራት ያስፈልገዋል የሚል እምነት አለኝ።

ማይክል፦ የትኛውን አባባል ማለትህ ነው?

ራሽድ፦ የኤቲዝም እሳቤንና ሃይማኖት ወይም አምላክ በሰው ልጅ ሕይወት ውስጥ ያለውን ስፍራ ማለቴ ነው።

ራጂቭ፦ የሰው ልጅ በሳይንስ መስክ ያስመዘገበው ዕድገት፣የማያውቀውን ነገር እንደ ቀድሞው ሜታፊዚካዊ በሆነ መንገድ የመተርጎምን አስፈላጊነት ያስቀሩ ብዙ ምስጢሮችን ግልጽ አድርጎለታል ብዬ አምናለሁ። ዩኒቨርስ የሚገዛው ተግባሩን በሚመሩ የሳይንስ ሕጎች ነው ባይ ነኝ። ዩኒቨርስ ወሳኝና ፍጹም ለሆኑ ሕግጋት ተመሪ የሆነ ሜካኒካዊ መሳሪያ ነው ማለት ይቻላል። በውስጡ የሚከሰት ማንኛውም ነገር ፍጹምና ውስን ወደ ሆነ ውጤት የሚያደርስ መንስኤ አለው። ሜካኒካዊ ሕግጋት በተዘረጋለት ሥርዓት መሰረት ፍጥረተ ዓለምን የሚመራ እስከሆነ ድረስ ፍጥረተ ዓለምን የሚቆጣጠርና የሚያስተዳድር አምላክ የመኖር እሳቤ አስፈላጊ አይደለም።

ራሽድ፦ ሳይንስ በዙሪያችን የሚገኙ ነገሮችን ለመተንተን ድንቅ መሣሪያ ነው። ጥያቄው ግን ይህ አይደለም። እንዲህ ያለውን ከባድ ጥያቄ፣በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ ከሁሉም ይበልጥ ብርቱና አሳሳቢ ሆኖ የኖረውን ጉዳይ አንድ ገጽታውን ብቻ ወስደን ልንነጋገርበት አንችልም። የሚጥመንን ወይም የምንተማመንበትን አንድ ጎኑን ብቻ አንስቶ መወያየቱ ተገቢ አይሆንም። ርእሰ ጉዳዩ ብዙ ገጽታዎች ያሉት ፈርጀ ብዙ ሲሆን ጥቂቶቹ የሚከተሉት ናቸው፦

ሳይንስ በዙሪያችን ላሉት ክስተቶች ሁሉ ትንታኔ ይሰጣልን? መልሱ በእርግጥ አይሰጥም ነው . . ሳይንስ ይህን ማድረግ አይችልም። ለምሳሌ ስነፈለክን ብንወስድ ከዩኒቨርስ ውስጥ እስከዛሬ ድረስ ያወቅነውና የደረስንበት 5%ብቻ መሆኑን ንድፈ ሀሳቦቹ ይነግሩናል። የቀረው 95% ምኑንም የማናውቀው ድፍን ጨለማ ነው። ይህን ያህልም ቢሆን ዛሬ በተደረሰበት የተራቀቀ ቴክኖሎጂ ሊታወቅ የተቻለ ሲሆን ግኝቶቹ ባይኖሩ ኖሮ የሚታወቀው መቶኛ ከዚህ በጣም ያነሰ ይሆን ነበር።

ይህ በተጨባጩ ቁሳዊ ዓለም ያለውን የሚመለከት ከሆነ፣ከሰው ልጅ ግንዛቤ በላይ የሆነውን ሜታፊዚካል ዓለምን በሚመለከት ምን ማለት ይቻላል?!

ይህም በተራው ሳይንስ መጣስ የማይቻለው ድንበር የለውም ወይ? ብለን እንድንጠይቅ ያደርገናል። ሳይንስ የቱንም ያህል ቢመጥቅ ሁሉንም ነገሮችና ክስተቶች የመተንተን አቅሙ ውስን መሆኑን ማወቅ ግድ ይለናል። ከሰው ልጅ ግንዛቤ ውጭ የሆነው ዓለም (ዓለም አልገይብ) ሳይንስ በሚደርስበት ክልል ውስጥ አይደለም። ሳይንስ በተጨባጭ የሚታዩ አንዳንድ ፊዚኦሎጂካዊ ክስተቶችን ምንነት መተንተን የተሳነው ሲሆን፣ከሰው ልጅ ግንዛቤ በላይ ስለሆነውና ለቤተሙከራም ሆነ ለሌሎች ቁሳዊ ግንዛቤ ስልቶች ተገዥ መሆን የማይችለውን ዓለም እንዴት አድርጎ መተንተን ይችላል?!

በተጨማሪም አንድ ነገር እንዴት እንደሚሠራ ማወቃችን ሠሪውን እንድናስተባብልም ሆነ ፈጠራውን አሳንሰን እንድንመለከት ሊያደርገን አይገባም። ምንም ዕውቀት የሌለው አንድ ሰው ቴሌቪዥን አይቶ በአድናቆት ተውጦ ቢደመምና ከዚያ በኋላ የቲቪ መሣሪያው እንዴት እንደሚሠራ ማወቅ ቢችል፣ማወቁ ሥራውን ዋጋ ማሳጣት ወይም የፈጠራውን ባለቤት ማስተባበል ማለት አይደለም። በተመሳሳይ መልኩ በስነሕይወት ሳይንስ የሕዋሳትን የምስጢር ኮድ ለመፍታት በቅተን የዲኤንኤን ክር ማግኘት በመቻላችን እጹብ ድንቅ የሚባሉ ነገሮች ተገልጸውልናል። ታድያ ይህ ማለት በዚህ ውስጥ ምንም ታምር የለበትም ማለት ነውን? ይህ ፍጥረተ ዓለም ፈጣሪና ሠሪ የለውም ማለት ነውን? ፈጽሞ። የሰው ልጅ መሰሉን ከምንም መፍጠር የማይችል ደካማ ሆኖ በአድናቆት መደመሙ፣ወይም እንዲህ እጅግ በጣም ኢምንት የሆነው ነገር እንዴት እንደሚሠራ መተንተን አለመቻሉ፣ይህ ድንቅ ተፈጥሮ ፈጣሪ አምላክ እንዳለው ወደ ማመን ይወስደናል።

ሌላ ምሳሌ ውሰድ፤አሜሪካዊው የስነሕይወት ፕሮፌሰር ሲሴይል ባይስ ሃማን እንዲህ ይላሉ፦

‹‹ምግብ ከሰውነት ጋር ተዋህዶ የገላ ክፍል የሚሆንበት ሂደት ቀደም ሲል ከእግዚአብሔር ጋር ይያያዝ ነበር። ዛሬ ግን በዓይን የሚታይ አዲሱ አስተውሎ ኬሚካላዊ መስተጋቢር ሆኗል። ታድያ ይህ የእግዚአብሔርን መኖር ውድቅ ያደርጋልን? ኬሚካላዊ ንጥረነገሮችን ጠቃሚ መስተጋቢር እንዲሆኑ ያደረገው ኃይል ምንድነው? . . የተበላው ምግብ ወደ ሰው አካል ከገባ በኋላ የራሱ በሆነ ሥርዓት አማካይነት ብዙ ሂደቶች ውስጥ ያልፋል። እንዲህ ያለ በጣም የተራቀቀ አስደማሚ ሥርዓት በአጋጣሚ ይሆንታ ተገኘ ብሎ ማሰብ ፈጽሞ የማይታሰብ ነው። ከዚህ አስተውሎ በኋላ እግዚአብሔር ሕይወትን በፈጠረበት ኃያል ሕግጋቱ የሚሠራ መሆኑን ማመን ግድ ይለናል››።

ማይክል፦ የዳርዊን የኢቮሊዩሽን ንድፈ ሀሳብ ግን ይህንኑ ጽንሰ ሀሳብ ማለትም የሳይንስን ፍጹምነትና የአምላክን አለመኖር እሳቤ ያረጋግጣል። ሕያው ፍጥረታት የተፈጠሩት በተፈጥሯዊ መረጣና በአዝጋሚ ዕድገት እንጂ በአምላክ አለመፈጠራቸውን ያብራራል።

ራሽድ፦ አባባሉ ይህን ንድፈሀሳብም ሆነ ሌላውን በተመለከተ አስፈላጊ የሆነ ጥያቄ እንድናነሳ ያደርገናል። ሳይንሳዊ ትንታኔ በሁሉም ሁኔታዎች ውስጥ ፍጹም የማይለወጥና የጸና ነውን? በሳይንሳዊ ዕድገት አስደናቂነት የተደመሙ ብዙ ሰዎች ከሳይንስ ባሕርያት አንዱ ተነባባሪነትና አብየታዊነት መሆኑን ይዘነጋሉ። እየተከማቸ መምጣትና በአንድ ነጥብ ላይ ወደ አብዮታዊነት ሁኔታ መድረሱ ለዕውቀትና ሳይንስ ግስጋሴ የአውቶማቲክነት ባህሪን ያላብሳል። ዕውቀትና ሳይንሳዊ ግኝቶች እየተከማቹና እየተነባበሩ መጥተው፣ቀደም ሲል ሰፍኖ የቆየ አመለካከት በድጋሜ እንዲፈተሽ የሚያደርጉ አዳዲስ ሁኔታዎችን ወደማመቻቸት ሁኔታ ይደርሳሉ፤በዚህም የሰው ልጅ ለዓለም ያለው አመለካከት እንዲቀየር ያደርጋሉ።

በዳርዊን ንድፈሀሳብ - ለነገሩ ሳይንሳዊ እውነታ መሆን ቀርቶ ወደ ንድፈ ሀሳብ ደረጃም ያልደረሰ መላምት ብቻ ነው - ዳርዊን የሚያራምዳቸው የኢቮሊዩሽን ሀሳቦች ከዘመናዊው የስነጽንስ (embryology) ግኝቶች ጋር ተላትሟል . . እንደዚሁም በቁፋሮ የተገኙ መረጃዎች፣ካምቤሪያን በመባል በሚታወቀው የስነምድር ዘመን፣መሰረታዊ የሆኑ አበይት የእንስሳት ስብስቦች በአጭር ወሰነ ጊዜ ውስጥ በድንገት መታየታቸውን አረጋግጠዋል። ይህ ዘመን በአብዛኛው ‹‹የካምቤሪያን ፍንዳታ›› ተብሎ የሚጠራው ነው። እናም ሕያው ፍጥረታት የተገኙት ዳርዊን እንደሚያስበው አንዱ ከሌላው እያደገ በረዥም አዝጋሚ ዕድገት አይደለም ማለት ነው።

ራጂቭ፦ ስለዚህ ይህ ዓለም ፈጣሪ ሳይኖረው በአጋጣሚ ይሆንታ የመገኘት ዕድል የለውም ማለት ነው?

ራሽድ፦ መልካም ፈቃድህ ይሁንና የማቴማቲክስን መርሕና የአጋጣሚ ይሆንታን ሕጎች በመጠቀም የአጋጣሚን ምንነትና የሚያመለክተውን ነገር ላብራራ። ይህ ከአጋጣሚ ወይም ከይሆንታ ክስተቶች መካከል የአንዱ የመከሰት ዕድል ምን ያህል እንደሆነ ለማወቅ ይረዳናል።

በሺዎች በሚቆጠሩ የፊደል ሆሄያት የተሞላ ትልቅ ሳጥን አለን እንበል። ‹‹አለ›› የሚለውን ቃል ለመመስረት የ‹‹አ›› ፊደል ከ‹‹ለ›› ፊደል ጎን የመገኘቱ አጋጣሚ በአንጻራዊነት ከፍተኛ ሊሆን ይችላል። እነዚህ ሳጥኑ ውስጥ የታጨቁ ፊደሎች አንድ ረዥም ግጥም ወይም አንድ ጥበባዊ ትረካን የሚያስገኙ ሆነው የመቀናበራቸው አጋጣሚ ግን ፈጽሞ የማይቻል ባይሆን እንኳ እጅግ በጣም አነስተኛ ነው የሚሆነው።

ሊቃውንት የአሚኖ አሲድን አንዱን አሃድ የሚመሰርቱ አቶሞችን አንድ ላይ የመሰባሰብን ይሆንታ (probablity) ወይም የመሆን አጋጣሚን ያሰሉ ሲሆን፣የደረሱበት ውጤት ይህን ለማድረግ በብዙ ቢሊዮን የሚቆጠሩ ዓመታትንና ይህ ወሰንየለሽ ግዙፍ ዩኒቨርስ የማይበቃው ንጥረ ነገር የሚያስፈልግ መሆኑን የሚያረጋግጥ ነው። ይህ አንዲቱን ኢምንት ክፍል ለማስገኘት ሲሆን እጽዋትንና እንስሳትን የሚያጠቃልለውን የሕያው ፍጥረታትን አካላት ለማስገኘት የሚያስፈልገውን ጊዜና ቦታ አስብ። የሕይወትንና የዩኒቨርስን መፈጠር አስተውል . . እናም ይህ ሁሉ በጭፍን አጋጣሚ አማካይነት ተከሰተ ብሎ አእምሮ ፈጽሞ ሊቀበለው አይችልም።

ሁሉም የሳይንስ ዘርፎች ይህ ዩኒቨርስ፣በቅንብሩና በቅንጅቱ እጹብ ድንቅ በሆነ ተአምራዊ ሥርዓት የሚመራ መሆኑን፣ሥርዓቱም በማይለወጡና በማይቀያየሩ የጸኑ ተፈጥሯዊ ሕግጋት ላይ የታነጸ መሆኑን ያረጋግጣሉ። ሳይንቲስቶችና ተመራማሪዎች ዘውትር የሚለፉት እነዚህን ሕግጋት ለማግኘትና ለማወቅ ነው። ሳይንሳዊ ግኝቶች ዛሬ የፀሐይና የጨረቃ ግርዶሾችንና ሌሎች ክስተቶችንም ከመድረሳቸው በፊት በመቶዎች በሚቆጠሩ ዓመታት አስቀድመው በትክክል ከመገመት ደረጃ ላይ ደርሰዋል።

ታድያ እነዚህን ሕግጋት አስገኝቶ በዚህ ዩኒቨርስ ውስጥ ባለችው እያንዳንዷ አቶም ብቻ ሳይሆን ስትፈጠር ከአቶም ባነሰችው ቅንጣት ውስጥ ያኖረው ማነው?! ይህን ሁሉ የተቀናባበረ የተቀናጀና ፍጹማዊ በሆነ መንገድ እርስ በርሱ የተጣጣመ ሥርዓት የፈጠረው ማነው?! የነደፈው ያቀደው ድንቅ በሆነ ሁኔታ አስልቶ የወሰነውስ ማነው?! ይህ ሁሉ ያለ ፈጣሪ ተገኝቶ ይሆን፣ወይስ ሰዎች ራሳቸው ፈጥረውት ይሆን?! የሙስሊሞች መጽሐፍ የሆነው ቁርኣን እንዲህ ሲል ነው የሚጠይቀው፦

{ወይስ ያለ አንዳች (ፈጣሪ) ተፈጠሩን? ወይስ እነርሱ ፈጣሪዎች ናቸውን?።}[አልጡር፡35 ]

ይህ ዩኒቨርስ የሚመራበት ሥርዓትና ሕግ፣ዓይኖቻችንን ወደ የትኛውም አግጣጫ ብናነጣጥር የምንመለከተው ያ ድንቅ ቅንብር፣ይህን ፍጥረተ ዓለም ያስገኘ ኃያል ችሎታ ያለው በጣም ዐዋቂ የሆነ አምላክ መኖሩን ያመለክታል።

ማይክል፦ ይዘቱን ባልደግፈውም እዚህ ላይ ግን የሚነሳ ጥያቄ አለ።ሃይማኖትና በአምላክ ማመን ለኛ ያለው አስፈላጊነት ምን ያህል ነው? ብዙ ሰዎች በአምላክ ሳያምኑ ወይም የሃይማኖት ተከታይ ሳይሆኑ ይኖራሉ።

ራሽድ፦ የሃይማኖት አስፈላጊነት በሁሉም ዘመናትና በሁሉም ሕብረተሰቦች ውስጥ፣በሁሉም ሕዝቦች ዘንድ መኖሩንየአንትሮፖሎጂና የሃይማኖቶች ጥናቶች ያረጋግጣሉ። የሰው ልጅ ከጥንት ጀምሮ የሚያመልከውን፣የሚማጸነውን፣ፍጥረተ ዓለምን የሚቆጠጠር ኃያይል ያለው፣ሁሉንም ነገር የፈጠረ፣ሕያውና የማይሞት አምላክ ሲፈልግ ኖሯል።

የሰው ልጅ ችግርና ፈተና ሲገጥመው፣አደጋ ሲጋረጥበት፣ተስፋው ሲመናመን፣በአላህ እንዲያምን የሚገፋፋው ስነሕይወታዊ ፍላጎት እውስጡ መኖሩን ሰብአዊ ተፈጥሮው ያስተውላል።

በተጨማሪም ያለዚህ እምነት የሰው ልጅ በአብዛኛው ስሜታዊ ፍላጎት የሚመራውና የሕሊና ዳኛ የሌለው እንስሳ ይሆናል።

ራጂቭ፦ ራሽድ ይቅርታ አድርግልኝና በተለያዩ ብዙ ሃይማኖቶች በታጨቀች አገር ነው የኖርኩት። ወደ አውሮፓ ስመጣ ከሌሎች ሃይማኖቶች ተከታዮች ጋር ለመተዋወቅ ችያለሁ፤የያንዳንዱ ሃይማኖት ተከታይ ስለእግዚአብሔር ያለው እሳቤና ግንዛቤ የሚለያይ መሆኑን ነው የተረዳሁት። ይህን ልዩነት እንዴት መረዳት እችላለሁ? እውነተኛው አምላክ ሊገለጽባቸው የሚገቡትን ባሕርያትስ እንዴት ማወቅ እችላለሁ? በተጨማሪም እውነተኛውን ሃይማኖት ከሌላው ለይቼ ማወቅ የምችለውእንዴት ነው?

ራሽድ፦ አስተናጋጁ ምግቡን እያቀረበ ነው። እነዚህን ነጥቦች በቀጣዮቹ ውይይቶች እንደምንመለከታቸው ቃል እገባላለሁ፤መጀመሪያ ግን በፊዚክስ ሊቁ በአልበርት አንሽታይን ብሂል እንስማማ፦ ‹‹ሳይንስ ያለ ሃይማኖት አንካሳ ነው፤ሃይማኖትም ያለ ሳይንስ ዓይነስውር ነው።››