የስነምግባር መጋረጃ

የስነምግባር መጋረጃ

ራሽድና ማይክል በቀጠሯቸው መሰረት በእንግሊዙ የውስጥ ለውስጥ ዋሻ በኩል ከለንደን ወደ ፓሪስ በሚጓዘው የባቡር ጣቢያ ውስጥ ተገናኙ . . እስከ ባቡሩ መነሻ ሰዓት ድረስ የሚያርፉበትን ተስማሚ መቀመጫ ይዘው ተቀመጡ።

ማይክል፦ በሴቶች አለባበስ ላይ ያላችሁን አቋም አንሰተን ለመነጋገር በቂ ጉዜ ያለን ይመስለኛል . . ስለ ሕጃብ ትነግረኛለህ . . አይመስልህም?!

ራሽድ፦ ብዙ ሰዎች ሕጃብን ዝም ብሎ የጸጉር መሸፈኛ ጨርቅ እንጂ ሌላ ምንም እንዳልሆነ አድርገው ያስባሉ። ሕጃብ አመለካከትና ማህበራዊ ሥርዓት መሆኑን አያውቁም . . እናም ጉዳዩን በዚህ ማእቀፍ ውስጥ ልናየው ይገባል።

ማይክል፦ ጉዳዩን ያወሳሰብከውና ከሚገባው በላይ ያገዘፍከው ይመስለኛል!

ራሽድ፦ የሰው ልጆች ገላቸውን መሸፈንን በሚመለከቱ ጉዳዮች ላይ የተለያዩ መመዘኛዎች አሏቸ። ሁሉም ወገን የራሱን መመዘኛዎች ሥልጣኔና ተራማጅነት አድርጎ ሲወስድ፣የሌሎችን ደግሞ ኋላ ቀርነትና ወግ አጥባቂነት አድርጎ ይቆጥራል። እነዚህ ደግሞ የነዚያን አለባበስ ኢሞራላዊነትና ዝቅጠት አድርገው ይመለከታሉ . . የያንዳንዱ ወገን አመለካከት ከራሱ እሴትና ርእዮት . . ይንደረደራል። በመሆኑም ገላ መሸፈንን በሚገዙ አጠቃላይ መስፈርቶች ላይ ከስምምነት መድረስ ግድ ይላል . .

ይህ እንዳልኩህ በጥቅሉ ሲታይ ነው። መልካም ፈቃድህ ከሆነ አቋሞቻችንን የሚያቀራርቡ አንዳንድ መሰረታዊ ነጥቦችን አቀርብልሃለሁ።

ማይክል፦ ቀጥል።

ራሽድ፦ ከሰው ልጆች ሕይወት ጋር ለተያያዙ መሰረታዊ ችግሮች መፍትሔ ወይም መፍትሔዎችን ማግኘት የሚቻለው፣የሰውን ምንነትና ተፈጥሮውን በተሟላ ሁኔታ ካወቅን በኋላ ብቻ በመሆኑ ላይ የተስማማን ይመስለኛል።

ማይክል፦ በጣም ግልጽ ነው።

ራሽድ፦ ዛሬ የምናየው አስደማሚው የሳይንስና የቴክኖሎጂ እመርታ፣የሰው ልጅ ዕውቀት ውስን ለመሆኑ አስረጅ ነው። ትናንት ያልደረሰበትን ዛሬ ይደርስበታል። ትናንት ትክክለኛ ነው ብሎ የወሰደውን ዛሬ በሚደርስበት አዲስ ግኝት ዳግም ይመረምራል። በዚህ መልኩም የሰው ልጅ ዛሬ አላዋቂ መሆኑን ወይም ቢያንስ ዕውቀቱና ዛሬ ያለው መረጃ ውስን የነበረ መሆኑን ነገ ይደርስበታል . . የኛ ቁርኣን በትክክል የገለጸው እውነታም ይኸው ነው ፦

{ከዕውቀትም ጥቂትን እንጂ አልተሰጣችሁም፣በላቸው። } [አልእስራእ፡85 ]

ማይክል፦ ልክ ነው፣እስማማበታለሁ። ይሁንና ይህ ሁሉ ከርእሰ ጉዳያችን ጋር ምን ተያያዥነት አለው?!

ራሽድ፦ ወዳጄ ታገሰኝማ፣ገና አልጨረስኩም . . በዚህ ከተስማማን በጥልቀት ልንደርስባቸው በማንችል ጉዳዮች ውስጥ ግልጽ ያልሆኑ ጎኖች መኖራቸውን በቀጥታ አምነን እንቀበላለን ማለት ነው። ይህም ከስሜት፣ከግላዊ ዝንባሌዎችና ከአካባቢ ተጽእኖዎች ነጻ ሆነናል ብለን በመገመት ሲሆን ይህን ማድረግ ደግሞ አስቸጋሪ ነው። በዚህ መልኩ ለነዚህ ጉዳዮች መፍትሔ ለመፈለግ መነሳትም ለመደናበር ያጋልጣል፤በዚህ መሠረት ላይ የምንዘይደው መላም ጎዶሎ ወይም የተዛባ ብቻ ሳይሆን የትክክለኛው መፍትሔ ተቃራኒ ሊሆንም ይችላል።

ማይክል፦ ይህ ሎጂካዊ ውጤት ነው። በሌላ በኩል ግን አእምሯችንን ከመጠቀም፣የደረስንበትን እሳቤና ዕውቀት ከመተግበር፣እየወደቅን ከመነሳት፣ከመሳሳትና ከስህተት ተምረን ከመታረም፣ከተሞክሮ ከመማር ውጭ ሌላ አማራጭ የለንም። ችግሮችን ለመፍታት ከመሞከር ተቆጥቦ ከመቀመጥና በተገቢው መንገድ ወደሚፈቱበት የተሟላ የመፍትሔ ደረጃ እስክንደርስ እጆቻችንን አጣምረን ከመጠበቅ ይህ ተመራጭ ነው።

ራሽድ፦ እናም እነዚህ መፍትሔዎች እንከንና ጉድለት እንዳለባቸው ከኔ ጋር ትስማማለህ ማለት ነው። ሌላ አማራጭ ስለሌለን ለመቀበል እንገደዳለን ባይ ነህ።

ማይክል፦ ልክ ነው፣እንደዚያ ነው የሚታየኝ።

ራሽድ፦ እኛ ግን ከዚህ ሁሉ መደናበር የሚያድንና ከእንከንና ከጉድለት ነጻ የሆነ ሌላ አማራጭ አለን!

ማይክል፦ {እኛ} ስትል ማንን ማለትህ ነው? የምትለው መፍትሔስ ምንድነው?

ራሽድ፦ ማለት የፈለግሁት እኛ ሙስሊሞች ለመላው የሰው ዘር መድሕን ይሆናል ብለን የምናምንበት ሌላ አማራጭ አለን ነው። ይህ አማራጭ ሰውን የፈጠረው ፈጣሪ አምላክ ለሰብአዊ ፍጡራኑ የሚበጀውን ነገር ሁሉ ከማንምና ከምንም በላይ ያውቃል በሚለው ውስጥ የሚጠቃለል ነው። ይህንኑ በማረጋገጥ አላህ (ሱወ) እንዲህ ብሏል፦

{የፈጠረ አምላክ እርሱ ዕውቀተ ረቂቁ፣ውስጥ ዐዋቂው ሲኾን፣(ምስጢርን ሁሉ) አያውቅምን?።}[አልሙልክ፡14 ]

ማይክል (በማቋረጥ)፦ ]ወዳጄ ራሽድ፣አነጋገርህ ቁልጭ ያለና ወጥነትን የተላበሰ ነው። ነገር ግን እኔ በአንተ ሃይማኖት የማላምን መሆኔን አትርሳ፤እናም የማላምንበትን ነገር ለመቀበል አልገደድም . . ቀደም ሲል ስንወያይ እንደ ነበረው ሁሉ በምንስማማበት ነገር ላይ እንነጋገር።

ራሽድ፦ ለመላው የሰው ልጅም እንደዚያ መሆን አለበት ብዬ የማምንበት ይህ መርህ የያንዳንዱ ሙስሊም የእምነት መንደርደሪያ ቢሆንም፣አንተ በምትፈልገው መንገድ ውይይታችን ለመቀጠል ምንም ችግር የለብኝም። ያ ማለት ግን በራሴ ግላዊ እምነት ማእቀፍ ውስጥና ሕጃብ አንዱ አካሉ ነው ብዬ በነገርኩህ ማሕበረሰባዊ ሥርዓት አመለካከት አኳያ ማለት ነው።

ማይክል፦ ችግር የለውም።

ራሽድ፦ ባለፈው ውይይታችን ላይ የሰውን ልጅ ሥጋዊ ጎን ብቻ ሳይሆን እንስሳዊነቱንም ጭምር ችላ ማለት እንደማንችል ጠቅሼ ነበር። ወንድ በተፈጥሮው ወደ ሴቷ ይሳባል፤በመጀመሪያ የሚስበውም ሰውነቷ ነው። ከዚህ ስንነሳ ጨዋነት የጎደለው አለባበስ ወንዶችን የሚያሳስት፣ስሜታቸውን የሚቀሰቅስና እንዲተናኮሱ. . ቀጥተኛ ያልሆነ ግብዣ የሚያደርግ መሆኑ ግልጽ ነው።

ማይክል፦ እንደኔ ግን ይህ ሴቷንም ሆነች ወንዱንም ጭምር በንቀት ዓይን መመልከት ነው። ለሴቷ ውርደት የሚሆነው አእምሯንና ዕውቀቷን፣ስነምግባሯንና ሰብእናዋን ችላ ብሎ በገላዋ ብቻ የሚያተኩር በመሆኑ ነው። ሕጻን ትመስል ምንም የማታውቅና ራሷን መጠበቅ የማትችል ደካማ አድርጎ ማሰብም ነው። ሴቷን የወሲባዊ ጥቃቱ ሰለባ ከማድረግ ውጭ ሌላ ሀሳብ የሌለው አውሬ አድርጎ የሚስል በመሆኑ ለወንዱም ወርደትና ንቀት ነው።

ራሽድ፦ ወዳጄ፣አንዲት ሴት ለመሽሞንሞንና ለመጋጌጥ መስታወት ፊት ቆማ ፈታኝ ልብሶቿን ስታማርጥ፣የወንዱን የአእምሮ ምጥቀት ወይም ምስጉን ስነምግባሩን ለማስደሰት ነው? ወይስ የወንዶችን ስሜት ለመቀስቀስ ወይም ለማጥመድ ባይሆን እንኳ ቢያንስ የወንዶችን ትኩረት ለመሳብ ነው ብለህ ታስባለህ? አማምራ ተቆነጃጅታ የወጣችን ቆንጆ ሴት መጀመሪያ ሲመለከት ወንዱ በአመዛዛኝ አእምሯ የሚደመም ወይም በዕውቀቷ ስፋትና ጥልቀት ፍቅር የሚነደፍ ይመስለሃል?!

ሁላችንም እንደምናውቀው ሰዎች በስሜታዊ ፍላጎቶቻቸውና በሥጋዊ ዝንባሌዎቻቸው ደረጃ፣ለጥቃትና ለጥሰት ባላቸው ዝግጁነትም ይለያያሉ። በጨዋ ስነምግባር፣በትሩፋትና በሞራላዊነት ደረጃቸውም እንዲሁ ይለያያሉ። ሕጃብ ደግሞ፣የለበሰችው ሴት የወንዶችን ትኩረት መሳብና ስሜታቸውን መቀስቀስ የማትፈልግ ቁጥብ ሴት መሆኗን ስለሚጠቁም፣ያልተገራ ጠባይ ያላቸው እኩይ ወንዶች እንዳይተናኮሷት መከላከያ ይሆናታል። ሕጃብ ሴቶችን ከጋጠወጦች የሚከላከል መሆኑን ቁርኣን በግልጽ አስቀምጧል።

ማይክል፦ ወዳጄ ራሽድ፣የአንዳንድ ሕጃብ ለባሽ ሴቶች ተግባር ከመልካም ስነምግባር ጋር የማይጣጣም ሆኖ ይስተዋላል። ይህም የችግሩ መንስኤ አስተዳደግና የመልካም ስነምግባር እሴቶችን የመሳሰሉ ሌሎች ነገሮች እንጂ ሕጃብ አለመልበስ መሆኑን ያረጋግጣል።

ራሽድ፦ ባልከው ነገር ከፊል እውነት አለበት፤አንዲት ሴት የጨርቅ ቁራጭ ስለ ለበሰች ብቻ ወደ ምግባረ ሰናይ ጨዋ ሴትነት ትለወጣለች የሚል ሰው የለም። ይህ ግን ሕጃብ አይለበስ ማለት አይደለም። ሳይሆን አንድ ሰው ሐኪም ነኝ ብሎ ወይም አንድ ሐኪም በሙያው ላይ ስህተት ቢፈጽም ወይም በተሳሳተ መንገድ ሙያውን ቢጠቀም፣ችግሩ የራሱ የሙያው ነው ማለት አይደለም። ሊባል የሚችለው ስህተት የፈጸመው ሰው መታረም ያስፈልገዋል ነው። ሐኪሙ፣ሕጃብ ለባሿና ሌላውም ዞሮ ዞሮ ሰብአዊ ፍጡር ነውና ሰብአዊ ድክመት ይጠናወታቸዋል . .

በሌላ በኩል ደግሞ እስላም ሕጃብን ወደ ኢሞራላዊ ተግባር ከመውደቅ ወይም ወደዚያ ከሚወስድ መረማመጃ የሚከላከል ሕጋዊ እርምጃ አድርጎ ሲደነግግ፣በዚህ ብቻ አልተወሰነም። ከዚህ ጋር ሰውን ወደ ከፍተኛው የሰናይነትና የትሩፋት ደረጃዎች ማድረስ የሚችል የተሟላ የስምግባርና የሞራል ሥርዓትን አኑሯል። በአጭሩ ጨዋ ሴት ሕጃብ ትለብሳለች፣ሕጃብ የለበሰች ሴት ሁሉ ግን የግድ ጨዋ ሴት ላትሆን ትችላለች።

ማይክል፦ ይህ ግን የሴትን ገላ ሰይጣናዊ የማድረግ አፍራሽ እይታ አላካተተም?! ይህን ገላ መተውና መራቅ ይጠበቅብናል ማለት ነው?!

ራሽድ፦ እስላም ሕጃብን ግዴታ አድርጎ የደነገገው ገላዋ ነውር በመሆኑ መሸፈን አለበት ብሎ ሳይሆን፣የየወንዶችን በተለይም የምግባረ ብልሹ ወንዶችን ተፈጥሯዊ የወሲብ ፍላጎት እንዳትቀሰቅስ በማሰብ ነው። ሕጃብ የተደነገገው ሴቷን ከወንዶች ጾታዊ ትንኮሳና ከአስገድዶ መድፈር ለመጠበቅ፣ወንዶችንም ከስሜት መነሳሳትና ወድ ዝሙት ከመገፋፋት ለማዳን ነው . . በተጨማሪም እስላማዊው ሸሪዓ በትዳራዊ ግንኙነቶች ክልል ውስጥ ብቻ እስከ ታጠሩ ድረስ ልባዊ የፍቅር ስሜቶችና የወሲባዊ ፍላጎቶች መነሳሳትን መኖር አጥብቆ ያበረታታል። ትዳራዊ ሕይወትን በማጠናከር ማህበራዊ መዋቅርን እንደሚያጎለብትም ያምናልል።

ማይክል፦ ወዳጄ ራሽድ፣ሕጃብ ወንድ ወደ ሴቷ እንዳይሳብ የመከላከያ እርምጃ ከሆነ፣ወንዶችም ሴቶች ወደነሱ እንዳይሳቡ ለመከላከል ለምን አይሸፋፈኑም? ሴቶቹም ሥጋዊ ፍላጎቶች አላቸው አይደለም'ንዴ?

ራሽድ (እየሳቀ)፦ ጥሩ ጥያቄ ነው . . በእርግጥ እስላም በወንዶች ላይ የደነገገው የአለባበስ ገደቦች በሴቶች ላይ ከተደነገጉት በጣም የቀለሉ ናቸው። ይህ ለምን እንደሆነ ግልጽ የሚሆነው ያያንዳንዳቸውን ልዩ በሕርያት የበለጠ በመረዳት ይሆናል። በዲዩክ ዩኒቨርሲቲ የኒዩሮሎጂ ባለሞያ የሆኑት ዶክተር ብንያምን ሃይደን ባካሄዱትና በጀርመኑ በርሊነር ሞርገን ፖስት ጋዜጣ ላይ በታተመው የቅርብ ጊዜ ጥናት መሰረት፣የአንጎል አንዳንድ ማእከሎች ወንዶች ወደ ቆንጆ ሴት በመመልከት እንዲደሰቱ ጥረት እንዲያደርጉ ስለሚገፋፏቸው ወንድ ሴትን በመመልከት ይደሰታል፤ሴት ግን መልከ መልካም ወንድ ለመመልከት ጥረት አታደርግም።

ወንድ አንዳንድ ጊዜ ቆንጆና መስህብነት ወዳላት ሴት ለመመልከት ጥረት ለማድረግ የሚገፋፋበትና ሴት ግን የማትገፋፋበት ምክንያት በዚህ ጥናት የተመረመረ ሲሆን፣በሁለቱ ጾታዎች መካከል ያለው ግልጽ ልዩነት መነሻው አንጎል ሆኖ ተገኝቷል። በወንዱ አንጎል ውስጥ ቆንጆ ሴት ሲመለከት የሚነሳሱ አንዳንድ ቦታዎች ሲኖሩ እርካታና ደስታ እንዲሰማው ያደርጉታል። ሴትን በተመለከተ ግን መስህብነት ያለውን ወንድ ስትመለከት ምንም ዓይነት ተጽእኖ የማያስከትልባት በመሆኑ ሁኔታው የተለየ ነው።

ጥናቱ ከደረሰባቸው ውጤቶች መካከል አንደኛው ከቆነጃጅት ወይዛዝርት ምስሎች የወንዶችን ትኩረት በቅድሚያ የሚስበው ፊት መሆኑ ነው። ሴት ግን በአንድ የተለየ አካሉ ላይ ሳታተኩር ምስሉን ሙሉ በሙሉ በጨረፍታ ታያለች።

ሌላው ነጥብ ደግሞ ወንድ ከሴቷ ይበልጥ ጥቃትና ጥሰት ለመፈጸም ድፍረትና ተነሳሳሽነት ያለው መሆኑ ነው። በወንዶች ዘንድ ያለው ወንጀል የመፈጸም ዝንባሌ በጥቅሉ ሲታይ ሴቶች ዘንድ ካለው በአምስት እጥፍ የሚበልጥ መሆኑን ጥናቶች ያረጋግጣሉ። ሴቷ ስሜት የመቀስቀሱን በር ከመጀመሪያው ከዘጋች ግን ወንድ ድንበር አልፎ ጥቃትና ጥሰት እንዳይፈጽምባት ማድረግ ትችላለች።

ማይክል (እየተጣደፈ)፦ ባቡሩ እንዳያመልጠን . . ሰዓቱ ደርሷል፣እንንቀሳቀስ።