የሰማይ ብርሃን (የመለኮታዊ መመሪያ አስፈላጊነት)

የሰማይ ብርሃን (የመለኮታዊ መመሪያ አስፈላጊነት)

ራሽድ ባረፉበት የወጣቶች ማእከል ወደሚገኘው የማህበራዊ አገልግሎት ሳሎን ሲገባ፣ማይክል አንዱን ጠረጴዛ ይዞ የተንጠለጠለውን የመብራቶች አቃፊ የሚያስተውል ይመስል ጣሪያ ጣሪያውን እየተመለከተ ቁጭ ብሎ አገኘው . . ራሽድ ወደርሱ አመራና ሰላምታ አቀረበለት . . ማይክል ግን አላስተዋለም . . ራሽድ ከፊት ለፊቱ ያለውን ወንበር ስቦ ተቀመጠና፦

በብርቱ ሀሳብ የተወጠርክ ትመስላለህ . . ጭንቀትህን መካፈል እችላለሁ?

ማይክል፦ ኦህ . . ይቅርታ፣መምጣትህን አላስተዋልኩም ነበር . .

ራጂቭ ገና አልመጣም?

ራሽድ፦ የቀጠሮ ሰዓታችን አምስት ደቂቃ ይቀረዋል . .

ያውና እየመጣ ነው . .

ራጂቭ፦ ወዳጆቼ ሰላም ለናንተ ይሁን . . ናፍቃችሁኛል።

ራሽድ፦ እኛም ናፍቀንሃል . .

ማይክል፦ እውነቱን ለመናገር በነዚህ ፍሬያማ ውይይቶች በጣም ደስተኛ ነኝ . . ከመምጣታችሁ በፊት በጣም አስፈላጊ በሆነ ጉዳይ ላይ በጥልቀት እያሰብኩ ነበር። እናንተም እንድትጋሩኝ የምፈልገውን ብርቱ ጉዳይ ሳሰላስል ነበር . . ሀሳቡ ካለፈው ውይይታችን ቡቃያ የተገኘ ፍሬ ነው . . አምላክ አድርገን መያዝ የሚገባን የፈጠረንን ጌታ ከሆነ . . እግዚአብሔር ከርሱ ጋር የምንገናኝበትንና እርሱን የምናውቅበትን መንገድ ሳይሰጠን እንዲሁ ሊተወን ይችላል ተብሎ ሊታሰብ ይችላልን? . . እንዳሻን እንድንሆን ዝም ብሎ ይተወናል ተብሎ እንዴት ሊታሰብ ይችላል ?!

ራጂቭ፦ እኔም ወደዚህ ከመምጣቴ በፊት ይህንኑ ነጥብ ሳሰላስል ነበር።

ራሽድ፦ ያነሳችሁት ነጥብ በጣም ወሳኝና ተገቢም ነው .. ሰውን በጥሩ ቁመና የፈጠረው አላህ ﷻ በሰማያትና በምድር ያለውን ሁሉ የገራለትና በቸርነቱ ጸጋውን የዘረጋለት ጌታ፣ይህን ዩኒቨርስ ያስገኘውና ሰብአዊ ፍጡራንን ፈጥሮ ይህን ጸጋ የዘረጋላቸው፣እንዲሁ በከንቱ ያለ ግብና ያለ ዓለማ ፈጠራቸው ሊታሰብ አይችልም፣ይህን አእምሮም አይቀበለውም።

ማይክል፦ ይህን ነጥብ ማንሳታችን በጣም ጥሩ ነገር ነው። ታድያ እግዚአብሔር ዩኒቨርስንና ሰዎችን ፈጥሮ ጸጋውን ለነርሱ የዘረጋበት ዓላማና ግቡ ምንድነው?

ራጂቭ፦ ባለፈው ውይይት ውስጥ ከተጠቀሰው የእውነተኛው አምላክ መገለጫ ባሕርያት ጋር የተያያዙ ይሆናል ብዬ ነው የምጠብቀው። ፈጣሪ አምላክ ይህ ፍጥረት ከመኖሩ በፊት የነበረ ነውና . . በትክክል ለይቼ ማውጣት ግን አልችልም።

ራሽድ፦ ራጂቭ፣የጠቀስከው ነገር ትክክል ነው። እኔ ደግሞ ለይቼ ለማስቀመጥና በምሳሌ ለግንዛቤ ለማቅረብ እሞክራለሁ። አንተ አንድን ነገር በምትወድበት ጊዜ የወደድከው ነገር በተጨባጭ እውን እንዲሆን መፈለግህ በጣም ግልጽ ነው . . አይደለም'ንዴ?

ራጂቭ፦ ልክ ነው።

ራሽድ፦ ታድያ በተጨባጭ እውን እንዳታደርገው ሊያደርግ የሚችለው ምንድነው?

ራጂቭ፦ አሁን ወደ አእምሮዬ የመጣልኝ ምክንያት፣እውን ለማድረግ አልችልም ብዬ መስጋቴ ነው።

ራሽድ፦ እናም አቅምና ችሎታውን ስታገኝ እውን ታደርጋለህ ማለት ነው . . በቃ ጉዳዩ ይኸው ነው።

ማይክል፦ ምሳሌህ ነገሩን የበለጠ ድፍንፍን ከማድረግ ውጭ ምንም አላጠራልኝም።

ራሽድ፦ እውነት አለህ። ለማንኛውም ግን ላሟላው . . ባለፈው ውይይት ፈጣሪ አምላክ ውብና መልካም የሆኑ ባሕርያት እንዳሉት ተስማምተናል። እነዚህ ባሕርያት የተወደዱ ባሕርያት ሲሆኑ፣አላህ ﷻ ይወዳቸዋል፤ ፍጥረታቱም ይወዷቸዋል። ከነዚህ ባሕርያት መካከልም አላህ ﷻ ፈጣሪ፣ኃያል፣ቻይ፣ገዥ፣ንጉሥ፣ . . መሆኑ ይገኙበታል። እነዚህን ባሕርያት መውደድም በተግባር መፈጸምንና ትግበራን ያስከትላል።

አላህ ﷻ ማንምና ምንም የሻውን ነገር ከመፈጸም የማይከለክለው ኃያልና ቻይ ነው። አላህ ﷻፍጥረታትን የፈጠረው ከተወዳጅ ባሕርያቱ አሻራዎች መካከል አንዱ አሻራ ይሆኑ ዘንድ ነው። ፈጣሪ በመሆኑ መፍጠርን ይወዳል፤ጸጋ ሰጭ በመሆኑ ጸጋውን መቸር ይወዳል። ርኅሩህ በመሆኑም መራራትን ይወዳል . . ቻይ በመሆኑም የፈለገውን ሁሉ ከማስፈጸም የሚያግደው ነገር የለም።

ማይክል፦ በዚህ ስሌት ውስጥ የኛ ስፍራ የትነው?!

ራሽድ፦ በዚህ ውስጥ እኛ የምንይዘው ስፍራ አላህ ﷻ እርሱን እንድናውቀውና ከጉድለቶችና ከእንከኖች ሁሉ እርሱን እንድናጠራው የፈጠረን መሆኑ ነው። እንድንጠቀምባቸውና እንድንደሰትባቸው ብቻ ሳይሆን በተግባር እንድናመሰግነውና እንዳናባክናቸው ጸጋዎቹን ዘርግቶልናል። አላህ ﷻ፣ መመስገንና መወደስን ይወዳል። ይህ ደግሞ ለርሱ ብቻ መገዛትንና እርሱን ብቻ በቅንነት ማምለክን ግዴታ ያደርጋል። አምልኮት የሚገባው ሲሳይ ሰጭ ፈጣሪ አንድ አምላክ እርሱ ብቻ ነውና።

ራጂቭ፦ አባባልህ ሁለት ነጥቦችን የሚቀሰቅስ ሲሆን፣አንደኛው አንተ የምትለውን እውን ለማድረግ ሲባል መኖሪያችንን ቤተመቅደስ ውስጥ ማድረግ አለብን ወይ? የሚለው ነው።

ራሽድ፦ ፈጽሞ፣እደዚያ ማለቴ አይደለም። ለአምልኮተ አላህ (ለዕባዳ) የሚሰጠውን እንዲህ ዓይነቱን ቁንጽል ትርጉም የኔ ሃይማኖት የሆነው እስላም አይቀበለውም። ለአላህ መግዛትና እርሱን ብቻ ማምለክ፣ምድሪቱን ማልማትና መገንባትን፣እንዲሁም ሰብአዊ ሥለልጣኔ ማነጽን ባጠቃለለ መልኩ ሁሉንም የሕይወት ፈርጆች የሚያቅፍ ሁለንተናዊ ትርጉም አለው።

ማይክል፦ እኛ ግን ሃይማኖትን ማማከር ሳያስፈልገን አገር እንገነባለን፣ልማት እንሰራለን፣ዘመናዊውን ስልጣኔም እናንጻለን።

ራሽድ፦ ለዚህ ነው የዚህ ሥልጣኔ ውጤት የሆኑና የሰውን ልጅ ደስተኛ እንዳይሆን የሚያደርጉ፣የጭንቀትና የውጥረት መሰረራጨትን፣ራስን የማጥፋት ሁኔታዎች መስፋፋትን፣ያፈነገጠና ተፈጥሮን የሚጻረር ወሲብን፣የማሕበራዊና ቤተሰባዊ ሕይወት መፈረካከስን፣የሰው በሰው መበዝበዝንና ግፍን የመሳሰሉ . . የመርገምት ገጽታዎችን እናንተ ዘንድ የምናስተውለው። በእነዚህ የሚገለጽ ሥልጣኔ፣ሥልጣኔ ከመሆን ይልቅ ከሰብአዊ ጎኖች በተራቆተ ሁኔታ አዳዲስ ነገሮችን መፈልሰፍ ማበልጸግና ማጎልበትን የሚያካትት ቁሳዊ ዕድገትን የማዘመን ሥርዓት ነው። ሰብአዊ ጎኖችን ግምት ውስጥ ካስገባን ሰውን ሰው የሚያሰኙ ገጽታዎቹን መመልከት ግድ ይላል። በቅድሚያ የምናገኘውም መንፈሳዊ ገጽታውን ሲሆን፣ሥልጣኔና ሰብአዊ እንቅስቃሴ ከሰው ልጅ ፈጣሪ ጋር የተሳሰረ በሚሆንበት ጊዜ በሁሉም ጎኖቹ ከሰው ልጅ ሰብእና ጋር የተጣጣመ ይሆናል። ከዚህ አልፎ ከመላው የሰው ዘርና ከዩኒቨርሱ ሁሉ ጋር የተናበበና የተቀናጀ ይሆናል። በቀላሉ ለማስቀመጥ ይህን ሰብአዊ ፍጡርና ፍጥረተ ዓለሙን የፈጠረው፣ምን እንደሚጠቅማቸውና ምን እንደሚጎዳቸው በፍጹምነት የሚያውቅ ነውና።

ማይክል፦ ለምሳሌ ኢንጂነር ራጂቭ ሥራው የተዋጣለት ይሆን ዘንድ የሃይማኖት መጽሐፎችን ማማከር አለበት ማለት ነው? . . እንዴት ነው ሊሆን የሚችለው?! በተጨማሪም የተናገርከውን አምነን ብንቀበል ሕይወታችን የተቃና ይሆን ዘንድ እግዚአብሔር ከኛ የሚፈልገውን እንዴት ነው ማወቅ የምንችለው?

ራሽድ፦ ሃይማኖት በሳይንስና በዓለማዊ እንቅስቃሴ ቴክኒካዊ ጉዳዮች ውስጥ ጣልቃ ይገባል ማለቴ አይደለም። የሚያደርገው ነገር ቢኖር ለሕይወት እንቅስቃሴዎች የስነምግባር ማእቀፎችንና መርሆዎችን ማስቀመጥ፣ለተለያዩ የኑሮ ዘርፎችም ሥርዓቶችን ማኖር ነው። በተጨማሪም የሰው ልጅ ከሌሎች ሰዎች ጋር፣ከማሕበረሰቡ ጋር፣ማሕበረሰቦችም እርስ በርሳቸው አንዱ ከሌላው ጋር ያላቸውን ግንኙነቶች ያደራጃል። ይህ ሰብአዊ ፍጡር በዚህ ዩኒቨርስ ውስጥ የሚይዘውን ስፍራና ከፈጣሪ ጌታው ጋር ያለውን ግንኙነት ለሰው ልጅ ያሳውቃል።

ለማብራራት ያህል ሁለት ምሳሌዎችን ልስጣችሁ። አላህ ﷻ እኛን ፈጥሮን መሬትንና በላይዋ ላይ ያለውን ሁሉ ፈጥሯል። ከሰማይ ባወረደው ውሃ ከምድር ቀለብ አብቅሎልናል። ከባቀለው እጽዋት ከፊሉን መድኃኒት ከፊሉን ገዳይ መርዝ አድርጓል። ለምግብ የሚሆነውን ጠቃሚ ከጎጂው ማወቅ የሚያስችለን አእምሮ አድሎናል። ልምዳችንን ተጠቀመን ከነዚህ እጽዋት መድኃኒቶችንና ቅመሞችን . . ማመንጨት የሚያስችለን ብቃትም ሰጥቶናል። ከዚያም በሃይማኖቱ ውስጥ መሰረታዊ መርሕ ያስቀመጠልን ሲሆን፣እኛን የሚጎዳን ወይም ሌሎችን የሚጎዳ ማንኛውንም ነገር መጠቀምም ሆነ መፈጸም ለኛ ፈጽሞ የተከለከለ መሆኑን ደንግጓል።

ሌላው ምሳሌ፣የሰው ልጆች ፍትሕ መልካም ነገር መሆኑንና ግፍና ፍርደ ገምድልነት መጥፎ ነገር መሆኑን ሙሉ በሙሉ ይስማሙበታል። ፍትሕን በሚመለከቱ ዝርዝር ጉዳዮች ውስጥ ሲገባ ግን ብዙ ልዩነቶች መኖራቸውን አንገነዘባለን። ይህ የሚሆነው ሰዎች በአስተሳሰብ በዓላማና በግባቸው የሚለያዩ ከመሆናቸውም በላይ፣በተለያዩ ቡድኖች መካከል የጥቅም ግጭት በመኖሩ ነው። ስለዚህም የዚህ ፍትሕ ምንጭና መገኛ ከሰው ልጆች በላይና የከፍተኛ ሥልጣን ባለቤት ከሆነ፣መላውን የሰው ዘር በእኩልነት ከሚመለከት፣ከወገንተኝነት፣ከአስመሳይነት፣ ከግላዊ ዝንባሌና ስሜት፣ከአድልኦና ከግላዊ ጥቅም ፈጽሞ ከጸዳ መሆን ይኖርበታል።

አላህ ﷻ ከእኛ የሚፈልገውን ነገር ማወቅ የምንችለው እንዴት እንደሆነ በሚመለከት፣ይህም ከአላህﷻ ባሕርያት ጋር የተያዘ ነው። እርሱ ንጉሥና ጥበበኛ ነው . . በውይይታችን መጀመሪያ ላይ አላህ ﷻይህን ዩኒቨርስ የፈጠረው ለከንቱ ሳይሆን ለታላቅ ጥበብ መሆኑን ስንገለጽ ካነሳነው ጋርም ተያያዥነት አለው . . ለምሳሌ ያህል አንድ ኩባንያ ያለ ሥርዓት፣ያለ ሥራ ዝርዝር፣ያለ መተዳደሪያ ደንብና ያለ አመራር፣ድርጅቶቹንና ተቋሞቹን . . መስርቶ ሠራተኞቹን አሰማርቶ ማምረትና መሸጥ አስተዋይነትና ጥበብ ነው ብለህ ታስባለህ?!

ማይክል፦ በእርግጥ አላስብም።

ራሽድ፦ ይህን ዩኒቨርስና ፍጥረተ ዓለም በተመለከተም ነገሩ ሳይታለም የተፈታ ነው . . ። ስለዚህም አላህ ﷻ የሰው ልጆችን ለሃይማኖታቸውና ለዓለማዊ ሕይወታቸው ወደሚበጃቸው መንገድ ይመሯቸውና ያደርሷቸው ዘንድ፣መጽሐፎቹንና መለኮታዊ ሰነዶቹን በርሱና በአገልጋዮቹ መካከል አምባሳደሮቹ ባደረጋቸው ነብያትና መልእክተኞች አማካይነት አስተላልፎላቸዋል። ነብያትና መልእክተኞች፣በአላህ ﷻ እና በፍጠራኑ መካከል ትእዛዝና እገዳውን አስመልክተው የሰው ልጆችን ከጌታቸው ጋር የሚያስተዋውቁ፣የፍትሕን መገለጫዎችና የግፍን ጉዳቶች የሚያመላክቷቸው፣በዛሬው ሕይወታቸውም ሆነ በወዲያኛው ሕይወታቸው የሚጠቅማቸውንና የሚጎዷቸውን ያብራሩላቸው ዘንድ አገናኞች ተደርገው ተልከዋል።

የሰው ልጅ በሁለት እንቅስቃሴዎች መካከል ማለትም ጥቅም በሚያስገኝለት እንቅስቃሴና ጉዳት በሚያስወግድለት እንቅስቃሴ መካከል በመሆኑ፣መለኮታዊ መልእክትና መመሪያ የግድ ያስፈልገዋል። መልእክቱ የሚጠቅመውን ከሚጎዳው የሚለይበት ብርሃን ሲሆን፣ለምድሪቱ የፈነጠቀ የአላህ ﷻ ብርሃንና በአገልጋቹ መካከል የርሱ ፍትሕ ነው።

የመለኮታዊው መልእክት ዓላማ ጠቃሚውን ከጎጂው በደመነፍስ መለየት አይደለም፤ይህንን እንስሳትም ያደርጉታል። ለምሳሌ ያህል አህያ ገብስና አፈርን ለይታ ታውቃለች። ተፈላጊው ዓለማ በዛሬውም ሆነ በወዲያኛው ሕይወቱ አድራጊውን የሚጎዱትን ድርጊቶች፣በዛሬው ሕይወቱም ሆነ በወዲያኛው ከሚጠቅሙት ድርጊቶች መለየት ነው። መለኮታዊው መልእክት ባይኖር ኖሮ የሰው ልጅ አእምሮ በሕይወቱ ውስጥ የሚጎዱትንና የሚጠቅሙትን ነገሮች ዝርዝር ለማወቅ ባልተመራ ነበር።

ራጂቭ፦ ሁለተኛው ነጥብ ደግሞ፣ሰዎች ለጌታ አምላክ ባላቸው አቋምና ለርሱ ባላቸው የተገዥነት ደረጃ የተለያዩ መሆናቸውን እንመለከታለን። ታድያ በርሱ ጸጋ በመታደልና በመጠቀም እንዴት እኩል መሆን ይችላሉ?!

ራሽድ፦ ይህ በጌታቸው ላይ ያላቸው አቋም ይገለጥ ዘንድ የመፈተኛና የመሞከሪያ ጥበቡ የወሰነው ነገር ነው። ይሁን እንጂ በተዘጋጀላቸው ሽልማትና በፍጻሜው ውጤት ግን ፈጽሞ እኩል አይሆኑም። የሽልማቱ መሰረት እንደ ውስጠ ደንቦችና ሰነዶች በማመሳከሪያ ዋቢነት የሚታዩት የመልእክተኞችና የነብያት መልእክቶች ናቸው።

ማይክል፦ ሦስተኛ ነጥብ ልጨምር፤የሰው ልጆች በመካከላቸው አታላይ፣ግፈኛና ውሸታም የሚገኝባቸውና አንዳንዶቹም ሕግ ሳይፈጽምባቸው ከሕብረተሰቡ ቅጣት ሊያመልጡ የሚችሉ እየሆኑ፣ሁሉም በእግዚአብሔር ጸጋዎች ተጠቃሚዎችና ተቋዳሾች የሚሆኑት እንዴት ነው?!

ራሽድ፦ ይህም እንደዚሁ የመፈተኛና የመሞከሪያ ጥበቡ መገለጫ ነው። እነዚህ ሰዎች ከሕግና ሕብረተሱ ከሚጥልባቸው መቀጫ ቢያመልጡ ግን፣ከሚወርድባቸው መለኮታዊ ፍርድና ከፍትሐዊ ቅጣቱ ፈጽሞ ማምለጥ አይችሉም። ይህ ከሞት በኋላ ዳግም መቀስቀስ፣በሰሩት ነገር መመርመርና በፍርዱ ቀን ዘላለማዊውን ውሳኔ ማግኘት የተደራጀበትን ጥበብ የሚገልጽ ነው። በዚህ የፍርድ ቀን የሰው ልጅ ራሱን፣ፈጣሪ አምላኩንና ሌሎች ፍጡራንን አስመልክቶ በሠራት እያንዳንዷ ጥሩም ሆነች ክፉ ሥራ ተገቢ ፍትሐዊ ዋጋውን ያገኛል።

ሰዎች የሚፋረዱበትና የሚዳኙበት ተለይቶ የታወቀ መፋረጃ ግን የግድ መኖር ይኖርበታል . . እዚህ ላይም የሰው ልጆችን በምን መሰረት ላይ እንደሚጠየቁና እንደሚመረመሩ፣በያዙት አቋሞቻቸው ወይም ይህን መሰረት በመጻረራቸው ሊያስከትልባቸው የሚችለውን ነገር የሚያሳውቋቸው የአላህ ﷻመልእክተኞች ሚና ይመጣል። መልእክተኞቹ የወዲያኛው የኣኽራ ሕይወት ዘላለማዊ ተድላና ደስታ ወይም ዘላለማዊ ሥቃይና ቅጣት እንዴት እንደሚሆንም ያሳውቋቸዋል።

ራጂቭ፦ ራሽድ፣በእውነተኛው ሃይማኖት መለያ ባሕርያት ላይ መነጋገር ግድ ነው ማለታችንን ታስታውሳለህ?

ራሽድ፦ ልክ ነው፤አስታውሳለሁ።

ራጂቭ፦ የዚህ ርእሰ ጉዳይ ፋይል የሚከፈትበት ተገቢ ጊዜ አሁን ይመስለኛል።

ማይክል፦ ራጂቭ እውነትህን ነው . . ቀጣዩን ውይታችንን በተለይ ለዚህ ርእሰ ጉዳይ እንመድብ ባይ ነኝ።