የርኅራሄ መንገድ

የርኅራሄ መንገድ

የቅዱስ ቁርኣን ምዕራፎች የሚጀምሩት {እጅግ በጣም ርኅሩህ በጣም አዛኝ} የሆነውን የአላህን ስም በማውሳት ነው። አላህ (ሱ.ወ.) በነፍሱ ላይ አዛኝ መሆንን ወሰኗል፦

{ጌታችሁ በነፍሱ ላይ እዝነትን ጻፈ፤}[አል አንዓም፡54]

እዘነቱና ችሮታው ለሁሉ ደራሽና የሰፋ ነው፦

{ችሮታም ነገሩን ሁሉ ሰፋች፤}[አል አዕራፍ፡156]

ሰዎችን ለርኅራሄው እንዲጓጉ አድርጎ አብስሯቸዋል፤ ከእዝነቱ ፈጽሞ ተስፋ እንዳይቆርጡም አስጠንቅቋቸዋል፦

{በላቸው ፦ እናንተ በነፍሶቻችሁ ላይ ድንበር ያለፋችሁ ባሮቼ ሆይ! ከአላህ እዝነት ተስፋ አትቁረጡ፤አላህ ኃጢአቶችን በመላ ይምራልና፣እነሆ እርሱ መሓሪው፣አዛኙ ነውና።}[አል ዙመር፡53]

አላህ (ሱ.ወ.) ምሕረትን የሚወድ አዛኝ ነው። ነቢዩ  እንዲህ ብለዋል፦ «(አላህ (ሱ.ወ.) ጸሐይ በምዕራብ ተመልሳ እስከምተወጣበት ጊዜ ድረስ፣ቀን ላጠፋው ሰው ምሕረት ሊያደርግ ሌሊት እጁን ይዘረጋል፤ሌሊት ላጠፋው ሰው ምሕረት ሊያደርግ ቀን እጁን ይዘረጋል።» [በሙስሊም የተዘገበ] ከጌታቸው የተላለፈላቸውን ሲነግሩንም ነቢዩ  እንዲህ ብለዋል፦ «አላህ (ሱ.ወ.) ፍጥረታትን ከመፍጠሩ በፊት እዝነቴ ቁጣዬን ቀድሟል የሚል ጽፏል።»[በቡኻሪና በሙስሊም የተዘገበ] የአላህን እዝነትና ርኅራሄ አስመልክተው ነቢዩ  እንዲህ ብለዋል፦ «አላህ (ሱ.ወ.) ርኅራሄን አንድ መቶ ክፍል አደረገው፤ዘጠና ዘጠኙን እራሱ ዘንድ ያዘው፤አንዱን ክፍል ብቻ ወደ ምድር አወረደው፤ከዚህ አንድ ክፍልም ባዝራ ፈረስ ልጇ እንዳይጎዳ በመራራት ኮቴዋን ከፍ እስክታደረግ ድረስ ፍጥረታት እርስ በርሳቸው ይተዛዘናሉ።» [በቡኻሪ የተዘገበ]

አላህ (ሱ.ወ.)ነቢዩን  ለዓለማት ርኅራሄና እዝነት አድርጎ ልኳቸዋል፦

{(ሙሐመድ ሆይ!) ለዓለማትም እዝነት አድርገን እንጅ አልላክንህም።}[አል አንቢያ፡107]

በመጠቀ ስነምግባርና በታላቅ ጠባይ የተዋቡም አድርጓቸዋል፦

{አንተም በታላቅ ጠባይ ላይ ነህ።}[አል ቀለም፡4]

ለዚህም ነው ርኅራሄና እዝነት የነቢዩ  ልዩ መገለጫ ባሕሪ የሆነው፤ይህ ባይሆን ኖሮ ሰዎች ከዙሪያቸው በተበተኑ ነበር። አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብለዋል፦

{ከአላህም በኾነች ችሮታ ለዘብክላቸው። ዐመለ መጥፎ ልበ ደረቅም በኾንክ ኖሮ ከዙሪያህ በተበተኑ ነበር።}[ኣሊ ዒምራን፡159]

በተጨማሪም ነቢዩ  የሕዝባቸውን መቸገር የማይፈልጉ ርኅሩህ አዛኝ ናቸው። አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብለዋል፦

{ከጎሳችሁ የኾነ፣ችግራችሁ በርሱ ላይ ጥኑ የኾነ፣በናንተ (እምነት) ላይ የሚጓጓ፣በምእመናን ርኅሩህ አዛኝ የኾነ መልክተኛ በእርግጥ መጣላችሁ።}[አል ተውበህ፡128]

ስለዚህም እጅግ በጣም ርኅሩህ፣በጣም አዛኝ ከሆነው አላህ (ሱ.ወ.) ዘንድ፣ለሕዝባቸው ርኅሩህ በሆኑት ነቢይ  አማካይነት የመጣው እስላም፤መላውን የሰው ልጅ ከግፍ፣ከመድልዖ፣ከጥላቻ፣ከጭንቀት፣ከትካዜ፣ ከአለመረጋጋት፣ከቂም በቀል፣ከእብሪት፣ከጭቆናና ከአምባገነንነት አበሳ ነጻ የሚያወጣ የዓለማት ሁሉ እዝነትና ርኅራሄ ሆኖ ነው፦

«(ሙሐመድ ሆይ!) ለዓለማትም እዝነት አድርገን እንጅ አልላክንህም።»[አል አንቢያ፡107]

ለሙስሊሞች እዝነት ነው፤ሙስሊም ላልሆኑትም እንደዚሁ እዝነት ነው። ለትጉሃን አማኞች እዝነት ነው፤ለአመጠኞችም እንዲሁ እዝነት ነው። ለትልቁ ለትንሹም፣ለወንዱ ለሴቱም፣ለወጣቱ ለሕጻኑም፣ለሀብታሙ ለድሃውም . . እዝነት ነው። ለዓለማት ሁሉ እዝነት ነው።

ለዚህም ነው እስላም እዝነትና ርኅራሄን መፈለግና ማበረታታትን፣ለርሱ መጓጓትንና ለመተዛዘን አደራ መባባልን ይዞ የመጣው። አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብለዋል፦

{ከዚያም ከነዚያ ከአመኑትና በመታገሥ አደራ ከተባባሉት፣በማዘንም አደራ ከተባባሉት ሰዎች አልኾነም።}[አል በለድ፡17]

ነቢዩ  እንዲህ ብለዋል፦ « ለሰዎች የማይራራ ሰው አላህ አይራራለትም።} [በቡኻሪና ሙስሊም የተዘገበ] ነቢዩ  እንዲህ ብለዋል፦ «ለሌሎች አዛኝ የሆኑትን አልረሕማን ያዝንላቸዋል። በምድር ለሚገኙት ርኅሩህ ሁኑ፣በሰማይ ያለው ይራራላችኋልና። ማሕጸን (ረሕም) አልረሕማን ከሚለው (የአላህ ስም) የወጣ ነውና (ዝምድና) የቀጠለውን ሰው አላህ ይራራለታል፤የቆረጠውን ሰውም አላህ እዝነቱን ይቆርጥበታል።» [በትርምዚ የተዘገበ] በተጨማሪም ነቢዩ  እንዲህ ብለዋል፦ «ከእዝነት የሚራቆተው እድለ ቢስ መናጢ ብቻ ነው።» [በትርምዚ የተዘገበ]

አላህ (ሱ.ወ.) በሰዎች መካከል መተዛዘንና ርኅራሄ እንዲኖር ያዘዘ ሲሆን፣በአጠቃላይ መልኩ እንደ ጠባይና የአነዋነዋር መንገድ እንዲያዝ አበረታቷል። ሸሪዓውም በእዝነትና በርኅራሄ የተለየ ትኩረት ሊሰጣቸው የሚገቡ የተወሰኑ ክፍሎችን ለይቶ አስቀምጧል። ከነዚህ መካከል የሚከተሉት ይገኛሉ፦

1-ለሰው ልጆች ሁሉ ርኅሩህ መሆን ፦ ነቢዩ  ለኡመታቸው እዝነትና ርኅራሄ ነበሩ፤በርሳቸው አማካይነት አላህ (ሱ.ወ.) ሕዝባቸውን ከጨለማ ወደ ብርሃን፣ከዕድለ ቢስነት ወደ መታደል በማውጣት መድህን እንዲያገኝ አድርጓል። የነቢዩ  እዝነት ግን በሕዝባቸው ላይ ብቻ ሳይወሰን እስላምን ያልተቀበሉ ካፍሮችንም ጭምር አካቷል። ያልሰለሙ የመካ ሰዎችን አስመልክተው ነቢዩ  እንዲህ ብለዋል፦ « . . የለም፤ አላህ ከአብራኮቻቸው በርሱ ምንም ሳያሻርክ እርሱን ብቻ የሚግገዛ ሰው እንዲያወጣ እመኛለሁ።» [በቡኻሪና ሙስሊም የተዘገበ] ነቢዩ  በኡሑድ ውጊያ ላይ ሲጎዱ ባልደረቦቻቸው «በነዚህ አጋሪዎች (ሙሽሪኮች) ላይ እርግማን እንዲያወርድባቸው አላህን ይለምኑ» ሲሏቸው መልሳቸው፦ {አላህ ሆይ! ሕዝቦቼን ምራቸው፤እነሱ አያውቁምና።} የሚል ነበር። በሌላ ዘገባ ደግሞ «የአላህ መልክተኛ ሆይ! በሙሽሪኮቹ ላይ ዱዓእ ያደርጉባቸው» ሲባሉ «ረጋሚ ሆኜ አልተላክሁም፤የተላክሁት ርኅሩህ ሆኜ ነው፡፡» [በሙስሊም የተዘገበ] ማለታቸው ተመልክቷል።

2-ለሕጻናት ርኅሩህ መሆን፦ አንዱ የነቢዩ  ባልደረባ እንዳሉት ከአላህ መልክተኛ ጋር ሆነው ልጃቸው ኢብራሂም በማጣጣር ላይ እያለ ወደ ክፍሉ አብረው ገቡ፤በዚህ ጊዜ የነቢዩ  ዓይኖች ሲያነቡ ተመለከቱና ዐብዱረሕማን ብን ዐውፍ {የአላህ መልክተኛ እርስዎም?!} አሉ። ነቢዩም መልሰው፦ {የዐውፍ ልጅ ሆይ ይህማ ርኅራሄ ነው} አሉና በመቀጠል ፦ «ዓይን በእርግጥ ያነባል፤ልብም ያዝናል፤ጌታችን ከሚወደው ነገር ውጭ ግን ምንም አንልም፤ኢብራሂም፣እኛ ካንተ በመለየታችን በእርግጥ አዛኞች ነን።» አሉ። [በቡኻሪና በሙስሊም የተዘገበ] በተጨማሪም ነቢዩ  ኡሳማን በአንደኛው ጭናቸው፣ሐሰንን ደግሞ በሌላኛው ጭናቸው ላይ አስቀምጠው ያቅፏቸውና {አላህ ሆይ! ራራላቸው እኔ እራራላቸዋለሁና።} ይሉ ነበር። አንድ ሰው ወደ ነቢዩ  መጥቶ ሐሰንና ሑሰይንን ሲስሟቸው አየና {ልጆቻችሁን ትስማላችሁ?! እኔ አስር ልጆች አሉኝ አንዳቸውንም ፈጽሞ ስሜ አላውቅም} ሲላቸው ነቢዩ  ፦ {የማይራራ ሰው አይራራለትም።} አሉ።

3-ለድኩማን ርኅሩህ መሆን ፦ ነቢዩ  መስጊድ ታጸዳ የነበረችን ጥቁር ሴት አጥተው ምን እንደሆነች ሲጠይቁ እንደሞተች ነገሯቸው። «አታሳውቁኝም ኖሯል . . በሉ ወደ መቃብሯ ምሩኝ» አሏቸውና መቃብሯን ሲያሳዩዋቸው የጀናዛ ሶላት ሰገዱባት። [በቡኻሪና ሙስሊም የተዘገበ] የነቢዩ  አገልጋይ (ኻድም) አነስ ብን ማሊክ (ረ.ዐ.)፦ {ነቢዩን  ለአስር ዓመታት አገልግያለሁ፤አንድም ቀን እፎይ፣ለምን እንዲህ አደረግህ፣ወይም ለምን እንዲህ አላደረግህም ብለውኝ አያውቁም።} ብለዋል። [በቡኻሪ የተዘገበ] ታላቁ ሶሓቢይ እብን መስዑድ (ረ.ዐ.) እንዲህ ይላሉ፦ አንድ ብላቴናዬን (ባሪያየን) በመምታት ላይ እያለሁ ከጀርባዬ {አንተ የመስዑድ አባት፣አንተ እርሱን ከምትችለው በላይ አላህ በእርግጥ ባንተ ላይ ቻይ መሆኑን ዕወቅ} የሚል ድምጽ ሰማሁ። ዞር ስል የአላህ መልክተኛ  መሆናቸውን አየሁ። {የአላህ መልክተኛ ሆይ! ለአላህ ብዬ (ከባርነቱ) ነጻ ለቅቄዋለሁ} አልኳቸው። እሳቸውም፦ {ባታደርገው ኖሮማ እሳት በለበለበህ ነበር} አሉ።

4-ለእንስሳት ርኅሩህ መሆን፦ የአላህ መልክተኛ  ሆዱ ከጀርባው ጋር በተጣበቀ ግመል አጠገብ አለፉና፦ «በነዚህ በማይናገሩ እንስሳት ሁኔታ አላህን ፍሩ፤ጉልበት ሲኖራቸው ጋልቧቸው፤ለቀጣይ አገልግሎት ብቁ ይሆኑ ዘንድም ሳይደክሙ ተውዋቸው።» አሉ። [በአቡ ዳውድ የተዘገበ] የአላህ መልክተኛ  ወደ አንድ የአንሷር ሰው አጥር ሲገቡ አንድ ግመል ያያሉ፤ግመሉ ነቢዩን  ሲያይ ጩሆ ዓይኖቹ እንባ አፈሰሱ፤ነቢዩ  ሄደው ራሱን ከኋላ ሲደባብሱት ጩኸቱን አቆመ። የዚህ ግመል ጌታ ማነው የማን ግመል ነው ብለው ሲጠይቁ አንድ የአንሷር ወጣት መጣና የአላህ መልክተኛ ሆይ! የኔ ነው አላቸው። እሳቸውም፦ «አላህ በሰጠህና ባለቤቱ ባደረግህ በዚህ እንስሳ ሁኔታ አላህን አትፈራም?! የምታስርበውና በሥራ የምትጎዳው መሆንህን በኔ ላይ ከሶሃል።» አሉት። [በአቡ ዳውድ የተዘገበ]

እነዚህ ነቢዩ  ለዓለማት ለእንስሳትም ጭምር እዝነትና ርኅራሄ ተደርገው መላካቸውን የሚያመለክቱ በጣም ጥቂት ምሳሌዎች ብቻ ናቸው። የዚህን ሃይማኖት አካሄድና መንገዱን የሚያብራሩ የእዝነት መገለጫዎችና የመተግበሪያ መስኮች እስላም ውስጥ በጣም ብዙ ናቸው። ይህ እዘነትና ይህ ርኅራሄ ግን የተዋራጅነትና የበታችነት ሳይሆን የልዕልና እና የከበሬታ እዝነትና ርኅራሄ ነው።