የማዘናጊያ ጽዋ

የማዘናጊያ ጽዋ

ራሽድ በቀጠሮው መሰረት ከወዳጁ ከማይክል ጋር ካፌቴሪያው ውስጥ ተገናኘ። እንደተቀመጡም ማይክል ለራሽድ እንዲህ አለው፦

ዛሬ ትስማማበታለህ ብዬ የማስበውን ርእሰ ጉዳይ አነሳለሁ።

ራሽድ፦ ወዳጄ ትንሽ ተረጋጋ፣መጀመሪያ ለመስተንግዶህ የሚጠጣ ነገር እንዘዝ!

ማይክል፦ በመጣደፌ ይቅርታ፣እውነትህን ነው . .

ማይክል አስተናጋጁን ጠራ . . አስተናጋጁ መጥቶ ምን እንደሚወስድ ራሽድን ጠየቀው።

ራሽድ፦ ሻይ።

አስተናጋጅ (በመገረም)፦ ሻይ?!

ራሽድ፦ በሎሚ።

አስተናጋጅ (የበለጠ በመገረም)፦ በሎሚ?!

ማይክል (እየሳቀ)፦ አዎ፣እርሱ ሙስሊም ነው፣አስካሪ መጠጥ አይጠጣም . . ከወዳጄ ጋር ለመመሳሰል ለኔም ሻይ በሎሚ ይሁንልኝ።

አስተናጋጁ የታዘዘውን ለማቅረብ ሲሄድ፣ራሽድ “ያስገረመው ምን እንደሆነ አይገባኝም!” ሲል አጉረመረመ።

ማይክል፦ ወዳጄ፣በኛ አገር አስካሪ መጠጥ መጠጣት ልክ ውሃ እንደ መጠጣት ነው። የተለያዩ ስሞች፣ጣዕሞች የመጠጫ መንገዶች ያሏቸው ቁጥራቸው የበዛ የመጠጥ ዓይነቶች ይገኛሉ። ለዚህ ነው ትእዛዝህ ከነዚህ አንዱን እንኳ ባለማካተቱ አስተናጋጁ የተገረመው፤ሻይ የሚያዙት ሕጻናት ብቻ ናቸው . . ይቅርታ . . በጣም ይቅርታ . .

ራሽድ፦ በጣም የሚገርም ነው!

ማይክል፦ ምኑ ነው የሚገርመው? ለኛ ምንም አዲስ ነገር የለበትም። እዚህ በኛ አገር ብቻ ሳይሆን በሁሉም የምዕራብ አገሮች ያለ ነገር ነው።

ራሽድ፦ እሰገራሚው ነገርም በትክክል ይህ መሆኑ ነው።

ማይክል፦ እንዴት?!

ራሽድ፦ ምክንያቱም አብዛኞቻችሁ የክርስትና እምነት ተከታዮች ናችሁ። በመጽሐፍ ቅዱስ ታምናላችሁ ተብሎም ይጠበቃል፤ብሉይ ኪዳን አስከሪ መጠጥ ከፍተኛ ጉዳት እንዳለበት በማስጠንቀቅ ሲያብራራ እንዲህ ብሏል፦ ((የወይን ጠጅ ከሚጠጡ ጋር አትቀመጥ፣ለሥጋም ከሚሣሡ ጋር፤)) [መጽ. ምሳሌ 23፣20] መጠጥ ጠጥቶ መስከርን ሲከለክልም እንዲህ ብሏል፦ ((ስካርን ለመከተል በጥዋት ለሚማልዱ፣የወይን ጠጅም እስኪያቃጥላቸው እስከ ሌሊት ድረስ ለሚዘገዩ ወዮላቸው፤)) [ኢሳ. 5፣11]

((እግዚአብሔርም አሮንን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ እንዳትሞቱ ወደ መገናኛው ድንኳን ስትገቡ አንተና ልጆችህ የወይን ጠጅና የሚያሰክርን ነገር ሁሉ አትጠጡ፤ይህም ለልጅ ልጃችሁ የዘላለም ሥርዓት ይሆናል፤)) [ዘሌዋውያን 10፡9] ((ከወይንም ከሚወጣው ሁሉ አትብላ፣የወይን ጠጅንም የሚያሰክርንም ነገር አትጠጣ፣. . )) [መሳፍንት 13፡14] ከነዚህ በተጨማሪ ጠጭዎችን የሚወቅሱ፣ከሰካራሞች ጋር መቀመጥን የሚከለክሉ፣በዓይን መመልከትን እንኳ የሚያጥላሉ ብዙ ጥቅሶች ይገኛሉ።

ማይክል፦ ራሽድ ተረጋጋ፤መጽሐፍ ቅዱስን አንተ ብቻ የምታውቅ አድርገህ አታስብ። ብዙዎቹ የሃይማኖት መሪዎቻችን አስካሪ መጠጥ የተፈቀደ መሆኑን ያረጋግጣሉ፤አንዳንዶቹ ነቢያትም ጠጥተው ስለ መስከራቸውም ብሉይ ኪዳንን በአስረጅነት ይጠቅሳሉ። ከአንዳንዶቻቸው እንደሰማሁትም የተከለከለው መስከር እንጂ መጠጣት አይደለም። ወንጌል ውስጥ ኢየሱስ ወይን ጠጅ መጠጣቱ ተመልክቷል። (ሉቃስ 7፡33) እንዲህ ይላል፦ ((መጥምቁ ዮሐንስ እንጀራ ሳይበላ፣የወይን ጠጅም ሳይጠጣ መጥቶ ነበርና፦ ጋኔን አለበት አላችሁት። የሰው ልጅ እየበላና እየጠጣ መጥቷልና፦ እነሆ በላተኛና የወይን ጠጅ ጠጭ፣የቀራጮችና የኃጢአተኞች ወዳጅ አላችሁት።))

ራሽድ፦ ወዳጄ አንተ የምትለው ነገር በምዕራቡ ሰውና በምዕራባዊው ሕብረተሰብ ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ ወዳላቸው ሁለት አሳሳቢ ጉዳዮች ይወስደናል።

አንደኛ፦ ይህን ስናገር እያዘንኩ ነው፣አሁን ያለው የመጽሐፍ ቅዱሳችሁ ሁኔታ የሚያረጋግጠው፣ብዙ ነገሮች ሰርገው የገቡበትና ዲያብሎስን የሚያገለግሉ እጆች ያዛቡት በመሆኑ በብዙ ጉዳዮች ላይ እርስ በርሱ የሚጣረስ መሆኑን የሚያረጋግጥ ነው። ከነዚህ መካከል መጠጥን መፍቀዱና መከልከሉ አንዱ ነው። አንድ ቦታ ላይ እየከለከለ ሌላ ቦታ ላይ ይፈቅዳል። ኢየሱስ እንደጠጣ አድርጎ ሲያቀርብ ሌላ ቦታ ላይ ደግሞ ከዚህ ያጠራዋል። ገብርኤል ስለ አልመሲሕ ሲገልጽ ሉቃስ ውስጥ እንዲህ ብሏል፦ ((በጌታ ፊት ታላቅ ይሆናልና፣የወይን ጠጅና የሚያሰክር መጠጥ አይጠጣም፤ . . )) [ሉቃስ 1፡15] ይህ መቼም ግልጽ የሆነ መጣረስ ነው።

ሁለተኛ፦ እናንተ ዘንድ መጽሐፍ ቅዱስን አንብቦ መረዳት ለሃይማኖት መሪዎች ብቻ የተፈቀደና የተተወ ሲሆን፣አንዳንዶቻቸው በእግዚአብሔር ስም የሚናገር ተጠሪ አድርገው ራሳቸውን ያቀርባሉ። አንዳንዶቹ ደግሞ እርም የማድረግና የመፍቀድ (ሐላልና ሐራም የማድረግ) መለኮታዊ ሥልጣን አለን ብለው ያስባሉ። በዚህ ሁሉ እናንተ እነሱን ትከተላላችሁ።

ማይክል፦ ይህ እውነት ነው። ለዚህም ነው ግልጽ ሆኜ ብዙዎቻችን በመጽሐፍ ቅዱስ የምር አናምንም፤በሃይማኖት መሪዎች ላይም እምነት አንጥልም ብዬ የምነግርህ። ከአውሮፓ የሕዳሴ ዘመን ጀምሮ በሕብረተሰባችን ውስጥ ከፍተኛ ለውጥ ተከስቷል። በመሆኑም ተግባራዊ እምነታችን በአእምሮና በቁሳዊ ዕውቀት ብቻ ላይ የተመሰረተ ሆኗል . . እናም መጽሐፍ ቅዱስንና ሃይማኖትን ወደ ጎን ብለን በአእምሮና በሳይንስ ቋንቋ ብቻ እንነጋገር።

ራሽድ፦ ፍቀድልኝና አንደኛ ይህ በቤተክርስቲያን አምባገነንትና በተለይም በመካከለኛው ክፍለ ዘመን በሳይንስና በዕውቀት ላይ ባካሄዴችው ጦርነት ምክንያት በናንተና በሃይማኖት መካከል የተፈጠረ የራሳችሁ ችግር ነው። በጣም የሚያሳዝነው ግን ሁሉንም ሃይማኖት ቤተክርስቲያን አድርጋችሁ መቁጠራችሁ ነው፤ሁሉም ሃይማኖት ከሳይንስ ጋር የሚጋጭና በቤተአምልኮው ውስጥ ብቻ ታጥሮ መቅረት እንዳለበት አድርጋችሁ መውሰዳችሁ ነው። እስላም ውስጥ ግን እኛ እንዲህ ዓይነት ችግር ፈጽሞ የለብንም። ይልቅዬ የኛ ሃይማኖት ሳይንስና ዕውቀት መገብየትን ያበረታታል፣የሃይማኖት መሪዎች ብቻ እንጂ ሌሎች የማያውቁት ሃይማኖታዊ ምስጢርም ሆነ ዕውቀት የለበትም ።

ለማንኛውም አንተን በሚያሳምንህ ቋንቋ እንነጋገር። በኔ በኩል የሳይንስ ቋንቋ ከሃይማኖቴ ጋር በምንም መንገድ አይጻረርም፤ይህንንም በሚገባ አረጋግጥልሃለሁ።

ማይክል፦ እንግዲያውስ መቀጠል ትችላለህ።

ራሽድ፦ ዛሬ የምታምኑት በአእምሮና በሳይንስ ነው ብለሃል፤እስኪ ከመነሻው ልጠይቅህና፣ለአእምሮ ይህን ያህል ከፍተኛ ግምት የምትሰጡት ከሆነ አስካሪ መጠጥ መውሰድ አእምሮን ይጠብቃል ወይስ ያናጋል?

ማይክል፦ ይህ ወጥመድ እንጂ ጥያቄ አይደለም።

ራሽድ፦ አላህ (ሱወ) የሰውን ልጅ ክቡር ፍጡር አድርጎት በብዙዎቹ ፍጥረታቱ ላይ ብልጫ ሰጥቶታል። የአእምሮን ታላቅ ጸጋም አጎናጽፎታል። እስላም ውስጥ አእምሮውን የሳተ ሰው ሃይማኖታዊ ግዴታዎች አይጸኑበትም፤አላህ (ሱወ) ይህን ታላቅ ጸጋ እንድንጠብቀው፣ እንድንከባከበውና ሊጎዳው የሚችል ማንኛውንም ነገር እንዳንፈጽምበት አዞናል። አእምሮን መጠበቅ እስላም ውስጥ ከአምስት መሰረታዊ አስፈላጊ ጉዳዮች አንዱ ነው። ከዚህ በመነሳትም እስላም አስካሪ መጠጥ መጠጣትን፣አደንዛዥ እጽንና አእምሮን ሊጎዱ የሚችሉ መሰል ነገሮችን ሁሉ መጠቀም ሐራም አድርጎ ከልክሏል።

ማይክል፦ ያልከው አምስቱ መሰረታዊ አስፈላጊ ነገሮች ምንድን ናቸው?

ራሽድ፦ ወደ ዝርዝራቸው መግባቱ ከርእሳችን ሊያስወጣን ይችላል፣በጥቅሉ ግን ሃይማኖት፣ሕይወት፣አእምሮ፣ሰብአዊ ክብርና ንብረት ናቸው።

ማይክል፦ በጣም ጥሩ፣ቀጥል።

ራሽድ፦ በሳይንስ እንደተረጋገጠው አልኮል በጨጓራና በትንሹ አንጀት ውስጥ በፍጥነት በመመጠጥ በተፋጠነ ሂደት ወደ ደም ዝውውር ሥርዓት ይገባል፤ከዚያም በቀላሉ ወደ ተለያዩ የሰውነት ክፍሎች በመሰራጨት ወደ ማእከላዊው የነርቭ ሥርዓት ሴሎች ይደርሳል።

አልኮል መጠኑ በጣም አነስተኛ - 0.3% ያህል - ቢሆን እንኳ በነርቭ ሴሎች ላይ ተጽእኖ የሚያሳድር ሲሆን፣በመካከላቸው ያለው የነርቭ ሞገዶች እንቅስቃሴ አዝጋሚ እንዲሆን ያደርጋል፤ይህ በተራው ትኩረት ማጣትን፣የእንቅስቃሴ መዛባትንና ነገሮችን በትክክል ማመዛዘን አለመቻልን ያስከትላል። በዚህ ምክንያት የኛ ቁርኣን አስካሪ መጠትን አጥብቆ ከልክሏል። አላህ (ሱወ) እንዲህ ብሏል፦

{እናንተ ያመናችሁ ሆይ! የሚያሰክር መጠጥ፣ ቁማርም፣ጣዖታትም፣አዝላምም (የመጠንቆያ እንጨቶች)፣ከሰይጣን ሥራ የኾኑ እርኩስ ብቻ ናቸው፤(እርኩስን) ራቁትም፤ልትድኑ ይከጀላልና።} ]አልማኢዳህ፡9 [

ማይክል፦ እኛ ግን መጠጥ አንዳንድ ጥቅሞች አሉት ብለን እናስባለን፤ከነዚህም መካከል የመነቃቃት ስሜት መፍጠሩ፣በኛ አገሩ ዓይነት ቀዝቃዛ አየር ሁኔታ ሙቀት ሰጭ መሆኑ . . ።

ራሽድ፦ አንዳንድ ጥቅሞች ሊኖሩት መቻሉን ቁርኣንም አያስተባብልም። አላህ (ሱወ) እንዲህ ብሏልና፦

{አእምሮን ከሚቃወም መጠጥና ከቁማር ይጠይቁሃል፤ በሁለቱም ውስጥ ታላቅ ኃጢአትና ለሰዎች ጥቅሞች አሉባቸው፤ግን ኃጢአታቸው ከጥቅማቸው በጣም ትልቅ ነው በላቸው፤} ]አልበቀራህ፡219 [ እነዚህ ጥቂት ጥቅሞች እጅግ ከበዙ ከባድ ጉዳቶቹ ጋር የማይነጻጸሩ በመሆናቸው አንተ በምታምንበት ሳይንሳዊ አካሄድ መሰረት እንወያይ።

ከስነምግባር ተጽእኖዎቹ፣ከስነልቦናዊና ማሕበራዊ ጉዳቶቹ ባሻገር፣ወንጀል ለመፈጸም፣የገንዘብ ኪሳራና በሌሎች ሰዎች ላይ ችግር ለመፍጠር ከሚዳርጉ አጉል የስካር ድርጊቶችም በተጨማሪ፣አስካሪ መጠጥ ቀጥሎ ለተዘረዘሩ የጤና ችግሮች የሚያጋልጥ መሆኑን ሳይንስ ያረጋግጣል፦

1-በሰውነት እጢዎች ላይ በአጠቃላይ ጉዳት በማስከተል የነሱና የልብን ሥራ እንዲዛባ ያደርጋል።

2-የመራቢያ አካላት ድርቀትን ያስከትላል።

3- የጨጓራና የትርፍ አንጀት ቁስለትና የምግብ ማሳለጫ ሥርዓት ኢንፌክሽን ያመጣል።

4-በአፍ፣በጉሮሮ፣በጨጓራ፣በአንጀት፣በነርቭና በኢንዶክራይን እጢ ላይ ቀጥተኛና ብርቱ የሆነ ኢንፌክሽን ያስከትላል።

5-ለጉበት መቁሰልና መበጣጠስ ምክንያት ይሆናል፤ከዚያም ወደ መበላሸትና መዳን ወደማይችል ሁኔታ በማድረስ የጉበት ካንሰርን ያስከትላል።

6-አስካሪ መጠጥ በመተንፈሻ አካላት ላይ የሚያደርሰው ጉዳት ተዘርዝሮ የሚያልቅ አይደለም።

መጠጥ ሙቀት ይሰጣል ያልከውን በሚመለከት፣በአልኮሉ ምክንያት ወደ ቆዳ የሚደርሰውና የደም ስሮችን እንዲሰፉ የሚያደርገው የሞቀ ደም፣የቆዳን የውጭ ክፍል ከሁሉም የሰውነት ክፍሎች በሚመጣ ትኩስ ደም ስለሚሞላው ነው። ይህም ለጠጭው እውነተኛ ያልሆነ የሙቀት ስሜት እንዲሰማው ያደርጋል። ጠጭው ቆዳው ቀልቶና በርቶ ብርድ የማይሰማው ሆኖ እናገኘዋለን። የሞቀው ደም ከሰውየው የሰራ አካላት በተለምዶ ዑደቱ ወደ ቆዳው ፍሰቱን ይቀጥላል፤ይህ ግን ለሕይወት አስፈላጊ ለሆኑ ፊዚኦሎጂያዊ ሂደቶች ተፈላጊ የሆነውን ውስጣዊ ሙቀትና ትኩሳት ሰውነት እንዲያጣ የሚያደርግ ነው።

ሙቀት ለማግኘት ከመጠጥ ውጭ ሌሎች አያሌ መንገዶች ይገኛሉ። እንደሚታወቀው ሁሉ በቀዝቃዛ አካባቢዎች የሚኖሩ ሙስሊሞች መጠጥ አይጠቀሙም።

ማይክል፦ ኡስታዝ ራሽድ፣አነጋገርህ ወደ መስከር ደረጃ መድረስን ከግምት ውስጥ በማስገባት ነው። በዚህ መሰረት ትንሽ መጠጥ መውሰድ ችግር የለውም የሚል እምነት አለኝ።

ራሽድ፦ ችግሩ መጠጥ መጀመሪያ ላይ ጥሩ ስሜትና መነቃቃት እንዲሰማህ የሚያደርግ መሆኑ ነው። ከዚህ በኋላ ነው ሰውነትህ ተጨማሪ አልኮል መጠየቅ የሚጀምረው። ይህም ደጋግሞ የመጠጣት ከፍተኛ ፍላጎት ያሳድርብሃል። የተወሰደው የአልኮል መጠን በጨመረ ቁጥርም ሰውነት ሌላ ተጨማሪ ይፈልጋል . . እንዲህ እያለም ይቀጥላል።

በኒውዚላንድ የተደረገ አንድ የሕክምና ጥናት የደረሰበትን ማጠቃለያ ልንገርህ። በጥናቱ መሰረት በጣም አነስተኛ ወይም መካከለኛ በሆነ መጠን እንኳ ቢሆን አልኮል መጠጣት የሚያስከትለው ጉዳት፣ሊያስገኝ ይችላል ተብሎ ሊጠበቅ ከሚችል ማንኛውም ጥቅም በእጅጉ ይበልጣል። ይህም በምዕራቡ ዓለም በስፋት ከተሰራጨውና በየቀኑ አንድ ብርጭቆ መጠጥ ከልብ በሽታዎች ሊጠብቅ ይችል ይሆናል ከሚለው ሀሳብ ጋር የሚጻረር ነው። በኒውዚላንድ የኦክላንድ ዩኒቨርሲቲ የተላላፊ በሽታዎች ፕሮፌሰር የሆኑት ዶክተር ሮድ ጃክሰን፣በላንሴት የሕክምና መጽሔት ላይ በሳተሙት ጥናት፣ቀለል ባለ ወይም መካከለኛ በሆነ የአልኮል አወሳሰድ ሊገኝ የሚችለው ከልብ በሽታዎች የመጠበቅ ደረጃ እጅግ በጣም ኢምንት መሆኑንና ከሚያስከትለው ጉዳት ጋር ሊነጻጸር የማይችል መሆኑን አስገንዝበዋል።

እዚህ ላይ «አስካሪ የሆነ ማንኛውም ነገር ሐራም ነው፤በብዛት ቢወሰድ የሚያስክር ነገር ሁሉ በትንሹም ቢወሰድ እንኳ ሐራም ነው።» የሚለው ነብያዊ ሐዲሥ ሳይንሳዊና ሕጋዊ ተአምር ጎልቶ ይወጣል።

ማይክል፦ ኦህ፣ሞቅ ያለ ብቻ ሳይሆን የጋለ ውይይት ነው። ውይይታችንን የምናሳርግበት አንድ ብርጭቆ ቀዝቃዛ ሎሚ የሚያስፈልገኝ ይመስለኛል።

ራሽድ (እየሳቀ)፦ ሎሚ ያለ ሻይ?! አንተም የምትስማማበት ርእስ ነው የማነሳው ያልከኝን ግን አልነገርከኝም።

ማይክል፦ ርእሳችን በሚቀጥለው ቀጠሯችን ይሁን።

ራሽድ፦ ጥሩ፣አላህ ይበለው።