የመንገዱ ጠቋሚ ምልክቶች

የመንገዱ ጠቋሚ ምልክቶች

በማህበራዊ አገልግሎት ሳሎን ውስጥ በሚገኘው አንደኛው ጠረጴዛ ላይ ሦስቱ ወዳጆች ራሽድ ማይክልና ራጂቭ ተገናኙ። ሁሉም መጣጣት የሚፈልጉትን አዘዙና ራጂቭ መናገር ጀመረ፦

ያለፈውን ውይይታችን ያቋረጥነው፣እውነተኛው አምላክ ስለሚገለጽባቸው ባሕርያትናእውነተኛውን ሃይማኖት ከሌላው ለይቶ ማወቅ ስለሚቻልበት መንገድ ስንነጋገር ነበር።

ራሽድ፦ ፍቀድልኝና እውነታውን አጽንቼ ጥያቄ ላቀርብ። ቁሳዊው ሳይንስ በተለያዩ ዘርፎቹ ግዙፍ እመርታዎችን አስመዝግቧል። ዛሬ ያለው የጤና ሳይንስ ከሁለት መቶ ዓመት በፊት ከነበረው በብዙ መቶዎች እጥፍ አድጓል። የኢንፎርሜሽንና ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂም በአስራሚ ሁኔታ ተመንድጓል። ኬሚስትሪን በተመለከተም ብዙ ቁሳዊ እውነታዎችን አውቀናል . . እነዚህን ሳይንሶች የሚያስተምሩ ሥርዓተ ትምህርቶችን የማሻሻሉ ሂደትም ከአዳዲስ ግኝቶችና ፈጠራዎች ጋር ተጣጥመው መሄድ ይችሉ ዘንድ በከፍተኛ ፍጥነት እየተከናወነ ነው። ለምሳሌ ያህል ዛሬ በቁሳዊው ዕውቀት መስክ መሬት ክብ አይደለችም የሚል ምሁር የለም። በርእዮትና በእሳቤ ዕውቀት መስክ ግን ከብዙ ሺህ ዓመታት ጀምሮ ክርክር ይደረግባቸው የነበሩ ጉዳዮች ዛሬም ክርክር እየተደረገባቸው ይገኛል። የፈጣሪ አምላክ መኖርንና የሃይማኖት ትክክለኛነትን በተመለከተ፣ለሰው ልጅ ሕይወት ይበልጥ ጠቃሚው ሥርዓት የትኛው እንደሆነ፣ስለ ፍትሕ ምንነት፣ . . በሌሎቹም ጽንሰ ሀሳቦችና አመለካከቶች ላይ የሚደረገው ክርክር ዛሬም የተጧጧፈ ነው። ሳይንስ ይሻሻላል ያድጋል ካልን፣ሃይማኖትም ሊሻሻልና ሊያድግ ይችላል ማለት የማይቻለው ለምንድነው?!

ራሽድ፦ ከብዙ ሺህ ዓመታት ጀምሮ እምነቶች አመለካከቶችና እሳቤዎች ሲወዛገቡ ቆይተዋል።እስከ ዛሬው ዘመናችን ድረስም ቀጥተኛ ወይም ቀጥተኛ ባልሆነ መንገድ መወዛገባቸውን ቀጥለዋል። ይህ ማለት ደግሞ የሰው ልጅ አእምሮ በርእዮትና በእሳቤ ዕውቀት መስክ ከቁሳዊው ዕውቀት ጋር ተነጻጻሪ የሆነ ከፍተኛ ዕድገትና እመርታ አላሳየም ማለት ነው። ለዚህ መንስኤው መሰረታዊው ሰብአዊ ሕልውናችን ያልተለወጠ መሆኑ ሲሆን፣የሰውን አእምሮና እሳቤውን ወጥረው የሚይዙ ታላላቆቹ የሰው ልጅ ጥያቄዎችም አልተለወጡም። ለአያያዙና ለአብሮነቱ መንደርደሪያ መሰረት ይሆነው ዘንድ፣የሰው ልጅ ስለዩኒቨርስና ስለ ሕልውና የተሟላ ትንታኔ ለማግኘት ሁሌም ይፈትሻል . . የሚሠራባቸውን የታላላቆቹን እውነታዎች ባሕሪለግንዛቤው ቅርብ የሚያደርግ፣በእነዚህ እውነታዎች መካከል የሚገኙ ግንኙነቶችንና ትስስሮችን ባሕሪ ለማወቅ ዘውትር እንዳጣረ ነው። እኛን የተፈጠርን ሰዎች የሚያደርገንን ነገር፣ማለትም ከአላህና ከፍጡራኑ ጋር ተለይቶ የሚታወቅ የተወሰነ ግንኙነት ያለን ፍጡራን የመሆናችን እውነታ፣በቀደምቶቹ ዘንድ የነበረው ያው ተመሳሳይ እውነታ ነው። በመሆኑም በነዚህ ጉዳዮች ላይ ዛሬ ከሚገኙት ሊቃውንት ዕውቀት መጠቀም እንደምንችል ሁሉ ከቀደምት አበው ሊቃውንት ዕውቀትም መጠቀም እንችላለን። ጥንት የተነሱትም ሆኑ ዛሬ የሚቀርቡት ርእሰ ጉዳዮች፣ከፍጥረተ ዓለም ከሕይወትና ከሰው ልጅ ጋር የተያያዙ አንድና ተመሳሳይ ርእሰ ጉዳዮች ናቸው። ሰዎች በአብዛኞቹ የቁሳዊ ዕውቀት እውነታዎች ላይ የተስማሙ ሲሆን፣እሳቤዎችን አመለካከቶችንና ርእዮቶችን በሚመለከቱ ብዙዎቹ እውነታዎች ላይ ግን ከስምምነት ላይ አልደረሱም። ይህ ሁኔታ በራሱ በሰው ልጅ ፍጻሜ እንጂ ፍጻሜና መቋጫ አይኖረውም።

ራሽድ፦ ስለዚህም በእንዲህ ዓይነቶቹ ጉዳዮች ላይ ወደ እውነታው መድረስ አንችልም ማለት ነው።

ራሽድ፦ ማነው ያለው? እንደዚያ ቢሆንማ መወያየት ምን ፋይዳ አለው?! ጭፍን ወገንተኝነትና ግላዊ ስሜትን እርግፍ አድርጎ በመተው በፍጹም ልቦና ወደ እውነታ ለመድረስ ትኩረት ከሰጠን፣ጥልቀት ባለው ውይይትና ክርክር አማካይነት ወደ እውነታው መድረስ እንችላለን ብዬ አምናለሁ። ከልብና በፍጹምነት ወደ እውነታ ለመድረስ ፈልጎ ወደዚያ የሚያደርሰውን መንገድ የያዘን ሰው፣አላህ ﷻ ይመራዋል። ለዚህ ማስረጃው እነዚህ ውዝግቦችና ተቃርኖዎች ቢኖሩም፣እነዚህ ጽንሰ ሀሳቦች፣እሳቤዎችና ግንዛቤዎች በሰው ልጆች ታሪክ ውስጥ በተለያዩ ዘመናት ውስጥ በነቢያት፣በተሐድሶ አራማጆች ወይም በርእዮተኞች አማካይነት ዕድገት ማሳየት መቻላቸው ነው። በነዚህ በኩል ብቻ ሳይሆን አንዳንድ ጊዜ በአገሮች አማካይነትም ዕድገት አስመዝግቧል። ዋናው ነገር ግን ግራ መጋባትና ተቃርኖ ከእሳቤና ከሰብአዊ ጉዳዮች ጋር የተቆራኙ መሆናቸው ሲሆን፣ችግሩ ጥንታዊም አዲስም ነው።

ለማንኛውም ይህን በተመለከተ ሁለት አበይት ነጥቦችን እንዳስቀምጥ ፍቀድልኝ። እነሱም፦

አንደኛ ፦ በቁሳዊ ዕውቀት መስክ ዕድገት ማስመዝገብ ማለት፣በሁለቱ መካከል ተያያዥነት ባለመኖሩ የግድ በእሳቤ በአመለካከትና በሰብአዊ ርእዮታዊ ዕውቀት መስክም ዕድገት ማስመዝገብ ማለት አይደለም። ለዚህ ማስረጃው፣ለምሳሌ በእሳቤ፣በአመለካከትና በሰብአዊና ሃይማኖታዊ ርእዮት በመካከላቸው መሰረታዊ ልየነቶች ቢኖሩም፣የአሜሪካና የጃፓን ቁሳዊ ዕድገት ተቀራራቢ መሆኑ ነው። ይህ ማለት የአንዳንድ ሕብረተሰቦች በተፈጥሮ ሳይንሶችና በቁሳዊ ዕድገት እመርታ ማሰየታቸው በሰብአዊ ሳይንሶችና ርእዮታዊ ዕውቀትም የግድ ዕድገትና እመርታ አስመዝግበዋል ማለት አይደለም።

ሁለተኛ፦ የሰው ልጆች ስብስብ ብዙ ጊዜ ሐሰትና ስህተት ላይ የሚወድቅ በመሆኑ፣ለእውነታ ትክክለኛነቱንና ጥንካሬውን የሚያጎናጸፈው የሰዎች ድጋፍ ወይም ተቃውሞ አይደለም። ሕብረተሰቦች በተሳሳተ እሳቤ፣ኢስነምግባራዊ በሆኑ ተግባራትና በአስከፊና አሰቃቂ ወንጀሎች ላይ ጭምር ላይ መስማማታቸውን የሰው ልጆች ታሪክ መዝግቦታል።

ራጂቭ፦ በዚህ ላይ ከአንተ ጋር እስማማለሁ። ይሁን እንጂ ሁላችንም ከተለያዩ የባህል ዳራዎችና ምንጮች የመጣን ነን፤እያንዳንዳችንም የተለያዩ እምነቶችንና አመለካከቶችን እናራምዳለን። ስለዚህም በቅድሚያ አንድን እውነታ ትክክል መሆን አለመሆኑን በምናረጋግጥባቸው መሰረተ ሀሳቦችና ማስረጃዎች ላይ የግድ መስማማት ይኖርብናል።

ራሽድ፦ ይህን ማድረግ የምንችለውበሁለት መንገዶች ብቻ ነው የሚል እምነት አለኝ። እነሱም፦ እእምሮ ወይም ሳይንስ ናቸው . . ይህ ሁላችንንም የሚያስማማ ነው።

ራሽድ፦ ከመርህ አኳያ እስማማለሁ፤ግና የእኔ አእምሮ የአንተ አእምሮ አይደለምና የትኛውን አእምሮ ማለትህ ነው? ሳይንስም ቢሆን እንደዚያ ነውና ተግባራዊውን ሳይንስ ብቻ ማለትህ ነው?

ራሽድ፦ አእምሮ ስል ሁለት ሰዎች የማይለያዩበትን ግልጽና ቀላል አእምሯዊ እሳቤ ወይም ሁላችንን የሚያስማሙ ምክንያታዊ ማስረጃዎችን ማለቴ ነው። በሳይንሳዊ መንገድ የተረጋገጡ ሳይንሳዊ እውነታዎችን በመቀበል ረገድ ልዩነት ይኖረናል ብዬ አልገምትም። ይህ ግን ወደ ተረጋገጠ እውነታ ደረጃ ያልደረሱ መላምቶችን፣ንድፈ ሀሳቦችንና ሳይንሳዊ ሙከራዎችን አያካትትም . . በዚህ ከኔ ጋር ትስማማ የለም?

ራሽድ፦ ሙሉ በሙሉ እስማማለሁ።ከሁለቱ ማስረጃዎች ያላነሰ አስፈላጊነት ያለው ሌላ ማስረጃም መጠቆም እፈልጋለሁ። እሱም የተፈጥሮ ማስረጃ ነው። በተጨማሪም የአእምሮና የሳይንስን አስረጅነት በተመለከተም ሌላው አስፈላጊ ነጥብ፣አእምሮ ስህተት ነው ወይም ፈጽሞ ሊሆን አይችልም ብሎ በሚቆርጠውና ለአእምሮ እሳቤ ወይም ግንዛቤ አስቸጋሪ በሚሆነው መካከል ልዩነት መኖሩን የሚመለከት ነው።

ራጂቭ፦ የተፈጥሮ ማስረጃ ምን ማለት ነው?

ራሽድ፦ የሰው ልጆች ሁሉ የሚጋሩት ውስጣዊ ተፈጥሯዊ ስሜትና ዝንባሌ ማለቴ ነው። ሁሉም ፍጥረታት ግዑዝ አካላት፣እጽዋትም ሆኑ እንስሳት የየራሳቸውን ተፈጥሯዊ ባሕርያትና መለያዎች እውስጣቸው ይዘዋል። ለምሳሌ ያህል የውሃ መለያ ባህሪን አስመልክተን በመቶ ዲግሪ ሙቀት ይፈላል እንላለን። ወይም የሰው ልጅ በሕይወት ለመቆየት የሰውነት ሙቀትቱ መጠን ከ34 እስከ 42 ዲግሪ መሆን ይኖርበታል እንላለን። እነዚህ መለያ ባሕርያት በፍጥረታቱ ውስጥ የተገኙት ለመገኘታቸው እነሱ ምንም ሚና ሳይኖራቸው በተፈጥሮ ነው።

ራሽድ፦ በሰውና በእንስሳት ዘንድ ያለውን ደመነፍስ ማለትህ ነው?

ራሽድ፦ ሰዎችና እንስሳት ደመነፍስ አላቸው። ይህም በሕይወታቸው ውስጥ የሚመሯቸውን ውስጣዊ ባሕርያት የሚገልጽ ነው። የዱር አራዊት አድነው ይበላሉ፣አድኖ የመብላት ስሜትና ዝንባሌን ማንም አላስተማራቸውም። ረዥም ርቀት ተጉዘው የሚሰደዱ አዕዋፍና ዓሳዎች፣ወደ መነሻ ቦታቸው መመለስ የሚያስችላቸውን ደመነፍሳዊ ስሜትና ዝንባሌ ያገኙት በተፈጥሮ ነው። የእንስት እንስሳት እናታዊ ደመነፍስም እንዲሁ ተፈጥሯዊ ነው። የደመነፍሱ ባለቤት ሊያወቀውና ሊሰማው የሚችል ቢሆንም ደመነፍሱን እንዲያውቅ ያደረገው ምስጢር ምን እንደሆነ ግን ልብ አይለውም።

ተፈጥሮ (ፍጥረህ) እና ተፈጥሯዊ ጉዳዮች ግን በሰው ልጆች ዘንድ ብቻ የሚገኙ ናቸው። ይህም እንደ ደመነፍስ ሁሉ ከውጭ የማይገበይ ባለቤቱ የሚያውቀውና የሚገነዘበው ውስጣዊ ስሜት ነው። በደመነፍስና በተፈጥሮ መካከል ያለው ልዩነት፣ደመነፍስ ቁሳዊ ጉዳዮችን የሚመለከት ሲሆን፣ተፈጥሯዊ ውስጣዊ ስሜት ግን ዕውቀትን መውደድ፣እውነትን መፈለግ፣የፈጠራና የጥበብ ፍላጎት፣ወደ በጎና ትሩፋት ነገሮች ማዘንበል፣ወደ ውበት መሳብ . . ከመሳሰሉ ሰብአዊ ጉዳዮች ጋር የተያያዘ ነው። የሰው ልጅ እነዚህን ነገሮች የሚፈልጋቸውና የሚሳብባቸው ከሚኖርበት አካባቢ ምንም ጣልቃ ገብነት ሳይኖርበትና በስልጠና በትምህርትም ሆነ በማህበራዊ አስተዳደጉ ሳያገኛቸው ነው። ተፈጥሯዊ ጉዳዮች እንደ እንስሳቱ ደመነፍስ ሁሉ ከሰው ልጅ ጋር አብረውት የተፈጠሩና ከውስጡ የሚመነጩ ሲሆኑ፣ብአዊና ሕሊናዊ ጉዳዮችን ብቻ የሚመለከቱ ናቸው። በሰው ልጅ ውስጥ የታነጸው ይህ ተፈጥሯዊ ግንዛቤ ሰዎች በጎ በጎውን እንዲቀበሉና ከመጥፎው እንዲርቁ የሚያደርጋቸው ሲሆን፣ለምሳሌ መልካም መዓዛንና ውብ ትእይንትን ጠልቶ ወደ መጥፎ ጠረንና አስቀያሚ ትእይንት ፊቱን የሚያዞር የተስተካከለ ተፈጥሮ ያለው ጤናማ ሰብአዊ ፍጡር አታገኝም።

ራጂቭ፦ ይህ ተፈጥሯዊ ነው ያኛው አይደለም ብለን እነዚህን ጉዳዮች ለያይተን መወሰን የምንችለው እንዴት ነው?

ራሽድ፦ በሰው ልጅ ዘንድ የሚገኙ ተፈጥሯዊ ጉዳዮች በተለያዩ ባህርያት ይገለጻሉ። ከነዚህም ዋነኞቹ የሚከተሉት ናቸው፦

•ሁሉንም የሚያካትቱ አጠቃላይና ሁለንተናዊ ናቸው።

•ከጊዜ አኳያ የተራዘሙ ሲሆኑ፣በአንድ ወቅት አንድን ነገር አስከትለው በሌላ ወቅት ሌላ ውጤት አያመጡም።

•በትምህርት ሊያጎለብታቸውና ሊያበለጽጋቸው ቢችልም፣የሚመጡት ከግለሰቡ ውስጣዊ ዓለምና ከገዛ ራሱ እንጂ በትምህርትና በልምድ ከውጭ የሚገበዩ አይደሉም።

•በአካባቢ ተጽእኖ ጫና ስር የማይውሉ ሲሆን፣በሆኑ ሁኔታዎች ውስጥ አንዳንድ ነገሮች ጫና ሊያሳድሩባቸው ይችላሉ። እንደ ተቀሩት የመስማት፣የማየት . . የስሜት ሕዋሳት ሁሉ በበሽታ ሲጠቁና ሲጎዱ ብቃታቸው ሊቀንስና ጥራታቸውም ሊለወጥ ይችላል። ሆኖም ግን በጠቃላይ አነጋገር ሙሉ በመሉ ሳይጠፉ ሊደክሙ ወይም ሊዝጉ ይችላሉ።

ራሽድ፦ እስካሁን በቀረበው ላይ የተስማማን ይመስለኛል። ይሁን እንጂ በዚህች በመጨረሻይቱ ነጥብ ምክንያት ተፈጥሯዊ ስሜትን በርእሰ ጉዳያችን ላይ በማስረጃነት ከምንጠቀምባቸው ነገሮች አንዱ እንዲሆን በማድረጉ ላይ ትንሽ ጥርጣሬ ገብቶኛል።

ራጂቭ፦ በተፈጥሯዊ ማስረጃ ላይ የተመረኮዘውን ጉዳይ በቦታው መከራከር እንችላለን፤ሁላችን ከተቀበልነው እንስማማበታለን፣ካልተቀበልነው ደግሞ ሌላ ማስረጃ እንፈትሻለን።

ራሽድ፦ በነገራችን ላይ በነዚህ የማስረጃ ስልቶች ላይ ከተስማማን በኋላ፣እስላምን የማያውቁ አንዳንድ ወገኖች በነዚህ የማስረጃ ስልቶች ላይ መስማማታችንን ከእስላም ሃይማኖት ጋር የማይስማማ አድርገው ሊገምቱ እንደሚችሉ ማሳሰብ እፈልጋለሁ፤ይህ ግን ፈጽሞ ስህተት ነው።

ራሽድ፦ እኔ እስከሚገባኝ ድረስ ሃይማኖት በመለኮታዊ ትእዛዝ በማመን፣ጥያቄና ክርክርን በማይቀበል መልኩ ሳያመነቱ ሙሉ በሙሉ አምነው በመቀበል ላይ የተመሰረተ ነው። በዚህ ምክንያት ነው በአውሮፓ ታሪክ ውስጥ ከሳይንሳዊ ግኝቶችና ከሕዳሴው ዘመን በኋላ ታላላቅ ጦርነቶች የተደረጉት። የጦርነቶቹ መንስኤም ቤተክርስቲያን እነዚያን ሳይንሳዊ ግኝቶች መዋጋቷና ከመጽሐፍ ቅዱስ የተለየ አእምሯዊ እሳቤን መጻረሯ ነበር።

ራሽድ፦ የተወሰነ ተዐቅቦ ቢኖረኝም ያልከው ነገር ትክክል ነው። ይሁን እንጂ እስላምን ግን የሚመለከት አይደለም። በእርግጥ ሃይማኖት በመለኮታዊ ሕግ በማመንና ትእዛዛቱን ሁሉ በፍጹም ተገዥነት በመቀበል ላይ ይመሰረታል። እስላም ግን አእምሮና እሳቤን፣ከምርምር ከአስተውሎና ከሙከራ የሚመነጨውን ዕውቀትን፣የገዛ ራስን አፈጣጠርና ፍጥረተ ዓለሙን ማስተዋልና ማስተንተንን . . በአላህ ﷻ፣ የሙስሊሞች ቅዱስ መጽሐፍ በሆነው በቁርኣንና በመልእክተኛው ﷺ. . ወደ ማመን የሚያደርስ የእምነት ጎዳና አድርጎታል። በእስላም ታሪክ ውስጥ በሃይማኖት፣በሳይንስና በአእምሮ መካከል አለ ብለህ አንተ የምትናገረው ዓይነት ቅራኔና ግጭት ተከስቶ አያውቅም።

ራጂቭ፦ ቅዱስ መጽሐፋችሁ አእምሮ እሳቤና ዕውቀት እንዲከበሩ የሚያበረታታ መሆኑ በጣም አስገራሚ ነው!

ራሽድ፦ የማህበራዊ ሳሎን አገልግሎት ኃላፊዎች የመዝጊያው ሰዓት መቃረቡን እያመለከቱን ነው። እናም እዚህ ላይ እናቆምና ነገ እንቀጥላለን።

ራጂቭ፦ እኔ ነገ ጉዳይ አለብኝ። ተነገወዲያ በሴይን ወንዝ ዳርቻ የመዝናኛ ጉዞ ስጋብዛችሁ ግብዣዬን እንደምትቀበሉ በመተማመን ነው።

ማይክልና ራሽድ፦ ግሩም ነው፣በደስታ እንቀበላለን።