እስላምና ሽብርተኝነት

እስላምና ሽብርተኝነት

ውይይታቸውን በተስማሙበት የቻት ሩም ለመጀመር በቀጠሮው መሰረት ማይክል ራሽድና ራጂቭ ተገናኙ . . ለወዳጆቹ ሰላምታ ካቀረበ በኋላ ማይክል ውይይቱን ከፈተ።

ማይክል፦ ራሽድ ባለፉት ውይይቶች ያቀረባቸው ነገሮች ስለ ሃይማኖቱ በግልጽ ከሚታወቀው ጋር የሚጻረር ስለሆነ መበጠርና መፈተሸ ያስፈልጋቸዋል። ወዳጃችን ራሽድ የሃይማኖቱን አንጸባራቂ ጎኖች ብቻ ለማቅረብ ነው የሞከረው፤ጨፍጋጋ ጎኖቹን ግን በቸልታ አልፏል . . ዛሬ ዓለምን በማተራመስ ላይ የሚገኘው ሽብርተኝነት በዋናነት እስላማዊ ሽብርተኝነት መሆኑን በዓይናችን የምናየው እውነታ ነው።

ራጂቭ፦ በከፊል ከአንተ ጋር እስማማለሁ። ይሁን እንጂ ሽብርተኝነት ከአንድ ሃይማኖት፣ሕዝብ፣ብሔር ወይም ዘር ጋር በተለይ የተያያዘ ድርጊት ተፈርጎ መታየት አይገባውም። ይህ በአገሬ በሕንድ በተግባር ያየሁት እውነታ ነው። የኃይል እርምጃዎችና የጥቃት ክስተቶች በተለያዩ አያሌ ምክንያቶች በሁሉም ዘንድ ሲፈጸሙ ይታያሉ። ለመከራከር እንዲረዳን አንተ ያነሳኸው ነጥብ በምን ላይ የተመሰረተ ነው?

ማይክል፦ በትክክል ማንሳት የፈለኩትም ይህንኑ ነው። እኔ እንደማምነው ሽብርተኝነት በራሱ በእስላም ውስጥ የሰረጸ የሃይማኖቱ ተፈጥሮ ነው። እንደሚታወቀው ሁሉ የተስፋፋው በሰይፍ በጎራዴ ነው . . ወዳጃችን ራሽድ ይህን ታስተባብላለህ‘ንዴ?

ራሽድ፦ በእርግጥ አስተባብለዋለሁ። እኔ ብቻ ሳልሆን እውነታዎችም እንዲሁ ያስተባብሉታል።

ማይክል፦ የትኞቹን እውነታዎች ማለትህ ነው?

ራሽድ፦ ሃይማኖታዊ እውነታዎችን፣ታሪካዊ እውነታዎችን፣ተጨባጭ እውነታዎችን . . ማለቴ ነው። ከሁሉ አስቀድሜ ግን፣ሚዲያውና ጥቅመኞች እንዳሻቸው አእምሯችንን ከሚቀርጹባቸው መሰረት የለሽ የሰበካ አሉባልታዎችና የሀሰት መረጃዎች ነጻ ማድረግ ይኖርብናል በሚለው ላይ ማስመር እፈልጋለሁ።

ራጂቭ፦ የምንኖረው በነጻ ሕብረተሰብ ውስጥ ይመስለኛል። አእምሯችንን ሌሎች በሚፈልጉት መንገድ ለመቅረጽ ተጽእኖና ጫና ይደረግብናል ብዬ አላስብም።

ራሽድ፦ እርግጥ ነው የመምረጥ ነጻነት ስላለን ጫና አይደረግብንም፤ይሁን እንጂ ዞሮ ዞሮ የምንመርጠው ግን ሚዲያውን የሚቆጣጠሩ ወገኖች የሚያቀርቡልንን ነው፤የምንነዳውም ፖለቲከኞችና ጥቅመኛ ሎቢዎች ወደሚነዱን አማራጮች ብቻ ነው። ምዕራባውያን ፖለቲከኞችና ልሂቃን ሽብርተኝነትንና ከእስላም ጋር ያለውን ትስስር አስመልክተው የሚሰጡት መግለጫ፣‹‹ሽብርተኝነትን መዋጋት›› በሚል ሽፋን ለዳግም የመስቀል ጦርነት የሚጎስሙት ነጋሪት፣ዘመቻው መቻቻልና ፍትሐዊነት መገለጫ ባህሪው ነው የሚሉትን የምዕራቡን ሥልጣኔ ለማደን ነው የሚለው አሉባልታቸው ሁሌም እንደ ቀጠለ ይገኛል።

ማይክል፦ ምንጩ የትም ይሆን፣ባሕርይውና ዓይነቱ ምንም ይሁን ምን፣እውነታን ብቻ እየፈለግን በነበርንበት የመደማመጥ ሁኔታ ለመቀጠል ቃል እገባልሃለሁ።

ራሽድ፦ እስላም በተፈጥሮው አጥቂ ሃይማኖት ሆኖ በሰይፍ የተስፋፋ ከሆነ፣ምዕራቡ ዓለም እከተለዋለሁ የሚለው ክርስትና የመቻቻል ሃይማኖት ከሆነ፣ወዳጄ ‹‹ሰይፍ›› የሚለው ቃል ቅዱስ ቁርኣን ውስጥ ስንት ጊዜ እንደ ተደጋገመና መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥስ ስንት ጊዜ እንደተደጋገመ ታውቃለህን?

ማይክል፦ ስንት እንደሆነ በትክክል አላውቅም፤ይሁን እንጂ በእርግጠኝነት መናገር ‘ምችለው ግን መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከተጠቀሰው በበለጠ ቁርኣን ውስጥ ብዙ ጊዜ የተጠቀሰ መሆኑን ነው።

ራሽድ፦ እንግዲያውስ እንካችሁ ዱብዳ . . ቅዱስ ቁርኣን 114 ምዕራፎች፣6236 አንቀጾች፣77439 ቃላት ያሉት ሲሆን፣‹‹ሰይፍ›› የሚለው ቃልም ሆነ ወይም ዐረብኛ ቋንቋ ውስጥ ካሉት 60 ያህል አቻ ቃላት ውስጥ አንዱ፣አንድም ጊዜ እንኳን ቁርኣን ውስጥ አልተጠቀሰም። መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ግን ‹‹ሰይፍ›› የሚለው ቃል ከ200 ጊዜ በላይ ተደጋግሞ ተጠቅሷል።

ማይክል፦ ኦህ . . በእርግጥም ዱብዳ ነው . . ሃይማኖታዊ እውነታዎች ስትል ማለት የፈለግኸው ይህንን ኖሯል?

ራሽድ፦ ይህ ሌሎቹን እውነታዎች ለመጠቃቀስ ጊዜ እንዳይሻማኝ በመስጋት ያቀረብከት፣ከሃይሞኖታዊ እውነታዎች መካከል አንዱ እውነታ ብቻ ነው።

ራጂቭ፦ ከነዚህ እውነታዎች መካከል ዋነኞቹ የትኞቹ ናቸው?

ራሽድ፦ ወዳጄ ራጂቭ፣ከነዚህ እውነታዎች ዋነኛውን በከፊል ታውቀዋለህ የሚል እምነት አለኝ። ይኸውም ሙስሊሞች በብዛት ከሚኖርባቸው የዓለም አካባቢዎች ውስጥ ምሥራቃዊና ምዕራባዊ የኤሽያ አካባቢዎች በቀዳሚነት የሚጠቀሱ ሲሆን፣እንደሚምታወቀው ሁሉ የሙስሊሞች ሠራዊት ወደ እነዚህ አካባቢዎች ፈጽሞ ደርሶ አያውቅም። ስፋት ያላቸው የአፍሪካ አካባቢዎችም እንደዚሁ ናቸው።

ማይክል፦ የጠቀስካቸውን የአንዳንድ ታሪክ ጸሐፊዎች አባበል እንዳለ ሆኖ፣የዚህ ተቃራኒ የሚናገሩ ሌሎች ታሪክ ጸሐፊዎችን እኔም መጥቀስ እችላለሁ። እናም ለምትለው ነገር ማስረጃው ምንድነው?

ራሽድ፦ የተናገርኩትን የሚያረጋግጡ አያሌ ማስረጃዎች ይገኛሉ።

አንደኛ፦ ሙስሊሞች በጦር ኃይል ድል አድርገው ከገቡባቸው አካባቢዎች በአብዛኞቹ ውስጥ፣የአገሩ ሰዎች በሙስሊሞች አስተዳደር ስር የቀድሞ ሃይማኖቶቻቸውን እንደያዙ ዘልቀዋል። አንዳንዶቹ አገሮች ዛሬም ድረስ የቀድሞ ሃይማኖታቸውን እንደያዙ ይገኛሉ። ይህ በግብጽ፣በፍልስጥኤም፣በሊባኖስ፣በግሪክ፣በሕንድ . . የምናስተውለው ተጨባጭ እውነታ ነው። ክርስቲያኖች በጦር ኃይል ድል አድርገው አንዱሉስን፣እየሩሳሌምን፣ ፊሊፒንስን . . ሲቆጣጠሩ በሃይማኖት በሚለዩዋቸው ነዋሪዎች ላይ የፈጸሙት ግን ከዚህ ሙሉ በሙሉ ተቃራኒ በሆነ ሁኔታ የጅምላ ፍጅት፣ዘር ማጥራት፣አስገድዶ ማጥመቅ፣ወይም በግዳጅ እንዲሰደዱ ማድረግ ነበር።

ሁለተኛ፦ በድል አድራጊነት በገቡባቸው አገሮች ውስጥ የሙስሊሞች ወታደራዊ ኃይል ሕልውና ባበቃበትና የሙስሊሞችም ሆነ የሌላ ወገን ተጽእኖ ባልነበረበት ጊዜ፣እነዚህ ሕዝቦች የእስላም ሃይማኖታቸውን ሲተው አላስተዋልንም። ከዚህ በተቃራኒው በቀድሞዋ የሶቭየት ሕብረት አገዛዝ ስር የነበሩ ሙስሊሞች በኮሙኒዝም የግፍና የጭቆና ሥርዓት ውስጥ እየማቀቁ በምስጢር የእስላም ሃይማኖታቸውን ጠብቀው ለመኖር መቻላቸውን አስተውለናል።

ሦስተኛ፦ የሙስሊሞችን ምድር በመውረር ወታደራዊ ኃይሉን ሰብረው ሰፊ ግዛቱን ስለያዙ ሕዝቦች ሁኔታ ታሪክ ብዙ ነገሮችን ተርኮልናል . . እነዚያ ሙስሊም ያልነበሩ ተታሮችንና ቱርኮችን የመሳሰሉ ድል አድራጊ ሕዝቦች ሃይማኖቱን ሲያዩና አብረውት ሲኖሩ እስላምን ተቀብለው ሙሉ በሙሉ ሰልመዋል።

ማይክል፦ እስላም በሰይፍ አልተስፋፋም ብዬ ከአንተ ጋር አምኜ ልቀበል፤ግና የታሪኩን ጉዳይ ተውና በአሁኑ በዛሬው ተጨባጭ ሁኔታ ላይ እንነጋገር። ዛሬ ዓለምን በመምታት ላይ ያለው ሽብርተኝነት የለየለት እስላማዊ ሽብርተኝነት ነው በሚለው አባባሌ አትስማማም?!

ራሽድ፦ በቅድሚያ ግን ‹‹ሽብርተኝነት›› የሚለውን ቃል ትርጉምና ምንነት እንወስን። ከዚያ በአሁኑ ዘመን ሽብርተኝነት በማን እንደሚወከል ለማየት በዓለም ላይ ያለውን የሽብርተኝነት ካርታ እንመርምር።

ራጂቭ፦ የዓለም አገሮችም ሆኑ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች የሽብርተኝነትን ትርጉምና ምንነት ለይቶ መወሰንን በተመለከተ ስምምነት ላይ አልደረሱም። ይሁን እንጂ ‹‹በፍላጎታቸው ላይ ተጽእኖ ለማሳደር፣ወይም ፖለቲካዊ ወይም ኢኮኖሚያዊ ጥቅምና ፋይዳ ለአጥቂው ወገን ለማስገኘት ዓለማ ሰላማዊ ሰዎችን በማንኛውም መልኩ ማሸበር ነው›› በሚለው ትርጉም መስማማት እንችላለን።

ራሽድ፦ ቁርጥ ባለ አንድ ትርጉም ላይ ለመድረስ ያልተቻለው፣አንዳንድ አገሮች ጽንሰ ሀሳቡን እንዳሻቸው ለመጠቀም ተለጣጭ ሆኖ እንዲቆይ ሆን ብለው ስለፈለጉ ነው። አንተ በሰጠኸው ትርጓሜ ላይ ግን ‹‹ጥቃት አድራሹ ግለሰብ፣ቡድንም ይሁን መንግሥት›› የሚል እጨምራለሁ።

ማይክል፦ መጨመሩ ችግር የለውም። በዚህ መሰረት ዓለም አቀፍ ክስተቶችን ብናስተነትን፣በ1994 በኒውዮርክ ሁለት መንትያ የዓለም ንግድ ማዕከል ሕንጻዎች ላይ የተፈጸመው ጥቃት፣ከዚያ በኋላ የተከሰተው የማድሪዱ የባቡር ፍንዳታ፣በምዕራባውያን ቱሪስቶች በሚዘወተረው የእንዶኔዥያው የባሊ የመዝናኛ ስፍራ የደረሱ ፍንዳታዎች፣ ፍልስጥኤማውያን በአይሁዶች ላይ የሚያካሄዷቸው ጥቃቶች . . እነዚህ ሁሉ በሙስሊሞች የተፈጸሙ የሽብር ድርጊቶች ናቸው።

ራሽድ፦ ወዳጄ ረጋ በል፣ፍልስጥኤማውያን በአይሁዶች ላይ የሚያካሄዷቸው ጥቃቶች በወራሪ ኃይል ላይ የሚደረግ ሕጋዊ ተቃውሞና የነጻነት ትግል ነው። ጥቁር የሽብር ታሪክ ባለው ወራሪ ኃይል ላይ የሚካሄድ ተጋድሎ ነው። ሕዝቡን ከገዛ መሬቱ በወረራ አባርሮ አስከፊ ጭፍጨፋዎችን የሚያካሄድባቸውን አሸባሪ ወራሪ ኃይል በዝምታ መመልከት እንዴት ይቻላል? በጽዮናውያን ሰፋሪዎች በፍልስጥኤም ሕዝብ ላይ ከተፈጸሙት የጅምላ ፍጅቶች ውስጥ ጥቂቶቹን ልጥቀስላችሁ፦

•እ.አ.አ በ31/12/1948 600 ንጹኃን ሲቪሎች በመኖሪያ ቤታቸው ውስጥ እንዳሉ የተገደሉበት የአልሸይኽ መንደር የጅምላ ፍጅት።

•እ.አ.አ በ11/4/1948 ከመንደሩ ነዋሪዎች ከግማሽ በላይ የሚሆኑት በጅምላ የተጨፈጨፉበት የዴር ያሲን መንደር ፍጅት።

•እ.አ.አ በ11/7/1948 በመንደሩ መስጊድ ውስጥ ተሸሽገው የነበሩ 426 ንጹኃን ሲቪሎችን ጽዮናውያን ወራሪዎች መስጊዱን ሰብረው በመግባት የጨፈጨፉበት የአልለድ ፍጅት።

•በ10/1965 በከፈር ቃሲም 94 ሴቶችና ሕጻናት የተጨፈጨፉበት የጅምላ ፍጅት።

•በ18/9/1982 በጦር ወንጀለኛው ጽዮናዊ አሸባሪ በኤርያል ሻሮን ጦር፣በሊባኖሱ የክርስቲያን ፈላንጂስት ሚሊሽያዎች ተባባሪነት የተፈጸመው ዘግናኙ የሰብራና ሻቲላ ጭፍጨፋ። 72 ሰዓታትን በፈጀው በዚህ የዘር ማጥራት ሽብር አብዛኞቻቸው ሴቶች ሕጻናትና በዕድሜ የገፉ ሽማግሌዎች የሆኑ 3500 ፍልስጥኤማውያንና ሊባኖሳውያን በእሳላማዊ ማንነታቸው ምክንያት ብቻ በዘግናኝ ሁኔታ ተጨፍጭፈዋል።

•በ25/4/1994 የተፈጸመው የአልእብራሂሚ መስጊድ ጭፍጨፋ። አንድ የእስራኤል ጦር ወታደር ከጽዮናውያን ሰፋሪዎች ጋር በመተባበር በፈጸመው የሽብር ጥቃት መስጊዱ ውስጥ በመስገድ ላይ የነበሩ 29 ሰጋጆችና ከመስጊዱ ውጭ የነበሩ 5 ሰዎች ሲገደሉ ከ350 የሚበልጡ ሰጋጆች ደግሞ ቆስለዋል።

እይታህ ሁለንተናዊ ይሆን ዘንድ፣በ1995 በኦክላሆማ ሲቲ በፌዴራል መንግስት ሕንጻ ላይ የተፈጸመውን 168 ሰዎች የተገደሉበትና ሌሎች 500 ሰዎች የቆሰሉበትን ፍንዳታ፤በ7/2011 በኦስሎና በቶያ ደሴት በተመሳሳይ ወቅት የተፈጸመውን፣ከ92 ሰዎች በላይ የሞቱበትንና 90 ሰዎች የቆሰሉበትን ሁለቱን የሽብር ጥቃቶችም በዚህ ላይ መደመር ትችላለህ። ሁለቱ ጥቃቶች የተፈጸሙት በለየላቸው አክራሪና ዘረኛ ክርስቲያን አሸባሪዎች ነበር።

በተጨማሪም ሽብርተኝነት ከአንድ ሃይማኖት ወይም ባሕልና ሥልጣኔ ጋር ያለውን ትስስር የምንፈትሽ ከሆነ፣የሚከተሉትን እውነታዎች በቸልታ ማለፍ አንችልም። እነሱም፦

•አሁን ባለንበት ዘመን ውስጥ አንድ ሙስሊም አገር አንድን የምዕራብ አገር ወርሮ አያውቅም። በተቃራኒው ግን ጥንታዊውም ሆነ አዲሱ ዓለም የምዕራባውያን ኃይሎች የወረራና የዘመቻ ዒላማ ሆኖ መኖሩን ታሪክ ይመሰክራል።

•የአሜሪካ ቀይ ሕንዶች የምዕራባውያንን የሥልጣኔ አርማ በሚያውለበልቡ አውሮፓውያን ወራሪዎች እጅ የጅምላ ጭፍጨፋ የተካሄደባቸው ሲሆን፣የገዛ ክፍለ አህጉራቸውን ከመነጠቃቸውም በላይ ቁጥራቸው ከአስር ሚሊዮን ወደ 200 ሺህ አሽቆልቅሏል።

•ምዕራባውያን ‹‹ሁለቱ የዓለም ጦርነቶች›› ብለው በሰየሟቸውና በተጨባጭ ግን የአውሮፓውያኑ የራሳቸው በሆኑት ሁለት ታላላቅ ጦርነቶች ምክንያት በዓለማችን ላይ አስከፊ አደጋ ደርሷል። በአንደኛው ጦርነት ወደ ሃያ ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች የተገደሉ ሲሆን፣ተመሳሳይ ቁጥር ያላቸው ሰዎች ቁስለኛና አካለ ስንኩል ሆነዋል። በሁለተኛው ጦርነት ደግሞ 55 ሚሊየን ያህል ሲገደሉ፣53 ሚሊዮን ሰዎች ቆስለው ሦስት ሚሊዮን የደረሱበት ሳይታወቅ ቀርቷል። የአውሮፓውያን ተዋጊዎች የጎላ ባህሪ የጠላትን ቅስም ለመስበር ሲባል ሲቪሎችን ዒላማ ማድረግ ስለነበረ፣ የጦርነቶቹ አብዛኞቹ ሰለባዎች የቅኝ ተገዥ አገር ሲቪሎች ነበሩ።

እንደዚሁም ደግሞ በንጹሃን ላይ የሚፈጸመውን ጥቃት በመኮነንና ወንጀል መሆኑን በማረጋገጥ መርሕ ላይ ከተስማማን፣በአንጻሩ እነዚህን የሽብር ድርጊቶች የሚፈጽሙትን ወገኖች ወደዚህ የሚገፋፋቸውን ነገርም ችላ ማለት አንችልም። አሜሪካና ምዕራባውያን በሙስሊሞች ላይ ለሚፈጽሙት የማያቋርጥ ጥቃትና ሽብር፣በተለይም በዕራቅ ላይ በጣሉትና በወቅቱ ሁለት ሚሊዮን ሕጸናት እንዲያልቁ ምክንያት ለሆነው ማዕቀብ፣በተጨማሪም በፍልስጥኤም ሕዝብ ላይ በጽዮናውያን ወራሪዎች የሚፈጸመውን ወንጀል በመደገፋቸው ምክንያት የሚሰጥ ምላሽ ነው የሚል ማመካኛ ያቀርባሉ።

ራጂቭ፦ እናም ልንደርስበት የምንችለው ማጠቃለያ፣ሽብርተኝነት ሃይማኖት፣ባህልም ሆነ ሥልጣኔ የለውም የሚለው ነው።

ራሽድ፦ ሃይማኖት የለውም በሚለው ላይ መስማማት እችል ይሆናል። ነገር ግን፣በትግልና በፍጥጫ መርሕና ኃይልን በማምለክ ላይ የቆመውን የምዕራቡን ሥልጣኔ መንደርደሪያዎችና ይህም ከሚፈጽሙት የጥቃት ድርጊቶቻቸው ጋር ያለውን ትስስር ቆም ብለን ማጤን ይገባል ባይ ነኝ። ዘመናዊው የምዕራብ ሥልጣኔ ያቆጠቆጠውና እሳቤውን የወረሰው ወሳኝ በሆነ መልኩ ከቀደሙት ሁለቱ የግሪክና የሮማውያን ሥልጣኔ ቅርሶች ነው። የበላይነት ቋጠሮ፣የኃይልና የጉልበት አምልኮ፣የትግልና የፍጥጫ አይቀሬነትን የመሳሰሉ . . እሳቤዎችን ዘመናዊው የአውሮፓውያን ሥልጣኔ የወረሰው ከግሪካውያንና ከሮማውያን ሥልጣኔዎች ነው። የክርስትና ትምሕርቶችም እነዚያን እሳቤዎች፣ራሷን አውሮፓንና መላውን ዓለም ያጥለቀለቁ፣አስከፊ ድርጊቶችና አስበርጋጊ የሽብር ጥቃቶች መልክ ይዘው ወደ ተግባር ከመለወጥ ማስቆም አልቻሉም።

ማይክል፦ በሌላ ውይይት እስክንገናኝ ደህና ሁኑ።