ቁርኣናዊ ስነምግባር

ቁርኣናዊ ስነምግባር

ራጂቭ ለማይክልና ለራሽድ፣እንዲህ በማለት ውይቱን ከፈተ፦

ባለፈው ውይይታችን ስለ አንዳንድ ሙስሊሞች ስነምግባር ያነሳናቸው ነገሮች፣ስነምግባር እስላም ውስጥ ምን እንደሚመስል እንድንነጋገር ይገፋፋናል። እናም ይህ ርእስ ወይይት ሊደረግበት የሚገባ አይመስላችሁም?

ማይክል፦ ልክ ነው። ብዙ ሙስሊሞችን የላቀ ጨዋ ስነምግባር የተላበሱ ሆነው ሳገኛቸው፣በሌላ በኩል ደግሞ የዚህ ተቃራኒ የሆነ ስነምግባር ያላቸውን አንዳንድ ሙስሊሞች ስመለከት እገረማለሁ።

ራሽድ፦ ለዚህ ሁለት ምክንያቶች አሉ። አንደኛው አንተ ራስህ ስለ ስነምግባር ያለህ እይታ ሲሆን፤ሁለተኛው ሰዎች ለአንድ የተለየ የስነምግባር ሥርዓት ያላቸው ተገዥነትና ሥርዓቱን በትክክል የሚወክሉበት ደረጃ ነው። ግለሰባዊ ስነምግባሮች፣ከውርስ በተጨማሪ የአካባቢና የአስተዳደግ ተጽእኖ በግልጽ ይታይባቸዋል . . ይህም የእስላም ነቢይ ﷺ ያመለከቱትና በሳይንሳዊ ሙከራና ጥናት የተረጋገጠ ነው።

ራጂቭ፦ ያመለከቱት ምን እንደሆነ ብታብራራው።

ራሽድ፦ ያመለከቱት ነገር ከሁለት የነቢዩ ﷺ ሐዲሦች የተጨመቀ ነው። በመጀመሪያው ረሱል ﷺ ለአንዱ ሶሓቢይ ፦ ‹‹አላህና መልክተኛው የሚወዷቸው ሁለት ባሕርያት፣ትእግስትና ቻይነት አሉህ›› ሲሉት፣‹‹የአላህ መልክተኛ ሆይ! እኔ በጥረት የተላበስኳቸው ናቸው ወይስ አላህ በተፈጥሮ ያደለኝ ናቸው?›› ሲል ጠየቃቸውና ‹‹አላህ በተፈጥሮ ያደለህ ናቸው እንጂ›› ያሉት ነው። ይህ ሐዲሥ ትእግስትና ቻይነት፣ውርስ (ጀነቲክ) በሆነ ተፈጥሮው አንድ ሰው ሊላበሳቸው ከሚችል ባሕርያት መካከል መሆናቸውን ያረጋግጣል። በሌላኛው ሐዲሥ ደግሞ ረሱልﷺ ፦ ‹‹ዕውቀት የሚገኘው ለመማር በመጣር ነው፤ትዕግስት የሚገኘው ለመታገስ በመጣር ነው፤በጎውን ነገር ሆን ብሎ የሚፈልግ ሰው ይሰጣል፤ክፉውን ሆን ብሎ የሚጠነቀቅ ሰውም ይጠበቃል›› ብለዋል። በመጀመሪያው ሐዲሥ ውስጥ የሶሓቢው ውርስ ባሕሪ የነበረው ትዕግስት፣በፍላጎትና በጥረት ሊገኝ እንደሚችል ሁለተኛው ሐዲሥ ያረጋግጣል። በእርግጥ ይህ እውን የሚሆነው የማህበራዊ እነጻ ሂደትን ተሳትፎ በሚጠይቅ የባህሪ እነጻና ቀረጻ አማካይነት ነው።

ማይክል፦ ይህ ጥልቀትና ብዙ ዝርዝሮች ወዳሉት ፍልስፍና ነክ ርእሰ ጉዳይ ይወስደናል። የፍልስፍና ብዥታዎቹን ወደ ጎን ብለን፣አንደኛ በሰው ልጅ ዘንድ ያለው ሞራላዊ ስነምግባራዊ ስሜት፣አንዳንዱን ባሕርያት እንዲወድና ሌሎቹን እንዲጠላ የሚያደርገው ተፈጥሯዊ ስሜት መሆኑን ላሰምርበት እፈልጋለሁ። በዓይነትና በመጠኑ ከሰው ሰው የሚለያይ ቢሆንም፣በአጠቃላይ ሲታይ ግን የሰው ልጅ በሁሉም ዘመንና ስፍራ አንዳንዱቹን ባህርያት ሰናይ ባሕርያት፣ አንዳንዱቹን ደግሞ እኩይ ባሕርያት አድርጎ መፈረጁን አላቋረጠም። ለምሳሌ ያህል እውነተኝነት፣ታማኝነት፣ፍትሐዊነት፣ቀጠሮ አክባሪነት . . እነዚህ ሁሉ በሁሉም ደረጃዎች በሰው ልጆች ዘንድ በአድናቆት መታየት የሚገባቸው ምጡቅ ስነምግባራት ተደርገው ይወሰዳሉ። የሰው ልጆች ውሸትን፣ግፍን፣ክህደትን፣እምነት ማጉደልን፣ . . ምንጊዜም ቢሆን በበጎነት ተቀብሎ አያውቅም። የመተሳሰብ፣የመተዛዘን፣የደግነት፣የመቻቻልና የልበ ሰፊነት ነገርም እንዲሁ ነው።

በዚህ ረገድ እስላም ከተቀሩት የሰው ልጆች ይለያል ማለት እንችላለን? እስላም ከተቀሩት የስነምግባር ሥርዓቶች የተለየ የራሱ የሆነ የስነምግባር ሥርዓት አለው ብሎ ማለት ይቻላል ወይ?

ራሽድ፦ በአቀረብከው ገለጻና የሰናይና እኩይ ስነምግባራትን ይዘት እውነታ በተመለከተ በጠቀስከው ላይ ተአቅቦ ቢኖረኝም፣በተናገርከው ላይ የሚከተለውን ማከል እፈልጋለሁ፦ ያምሆኖ ግን በእስላም ዘንድ ብቻ ሳይሆን በሁሉም ሃይማኖቶችና ሰው ሰራሽ ማሕበራዊ ሥርዓቶች ዘንድም የተለያዩ የስነምግባር ሥርዓቶች ተመስርተዋል። ይህ የሆነው ሁሉም በስነምግባር ውስጥ የሰናይነትና የእኩይነት መመዘኛንና ጥሩውና መጥፎው የሚታወቅበትን መንገድ በመወሰን ረገድ የሚለያዩ በመሆናቸው ነው። በተጨማሪም ከሕግ በስተጀርባ ሆኖ የሚሰራውን አስፈጻሚ ኃይል በመወሰኑ ላይም ልዩነት አላቸው። የልዩነቱ ምክንያት ለዚህ ዩኒቨርስና በተንጣለለው ሥርዓቱ፣በውስጡ የሰው ልጅ በሚኖረው ስፍራና በሕይወት ዓላማ ላይ ያላቸው እሳቤ የተለያየ መሆኑ ነው።

ለምሳሌ ያህል፣ብዙዎቹ የስነምግባር ንድፈ ሀሳቦች ራስ ወዳድነትን መነሻ መሰረታቸው ያደርጋሉ። በአውሮፓ ዘመነ ሕዳሴ፣ሆፕዝ እና እስፒኖዛ በየፊናቸው በተለያየ መንገድ፣ሰናይነት የራስን ሕልውና ማቆየት መሆኑን ያሰምሩበታል። ፍሮይድ ደግሞ ከቀዳሚ ጽሑፎቹ ጀምሮ የብዙዎቹን ምዕራባውያን ስነምግባራት እስካሁንም ድረስ በመቅረጽ ላይ የሚገኘውን ንድፈ ሀሳብ ያቀረበ ሲሆን፣ራስን ማስደሰትና ወሲባዊ ፍላጎትን ማርካት የሚመለከተው ሀሳብ ሙሉ በሙሉ ጥላውን ያጠላበት ንድፈ ሀሳብ ነው። በዚህ ብቻ ሳይወሰን ይህን ጽንሰ ሀሳብ ከተቀሩት የስነልቦና ጽንሰ ሀሳቦች በመጀመሪያው ፈድፍ ላይ ያስቀመጠ ሲሆን፣ስለ ሌሎች ማሰብንና ደግነትን ፣የሚኖራቸውን ተጽእኖ የሚያመነጩት የራስን ግላዊ ፍላጎት ከማርካት የተለያዩ ገጽታዎች ጋር የተሳሰሩ ከመሆናቸው አንጻር የሁለተኛ ደረጃ ክስተቶች ያደርጋቸዋል።

ከነዚህ ግላዊ ስነምግባሮች ስብስቦችንና ሕብረተሰቡን መሰረት ያደረገ የስነምግባር ስርዓት ይዋቀራል። እንዲህ ዓይነቱ ስነምግባር ከግለሰብ ይልቅ ለቡድን አስፈላጊነት ከፍተኛ ግምት ከሚሰጡ ንድፈ ሀሳቦች ይመሰረታል።

ማይክል፦ እስላም በተጨባጭ ከሌሎች የሚለየው የስነምግባር ሥርዓት አለው ብለን ካልን፣ሥርዓቱ በምን መሰረት ላይ ይቆማል? ልዩ መገለጫዎቹና ባሕርያቱስ ምንድናቸው?

ራሽድ፦ ባለፉት ውይይቶች እንደ ገለጽኩት ሁሉ፣እስላም ለመላው የሰው ልጆች የተሰጠ የተሟላ የአነዋነዋር ሥርዓት ነው። የዩኒቨርስን ምንነት የሚተነትንና በዚህ ዩኒቨርስ ውስጥ የሰው ልጅ የሚይዘውን ስፍራ የሚወስን፣የሰውን ልጅ የሕይወት ተልእኮና የተፈጠረበትን ዓላማ ለይቶ የሚያስቀምጥ . . የእምነት እሳቤን ያካተተ መርሕ ያለው ሥርዓት ነው። ከዚህ የዐቂዳ እሳቤ የሚመነጩ ተጨባጭ መዋቅሮችና አደረጃጀቶች ያሉት ሲሆን፣በሰው ልጆች ሕይወት ውስጥ ተጨባጭ ገጽታዎች ያሏቸው የስነምግባር ሥርዓቱንና ምንጩን፣የሚቆምባቸው መሰረቶቹን፣ከዚህ የሚመነጨውን ሥልጣን፣የፖለቲካ ሥርዓቱን ቅርጽና ባሕርያቱን፣ማሕባራዊ ሥርዓቱን መሰረቶቹንና ማእዘናቱን፣ኢኮኖሚያዊ ሥርዓቱን ፍልስፍናውንና አወቃቀሩን፣ዓለም አቀፍ ግንኙነቱንና ትስስሮቹን . . ያቀፈ ሁለንተናዊ ሥርዓት ነው።

ይህም፣የሕይወታቸውን ረዥም ዘመን በአንገሊካን ቤተክርስቲያን በቄስነት ያገለገሉት ዶክተር ኤም. ኤች. ዱራኒ እንዲህ በማለት የገለጹት ነው ፦

‹‹እስላም የራሱ የሆነ ሥርዓት፣ሕግና ስነምግባርን አጠቃሎ የያዘ ነው። በግለሰቦች ላይ በግዴታነት የተደነገጉ ሃይማኖታዊ ስነሥርዓቶች ስነምግባራዊ ዓላማ አላቸው . . በስነምግባራዊና መንፈሳዊ ጎኑ አሳማኝ በሆነ መንገድ ግለሰብን ለማነጽ የሚያነጣጥሩ ሲሆኑ፣አብረውት ለሚኖሩ ሌሎች ሰዎች ያለበትን ግዴታ በአግባቡ ይወጣ ዘንድ አእምሮውን ማጥራት፣ማጽዳትና ማጠናከርም ሌላው ግባቸው ነው። እስላም ንድፈ ሀሳባዊና ተግባራዊ ከመሆኑ አኳያ፣በክርስትና እምነት ውስጥ እንዳለው ዓይነት ነፍስ አልባ በሆኑ መርሆዎችና ስውር ምስጢራት እንዲያምን ሰውን የማይጠይቅ ብቸኛው ሃይማኖት ነው። ይህም እስላም የሕይወትን መንፈሳዊና ቁሳዊ ገጽታዎች በእኩልነት የሚቀበል፣ሁሉንም በተገቢ ቦታቸው የሚያስቀምጥና ሁሉንም የሰው ልጅ የሕይወት ፈርጆች በሚሸፍን መሰረት ላይ ፍልስፍናውን የሚያንጽ በመሆኑ ነው።››

ራጂቭ፦ የእስላም የስነምግባር ሥርዓት የሚቆምበት መሰረት ይህ ነው ካልን፣የዚህን ሥርዓት አበይት ባሕርያትና ከሌላው የሚለዩትን ጉዳዮች መጥቀስ አስፈላጊ ይመስለኛል።

ራሽድ፦ እስላማዊውን የስነምግባር ሥርዓት መገለጫ ባሕርያትን እንደሚከተለው ማጠቃለል ይቻላል፦

የዐቂዳ መሠረት፦ ይህ የሰው ልጅ ለፈጣሪ አምላኩ ተገዥ የሆነ ፍጡር በመሆኑ፣ለርሱ የሚበጀውን ከማንም በላይ የሚያውቀው ፈጣሪው በመሆኑ፣ፈጣሪው እንዲሁ ያልተወውና መልክቱንና ትምሕርቶቹን የሚያደርሱለት፣መንገዱንም የሚያሳውቁት መልእክተኞችን የላከለት በመሆኑ፣የሰው ልጅ ከሞት በኋላ በሌላ ሕይወት ዳግም በመቀስቀስ በመጀመሪያ ሕይወቱ በሠራው በጎና ክፉ ሥራዎች ተመርምሮ የሚሸለም ወይም የሚቀጣ በመሆኑ የሚገለጽ ነው። ይህ ደግሞ የሳይንስና የሕይወትን ከቤተክርስቲያን መነጠል ተከትሎ፣ከሃይማኖት በተነጠለው የዛሬው የምዕራቡ ዓለም ውስጥ ካለው ስነምግባር ጋር የሚጻረር ነው።

ጽናት፦ እስላማዊ ስነምግባራት፣የሰውን ልጅ፣ሕይወትንና ዩኒቨርስን ከሚመለከቱ የጸኑ መሠረቶችና እሳቤዎች የመነጩ፣የጸኑ መርሆዎችና እሴቶች መገለጫዎች ናቸው። ዓላማቸው የሰው ልጆች ሲሆኑ፣በዙሪያቸው ያሉት የሕይወት ሁኔታዎችና ክስተቶች ቢለዋወጡ እንኳ ምንጊዜም እውነታቸው የማይለዋወጥና ይዘታቸው የማይቀያየር ነው። እውነተኛነት፣ታማኝነትና ታጋሽነት ዝንተዓለም ትሩፋት እንደሆኑ ይቀጥላሉ። መዋሸት፣ማሳበቅና ሐሜት ደግሞ ዝንተዓለም እኩይ ባሕርያት እንደሆኑ ይኖራሉ። ጋጠወጥና አፈንጋጭ ባህርያትም እንደዚሁ፣በሰዎች መካከል መሰራጨታቸው ወይም በአንዳንድ መንግስታት ዘንድ የተፈቀዱ እንዲሆኑ መደረጋቸው፣የሰው የአነዋነዋር ዘይቤ የፈለገውን ያህል ቢለወጥ እኩይና ተልካሻ ባርያት መሆናቸውን ቅንጣት ታህል አይለውጥም።

ተጨባጭነትን የተላበሰ ተምሳሌታዊነት፦ እሰላማዊ ስነምግባራትን የማያውቁ አንዳንድ ወገኖች ተምሳሌታዊ ብሎ የሚጠሩ ከሆነ፣እውነታው ግን የሰውን ልጆች ተጨባጭ ሁኔታና አቅማቸውን ግንዛቤ ውስጥ የሚያስገቡ ተጨባጭነትን የተላበሰ ተምሳሌታዊነት ያላቸው መሆኑ ነው። እያንዳንዱ ግለሰብ ሊተገብራቸውና ሊላበሳቸው የሚችል ስነምግባራት ሲሆኑ፣ክቡር ፍጡር ከመሆኑ አንጻር የግለሰብን ሕይወት የሚጠብቁ፣ሕይወቱን ያለ እንቅፋትና መሰናክል እንዲመራ የሚያደርጉ፣ከሰው ልጆች ተፈጥሮ ጋር የማይጋጩና የማይፋለሱ፣ይልቁንም የሚጣጣሙና የሚቀናጁ ስነምግባሮች ናቸው። እስላማዊው እሳቤ አይሁዳዊነት ትኩረት የሰጠውን ሕጋዊ ገጽታና ክርስትና አጽንኦት የሚሰጠውን መንፈሳዊ ገጽታ በጥምረት የያዘ ሲሆን፣ሕንዳዊው ጸሐፊ ፔጂ ራዴሪክ ይህን ጥምረት እንደሚከተለው ገልጾታል፦

‹‹የእስላም ስነምግባራዊ ትምሕርቶች ተምሳሌታዊነትንና ተጨባጭ ተግባራዊነትን በተሟላ መልኩ አንድ ላይ ያጠመሩና ያጣጣሙ ናቸው። በመሆኑም አንድ ሰው በትምሕርቶቹ አማካይነት በዕለታዊ ሕይወቱ ጉዳዮች ውስጥ ተጠምዶ እያለ፣አላህን አውቆ ትጉህ መንፈሳዊ ሰው መሆንም ይችላል . . ››

ቁርጠኝነት፦ ይህ ደግሞ አንድ ሰው መላው የሰው ዘር ቢጋፈጠው እንኳ ለነዚህ ስነምግባሮች በቁርጠኝነት ተገዥ ለመሆን የሚገባው ቃል ኪዳን ነው። ይህም የሰው ልጅ በዚህች ዓለማዊ የዱንያ ሕይወቱ ኃላፊነት የተጣለበት፣ተልእኮ ያለውና አደራን የተሸከመ፣ሥራዎቹን የሚገዛና የሽልማት ወይም የቅጣት መነሻ የሆነ የፍላጎት ነጻነት ያለው ፍጡር ከመሆኑ አንጻር ነው። ለዚህም ነው የስነምግባር ተገዥነትና ጽናት ከግለሰባዊ ኃላፊነትና ከጠጠያቂነት ገጽታዎች ዋነኛው የሆነው።

ተጠያቂነት፦ አንድ ሰው የኃላፊነት ስሜት የሚፈጠርበት ሳይሆን የትሩፋትና የመልካም ስነምግባር ባለቤት መሆን አይችልም። እዚህ ላይ ተጠያቂነት ወይም ኃላፊነት ሲባል ግለሰቡ የራሱን ድርጊቶች አውቆ ኃላፊነት መውሰድ፣የሚያስከትሉትን ውጤቶች ለመቀበል፣ለውሳኔዎቹና ለምርጫዎቹ ገንቢም ሆኑ አፍራሽ በአላህ ፊት፣ለገዛ ሕሊናውና ለሕብረተሰቡም ተጠያቂ ለመሆን ዝግጁ መሆን ማለት ነው።

የተጠያቂነት ገደብ ከተጠያቂነት ጋር የተያያዘ ሲሆን፣እስላም ውስጥ ኃላፊነትና ተጠያቂነት የተግባሩን ወይም የውሳኔውን ባለቤት ብቻ የሚመለከት ግለሰባዊ ኃላፊነት ነው። በድርጊቱ ወይም በውሳኔ አሰጣጡ ላይ ከአንድ የበለጡ ግለሰቦች ተሳታፊ ከሆኑ ግን፣ኃላፊነቱ የጋራ ይሆናል። ግለሰብና ሕብረተሰብም አንዱ ለሌላው ኃላፊነትና ተጠያቂነት አለባቸው። መርሑ ግን አንድ ግለሰብ ለሌላው ግለሰብ ድርጊት ወይም ውሳኔ ኃላፊና ተጠያቂ የማይደረግ መሆኑ ነው።

ስነምግባርን ከአጠቃላዩ ማሕበራዊ ሥርዓት ከማስተሳሰር ጋር የሕሊናን ውስጣዊ ግፊት ማጎልበት፦ ውስጣዊ ዓለሙን የሚመሰርተው ሰው ራሱ ነው። ከዚህ ዓለም ነው ለስነምግባር የመገዛት እውነተኛው ግፊት የሚወለደው። እስላም፣‹‹ንይያህ›› በመባል በሚታወቀውና አንድ ሰው ለሚሠራው ሥራ የተወሰነ ሕጋዊና ተገቢ የሆነ ቁርጠኛ ውስጣዊ ፍላጎት ማሳደር ለሆነው፣በሁሉም ሁኔታ ውስጥ አጽንኦት በመስጠት አማካይነት ይህን ውስጣዊ ግፊት ለማጎልበት ይሠራል። ይሁን እንጂ የሰው ልጅ ምሉእ ወይም ከስህተት የተጠበቀ አለመሆኑን፣በዙሪያው ባሉት ላይ ተጽእኖ የሚያሳድር ድክመት ሊያገኘው እንደሚችልም እስላም ይገነዘባል። በመሆኑም የሰውን ልጅ ለውስጣዊ ግፊቱና ለሕሊናው ዳኝነት ሳይተወው፣በደነገጋቸው ማሕበራዊና ሕጋዊ መቀጫዎች፣ማረሚያዎችና ከመርሆዎቹ ለሚያፈነግጡ በተሰናዱት የወዲያኛው የኣኽራ ሕይወት ቅጣቶች አማካይነት፣ግለሰቦች ለስነምግባራዊ መርሆዎች ያላቸውን ተገዥነት እስላም አጠናክሯል።

ራጂቭ፦ በእውነት ሊጤንና ከበሬታ ሊቸረው የሚገባ ሥርዓት ነው።