ሰብአዊ መብቶች በእስላም

ሰብአዊ መብቶች በእስላም

ራሽድ ኮምፒውተሩን ከፍቶ ወደ ቻት ሩም ሲገባ የሚከተለውን የማይክል መልእክት አገኘ፦ ‹‹ለመጪው ውይይት ራስህን አዘጋጅ . . ልንነጋገርባቸው የሚገቡ ከሌላው ጋር የሚኖረውን ግንኙነትን፣የፍላጎት እመቃን፣የሀሳብ ነጻነትን . . የሚመለከቱ አስፈላጊ የሆኑ ጉዳዮች አሉን . . ደህና ሁን።

ራሽድ ሁለቱን ወዳጆቹን ቻት ሩም ውስጥ ሆነው አገኛቸውና ሰላምታ ሰጥቷቸው እንዲህ ሲል ቀጠለ፦

ከሰብአዊ መብት ጋር የተያያዙ ጉዳዮች ወዳጄ ማይክል በጠቀሳቸው ላይ ብቻ የሚወሰኑ ሳይሆኑ በጣም ብዙ ናቸው። በመሆኑም የፈለጉትን ያህል ቢለያዩ ወይም ቢራራቁ ጉዳዮቹን መገንዘብ እንችል ዘንድ አጠቃላይ የሆነ ማእቀፍ ውስጥ ማስቀመጥ ግድ ይላል።

ማይክል፦ የምንናገረው ሊተገበር የሚችል ተጨባጭ እንዲሆን፣በጻፍኩልህ መልእክት እንደጠቀስኩት ዓይነት አንዳንድ ምሳሌዎችን ማቅረብ ክፋት የለውም።

ራሽድ፦ በእርግጥ ችግር የለውም።

ራጂቭ፦ ባለፈው ውይይታችን ላይ መንደርደሪያ ሊሆነን ስለሚችል መሰረታዊ መርህ አንስተህ ነበር። እነዚህን መብቶችና ነጻነቶች የምር ለማጤን ከፈለግን መመርመር ያለብን የቆሙበትን እሴቶችና መርሆዎች እንጂ፣መተግበሪያዎቻቸውንና የሰዎቹን አድራጎቶች መሆን የለበትም፣ብለህ ነበር።

ራሽድ፦ ልክ ነው . . የ‹‹ነጻነቶች›› እና የ‹‹ሰብአዊ መብት›› ጽንሰ ሀሳብ፣እነዚህ መብቶች ከወጡበት ፍልስፍናዊ ዳራ አንጻር የሚቃኝና በውስጡ ለተገኙ አጠቃላይ ማህበራዊ የእሴቶች ስብስብ የሚገዛ ነው . . እዚህ ላይ ለወዳጄ ለማይክል የማቀርበው ጥያቄ፣ከምዕራባዊው ግንዛቤ አኳያ ሰብአዊ መብቶች የቆሙበትን ፍልስፍናዊ ዳራና የእሴቶች ሥርዓትን ብታብራራልንስ? የሚል ይሆናል።

ማይክል፦ በምዕራቡ ዓለም ነጻነቶችንና መብቶችን ያመነጩትን የፍልስፍናዊና የእሴታዊ ማእቀፍ ገጽታዎችን በሚከተሉት ነጥቦች ማጠቃለል ይቻላል፦

1-የእነዚህ ነጻነቶችና መብቶች መሠረት ነጻ አእምሮ ነው። ይህ ነጻ አእምሮ - ፕሮቴስታንት በሊብራሊዝም ላይ እንደ አሳደረው ተጽእኖ - አንዳንድ ሃይማኖታዊ እሴቶችን ቢዋስ እንኳ፣እነዚህን እሴቶች ወድቅ ለማድረግም ሆነ ለመቀበል ወሳኙ ግን ነጻው አእምሮ ይሆናል።

2-እነዚህ መብቶችና ነጻነቶች የሚደራጁበት ስልትና መርህ ሴኩላሪዝም (ሃይማኖትን ከሕይወትና ከመንግሥት መነጠል) ነው።

3-‹‹ነጻነት›› እና ‹‹እኩልነት›› የተቀሩት የሕብረተሰቡ እሴቶች የሚመሩባቸውና ራሳቸውን የሚያስማሙባቸው ሁለቱ የሕብረተሰቡ የበላይ ገዥ እሴቶች ናቸው። ጸንተው የሚኖሩ የተቀደሱና ሊደፈሩ የማይችሉ አይነኬዎች ናቸው።

4-የሕብረተሰቡን ሚና እና ጥቅሞቹን ችላ ካለ ማለት ጎን፣የግለሰብ ሕይወት ደስታ የሰፈነበትና ይበልጥ የተደላደለ ይሆን ዘንድ ግለሰባዊ እሴትና ግለሰባዊ ጥቅሞችን ከፍ ከፍ ማድረግና ማላቅ።

ራሽድ፦ ግልጽና ቁልጭ ያለ ገለጻ ነው፣አመሰግናለሁ። እንግዲያውስ የምዕራቡ ዓለም በሁሉም የሕይወት መስኮች ከቤተ ክርስቲያን ጋር ከተቆራረጠ በኋላ፣የመሪነት ሚናው ለአእምሮና ለተግባራዊ ግንዛቤ ተላልፏል ማለት ነው። እነዚህ መብቶችና ነጻነቶች የፈለቁትም ከዚህ ከአዲሱ አመራር ነው ማለት ነው። በተጨማሪም መብቶቹና ነጻነቶቹ የታነጹበት መሰረትም ሴኩላሪዝም መሆኑ ግልጽ ነው።

እንደዚሁም ‹‹ነጻነት›› እና ‹‹እኩልነት›› በዚህ መንደርደሪያ መርህ መሰረት በምዕራቡ ዓለም በጸናው የእሴቶች ቅደም ተከተል ፒራሚድ ውስጥ ቁንጮውን ቦታ ይይዛሉ ማለት እንችላለን። በምዕራባዊው ግንዛቤ መሰረት እነዚህን ሁለት እሴቶች እውን ማድረግ፣የተቀሩት የሕብረተሰቡ ሁሉም እሴቶች ሊታዘዟቸው የሚገባ፣ገደብ ሊጣልባቸው ወይም ተኳኳኝ ሊሆኗቸው የሚገባ ፍጹማዊ አስፈላጊነት አለው። ከዚህ የምንረዳው ‹‹ነጻነት›› እና ‹‹እኩልነት›› በቋሚና አይነኬ በሆኑ የተቀደሱ መርሆዎች አናት ላይ የተቀመጡ፣እነርሱን ለማስከበር ሲባል ሌሎች እሴቶችና መብቶች ሊሰው የሚችሉ መሆናቸውን ነው።

ይህ ደግሞ እነዚህን መሰል ጽንሰ ሀሳቦች ወይም ቴክኒካዊ ቃላትን ከያዘው እስላማዊ ዳራ ሙሉ በሙሉ የተለየ ነው።

ራጂቭ፦ ለማነጻጸር እንዲመቸን፣ይህ ጽንሰ ሀሳብ (ሰብአዊ መብት) እስላም ውስጥ ያለውን ፍልስፍናዊ ማእቀፍና የሚዋኝበትን እሴታዊ ኅዋ አብራራልን።

ራሽድ፦ በእስላምና በእስላማዊ ሕብረተሰብ ውስጥ ከዚህ ሙሉ በሙሉ የተለየ ማእቀፍ የምናገኝ ሲሆን፣በሚከተሉት ነጥቦች ማጠቃለል ይቻላል፦

1-ከ‹‹ነጻ አእምሮ›› እና ከ‹‹ከተግባራዊ ግንዛቤ›› አንጻር፣የእሴቶች ዋነኛውና ቀዳሚው መስፈርትና ማመሳከሪያ ዋቢ፣የጸኑ መሰረቶችና የተቀደሱ አይነኬዎች መነሻ የሆነው ‹‹ወሕይ›› (መለኮታዊ መገለጥ) ሆኖ እንገኛለን። ይህም የራሳቸው በሆነው ክልል ውስጥ አእምሮና ተግባራዊ ግንዛቤ የሚመሰርቱትን ዕውቀታዊ መስፈርት አስፈላጊነት ችላ ሳንል ነው።

2-ከ‹‹ሴኩላሪዝም›› አንጻር ደግሞ እስላም ውስጥ ‹‹ሸሪዓ›› እና የሃይማኖት ከዓለማዊ ሕይወት (ከዱንያ) ጋር መጣጣም፣ሕብረተሰቡ የሚታነጽባቸው መሰረቶች ሆነው እናገኛለን።

3-ከ‹‹ነጻነት›› እና ‹‹እኩልነት›› አንጻር ደግሞ፣የአላህ ‹‹ተገዥ›› መሆንና በሰዎች መካከል ‹‹ፍትሕ›› ማስፈን (ፍትሕን ማስፈን አንዳንድ ሰዎች እንደሚያስቡት የግድ እኩልነትን ማስፈን ማለት አይደለም)፣በእስላማዊው ሕብረተሰብ ውስጥ የእሴቶች ፒራሚድ አናት ላይ ተቀምጠው እናገኛቸዋለን። እነዚህን ሁለት እሴቶች እውን ማድረግና ፈጽሞ አለመጣስ፣መብቶችንና ነጻነቶችንም ጨምሮ የተቀሩት የሕብረተሰቡ እሴቶች፣ከነሱ በታች መሆንና በነሱ መገደብ ወይም ከነሱ ጋር መጣጣምና መኳኳን ይገባቸዋል።

4-ከ‹‹ግለሰባዊነት›› አንጻር ደግሞ፣እስላም ውስጥ በግለሰብና በሕብረተሰብ መካከል፣አንዱ የሌላውን ድንበር ሳይጋፋና መብት ሳይጥስ የጋራ ኃላፊነትና ተራድኦ መኖሩን እንገነዘባለን።

ራጂቭ፦ ሥዕሉ የበለጠ ግልጽ ይሆንልን ዘንድ እነዚህን ሁለት የእሳቤ መንገዶች፣ስምምነት ካልተደረሰባቸው አንዳንድ መብቶች ጋር እያስተሳሰርን ብንመለከታቸው መልካም ይመስለኛል።

ማይክል፦ በየአንዳንዳቸው ዘንድ ባለውና የሰብአዊ መብቶች መንደርደሪያ በሆነው የእሰቶች ዳራ ላይ በመመርኮዝ፣እስላማዊውንና ምዕራባዊውን እሳቤ ለማነጻጸር ያህል የእምነት ነጻነትን ርእስ መውሰድ እንችላለን።

ራሽድ፦ የእምነት ነጻነት ወይም ‹‹የሃይማኖት ነጻነት›› በእርግጥ ለንጽጽሮሽ የተመቸ መስክ ነው። ርእሰ ጉዳዩ በሁለቱ እሳቤዎች መካከል ባለው የ‹‹ሃይማኖት›› ጽንሰ ሀሳብ ልዩነትና በሁለቱ ሥርዓቶች ውስጥ ሃይማኖት ከእሴቶች ፒራሚድ ጋር ባለው ግንኙነት ላይ የተመረኮዘ ነው።

በምዕራቡ ዓለም አንድ ሰው የፈለገውን ዓይነት ሃይማኖት የመከተል፣ኢ-አማኝ (ኤቲስት) መሆን ወይም ሃይማኖቱን መለወጥ መብቱ ነው። ይህ ሁሉ በ‹‹የእምነት ነጻነት›› ማእቀፍ ውስጥ የሚካተት ሲሆን፣‹‹ግለሰባዊ›› መብት ነውና ማንም ጣልቃ ሊገባበት አይችልም።

ይሁን እንጂ በምዕራቡ ዓለም አንድ ሙስሊም ያሻውን ‹‹የማመን መብት›› አለው ተብሎ የሚጠበቅ ቢሆንም . . በዚህ መብት መሰረት የሚያምንበትን ነገር የመተግበር ነጻነት ግን የለውም። ይህም ማለት ምዕራቡ ዓለም ሕይወቱን በእምነቱ አስተምህሮ መሰረት እንዳይመራ የሙስሊሙን መብቱን ይጋፋል ማለት ነው። ለምሳሌ ያህል በብዙ አገሮች ውስጥ ሙስሊሙ በሸሪዓዊ መንገድ የታረደ ሐላል ሥጋ እንዳያገኝ ይከለከላል። ከአንድ በላይ ሚስት እንዳያገባም ይከለከላል። በአንዳንድ አገሮች ውስጥ ደግሞ ሙስሊም ሴት የእምነቴ ግዴታ ነው ብላ የምታምነውን የአለባበስ ይትባሃል (ሕጃብና ንቃብ) እንዳትለብስ ትከለከላለች። እነዚህን ነገሮች መፈጸም ግን ለአንድ ሙስሊም የሃይማኖቱ አንድ ክፍል ነው . . ይህንንስ ማብራራት ትችላለህ?

ማይክል፦ እነዚያ ድርጊቶች ከ‹‹ግላዊ ስሜትና ከራስ ሕሊና›› ማእቀፍ የወጡ በመሆናቸው ከ‹‹እምነት ነጻነት›› መብት ማእቀፍ ውጭ ስለሆኑ ነው። በተጨማሪም ሕግንና ብዙኃኑ የሕብረተሰብ አባላት የመረጡትን ሃይማኖትን ከሕይወት ጉዳዮች የመለየት ማህበራዊ ውልን መጣስ ነው።

በተመሳሰሳይ ወቅት ግን ለዚህ ሙስሊም ከትዳራዊ ሕይወት ውጭ ፈቃደኞች እስከሆኑና በትዳር አልጋ ላይ እስካልሆነ ድረስ፣ከሌሎች ሴቶች ጋር ወሲባዊ ግንኙነት መፈጸም ሕጉ ይፈቅድለታል እለሃለሁ።

ራሽድ፦ በሕግ የሚፈቀድለት ይህ አድራጎት ግን ከሚያምንበት ሃይማኖት ጋር ይጻረራል!

በነዚህ ድርጊቶችና በሃይማኖት መካከል ትስስር አለ ብላችሁ ጭራሹንም የማታምኑ በመሆኑ፣እነዚን ገደቦች መብቶችንና ነጻነቶችን የሚያጎድሉ አድርጋችሁ እንደማትቆጥሩ በእርግጥ አውቃለሁ። ይልቅዬ ይህን ጥሰትና የመብት አፈና፣የተቀደሱ ‹‹አይነኬዎች›› ለሆኑት ሲቪል ድሎቻችሁ መጠበቂያና መቆጣጠሪያ አድርጋችሁ ነው የምትወስዱት።

ለዚህ መነሻው፣የ‹‹እምነት ወይም የሃይማኖት›› እሳቤ ሃይማኖትን ከሕይወት ከሚነጥለው የምዕራቡ ሴኩላሪዝም አመለካከት ጋር የተጣጣመ መሆኑ ነው። በዚህ እሳቤ መሰረት ሃይማኖት ግለሰብ እውስጡ ብቻ የሚሰማው ግላዊ ስሜት ወይም የራሱ የሆነ ሕሊናዊ ጉዳይ እንጂ፣ከሕብረተሰቡ ጋር ምንም ግንኙነት የለውም። በዚህም ቀደም ሲል እንደ አብራራኸው ሃይማኖትን ሙሉ በሙሉ ከተግባራዊ የሕይወት ጉዳዮች የተነጠለ እንዲሆን ያደርገዋል።

ራጂቭ፦ ገና አሁን እስላማዊውን አመለካከትና እሳቤ መገንዘብ ጀምሬያለሁ።

ራሽድ፦ በእስላማዊ እሳቤ ‹‹የእምነት ነጻነት››፣ለዚህ ሕብረተሰብ የተቀደሰ ላእላይ እሴት (ለአላህ ተገዥና ተመሪ መሆንን) ግንዛቤ ውስጥ በሚያስገባ ማእቀፍ ውስጥ የተረጋገጠ ነው። በዚህም መሰረት እስላማዊ ሕብረተሰብ፣የአላህን ስልጣን በጥቅሉ ለመቀበል የሚያውጀውንና በዚህ ስልጣን ላይ እምቢ ብሎ የሚያምጸውን ሁሉ ውድቅ ለማድረግ የሚያውጀውን ሁሉ በጥላው ስር ያሰባስባል። ከዚህ የተነሳ ነው እስላማዊው ሕብረተሰብ ለተለያዩ ሃይማኖቶች መኖር ክፍት የሆነው። አይሁዳዊነትንና ክርስትናን ለሚከተሉ ወገኖች የራሳቸውን ግለሰባዊ ጉዳዮች የማደራጀት ነጻነት አውቆላቸው በመቻቻል እንዲኖሩ ሕብረተሰቡ የተቀበለውም ለዚህ ነው። በተቃራኒው ግን ከነዚህ ውጭ ለሚገኙት ጣዖት አምላኪዎች ወይም ኤቲስቶች ክፍት አልሆነም። ይህም አይሁዳዊነትና ክርስትና መለኮታዊ መሰረት የነበራቸውና የአላህን ስልጣን በጥቅሉ ለመቀበል በጥላው ስር ከተጠለሉት ጋር ራሳቸውን የሚያስተሳስሩ መሆናቸውን ግንዛቤ ውስጥ በማስገባት ነው።

በእስላም እይታ፣የአላህን ስልጣን በጥቅሉ ከመቀበል ‹‹የጸና›› እውነታ ጋር የሚላተመውና በሁለቱ ሃይማኖቶች ላይ ከጊዜ በኋላ የተከሰተው መዛባትና ተአማኒነትን የማጣት ሁኔታ ግን፣ እነሱን በተመለከተ ‹‹ሀሳብን የመግለጽ ነጻነት›› አድማስ ከ‹‹እምነት ነጻነት›› አድማስ ይበልጥ የጠበበ እንዲሆን ያደርጋል። በመሆኑም ሃይማኖቶቻቸውን የመስበክም ሆነ፣የተውሒድ መሰረታቸውን የለቀቁ መሆናቸውን የሚጠቁሙ የአምልኮ ስርዓታቸውን ከአማኞቻቸው ክልል ውጭ መግለጽና ማሳየት አይችሉም። የ‹‹ሀሳብን በነጻ የመግለጽ›› መብት ከዚህ ክልል ከወጣ፣በሕብረተሰቡ የእሴቶች ፒራሚድ አናት ላይ የተቀመጠውን ማሕበራዊ ሥርዓት የሚጥስና የተቀደሰውን ጽኑ አይነኬ መሰረት የሚንድ ይሆናል።

ማይክል፦ እስላም ተከታዮቹ ወደ ሌላ ሃይማኖት እንዳይለወጡ መከልከሉን በተመለከተስ?

ራሽድ፦ ይህ ጥያቄም አሁን ካነሳሁት ጋር የሚታይ ነው። ከእስላም የተቀለበሰ (ሙርተድ) ሰው ጉዳይ፣እስላማዊው አመለካከት ከሚያራምደው የ‹‹እምነት ነጻነት›› እሳቤ ጋር የተሳሰረ ነው። እስላም ከመነሻው ሃይማኖቱን ያልተቀበለውን ሰው አይቀጣም፤ ሃይማኖቱን እንዲቀበል ማንንም አያስገድድም። አላህ ﷻ እንዲህ ብሏል፦

{በሃይማኖት ማስገደድ የለም፤ቅኑ መንገድ ከጠማማው በእርግጥ ተገለጠ፤}]አልበቀራህ፡286 ]

{ ፦ እውነቱም፣ከጌታችሁ ነው፤የሻም ሰው ይመን፤የሻም ሰው ይካድ፣በላቸው፤} [አልከህፍ፡29 ]

{ ለናንተ ሃይማኖታችሁ አላችሁ፤ለኔም ሃይማኖት አለኝ።} [አልካፊሩን፡6] በተመሳሳይ ወቅት ሃይማኖቱን ትቶ ወደ ሌላ ሃይማኖት መለወጥን ግን የሚከለክልና ‹‹የሚቀጣ›› ሆኖ እናገኛለን።

ከሃይማኖቱ የተቀለበሰን (ሙርተድ) ሰው በተመለከተ እስላምን ያለውን አቋም መረዳት የምንችለው፣አድራጎቱ ሕብረተሰቡ የቆመበትን ታላቅ እሴትና የጸና መሰረት መንካት ተደርጎ የሚወሰድ ከመሆኑ አንጻር ነው። በሌላ አነጋገር ይህን ማድረግ የዚህን ሃይማኖት ትክክለኛነት መዝለፍ ወይም ለሰው ልጅ አስፈላጊ አለመሆኑን ማወጅ አድርጎ ይቆጥረዋል። ይህ ደግሞ ሕጋዊነቱንና ዋቢውን በዚህ ሃይማኖት ትክክለኛነት አስፈላጊነት ካለው እምነቱ በሚያመነጨው ሕብረተሰብ ውስጥ ተቀባይነት የለውም።

ይህ በምዕራቡ ዓለም ውስጥ ካለው መብት በመነሳት የ‹‹ጸናውን›› እና ‹‹የተቀደሰውን›› አይነኬ ‹‹ነጻነት›› ለማፍረስና ለማውደም እንደሚጠይቅ ሰው ልንወስድ እንችላለን። ከአፍቃረ ነጻነት ሰዎች ወዲያውኑ የሚጠብቀው ዝግጁው ምላሽ ‹‹የነጻነት ጠላቶች ነጻነት አይገባቸው›› የሚለው የታወቀው መፈክር ነው። ይኸውም ይህ ጥያቄ ነጻነትን ለመግደል ነጻነትን በመሳሪያነት የሚጠቀም ማለትም ሕብረተሰቡ የቆመበትን ታላቅ እሴትና የጸና መሰረት ለመናድ የሚገለገል በመሆኑ ነው።

ማይክል፦ ራሽድ፣ለሰጠኸን ማብራሪያ ከልብ አመሰግናለሁ . . በነዚህ ውይይቶች በጣም ደስተኛ ነኝ፤ቀጣይነት እንዲኖራቸውም ምኞቴ ነው።