መጪው ዘመን የእስላም ነው

መጪው ዘመን የእስላም ነው

ያለልማዱ ከቀጠሮው ሰዓት ዘግይቶ የነበረውን ራጂቭን በኮምፒውተሩ ስክሪን ላይ ገና ብቅ ብሎ ሲመለከት ወዳጁ ማይክል እንዲህ እያለ ተቀበለው፦

ራጂቭ እንኳን ደህና መጣህ፣በቀጠሮ መገኘትን ነበር የለመድንብህ፣የዘገየኸው ችግር ገጥሞህ እንደማይሆን ተስፋ አደርጋለሁ።

ራጂቭ፦ ወዳጆቼ በጣም ይቅርታ፣ችግር እንኳ አላጋጠመኝም፣ግና ላቀርብላችሁ ያሰብኩትን አንድ ጥናት ብጤ ማጠናቀቅ ጊዜ ወስዶብኝ ነው።

ማይክል፦ በጣም ጥሩ፣እንግዲያውስ ውይይቱ የጎለበተና ጥልቀት ያለው ይሆናል፤ለመሆኑ ጥናትህ በምን ዙሪያ የሚያጠነጥን ነው?

ራጂቭ፦ እውነቱን ለመናገር በውይይቶቻችን ውስጥ እስላምን አስመልክተው በቀረቡ መረጃዎች ትኩረቴ በጣም በመሳቡ፣ይህ ሃይማኖት ከስርጭት አንጻር ዛሬ በዓለም ላይ ያለበት ሁኔታ ምን ይመስላል የሚለውን ለማየት ነው የሞከርኩት።

ማይክል፦ እኔንም እንዳጠናው የገፋፋኝ ይኸው ነው። የኔ ጥናት ግን ሌሎች ገጽታዎቹን ዳሰሰ፣በጥልቀት የምንመለከታቸውን ጎኖቹን ከመደበኛ ምንጮቻቸው በመፈተሽ ላይ ያነጣጠረ ነው . . ለመሆኑ በጥናትህ ምን አዲስ ነገር አገኘህ? . . ራሽድ !! ከኛ ጋር ነህ? እየተከታተልከን ነው አይደለ?!

ራሽድ፦ አዎ፣አዎ፣እየተከታተልኳችሁ ነው።

ራጂቭ፦ ሁሉም ምንጮችና መረጃዎች እስላም በዓለም ላይ ስርጭቱ ከቀን ወደ ቀን እየጨመረ በመሄድ ላይ የሚገኝ ሃይማኖት መሆኑን የሚያሳዩ ሆነው አግኝቻለሁ። በጥናቴ እንደ ደረስኩበት በዓለም ላይ ከ4200 የሚበልጡ የእምነት ቡድኖችና ጎራዎች የሚገኙ ሲሆን፣አኃዛዊ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት እስላም ከተቀሩት ሃይማኖቶች ሁሉ ይበልጥ በፍጥነት በመሰራጨት ላይ የሚገኝ ሃይማኖት ነው! ዛሬ በሁሉም ክፍለ አህጉራት ትኩረት በሚስብ ሁኔታ በፍጥነት በመስፋፋት ላይ ሲሆን፣የሙስሊሞችን እድገት ከክርስቲያኖች እድገት መቶኛ ጋር ስናነጻጽር ልዩነቱ ብዙ መሆኑን እንረዳለን። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አኃዛዊ መረጃ እንደሚያመለክተው፣በዓለም ላይ የሙስሊሞች ዓመታዊ አማካይ እድገት 6.4% ሲሆን፣የክርስቲያኖች ዓመታዊ አማካይ እድገት ግን ከ 1% የሚያልፍ አይደለም።

ጥናቴ አውሮፓ ላይ በተለይ ያተኮረ ሲሆን፣ለምሳሌ ያህል እስላም በእስፔይን፣በፈረንሳይና በእንግሊዝ ሁለተኛው ትልቅ ሃይማኖት ሆኖ ነው ያገኘሁት።

በጀርመንም የሙስሊሞች ቁጥር እየጨመረ በመሄድ ላይ ሲሆን፣በጀርመኑ ዕለታዊ ጋዜጣ ‹‹ዲቬልት›› ዘገባ መሰረት፣እስላም ጀርመን ውስጥ በፈጣን ሁኔታ በነሰራጨት ላይ ይገኛል።

የፈረንሳይ የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር ባዘጋጀው ጥናት፣በየዓመቱ ከ3600 የሚበልጡ ሰዎች እስላምን ተቀብለው ይሰልማሉ። ጥናቱ ፈረንሳይ ውስጥ 2300 መስጊዶችና 7 ሚሊዮን ሙስሊሞች የሚገኙ መሆኑን፣በ2025 ሙስሊሞች ከፈረንሳይ ሕዝብ ቁጥር 25%ውን እንደሚይዙ፣በአውሮፓ ደግሞ በ2025 የሙስሊሞች ቁጥር 20% እንደሚደርስ ግምቶች መኖራቸውን አመልክቷል። በ2040 ሙስሊሞች በአውሮፓ አብላጫውን ቁጥር እንደሚይዙ የሚያመለክቱ ሌሎች አኃዛዊ መረጃዎችም አሉ።

ከአስር ዓመት በኋላ ከሆላንድ ሕዝብ አንድ ሦስተኛው ሙስሊም እንደሚሆን አኃዛዊ መረጃዎች ይናገራሉ። አንድ ጥናት በስዊድን ሕዝብ መካከል እስላም በሚያስገርም ሁኔታ በመሰራጨት ላይ መሆኑን ያረጋገጠ ሲሆን፣ዛሬ ከ120 ሺህ እንደሚበልጥ የተገመተው የሙስሊሞች ቁጥር በማያቋርጥ ስርጭት ላይ መሆኑን ኦፊሴላዊ አኃዛዊ መረጃዎች ያመለክታሉ።

የመስጊዶች በብዛት መገንባት የሙስሊሞች ቁጥር በተለይም ሃይማኖታቸውን የሚተገብሩ ሙስሊሞች ቁጥር እየጨመረ በመሄድ ላይ መሆኑን የሚጠቁም ሲሆን፣በከፍተኛ ቁጥር ሙስሊሞች የሚጎርፉባቸው ከ25 ሺህ የሚበልጡ መስጊዶች ድፍን አውሮፓ ውስጥ መኖራቸውን አኃዛዊ መረጃዎች ያሳያሉ።

በተቃራኒው ግን ወደ ቤተ ክርስቲያኖች የሚሄዱ ሰዎች ቁጥር እያሽቆለቆለ በመሄድ ላይ መሆኑን ጥናቶች ያረጋገጡ ሲሆን፣‹‹ደረስድን ባንክ›› ያካሄደው ጥናት በመጪዎቹ ዓመታት ውስጥ ጀርመን ውስጥ የቤተክርስቲያኖች ቁጥር እያሽቆለቆለ እንደሚሄድ፣‹‹አይስን አገረ ስብከት›› ስር ካሉት 350 ቤተ ክርስቲያኖች ውስጥ በ96ቱ ቅዳሴዎች እንደሚቆሙና የቤተክርስቲያኖቹ ሕንጻዎቹ ለሌላ አገልግሎት እንደሚውሉ የሚጠበቅ መሆኑን አመልክቷል። ይህም ወደ አብያተ ክርስቲያናቱ የሚመጡ ምእመናን ቁጥር እየቀነሰ በመምጣቱና ገቢው በማሽቆልቆሉ ምክንያት ነው።

ክርስቲያኖች በከፍተኛ ደረጃ ከቤተክርስቲያኖቻቸው እየራቁ መሄዳቸውን ከሚያሳዩ ክስተቶች አንዱ፣በአንዲት የአውሮፓ አገር ውስጥ የምእመናን ቁጥር በጣም በማነሱ ሰዎች ወደ ቤተክርስቲያን መጥተው እንዲጸልዩ ለመሳብ መኪኖችን የሚያሸልም የሽልማት ኩፖን እስከማደል የተደረሰበት ሁኔታ መኖሩ ነው!!

ማይክል፦ ይህ እስላምን ለማፈን፣በሃይማኖቱና በመርሆዎቹ በማፌዝ፣በተከታዮቹና በመሪዎቹ ላይ ጥቃት በመፈጸም፣ከዚህም አልፎ ሙስሊሞች ከመላዋ አውሮፓ ለቀው እንዲወጡ እስከመጠየቅ የደረሱት፣ቀኝ አክራሪ ፓርቲዎችና የዘረኛ ቡድኖች በዚህ መልኩ ሲራወጡ የምናስተውልበትን እውነታ የሚያብራራ ሊሆን ይችላል። ለመሆኑ ለዚህ ስርጭት ምክንያቶቹ ምን ይሆኑ?. . ወዳጃችን ራሽድ አንተም ከለመድንብህ በተቃራኒ ስለምክንያቱ ስታነሳ አልሰማንህም!

ራሽድ፦ በእርግጥ በምሰማው ነገር ደስተኛ ነኝ። ለዚህ ነው የበለጠ ለማዳመጥ ዝምታን የመረጥኩት . . በኔ እምነት የእስላም የራሱ የሆኑ ምክንያቶች፣የምዕራቡ ሕብረተሰብ የሆኑ የራሱ ምክንያቶች፣እንደዚሁም ከተጨባጭ ሁኔታ ጋር የተያያዙ ምክንያቶች ይገኛሉ . . እነዚህ ሁሉ ተጣምረውና ተደጋግፈው ለእስላም መስፋፋትና መሰራጨት መንስኤ ሆነዋል . . ማለት 'ምፈልገው ግን ፍጥረት ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ ከኣደም  ጀምሮ እሰካሁን ድረስ ያልተቋረጠ ጥልቅ ታሪካዊ መሰረትና ሰንሰለት ላለው ሃይማኖት ይህ እንግዳ ነገር አለመሆኑን ነው።

ራሽድ፦ ወዳጃችን ራሽድ፣እኛ የምናውቀው እስላም የመጣው ከአንድ ሺህ አራት መቶ ዓመት ወዲህ ብቻ መሆኑን ነው። በተጨማሪም አይሁዳዊነትንና ክርስትናን የመሳሰሉ ሌሎች ሃይማኖቶችም ነበሩ፤ይህን ታስተባብላለህ?

ራሽድ፦ በዚህ ረገድ ሊታረም የሚገባ ተሳሳተ ግንዛቤና ጽንሰ ሀሳብ አለ። እሱም የአላህ ሃይማኖት አንድ ብቻ እንጂ ብዙ አለመሆኑ ነው። ፍጥረታትን ከፈጠረው ከአንድ ምንጭ ከአላህ ﷻ የመነጨ በመሆኑ ሃይማኖት በመሰረቱ አንድ ብቻ ነው። ይሁን እንጂ ይህ አንድ ሃይማኖት ግምት ውስጥ የሚያስገባቸው አንዳንድ ሁኔታዎች ሲኖሩ፣ይህም እነዚህን ሁኔታዎች ወይም ሕዝቦች የሚመለከቱ የተለዩ አንዳንድ ሕግጋትን መኖር ይጠይቃሉ። እንደዚሁም ከመልእክቱ ምንጭ በዘመን ርዝመት ምክንያት ከሚኖረው ርቀት የተነሳ ከዚህ ሃይማኖት የመዛነፍ ሁኔታም ሊያጋጥም ይችላል። ይህ ሲሆን ደግሞ የዚህን ሃይማኖት ስረ መሰረቶችና መርሆዎቹን የሚያረጋግጥ ነቢይ መልእክተኛ በመላክ ሃይማኖታዊ ተሐድሶ ማድረግን ይጠይቃል። የእስላም ነቢይ ﷺ ፦ ‹‹ነቢያት በአባት አንድ የሆኑ ከብዙ እናቶች የተወለዱ ወንድማማቾች ናቸው፤ሃይማኖታቸው አንድ ሲሆን እናቶቻቸው የተለያዩ ናቸው›› ያሉት ለዚህ ነው። ይህም ዘመኖቻቸውና ሕጎቻቸው (ሸሪዓዎቻቸው) ብዙና የተለያዩ ናቸው ማለት ነው . . በእስላም ነቢይ ﷺ ዘመን የሰው ልጅ ወደ ጉልምስና ዘመኑ የደረሰ በመሆኑ፣የዚህ ረሱል ﷺ መልእክት ይህን ሃይማኖት ከጥፋትና ከመዛባት የሚጠብቁት፣አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ተሐድሶ በማድረግ ወደ መሰረታዊ ጥራቱ የሚመልሱት የራሱ የሆኑ ውስጣዊ ምክንያቶችን ያካተተ እንዲሆን ተደርጓል። በመሆኑም ይህ ሃይማኖት የሰው ልጆች ፈጣሪ ጌታ የመረጠላቸው የማጠቃላያው ሃይማኖት እንደ መሆኑ ፈጽሞ አይቋረጥም። ሕልውናውና ታሪካዊ ሰንሰለቱ እስከ ሰው ልጆች ፍጻሜ ድረስ ይቀጥላል። ሰዎችን የፈጠረ አምላክ ነውና የሚስማማቸውንና ከተፈጥሯቸው ጋር የሚጣጣመውን ሃይማኖት የሚመርጥላቸው መሆኑም ሳይታለም የተፈታ ነው። ነገሮች እንደ ወረዱ በራሳቸው ተፈጥሯዊ መንገድ እንዲሄዱ ከተተው፣እንዲህ ያለው የሃይማኖቱ የስርጭትና የመስፋፋት ሁኔታ መኖሩም እንደዚሁ ተፈጥሯዊ ነው ።

ራጂቭ፦ ይህ ድንቅ ጽንሰ ሀሳብና ለኔ ደግሞ አሰገራሚም ነው። እንግዲያውስ ወዳጃችን ራሽድ፣ስትጠቃቅሳቸው ወደነበረው የእስላም መሰራጨት ምክንያቶች እንመለስ።

ራሽድ፦ እሽ፣የራሱ የሆነውን የእስላምን ውስጣዊ ምክንያቶች በተመለከተ ልዩ ባሕርያቱ ለዚህ ዓይነቱ ስርጭት ብቁ ያደርጉታል፣በሚለው ውስጥ ይጠቃለላል። እሱም ፦

በአወቃቀሩ ቀለል ያለ፣በይዘቱ ጥልቀት ያለው፣ጽንሰ ሀሳቦቹ ግልጽ የሆኑ፣በአመለካከቱ ምሉእና ሁለንተናዊ የሆነ፣በትምሕርቶቹ ገርና ቀላል የሆነ፣ለማወቅና ለመረዳት ከፍ ያለ የአእምሮ ችሎታና የግንዛቤ ብቃትን የማይጠይቅ፣ምስጢራትና ሽፍንፍንነት፣ድብቅነትና ውስብስብነት የሌለበት ሃይማኖት መሆኑ ነው።

ሰብአዊና ሰውኛ የሆነ፣የሰውን ተፈጥሮ የሚያናግር፣እንደ ሁኔታዎቹ የሚይዘውና የሚያስተናግደው፣ለፍላጎቶቹ ምላሽ የሚሰጥ፣ችግሮቹን የሚፈታ፣ጥያቄዎቹን የሚመልስ፣ያካተታቸውን እውነታዎች ከሕይወት ተጨባጭ ሁኔታ ጋር በተቀናጀና በተደራጀ መንገድ በማጣጣም የሚያስተሳስር፣ሁሉንም ዓይነት ማህበራዊ ጭቆና እና ግፍ እርም የሚያደርግ፣በዘር ግንዳቸው፣በቆዳ ቀለማቸው፣በቋንቋና በብሔራቸው፣በማህበራዊ ደረጃቸው፣. . ምንም ዓይነት ልዩነት ሳያደርግ በሰው ልጆች መካከል ፍትሕና እኩልነትን የሚያረጋግጥ ሃይማኖት ነው።

ከሰው ልጆች ተጨባጭ ሁኔታ በላይ ራሱን የማያስቀምጥ፣በዚያ ውስጥ ቀልጦና ሟምቶ የማይቀር ተጨባጭ ተግባራዊ ሃይማኖት ነው። ከዚህ ተጨባጭነት በመነሳትም ዱንያን ከኣኽራ ጋር የሚያጣምርና በሁለቱ መካከከል ግጭት መኖሩን የማይቀበል ሃይማኖት ነው።

ሰብአዊ አእምሮን የሚያከብር፣ለሰው ልጅ እሳቤ ግምት የሚሰጥ፣አእምሯዊና ምክንያታዊ ማስረጃዎችን የሚያቀርብ፣ለመግባባት፣ለውይይትና ለጠቃሚ ክርክር ሎጂካዊ ስልቶችን የሚያስቀምጥ ሃይማኖት ነው።

ሳይንሳና ዕድገትን የሚያበረታታ እንጂ የማይዋጋ፣ዘመናዊው ሳይንስ ከደረሰባቸው የተረጋገጡና የጸኑ ሳይንሳዊ እውነታዎች፣እነዚያን መስኮች ከሚመለከቱና ከአስራ አራት ምእተ ዓመታት በፊት ከተላለፉ ቁርኣናዊ ገለጻዎች ጋር የተጣጣሙበት ሃይማኖት ነው።

ከእድገትና መሻሻል ንቅናቄ ጋር ተጣጥሞ የሚጓዝ ሃይማኖት ነው። እስላም በጊዜና ስፍራ መለዋወጥ ምክንያት ሕይወትን ከሚያጋጥሙ አዳዲስና ተለዋዋጭ ማሕበራዊ ሁኔታዎች ሁሉ ጋር ራሱን የማጣጣምና የማገናዘብ ብቃቱን አረጋግጧል።

የሰው ልጅ ራሱን በፍጹምነት ለፈጣሪ አምላኩ ተገዥ ካለደረገ በስተቀር በምጡቅ ትርጉሞቹ እውን መሆን የማይችለውን እውነተኛውን የሰው ልጆች ነጻነት እውን የሚያደርግ ሃይማኖት ነው። የሰው ልጅ ይህን ሲያደርግ ለማንም ሰው ሆነ ለሌላ ማንኛውም ፍጡር ተገዥ አይሆንም።

ለሌሎች ሥልጣኔዎችና ባህሎች ክፍት ሆኖ የኖረና በዚያው የቀጠለ ሃይማኖት ነው።

ማይክል፦ እኔ ደግሞ በምዕራቡ ሕብረተሰብ በራሱ ውስጥ ስለታቀፉ ምክንያቶች ላብራራ፦

የምዕራቡ ሕብረተሰባችን በተለይም ከተገባደደው ምእተ ዓመት መጀመሪያዎችና ከዚያም ቀደም ካለው ጊዜ አንስቶ የምር በሆነ የእሳቤና የአመለካከት ቀውስ ውስጥ ይናራል። ይህ ቀውስ የመነጨው ሕብረተሰባችን ከሳለፋቸው አያሌ ትግሎችና ፍጥጫዎች፣በተለይም በቤተክርስቲያንና በሳይንስ፣ከዚያም በተለያዩ የፍልስፍና ጎራዎችና በተለያዩ የሕብረተሰቡ መደቦች መካከል በተካሄዱ ትግሎችና ፍጥጫዎች ነው። ይህ ሁሉ የእሴቶችን መፍረክረክ፣ግራ የመጋባትንና የማንነት ቀውስ ስሜትን ፈጥሯል።

በተጨማሪም የእሴቶች መናጋትና የመንፈሰ ባዶነት ስሜት የምዕራቡን ሰው ሰብእና እንደ ነቀዝ በልቶታል . . የሰውን ልጅ መንፈስ የሚያፍን፣በሰው ልጅ ውስጥ የሰብእና እሴቱን የሚያወድም፣የሰውነት መለያ ባህርያቱን የሚያዘቅጥ ባዶነት ገጥሞታል . . የሰው ልጅ መገልገያ መሳሪያ ወይም የግዙፍ መሳሪያ አንድ አካል እስኪሆን ድረስ ሰብእናው እዘቀጠ፣የቁሳቁሶች ዋጋና እሴት እያሻቀበና እየወጣ ሄዶ ከሁሉም የሰው ልጅ እሴቶች በላይ ሆኗል።

ሌላው ምክንያት ደግሞ ብዙዎቹ ምዕራባውያን በሃይማኖታቸው ላይ ያላቸው ጥርጣሬ፣ብዙዎቹ ላይ ላዩን ለሃይኖቶቻቸው ቀናኢዎች መስለው ለመታየት ቢሞክሩም፣በእምነቶቻቸው ውስጥ የሚያስተውሉት እርስ በርስ የመጣረስና የጉድለት ሁኔታዎች መኖር ነው። በተጨማሪም ቤተክርስቲያን የንጽሕና እና የመድህን መንገድ አድርጋ የምትወስደውን የምናኔና የምንኩስና መንገድ፣ብዙዎቻችን የሰውን ልጅ ተፈጥሮ የሚጻረርና ከሕይወት ተልእኮ ጋር የሚጋጭ አድርገን የምንቆጥር መሆኑም ሌላው ምክንያት ነው።

የስነምግባር መላሸቅንና የቤተሰብ መበተንን፣በአጠቃላይ የምዕራቡ ሕብረተሰብ እጣ ፈንታ የሆነውን የማሕበረሰባዊ መዋቅሮች መናድን በቸልታ ማለፍ አንችልም።

ራሽድ፦ ስለተጨባጭ ሁኔታ ምክንያቶች መናገር ከፈለግን ደግሞ፣እስላምን ለማጠልሸት የሚካሄዱ የተቀነባበሩ ዘመቻዎች፣በተከታዮቹ ላይ የሚፈጸመው ግፍና ጭቆና፣ያልተጠበቀ የተገላቢጦሽ ውጤት የሚያስከትል ሊሆን የመቻሉ ሁኔታ ነው። ገጽታን የማበላሸትና የማጠልሸት ዘመቻዎቹ ይህን ሃይማኖት ለማወቅ የሚፈልጉ ሰዎችን ግብረመልስ ማስከተሉ ሌላው የስርጭቱ ምክንያት ነው።

 

የሙስሊም ንዑሳን ስብስቦች በምዕራቡ ዓለም መገኘት የሚኖረውን በጎ ተጽእኖም መዘንጋት የለብንም። ሙስሊሞች በአውሮፓውያን መካከል በአብሮነት መኖራቸው ምዕራባውያን እስላምን በቅርበት እንዲያውቁ መልካም አጋጣሚን የሚፈጥርላቸው ሲሆን፣እስላማዊ ጽንሰ ሀሳቦችን ለማወቅና የሙስሊሞችን የአነዋነዋር ዘይቤ በተጨባጭ እንዲያጤኑ መንገዱን ያመቻቻል።

ይህ ሁሉ፣መጻኢው ዘመን የዚህ ሃይማኖት መሆኑን የሚያረጋግጥ በተስፋ የተሞላ ብሩህ ስሜት እንዲሰማኝ ያደርገኛል።