መልክተኞች ለሰዎች አስፈላጊ ናቸውን?

መልክተኞች ለሰዎች አስፈላጊ ናቸውን?

አላህ (ሱ.ወ.) የሰው ልጆችን የፈጠራቸው በትክክለኛው ሚዛናዊ ተፈጥሮ ሲሆን፣እውነትን ከሐሰት መለየት ይችሉ ዘንድም አእምሮ ሰጥቷቸዋል። የሰው ልጅ አእምሮ ጉድለት፣እጥረት፣ስሜታዊ ዝንባሌና የጥቅም ተገዥነት የሚጠናወተው ከመሆኑም በላይ ለልዩነትና ለቅራኔም የተጋለጠ በመሆኑ ከፊሉ ሰው በጎ አድርጎ የሚመለከተውን ነገር ሌሎች መጥፎ አድርገው ይወስዳሉ። ይህ ብቻ ሳይሆን የአንድ ሰው ሀሳብ ራሱ በጊዜና በቦታ መለወጥ ሊለዋወጥ ይችላል። ይህ ሰብአዊ አእምሮ ከግንዛቤው ውጭ የሆኑ ክስተቶችን፣ያልተማራቸው እውቀቶችንና በግለሰቦች አእምሮ ውስጥ የሚመላለሱ ሀሳቦችን ማወቅ የማይችል እስከሆነ ድረስ፣ስለ ፈጣሪ ዓለማዎች፣ትእዛዛትና እገዳዎች ማወቅ በእጅጉ ይሳነዋል። በመሆነም የአላህ መልክት ለሰዎች በቀጥታ ሊተላለፍላቸው አይችልም። አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{ለሰውም አላህ በራእይ ወይም ከግርዶ ወዲያ፣ወይም መልክተኛን (መልአክን) የሚልክና በፈቃዱ የሚሻውን ነገር የሚያወርድለት ቢኾን እንጅ፣(በገሃድ) ሊያናግረው ተገቢው አይደለም። እርሱ በላይ ጥበበኛ ነውና።}[አል ሹራ፡51]

በአላህና በአገልጋይ ባሮቹ መካከል ምርጥ አምባሳደሮች ይሆኑ ዘንድ፣አላህ (ሱ.ወ.) መልክተኞችንና ነቢያትን ከሰው ልጆች መካከል ምርጦች አድርጎ የመረጣቸውም ለዚህ ነው። አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{አላህ ከመላእክት ውስጥ መልክተኞችን ይመርጣል፤ከሰዎችም፣(እንደዚሁ)፤አላህ ሰሚ ተመልካች ነው።}[አል ሐጅ፡75]

ሰዎችን ወደ ጌታቸው መንገድ እንዲመሩና ከጨለማ ወደ ብርሃን አንዲያወጧቸው፣መልክቱ ከደረሳቸው በኋላ ለሰዎች በአላህ ላይ አስረጅ እንዳይኖር አላህ (ሱ.ወ.) መልክተኞችን ልኳል። አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{ከመልክተኞቹ በኋላ ለሰዎች በአላህ ላይ አስረጅ እንዳይኖር፣አብሳሪዎችና አስጠንቃቂዎች የኾኑን መልክተኞች (ላክን)፤አላህም አሸናፊ ጥበበኛ ነው።}[አል ኒሳእ፡165]

ለሰብአዊ ፍጡራን የሚበጀውን ለማስተማርና ስነምግራቸውን ለማረቅ፣ነቢያትና መልክተኞች ከሰው ልጆች መካከል የተመረጡ መሆናቸው አላህ ለአገልጋዮቹ ከዋለላቸው ታላላቅ ችሮታዎች አንዱ ነው። አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{አላህ በምእመናን ላይ ከጎሳቸው የኾነን፤በነርሱ ላይ አንቀጾቹን የሚያነብ የሚያጠራቸውም፣መጽሐፍንና ጥበብን የሚያስተምራቸውም የኾነን መልክተኛ በውስጣቸው በላከ ጊዜ፤በእርግጥ ለገሰላቸው፤እነርሱም ከዚያ በፊት በግልጽ ስሕተት ውስጥ ነበሩ።}[ኣሊ ኢምራን ፡164]

አላህ (ሱ.ወ.) መልክተኛን መላኩና መልክተኛውም፦

{ከጎሳቸው የኾነ}

መሆኑ በእርግጥም ታላቅ ጸጋ ነው።

ይህ ጸጋ ከራሱ ዘንድ ክቡር ቃሉን ለሰው ልጅ እንዲያደርስ፣ስለ አላህ ሕልውና ስለ ባሕርያቱ አንዲያሳውቅ፣ስለ አምላክነት አውነታና ልዩ መለያዎች እንዲያስተምረው፤ከዚያም ስለራሱ ስለ ሰው ልጅ ስለ ደካማው አገልጋይ፣ስለ አነዋነዋሩ፣ስለ እንቅስቃሴውና ስለ እርጋታው፣ ሕያው ወደሚያደርገው ነገር ሊጠራው፣ቁሳዊና ሕሊናዊ ሁኔታውን ወደሚያሻሽለው ሊመራው፣የሰማያትና የምድር ያህል ስፋት ወዳለው ገነት ሊጠራው . . መልክተኛ በመላክ የሚንጸባረቅ ነው። ይህ ሁሉ ገደብ የለሽ ጸጋ፣ይህ ታላቅ ችሮታ፣ይህ ታላቅ ስጦታ በቃላት የማይገለጽ ወሰን የለሽ ቸርነቱ ከመሆን ውጭ ሌላ ምን ሊሆን ይችላል?! ይህም ብቻ ሳይሆን ያነጻቸዋል፤ከፍ ያደርጋቸዋል፤ያጠራቸዋልም። ልቦናቸውን አስተሳሰባቸውንና መንፈሳቸውንም፤ቤቶቻቸውን፣ክብራቸውንና ግንኙነቶቻቸውንም፤አነዋነዋራቸውን፣ሕብረተሳቦቻቸውንና ስርዓቶቻቸውንም ከማጋራት፣ከጣዖታዊነት፣ከተረትና ከቅዠቶች ቆሻሻ ያጠራል። እነዚህ ሁሉ በሰው ልጅ ሕይወት ላይ ከሚረጩትና የሰውን ሰብእና እና ክቡርነት ከሚጻረሩ ወራዳ አምልኮዎችና ልማዶች ያነጻል። ግንዛቤን፣አምልኮተ አላህን፣በጎ ልማዶችንና እሴቶችን ከሚበክለው የዘመነ ጃህሊያ ብክለቶችም ያነጻል። ማይምነት ወይም ጃህሊያ ዛሬም ጃህሊያ ነውና። የሁሉም ዘመንና ስፍራ ጃህሊያ የየራሱ ብክለትና ርክሰት አለውና። የሰው ልጆች አመለካከታቸውን ከሚገዛ መለኮታዊ እምነትና ከዚህ እምነት ከሚመነጨው የሕይወት መመሪያ ሕግ የሚራቆቱበት ሁኔታ ካለ ብዛት ካላቸው የጃህሊያ ገጽታዎች አንዱ እንጂ ሌላ ምንም ሊሆን አይችልም። በመሆኑም የሰውን ዘር ከዚህ ጥንታዊም ይሁን ዘመናዊ ጃህሊያ ማዳን ወሳኝ ይሆናል። ዘመናዊው ጃህሊያም በስነምግባራዊና ማሕበራዊ ገጽታው፣ስለሰው ልጅ የሕይወት ግቦችና ዓላማዎች ባለው ግንዛቤም ጭምር፣ዛሬ በተደረሰበት የላቀ የሥልጣኔና የዕድገት ዘመንም ያው የጥንቱን የማይማዊነት ባሕርያት የሚወክል ነው።

{እነርሱም ከርሱ በፊት በግልጽ ስሕተት ውስጥ ነበሩ።}[አል ጁሙዓ፡2]

ቀደም ሲል በአመለካከትና በእምነት ግልጽ ስሕተት፣በሕይወት ዓለማ ግንዛቤና አካሄድ ግልጽ ስሕተት፣በወግና ልማድ ግልጽ ስሕተት፣የሥርዓትና የስነምግባር ግልጽ ስሕተት፣በማህበረሰብና በሞራላዊ ጉዳዮችም ግልጽ ስሕተት . . በሁሉም መስክ ግልጽ ስሕተትና ጥመት ውስጥ ነበሩ።