ሃይማኖት ለሕብረተሰቦች ያለው አስፈላጊነት

ሃይማኖት ለሕብረተሰቦች ያለው አስፈላጊነት

ሃይማኖት ለግለሰብ ወሳኝ አስፈላጊ ከሆነ ዘንዳ ለሕብረተሰቦች የሚኖረው አስፈላጊነት ይበልጥ የጸና ይሆናል።

የሰው ልጆች ሕይወት በመካከላቸው በሚኖረው በበጎ ነገሮች ላይ የመረዳዳትና የመተባበር መሰረት ላይ እንጂ የማይታነጽ በመሆኑ፣ሃይማኖት ለአንድ ሕብረተሰብ የመከላከያ ጋሻ ነው። አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{በበጎ ነገርና አላህን በመፍራትም ተረዳዱ፤ግን በኃጢአትና ወሰንን በማለፍ አትረዳዱ።}[አል ማእዳህ፡2]

ይህ ተራድኦና ትብብር ሊኖር የሚችለው ደግሞ ግንኙነቶቻቸውን በሚያደራጅ፣ግዴታዎቻቸውን በሚወስንና ለመብቶቻቸው ዋስትና በሚሰጥ ሥርዓት አማካይነት ብቻ ነው።

እንዲህ ዓይነቱ ሥርዓትም የግዴታ ውስጠ ዐዋቂና ጥበበ ረቂቅ በመሆኑ ከማንም በላይ ለፈጠራቸው ፍጡራን የሚበጀውን ከሚያውቀው ኃያል አምላክ ዘንድ የመጣ መሆን ይኖርበታል።

{የፈጠረ አምላክ እርሱ ዕውቀተ ረቂቁ፣ውስጥ አዋቂው ሲኾን (ምስጢርን ሁሉ) አያውቅምን።}[አል ሙልክ፡14]

የሰው ልጆች ከሃይማኖት ከሕግጋቱና ከሥርዓቱ ባፈነገጡ ልክ፣በጥርጣሬ፣ በጥመት፣በብክነት፣በመባዘን፣ግራ በመጋባት፣በመናጢነትና በመላየለሽነት ጨለማ ውስጥ ይዋጣሉ።

በሕብረተሱቡ ውስጥ አንድነትን ሰላምንና መረጋጋትን ለማስፈን፣ሕግና ሥርዓትን ለማስከበር ከሃይማኖት ኃይል ጋር የሚነጻጸር ወይም የሚቀርበው ምንም ዓይነት ሌላ ኃይል በዓለም ላይ የለም። የዚህ ምስጢር ደግሞ የሰው ልጅ እንቅስቃሴዎቹና ድርጊቶቹ በራሱ ምርጫ የሚፈጸሙና በማይታይና በማይጨበጥ ነገር የሚመሩ በመሆናቸው ከተቀሩት ሕያው ፍጥረታት ሁሉ የተለየ ነው። እንቅስቃሴዎቹና ድርጊቶቹ የሚመሩት መንፈሱን በሚያጠራ፣ ጸባይና ስነምግባሩን በሚገራ፣ግልጹን አካላዊ እንቅስቃሴውን እንደሚቆጣጠረው ሁሉ ስውሩን ውስጣዊ ሕሊናዊ ሁኔታውንም በሚቆጣጠረው ሃይማኖታዊ እምነት ነው።

{በንግግር ብትጮኽ፣(አላህ ከጩኸቱ የተብቃቃ ነው)፤እርሱ ምስጢርን፣በጣም የተደበቀንም ያውቃልና።}[ጣሃ፡7]

የሰው ልጅ ትክክለኛም ይሁን የተሳሳተ የሚመራው ሁሌም በእምነት (በዐቂዳ) ነው። ዐቂዳውጥሩና ትክክለኛ ከሆነ ነገሩ ሁሉ መልካም ይሆንለታል፤መጥፎና የተሳሳተ ከሆነ ደግሞ ነገሩ ሁሉ የተበላሸ ይሆናል።

በመሆኑም ሃይማኖት በሰዎች መካከል በይነሰባዊ ግንኙነቶች በፍትሕና ርትእ መሠረቶች ላይ የታነጹ እንዲሆኑ የሚያደርግ አስተማማኝ ዋስትና ነው። በዚህ ምክንያትም ሃይማኖት ማሕበረሰባዊ ግዴታ በመሆኑ በሕዝቦች መካከል የሚይዘው ስፍራ ልብ በሰው አካል ውስጥ የሚይዘው ስፍራ መሆኑ አስደናቂ አይሆንም።

ሃይማኖት በአጠቃላይ መልኩ ይህን የመሰለ ደረጃ የያዘ ሲሆን፣ዛሬ በዓለም ላይ የምናስተውለው ግን የተለያዩ ሃይማኖቶች፣እምነቶችና ጎራዎች መኖራቸውን ነው። የእያንዳንዱ እምነትና ጎራ ተከታዮችም በእምነታቸው ደስተኞች ሆነው የሙጥኝ መያዛቸውን እንመለከታለን። ታድያ የሰው ልጅ የሚጓጓለትን ግብ እውን የሚያደርግለት እውነተኛው ሃይማኖት የትኛው ይሆን?! የእውነተኛ ሃይማኖት መመዘኛዎችስ ምንድናቸው?!