ይቅርታ . . አንዴ!!

ይቅርታ . . አንዴ!!

ማይክል፦ አስር ደቂቃዎች ያለፉ ቢሆንም ራሽድ እስካሁን ብቅ አላለም . . የሚገርም ነው!!

ራጂቭ፦ ልክ ነህ፣መዘግየቱ በሌሎች ጉዳዮቻችንና ቀጠሮዎቻችን ላይ ጫና ሊፈጥር ይችላል . .

ከአፍታ በኋላ ራሽድ ወደ ቻት ሩም ይገባና ለወዳጆቹ ሰላምታ በማቅረብ እንዲህ አላቸው፦

ሳልገባ በመዝግየቴ ይቅርታ እጠይቃለሁ። መፈጸም የነበረብኝ ሥራ ነው ያስቀረኝ፤ማስቀረት የሚቻል አልነበረም።

ማይክል፦ ራሽድ ይቅርታ አድርግልኝና ይህች የቀጠሮ ነገር በዐረብና ሙስሊም ሕዝቦች ዘንድ ስር የሰደደ ችግር ነው። እናንተ ዘንድ ለጊዜ ዋጋ አይሰጥም፤ግልጽነቴ አስከፍቶህ ከሆነ ይቅርታ እጠይቃለሁ።

ራሽድ፦ ያልከው ነገር በአብዛኛው እውነት ነው። እውነቱን ለመናገር ራሳችንን በድለን ሌሎች ስለ እኛ መጥፎ እይታ እንዲኖራቸው ያደረግነው እኛው ራሳችን ነን . . መታረም የሚገባው ግን እነዚህን ድርጊቶች ከእስላም ጋር የማያያዙ ጉዳይ ነው።

ማይክል፦ ከእስላም ጋር ካልተያያዘ ከምን ጋር ሊያያዝ ኖሯል?! ይህን የሚያደርጉት አብዛኞቹ የናንተ አገር ሰዎች መሆናቸውን ነው እምረዳው።

ራሽድ፦ በኛ ሕዝብና በእናንተ ሕዝብ መካከል ሁለት አቢይ ልዩነቶች አሉ። እነሱም ባህልና አከባቢ ናቸው . . እውነቱን ለመናገር እነዚህን ለመሳሰሉት ድርጊቶች ተጠያቂው እስላም ሳይሆን አካባቢ ነው።

ራጂቭ፦ እናንተ ዘንድ ሃይማኖት የባህል ዋነኛ መሰረት ነው ተብሎ የሚጠበቅ ሆኖ እያለ፣ይኸ እንዴት ሊሆን ይችላል?!

ራሽድ፦ ልክ ነህ። ይሁን እንጂ እውነታው የዘመናችን ብዙ ሙስሊሞች፣ወይ ባለማወቅ አልያም በቸልተኝነት በሃይማኖታቸው አስተምህሮ መሰረት የማይኖሩና የማይተገብሩት መሆናቸው ነው። በሰው ልጅ ዘንድ የሃይማኖትና የዐቂዳ አሻራና ዱካቸው እየሳሳ ሲመጣ፣ለአካባቢ ተጽእኖ ተገዥ ይሆናል።

ማይክል፦ የአካባቢ ተጽእኖ ከምንወያይበት ርእሰ ጉዳይ ጋር ምን ተያያዥነት አለው?

ራሽድ፦ አብራራልሃለሁ። ለምሳሌ ያህል በእናንተ አገር ከጥንት ጀምሮ በጣም ቀዝቃዛ በሆነ የአየር ሁኔታ ውስጥ ትኖራላችሁ። የመኖር ሕግ ለዚህ ከባድ ቅዝቃዜ ተጽእኖዎች ራሳችሁን ማዘጋጀት ግዴታ ስለሚያደርግባችሁ ለክረምቱ ወቅት ቀለብ ታሰናዳላችሁ። ቅዝቃዜውን ለመቋቋም እንጨትና ማገዶ ታዘጋጃላችሁ . . በዚህ መልኩም ከእሳቤና ከቅንጅት በፊት የወቅት መለዋወጥንና የአየር ሁኔታን ግምት ውስጥ ያስገቡ በትክክለኛነትና በጥንቁቅነት የሚገለጹ ስልቶችን እንድትከተሉ አካባቢ አስገድዷችኋል።

የኛ አገሮች ደግሞ በመካከለኛ የአየር ሁኔታ ዞን ወይም በመካከለኛ ሞቃት ዞን ውስጥ የሚገኙ ሲሆኑ፣በአብዛኞቹ የዓመቱ ወቅቶች መካከለኛና ምቹ የሆነ የአየር ሁኔታ አላቸው። በተፈጥሮ ሀብታቸው ብዛትና ዓይነትም እንዲሁ የታደሉ ናቸው። በመሆኑም ለመኖር እንደ እናንተ ብዙ ቅድመ ጥንቃቄ ዝግጅትና ጥረት ማድረግን አይጠይቃቸውም። ይህ ሁኔታ በነዋሪዎቹ እንቅስቃሴና ምግባር ላይ ተጽእኖ በማሳደሩ ወደ ቸልተኝነት አዘነበሉ፤ወይም ሞቃቱ የአየር ሁኔታ በሚያባብሰው ስንፍና እና ግድ የለሽነት ተዘፈቁ ማለት ትችላለህ። ስለሆነም ለአየር ሁኔታ ጫና ቅድመ ጥንቃቄ አለማድረግን በሕልውናቸው ላይ ተጽእኖ ይኖረዋል ብለው አላሰቡም።

ራጂቭ፦ አከባቢ በሰው ልጅ ላይ ብርቱ ተጽእኖ እንዳለውና ተጽእኖውን ለመቋቋም ከርሱ የበረታ ተጽእኖ ማሳደር የሚችል ወገን የሚያስፈልግ መሆኑ ጥርጥር የለውም። እናም እስላም ይህን የአካባቢ አፍራሽ ተጽእኖ ያልለወጠው ለጉዳዩ ትኩረት ባለመስጠቱ፣ወይስ ባለመቻሉ ነው?

ራሽድ፦ አለመቻሉን በተመለከተ፣አሁን ልንነጋገርባቸው ቦታቸው ያልሆኑ ብዙ መንስኤዎች አሉት። በአጠቃላይ አነጋገር ግን ለሥርዓቱ ተገዥ የሆኑ ተከታዮቹን ሕይወት በሁሉም ጊዜና ቦታ እንዳደረጀ ሁሉ፣እስላም ርእዮቱን መመሪያቸው ያደረጉ ሕብረተሰቦችን ማደራጀት ችሏል ማለት ይቻላል። በዚህ ረገድ አንጸባራቂ የሆኑ ሞዴሎች ይገኛሉ።

ማይክል፦ ከነዚህ ሞዴሎች መካከል አንዳንዱን ልትጠቅስልን ትችላለህ?

ራሽድ፦ ብዙ ሞዴሎች ያሉን ሲሆን ጥቂቶቹን እነሆ፦

ዐምማራህ ብን ኹዘይማ ብን ሣብት፣ኸሊፋው ዑመር ብን አልኸጧብ  ለአባታቸው ለኹዘይማ፦ ‹‹መሬትህን እንዳታለማና እንዳትተክል የከለከለህ ምንድነው?›› ብለው ሲጠይቋቸው፣ኹዘይማ፦ ‹‹እኔ ያረጀሁ ሽማግሌ ነኝ፣ነገ እሞታለሁ›› አሏቸው። ዑመር መልሰው ‹‹ትከል አልማ ብየሃለሁ›› አሏቸው። ዐምማራህ፣ዑመር ብን አልኸጧብ ከአባታቸው ጋር ሆነው በእጃቸው ሲተክሉ ማየታቸውን ተናግሯል። ታላቁ ሶሓቢይ ዐብዱላህ ብን መስዑድ  ፦ ‹‹ለዓለማዊ ሕይወቱም ይሁን ለወዲያኛው የኣኽራ ሕይወቱ የሚሆነውን አንዳች ነገር ሳይሠራ ሥራ ፈቶ የሚቀመጥን ሰው ማየት በእርግጥ እጠላለሁ።›› ብለዋል። የኢማም አቡ ሓትም አልራዚ ልጅ የሆኑት ዐብዱረሕማን ደግሞ የአባታቸውን ሁኔታ አስመልክተው እንዲህ ይላሉ፦ ‹‹ብዙ ጊዜ እየተመገቡም አነብላቸዋለሁ፤እየተጓዙም አነብላቸዋለሁ፤ወደ መጸዳጃ ቤት ገብተውም አነብላቸዋለሁ፤ለሆነ ነገር ወደ ቤት ገብተውም አነብላቸዋለሁ።››

ራጂቭ፦ ለመሆኑ እስላም በአስተምሕሮው ውስጥ በሁሉም ዘመን ለሚከተሉት መመሪያ ሆኖ ይቀጥል ዘንድ፣የጊዜን አስፈላጊነት አጽንኦት ሰጥቶ አስምሮበታል?

ራሽድ፦ አዎን፤እስላም የጊዜን ነገር እጅግ ከፍ አድርጎ በቁርኣንና በነቢዩ ﷺ ሱንና ውስጥ የላቀ ትኩረት ሰጥቶታል። ቁርኣንን፣የነቢዩን ﷺ ተግባራዊ ሕይወት፣የሶሓባንና የተከታዮቻቸውን . . ታሪክ ያጤነ ሰው ለጊዜ የሚሰጡት ክብርና ግምት፣በሁሉም ሁኔታዎች ውስጥ ቀጠሮን በማክበር ረገድ የነበራቸው ጥንቃቄ እጅግ ከፍተኛ መሆኑን ይገነዘባል። ከዚህ መገለጫዎች መካከል አላህ ﷻ ቁርኣን ውስጥ ከአንድ ጊዜ በላይ በጊዜ መማሉ አንዱ ሲሆን፣እንዲህ ብሏል፦

{በጎህ እምላለሁ። በዐሥር ሌሊቶችም።} ]አልፈጅር፡1-2 ] በተጨማሪም እንዲህ ብሏል፦

{በሌሊቱ እምላለሁ፣(በጨለማው) በሚሸፍን ጊዜ። በቀኑም፤በተገለጸ ጊዜ።} [አልለይል፡1-2 ] ከተአምራቱ መካከል የዓመታትን አቆጣጠርና ሂሳብ እናውቅ ዘንድ ፀሐይና ጨረቃን መፍጠሩ አንዱ መሆኑን አመልክቷል።

{በጊዜያቱ እምላለሁ፤} [አልዐስር፡1]ከተአምራቱ መካከል የዓመታትን አቆጣጠርና ሂሳብ እናውቅ ዘንድ ፀሐይና ጨረቃን መፍጠሩ አንዱ መሆኑን አመልክቷል።

ይህ ሁሉ በእስላም የአምልኮ (ዕባዳ) ተግባራት ውስጥ የተተገበረ ሲሆን፣ሁሉም ዕባዳዎች በአጀማመርም ሆነ በአጨራረስ ከጊዜ ጋር የተሳሰሩ ናቸው። ይህ ብቻ ሳይሆን ለያንዳንዱ ዕባዳ የተመደበው ጊዜ፣ዕባዳው ትክክለኛ እንዲሆንና ቀቡልነት እንዲኖረው መሟላት ካለባቸው መስፈርቶች (ሹሩጥ) አንዱ ነው። ለዚህም ነው እስላማዊው ሸሪዓ ለዚህ አስፈላጊ እሴት ማለትም ለጌዜ አጠቃቀምና ቀጠሮን በማክበር ሁሉንም በተወሰነለት ጊዜያቱ ውስጥ ለመፈጸም አጽንኦት የሰጠውና ለዕባዳዎቹ ተቀባይነት ማግኘት እንደ መስፈርት ያስቀመጠው። ለምሳሌ ያህል አላህ ﷻ እንዲህ ይላል፦

{ሶላት በምእመናን ላይ በጊዜያት የተወሰነች ግዴታ ናትና።} [አልኒሳእ፡103 ] የሃይማኖቱ ምሰሦና የጀርባ አጥንት የሆነው የሶላት ግዴታ፣በቀንና በሌሊት ሰዓቶች ውስጥ የተከፋፈለ፣የጸኑና የተወሰኑ ግልጽ ምልክቶች ያሉት ጊዜ አለው። የተቀሩት የእስላም ማዕዘናትም እንደዚሁ ናቸው። ጾም ዓመታዊ የሆነ የጊዜ ወሰን ያለው ሲሆን፣በዚያ የጊዜ ወሰን ውስጥ ጾመኛው ሙስሊም ጥብቅና ተለይተው የተቀመጡ ዕለታዊ ቀጠሮዎችን ማክበር ይኖርበታል። ማሕበራዊ ኢኮኖሚያዊ ሥርዓት የሆነው ዘካም እንደዚሁ ተለይቶ በሚታወቅ የጊዜ ገደብና የክፍያ ስሌት መጠን የሚገዛ ሲሆን፣በሕጅ ሥርዓተ ጸሎትም ተመሳሳይ ነገር እናገኛለን።

የጊዜን አስፈላጊነትና አጠቃቀሙን አስመልክቶ በነቢዩ ﷺ ሱንና ውስጥ ብዙ ማስረጃዎችን የምናገኝ ሲሆን፣ቅዱስ ቁርኣን ውስጥ ትኩረት እንደተሰጠው ሁሉ በነቢያዊው ሱንና ውስጥም ተመሳሳይ ነገር እናስተውላለን። ረሱል ﷺ ፦ ‹‹ሙስሊሞች የገቡትን (በሸሪዓው የተፈቀደ) ቃልና ግዴታ ያከብራሉ›› ብለዋል። ከሌላ ሰው ጋር ለመገናኘት ወይም ለስብሰባ ጊዜ መወሰን ማለት፣እያንዳንዱ ግለሰብ በቀጠሮው ሰዓት ለመገኘት በራሱ ላይ የወሰነው ግዴታ (ሸርጥ) ነው። ቀጠሮውን ካለከበረ በራሱ ላይ የወሰነውን ግዴታ ጥሷል ማለት ነው። ረሱል ﷺ ቀጠሮን አለማክበር ከአስመሳይ መናፍቃን ባሕርያት አንዱ መሆኑን ሲናገሩ እንዲህ ብለዋል፦ ‹‹የመናፍቅ ሰው ምልክት ሦስት ነው፤ሲናገር ይዋሻል፤ሲቀጥር ያፈርሳል፤ሲታመን ይክዳል።›› እናም ቀጠሮ ይዞ በማንአለብኝነት ወይም በንቀት ያፈረሰ ሰው ቀጠሮውን አላከበረም።

ማይክል፦ ለጊዜ ትኩረት መስጠት ግን በሁሉም ባህሎችና ስልጣኔዎች ዘንድ የጋራ የሆነ እሴት ነው። በዚህ እሴት ላይ እስላም ምንድነው የጨመረው?

ራሽድ፦ እስላም በጊዜ አጠቃቀምና በአደረጃጀቱ ፋይዳ ላይ ሦስት አበይት ገጽታዎችን ጨምሯል።

የመጀመሪው ገጽታ የጊዜ ወሰን (ልኬት) ሲሆን፣ጊዜ የሰው ልጅ ካፈራው ሁሉ እጅግ በጣም ውዱ ሀብት ነው፤ጊዜ ሕወቱ ነው። ማስቀደም ማዘግየትም ሆነ መጨመር አይቻልም። አንዴ ከጠፋ የመተካት ተስፋ የለውም። ለዚህ ነው እስላም በተቻለ መጠን እስከ መጨረሻዋ ደቂቃ ማለትም እስከ ሕይወት ፍጻሜ ድረስ ጊዜን በምጣኔ እንድንጠቀም ያበረታታው። ከዚህም አልፎ ጊዜን ከሞት በኋላ ያለውን ዳግም መቀስቀስና ምርመራን ከሚያጠቃልለው የትንሣኤ (ቅያማ) ቀን ጋር አስተሳስሯል። በተጨማሪም አንድ ሙስሊም በጣም አስቸጋሪ በሆነ ሁኔታ ውስጥ እንኳ ቢሆን ጊዜውን አሟጦ እንዲጠቀም እስላም ያሳስባል። ረሱል ﷺ ፦ ‹‹አንዳችሁ በእጁ ችግኝ ይዞ የትንሣኤው ቀን ቢጀምር፣ከቻለ ሳይተክላት አይነሳ።›› ብለዋል።

ሁለተኛው ገጽታ ደግሞ አስገዳጅ ማድረጉ ነው። እስላም የጊዜ አጠቃቀምንና የምጣኔውን ፋይዳ፣ይህ አጠቃቀምና ምጣኔ የሙስሊሙ ምርጫና በጎ ፈቃድ ሳይሆን ግዴታው መሆኑን ግምት ውስጥ ከማድረግ የሚመነጭ እንዲሆን አድርጓል። ይህም ዕድሜው - የሥራው ወሰነ ጊዜ - የራሱ ግላዊ አንጡራ ንብረት ሳይሆን፣እርሱን በሚያስደስት ነገር በተገቢው መንገድ ይጠቀምበት ዘንድ ከአላህ ﷻ የተለገሰው ስጦታ ከመሆኑ እውነታ የሚንደረደር ነው። ከዚህ በመነሳትም እስላም ጊዜን የሰው ልጅ እንዴት እንደ ተጠቀመበትና ምን እንደ አመረተበት የሚጠየቅበት ዋና ገንዘብ ወይም ካፒታል አድርጎታል። የአላህ መልክተኛ ﷺ ይህን በማስመልከት እንዲህ ይላሉ፦ ‹‹በትንሣኤ ቀን የአንድ ባሪያ እግሮች ስለ አራት ጉዳዮች ሳይጠየቅ ንቅንቅ አይሉም። ስለ ዕድሜው በምን ላይ እንዳጠፋ . . . ›› በተጨማሪም ረሱል ﷺ፦ ‹‹ሁለት ጸጋዎችን ጤንነትንና ነጻ ጊዜን መጠቀምን በተመለከተ ብዙ ሰዎች ተረቺዎች ናቸው›› ብለዋል። ነቢዩ ﷺ በተጨማሪ እንዲህ ብለዋል፦ ‹‹አምስት ነገሮችን ከአምስት ነገሮች አስቀድመህ ተጠቀምበት፦ ሕይወትህን ከሞትህ በፊት፤ጤንነትህን ከሕመምህ በፊት፤ነጻ ጊዜህን በሥራ ከመጠመድህ በፊት፤ወጣትነትህን ከሽምግልናህ በፊት፤ሀብታምነትህን ከድህነትህ በፊት።›› ዋና ገንዘብ ወይም ካፒታል ሲጨምር የሂሳብ ሥራ የሚጨምር መሆኑ ጥርጥር የለውም። አላህ ﷻ እንዲህ ይላል፦

{በርሱ ውስጥ ያስታወሰ ሰው የሚገሠጥበትን ዕድሜ አላቆየናችሁምን? አስጠነምቃቂውም መጥቶላችኋል፤} [ፋጢር፡ 37 [ተወዳጁ ነቢይም ﷺ እንዲህ ብለዋል፦ ‹‹አላህ አንድን ሰው እስከ ስልሳ ዓመት እድሜ ካኖረው (በጎ ነገር ባለ መስራቱ ወይም ኀጢአት በመፈጸሙ) ምንም ማመካኛ አላስቀረለትም።›› ሐሰን አልበስሪ (ረ.ዐ) ‹‹‹የአዳም ልጅ ሆይ! አንተ‘ኮ ቀናት እንጂ ሌላ አይደለህም፤አንድ ቀን ባለፈ ቁጥር ከፊልህ ሄዷል ማለት ነው።›› ማለታቸው ተዘግቧል። . . ይህ ከፊል ወደ ሰዓታት ደቂቃዎችና ሰከንዶች እየተከፋፈለ ይነጉዳል . . እያንዳንዷ ደቂቃ ወይም ሰከንድ ባለፈች ቁጥር ከፊልህ እየነጎደ ነው ማለት ነው፤ጊዜ ሕይወት ነውና።

ሦስተኛው ገጽታ ለዚህ እሴት የሰጠው መትጊያ፣ሽልማትና ማበረታቻ ነው። ጊዜ ከግለሰቡ ከራሱ በስተቀር ለሌላ ሰው ሥልጣንና ቁጥጥር ከሚያስቸግሩ ውጫዊ ተለዋዋጭ ነገሮች አንዱ ነው። ለዚህም ነው እስላም ለሙስሊሙ ግለሰብ ከቁሳዊ ማትጊያዎችና ማበረታቻዎች የላቁና የመጠቁ ውስጣዊ ማትጊያዎችን ያደረገው። ተቀባይነት ያለውን አነስተኛውን የአበርክቶ መጠን ለመወሰን መሰረታዊ መነሻ ከመሆኑ አንጻር፣የራስ ሕሊናዊ ዳኝነትና ቁጥጥር አስፈላጊነት የሚመጣው እዚህ ላይ ነው። እስላም ውስጥ የገዛ ራስን በራስ መቆጣጠር የፈጣሪን ጥያቄና ምርመራ በመፍራት፣የርሱን ሽልማትና አጅሩን በማሰብ የሚወከል ሲሆን፣ይህም ሙስሊሙ ጊዜውን ግለሰብንና ሕዝቡን በሚጠቅም ነገር ላይ እንዲያውል ያደርገዋል።

ማይክል፦ ይህ በእውነት አስደናቂ ሃይማኖት ነው! . . በያንዳንዱ የሰው ሕይወት ጉዳይ ውስጥ ጣልቃ ይገባል። በግላዊ ሕይወቱ ጉዳዮች እንኳ ለሰው ልጅ አማራጭ አይተውለትም።

ራሽድ፦ አይደለም፤ለሰው ልጆች ምርጫዎችና ለጉራማይሌነት ቦታ ይሰጣል። ዳሩ ግን በራሱ ሥርዓት ማእቀፍ ውስጥ ብቻ ካልሆነ ሌሎች መርሆዎችን እንዲጋፉ ቦታ አይሰጥም። ይህም እስላም ሰውን፣ዩኒቨርስንና ሕይወትን አስመልክቶ ከሚያራምደውና ቀደም ሲል ከፊሉን ካብራራሁላችሁ አመለካከት ጋር የሚጣጣም ነው።

እስላም የጊዜን ፋይዳ የሚመለከተው በአስተዳደራዊ ወይም ኢኮኖሚያዊ ጎኖች ውስጥ ከሚገባው ቁሳዊ አጠቃቀም አኳያ ብቻ አይደለም። እይታው ከዚህ ብዙ የመጠቀና የላቀ ነው። ከእስላማዊ አመለካከት አንጻር የሰው ልጅ በዓለማዊ ወይም ቁሳዊ መስኮች ሠራተኛና አምራች ከመሆኑ በፊት፣የአላህን ቅጣት የሚፈራና ምንዳውን ተስፋ የሚያደርግ፣በሚሠራውና በሚናገረው ሁሉ የርሱን ቁጥጥር የሚያስብ፣ለርሱ የተገዛ ሙስሊም ነው። እስላም ውስጥ ጊዜን በአግባቡ መጠቀምና ማደራጀት እንዲሁ ጊዜን ለመጠቀም ብቻ ያለመ፣ቁሳዊ ትርፍንና ምርታማነትን ለመጨመር የሚያስችል ባዶ እሳቤ አይደለም። መጭውን የኣኽራ ሕይወት በማሰብ፣የትንሣኤን ቀን ምርመራና መሪር ቅጣት ከመፍራት የሚንደረደር መንፈሳዊ ዓለማ በመሆኑ ከዚህ በብዙ የመጠቀ ነው።

ራጂቭ፦ የአንዳንድ ሙስሊሞችን ምግባር በተመለከተ ሌላ የምናገረው ነበረኝ። ይሁን እንጂ ለሚቀጥለው ውይይት ማቆየት መርጫለሁ . . በል ደህና ሁን።